Friday, 06 August 2021 00:00

የዓለም ብርሃናት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ

Written by  እህተ ሚካኤል
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከረማችሁ? ደኅና ናችሁ? የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን!!    ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ሐምሌ ፭ ቀን በየዓመቱ መታሰቢያቸው ስለሚደረገው እና ስለሚከበረው ስለ ሁለቱ የቤተ ክርስቲያን ብርሃናት እና ሰማእታት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ታሪክ ነው፤መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!     ልጆች! ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በዓለም ዞረው በማስተማር በሰማእትነት ያረፉት በዓላዊው ንጉሥ በኔሮን ቄሳር ዘመነ መንግሥት ነው።የነዚህን ሁለት ሰማዕታት ታሪክ እንደሚከተው በየተራ እናቀርብላችኋለን።ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ልጆች! ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ አውራጃ በቤተ ሳይዳ ሲሆን አባቱ ከነገደ ሮቤል እናቱ ደግሞ ከነገደ ሰምዖን የተገኙ ናቸው።ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓሣ ሲያጠምድ በጥብርያዶስ ባህር ዳር አግኝቶት ለሐዋርያነት እንዲሆን ጠርቶታል።ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የቀድሞ ስሙ ‹‹ስምዖን›› ሲሆን ጌታችን ለሐዋርያነት አገልግሎት ሲመርጠው ‹‹ጴጥሮስ›› ብሎ ጠርቶታል።

 

ልጆች! ጴጥሮስ ማለት በግሪክ ቋንቋ ‹‹ ዓለት ›› ማለት ነው።ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ለጌታችን በነበረው ጥልቅ ፍቅር እና መንፈሳዊ ቅንዓቱ በሐዋርያት ላይ አለቃ እንዲሆን በክርስቶስ ተሹሟል።ቅዱስ ጴጥሮስ በአገልግሎት ዘመኑ በሮም፣ በእስያ፣ በሰማርያ በኢዮጴ፣በልዳ ፣ በአንጾኪያና በሌሎች የተለያዩ ሀገሮች ክርስትናን በመስበክ ብዙዎች የክርስቶስን ወንጌል ሰምተው ክርስቲያን እንዲሆኑ አድርጓል።ከወንጌል አስተማሪነቱ በተጨማሪ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ፀጋ በጥላው ብዙ ሕሙማን ይፈውስ ነበር ሐዋ.፭፥፲፭።

ልጆች! በአንድ ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ‹‹ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ?›› በማለት ስለራሱ ጠይቋቸው ነበር።ከሐዋርያት አንዳንዶቹ ‹‹ኤርሚያስ ነህ ›› ይሉሃል ሲሉት አንዳንዶቹ ‹‹ ኤሊያስ ነህ›› ይሉሃል አሉት  ቀሪዎቹ ደግሞ ‹‹ከነቢያት አንዱ ነህ›› ይሉሃል ብለው መለሱለት።ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ‹‹ አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ መልሶለታል።ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹ አንተ አለት ነህ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርቲያኔን እሰራለሁ›› በማለት የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ ሰጥቶታል።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ  በዓለም ላይ ተዘዋውሮ ካስተማረው ትምህርት በተጨማሪ  በስሙ የተመዘገቡ እና የቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት አንደኛና ሁለተኛ የሚባሉ መልእክታትን ለክርስቲያኖች መጻፉ ይታወቃል።

ልጆች! ቅዱስ ጴጥሮስ ዓለምን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በእርጅና ዘመኑ የክርስቲያኖች ጠላት በሆነው ዓላዊው ንጉሥ በኔሮን ዘመነ መንግሥት የሞት ፍርድ ስለታወጀበት ወንጌልን ሲያስተምር ቆይቶ የሮም መኳንንቱ እንዳይገድሉት ልብሱን ቀይሮ ከሮም ከተማ ሲወጣ ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ከፊቱ ሲመጣ አየው። በዚህ ጊዜም ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን‹‹ ጌታ ሆይ ወዴት ትሄዳለህ?›› ብሎ ጠየቀው 

