Friday, 04 September 2020 00:00

፲፪ ፲፪ ፲፪ አስፈሪው የጥፋት ኮድ

Written by  ረቂቅ መቻል
ወሩ እንዴት ነበር? መቼም ከባለፈው  ወር ጋር እንደምታነጻጽሩት እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ፡፡ በቁስል ላይ ቁስል ሲጨመር ምን ያህል  እንደሚያም መገመት አያዳግትም? በዚህ ዓመት ሀገሬና  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሆነባቸውን ሁልጊዜ እየታዘብኩት ነው የማልፈው፡፡  ያሳለፍናቸው  ዓመታትና ወራት፣ አሁን ያለንበት የክረምት ወር በተፈጥሮ ዑደቱ ጥሩ መጥፎም አልነበረም፡፡ ተፈጥሮ የራሷን ሥራ በአግባቡ ታከናውናለች፡፡ የክረምቱ ዝናብ ይዘንባል ፣ ፀሐይና ጨረቃም እንደ ወትሮቸው  ባይሆኑም በተሰጣቸው የተፈጥሮ ሚዛን ላይ ሆነው  ብቅ ጥልቅ ማለታቸውን ቀጥለዋል ፡፡ እኔም ወደ ውጪ የሚላክ ዕቃ ለማድረስ ከቤቴ ወጥቻለሁ:: መንገዱ በተለየ ሁኔታ ፀጥ ረጭ ብሏል፤ አዲስ አበባን ወትሮ ለሚያውቃት ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ አትመስልም፡፡ ደግሞ ዛሬ ምን ተከሥቶ ይሆን? ብዬ የተሳፈርኩበትን  የታክሲ  ሾፌር ፈራ ተባ እያልኩ ጠየኩት፡፡ አልሰማሽም እንዴ? ሲል በመኪናው የኋላ በስፖኪዮ  እያየኝ  ማውራት ጀመረ፡፡  ወይ ሀገሬ  ደግሞ ምን ሆነሽ  አደርሽ?  ባለፈው ሰኔ ፳፫ ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ጽፈኞች ከተማችንን ሲያተራምሱ አደሩ ዛሬ ደግሞ ማን ሞተ  አልኩት? ማን ይሞታል ብለሽ ነው አክቲቪስት ጁዋር መሐመድ ትናንት ፍርድ ቤት  ቀጠሮ ነበረው እናም ዳኛውን  አሞኛልና  እባክህን በነፃ ልቀቀኝ ብሎ በለቅሶ ሲማጸን መዋሉን የሰሙ ተከታዮቹ እንደለመዱት  ሀገር ለማተራመስ ሰው ለማረድ፣ ንብረት ለማውደም የጥፋት አዋጁን ማስፈጸሚያ ያዘጋጀውን ቅጥር ፲፪/፲፪/፲፪ ብሎ በመሰየም የሰው ማረጃና ንብረት ማውደሚያ ኮድ  ያሴሩት ሴራ በፖሊስና በመከላከያ  ኃይል ከሽፎ አደረ:: በርግጥ በአንዳንድ የሀገራችን ከተሞች  ንቅናቄው ተካሄዷል፡፡ በተለይም በአወዳይ፣ ሻሸመኔ ፣ጊነር፣ አዳማና ባሌ መስመር  እያለ ተረከልኝ፡፡ 

 

አስቡት እንግዲህ በአንድ ግለሰብ ምክንያት ሀገርና መንግሥትን ማሸበር ፡፡ ሰው ነኝና እንዲህ ሲለኝ የሆነ ነገር ብዥታን ፈጥሮብኝ ማለፉ አልቀረም፡፡ ያሳለፍናቸው  ሁለት ዓመታት ጥሩ አለመሆናቸው ሲገርመኝ የዘንድሮው ደግሞ  ይባስ አስገረመኝ አሳዘነኝም ፡፡ ሀገሬና ቤተክርስቲያኔ የቆሰሉት ቁስል ሳይሽር ሌላ ቁስል ሊመጣ ነው ሲባል አያስገርምም ትላላችሁ? መች ይሆን  ኢትዮጵያ ያረገዘችውን መጥፎ ሽል የምትገላገለው አልኩ ፡፡ ይህችን ሀገር ማን እንደሚመራት ግራ ገባኝ እንግዲህ የሀገር ነገር ሲነሣ እኛ ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበት ድንቅ የሀገርና የሕዝብ ማስተዳደሪያ መርሕ  እንዳለን አይዘነጋም፡፡

