Monday, 28 June 2021 00:00

ቦታውን ያላወቀ ገበያ

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
ቤተ ክርስቲያን በስመ እግዚአብሔር ወይም እርሱን በሚወዱና በሚያከብሩ ቅዱሳን ስም ተሠይማ በየአካባቢው ትሠራለች። በዚያም ምእመናን ተሰብስበው መንፈሳዊ አገልግሎት ያገኙባታል። የእግዚአብሔር አገልጋይ ካህናት የእግዚአብሔርን መንጋ ሰብስበው ያገለግሉባታል። ሁሉም በጋራ ይጸልዩባታል። ስለዚህም የጸሎት ቦታ ነች። የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫና ማደሪያ የሆነው የቃል ኪዳኑ ታቦትም ማደሪያ ናት። ሌሊትና ቀን ስመ እግዚአብሔር በዝማሬ ይከብርባታል። ስለዚህም የተወደደች የምስጋና ቦታ ነች። እግዚአብሔርን የሚያምኑ ሁሉ በትሕና ተገኝተው ይሰግዱባታል። ለፈጣሪያቸው ያላቸውን ታማኝነት ይገልጡባታል፤ ስለዚህም የተከበረች የአምልኮ ቦታ ነች። እንደ ሰማያውያን መላእክት ምድራውያን ካህናት ሆነው በኅብረት እግዚአብሔርን የሚያክብሩባት፣ ምሥጢራትን ሁሉ የሚፈጽሙባት፣ ሰውን ከፈጣሪው ጋር የሚያገናኙባት የአንድነት/የፍቅር/ ቦታ ነች።  በዚህ ደረጃ የምትገለጽ ቤተ ክርስቲያን በሚገባት ክብር መጠን ልትጠበቅ ይገባል። ምእመናን በመንፈሳዊ ሕይወት የሚታነጹት መንፈሳዊ ስፍራ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ሥፍራ የሚፈጸሙ ተግባራት ሁሉ ዓላማቸው መንፈሳዊ ብቻ ሊሆን ይገባል። በዝክር፣ በተዝካር፣ በሰንበቴ፣ በጽዋ ማኅበር ስም ሊበላባቸው፣ ሊጠጣባቸው ይችላል። መንፈሳዊ በዓላትን ለማክበር አስበን ነጭ ልብስ ልንለብስባቸው እንችል ይሆናል። ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቅሙ የግብርና ሥራዎችን ልንሠራባቸው እንችል ይሆናል። ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ጧፍ ዕጣን፣ ጥላ፣ ጽዕሓ፣ ልብሰ ተክህኖ ወዘተ ንዋየ ቅድሳትን ልንሸጥባቸው እንችል ይሆናል። ከዚህ ባለፈ ግን ለአንድ ሰው ወይም ለሆነ ቡድን/ማኅበር/ ለግሉ ጥቅም የሚውል ተግባር ማከናወን የማይገባ ነው። 

 

ይህንን ያስተማረን ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምስጋና ለስሙ ይሁንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በተገኘ ጊዜ ቤተ መቅደሱን የንግድ ቦታ አድርገውት አገኘ። ‹‹በመቅደስ በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ። የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው። የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ። ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድጉ አላቸው።›› እንዲል /ዮሐ ፪፥ ፲፬/። ቤተ ክርስቲያን የዚህ ጌታ ቤት ነች። ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለቤቱ እንዲህ የሚቀና ጌታ ዛሬም በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ቢመጣ ምን ያያል ብለን አስበን እናውቅ ይሆን! 

ዛሬ በእግዚአብሔር ቤት ዙሪያ የወርና የዓመት በዓላትን ምክንያት ተደርጎ የሚዘረጋውን ገበያ ያየ ሰው የጌታን ቁጣ ለመረዳት አይከብደውም። የጌታችን ትዕግሥቱን አለመረዳት፣ ወይም ቅጣቱን አለማስተዋል ግን በዚሁ የማይገባ ተግባራችን እንድንቀጥል እያደረገን ይገኛል።

ዛሬ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ወይም ዙሪያ የጨርቃ ጨርቅ ንግድ በስፋት ይካሄዳል። ዕጣኑና ሽቶው፣ እህል፣ ፍራፍሬ፣ አትክልቱ፣ የኤሌክትሮኒክስ ምርት ወዘተ ሁሉ የግብይት ቦታው በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ሆኗል። በዓላት ሲሆኑ የእንቁላልና የዶሮ ገበያው በዚያው አካበቢ ይደራል። አርቲና ቄጠማው፣ ጀበናና ስኒው ዋነኛ ተራው ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ሆኗል። 

