Saturday, 15 May 2021 00:00

የጌታችን ትንሣኤ

Written by  እህተ ሚካኤል
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን .. . በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን አሰሮ ለሰይጣን  .  . . . . . አግዐዞ ለአዳም ሰላም  . . . . . . . . . . . . እምይእዜሰ ኮነ  . . . . . . . . . . . . . .ፍሥሐ ወሰላም ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ! ልጆች! የዛሬውን ጽሑፍ ከላይ ባለው ቃል ለምን  እንደጀመርን ታውቃላችሁ? ከትንሣኤ ጀምሮ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ያሉትን ፶ ቀናት ክርስቲያኖች ሰላምታ የምንለዋወጠው በዚህ መልኩ ስለሆነ ነው። ልጆች እናንተም ሰላምታ ስትለዋወጡ ‹‹ ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን. . . ›› እያላችሁ ሰላምታ መለዋወጥ አለባችሁ። ልጆች! ባለፈው እትማችን በዐቢይ ጾም ስያሜ ስለተሰጣቸው ስምንቱ ሳምንታት እና ታሪካቸው እንዲሁም ስለ ሰሙነ ሕማማት በተከታታይ ጽፈንላችሁ ነበር አስታወሳችሁ? ጎበዞች! ዛሬ ደግሞ ስለ ትንሣኤ እና ዳግማይ ትንሣኤ ጽፈንላችኋልና ተከታተሉን።  ትንሣኤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበረ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። በሰንበት ማታ ለእሑድ አጥቢያ መግደላዊት ማርያም እና ሁለተኛዋ ማርያም እንደ አይሁድ ልማድ የጌታችንን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ወደ መቃብሩ መጥተው ነበረ። ማርያም መግደላዊት እና ሁለተኛዋ ማርያም እየቀረቡ ሲሄዱ የመቃብሩን ድንጋይ ማን ያንከባልልልናል እያሉ እየተነጋገሩ ነበር።  ከመቃብሩ ሲደርሱ ግን የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆኖ ነበር። መልአኩም ጌታችን ተቀብሮበት የነበረበት መቃብር ላይ ተገጥሞ የነበረውን ድንጋይ አንከባሎ በላዩ ላይ ተቀመጠ። ሴቶቹም ነጭ በረዶ የመሰለ ልብስ የለበሰውንና መልኩ እንደመብረቅ የሆነውን መልአክ ባዩ ጊዜ ፈሩ። መልአኩም ሴቶቹን ‹‹እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና። እንደተናገረ ተነሥቷል ከዚህ የለም፤ እርሱ እንደተናገረ ተነሥቷል ፤ ነገር ግን ኑና ተቀብሮበት የነበረውን ቦታ እዩ. . . ›› አላቸው (ማቴ ፳፰፥፥፬።) ሴቶቹም ከደስታቸው ብዛት የተነሣ ወደ መቃብሩ ፈጥነው ሄዱ መቃብሩም ባዶ ነበረ መልአኩ እንደነገራቸው ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው ጌታችን መነሣቱን ነገሩአቸው። ከሐዋርያትም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መቃብሩ ሮጠው ሄዱ መቃብሩም ባዶ ነበርና ጌታ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን አረጋገጡ።   ልጆች! ሴቶቹ ከተመለሱ በኋላ የመቃብሩ ጠባቂዎች ወደ አይሁድ አለቆች ሄደው ክርስቶስ  በመቃብር ውስጥ አለመኖሩን ነገሯቸው ምክንያቱም የካህናት አለቆች የክርስቶስን መቃብር እንዲጠብቁ አዘዋቸው ነበርና እጅግ ደነገጡ። ለጠባቂዎቹም ብዙ ገንዘብ ሰጥተው እንዲዋሹ ነገሩአቸው። ‹‹እኛ ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀው ወሰዱት ብላችሁ በከተማው ውስጥ አውሩ›› (ማቴ. ፳፰፥፲፩—፲፬) አሏቸው። ጠባቂዎችም እንደተነገራቸው በከተማው ውስጥ እየዞሩ ይህን ማውራት ጀመሩ። ልጆች! የካህናት አለቆች ለምን ይህ ያደረጉ ይመስላችኋል? ክርስቶስ በምድር ላይ ተመላልሶ በሚያስተምርበት ጊዜ የካህናት አለቆችና ጻፎች እንደሚይዙት ፣ የሞት ፍርድ እንደሚፈርዱበትና እንደሚሰቅሉት ከተቀበረ በኋላ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ተናግሮ ነበርና የጌታችንን ትንሣኤ ላለመቀበል እና ተነሣ ብሎ ላለማመን ነው።  