Monday, 02 November 2020 00:00

“ቅርሶችን መጠበቅ ማንነትን መጠበቅ ነው”

Written by  ረቂቅ መቻል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከስድሳ ሚሊዮን በላይ አማኝ ያላት፣ በውስጧ ብዙ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ቅርሶችን ይዛ በሀገር በቀል ዕውቀቶቿም ለኢትዮጵያ የሥልጣኔ  አሻራዋ መሆኗ እሙን ነው፡፡ ታዲያ ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ቅርስና ልዕልና መነሻ በመሆን ትልቁን አስተዋጽኦ  ያበረከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፡፡ ይሁን እንጂ  አሁን ቤተ ክርስቲያንና ቅርሶቿ  ለሀገር ያበረከቱትን አበርክቶት በዘመን ከፍታ  ላይ ቆመው እንዳይመለከቱ ልባቸው የጠፋ፣ ዐይናቸው የተንሸዋረረ  ግለሰቦችም ሆኑ  ጽንፈኛ ቡድኖች  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ መምጣታቸው አሳዛኝ ነው፡፡  ከቅርብ ዓመታት ወዲህም እየመጣ ካለው ትውልድ ውስጥ አንዳንድ ግለሰቦች የሀገራችንንም ሆነ የሃይማኖታችንን ታሪክና ቅርስ እንዲሁም የማንነት ገጽታውን ጥላሸት እየቀቡ ይገኛሉ፡፡  ስለዚህነ ገን እንዴትና ማን ቅርሶቻችንን ለትውልድ ያሻግር? ሀገሬና ሃይማኖቴ ያፈሩትን የጋራ ታሪክና ቅርስ  ማን ይሆን የሚጠብቀው ብዬ እንድታዘብ የተገደድኩባቸው ዐበይት ምክንያቶችም አሉኝ፡፡  ባለፉት  ዓመታት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እና ኦርቶዶክስ  ሃይማኖት በዓለም  መድረክ   እንደ አንድ ልብ መክረው በሰላም፣ በበጎነት፣ በመከባበር ለሌሎች  አርአያ በመሆን የሚታወቁ፣ምእመናን በመፈቃቀር አብረው የሚኖሩ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ባህላቸውን፣ ዕሤታቸውን፣ ቅርሶቻቸውን ለመጠበቅ ችለዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ቤተ ክርስቲያን  የሀገር ባለውለታ የሆኑ የታላላቅ ነገሥታት ታሪክን ሰንዳ የያዘች ፣ ቅርሶችን በመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘገብ ያደረገችበት የታሪክ ዐውድም ብዙ በመሆኑ  የቀደሙት መንግሥታት በሚሄዱበት ሁሉ ከፍ አድርገዋት ቅርሶቿንና ልዕልናዋን አስጠብቀዋል፡፡ አዲሱ የዘመን ብራናችን እንዲበላሽና ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ቅርሶቻችን ለትውልድ  እንዳይቀመጡ  በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦችና  አክራሪ ቡድኖች  በሃይማኖታችን ላይ  እያደረጉት ያለውን ዘመቻ እንዴት ተባብረን እናስቁም? የሚለውን እናስብ፡፡ እነዚህን ቅርሶች እንዳይጠፉ በትጋት የሚጠብቁት ታላላቅ አባቶች ከየቦታው በግፍ ተገድለዋል፣ ደማቸውም እንደ አቤል ደም በሁላችን ሕሊና ውስጥ እየጮኸች ዓመቱ እንደዋዛ አልፏል፡፡ በተለይ ስለ አብያተ ክርስቲያናት ሲሉ የንዋያተ ቅድሳት መቃጠል አስጨንቋቸው ሥጋቸውን የሚገድሏቸውን ሳይፈሩና ለሥጋቸው ሳይሳሱ  የተቃጠሉ፣ ቤተ ክርስቲያናቸውን ከቃጠሎ ለመከላከል ሲሉ በሚሰጡት ተግሣጽ ዘወትር  ግፍና መከራን በሰማዕትነት የተቀበሉትን ልንረሳቸው አንችልም፡፡  በእርግጥ  ቤተ ክርስቲያንን  የናቋትና ሁሉ ነገ እውነቱ ሲገባቸው ከእግሯ ዝቅ ብለው ማሪን እንደሚሉ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም በቅዱስ መጽሐፍ ትንቢት እንዲህ የሚል ተጽፏል “ለአንቺም የማይገዙ ነገሥታት ይሞታሉ፤ እነዛም አሕዛብ ፈጽመው ይጠፋሉ፤ የመቅደሴንም ስፍራ ያከብሩ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው ባርስነቱም ወደ አንቺ ይመጣሉ የአስጨናቂዎችሽ ልጆች  እየተንቀጠቀጡ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም  ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእስራኤል ከተማ ቅዱስ ተብለሽ ትጠሪያለሽ፡፡” (ኢሳ. ፷፥፲፪‐፲፬) የትም ሊገኙ የማይችሉ ቅርሶችን የያዘች ቤተ ክርስቲያን በብርቅዬ ቅርሶቿ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እንድትታወቅ ከማድረግ አኳያ የበኩሏን አስተዋጽኦ ማበርከቷ መዘንጋት አልነበረበትም፡፡  አባቶቻችን ያቆዩልን  ቅርስ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ሳስብ ይኸኛው ትውልድ ጥበብ መውረስ ይቅርና እንዳለ ጠብቆ ማቆየት አለመቻሉ ምን ያህል ተጠያቂ እንደሚያደርገው መገንዘብ ከባድ አይሆንም፡፡  የዚህችን የታላቋን ቤተ ክርስቲያን ቅርሶችና ሀብቶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ማንም እንደፈለገው ሲያደርጋቸው ”መጣፉም ዝም ቄሱም ዝም ” እንደሚባለው ዝምታው እስከመቼ ነው? መጽሐፉ እንኳን የሚያነበው አለመኖሩ እንጂ አንዴ የተጻፈው ለዘላለም ይናገራል፡፡ በእውነቱ የቤተ ክርስቲያናችን ዜማ እንዲሁም መሣሪያዎቹ በሌሎች እየተወሰዱ ባንጻሩ ደግሞ የኛዎቹ መዝሙራት ከያሬዳዊ ዜማና መሣሪያዎቹ እየተፋቱ ዘፈን ዘፈን እየሸተቱ መሄዳቸው ዕለት ዕለት የምናይና የምንሰማው ቢሆንም ችግሩን ተረድቶ ሕጋዊ ማስተካከያ (ርምጃ) የሚወስድ አካል ከሌለ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የባለቤትነት መብታችንንም እንዳናጣ ያሰጋል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያሏት የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ማንነታቸው እንዳያጡ ፣ ከሥሪታቸው እንዳይለዩ እና ጠፍተው እንዳይቀሩ ብሎም ተጠብቀው እንዲቆዩ የቤተ ክርስቲያን፣ አባቶች እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን በጋራ በመሆን ሊሠሩ ይገባል  በአጠቃላይ ቅርስን መጠበቅ ማንነትን መጠበቅ ነውና እነዚህ የማይነጣጠሉ ሀገርና ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ እንዴት ለመጪው ትውልድ  እናቆይ?  ቅርስ ማጣት ታሪክ ማጥፋት ነውና የነገሥታቶቻችን ታሪክ፣የቤተ ክርስቲያን ቅርስ ሁሉም የኢትዮጵያ መሠረቶች በመሆናቸዉ ሐሳብና መፍትሔ ቢሆኑ ያልኳቸውን ጥቂት ሐሳቦች አክዬ የዛሬ ትዝብቴን እቋጫለሁ  ቅርሶች የአንድን ማኅበረሰብ ታሪክና ማንነት በማሳየት ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ለቅርሶቹ ግንባታ የዋሉት ቁሳቁሶችና አሠራራቸው ለዘመናዊ ሥነ ሕንፃ መማሪያም ነው፡፡ ቅርሶች ለሚገኙበት አካባቢ ነዋሪዎች ሥራ ከመፍጠር ጀምሮ ለሀገር ውስጥና የውጪ ኢንቨስትመንት መስፋፋትና ለቱሪዝም ዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦም ታላቅ ነው፡፡ ስለዚህ ቅርሶች ለሀገርና ለቤተክርስቲያን  ያላቸውን ጠቀሜታ ለምእመናን በየዐውደ ስብከቱ እንዲሁም በሥርዐተ ትምህርት ተካቶ በሕዝቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲጨምር ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ፩. የቤተ ክርስቲያንም ሆነ የሀገርን ቅርሶች የሚመለከታቸው አካላት በእኩል አይተው ተገቢውን  እንክብካቤና ጥበቃ ቢያደርጉ፤ ፪. የቤተክርስቲያን ቅርሶች የሀገር ቅርሶች እንደመሆናቸው መንግሥት ሁሉንም የኢትዮጵያ ቅርሶች እኩል ቢመለከት፣ ከርዳታ ሰጪዎች ከሚመጣው ገንዘብ ላይ በቤተ ክርስቲያን ለሚገኙ ቅርሶች በጀት ቢበጅትና ቅርሶቹ የሚገኙባቸው ነባራዊ ሁኔታ ተመዝነው በየጊዜው እድሳት ቢደረግላቸው፤ ፫.የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች የሀገሪቱ ዜጎች( ምእመን) ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም መገለጫ በመሆናቸው ለጥበቃቸው በጋራ መረባበረብ ቢቻል፤ ፬.የቅርሶች ጥበቃ ጉዳይ በመንግሥት ወይም በበጎ አድራጊዎች ችሮታ ብቻ ግቡን ስለማይመታ  የማኅበረሰቡን  ተሳትፎ ማሳደግ፣ ማኅበረሰቡ ቅርሶችን እንዲጠብቅ ማበረታታት፤ ብሎም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ፡፡ ፭. ቤተ ክርስቲያን በሁሉም ቅርሶቿ አሠራር እና አጠባበቅ ላይ ብቻ የሚሠራ በሊቃውንት አባቶቻችን የሚመራ በባለሙያዎች የተደራጀ አካል ቢኖራት፤ እያንዳንዱ ባለሙያ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ማእከላዊ በሆነ መንገድ ሥልጠና የሚያገኝበት ሁኔታ ቢቀረጽ እንዲሁም እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ቅርስ ሕጋዊ ጥበቃ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ቢመቻች ቤተ ክርስቲያን ነገ ለልጆቿ የምታስረክበው ያልተበረዘ ቅርስ ይኖራታል፡፡  ፮. የቅርሶቹ ባለቤቶች ውስጥ ከሆኑት አንዷ የሆነችው  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶቿ ይሰረቃሉ በሚል ስጋት  ላለፉት ዓመታት ዲጂታላይዜሽንን እንደማታበረታታ ይነገራል። "በተለይም የውጪ ሀገር ምሁራን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ሲመጡ፤ ቅርሶቹ ተዘረፉ ስለሚባል በቤተ ክርስቲያን ዘንድ የዲጂታይዜሽን ጥቅም ብዙም አይታይም።  ደግሞም ቤተ ክርስቲያኗ በውጪ ተመራማሪዎች በቅርስ ጥናት ስም ከሚደርስባት  የቅርስ ዘረፋ ቤተ ክህነት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችም ለዲጂታላይዝ ተግባሩ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ብዙም አያስደንቅም ምክንያቱም ቅርሶች ይሰረቃሉ የሚለው  የቤተ ክርስቲያን ስጋት መሠረት ስላለው ነው። ይሁንና  ከዘመኑ ሥልጣኔ አንጻር ዛሬ ላይ ቅርሶችን ዲጂታላይዜሽን ማድረግ ደግሞ አማራጭ የሌለው ዘዴ ነው። ስለሆነም ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ቅርሶችን ሰንዶ መያዝ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡  
Read 1568 times