Friday, 06 August 2021 00:00

የ‹‹ቴዎድሮሳውያን›› ማሰናከያ

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
በኢትዮጵያ ‹‹መልካም ንጉሥ ይነግሣል›› የሚል ትንቢት እንዳለ በትውፊት ሲወራረድ የመጣ ንግር አለ።ከዚያ በመነሣትም ከመካከለኛው የኢትዮጵያ የታሪክ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ ጭንቅ በከበባት ቁጥር የትንቢቱ ፍጻሜ ይናፈቃል።እንዲህ ያለው ልማድ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ ቆይቷል።በኢትዮጵያ የረጅሙ ዘመን በተለይ በዘመነ መሳፍንት የዚህ ንግር ፍጻሜ ናፋቂዎች በርክተው ስለነበር መሳፍንቱን አሸንፈው የነገሡት ራስ ካሣ ኃይሉ ዐጼ ቴዎድሮስ ተብለው እንዲነግሡ ምክንያት እንደሆነ ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ “Literary Origins of Ethiopian Millenarianism” በሚለው ጥናታቸው ይጠቅሳሉ።በዚህም ሳያበቃ ውጣ ውረድ በመጣ ቁጥር ይሄንኑ ፈታሒ ንጉሥ የመናፈቅ ጉዳይ በክርስቲያኑ  የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ ሲንጸባረቅ ቆይቷል።በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ በርካቶች ራሳቸውን ‹‹ቴዎድሮስ›› አድርገው በማሰብ፣ በመቃዠት ከትውልድ ትውልድ ተፈራርቀዋል።በርካቶች ለአእምሮ መታወክ ተዳርገዋል።ዛሬም ድረስ ይሄው ልማድ ይንጸባረቃል።በብዙኃን መገናኛዎች ጭምር እኔ ንጉሥ ነኝ የሚሉ ወጣቶች ታይተዋል።ያልጨበጡትን እንደጨበጡ፣ ይልሆኑትን እንደሆኑ የሚሰማቸው ተጎጂ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ነው።

 

ይህ ጉዳይ ግን በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚፈትናት ሆኖ እየተገለጸ ነው።ከዚያም አልፎ ፖለቲከኞች ‹‹እህ …›› ብለው ጉዳዩን ለመከታተል እንዲገደዱ እየተደረገ ነው። በአንጻሩ ‹‹ቴዎድሮሳውያን›› ነን የሚሉ ሰዎች በተለያየ መንገድ ራሳቸውን እያደራጁ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጭንቅና ችግር ስም ሰዎችን በማሰባሰብ ሲያወናብዱ እየታየ ነው።የእነዚህ ሰዎች እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ አገልግሎት ላይ በርካታ ፈተናዎች ሊደቅን እንደሚችልም ጠቋሚ ነገሮች አሉ።

አንደኛው ምእመናን በእነዚህ ሰዎች እንቅስቃሴ እየተደናበሩ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ታርቀው በንስሓ ሕይወታቸውን እየመሩ የክርስቶስን ምጽአት መጠበቅ ሲገባቸው በዝንጋዔ ተውጠው የኢየሱስ ክርስቶስን ሰማያዊ መንግሥት እንዲረሱ እያደረጉ ነው።ሁለተኛው  የሚባለው ንግር ተፈጽሞ ይሁን በመፈጸም ላይ ይሁን ገና የሚጠበቅ ይሁን እርግጠኛ ሊሆን በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ትንቢቱን በግድ በጉልበት ፍጻሜ ለመስጠት ሰዎችን ወደማይገባ ተስፋ በማስገባት ማደንዘዙ ነው።ይህ ደግሞ የሚነገረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በመሆኑና የሐሳቡ ተከታዮች እንዲሰባሰቡና እንዲደራጁ የሚፈለገው በገዳማትና አድባራት አካባቢ በመሆኑ ተከታዮቹ በሚደርስባቸው ኪሳራ ሁሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲያዝኑና በክርስትና እምነት ተስፋ እንዲቆርጡ ሊያርግ የሚችል በመሆኑ ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን የማስወጣት ስልታዊ እንቅስቃሴ ሆኖ ይታያል።በሦስተኛ ደረጃ በርካቶች ቤተሰቦቻቸውን እየበተኑና እያወኩ በፍርሃት፣ በጭንቀት፣ በአጉል ተስፋ፣ ወዘተ ስለተያዙ ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ ነው።

በአራተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን ንጉሥ ለማንገሥ አሁንም የምታስብና የምትሠራ አድርገው በማሳሰብ በፖለቲካው ዓለም ያሉ ሰዎች ተቋማዊ አገልግሎቷን እንዲጠራጠሩ እያደረገ ነው።እነዚህ ሁኔታዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከጊዜ ጊዜ በዘርፈ ብዙ ወጥመዶች እየተያዘ መሔዱን ያመለክታል።ለዚህ እንቅስቃሴ በስውርና በግልጽ የሚተባበሩ ምእመናንና ልዩ ልዩ ሰዎች ወዘተ መኖር ደግሞ ነገሩን የሚያስተዛዝብ ያደርገዋል።ይህ እንቅስቃሴ ፍጻሜው ቤተ ክርስቲያንን መከፋፈል አገልግሎቷን ማስናቅ የአገልግሎቱን ዓላማም ማዛባት ያስከትላል፤ በመሆኑም ሳይቃጠል በቅጠል የሚስብል ነው።

የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳር የነገሩን ሥር በውል ማጥናት ለዚህ የሚጋብዙ ትውፊታዊ መልእክቶችን እንዴት ሊተረጎሙና ሊያዙ እንደሚገባቸው ማስተማር ያስፈልጋል።ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በሚነገሩ ትንቢቶችና በሚኖሩ ተስፋዎች ስም የሚደናበሩ፣ ውዥንብር የሚነዙና ሥራ ፈት ሆነው የትንቢት ፍጻሜ የሚናፍቁ ሰዎች ነበሩ።እነዚህን ወገኖች ሐዋርያት በተለያየ ቃል ሲገሥጹና ሲመክሩ ነበር።

 

ቅዱስ ጳውሎስ የምጽአት ናፋቂዎችን ‹‹የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክሕደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ ፥ አይደርስምና።››  (፪ኛ ተሰ ፪ ፥ ፪-፫) ብሏቸው ነበር።ትንቢትን በራሳቸው ማስተዋልና ግምት እየተረጎሙ እንዳይታወኩ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።›› (፪ና ጴጥ ፩፥፳) በማለት መክሯል።ስለዚህ በየዋህነት ‹‹ቴዎድሮሳውያንን›› ነን የሚሉትን ሰዎች መንገድ የሚከተሉትን መምከር ማስተማር ያስፈልጋል።

በሌላም በኩል ያለፈቃድ በገዳማትና አድባራት አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ካሉ ማጽዳትና በሕግ ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል።ንግሥና ፖለቲካዊ አንድምታም ያለው በመሆኑ የዚህ ህልም ባለቤቶች የሀገሪቱ ሕግና የፖለቲካ ሥርዓት በሚፈቅደው መንገድ መስተናገድ እንጂ የቤተ ክርስቲያን መዋቅርን መታገጊያ እንዳያደርጉ በሕግ መከላከል ያስፈልጋል።ይህ ጥረት በአስተዳዳሩ በኩል በግልጽ መታየት ካልቻለ ነገሩ በተለያዩ አካላት ፊት ትዝብት ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑ ‹‹ቴዎድሮሳውያን››ን አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል።

የሀገራችን የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ባህል በንጉሥ የመመራት ባህል በመሆኑ ነገሥታቱም የሚቀቡት በቤተ ክርስቲያን ስለነበር የሚጨቁን ንጉሥን እንዲያስታግሥ በጸሎት መጠየቅ እንዳለ ሁሉ ቅን መሪ እንዲሰጥም ይጸለያል።ይሄንን ማድረግ አያስከፋም።ነገር ግን ክርስቲያን ማኅበረሰቡን ጨው ግዙ፣ በርበሬ ቀንጥሱ፣ ጤፍ ሸምቱ… ወዘተ እያሉ ማሸበራቸው ሳያንስ ያሉት ነገር በሰፈሩት በቆረጡት ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ባልተፈጸመ ቊጥር የበርካቶችን አእምሮ ይጎዳሉ፤ ከሃይማኖታዊ ሕይወታቸው ያሰናክላሉ። ካልሆነም ደግሞ ማስተባበያና ማጽናኛ መልእክቶችን በማስተላለፍ ተከታዮቻቸውን የሁልጊዜም እስረኛ የማድረግ ምኞት አላቸው።በታመመች ሀገር ላይ ቁስልና ጥዝጣዜ እየጨመሩ መቀጠል ይፈልጋሉ።የተልእኳቸው ፍጻሜ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዳይጎዳ ንቁ ክርስቲያኖች የእነዚህን ሕልመኞች እንቅስቃሴ ከቤተ ክርስቲያን ማውጣት ይጠበቅባቸዋል።

Read 569 times