ነጋዴዎች እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያቀርቡት ሥራው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ገቢ ስለሚሆን አይደለም። ዓላማቸው ለራሳቸው ዓላማ የሚያተርፉበት ተግባረ ሥጋ ስለሆነ ነው። ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የእምነት ተከታዮችም በንግዱ ተሳታፊ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ቅጽር አጠገብ የሚነግዱት ገዢ ስላላቸው ነው። እነዚህን ገበያዎች አስበው ለግብይት ዕቅድ ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ ብዙ ወገኖች ናቸው። 

ነገር ግን እነዚህ ግብይቶች ብዙ ጉዳት እያስከተሉ ነው። የመጀመሪያው ጉዳት የተቀደሰውን ሥፍራ ለተግባረ ሥጋ በማዋል ክብር መንፈግ ነው። በዚህም እግዚአብሔር እንዳያከብረን፣ እንዲቀጣንም ቁጣ የሚጠሩ እየሆኑ ነው። ሌላው ደግሞ በሥፍራው ለሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት አዋኪ ሁኔታዎች ሆነው ይስተዋላሉ። የንግድ ማስታወቂያዎች ትርምስ፣ የገዢና ሻጭ ጩኸት ከተሸከርካሪዎች፣ ከጃንጥላ ገልባጭ ለማኞች፣ ከባሕታውያን ነን ባይ ተናጋሪዎች ጩኸት ጋር አካባቢውን የሰላማዊት ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን የሁከትና የትርምስ ቀጠና ያደርጉታል። ስለዚህም የቤተ ክርስቲያን አባቶች በተሰጣቸው ተልእኮ መሠረት የሚሰጡት ሥርዐት ያለው አገልግሎት ተመልካችና አድማጭ አያገኝም። በቦታው በጸሎት ለመትጋት በምስጋና ለመመሰጥ ለሚፈልጉ ሁሉ ምቹ ሁኔታን አይፈጥርም።

ሌላው ከባድ ጉዳት ግን ምእመናን ከቤታቸው የሚወጡበትን ዓላማ የሚያዛባ፣ የሚሻማ፣ ልባቸውን የሚከፍል፣ ፍቅራቸውን የሚያጎድል ሆኖ መገኘቱ ነው። አንድ ምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመጣ የሚገባው እግዚአብሔርን ብቻ ፈልጎ መሆን ሲገባው ሽንኩርት እገዛለሁ፣ እህል እሸምታለሁ….ወዘተ በሚል ደባል ዕቅድ ይዞ የሚመጣ ከሆነ አምልኮታችን ሙሉ አይሆንም።

በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሊገዙ የሚገባቸው ነገሮች ለቤተ ክርስቲያን መባእ ሆነው የሚገቡ ንዋያትን፣ ነፍሳቸውን ሊያንጹ የሚችሉ የጸሎት፣ የትምህርት መጻሕፍትን ብቻ ነው። ከዚህ ባሻገር የሚዘረጉ ሕገ ወጥ ገበያዎች ግን ለቦታው ቅድስና የማይመጥኑ ናቸው። ግለሰቦች ከሚያደርሱት ጥፋት አልፎ ግን ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም በቅጽሯ አካባቢ የምትሠራቸውን ሕንጻዎች ለዚህ ዓይነት የሥጋ ገበያ እያዋለቻቸው በመሆኑ ነገሩን ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል። 

ነጋዴው ቦታውን ረስቶ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ደጅ አፍ ደርሷል። ይህን ጉዳይ ደግሞ የሚታዘቡት ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ናቸው። ንግዱ መንፈሳዊንም ሥጋዊ ሕግንም ጥሶ የሚካሄድ በመሆኑ ውሎ አድሮ ቀውስ የሚወልድ ለቤተ ክርስቲያን አካባቢም ሰላም መጥፋት ምክንያት ወደሚሆንበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል።

ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳር በየአጥቢያው ያለውን ሁኔታ መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ይገባዋል። በየአጥቢያው ቅጽር የሚሠሩ ሕንጻዎችን ለንዋየ ቅድሳት ማምረቻ መሸጫ ማከፋፈያ ከማድረግ ጀምሮ ሌሎች አካላት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ በወርና በዓመት በዓላት አስታከው የሚያደርጉትን ሕገ ወጥ ገበያ ሥርዓት ማስያዝ ይጠበቅበታል። የሥጋን ገበያ ወደ ተራው፣ ወደ ጣቢያው መመለስ ይገባል። ይህን ለማድረግ መነሻ የሚሆነው የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው። ለቤቱ መቅናት ለልጆቹ የሚገባ ነውና። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ትዝብት ላይ የሚጥል በኋላም ቅጣት የሚያስከትል ይሆናል እንላለን።   

 

Read 975 times