Friday, 04 September 2020 00:00

ልጅ መውለድ ባለመቻላችን  የትዳር ሕይወታችን እየተፈተነ ነው

Written by  ረቂቅ መቻል
ክፍል አንድ የተወደዳችሁ የስምዐ ጽድቅ ዝግጅት ክፍል እንደምን አላችሁ  በክርስትና ስሜ ዐምደ ሚካኤል እባላለሁ ዕድሜዬ ሠላሳዎቹ አጋማሽ ውስጥ ነው፡፡ የምኖረውም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን ላለፉት አሥራ ሁለት ዓመታት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የሚወጡ መካሪና አስተማሪ ዐምዶችን እከታተላለሁ፡፡ ምሥጢሬን ላካፍላችሁ በሚባለው  የዝግጅት ዐምድ ላይ የሚወጡ ምሥጢራዊ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ደግሞ አስተማሪና መካሪ በመሆናቸው እንደሌሎች ሰዎች ብዙ የታፈኑ ምስጢሮቼን በሆዴ ብቻ እያብሰለሰልኩ ከምቀመጥ ከእናንተ መፍትሔ አገኝበታለሁ ብዬ ስለተማመንኩ  ምሥጢሬን አካፍላችሁ ዘንድ እንዲህ ጻፍኩላችሁ ፡፡ የእኔ ታሪክና ዛሬ ድረስ ውስጤን  ሲያብሰለስለኝ የኖረው የትዳር ሕይወት ችግሬ ሲሆን ይህንንም ወደ ፊትም እንዴት አድርጌ እንደማስወግደው የሚያስጨንቀኝ ጉዳይ  ሆኗል፡፡ እኔን የገጠመኝ የትዳር ቀውስ ከባድ ነው ፡፡ የማይቻል የማይታለፍ ነገር የለም ልትሉኝ ትችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እኔ ውስጥ የሚቻል የሚመስል ግን የማይቻል ነው፡፡ የትዳር መሠረታዊ ጣዕም የሚሰጠው ጉዳይ ግን ባዶ ነበር፡፡ ባለቤቴ የሩካቤ ስጋ ችግር አለባት በዚህ ምክንያት ይሁን በሌላ ልጅ እንድንወልድ እፈልግ ነበር አልቻልንም፡፡ በዚህ ላይ  ባለቤቴ አብዝታ የምትጨነቀው ስለምንበላው፣ ስለምንጠጣው፣ ስለምናሽከረክረው መኪናና ስለምንኖርበት ዘመናዊ ቤት ብቻ ነው፡፡  ለእኔ ግን የተሟላ ሕይወት አለኝ ለማለት አልደፍርም፡፡ ዘወትር የሚያስጨንቀኝን ጉዳይ ለቤተሰቦቼና ለባልንጀሮቼ ላማክር እፈልግና ሰዎችን ምን ይሉኛል የሚለው የባህላችን ተጽዕኖዎች አንቀው ይይዙኛል ፡፡  በተለይ እኔ   ያደግኩት ማኅበረሰብ  ደፍሮ መናገር ነውር የሆነበት በመሆኑ ችግሬን ደፍሬ ልናገር አልወደድኩም፡፡ እየዋለ እያደረ የቤታችን ሰላም እየተናጋ መጣ ፡፡ በቅርብ ሰዎች ዳኝነት ስንዳኝ ነገሩ እየባሰ መጣ ሥጋችን ብቻ ሳትሆን መንፈሳችንም ተፈተነች፡፡ 

 

 የጨነቀ ዕለት እንደሚባለው ከቤተ ክርስቲያን እየተመላለስኩ ደጅ መጥናቱን ተያያዝኩት፡፡  አንድ ቀን የሰርክ ጉባኤ እየተከታተልኩ  ‹‹ የጋብቻ ሦስቱ ምሰሶዎች›› የሚል  ትምህርት ተማርኩ፡፡ ታሪኩ የእኔን ታሪክ የሚዳስስ ነበር የመሰለኝ፡፡ በተለይ ስለመተጋገዝ፣  ዘር ስለመተካትና ከዝሙት ስለመጠበቅ፡፡ ሰባኪው ሲያስተምር እያንዳንዱ ኃይለ ቃል ውስጤን ጠዘጠዘኝ፡፡ አሁንም ችግሬን አፍ አውጥቼ መናገር የከበደኝና ከሌላ ብወልድ  እያልኩ ሳስበው የነበረው ጉዳይ ከብዙ በጥቂቱ በትምህርቱ ክፍል ውስጥ ሲመለስልኝ እየሸፈተ የነበረው ልቤን ሰብሰብ አድርጌ በመንፈሳዊ መነጽር እንዳይ  ረዳኝ፡፡  ያ ማለት ግን ችግሮቻችን ተፈተዋል ማለት አይደለም ፡፡ ከቤታችን የመንፈስ ፍሬ የሆኑት ፍቅር እና ሰላም ከራቁ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡  በልጅ እጦት ምክንያት በቤታችን የሰላም ዋጋዋና የየግል ጤናችን ብሎም የእግዚአብሔር በረከት ጠፍቷል፡፡ በዓለማዊ መንገድ ያሉ የመፍትሔ  አማራጮችን  ሁሉ ሞክሪያለሁ የቀረኝ መንፈሳዊ  በመሆኑ እርዳታችሁን  ፈለግኩኝ ፡፡

