Tuesday, 18 August 2020 00:00

በቃልህ አዝዝ ልጄም ይድናል (ማቴ.፰፥፰)

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
  ነቢያት በትንቢታቸው፣ ሐዋርያት በስብከታቸው ሕይወት፣ መድኃኒት እንደሆነ የመሰከሩለት፣ የስሙ ትርጓሜም መድኃኒት የሆነ ሁሉ የሚቻለው አምላክ በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህ ዓለም ሲመላለስ በዋናነት ዓለምን የማዳን እና ለዓለም አርአያ የመሆን ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ሕሙማነ ሥጋን  በተአምራት ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት አድኗል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን በዚህ ዓለም ያከናወነውን ተግባር ሁሉ ጠቅሶ መጨረስ አይቻልም። በመጽሐፍም ሁሉ ተዘርዝሮ አልተጻፈም። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ጌታችን ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልጻፈ ብዙ ሌላ ተአምራት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ። ነገር ግን ይህ የተጻፈ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እናንተ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ የዘለዓለም ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ነው” (ዮሐ.፳፥፴-፴፩) በማለት እንደመሰከረለት የተጻፈው ጥቂቱ ብቻ ነው። ጊዜ ገጥሟቸው ከመዋዕለ ሥጋዌው ደርሰው  በስብከቱ፣ በተአምራቱ አምነው የዳኑት እጅግ ብዙ ናቸው። ነገር ግን እርሱ የማዳን ተግባሩን ፈጽሞ በክብር ወደ ባሕርይ አባቱ እና ወደ ባሕርይ ሕይወቱ ካረገ በኋላ እርሱ የሾማቸውን መምህራን ሰምተን፣ የፈጸማቸውን ተግባራት ከመጻሕፍት ተረድተን ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንወርስ ዘንድ እግዚአብሔር ባወቀ ለእኛ የሚሆነን ያህል ተጻፈልን። ሐዋርያትን፣ ሊቃውንትን መምህራንን የሾመልን፣ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ አካላዊ ቃል በሥጋ ተገልጦ ወደዚህ ዓለም የመጣ፣ ዓለምን ያዳነ የሕይወት ቃል ነው።

 

ወንጌላዊውና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ከዋለበት እየዋለ ከአደረበት እያደረ የተማረውንና ያየውን ሲያስረዳ “ንዜንወክሙ በእንተ ውእቱ ዘሀሎ እምቅድም ውእቱ ዘሰማዕናሁ በእዘኒነ ወዘርኢናሁ በአዕይንቲነ ወዘጠየቅናሁ ወዘገሠሣሁ እደዊነ በእንተ ነገረ ሕይወት፤ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዓይናችንም ያየነውን የተመለከትነውንም  እጆቻችንም  የዳሰሱትን  እናወራለን፡፡” (፩ዮሐ.፩፥፩) በማለት ጽፎልናል፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ዓለምን ሊያድን በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ ወደዚህ ዓለም የመጣው ቅድመ ዓለም የነበረ መሆኑን መጀመሪያ የነበረው በማለት ቀዳማዊነቱን አስረዳን። ይህ ሐዋርያ ወንጌሉን ሲጽፍም “ በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለእርሱ ምንም የሆነ የለም” (ዮሐ.፩፥፩-፫) በማለት ቀዳማዊነቱን፣ ሁሉን ቻይነቱን፣ ሁሉን ፈጣሪነቱን ዘለዓለማዊነቱን አስረዳን። ይህን ቀዳማዊ የሆነውን አምላክ የሕይወት ቃል ብሎታል፡፡ ይህ የሕይወት ቃል ደግሞ ጥንት ፍጥረታትን ሲፈጥር ከብርሃን መፈጠር  ጀምሮ ለመላእክት የተሰማ፣ በኋላም ለሰው ልጆች ሁሉ እርሱ በፈቀደው መጠን እየተገለጠ ሲያናግር የተሰማ፣ በኋላም በሥጋ ማርያም ተገልጦ ሲያስተምር በሐዋርያት ጆሮ  የተሰማ አምላክ ነው። ለዚህም ነው በጆሯችን የሰማነውን በማለት የገለጸው።

