ሰው የሥጋ ሞት ያለበት ቢሆንም በታላቅ ክብር የተፈጠረ መሆኑን ስለሚያውቅ ሲሞት ሥጋውን በክብር ማሳረፉ ከቀደመ ዘመን ጀምሮ ያለ ነው። የሰው ሥጋ እንደ እንስሳት በከንቱ አይጣልም። አጽመ ቅዱሳን አውሬ እንዲበላው፣ እንዲጣል፣ እንዲረጋገጥ፣ እንዲናቅ፣ እንዲገፋ አይደረግም። እግዚአብሔርን የሚያምኑ ሰዎች የሰውን ክብር ስለሚያውቁ ሰው ሲሞት ለጊዜው ከእነርሱ ስለመለየቱ አዝነው አልቅሰው በክብር ይቀብሩታል። እግዚአብሔርን በማመን ጸንተው የነበሩ እስራኤላውያንና የቀደሙ አባቶቻቸው በዚሁ መንፈስ ወገኖቻቸውን በክብር ይቀብሩ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ፩ኛ ነገሥት ፲፫፥፴፬።
አብርሃም ሚስቱ ሣራ በሞተች ጊዜ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሥቷል። ከዚያም በኋላ ለኬጢ ልጆች ሚስቱን በክብር የሚያሳርፍበት የቀብር ቦታ በጠየቃቸው ጊዜ እንደ ምኞቱ እንዲሆንለት ‹‹ጌታ ሆይ ስማን አንተ በእኛ መካከል ከእግዚአብሔር ንጉሥ ነህና ከመቃብር ሥፍራችን በመልካም ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ›› ዘፍ ፳፫፥፮ ብለውት ነበር። ከዚያም በኬብሮን ድርብ ስፍራ ያላትን የዋሻ ውስጥ መቃብር መርጦ በዋጋም ገዝቶ ሣራን በዚያ ቀበራት። ያም ሥፍራ የቤተሰቡ ሁሉ መቃብር ሆኖ ያገለግል ነበር። ዘፍ ፳፫፥፲፮-፳ ።
ሰዎች የሞተን ሰው ካላቸው ፍቅርና ከሚገባው ክብር የተነሳ በልዩ ልዩ መንገድ ይቀብሩ፣ ሬሳውንም ያከብሩ ነበር። ሰዎች የሰውን ሬሳ ያጥቡ ነበር።(የሐዋ ፱፥ ፴፯) ቅባት ይቀቡት ነበር፤ ቅመም ጨምረው በልብስ ይከፍኑታል። በመግነዝ ይገንዙታል፤ ፊቱን በጨርቅ ይሸፍኑታል፤ (ማር ፲፮፥ ፩፤ ዮሐ ፲፱፥ ፵) በየዘመኑ ክብር ነው በሚሉት መንገድ ይቀብሩ ነበር። ሰውን ከዓለት በተወቀረ ድንጋይ ውስጥ ይቀብሩ ነበር። (ማቴ ፳፯፥ ፷) በኖራ በተቀባ ድንጋይም ይቀብሩ ነበር። መቃብሮቻቸውም ያስጌጡ ነበር። (ማቴ ፳፫፥ ፳፯) ሳያውቅ ካልሆነ በስተቀር በሰዎች መቃብር ላይም ሰው አይረማመድም (ሉቃ ፲፩፥ ፵፬)።
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ተስፋ ትንሣኤን ስላገኘን ለክርስቲያኖች ለሟች የሚደረግ ሐዘንና ለቀብር የሚሰጠው አስተያየት ከክርስትና አስተምህሮ የመነጨ ነው። ሞትን ማድነቅ በክርስትና አይፈቀድም። ሞት የተሸነፈ፤ ሥልጣኑንም ያጣ ስለሆነ የሞተን ሰው ከልክ በላይ በማዘን አንሸኝም። የእርሱ ክብሩ መቃብሩ እንደሆነ በማሰብ ቀብርን አናደምቅም። ክርስትና ትኩረቱ ለሟች በሚደረግ ጸሎተ ፍትሐት ላይ ነው። እግዚአብሔር በክብር ነፍሱን እንዲቀበላት የሚደረገው ተማጽኖ ላይ ነው። በየጊዜውም የሙቱን ስመ ክርስትና እየጠራን በመታሰቢያው ቀን ስለምናደርገው ጸሎት ነው። ቀብር ስንፈጽምም ስናዝንም ሐዋርያው ‹‹ወንድሞች ሆይ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ አንቀላፍተውም ስላሉት ታውቁ ዘንድ እንወዳለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሞተና እንደተነሣ ካመንን እንዲሁ በኢየሱስ ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋል።›› ያለውን ቃል አንረሳም። /፩ኛ ተሰ ፬፥፲፫/።