ውድ ጠያቂያችን  ከጥያቄህ እንደተረዳነው በትዳር ሕይወት ልጅ አለመውለድ  በሩካቤ ሥጋ አለመጣጣምና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ  በዕውቀት አለመረዳት፣ለችግሩ መፈትሔ ከመፈለግ መዘግየት፣ ችግሩን መፍትሔ እንደሌለው አድርጎ ማሰብ፣ችግሩን ከሌላ ችግር ጋር መቀላቀል ፣ ይሉኝታና ማኅበራዊ መገለልና መፍራት  በነዚህ  ዐበይት ምክንያቶች ናቸው፡፡ 

የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮን ስናስብ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንደመሆናቸው  መጠን የሳሙኤል እናት  የሐና ጸሎት “ልቤ በእግዚአብሔር ጸና ቀንዴም በአምላኬ ከፍ ከፍ አለ” እያለች የጸለየችው ጸሎት ኃይልን እንዳደረገና የምትፈልገውን ልጅ እንዳስገኘላት እንዲሁም በ፪ኛ ነገሥት የሱናማይቷን  ሴት ችግር ተረድቶ  በነቢዩ ኤልሳዕ አማካይነት ልጅ ላጡት ልጅ የሰጠ አምላክ አሁንም ሁሉን ማድረግ የሚችል መሆኑን መረዳትና  ልብ ማድረግ ይገባል ፡፡ (፩ኛሳሙ. ፩፥፩፣ ፪ኛሳሙ )

ውድ ጠያቂያችን  ሕገ እግዚአብሔርን  ተረድተህ  ወደ ቤተ እግዚብሔር መፍትሔ  ለማግኘትና የተጨነቁትን ከጭንቀት የሚያድን አምላክ  መሆኑን አምነህ በትዳርህ ልጅ መውለድ ብችል፣ ሰላም ባገኝ ብለህ ማሰብህ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በክርስትና ለሚኖር ሰው  የኑሮ ፈተና፣ ማግኘት፣ ማጣት፣ መውደቅ፣ መነሳትና የሰላም እጦት መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡  በዚህ ጉዞ ውስጥ  ዋናው ቁም ነገር የሚያጋጠጥሙንን አሉታዊ ሁኔታዎች እንዳሉ አውቀን ችግሮችን ተቋቁመን ለማለፍ ምን ያህል ቁርጠኞች ነን የሚለው ነገር ነው፡፡ 

አንዳንድ ጊዜ ችግሮቻችን  መፍትሔ እንደሌላቸው አድርጎ ማሰብ ያጋጠመንን  ችግር ከሚገባው በላይ አክብደን ማየታችን  የመፍትሔ አማራጮችን እንዳናገኝ ያደርጋል፡፡ ብሎም  ለችግሩ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ከችግሩ ጋር መኖርን እንደ አማራጭ አድርጎ መውሰድ የብዙዎች አማራጭ ሲሆን ይታያል፡፡  አንተም ጋር ያስተዋልነው ነገር ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል፡፡ መፍትሔ የሌለው ችግር የለም ነገር ግን መፍትሔው እኛ በምንፈልገው መንገድ፣ ጊዜና ሁኔታ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡  እኛም ችግሩን መፍትሔ እንደሌለው አድርጎ ማሰብህ ከጻፍክልን ሐሳብ ለመረዳት ችለናል፡፡ ለዚህም  በትዳር ሆኖ በተራክቦ ሥጋ ልጅ ባለመውለድ ምክንያት የሚደርሱ  ጫናዎችን  እንደ ምክንያት በመውሰድ  ከተነሡት ዐበይት  ጉዳዮች በመነሣት  ለጥያቄዎቻችሁ መልስ ሊሆኑ ይችላሉ  ብለን ያመንባቸውን  ምክረ ሀሳቦች  እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ 