ልጆች! በዚያው ቀን በዕለተ እሑድ ሁለት ሰዎች ኤማሁስ ወደምትባለው መንደር ሲሄዱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸው። እነርሱም የጌታችንን መነሣት ለሐዋርያት ሊናገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ በደረሱም ጊዜ ጌታችንን እንዴት እንዳዩት ፣ ከእነርሱም ጋር ለማዕድ ተቀምጦ እንጀራን ቆርሶ በሰጣቸው ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። ይህንንም እየተነጋገሩ ሳለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ቆሞ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን፤አትፍሩ፤ እኔ ነኝ›› (ሉቃ.፳፬፥፴፮ ) አላቸው። ሐዋርያት ግን እጅግ ፈሩ መንፈስም ያዩ መስሎአቸው ነበር። ጌታችን ግን ‹‹ኑና እዩኝ መንፈስ እንደ እኔ ሥጋና አጥንት የለውም›› በማለት  የተወጉ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። ሐዋርያትም እጅግ ደስ አላቸው።  ልጆች! ትንሣኤን የምናከብረው ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ስለተነሣ ነው። ይህች ዕለትም ሰንበት ተብላ በክርስቲያኖች ዘንድ ትከበራለች። ምክንያቱም ጌታችን የተነሣባት የከበረች ዕለት ናትና።  ዳግማይ ትንሣኤ ዳግማይ ትንሣኤ ማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በስምንተኛው ቀን በዕለተ እሑድ ሐዋርያት በአንድ ቤት ተሰብስበው ሳለ ለሁለተኛ ጊዜ የተገለጠበት ቀን ስለሆነ ነው። ይህ ዕለት ጌታችን የተጠራጠረውን ቶማስን ና ዳሰኝ በማለት እንዲዳስሰው ያደረገበት ዕለት ነው። ልጆች! በመጀመሪያው እሑድ ጌታ ከመቃብር እንደተነሣ ሐዋርያት ወደተሰበሰቡበት ቤት ሲሄድ ቶማስ አልነበረም ተመልሶ ሲመጣ ሐዋርያት ‹‹ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል ብለው በነገሩት ጊዜ አላመናቸውም።ሐዋርያት የነገሩትን ያላመነበት ምክንያትም ቶማስ ከሰዱቃውያን ወገን ስለነበረ ነው። ሰዱቃውያን ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን አያምኑምና (ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ ይነሣል ብለው አያምኑም ነበርና ስለዚህ ነው) ማቴ. ፳፪፥፳፫። ቶማስም ክርስቶስ ተነሣ ሲባል የተጠራጠረው በዚያ ምክንያት ነው። ሐዋርያት በነገሩት ጊዜ ‹‹በዕለተ አርብ በጦር የተወጋ ጎኑን ካላየሁ እጆቼንም በተወጋው ጎኑ ካልከተትኩ አላምንም ›› ብሎ ነበር።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሣ በስምንተኛው ቀን ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት ሲገለጥ ቶማስም እዚያ ነበርና ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ዮሐ.፳፥፳፮ አላቸው። ቶማስንም ጠርቶ ‹‹ ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን›› (ዮሐ.፳፥፳፯) አለው። ቶማስም ጣቶቹን በተበሳው የጌታችን ጎን አስገብቶ ነበር በዚያ ሰዓት እጁ እሳት ውስጥ እንደገባ ጅማት ኩምትር ብላ ስለነበር ‹‹ ጌታዬ አምላኬም›› ዮሐ.፳፥፳፰ ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም ቶማስን ‹‹አንተ ስለአየኸኝ አምነሃል ሳያዩኝ የሚያምኑብኝ ግን ብፁዓን ናቸው›› ብሎታል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በስምንተኛው ቀን ለደቀ መዛሙርቱ መገለጡ በፊተኛው ትንሣኤ ሲገለጥላቸው ቶማስ ስላልነበር እርሱን ለማሳመን ነው። ሌላው ጌታችን የተነሣባት እለተ እሑድ የከበረች የክርስቲያኖች የዕረፍት ቀን መሆንዋን ሲያጸናላቸው እና እንዲያከብሯት ሊያሣስባቸው ነው።  ልጆች! ስለትንሣኤ እና ዳግማይ ትንሣኤ ምንነት በመጠኑም ቢሆን ልንገልጽላችሁ ሞክረናል። እናንተም በዓሉን አውቃችሁ በደንብ ልታከብሩት ይገባል። ዳግመኛ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ! መልካም በዓል ይሁንላችሁ! በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ደኅና ሁኑ እሺ ልጆች!
Read 689 times