Monday, 28 June 2021 00:00

የሞቱ ደብዳቤ ወደ ሕይወት የተቀየረለት ሕፃን

Written by  እህተ ሚካኤል
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከረማችሁ? ደኅና ናችሁ? የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን!!   ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ቅዱስ ሚካኤል ለባሕራን ስላደረገው ተአምራት ነው፤መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!  ሰኔ ፲፪ ቀን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል በዓል የሚከበርበት ልዩ ቀን ነው። ልጆች! ‹‹ሚካኤል›› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ  ‹‹ሚ›› --  መኑ   ‹‹ካ ›› -- ከመ   ‹‹ኤል›› -- አምላክ ማለት ሲሆን  በአንድነት ሲነበብ ‹‹ መኑ ከመ አምላክ›› (እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው) ማለት ነው።  ‹‹ሚካኤል›› ማለት አንድም የቸርነትና የርኅራኄ መገኛ መዝገብ ማለት ነው። ቅዱስ ሚካኤል ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ›› ራእይ ፰፥፪ ብሎ ከተናገረላቸው መላእክት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የሰባቱም ሊቃነ መላእክት አለቃ እንዲሆን እግዚአብሔር መርጦ  የሾመው ነው።  ልጆች! ንግሥት ክሌዎፓትራ ‹‹ ሳተርን›› የሚባለው ጣዖት  ቤተ ጣኦት በእስክንድርያ አሠርታ ነበር። ይህ ቤተ ጣኦት እስከ እስክንድርያው ፓትርያርክ እለ እስክንድሮስ ዘመን ድረስ ነበር። እለ እስክንድሮስም ይህን ቤተ ጣኦት ሊያጠፋው ሲነሳ የሀገሩ ሕዝብ ያመልክት ነበርና ‹‹እስከዛሬ የነበሩ ዐሥራ ስምንት ፓትርያርኮች ያልነኩትን ቤተ ጣዖት አንተ ለምን ታፈርስብናለህ? ብለው ተቃወሙት። 

 

እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን መክሮና አስተምሮ የ‹‹ሳተርን›› በዓል ይውልበት በነበረው ዕለት የቅዱስ ሚካኤልን በዓል እንዲያከብሩ አውጆ ቤተ ጣቱንም በቅዱስ ሚካኤል ስም ሰይሞ ባርኮ ቤተ ክርስቲያን አደረገው። ሕዝቡ በየዓመቱ መሥዋዕት እየሠው ከመሥዋዕቱ የተረፈውን እየተመገቡ እየዘፈኑ እያጨበጨቡ ያከብሩ ነበር። የንግሥት ዕሌኒ ልጅ ታላቁ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ “አብያተ ጣኦታት ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ” ብሎ ካወጀ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት እለ እስክንድሮስ ቤተ ጣኦቱን አፍርሶ ከቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ታቦተ ሚካኤልን አግብቶ በዓሉን በደስታ በሐሴት እንዲያከብሩ አደረገ። እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን የጣኦቱን በዓል ተው “ይህን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል አክብሩ” ብሎ በየዓመቱ በዚህ ቀን በዓል እንዲሆን ሥርዓት ሠራላቸው። 

ይህንንም የቅዱስ ሚካኤልን በዓል ከሚያከብሩ ምእመናንን አንዱ የባሕራን አባት ነበር። እርሱም እግዚአብሔርን እጅግ አድርጐ የሚፈራ ወር በገባ በየዐሥራ ሁለቱ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን ዝክሩን የሚዘክርና ይልቁንም በኅዳር ዓሥራ ሁለትና በሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን በታላቅ ክብር የሚያከብር  ሰው ነበር። ለዚህ እግዚአብሔርን ለሚፈራ ሰውም ርኅራኄ የሌለው በእርሱም ላይ ጥላቻ ያደረበት አንድ በለጸጋ ጐረቤት ነበረው። የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በሚያከብርበት ጊዜ ሁሉ ይዘብትበት ይሳለቅበት ነበር። 

ባሕራን አባት በጎ ሥራን በመሥራት ብዙ ጊዜ ከኖረ በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ያርፍ ዘንድ የሞቱ ጊዜ ቀረበ። ሚስቱንም ጠርቶ “በጐ ከመሥራት ለድኃ ከመመጽወት ቸል አትበይ የቅዱስ ሚካኤልንም በዓል በየወሩ ከማክበር አትቦዝኝ ይልቁንም በኅዳር ዐሥራ ሁለትና በሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓት እንድታከብሪ አደራ እልሻለው” አላት። እርሱ በሚሞትበትም ጊዜ ሚስቱ ፀንሳ ነበር።

