Thursday, 08 April 2021 00:00

ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ)

Written by  በእህተ ሚካኤል

Overview

ልጆች! ባለፈው እትማችን በዐቢይ ጾም (በጾመ ሁዳዴ) ውስጥ ከሚገኙ ሳምንታት እና መጠሪያዎቻቸው ውስጥ ‹‹ምኲራብ›› እና ‹‹መጻዕጉ››ን ስያሜያቸውንና ታሪካቸውን ነግረናችሁ ነበር። መቼም እንዳልረሳችሁት ተስፋ እንዳርጋለን። እነሆ በዚህ ዝግጅት ደግሞ ስለ ‹‹ደብረ ዘይት›› እና ስለ ‹‹ገብርኄር›› ይዘንላችሁ ቀርበናል ተከታተሉን።  5. ደብረ ዘይት  ልጆች! አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› በመባል ይጠራል። ይህ ቀን  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ወደዚህች ምድር ዳግመኛ ስለመምጣቱ ፣ስለ ዓለም ፍጻሜ እንዲሁም ስለ ትንሣኤ ሙታን ያስተማረበት ነው። 

 

ልጆች! የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ደብረ ዘይት ሲናገር፡- ‹‹ደብረ ዘይት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው። ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ይገኛል። በደብረ ዘይትና በኢየሩሳሌም መካከል የቄድሮን ሸለቆ ይገኛል። ከቤተ መቅደስ  አደባባይ እስከ ደብረ ዘይት ሰባ አምስት ሜትር ገደማ ነው። . . . ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ስለ ኢሩሳሌም መፍረስና ስለ ዓለም መጨረሻ አስተማረ ማር ፲፫፥፫ ። . . .  እያለ ይዘረዝራል። 

ልጆች! ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ታሪክ መነሻ በማድረግ የዐቢይ ጾምን አምስተኛ ሳምንት ደብረ ዘይት ብላ በመሰየም ዕለቱን ታከብረዋለች፣ በዕለቱም ስለ ዓለም ፍጻሜ ትምህርት ትሰጥበታለች። ደብረ ዘይት በዐቢይ ጾም ዕለታት አጋማሽ  ላይ የሚገኝ ስለሆነም ‹‹እኩለ ጾም›› በመባል ይጠራል።

ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው? ማቴ ፳፭፥፫ ብለው ጠየቁት። ጌታችን ስለ ዓለም ፍጻሜ እና የዓለም ፍጻሜ ከመድረሱ በፊት ስለሚከናወኑ ምልክቶችም አንድ በአንድ ነገራቸው። ጌታችን ከተናገራቸው (ካስተማራቸው) ምልክቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው ፦  

1. የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ።

2. የጦርነትንም ወሬ ትሰማላችሁ፤ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ፤ ፍጻሜው ገና ነው።

3. ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ።

4. በየሀገሩም ረኃብ፣ ቸነፈርም ፥ የምድር መናወጥ ይሆናል።

5. ያን ጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።

6. ያን ጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ። 

7. ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይመጣሉ፤ ብዙዎቹንም ያስታሉ።

8. ከዐመፅም ብዛት የተነሳ ፍቅር ከብዙዎች ዘንድ ትጠፋለች። እስከመጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል። በአሕዛብ ሁሉ ላይ ምስክር ሊሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ያን ጊዜም ፍፃሜ ይደርሳል። ማቴ ፳፬፥፬ - ፲፬

ልጆች! በአጠቃላይ አምስተኛው ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት ጌታችን በተራራው ላይ ተቀምጦ ስለ ዓለም ፍጻሜና ዳግመኛ ስለመምጣቱ ምልክቶች ለሐዋርያት ማስተማሩ እኛም ይህንን በማሰብ ተዘጋጅተን እንድንኖርም ለማሳሰብም ጭምር ነው። 