በነቢያት ትንቢት ይወርዳል ይወለዳል ተብሎ እንደተነገረለት በመለኮቱ ከባሕርይ አባቱ ሳይለይ በተለየ አካሉ ሥጋ ማርያምን ተዋሕዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በሐዋርያት ዐይን ታየ፣ በእጃቸውም ተዳሰሰ። በመጽሐፈ ኪዳን “ዘውእቱ አምላክ ዘበአማን ዘበነቢያት አቅደመ ተዐውቆ ወበሐዋርያት ተሰብከ ወእመላእክት ተአኵተ ወእምኀበ ኵሉ ተሰብሐ፤ በነቢያት መታወቅን ያስቀደመ፣ በሐዋርያት የተሰበከ፣ በመላእክት የተመሰገነ፣ በሁሉ ዘንድ የተመሰገነ በእውነት አምላክ ነው” (ትምህርተ ኅቡአት) ተብሎ የተነገረለት አምላክ ነው።

ነቢያት አስቀድመው ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩለት፣ ሐዋርያት ወረደ ተወለደ ብለው የሰበኩትና የመሰከሩለት አምላክ መድኃኒት ነው፣ የሕይወት ቃልም ነው፣ ሁሉን ይችላል፡፡ ስለዚህ በመቶ አለቃው አንደበትም “በቃልህ አዝዝ ልጄ ይድናል” ተብሎ ተነገረለት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልዩ ልዩ መንገድ ሕሙማንን ፈውሷል። ለማሳያ ያህል በሚከተሉት መንገድ እንደፈወሰ እንመለከታለን። 

በገሢስ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕሙማንን ዳስሶ እንደፈወሰ ወንጌላዊው ማቴዎስ “ጌታችን ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ የጴጥሮስ አማት በንዳድ ታማ ተኝታ አገኛት፡፡ እጇንም ይዞ ዳሰሳት፤ ንዳዱም ተዋት፤ተነሥታም አገለገለቻቸው፡፡” (ማቴ. ፰፥፲፬-፲፭) በማለት የጻፈውን የወንጌል ክፍል እናነባለን። ጥንት ዓለምን ሲፈጥር በኀልዮ፣ በነቢብና በገቢር የፈጠረ አምላክ በመዋዕለ ሥጋዌውም በኀልዮም፣ በነቢብም ፣ በገቢርም ፈውሷል። ሁሉ የሚቻለው አምላክ ነውና በሽተኞችን መድኃኒት በሆነው እጁ ሲዳስሳቸው ይፈወሳሉ። 

በወሪቀ ምራቅ ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ፣ ዓለምን የፈጠረ፣ ዓለምን ሊያድን ወደዓለም የመጣ ነውና ሁሉ የሚቻለው አምላክ እንደሆነ እንድንረዳ በምራቁ ዕውሩን ፈወሰ። “የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ ይህንም ብሎ በምድር ላይ ምራቁን እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ የዕውሩን ዐይኖች ቀባው፡፡ እንዲህም አለው ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ….ሄዶም ታጠበና እያየ ተመለሰ፡፡” (ዮሐ.፱፥፩-፯) እንዲል። የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ ያለ አምላክ ብርሃንነቱን እንረዳ ዘንድ በምራቁን ዕውሩን አበራ። እኔ እንዲህ ነኝ ያለ አካል መሆኑን ማረጋገጥ መቻል አለበት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ነኝ ሲል ዕውራንን አበራ፣ መድኃኒት ነኝ ሲል ሕሙማንን ፈወሰ።

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በጾመ ድጓ ድርሰቱ “ከልሐ ዕውር በውስተ ፍኖት ወገሠጽዎ እለ ይመርሕዎ ከመ ያርምም ወአእበየ ከሊሐ እንዘ ይብል ተሣሃለኒ እግዚእየ ወልደ ዳዊት ርድአኒ፤ ዕውሩ በመንገድ ላይ ጮኸ፤ የሚመሩትም ዝም ይል ዘንድ ገሠጹት እሱ ግን የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ እያለ ዝም ማለትን እንቢ አለ” (ጾመ ድጓ ዘምኵራብ) በማለት የዐይነ ስውሩን ጩኸት መዝግቦልን እናገኘዋለን። ከላይ በወንጌሉም እንዳነበብነው የለመኑትን የማይነሳው የነገሩትን የማይረሳው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምራቁን እንትፍ ብሎ ቀባው ዐይነ ስውሩም ተፈወሰ። የሰዎች ምራቅ በዐይን ላይ ቢተፋ ዐይን ሊያጠፋ ይችላል። ኅሊናም ይጎዳል። እገሌ እኮ ፊቴ ላይ ተፍቶብኝ ሄደ ብለው ሰዎች እርስ በእርስ ይጋጫሉ። በእርግጥም አንድ ሰው ሌላ ሰው ፊት ቢተፋበት ነውር ነው ያስቀይማል። ሁሉ የሚቻለውና ሁሉ መድኃኒት የሆነው አምላክ ግን ምራቁ መድኃኒት ነውና ዕውር አበራ።

