Wednesday, 24 March 2021 00:00

ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ)

Written by  እህተ ሚካኤል
ልጆች! ባለፈው እትማችን ላይ ስለ ዐቢይ ጾም(ጾመ ሁዳዴ) እንዲሁም በጾመ ሁዳዴ ውስጥ የሚገኙ ሳምንታት የየራሳቸው መጠሪያ እንዳላቸው ነግረናችሁ ነበር አስታወሳችሁ? መልካም። የዐቢይ ጾም ሳምንታት ከተሰጣቸው መጠሪያዎች ውስጥ የመጀመሪያውንና የሁለተኛውን ሳምንት ስያሜ ‹‹ ዘወረደ›› እና ‹‹ ቅድስት›› እንደሚባሉ ነግረናችሁ ነበር። እነሆ በዚህ ዝግጅት ቀጥሎ ስላሉት ሁለት ሳምንታት ስለ ‹‹ምኩራብ›› እና ስለ ‹‹መጻጉዕ›› እንነግራችኋለን ተከታተሉን። 3. ምኲራብ  ልጆች! ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ምኲራብ በመባል ይጠራል። ይህ ቀን  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ያስተማረበት ቀን ነው።  ልጆች! የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ምኩራብን ‹‹ የአይሁድ የጸሎት ቤት ›› በማለት ይፈታዋል። በብሉይ ኪዳን ዘመን የአይሁድ አምልኮ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስና በሥርዓቱ የተመሠረተ ነበር። ናቡከደነጾር ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚገኙባቸው ስፍራዎች ሁሉ ምኲራብ ሊሠሩ እንደጀመሩ ይገመታል። በእስራኤል ሀገር በየቦታው በኢየሩሳሌም ብዙ ምኲራቦች ነበሩ። ሐዋርያትም አይሁዶች በተሰበሰቡባቸው ቦታዎች ሲዘዋወሩ አስቀድመው ወደ ምኲራቦች ገብተው ወንጌልን ያስተምሩ ነበር ይላል። ማቴ ፬፥፳፫ ፤ ሐ.ሥ ፮፥፱  ልጆች በምኩራብ ውስጥ የሕግ እና የነቢያት መጻህፍት የብራና ጥራዞች በሳጥን ውስጥ ይቀመጣሉ። የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብ መጽሐፉን የሚያነበው ሰው በደንብ እንዲሰማና እንዲታይ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ቆሞ ያነብ ነበር። የክብር ወንበሮች ከዚህ ቦታ ፊት ለፊት ነበሩ ማቴ ፳፫፥፮ ። ወንዶችና ሴቶች ለየብቻቸው ይቀመጡ ነበር።  ምኲራብ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት በአይሁድ የተሰራ የጸሎት ቤት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ተመላልሶ በሚያስተምርበት ጊዜ በአይሁድ ምኲራብ ገብቶ ያስተምር ነበር።  ልጆች! የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ስለነበር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ወደ አይሁድ ምኲራብ ገባ። ጌታችን ወደ አይሁድ ምኲራብ የገባው የእግዚአብሔርን ቃል ለማስተማር ነበር። ነገር ግን በቤተ መቅደሱ ብዙ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በሬ፣ ላም፣ ፍየል፣ ርግብ የመሳሰሉትን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይሸጡ ይለውጡ ነበር። ጌታችን በተከበረው የእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ብዙ ጫጫታም የማይገባ ነገርም ሲደረግ ተመለከተ። ጅራፍንም ውስዶ ሻጮቹን እየገረፈ ከቤተ መቅደሱ አስወጣ፤ የሚሸጡትንም ነገር ገለባበጠባቸው ‹‹ የአባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል›› እያለም የእግዚአብሔርን ቃል አስተማራቸው። ዮሐ ፪፥፩— መጨረሻው። ልጆች! ባጠቃላይ የዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት ‹‹ምኲራብ›› ተብሎ የተሰየመው ጌታችን መድኃኒታችን ወደ ምኩራብ ገብቶ ስላስተማረና በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚሸጡትን በጅራፍ ገርፎ ያስወጣበት ቀን በመሆኑ ነው። 