ውድ ጠያቂያችን ይህ አይነቱ አካሔድ የአንተ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ባለትዳሮች ሕይወት ውስጥ እንደምንሰማው ትዳራቸው በተፈቀደው መንፈሳዊ መንገድ አለመቃኘቱ ብሎም ከቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ውጭ በሆነ መንገድ መመስረቱ ትዳራቸውን ያለጊዜው እንዲፈርስ ያለ ዓላማ እንዲኖሩ ሆነዋል፡፡ ይሁንና አንተ በልጅነት እድሜህ በቃለ እግዚአብሔር ተኮትኩተህ አድገህ አሁን በተለያየ የዓለም ወጥመድ ከእግዚአብሔር እቅፍ የወጣህ ቢመስልህም እንዳትሳሳት፡፡ የቀደመው ጥቂት የክርስትናህ እርሾ ብዙ ይሰራልና በትዕግስት ነገሮችን ልታይ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ልጅ መውለድ አለመውለድ አልያም በሩካቤ አለመጣጣም አይደለም ቁልፍ ተግባሩ፡፡ እግዚአብሔር በናንተ ሕይወት ውስጥ ይሄንን ለምን አደረገ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ አሮጊቷ ሳራ ሽማግሌው አብርሐምም እድሜያቸው ካለፈ በኋላ ልጅ ወልደዋል ፡፡ በእግዚአብሔር ተጎብኝተዋል ፈጣሪ ልጅ እንዳይኖር የፈለገበትን ዓላማን በማስተዋል በመገንዘብ በጸሎትና በትዕግስት በመጠበቅ አስተውሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በጥድፊያ እግዚአብሔርን ወደ ሚያሳዝን ውሳኔ መግባት፣ፍቺንና ከትዳር ውጪ ደስታን ፍለጋ አለመሔድህ በእምነት መጽናት ያስፈልጋል፡፡ አንተም ሆንክ ባለቤትህ ሰዋዊ ፍላጎታችሁን አምቃችሁ በትዕግስት፣በጸሎትና በመበረታት ከእግዚአብሔር የሚሆነውን እስከ መጨረሻው ልትጠብቁ ይገባል፡፡
ውድ ጠያቂያችን በአንድም በሌላ መፍትሔ የሚሰጠው እግዚአብሔር ነውና ከላይ የተጠቀሱት መፍትሔዎች እንዳሉ ሆነው በመንፈሳዊ ሕይወታችን ልንጠቀምባቸው የሚገቡ መፍትሔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ጸሎት
በትዳር ሕይወት ውስጥ በሩካቤ ሥጋ ያለመጣጣም ችግርን ምክንያት አድርጎ ትዳርን ለመበተን ወይም ሰላምን ለማሳጣት የሚተጋውን ዲያብሎስን ከምናርቅበት መንገዶች አንዱ ጸሎት ነው፡፡ በመሆኑም ጸሎት ባልና ሚስት በትዳራቸው ማግኘት ያለባቸውን ደስታ እንዳያገኙ በመሃል እየገባ እንዳይስማሙ፣ እርስ በርስ እንዲጠራጠሩ፣ የሚያደርጋቸውን ጠላት ዲያብሎስ የሚያሸንፉበት መሣሪያቸው ነው፡፡
በመጽሐፈ ጦቢት ተጽፎ እንደምናነበው የራጉኤል ልጅ ሣራ ለሰባት ወንዶች አጋብተዋት አስማንድዮስ የሚባል ክፉ ጋኔን ከጭኗ ላይ አርፎባት ሰባቱን ባሎቿ እንዲሞቱ አድርጓቸዋል፡፡ ኋላም ጦብያን አጋቧት፡፡ “ወደ ጫጉላቸው ባስገቧቸው ጊዜ ጦብያ ከአልጋው ተነሥቶ፡- “እኅቴ ተነሽ፥ እግዚአብሔር ይቅር ይለን ዘንድ እንጸልይ” አላት፡፡ ከዚያም “አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ቅዱስ ስምህም ይባረክ፤ ለዘለዓለሙም ይመሰገናል፡፡ ሰማያትና የፈጠርሃቸው ሁሉ ያመሰግኑሃል፡፡ አንተ አባታችን አዳምን ፈጠርኸው፤ ትረዳውና ታሳርፈውም ዘንድ ሔዋንን ሰጠኸው፤ ከእነዚያም የሰው ዘር ተወለደ፤ አንተም አልህ፡- ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የሚረዳውን እንፍጠርለት፡፡ አሁንም ይህቺን እኅቴን የማገባት በሚገባ ነው እንጂ ስለ ዝሙት አይደለምና አቤቱ አብረን ወደ ሽምግልና እንድንደርስ እንረዳዳ ዘንድ ለእኔና ለእርሷ ይቅርታን ላክልን፡፡” በማለት ሲጸልይ ሣራም ከእርሱ ጋር “አሜን” እያለች በጸሎቱ እንደተባበረች ተጽፏል፡፡ ከጸሎታቸውም በኋላ ሁለቱም በዚያች ሌሊት አብረው አደሩ፡፡ ከጸሎታቸውም የተነሣ ጋኔኑ ከሣራ መራቁን እንረዳለን፡፡ (መጽሐፈ ጦቢት. ፰፥፬-፱ ፣ ፫፥፯‐፱)
በመዝሙረ ዳዊት “ጻድቃን በክብሩ ይመካሉ፤ በመኝታቸውም ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ፡፡” ተብሎ እንደተጻፈ ባልና ሚስት ሩካቤ ሥጋ የተሰጠበትን ዓላማ በአግባቡ እንዲፈጽሙ እንዲሁም ጣዕምና ደስታ ያገኙበት ዘንድ መጸለይ ይገባቸዋል፡፡ (መዝ. ፻፵፱፥፭)
በገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም ከተጠቀሱት ተአምራት አንዱ ፈቃደ ሥጋውን መፈጸም ስላልቻለ ሰው ይናገራል፡፡ ይህ ሰው ፈቃዱን በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ ወደ ጻድቁ ገዳም በመሔድ ችግሩ ይወገድለት ዘንድ ጸልዮ ሲመለስ የነበረበት ችግር እንደራቀለትና በትዳሩ ተደስቶ እንደኖረ ተጽፏል፡፡ በመሆኑም ፈቃደ ሥጋቸውን በአግባቡ መፈጸም ያልቻሉ ሰዎች ጸሎት በማድረግ ፈጣሪያቸውን መማጸን ከቅዱሳን ርዳታን መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ስለዚህ የተቀደሰው ሩካቤ ሥጋና የተባረከ ልጅ በፈቃደ እግዚአብሔር ስለተሰጠ የተሰጠበትን ዓላማ እንዳይስት በሥርዓት ይፈጸምና በአግባቡ የሚፈለገውን ደስታ ያስገኝ ዘንድ መጸለይ የሚገባ ሲሆን ይልቁንም ባልና ሚስት ፈቃዳቸውን ለመፈጸም የማያስችል እክል ሲገጥማቸው ደግሞ በይበልጥ በጸሎት በመትጋት ፈጣሪያቸው ፈተናቸውን እንዲያርቅላቸው፣ ቅዱሳኑ ደግሞ እንዲራዷቸው መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡
መረዳዳት
የሰው ልጆች ከእነርሱ ዕውቀት፣ አቅምና ጉልበት በላይ ለሆኑ ነገሮች ረዳት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንዱ ያለው ሌላው የለውም፤ ሌላው ያለው ደግሞ አንዱ የለውም፡፡ በመሆኑም ባልና ሚስት የተቀደሰውን ጋብቻ መሥርተው በሚኖሩት የትዳር ሕይወት ውስጥ ከሚያገኟቸው ጥቅሞች አንዱ አንዳቸው የአንዳቸውን እርዳታ ማግኘታቸው ነው፡፡