በዘፈረ ልብስ፡- ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ባለመድኃኒት አጥታ ስትቸገር የነበረች አንዲት ሴት በመድኃኒትነቱ አምና የልብሱን ጫፍ በነካችው ጊዜ ደሟ ቆሞላት ከሕመሟ መፈወስ ችላለች። ይህንም ወንጌላዊው ማቴዎስ በቅዱስ ወንጌል “እነሆ ከዐሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም ይፈሳት የነበረች ሴት በኋላው መጥታ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች በልቧም የልብሱን ጫፍ ብቻ የዳሰስሁ እንደሆነ እድናለሁ ብላ አስባ ነበርና ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ አያትና ልጄ ጽኚ እምነትሽ አዳነችሽ አላት፤ ከዚያም ሰዓት ጀምሮ ያቺ ሴት ዳነች፡፡” (ማቴ.፱፥፳-፳፪) በማለት መዝግቦታል።

በስሙ አምነው የእርሱን መከራ መስቀል ለመቀበል ወስነው ለአገልግሎት የተሰማሩት ሐዋርያትም በልብሳቸው ጫፍ በጥላቸው ሕሙማንን ሲፈውሱ ኖረዋል። ዛሬም ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆኑ አባቶች ሀብተ ፈውስ የተሰጣቸው ቅዱሳን ይኖራሉ። የእነርሱ ግን የጸጋ ነው፤ የእርሱ የባሕርዩ ነው። እርሱ ስሙ መድኃኒት ነው፣ ልብሱ መድኃኒት ነው፤ እጁ መድኃኒት ነው። ሕመምተኛው ግን ያድነኛል ብሎ አምኖ መቅረብ ይኖርበታል። ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት “እምነትሽ አዳነችሽ”  እንዳላት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል።

በቃል፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከላይ በዘረዘርናቸው ማለትም በመዳሰስ፣ በምራቁ፣ በልብሱ ጫፍ እንደፈወሰ ሁሉ በቃሉም የፈወሳቸው  ሕሙማን በርካታ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በርእሳችንም መነሻ ያደረግነውን የመቶ አለቃውን ልጅ ታሪክ እንመልከት። ይህን ታሪክ ወንጌላዊው ማቴዎስ “ወአውሥአ ሐቤ ምዕት ወይቤ እግዚኦ ኢይደልወኒ ከመ አንተ ትባእ ታሕተ ጠፈረ ቤትየ ዳእሙ አዝዝ በቃልከ ወየሐዩ ወልድየ፤ የመቶ አለቃውም መልሶ አቤቱ አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም ነገር ግን በቃልህ አዝዝ ልጄም ይድናል ፤…(ማቴ.፰፥፭-፲፫) በማለት በቅዱስ ወንጌል መዝግቦት እናገኘዋለን።

የመቶ አለቃው መጥቼ አድንልሃለሁ እየተባለ አንተ መጥተህ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም በቃልህ አዝዝ ማለቱ እየለመነው ያለው ሁሉ የሚቻለው አምላክ እንደሆነ በእርሱ ላይ አድሮ ሊያስተምረን ስለፈቀደ ነው። የመቶ አለቃው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ በማዘዙ እንደሚሆንለት አምኖ ተናገረ። በእርግጥም ሁሉ ይቻለዋል ሊቁ ቅዱስ ያሬድም እንዲህ በማለት ይገልጸዋል።

“ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ፤ቅድመ ዓለም የነበረ ዛሬም ያለ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር እግዚአብሔር ከላይ ከሰማይ የወረደው ፤አይሁድ ሰቀሉት፤ግን ምንም አላወቁም ሁሉን በቃሉ የሚያድነውን የሁሉን ጌታ ሰቀሉት፡፡” (ቅ/ያሬድ፣ ጾመ ድጓ) በቦታ የማይወሰነው አምላክ ልዕልናውን ለመግለጽ ከላይ የወረደውን ተብሎ ይነገርለታል። ይህ ከላይ የወረደው አምላክ አይሁድ የሰቀሉት፣ የሁሉ ጌታ፣ በቃሉ የሚያድን እነርሱ ግን ያላወቁት አምላክ እንደሆነ ሊቁ ያስረዳናል።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የራሱን የመቶ አለቃውን ቃልም “ይቤሎ መስፍን ለኢየሱስ በዕለተ ሰንበት ኢይደልወከ ትባእ ታሕተ ጠፈረ ቤትየ አዝዝ በቃልከ ይሕየው ወልድየ፤ መስፍኑ ኢየሱስን በዕለተ ሰንበት እንዲህ አለው ከቤቴ ጣራ በታች ትገባ ዘንድ አይገባህም በቃልህ ብቻ አዝዝ ልጄ ይድናል፡፡ (ቅ/ያሬድ፣ ጾመ ድጓ) በማለት ገልጾታል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም “ዐቃቤ ሥራይ ወረደ እምሰማየ ሰማያት ወዕፀ ፈውስ ተረክበት በቤተ ዳዊት፤ ባለመድኃኒቱ ከሰማየ ሰማያት ወረደ ለመድኃኒትነት የምትሆነው እንጨት ከዳዊት ቤት ተገኘች” (መጽሐፈ ምሥጢር) በማለት ያስረዳል። ባለመድኃኒቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ለመድኃኒትነት የምትሆነው እንጨት የተባለች አምላክን በኅቱም ድግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና የወለደች ድንግል ማርያም ናት። ከእርሷ በተዋሐደው ሥጋ ዓለምን አድኗልና ለመድኃኒትነት የምትሆነው ዕንጨት ከዳዊት ቤት ተገኘች በማለት አስረዳን።

ስለዚህ የመቶ አለቃው ልጁን እንዲፈውስለት የለመነው ቅድመ ዓለም የነበረው፣ ዓለምን የፈጠረው፣ ዓለምን ለማዳን ወደዚህ ዓለም በሥጋ ማርያም የተገለጠው አምላክ ወልደ አምላክ ነው። ይህን ስለተረዳም ከሩቅ መጥቶ መድኃኒት የሆነውንና ሁሉን የሚችለውን አምላክ ለመነው። ፈቃዱም ተፈጸመለት። መተርጉማን እንደሚያስረዱት በዚህ ታሪክ የመቶ አለቃው ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን አሟልቶ ተገኝቷል። እነርሱም፡-

ሀ. ሃይማኖት፡- የመቶ አለቃው በፍጹም ሃይማኖት  ያድንልኛል ብሎ መምጣቱ የፈለገውን ከማግኘት ባሻገር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም  አስመስግኖታል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም” (ዕብ.፲፩፥፮) በማለት እንደገለጸው ሃይማኖቱ ፍጹም መሆኑ እግዚአብሔርን አስደስቶታል። ስለዚህ እንደ መቶ አለቃው የፈለግነውን እንድናገኝ፣ እኛም የፈለግነውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር የፈቀደልንን እንዲሰጠን በሃይማኖት መጽናት ያስፈልጋል።

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም “ጥበብን ያጣ ሰው ቢኖር ሳይነቅፍና ሳይነፍግ ለሁሉ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱ ይሰጠዋል። ነገር ግን አምኖ ይለምን፤ አይጠራጠርም፤ የሚጠራጠር በነፋስ የሚገፋና የሚነዋወጥ የባሕር ማዕበልን ይመስላልና” (ያዕ.፩፥፭-፮) በማለት እንደገለጸው ያለምንም ጥርጥር የሚለምን ሁሉ የፈለገውን ያገኛል፣ ቢታመም ይፈወሳል፣ ቢያጣ ያገኛል፣ ቢያዝን ይደሰታል፤ ቢቸገር ከችግሩ ይወጣል። ግን ያለምንም ጥርጥር መለመን አለበት። ከመቶ አለቃው የምንማረው ይህን ነው። 

ለ. ጥበብ፡- መቶ አለቃው እርሱ ያለበትን የሥልጣን ደረጃ በምሳሌነት አቅርቦ እኔም እንደአቅሜ አለቃ ነኝ ከእኔ በታች ያሉትን ማዘዝ እችላለሁ። ለእኔ እንዲህ የሚቻል ከሆነ ለአንተማ ሁሉ ይቻልሃል በማለት ነው ጥያቄውን ያቀረበው። ስለዚህ ጉዳዩን ለመግለጽ በጥበብ መጓዙን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ወዶለታል። እኛም ሥራችንን በጥበብ ብናከናውን፣ ጉዳያችንን ከእኛ በላይ ለሆነ አካል በጥበብ ብናስረዳ በፍጥነት ችግራችን ይፈታልናል። 