አሁን አሁን ግን በቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ የሚታዩ አንዳንድ ሁኔታዎች አማንያን በሞት ላይ ያላቸው አመለካከት እየተደበላለቀ መምጣቱን ይጠቁማል። በአንድ በኩል የተጋነነ ሥርዓተ ቀብር ይታያል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ነገሩ የሆነ ሥርዓተ ቀብር ይታያል። በክርስቲያን ሟቾች መካከል በሚደረግላቸው የተጋነነ ሥርዓተ ቀብር ወይም የፍትሐት ሥነ ሥርዓት ልዩነት እየታየ መምጣቱ ያልተገራ አስተሳሳብ የመኖሩ ማሳያ ነው።
የሞተው ሰው ከሞተ በኋላ ሌላ የሚከብርበት ትንሣኤ እንደሌለው በሚያስመስል ሁኔታ ባለ በሌለ ኃይል ቀብሩን ማድመቅና ከፍ ከፍ ማድረግ ጎልቶ ይታያል። ለቀብርም ከፍተኛ ወጪዎችን ማውጣት የተለመደ ሆኗል። ሬሳ የሚቀበርበት ሳጥን የሚዘጋጅበት መንገድም ሆነ የሚቀርበት ዋጋ ሟቹን ከሞት ይመልሰው ይመስል በእጅጉ ውድ እየሆነ ነው። ድሆች የሚቀበሩበትን ሳጥን በአቅማቸው ማግኘት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ለቀብር አስፈጻሚዎች፣ ለቀብር ማድመቂያና ማክበሪያ ለሚዘጋጁ አበባ ጉንጉኖች፣ የቀብር ሥነ ሥርዓትን እንደ ሠርግ ቀርጸው ቪዲዮ የሚያዘጋጁበት ወዘተ ነገሮች ሲታዩ ቀብርን ማድመቅና ለሐዘን መደገስ ተበራክቷል።
በሌላ በኩል ችግረኞች ቀብር ዕዳ እየሆነባቸው ነው። መቀበሪያ ሳጥን፣ ለሐዘን የሚቀመጡበት የሚጽናኑበት በቂ ስፍራ፣ እንግዶችን የሚያስተናግዱበት እህል ውሃ በማጣት በሰቀቀን ሬሳቸውን የሚቀብሩ እጅግ ብዙ ናቸው። የተቀማጠሉ መቃብሮች ባሉበት እንዲሁ ሬሳቸውን እንኳን ከአፈር ለማገናኘት ጭንቀት ውስጥ የወደቁ ብዙ ናቸው።
የተጋነነ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተስፋ ትንሣኤን የረሳን ስለሚያስመስልና ከንቱ ውዳሴን የመናፈቅ ነገር ስለሆነ መታረም ያለበት ነው። በተቻለ መጠን እኩል መጥቶ በሚወስደን ሞት ሳንበላለጥ በሥርዓተ ቀብር ለመበላለጥ መሞከር ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። ራስን ማታለል ሆኗል። ስለዚህ ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ ቀብርን የማቀማጠልና ቀብርን የማጎስቆል ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን ማጣጣም አለመቻሉም የሚያስተዛዝብ ይሆናል። ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጫናና የልብ ስብራት የሚፈጠርባቸው ሰዎች ስላሉ መፍትሔ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። በተለይ ካህናት ሁሉንም ወገን ስለሚያገለግሉ በተቻለ መጠን ሥርዓት የያዘ፣ ከልኩ ያላለፈ ከልኩም ያልወረደ የቀብር ክዋኔ እንዲኖር ከየቤተሰቡ ጋር መምከር ይጠበቅባቸዋል። ይህ ነገር በካህናት አገልጋዮችና በምእመናንም ላይ በሚሰጡት ግምትና አንዱን ከአንዱ የሚያበላልጡበት ሁኔታ ሲፈጠር መተዛዘቦችና ትችቶች ስለሚያስከትል ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› በመቃብር ስፍራዎች፣ለሞተ ሰው በሚደረገው የፍትሐት ሥነ ሥርዓት በመሳሰሉት የሚታዩት ልዩነቶች እና የተጋነኑ ነገሮች ያስወግዱ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ልታስተምር ይገባል።