 ከዚህም በኋላ ሚስቱ መልኩ በጣም ያማረ ልጅ ወለደች። የእግዚአብሔር መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ያን ሕፃን ባረከውና “ቸርነት ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት እርሻውንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዟል” አለ። ያን ጊዜ ያ ባለጸጋ በሴትዮዋ ቤት መስኮት አጠገብ ሆኖ ሁኔታውን ሁሉ ይመለከት ነበርና ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ልቡ በታላቅ ኅዘን ተነካ፤ ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመር። ነገር ግን እግዚአብሔር በቅዱስ ሚካኤል ጸሎት ብላቴናውን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀው ነበር። ባለጸጋውም በልጁ ቁመት ልክ ሳጥን አሠርቶ ሕፃኑን ከውስጥ አግብቶ በላዩ ላይ ቆለፈበትና ወስዶ ከባሕር ጨመረው፤ እንዲሁም መክፈቻ ቁልፉን አብሮ ወረወረው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሰጥም በባሕሩ ላይ እየተንሳፈፈ ከዚያች አገር ርቃ ወደምትገኝ የባሕር ወደብ ደረሰ።

በባሕሩ አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበርና ያንን ሣጥን ባየው ጊዜ ከባሕሩ አወጣውና ወደ ቤቱ ወስዶ ቢከፍተው እጅግ የሚያምር ልጅ ሆኖ አገኘው። ከባሕርም ስላገኘው  ስሙን “ባሕራን” ብሎ ሰየመውና እንደ ልጁ አድርጐ ይንከባከበው ዘንድ ወሰነ።

ከባሕራን ሀገር የበግ ጠባቂው አገር የዐሥር ቀን ጐዳና የሚያስኬድ ርቀት ነበረው። ከብዙ ዓመታት በኋላ ያ ባለ ጸጋ ሰው ለንግድ ከሀገሩ ወጣ። በጉዞውም ላይ ሳለ ፀሐይ ስትገባ ከዚያ የበግ ጠባቂው ዘንድ ደረሰ። ባለጸጋውም ከበግ ቤት ገብቶ ጥቂት ካረፈ በኋላ በግ ጠባቂው ያን ብላቴና ባሕራን ብሎ ሲጠራው በሰማ ጊዜ “ልጅህ ነውን?” ብሎ ጠየቀው። በግ ጠባቂውም “አዎን ይህ አሁን ጐልማሳ ሆኖ የምታየው ወጣት ገና ሕፃን ሆኖ ሳለ በሣጥን ተከቶ ከባሕር ውስጥ ተጥሎ አግኝቼው ወስጄ አሳድጌዋለሁና ልጄ ነው” አለው። 

ባለጸጋውም በባሕር ውስጥ የጣለው ሕፃን መሆኑንም ስላወቀ ይህንን ነገር በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ፤ ይገድለውም ዘንድ ፈለገ። በማግሥቱም በግ ጠባቂውን ጠርቶ “ወንድሜ ሆይ አንድ የማስቸግርህ ጉዳይ አለኝ ይኸውም በቤቴ የረሳሁት ነገር ስላለ ወደዚያ ሄዶ መልእክት ያደርስልኝ ዘንድ ይህን ብላቴና እንድትሰጠኝ ነው የድካሙንም ዋጋ ሃያ ወቄት ወርቅ እከፍላለሁ” አለው። ያም በግ ጠባቂ ስለ ወርቁ ስጦታ ደስ በመሰኘት ያን ጐልማሳ ጠርቶ “ልጄ ባሕራን ሆይ ይህ ክቡር ሰው ለሥራ ጉዳይ ወደ ቤቱ ሊልክህ ይፈልጋልና መልእክቱን አድርስለት እግዚአብሔር በሰላም ያግባህ” ሲል ጠየቀው። ልጁም “እሺ መልካም ነው አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ” አለው። 

ከዚህም በኋላ ያ ባለጸጋ “ይህችን የመልእክት ደብዳቤ ይዞ ወደ አንተ የመጣውን ስሙ ባሕራን የተባለውን መልእክቷ በደረሰችህ ጊዜ ፈጥነህ ግደለው ገድለህም ሬሣውን ከጉድጓድ ጣለው እኔ በሰላም ተመልሼ እስክመጣ ድረስ ማንም ይህን ምሥጢር አይወቅ” የሚል ጽሑፍ ለሹሙ ጽፎ አዘጋጀ። እንዲሁም በሹሙና በእርሱ መካከል የሚተዋወቁበትን ማኅተም በደብዳቤው ላይ አትሞ ለባሕራን ሰጠው። ለመንገዱም የሚሆነው ስንቅ ሰጥቶ ላከው።

