Saturday, 15 May 2021 00:00

አገልጋይ ሆይ! ስንት ቋንቋ ታውቃለህ?

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
ክርስትና ለመላው ዓለም ሕዝብ መንፈሳዊ ነጻነት እንዲሰጥ የተሰጠን የእውነት መንገድ መሆኑን አብ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ በገለጠው ፍቅር የታወቀ ነው። በዚህም መሠረት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ፣ መልእክተኛ አድርጎ የመረጣቸውን ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።›› (ማቴ. ፳፰፥ ፲፱) በማለት አዟቸዋል።  የዓለም ሕዝቦች ደግሞ ልዩ ልዩ ቋንቋና ባህል ያላቸው በብዙ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው። እንኳን በዓለም በአንድ ሀገር እንኳን ብዙ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ማኅበረሰቦች ይኖራሉ። ለዚህም ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ምሳሌ ነች። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ለእነዚህ ብዙ ሕዝቦች መድረስ ስላለበት አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የዓለም ሕዝቦችን ቋንቋ ገልጦላቸዋል። በኢየሩሳሌም የነበሩ ከተለያዩ ግዛቶች የመጡ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦‹‹ እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?›› (የሐዋ. ፪፥ ፮—፯) ይህ የሚያመለክተው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የወንጌል መልእክተኞች ለሁሉም የተላኩና የሁሉም አገልጋይ ስለሆኑ የሚያገልግሏቸውን የየሀገሩን ሕዝቦችና የሀገራቸውን የተለያዩ ማኅበረሰቦች ቋንቋና ባህል ማወቅ እንደሚገባቸው ነው። የጥንት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አብዛኞቹ ከአንድ በላይ ቋንቋ የሚያውቁና በሚያውቁትም ቋንቋ በቃል በማስተማር፣ መጻሕፍትን በመጻፍ፤ መጻሕፍትን በመተርጎም በርካታ አገልግሎት ሰጥተዋል።  በኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክም እነ ቅዱስ ፍሬምናጦስ ግዕዝን ጽርዕን ሱርስትን በማወቃቸው ወደ ግእዝ ተርጉመው ለማስተማር፣ ሥርዓትን በውል ለመሥራት የአብያተ ክርስቲያናትን ግንኙነት ለማጠናከር አውለውታል። አባ ሰላማ መተርጉምም ስሙን የተላበሰበትን ድንቅ ሥራ የሠራው ከአረብኛ በርካታ መጻሕፍትን በመተርጎሙ ነበር። እጨጌ ዕንባቆም ከአረብኛ ግእዝን በማወቃቸው መጻሕፍትን ለማስተማሪያነት ጽፈዋል። እነዚህና መሰል ምስጉን ሰዎች እውነተኛ አገልጋዮችና የፍቅር ሰዎች በመሆናቸው ለብዙ ወገኖች የሚጠቅሙ ትምህርቶችን በተሰጣቸው የቋንቋ ጸጋና ክህሎት ሰጥተዋል። በአሁን ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቋንቋ ጉዳይ መነጋገሪያና መጨቃጨቂያ ሆኖ ሲታይባት ነገሩን በትዝብት የሚያዩ ቁጥራቸው ቀላል አይሆንም። ቤተ ክርስቲያን በውጪ ሀገር ለሚኖሩ በርካታ አፍሪካውያንንና በሌላም አህጉር ለሚኖሩ አገልግሎቷን ለሚፈልጉ ወገኖች አገልግሎት በስፋት መስጠት ነበረባት። ቤተ ክርስቲያን እኅትነቷን ከሚፈልጉ አኃት አብያተ ክርስቲያናትና ጥንታውያን የኦርቶዶክስነት መሠረት ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር ኢኪዩሜኒዝም ወይም ዓለም ዓቀፋዊ ግንኙነትን ማጠናከር ይጠበቅባት ነበር። የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪኳን አስተምህሮዋን ትውፊቷን ልዩ ልዩ የሃይማኖት ሥርዓቶቿን ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማስተዋወቅ፣ ላላመኑት መንገር ማሳመን ነበረባት። ቤተ ክርስቲያን ከውጪ ያልተተረጎሙ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ የምእመናንን ሕይወት የሚያንጹ፣ በሃይማኖት የሚያጸኑ መጻሕፍትን ተርጉማ ማቅረብ ነበረባት።