የባል ፍጹም ረዳቱ ሚስቱ ናት፤ የሚስት ፍጹም ረዳቷ ባሏ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሔዋንን ለአዳም ሲፈጥር “ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት እንጂ” ያለው ይህን ያስገነዝባል፡፡ (ዘፍ. ፪፥፲፰)
በተመሳሳይ ቅዱስ ጴጥሮስ “እንዲሁም እናንተ ባሎች ሆይ፥ ከሚስቶቻችሁ ጋር ስትኖሩ፥ ሚስቶቻችሁን አክብሩ፥ እነርሱ ከእናንተ ጋር ክብርንና ሕይወት ይወርሳሉና፡፡” በማለት ሚስቶች “ተፈጥሮአቸው ደካማ ነውና” በማለት በባሎቻቸው መረዳት የሚገባቸው መሆኑን ተናግሯል፡፡ (፩ጴጥ. ፫ ፥፯-፱)
በመሆኑም ባልና ሚስት በኑሯቸው የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ ለመግፋት ከሚያደርጉት መረዳዳት በተጨማሪ በሐሳብ እንዲሁም በስሜት በረቀቀ መልኩ ይረዳዳሉ፡፡ ከተረዳዱም የሚፈልጉትን ሁሉ እንዲያገኙ ፈጣሪ ይረዳቸዋል፡፡ ስለዚህ አንተም ሆንክ ባለቤትህ በአግባቡ ፈቃደ ሥጋውን መፈጸም ያልቻለውን ሰው ያለበትን ችግር በመረዳትና በመንፈሳዊውም ሆነ በሕክምና ጥበብ የሚረዳበትን መንገድ በማመቻቸት መተጋገዝ ይገባል እንጂ ጸብና ክርክርን በማስቀደም ለመለያየት መንገድ መጥረግ አይገባም፡፡
የጋብቻ ዓላማ ጊዜያዊ ደስታ አለመሆኑን መረዳት
በቅዱስ ጋብቻ የሚወሰኑ ጥንዶች ዓላማቸው አካላዊና ጊዜያዊ ደስታ ላይ ያተኮረ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ የትዳር አጋር ሌላውን/ሌላዋን ሰው በመሆኑ/በመሆኗ ለተጣማሪያቸው ንጹሕ ፍቅርን ከርኅራኄ ጋር መስጠት አለባቸው፤ ይህም ሲባል የተጣማሪውን አእምሮ ደኅንነት፣ ምግባር፣ ፀባይ፣ መላ አካልን ተቀብሎ መኖርን ይጠይቃል፡፡
ሩካቤ ሥጋ ደግሞ ጥልቅ የሆነውን ውስጣዊ ፍቅርን መግለጫና ማረጋገጫ መንገድ ቢሆንም በተራክቦ ሥጋ ብቻ ደግሞ እውነተኛ እርካታ አይገኝም፡፡ ሆኖም የውስጥ ስሜትንና ጭንቀትን እንዲቀንስ ግን ያደርጋል፡፡ ያ ደግሞ ጊዜያዊ ደስታን ያመጣል እንጂ ዘላቂ አይደለም፡፡
በመሆኑም በቅዱስ ጋብቻ የተመሠረተ ትዳር ንጹሕ ስሜትንና የጋራ መንፈሳዊ ሕይወትን ገንዘብ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን ምሉዕ የሆነ ደስታን መጎናጸፍን ዓለማው ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ በተጋቢዎች መካከል ሊኖረው የሚገባውና ጊዜያዊ ደስታን የሚያስገኘው ሩካቤ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከጥንዶቹ ባንዳቸው ሊፈጸም ባይቻል ዘላቂ የሆነውን ዘለዓለማዊ ደስታ በማሰብ በፍቅር ሊታገሡት ይገባል፡፡
አንዳቸው ሌላቸውን ማበረታታት