4. መፃጉዕ ልጆች! የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት ‹‹ መፃጉዕ›› በመባል ይታወቃል። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው መግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ‹‹ መፃጉዕ›› ማለት ‹‹ ጐባጣ›› ማለት ነው ብለው ይፈቱታል። የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት በዚህ ስያሜ መጠራቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ታሞ አልጋ ላይ የነበረውን በሽተኛ የፈወሰበት ቀን በመሆኑ ነው። በኢየሩሳሌም ውስጥ በበጎች በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ  አምስት ያህል መመላለሻ የነበረባትና በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ቤተ ሳይዳ›› የምትባል አንዲት የመጠመቂያ ቦታ ነበረች። በዚህች ቦታ ብዙ በሽተኞች እየመጡ እየተጠመቁ ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር። በዚህች ቦታ ላይ ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛ በሽተኛ ነበር።   ልጆች! የእግዚአብሔር መልአክ ወደዚህች የመጠመቂያ ቦታ መጥቶ ውሃውን ያንቀሳቅሰው ነበር። መልአኩ ውሃውን ባንቀሳቀሰው ጊዜ በመጀመሪያ የገባ ታማሚ ተፈውሶ ይወጣ ነበር። ስለዚህ መልአኩ ውሃው እንዳንቀሳቀሰ ቀድሞ ለመግባት እና ለመዳን ሽሚያ ነበረ። በዚህ ቦታ ደግሞ ለሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛ ምንም ዓይነት ዘመድ ያልነበረው አንድ ሰው ነበረ። ውሃው በመልአኩ በተንቀሳቀሰ ጊዜ የሚወስደው ሰው ባለመኖሩ ለዚያን ያህል ዓመት በዚያች የመጠመቂያ ቦታ ተኝቶ ነበረ። በአንድ የሰንበት ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ወደዚህች የመጠመቂያ ቦታ መጣ መፃዕጉንም በአልጋው ላይ ተጣብቆ ተኝቶ አገኘው ለብዙ ዘመናት መተኛቱን ስላወቀም፦ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› አለው መፃዕጉዕ ‹‹ጌታ ሆይ ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ፤ እኔ ወደ መጠመቂያው ልሄድ ስል ሌላው ቀድሞኝ ይገባና ተፈውሶ ይዳል›› በማለት መለሰለት። ጌታም ‹‹ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› አለው ወዲያውም መፃጉዕ ዳነ ይተኛበት የነበረውንም አልጋ ተሸክሞ ሄደ። በሽተኛው የተፈወሰበት ቀኑ ሰንበት ነበርና አይሁድ ወደ በሽተኛው መጥተው ‹‹ በሰንበት አልጋህን መሸከም አትችልም ሰንበት ነውና›› አሉት ። መፃዕጉም ‹‹ ከበሽታዬ ያዳነኝ እሱ ነው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለኝ‹  ብሎ መለሰላችው። እይሁድም ‹‹የፈወሰህን ሰው አሳየን›› አሉት። ነገር ግን በዚያ ቦታ ብዙ ሰው ይጋፋ ነበርና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለይቶ ሊያሳያቸው አልቻለም። ዮሐ ፭፥፩፲፭ ።  ልጆች! የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት መፃጉዕ የተባለበት ምክንያት ከላይ እንደነገርናችሁ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ሳይዳ ተገኝቶ  መፃጉዕን ያዳነበት ቀን ስለሆነ ነው። በሚቀጥለው ዝግጅታችን ስለቀሩት የዐቢይ ጾም ሳምንታት መጠሪያና ታሪክ እንነግራችኋለን እስከዚያው ደህና ሰንብቱ!  እግዚአብሔር ቸርነት፤ የእመቤታችን ፍቅር አይለያችሁ!    
Read 589 times