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጪ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥም ላሉ ላመኑና ለላመኑ ማኅበረሰቦች በየቋንቋቸው አግልግሎት መስጠት፣ መገልገያ መጻሕፍትን በየቋንቋቸው ተርጉማ ማቅረብ ነበረባት።  እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ግን እስከ አሁን ድረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ የቋንቋዎች ማሰልጠኛ ተቋም የለም። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ቋንቋና ባህሎች የሚጠኑበት ተቋም የለም። ይህ ባለመኖሩ ደግሞ አገልጋይ ደቀ መዛሙርት ከአንድ በላይ ሁለት ሦስት ቋንቋዎችን በማወቅ በበቂ ሁኔታ በዓለምና በሀገር ውስጥ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ተዘዋውረው ማስተማር፣ መጻሐፍትን ጽፈው ማቅረብ አልቻሉም። ቤተ ክርስቲያን በቅርሶቿ ኢትዮጵያን እንደምታኮራ ሁሉ የብዙ ቋንቋዎች ባለቤት ሆና እንደ መጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን የብዙ ቋንቋና ባህል ማኅደር ሆና መቀጠል አልቻለችም።   ቤተ ክርስቲያን ግዕዝና አማርኛን በማሳደግና በማስፋፋት ሚና እንዳላት ሁሉ አሁንም በርካታ የውጪና የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በማስፋፋት ዓለም ዓቀፋዊት ባሕርይዋን ተላብሳ መገኘት ግዴታዋ ነው፡ በተለይ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ቢያንስ አረብኛ ቋንቋን ሱርስትን የሚያውቁ በርከት ያሉ ሊቃውንት ሊኖሯት ይገባል። የጥንት ኦርቶዶክሳውያንን መጻሕፍት ለመመርመርና ታሪካቸውን ለማጥናት የግሪክና የራሺያኛ ቋንቋ የሚያውቁ በርካታ ሊቃውንት ሊኖሯት ይገባል።  ስብከተ ወንጌልን ለዓለም ለማድረስና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማንነት ለዓለም ለመግለጥ ደግሞ ቢያንስ የእንግሊዝኛና፣ የፈርንሳይኛ ቋንቋዎችን ያጠኑ አገልጋዮች በስፋት መበራከት ይኖርባቸው ነበር። በሀገር ውስጥ ቋንቋዎቹን የሚናገሩ አማኝ ክርስቲያኖች በርካታ ቢኖሩም አገልጋዮች ግን ከግእዝና አማርኛ በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ሁለትም ሦስትም ደርበው በመያዝ ሐዋርያዊ ወግ መላበስ ነበረባቸው።   አሁን በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያን ያሏት አግልጋዮች ቢኖሩ እንኳን ጥቂቶችና በራሳቸው ጥረት አቅም የፈጠሩ፣ ጸጋን የተላበሱ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ግን ይህን አገልግሎት ተቋማዊ አድርጋ በመያዝ በትኩረት ልትሠራበት ይገባል። በመንፈሳዊ ኮሌጆችና የካህናት ማሠልጠኛዎች ቋንቋ ትምህርት ማጥናትና ማበልጸጊያ ክፍሎችም ኖረው በውል ሊሠራባቸው ይገባል። ይህ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ለኦርቶዶክሳዊ አገልግሎት አምባሳደሮች ከመሆን አልፈው ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ክብርና አግልግሎትም አስተዋጽኦ እስከማበርክት ይደርሳሉ። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ በቁጭት መሥራትና ከችግር መውጣት ያስፈልጋል እንላለን።
Read 561 times