6. ገብርኄር 

ልጆች! የዐቢይ ጾም ስድስተኛው ሳምንት ‹‹ገብርኄር›› በመባል ይጠራል። ገብርኄር ማለት ‹‹በጎ፣ታማኝ አገልጋይ›› ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ የ‹‹ገብርኄር›› ታሪክ ይገኝበታል። 

ልጆች! ወደ ሌላ ሀገር የሚሄድ አንድ ጌታ ባሮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደየ አቅማቸው ገንዘብ ሰጣቸው። ለአንደኛው አምስት መክሊት ፣ለሁለተኛው ሁለት መክሊት፣ለሦስተኛው ደግሞ አንድ መክሊት ሰጣቸው። በዚህ በሰጣቸው መክሊት ነግደው፣ አትርፈው እና እጥፍ አድርገው እንዲቆዩት አደራ ሰጥቶአቸው ወደ ሌላ ሀገር ሄደ።

ባሮቹም ጌታቸው እንዳዘዛቸው የተሰጣቸውን መክሊት ነግደው አተረፉበት። አምስት መክሊት የተሰጠው ነግዶ ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፤ሁለት መልክሊት የተሰጠውም እንዲሁ ነግዶ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፈ፤ሦስተኛው እና አንድ መክሊት የተሰጠው ባርያ ግን የተሰጠውን ገንዘብ ወስዶ በምድር ውስጥ ቀበረው፤ ጌታው ከሄደበት ሀገር እስኪመጣም ምንም ሳያደርግ ቁጭ ብሎ ጠበቀው። 

ከብዙ ዘመንም በኋላ ጌታቸው ከሄደበት ሀገር ተመልሶ እነዚያን ባሮች ጠራና ስለሰጣቸው መክሊት ጠየቃቸው። አምስት መክሊት የተቀበለው ባሪያ ቀረበና ‹‹ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበረ፤ ነግጄበት ሌላ አምስት መክሊት አትርፌያለሁ›› ብሎ ሰጠው። ጌታውም አንተ በጎ ታማኝ ባርያ በጥቂቱ ታምነሀል በብዙ እሾምሀለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊት የተቀበለው ባርያም ‹‹ ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበረ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍኩ›› ብሎ ሰጠው። ጌታውም አንተ በጎ ታማኝ ባርያ በጥቂቱ ታምነሀል በብዙ እሾምሀለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። 

አንድ መክሊት የተቀበለው ባርያም መጥቶ ‹‹ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ካልበተንክበት የምትሰበስብ፤ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርኩት ይኸው መክሊትህ›› ብሎ  የተቀበለውን አንድ መክሊት ለጌታው መለሰለት። ጌታውም ‹‹አንተ ክፉ ሀኬተኛ ባርያ ካልዘራሁበት እንደማጭድ፤ ካልበተንኩበት እንደምሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጥ ይገባህ ነበረ። እኔም መጥቼ ገንዘቤን ከነትርፉ እወስደው ነበረ። አሁንም መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት ላለው ሁሉ ይሰጠዋል ይበዛለትማል ፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውን ባርያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት›› አለ ። ማቴ ፳፬፥፲፬-፴

ልጆች! ባጠቃላይ የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ‹‹ገብርኄር›› ተብሎ መሰየሙ ጌታችን ባስተማረው በዚህ ምሳሌያዊ ትምህርት ውስጥ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ልዩ ልዩ ጸጋ በሚገባ እንድንጠቀምበትና እግዚአብሔርን እንድናገለግልበት እንደሚገባ ለመግለጽ ነው። 

ልጆች! በሚቀጥለው ዝግጅታችን ስለቀሩት የዐቢይ ጾም ሳምንታት መጠሪያና ታሪክ ይዘንላችሁ እንቀርባለን እስከዚያው ደህና ሰንብቱ! እናንተም በተሰጣችሁ ጸጋ እግዚአብሔርን ልታገለግሉ ይገባችኋል እሺ ልጆች! 

የእግዚአብሔር ቸርነት፤

የእመቤታችን አማላጅነት፤

የመላእክት ጥበቃ አይለያችሁ!  

Read 622 times