እውነታው መታወቅ አለበት እላለሁ ፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ  ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ጌጥ ነች፡፡ ለምን ብትሉኝ ሀገሬና ቤተክርስቲያን ከሦስት ሺ ዘመን በፊት በቅዱስ መጽሐፍ ቃል የተሳሰሩ በቃል ኪዳን  የተሳሰሩ  የቃል ኪዳን አምባዎች (ተራሮች) ታቦርና አርሞንኤም ናቸው፡፡

የሀገሬና የቤተ ክርስቲያኔ ደስታቸውም ሆነ መከራቸው የጋራ ነው፡፡ ሁልጊዜም ሀገሬ የመከራ ጽዋን ስትጎነጭ ቤተ ክርስቲያን የዚሁ ጽዋ ተካፋይ ማኅበርተኛ ትሆናለች፡፡ አጥፊዎች ከመንደር ፖለቲከኞች ጋር በማበር በአንድ ሌሊት ሲያቃጥሉ እና ሲያወድሙ ስላደሩት አብያተ ክርስቲያናትና  ምእመናን  ሳስብ ሁልጊዜ ይጨንቀኛል፡፡  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፊደልን ከነ ቁጥሩ  ለሀገር  ለዓለም ያበረከተች ፣ ሕግን ከነ ሥርዐቱ የደነገገች ቀዳሚና ወደር የማገይኝላት ሆና ሳለች ሁልጊዜ  የሕዝብና የመንግሥት ችግሮችን ገፈት ቀማሽ መሆኗ ያሳዝናል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰው ጥቃት በተደላደለ መሠረት ላይ በቆመ መንግሥታዊ መዋቅር የተደገፈ እንደነበር ብዙ ማሳዎችን መታዘብ ችያለሁ፡፡ በመሆኑም ችግሮችን ከሥሩ በመንቀል እንጂ እገሌን እንዳይከፋው በሚል የተድበሰበሰ ርምጃ የሚታረም እንዳልሆነ  አሁን ሁላችንም ተረድተናል ፡፡

 በዚህ ዓመት ብቻ ከአንዳንድ ግለሰቦች ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ውስጥ በተለይም በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት ቀላል የሚባል አልነበረም  ለምሳሌ በጥቅምት ወር አክቲቪስት ጁሀር መሐመድ ተከብቤአለሁ በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ  ሲጮህ  በዚያ ሳቢያ በመላው ሀገር የሞቱት፣  በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት፣ ከመቶ ያላነሱ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን  ያጣንበት፣ ምእመናን ሀገሬ ብለው ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩት ንብረት የወደመበት  ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በርግጥ  ድርጊቱ በሁላችንም ከባድ የኃዘን ሸክም ጥሎብን ነው ያለፈው፡፡

አሁንም ድረስ በጽንፈኛው ቡድን አማካይት በሀገሪቱ ፣በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ በተከታታይ እየተካሄደ ያለው ኦርቶዶክስን የማጥፋት ዘመቻ አልቆመም፡፡ የመንግሥት አካላት በመንግሥታዊ ቁመናቸው (ኃላፊነታቸው) የቤተክርስቲያንን ክብርና መብት ማስጠበቅ ሲገባቸው ግለሰባዊ ቁመናቸው ፣ ዘራቸውና ብሔራቸው እያስጨነቃቸው ቤተ ክርስቲያንንና ሕዝበ ክርስቲያኑን ሲበድሉ አይተናል ሰምተናል፡፡ ይህ አስከፊ ምድራዊ የሰዎች አሠራርና ክፉ እሳቤ  እንደ ሀገር ሕዝቡን፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን  ደግሞ ምእመናንን እና አባቶችን አሳዝኖ እንደ ነበር ከማንም የተሠወረ አይደለም፡፡ 