ጌታችንም ‹‹በሮም የሚሰቀልልኝ ስላጣሁ ልሰቀል መሄዴ ነው ›› አለው

ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ አይሆንም››  በማለት መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ሮም ተመለሰ።ሮማውያንም እንደ ሥርዓታቸው ቅዱስ ጴጥሮስን ከገረፉት በኋላ ሊሰቅሉት ወደ ሮም አደባባይ ይዘውት ሲሄዱ ‹‹ እንደ ጌታዬ ወደ ላይ ሳይሆን ቁልቁል ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ›› በማለቱ የሮም ወታደሮች እርሱ እንደነገራቸው ዘቅዝቀው በመስቀል ሰማእትነትን ተቀብሏል።ሥጋውንም መርቄሎስ የሚባለው ደቀ መዝሙሩ ሽቶ ቀብቶ እና በነጭ ሐር ገንዞ ዛሬ ቫቲካን በምትባለው የሮም ከተማ በክብር ቀብሮታል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ

ልጆች! ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተወለደው በንግድ በምትታወቀውና የኪልቂያ ዋና ከተማ በሆነችው በጠርሴስ ከተማ ሲሆን ቤተሰቦቹም ከብንያም ነገድ ናቸው (ሐዋ.፲፫፥፫)።አባቱ ሮማዊ ዜግነት ስለነበረው ቅዱስ ጳውሎስም በአባቱ በኩል ይህን ዜግነት አግኝቷል።

ቅዱስ ጳውሎስ ለሐዋርያነት ከመጠራቱ በፊት ስሙ ‹‹ሳውል›› ይባል ነበር።ጳውሎስ የሚለውን የራሱን ስም የሰጠው ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለ ሀገረ ገዥ ነው። ‹‹ቅዱስ ጳውሎስ›› የስሙ ትርጉም ‹‹ብርሃን›› ማለት ነው።በሌላም በኩል ‹‹ጳውሎስ›› ማለት ‹‹ምርጥ ››እቃ ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ ይህ በአሕዛብም፣ በነገሥታትም፣ በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው›› ሐዋ. ፱፥፲፭ ብሎታልና።ቅዱስ ጳውሎስ ድንኳን የመስፋት ሞያ ስለነበረው ያን እየሠራ ገንዘብ ያገኝ ነበር።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ፲፭ ዓመቱ በኢየሩሳሌም ከነበረው እና እጅግ ከሚታወቀው የገማልያ ትምህርት ቤት ገብቶ የኦሪትን ሕግና የነቢያት መጸሕፍትን፣የአይሁድን ሕግ  እየተማረ እስከ ፴ ዓመቱ ቆየ። ለኦሪት ሕግ እጅግ ቀናተኛ ነበር በዘመኑ የነበሩትን ክርስቲያኖች እጅግ ከመጥላቱ የተነሣም ለማጥፋት ያሳድዳቸው ነበር። ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተደብድቦ ሰማዕትነትን በተቀበለ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ የገዳዮቹን ልብስ ይጠብቅ ነበር (ሐዋ. ፯፥፶፰):: 

በደማስቆ ከተማም ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀርቦ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የሚያስችለውን የፈቃድ ደብዳቤ ተቀብሎ ወደ ደማስቆ ሄደ።በመንገድ ላይም እያለም ከሰማይ በወረደ ብርሃን አካባቢው ስለተሞላ ቅዱስ ጳውሎስ ማየት ተስኖት መሬት ላይ ወደቀ ከሰማይም፦

‹‹ሳውል  ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?›› የሚል ድምፅ ሰማ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ ጌታ ሆይ ማንህ?›› አለው ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹አንተ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፣ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብኻል›› በማለት ተናገረው። ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ጌታ ሆይ ምን እንዳደርግ ትወዳለህ?›› ሲል ጠየቀው 