ምንም እንኳ በተቃራኒው ወገን ሩካቤን ለመፈጸም ድክመት፣ ልጅ አለመውለድ ችግር ቢኖርም አጋርን ከነችግሩ በመቀበል በሩካቤ ጊዜ በሚያደርገው ጥረት መደገፍና እርካታን መግለጥ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ጥንዶቹን ባላቸው ነገር አመስጋኝና ደስተኛ እንዲሆኑ ፣ የሚያልፈውን ደስታ በማሰብ የአጋራቸውን ሕሊና ከሚነኩ ንግግሮች ወይም ድርጊቶች እንዲታቀቡ፣ አጋራቸው በጊዜ ሒደት ካለበት ችግር እንዲወጣ እንዲያግዙ እንዲሁም ትዳርን ከመፍረስ እንዲጠብቁ ይረዳቸዋል፡፡
የንስሐ አባትን ማማከር
ክርስቲያን ሕይወቱን በምክረ ካህን መምራት ይጠበቅበታል፡፡ የንሰሀ አባቶች የንሰሀ ልጆቻቸውን የወደፊት ሕይወት አቅጣጫ የማስያዝ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ድልድይ ሆነው የማገናኘት ፣ የንሰሐ ልጆች ጋር በሀዘን በደስታ ተገኝተው መንፈሳዊ አገልግሎት የመስጠት እና በዕለት ዕለት ለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎችን ሊመክሩ ሊያጸኑ ብሎም ለእኛ የተሰጡን እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ለንስሐ አባቶች የትኛውንም አይነት ችግር ቢገጥመን ሳንደብቅ፣ ሳንፈራ፣ ሳናፍር፣ ችግራችንን በመናገር በምክራቸው በጸሎታቸው ሊራዱን ስለሚችሉ በግልጽ ከንስሐ አባት ጋር በመመካከር ለችግራችን በወቅቱ መፍትሔ ልንፈልግ ያስፈልጋል፡፡ ውድ ጠያቂያችን አንተም የንሰሀ አባት ከሌለህ የንሰሀ አባት በአጥቢያህ የሚያገለግሉ አባቶችን በመያዝ አሁን ያለብህን ከባድ ፈተና ለሰውና ለባልንጀራ ከማማከር ከንስሐ አባታችሁ ጋር በመሆን ሳትፈሩ በግልጽ በመወያየት ወደ መፍትሔ ልትመጡ ይገባል፡፡
ውድ ጠያቂያችን በአጠቃላይ ያጋጠመህ የትዳር ሕይወት ችግር ከመንፈሳዊ ዕውቀት ማነስ ብሎም ለሀይማኖታዊ ጉዳዮች ትኩረት ካለመስጠትና ትዳርን በጥበብ ካለመምራት የተነሣ ነው፡፡ ስለዚህ ምህረቱ የበዛ እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ ስለሚችል አሁን ካላችሁበት ከተሳሳተ የትዳር አካሄድ ለመውጣት በመወሰን በንሰሀና በልብ ዝግጅት እንድታደርጉ ብሎም በሩካቤ ፣በልጅ አጦት ሳቢያ ደስታ ማጣት፣ ችግሩን መፍትሔ እንደሌለው አድርጎ ማሰብ፣ ይሉኝታና ማህበራዊ መገለልን መፍራትን ማቆም ወደ እግዚአብሔር መመለስ አለባችሁ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ጋብቻ ቅዱስ መኝታውም ንጹሕ ነውና ስለ ሩካቤ ሥጋ በግልጽ በጨዋነት ማውራት መመካከር የሚያሳፍር ነውር ስላልሆነ መመካከራችሁ ሊቀጥል ይገባል ፡፡ የልብ መዘጋጀት ከሰው ፣ የነፍስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር እንደሚባለው መልካም ሀሳቦችን ይዛችሁ ፈጣሪን ከተማጸናችሁ የለመኑትን የማይነሳ መድኃኔዓለም በትዳራችሁ የጎደለውን ሁሉ ይሞላል፡፡