ውድ ጠያቂያችን እንግዲህ በሩካቤ ሥጋ መፈቃቀድ ፣ልጅ አለመውለድ፣ በትዳር መባረክ አለመባረክና ሌሎች የትዳር ደስታዎች ዕርካታ የሚመዘኑት በእግዚአብሔር እንደመሆኑ አንተ ታውቃለህ አንተ እንደወደድክ ልንል ይገባል፡፡ የልጅ ማጣትም ሆነ የሩካቤ  መስነፍ ጋብቻን ሊለያይ ወይም የቤታችንን ሰላም ሊያደፈርስ አይገባም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ሩካቤ ሥጋ በተመለከተ ሥልጣን የማን እንደሆነና በሩካቤ ምክንያትነት ከሰይጣን የሚመጣ ፈተና ሊኖር እንደሚችል በግልጽ አስተምሮናል፡፡ ከዚህም የተነሳ በፈተናው እንዳይወድቁ ሁለቱም ሚስትም ባልም በገዛ ሥጋቸው ስልጣን የላቸውምና አንዳቸው የሌላኛውን ፍቃድ ሊፈጽሙ እንደሚገባ  እንዲህ ሲል አስተምሯል ። “ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ።ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ ፤ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ።”(፩ኛቆሮ. ፯፥ ፬) 

ሰው ለኃጢአት ሥራ እግዚአብሔርን መፍራት ሰውን ማፈር ይገባው ይሆናል፡፡ ነገር ግን በትዳር ሕይወት ውስጥ ስለተፈቀደ ተራክቦ ችግር ምስጢራችንን ለሚጠብቁልን ለንስሓ አባቶቻችን   ችግራችንን ለማካፈል ይሉኝታ ሊይዘን ግን ፈጽሞ አይገባም፡፡ ምክንያቱም የንስሐ አባቶቻችን ኃላፊነታቸው እኛን ልጆቻቸውን በሚያጋጥሙን ፈተናዎች በጸሎታቸው በምክራቸው የሚራዱን ስለሆኑ ነው፡፡ ለንስሓ አባቶች ጆሮ አዲስ የሆነ፤ ያልተሰማ ነገር የለም፡፡  ወንድማችን  ችግሩ ከዚህ በፊት ያልነበረ ዛሬ በአንተና በባለቤትህ  ላይ ብቻ የተፈጠረ  መስሎህ  ያጋጠመህን ችግር በግልጽ ከመናገር ሰው ምን ይለናል ብለህ በይሉኝታ ከችግሩ ጋር  መኖራችሁ  ችግሩን ዕለት ከዕለት እንዳባባሰው ግልጽ ነው ፡፡ ልጅን በተራክቦ ሥጋ መውለድ የሰው ግብሩ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ልጅ በሰዎች አካል ውስጥ ተሰርቶ ሰው ተብሎ እንዲወለድ የማድረግ ኃይልና ስጦታው የእግዚአብሔር መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ 

አንዳንድ ሰዎች ልጅ መውለድ እየፈለጉ ሳይወልዱ ሲቀሩ  እነርሱ ሞክረው ያልተሳካ የሚመስላቸው ወይም ደግሞ በትዳር ውስጥ ሆነው በሚያደርጉት ሩካቤ ሥጋ አለመጣጣም የሚፈጠር  ነው  በማለት አንደኛው ሌላኛውን መተቸትና  ይህ የአንተ የአንቺ ችግር ነው እየተባባሉ ሲወቃቀሱ ይስተዋላል ፡፡  ከዚህ በዘለለ ስለ ሩካቤ  ምንነት አለመረዳት  በራሱ ለችግሩ   ምክንያት ነው ፡፡

ጋብቻ ቅዱስ መኝታውም ንጹሕ ነውና ስለ ሩካቤ ሥጋ በግልጽ ማውራት መመካከር የሚያሳፍር  ነውር አይደለም ፡፡ ወደ ትዳር ሕይወት ሲገባ ስለ ሩካቤ ሥጋ ምንነትና ዓላማ በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ምን ማለት እንደሆነ በጥልቀት  ማወቅ ይገባል፡፡ ባለትዳሮች ተገቢውን ዕውቀትና አመለካከት ከያዙ ሩካቤን በተመለከተ በዓለም ከሚነገሩ ያልተገቡ አመለካከቶችና አሉታዊ ተጽዕኖዎች አስቀድመው ራሳቸውን መከላከል ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ሩካቤን ሥጋ ሥርዐት ባለው መልኩ ባለትዳሮች  ስሜቶቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን ማዕከል ባደርገ ሁኔታ በመፈጸም የሚፈልጉትን ደስታን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተለየ ግን ስለ ሩካቤ ሥጋ ተገቢውን ዕውቀትና ግንዛቤ ባለመኖር  የፈተና ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡ ከፍ ብለን እንዳየነው በአንተ በወንድማችን የትዳር ሕይወት ፈተና ከሆኑ ችግሮች አንዱ ከሩካቤ ሥጋ ጋር ተያይዘው  ከሚነሱ ችግሮች መካከል የፈቃድ አለመጣጣም እንደሆነ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ 