ጌታችንም ከዚያ ተነስቶ ወደ ደማስቆ እንዲገባ ነበረው። ወደ ደማስቆም በገባ ጊዜ ሐናንያ የተባለው አባት ወደ እርሱ ሄዶ ወንጌልን በማስተማር አጠመቀው። ቅዱስ ጳውሎስም ከተጠመቀ በኋላ ያሳድዳቸው የነበሩትን ክርስቲያኖች እና ያላመኑ ሰዎችን ለማስተማር ወጣ። ልጆች! ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ሲሄድ በጌታችንና በመድኃታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠራ በኋላ በዐረብ፣ በሦርያ፣በግሪክ እንዲሁም በልስጥራ ተዘዋውሮ ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን ወደ ክርስትና እምነት አምጥቷል። እግዚአብሔር በሰጠው ፀጋ ብዙ ተአምራትን አድርጓል። በልብሱ ዘርፍም ብዙ ሕሙማን ይፈወሱ ነበር (ሐዋ. ፲፱፥፲፩)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዓለምን ዞሮ በቃል ካስተማረው በተጨማሪ በስሙ የሚጠሩ ፲፬ መልእክታት አሉት። ልጆች! ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሲሰብክ የቤተ መንግሥት ሰዎች ሳይቀሩ ብዙዎች ወደ ክርስትና ተመልሰው ነበር። በዚህም የተበሳጨው የሮም ንጉሥ ኔሮን ቄሣር ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ፍርድ ሸንጎ አስቀርቦ እንዲሞት ፈረደበት። ወታደሮች ሊገድሉት ሲወስዱትም ከንጉሥ ኔሮን ወገን የኾነችውን የአንዲት ብላቴና መጐናጸፊያ ‹‹ዛሬ እመልስልሻለሁ›› ብሎ ከተቀበላት በኋላ ፊቱን በብላቴናዋ መጐናጸፊያ ተሸፍኖ አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ በሰማዕትነት አርፏል። ደቀ መዛሙርቱም ራሱን ከአንገቱ ጋር ቢያደርጉት እንደ ቀድሞው ደኅና ኾኖላቸው በክብር ገንዘው ቀብረውታል።ሰያፊው ቅዱስ ጳውሎስን እንደ ገደለው ለመናገር ወደ ንጉሡ ሲመለስም ያቺ መጐናጸፊያዋን የሰጠችው ብላቴና ‹‹ጳውሎስ ወዴት አለ?›› አለችው።እርሱም ‹‹ራሱን ተቈርጦ በመጐናጸፊያሽ ተሸፍኖ ወድቋል›› ሲላት ‹‹ዋሽተሃል፤ እነሆ ጴጥሮስና ጳውሎስ በእኔ በኩል አልፈው ሔዱ። እነርሱም የመንግሥት ልብስ ለብሰዋል። በራሳቸውም በዕንቍ ያጌጡ አክሊላትን አድርገዋል። መጐናጸፊያዬንም ሰጡኝ። ይህችውም እነኋት፤ ተመልከታት›› ብላ ሰጠቸው። ከእርሱ ጋር ለነበሩትም አሳየቻቸው። አይተውም አደነቁ፤ ስለዚህም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ልጆች! ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁሌም በየዓመቱ ሐምሌ ፭ በድምቀት  የምታከብረው ቅዱስ ጴጥሮስ ተዝቅዝቆ በመሰቀል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ፊቱን በጨርቅ ተሸፍኖ በመሰየፍ በሮም አደባባይ ስለ ክርስቶስ መስክረው ሰማዕትነትን በመቀበላቸው በዓለ እረፍታቸውን በማሰብ ነው። እናንተም ከነዚህ ሁለት ሰማእታት ብዙ እንደተማራችሁ ተስፋ እናደርጋለን። ልጆች! በሚቀጥለው ትምህርታችን እስክንገናኝ ደኅና ሰንብቱ!

          ከቅዱሳኑ በረከት ያድለን አሜን!!

Read 801 times