Wednesday, 24 March 2021 00:00

የዘረኝነት ኑፋቄ

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ

Overview

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአሜሪካና በአውሮፓ አንዳንድ በክርስትና ስም የተደራጁ አካላት ክርስትናውን በቆዳ ቀለም ለይተው የጥቁርና የነጭ ቤተ ክርስቲያን ወደሚል ፀረ ክርስትና አደረጃጀት መፍጠር እንደ ጀመሩ ይነገር ነበር። ለስሙ ምስጋና ይሁንና ‹‹ኢየሱስ›› በሚለው ስም በመጠቀምም ‹‹ጥቁሩ ኢየሱስ፣ ነጩ ኢየሱስ›› ወደሚል የጽርፈት ተግባር ውስጥ ገብተዋል።  እነዚህ ወገኖች ‹አንድ አስተምህሮ አለን› እያሉ በዘረኝነት ምክንያት ግን እምነታቸውን መክፈላቸው ያነጋግር ነበር። በአንድ ቋንቋ መሰብሰብ እየቻሉም በዘረኝነት ምክንያት ግን አንድ ስብስብ መፍጠር አለመቻላቸው ጉድ አስብሏል። በዚህ ተገርመን ሳናበቃ በአህጉራችንና በሀገራችን ክርስትናን በጎሳና በነገድ የሚያይ ወገን ማቆጥቆጥ ጀመረ። የጥቃቱም ዒላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሆነች።  ቤተ ክርስቲያን በነበራት ታሪክ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድን አልፋ ለሰይጣን የጥፋት ዘር ሳትንበረከክ እዚህ ደርሳለች። በጎጥ ከፋፍለው ጸጋ፣ ቅባት፣ ተዋሕዶ በሚል የነበረውን መለያየት በሊቃውንቷ ጉባኤዎች መትፍሔ ሰጥታ ቤተሰቧን ሁሉ በአንድ ማኅበር አጽንታ ቆይታለች። ለቤተ ክርስቲያን የማይተኛው ሰይጣን ግን አሁን ደግሞ ‹‹የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የእገሌ ጎሳ እምነት እንጂ የእኛ አይደለም›› በሚል መንጋዋን ከቤቱ ለማስበርገግ ሲሠራ ቆይቷል። ብዙዎችም በዚህ አካሔድ ተሰናክለዋል። ኦርቶዶክሳዊ እምነትን በአስተምህሮው ሳይሆን የእነእገሌ እምነት ነው በሚል የጎሰኝት አመለካከት የተለዩት ብዙ ናቸው።  እነዚህ ወገኖች ዓለምአቀፋዊት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የአንድ ነገድ ብቻ እንደሆነ፣ ለብዙ ዘመናት የኖረችውን ቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ‹እገሌ የሚባለው ንጉሥ እምነት› በማለት ሲቀሰቀሱ ይታያል። ቢጠይቋት መልስ የማታጣ ስትሆንባቸው፣ ሊቃውንቷን ሊከፋፍሉ ሲሞክሩ ጉባኤዋን መበተን ሲሳናቸው ይህንን የሰነፍ መንገድ ለመጠቀም ተገደዋል። የመናፍቃኑን የሰነፍ ቅሰጣ ተመልክተን ሳናበቃ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተ ክርስቲያን በነገድና በጎሳ እንድትደራጅ፣ ከተቻለም እንድትበጣጠስ የሚደረግ ቅስቀሳ እየታየ ነው። ያለውን ፖለቲካዊ ሥርዓት የሚቀየሙና ለፖለቲካዊ ትርፍ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ አሁንም ከቤተ ክርስቲያን ራስ ላይ መውረድ ያለመቻላቸውም ማሳያ ነው። የፖለቲካ ግብግቡን በሌላ ሜዳ ማድረግ ሲሳናቸው በዘረኝት ኑፋቄያቸው ቤተ ክርስቲያንን ሊያውኳት እየሞከሩ ነው። አንዲትን ቤተ ክርስቲያን በአንድ ሀገር ውስጥ ብዙ ሊያደርጓት ይፈልጋሉ። ይህ የሚያስደስተው ማንን ነው? የሚሠሩትስ ለማን ነው? ለሰይጣን አይደለምን?። ይህ ኑፋቄን