Wednesday, 28 April 2021 00:00

የቅዱሳት ሥዕላት ክብር ከየት ወደ የት?

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ

Overview

ቅዱሳት ሥዕላት በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ አላቸው። የሥላሴዎች፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢሱስ ክርስቶስ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የቅዱሳን መላእክት፣ የቅዱሳን ሰማዕታት ሥነ ሥዕል መሣል ብሎም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማድረግ እና ለጸሎት እና ለትምህርት መጠቀም የተለመደ ነው። አብያተ ክርስቲያናቱንም ሆነ ገዳማቱን ካለ ቅዱሳት ሥዕላት ማስብ አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቻችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ በቅዱሳት ሥዕላቱ ፊት በመቆም፣ በመንበርከክ እንዲሁም በመስገድ ጸሎት እናደርሳለን፣ ሰላምታ እናቀርባለን ፣ ምልጃ እንጠይቃለን። በቤታችንም ለቅዱሳት ሥዕላት የተለየ ቦታ አዘጋጅተን በክብር በማስቀመጥ ለጸሎት አገልግሎት እንጠቀምባቸዋለን። ቅዱሳት ሥዕላት በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤታችን ለጸሎት የምንጠቀመው ዝም ብለን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትመጣውን አብነት አድርገን ነው። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን የኪሩብን ሥዕል በሥርየት መከደኛው ላይ እንዲያዘጋጅ፣ በዚያም ላይ ተገልጦ እንደሚያነጋግረው ነግሮታል (ዘጸ ፳፭፥፲፰—፳፪።) በሐዲስ ኪዳንም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ‹‹ምስለ ፍቁር ወልዳ ›› ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ሥሏታል። ቅዱስ ኤፍሬም በእሑድ ውዳሴ ማርያም ላይ ‹‹በእግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ አንቺ ነሽ›› በማለት በብሉይ ኪዳን በእግዚአብሔር አዛዥነት በሙሴ ሠሪነት የተከናወነውን የሥነ ሥዕል ምንነት ያጠናክርልናል።

 

እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትመጣ ያላቸው የአምልኮ መግለጫ፣ ነገረ ድኅነትንም ሆነ ነገረ ቅዱሳንን የምንማርባቸው ቅዱሳት ሥዕላት ቤተ ክርስቲያን ከሰጠቻቸው የክብር ቦታ ወርደው ለጸሎት፣ ለአምልኮ፣ ለትምህርት መዋላቸው ከቁብ ሳይቆጠር እንደ አልባሌ እና ተራ ነገር ማየት የተለመደ ሆኗል። በቤተ ክርስቲያን ሳይቀር በቅጽረ ግቢው አንዳንድ ቦታ ላይ ተጥለው፣ ተቀዳደው የሚታዩበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። እዚያ ቤተ መቅደስ ውስጥ የምንሳለምውን፣ የምንሰግድለትን፣ ሥዕለ ቅዱሳን ውጪ ላይ ሲረገጥ ማየት በአእምሮ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም።

ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ብዙም ሳንርቅ በጎዳና ላይ እንዳልባሌ ዕቃ ተሰጥተው የምናያቸው ቅዱሳት ሥዕላት ቁጥር ቀላል አይደሉም። ከሌሎች ተራና ዓለማዊ ሸቀጣ ሸቀጦች ጋር ተደባልቀው ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባቸው አቧራ እየጠጡ መንገድ ላይ የሚሸጡት ቅዱሳት ሥዕላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብር ሰጥታ ለአምልኮ የምትጠቀምባቸው የአምልኮ መገለጫዎቿ መሆናቸውን ስንቶቻችን እንገነዘብ ይሆን?  ምእመኑም እንደ ተራ እቃ ከመንገድ ላይ እየገዛ ሲጠቀምባቸው እውነት ያላቸውን ክብር እያሰበ ነው ወይ? ለማለት ያስቸግራል። ምክንያቱም በክብር ያልተያዙ ቅዱሳት ሥዕላቱን እንዴትስ አክብሮ ሊጸልይባቸው፣ ሊሰግድላቸው ይችላል? ነገሩ ዘልማድ ነው የሚመስለው።

ወደ ቤትም ከደረሱ በኋላ በእያንዳንዱ ምእመናን ቤት የሚኖራቸው የክብር ሥፍራ ሌላው አስተዛዛቢ ጉዳይ ነው። ቅዱሳት ሥዕላቱ አንዳንዱ ቤት እንደማንኛውም ዓለማዊ ሥዕል ቦታ ሳይመረጥላቸው ይሰቀላሉ ፣ የጸሎት ሳይሆን የቤት ማድመቂያም ነው የሚመስሉት። ከተሣሉበት ዓላማ ጋር የማይገናኝ አገልግሎትም ነው ያላቸው። ዛሬ ዛሬ ቤት ውስጥ እንዳልባሌ ከመሰቀላቸው አልፎ በየ ቡና ቤቱ እና በየመጠጥ ቤቱ ቅዱሳት ሥዕላትን ማየት የተለመደ ሆኗል። ይህም የእያንዳንዱን ምእመን ለቅዱሳት ሥዕላት ያለውን የዕውቀት ደረጃ አናሳ መሆን የሚያሳይ ነው።