በእርግጥ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጴጥሮሳውያን ህብረትና ሌሎች ኦርቶዶክሳውያን ማኅበራት በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲከሠቱ ከእሾህ ወይን ፥ ከኵርንችት በለስ እንደማይለቀም እያወቁም ቢሆን መፍትሔ ለማምጣት ብዙ ሲደክሙ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ የኦርቶዶክሳውያን አፍ የሆኑት እነዚህ አባቶች ፣ ወንድሞች እና የሐገር ሽማግሌዎች  የቤተክርስቲያን አለኝታና መከታ የሆኑ  የቁርጥ ቀን ልጆች ስለ አብያተ ክርስቲያናትና ምእመናን  በየሹማምንቱ በራፍ ፍትሕ ለማግኘት ደጅ ቢጠኑም  የሚሰማቸው አልተገኘም፡፡ በተቃራኒው የእናንተም እጅ ስላለበት ነው የሚል ስላቅና ትችት ነበር የገጠማቸው።  እውነት ነው የደማቸውን ጩኸት የሚሰማው መድኃኔዓለም ክርስቶስ ብቻ በመሆኑ እርሱን ለእርሱ መተው ነው የሚበጀው፡፡ ነገር ግን "ከመንግሥት መመሪያ አልተሰጠኝም" እየተባለ ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል፣ሀገር ስትወድም ፥ ሰው ሲታረድ  ርምጃ የማወይስድ መንግሥት ማየቱ  በራሱ ውስጥን ያሳምማል ነገሩ ሁሉ የተገላባቢጦሽ ነው ወገኖቼ፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንና ሀገሬ  በገዛ ልጆቿ እንደ አሁኑ ዘመን ተዋርዳና ተደፍራ አታውቅም፡፡  

ሌላው የሚያስገርመው ክረምቱ በመጣ ቁጥር የሚዘወረው የፖለቲካና ፖለቲከኞች ቁማር ፍጻሜው ቤተ ክርስቲያንን ማውደም፣ ምእመኖቿን ማረድ መሆኑን ከብዙ ተሞክሮዎች ደጋግመን ታዝበናል፡፡ ቤተክርስቲያን  ሆይ ሀገርን  በእምነት አጽንተሸ መልካም ዜጎችን በዕውቀትና በምግባር ኮትኩተሽ ለፍሬ እንዳላበቃሽ የወላድ መካን ትሆኚ?  እፎይ የሚያስብልሽ የብሥራት ዜና መች ይሆን የምትሰሚው? ፣ መች ይሆን  እንደ ጥንቱ እንደ ጠዋቱ ኢትዮጵያና ቤተ ክርስቲያን በዓለም የከፍታ ዘመን ላይ በሰላም ቀና ብለው ፈጣሪን የምታመሰግኑት?  የሚል መንፈሳዊ ቁጭት ውስጤን ይጠዘጥዘኛል፡፡   

የቀደሙ አባቶቻችን ዮዲት ጉዲትን፣ ግራኝ አህመድን፣ ጣልያንና መሰል የሀገርና የቤተክርስቲያን  ጠላቶችን እንዴት አድርገው በጸሎት እንደረቱ ባሰብኩ ሰዓት እጽናናለሁ፡፡ በእርግጥ የነግራኝን፣ የነ ዮዲት ጉዲትን በታሪክ ነበር የሰማነው፣  በመጽሐፍም ነበር ያነበብነው፡፡  የዚህኛውን ትውልድ ግፍ ግን በዓይናችን እያየነው ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት ለደረሰባት ጥቃት ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችን ስንዱ እመቤት ነበረች አሁን ማን ይሆን አቅሟንና ባለሙያነቷን የሰለበው ?