ለመቀፍቀፍ የሚመች ብቻ ሳይሆን በራሱ ኑፋቄ አይደለምን? የዘር ጥራትን፣ ቋንቋን፣ መሠረት ያደረገ ማግለል፣ እንዴት ክርስቲያናዊ መንገድ ሊሆን ይችላል? በአንድ ክርስቶስ ወንድማማች ሆነው የኖሩ፣ በአንድ የቁርባን ማዕድ የሚታደሙ ወንድማማቾች መለያየትና አንዱን ለሌላው እንግዳ ማድረግ በክርስትና እንዴት ተቀባይነት ይኖረዋል? ‹በእኛ ዘር ቄስ ብቻ፣ በእኛ ዘር ዲያቆን ብቻ ይገልገል› የሚል ጉባኤ ቢፈጠርስ ይህ የዘር ቤተ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ መልኩን እንዴት ያገኛል? በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዎች አብያተ ክርስቲያናት ሲመሠረቱ በአንድ ከተማ በአንድ አካባቢ የሚቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉንም በከተማው ወይም በአካባቢው ያሉ የእምነቱን ተከታዮች ያስተናግዳሉ፣ ያቅፋሉ እንጂ የአንድ በቁጥር የበለጠ ወይም ያነሰ ዘር ቤተ ክርስቲያን ሆነው አልተደራጁም። ስማቸው በከተማው ወይም በአካባቢው የኤፌሶን፣ የአንጾኪያ፣ የኢየሩሳሌም የትያጥሮን፣ የሰርምኔስ ወዘተ ይባላል እንጂ የአይሁድ፣ የግሪክ፣ የሮማዊ እየተባሉ አልተለያዩም። እግዚአብሔር በሚሰጠው ጸጋ ሁሉ አንድነታቸውን ይጠብቃሉ እንጂ ሰበብ እየፈለጉ አይበጣጠሱም።  የሮማው ንጉሥ ጭካኔ ሮማዊ ዜግነት ወይም ትውልድ የሌላቸውን ሁሉ እንደ እንግዳ እንዲያዩ አላደረገም። የግሪክ ሰዎች መመካት ግሪክ ቋንቋ ተናጋሪ ያልሆኑትን ክርስቲያኖችን ተለይታችሁ የራሳችሁ ቤተ ክርስቲያን ፍጠሩ አላስባላቸውም። የአይሁድ ክርስቲያኖች ንቀት ሌሎች የአሕዛብ ወገን ክርስቲያኖች ለብቻቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲያቋቁሙ አላደረጋቸውም።   በኢየሩሳሌም የነበረችው ቤተ ክርስቲያን በዋናነት ከአይሁድ ወገን የነበሩ ክርስቲያኖችን አብዝቶ ይቀፍ እንጂ ገና ከምሥረታው ጀምሮ ከልዩ ልዩ ሀገር/ነገድ/ የመጡ ክርስቲያኖችም አብረው ያመልኩ ነበር። የሮም ቤተ ክርስቲያን በአመዛኙ ከአሕዛብ ወገን የነበሩ ክርስያኖችን ይቀፍ እንጂ በርካታ ከአይሁድ ወገን የነበሩ ክርስቲያኖችም ነበሩበት። ታዲያ በእኛ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች የዚህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ወይም ትውልድ ነን ካልን የአሁኑን የጎሳ ቤተ ክርስቲያን ምሥረታ ከየት አመጣነው? ይህ የሰይጣን ሐሳብ የዓለማውያን መንገድ ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚጭኑ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን ያናጋልና ኑፋቄ ነው። ሊወገዝ የሚገባው የዘረኝነት ኑፋቄ እንደሆነ ታዝቤያለሁ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች የቅዱሳን ሐዋርያትን ማሳሰቢያ መልእክቶች ደጋግመው ማንበብ አለባቸው። ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፣ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።››(፩ ቆሮ ፩፥፲) ያለው መልእክቱን ያስተውሉ እላለሁ።
Read 536 times