ባሕራንም መልእክቱን ለማድረስ ዘጠኝ ቀን ተጉዞ የአንድ ቀን ጎዳና ሲቀረው እነሆ ክቡር የሚሆን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በንጉስ ጭፍራ አምሳል በፈረስ ተቀምጦ ወደሱ ደረሰና ወዴት እንደሚሄድ ጠየቀው።  ባሕራንም “ከአንድ ባለጸጋ ሰው የተጻፈ ደብዳቤ ይዤ እርሱን ለማድረስ ወደ ቤቱ እሄዳለሁ” አለው። ንዑድ ክቡር የሚሆን ቅዱስ ሚካኤልም “እስኪ የመልእክቱን ደብዳቤ አሳየኝ?” አለው። ባሕራንም “ጌታዬ ለማንም አታሳይ ብሎኛል” አለው። መልአኩም “እሺ ያም ባይሆን እንደተጠቀለለ አሳየኝ” አለው። ባሕራንም አሳየው። ቅዱስ ሚካኤልም በሞቱ ደብዳቤ ላይ እፍ ቢልበት የሞቱን ትእዛዝ አጥፍቶ የሕይወት ትዕዛዝ ጻፈበት። 

በደብዳቤው ላይ የተጻፈውን የሞት መልእክት ደምስሶ “ይህን መልእክት ይዞ ለመጣ ሰው ልጄን አጋቡት (ዳሩለት) በዱር የተሰማራውን ከብቴን በቤት ያለውን ሀብቴን በጠቅላላው ንብረቴን በሙሉ አውርሼዋለሁና እኔ በሄድኩበት ሀገር የምቆይበት ጉዳይ አለኝና፤ በቤቴና በንብረቴ ላይ ሙሉ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና የወደደውን ያደርግ ዘንድ አትከልክሉት ስለዚህም በእኔና በአንተ መካከል የምንተዋወቅበትን ምልክት አድርጌበታለሁ” የሚል ጽሑፍ ጽፎ ሰጠውና “እንግዲህ ወደ ባለጸጋው ቤት ሂድና ይህን መልእክት አድርስ ነገሩ እንዳይገለጽብህ ከእኔ ጋር መገናኘታችንንና የመልእክቱን ጽሑፍ እንደለወጥኩልህ ለማንም አትንገር” ሲል አስጠነቀቀው። 

ባሕራንም “እሺ ጌታዬ እንዳዘዝከኝ አደርጋለሁ” ወደ ባለጸጋው ቤት ደርሶ ደብዳቤውን ለሹሙ ሰጠው። ያም ሹም ደብዳቤውን ተቀብሎ ሲያነብ የታተመበት ማኅተም ዕውነተኛ መሆኑን ከአረጋገጠ በኋላ እግዚአብሔር እንዳዘዘው በቤተ ክርስቲያን ደንብ የባለጸጋውን ልጅ በተክሊል አጋባው፣ የሠርጉንም በዓል እስከ ዐርባ ቀን ድረስ በታላቅ ደስታ አከበሩ። ከሠርጉም በዓል ፍጻሜ በኋላ ያ ባለጸጋ ሰው ከሄደበት አገር ሲመለስ ባሕራን ልጁን አግብቶ ንብረቱን መውረሱን ሰማ። 

ያም ባለጸጋ ያህን ቃል በሰማ ጊዜ ከድንጋጤው የተነሳ በታላቅ ቃል በመጮኽ ከመሬት ላይ ተከስክሶ ሞተና ነፍሱን አጋንንት ተረክበው ወደ ሲኦል አወረዷት። ከዚህም በኋላ ባሕራን የተባለ ያ ጐልማሳ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በየወሩ እያከበረ ዝክሩን እየዘከረ ይኖር ጀመር። በዚያን ጊዜ በጉዞ ላይ ሳለ ተገልጾለት የሞቱን መልእክት ወደ ሕይወት የለወጠለት ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነም አወቀ። 

ልጆች! ቅዱስ ሚካኤል ባሕራንን ከሞት እንዴት እንደታደገው አስተዋላችሁ? በመጀመሪያ የባሕራን አባት እና እናት  ቅዱስ ሚካኤልን የሚያከብሩ እጅግ መልካም ባለትዳሮች ነበሩ። በእግዚአብሔር፣ በቅዱሳን መላእክት ምልጃ የሚያምኑ ፍጹም መንፈሳውያን ነበሩ። ልጃቸው ባሕራንም በኖረበት ቤት ውስጥ በታማኝትና በቅንነት ሲያገለግል የነበረ ልጅ ነው። ቤተሰቦቹ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት የሚያምኑ ስለነበሩ እንዲሞት የተፈረደበት ልጃቸው ባሕራን መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል የሞቱን ደብዳቤ ወደ ሕይወት ቀይሮለት በሕይወት እንዲኖር እና  ትዳር መስርቶ ተድላ ደስታ እንዲያደርግ አድርጎታል። ልጆች እናንተም እንደ ባሕራን ታዛዥ መሆን ይጠበቅባኋል። እንዲህ ካደረጋችሁ ከክፉ ሁሉ ተጠብቃችሁ በሕይወት ትኖራላችሁና።  መልካም ልጆች! በሚቀጥለው በሌላ ታሪክ እስክንገናኝ ደኅና ሰንብቱ! ክቡር የሚሆን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ረድኤት በረከቱ አድሮብን ይኑር አሜን!

 

Read 1012 times