እግዚአብሔር እንደ ልቤ ያለው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ  (መዝ.፷፰፥፱ ) “የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና፡፡ ሰውነቴን በጾም አስመረርሁአት ለስድብንም ሆነብኝ፡፡” እንዳለው በነዚህ ሰዎች ላይ ቅጣቱን ቢያዘገይም እኔ ግን  በጣም ተናደድኩና ቁጭቴን እንደ ዳዊት ለእግዚአብሔር በቅንዓት ጮህኩ፡፡ ግን እስከመቼ? 

ሀገር አጥፊ ቡድኖች ከየት መጡ ሳይባል  ግልብጥ ብለው በአንዴ መዲናዋንና የገጠር ከተሞቿን የሚወሯት ሀገራችን እየታወሰችን በንጹሐን ደም እየታጠበች ያለችው  በባዕዳን ሀገር ቁጭ ብለው ሀገር የማተራመስ አባዜ የተፀናወታቸው የእናት ጡት ነካሾች በሚልኩት እኩይ መልእክት ነው ። ለዚህ ደግሞ በየዕለቱ በየማኅበራዊ ሚዲያው የምናየው የጥላቻ እና አንዱን በአንዱ ላይ እንዲነሣሣ የሚያረድጉ ጽሑፎች ዋቢ ምስክሮቻችን ናቸው። እነርሱ በባዕዳን ሀገር ተቀምጠው ሀገር ትውደም ሃይማኖቷም ትጥፋ እያሉ ሀገርን በገንዘብና  በራስ ወዳድነት የስካር ሀሳብ የሚሸጡት እርስ በርስ እንድንጨራረስ የሚያደርጉን ምስኪኖቹ የሀገሬ ልጆች ሳይሆኑ ለሆዳቸው ያደሩ ሀገር በቀል ባንዳዎች መሆናቸው አሁን ገባኝ፡፡  

     ለሁላችንም ገዳዮቻችን ከየጎጡ የወጡ የዘውግ ፖለቲከኞችና በሃይማኖት ስም የሚጦምሩ ጦማሪዎች ናቸው ፡፡ ይኸው  የሰቆቃ መዓት ከክረምቱ ዝናብ ጋር አኮስምኖን አስቆዝሞናል፡፡ የዚህ ትውልድ መጨረሻ ምን ይሆን? እግዚአብሔር ይሁነን እንጂ ፡፡

የቄሳርን ለቄሳር  እንተወውና የሀገሬ ክርስቲያኖች በውጭም ያላችሁ ኦርቶዶክሳውያን አንድ ነገር አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላልና “ሥራህንና ፍቅርህን ፥ እምነትህንም አገልግሎትህንም ፥ ትዕግሥትህንም የኋለኛይቱ ሥራህም ከፊተኛይቱ ይልቅ እንደምትበዛ አውቃለሁ”  ተብሏልና የምድሩን ክፉ ዘር ለምድራውያኑ ትተን የሰማይ ቤታችንን እንስራ መልእክቴ ነው (ራእ. ፪፥፲፱)፡፡

በመጨረሻም  በአብያተ ክርስቲያናትና ክርስቲያኖች  ላይ  ፈተናዎች  ክፉኛ ማንጃበብ ከጀመሩበት ከ፳፻፲ዓ.ም ጀምሮ  እስከ አሁን የደረሰው መከራ በዚህ ይብቃንና  ሁላችንም በተንኳሾች ተግባር ሳንወናበድ  ቅዱሳን ኣባቶቻችንን የሄዱባት መንገድ ተከትለን ፣በእምነታችን ሳንደክም ኅብረታችን አጠናክረን ከአባቶቻችን ጋር እንቁም፡፡  በጸሎት እንበርታ፡፡  ክርስትናችንን  እና ቤተ ክርስቲያንን በማያስነቅፍ ሁኔታ  ፍትሐዊ ርምጃ መውሰድ ፣ራስንና ቅድስት ቤተክርስቲያንን በጋራ መጠበቅ ብሎም መከላከል  ብቸኛው አማራጭ ነው። አምላክ በቸር ያቆየን መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን ይሁንላችሁ፡፡   

 

 

Read 950 times