በኪስ እና በቦርሳ የሚያዙ ቅዱሳት ሥዕላት ዕጣ ፈንታም ከላይ ካነሣናቸው ገጠመኞች የተለየ አይደለም። በኪስም ሆነ በቦርሳ እንደ ተራ ነገር ከብር፣ ከተለያዩ ወረቀቶች፣ ከሴቶች የተለያዩ የመዋቢያ ዕቃዎች ጋር ተደባልቀው የሚያዙ ቅዱሳት ሥዕላት የተሣሉበትን ዓላማ ከመግለጽ ይልቅ የኪስ ወይም የቦርሳ ማድመቂያ ነው የሚመስሉት። በቤተ ክርስቲያን በክብር ተቀምጠው፣ ተሰቅለው በፍርሃት የምንሳለማቸው ቅዱሳት ሥዕላት ከተራ ወረቀት ጋር ከቦርሳና ከኪስ ተመዘው ሲወጡ እንደ ማየት የሚያሳዝን ብሎም የሚያስተዛዝብ ነገር የለም።

በቤተ ክርስቲያን ካላቸው ክብር አንሰው ከመገኘታቸውም በላይ የቅዱሳት ሥዕላቱ አሣሣል የተሣሉበትን ዓላማ የዘነጋ ነው። ቅዱሳት ሥዕላት በቤተ ክርስቲያን ሲሳሉ የራሳቸው ሕግ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት አላቸው። ሥዕላቱ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ትንሣኤን፣ ነገረ ድኅነትን፣ ነገረ ቅዱሳንን በትክክል እንዲያሳዩ ሆነው ነው የሚሣሉት። የሚሳሉበት የቀለም ዓይነት ሳይቀር የተወሰኑ፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ትርጓሜ ያላቸው ናቸው።

ዛሬ ዛሬ  በገበያ ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ሥዕላት ግን ከታሪክም ሆነ  ከዶግማ የተፋቱ ሆነው ነው የሚታዩት። እነዚህ ሥዕላት በገበያ ብቻ የተወሰኑ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ሳይቀር የሚሸጡ ናቸው። ለምሳሌ አንድ የትንሣኤ ሥዕል እንወሰድ በብዙ መልኩ ተሥሎ የምናገኘው በየቤታችንም አድርገን የምንጠቀምበት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ‹‹መቃብር ተከፍቶ ጌታችን መቃብር ውስጥ ቆሞ የሚያሳይ ነው።›› መጽሐፍ ቅዱስ ጌታችን ‹‹መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል›› ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ነው የሚነግረን (ማቴ፳፰፥፩—፮።) ይህ ሥዕል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳይቀር ተሥሎ እያየን ነው። ሌሎችም ቅዱሳት ሥዕላት በተመሳሳይ ከታሪካቸው ከእውነተኛው ገጽታቸው ጋር የተጣረሱ ናቸው።

እነዚህ ሁሉ በቅዱሳት ሥዕላት ዙሪያ ከምናያቸው ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው። የሚገርመው ዛሬም ድረስ የሚገዛውም ሆነ የሚጠቀምበት የቤተ ክርስቲያን ልጅ በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን አስተምህሮም ሆነ ክብር በማገናዘብ አይደለም። ምክንያቱም በአንድም በሌላ ችግሮቹ በሁላችንም ዘንድ ይታያሉና። ሆኖም ችግሩን ብቻ ሳይሆን ችግሩን እንዴት እናስወግድ ማለት ከእኛ ይጠበቃል። በመጀመሪያ ደረጃ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን እንደሌሎቹ ትምህርቶች ሁሉ ስለ ቅዱሳት ሥዕላት ክብር እንዲሁም በቤትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደምንገለገልባቸው ትምህርት ልትሰጥ ይገባል። የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቀው የተሳሉ ቅዱሳት ሥዕላት የትኞቹ መሆናቸውን እንዲሁም ከሌሎቹ በምን እንደሚለዩ ማሳየት ይጠበቅባታል።

ቅዱሳት ሥዕላቱን ገዝተን ለቤተ ክርስቲያን የምንሰጥም ሆነ በቤታችን የምንጠቀም ክርስቲያኖች ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያን ሥዕል መግዛት ይገባናል፤ እንዲሁም ቅዱሳት ሥዕላቱን በክብር ልንይዝ ይጠበቅብናል።

Read 1481 times