ይህ ዘመን በሥጋ ጥበበኞች ነን ለሚሉት ያልተቻላቸው ምልክቱ እንኳን ከቀን ወደ ቀን እየተለዋወጠና እየተቀያየረ የሚያስቸግር በሽታ የተስፋፋበትና ዓለምም የተጨነቀበት ዘመን ነው። ስለዚህ ሃይማኖታችንን አጽንተን እንደመቶ አለቃው ጥበበኛ ሁነን ይህን ክፉ ቀን ማለፍ ያስፈልጋል። ይህን ክፉ ቀን የምናልፍበት ጥበብም የሚገኘው ከራሱ ከባለቤቱ ነውና ይህም እንዲሆን “በቃልህ አዝዝ ልጄ ይድናል” እንዳለው ሁሉ የአንተ ፈቃድ ከሆነ ከመጣው መከራ እድናለሁ ማለት ይኖርብናል። ጥበቡንም የሚያድል የጥበብ ባለቤት እግዚአብሔር ነውና የእኛን ጥበብ ከእግዚአብሔር ሳናስቀድም በእግዚአብሔር ቸርነት እንደተገለጠልን እያሰብን እና እያመንን የምንችለውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሐ. ትሕትና፡- ራስን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን ማክበር፣ ከራስ ይልቅ ሌሎችን ከፍ ማድረግ ነው። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ደቀ መዛሙርቱን “ለእናንተ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከእናንተ ታላቁ እንደ ታናሽ ይሁናችሁ፤ አለቃውም እንደ አገልጋይ ይሁን” (ሉቃ .፳፪፥፳፮) በማለት አስገንዝቧቸዋል። የመቶ አለቃውም ምንም እንኳን በሀገሩ ገዢ ቢሆንም ወደ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ራሱን ዝቅ በማድረግ በፍጹም ትሕትና መጣ። ይህ ብቻ ሳይሆን መጥቼ አድንልሃለሁ ሲባልም አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ትገባ ዘንድ አይገባኝም በማለት ፍጹም ትሕትናውን ገልጾአል።

ትምህርቱን ከምንጩ የተማረው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም በመንፈስ ቅዱስ ለወለዳቸው ምእመናን መልእክት ሲልክ “ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ” (፩ጴጥ.፫፥፰) በማለት አስረድቷል። ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ምዕራፍ በተሰኘ ድርሰቱ “እስመ በትሕትና ረከበ ልዕልና ወብፁዕ ሚካኤል ዘቦቱ ትንብልና መጽአ ከመ ይዜኑ ሠናየ ዜና፤ ንዑድ ክቡር የሆነ ሚካኤል በትሕትና ክብርን አገኝቷልና መልካም ዜናን ሊነግር መጣ” በማለት የትሕትናን አስፈላጊነትና የሚያስገኘውን ክብር ያስረዳል።

በአጠቃላይ ከላይ በተዘረዘረው መሠረት በመዳሰስ የፈወሳቸውንም፣ በምራቁ የፈወሳቸውንም፣ በልብሱ ጫፍ የፈወሳቸውንም፣ በቃሉ የፈወሳቸውንም ስንመለከት ከተፈወሱት በኩል የተሟላ ነገር እንደነበር እንገነዘባለን። እርሱም ሃይማኖት በዋነኛነት ሲሆን ትእግሥት፣ ጥበብ፣ ትሕትና የመሳሰሉት ናቸው።  እኛም  ሃይማኖትሽ አዳነችሽ፣ ሃይማኖትህ  አዳነህ፣ እንደወደድህ ይሁንልህ እንደተባሉ ሰዎች በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር ሠርተን በእግዚአብሔር ዘንድ እንድንመሰገን፣ ከመጣብን ቸነፈር እንድንድን፣ በቸርነቱ እንዲሰውረን እግዚአብሔርን በቃልህ አዝዝ እንድናለን፣ ፈቃድህ ይሁን እንፈወሳለን ብለን በእምነት ልንጠይቀው ይገባል። ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክን የኢየሩሳሌምን መጥፋት እንዳያይ ለስልሳ ስድስት ዓመት ያህል የሰወረ አምላክ አምላካችን ነውና ከመጣው ቸነፈር እንዲሰውረን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን።

 

Read 2775 times