ይሁን እንጂ የዚህን ችግር መሠረታዊ ትንታኔዎችና ማብራሪያዎች አካላዊና ሥነልቡናዊ ጫናዎቹንም ለሕክምና ለሥነ ልቡና ባለሙያዎች እንተውና በትዳር ሕይወታችሁ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመፍታት የቅድስት ቤተክርስቲያንን አስተምሮና መሠረት ያደረጉ  መንፈሳዊ ምክረ ሀሳቦችን ከዚህ እንደሚከተለው እንመልከት

‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም›› እንደሚባለው አንተም ጠያቂችን እንዳልከው  ብዙ ጊዜ ‹‹በባህል›› ተጽዕኖ የተነሳ በግልጽ ሩካቤን ሥጋ በተመለከተ መነጋገር ስላልተለመደና ብዙዎቻችን ፈቃደኝነቱም ስለሌለን  ቀላል የሆኑ ችግሮች ሳይፈቱ ይቆዩና ችግሮቹ ከክብደታቸው  በላይ እንዲጎሉ እናደርጋቸዋለን፡፡   በትዳር ሕይወት ውስጥ በሩካቤ ሥጋ አለመጣጣም መፍትሔ የሌለው ችግር ነው ወደሚል ድምዳሜ ላይ ይደረሳል፡፡ እንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሃይማኖታዊ አስተምሮውን  በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡   

 ውድ ጠያቂያችን በአርባና በሠማኒያ ቀን ተጠምቆ  ኦርቶዶክስ የሆነ ምእመን ሁሉ የክርስትና ሕይወት የሚመራው በቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምህሮ መሠረት ነው፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሰዎች ምንጩ በማይታወቅ፣በተሳሳተ ትምህርትና በዓለም ሀሳብ እየተወሰዱ በሩካቤ ሥጋ አለመጣጣም ሲያጋጥማቸው እንመለከታለን፡፡ ከዚህም የተነሳ በግል የሕይወት ፍልስፍናና የተሳሳተ ትምህርታቸው በሩካቤ ሥጋ አለመጣጣም ብሎም ልጅ ያለመውለድ  የአንድ ወገን (የባል ወይም የሚስት) ችግር አድርጎ ማየት ብሎም ችግሩን በግልጽ ለንሰሐ አባት ከመናገር በመቆጠብ ወደ አላስፈላጊ ውሳኔና ድርጊት ውስጥ ይገባሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሩካቤ አለመጣጣም ምክንያት የግልና የቤተሰብ ጸሎት ሲያስታጉሉ፣ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሔድ ሲከለክሉና ቅዱሳት መጸሐፍትን ከማንበብ ሲቆጠቡ እንመለከታለን፡፡  ታዲያ የዚህ ሁሉ መንስኤው በሰው አቅም የማይታወቅ  ሆኖ ሳለ እውነተኛውን አምላክ እያመለክን  እግዚአብሔር ሁሉን አድራጊ ቸር አምላክ መሆኑን ማመን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ 

ውድ ጠያቂያችን  በቅዱስ መጽሐፍ “አንተ ፈጣሪችን ግን ቸር፣እውነተኛ ነህ ፣ታጋሽም ነህ በምህረትህ ሁሉን ትሰራለህ”፡፡ እንደተባለው በእንደዚህ አይነት የትዳር ፈተና ውስጥ ስንወድቅ ከመቼውም በላይ  እግዚአብሔርን ብንበድልም ሁሌም የእርሱ መሆናችንን እያወቅን  አንተ እንደወደድክ እንደፍቃድህ ይሁን  ልንል ይገባል፡፡ (ጥበ. ፲፭፥፩)   ምክንያቱም እግዚአብሔር በባሕሪው ምሉዕ ነው አይሳሳትም፡፡ በምሕረቱ  ሁሉን መሥራት ይችላልና፡፡ 

 

 

 

 

 

 

Read 746 times