Monday, 02 November 2020 00:00

«በሃይማኖት መለያየት ምክንያት የምወዳትን ባለቤቴንና ልጆቼን እንዳላጣቸው እፈራለሁ›› ክፍል አንድ

Written by  ረቂቅ መቻል
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ሰነበታችሁ ስሜ  ጸጋ ሥላሴ ይባላል የምኖረው  ወሊሶ ከተማ ሲሆን  በየጊዜው የሚወጡ ጽሑፎቻችሁን አነባለሁ ፡፡ እናም እኔም በትዳር ሕይወቴ ችግር የሆነብኝን ጉዳይ እንደሚከተለው ጻፍኩላችሁ ፡፡ እኔና ባለቤቴ ትውውቃችን ዩኒቨርስቲ እያለን ነበር አሁን የአንድ ወንድ ልጅና የአንዲት ሴት ልጅ  ወላጆች ሆነናል፡፡ ከተጋባን ድፍን ፲፪ ዓመት ሞላን፡፡ ነገር ግን በወቅቱ እኔም የነበረኝ የእምነት ጥንካሬ የላላ በመሆኑ የትዳሬ ዋና ጉዳይ እምነት መሆኑን ብዙም አስተውዬ አላውቅም ነበር፡፡ እናም ትዳራችንን በመግባባትና በመፈቃቀድ ላይ አድርገን መሠረትን፡፡ እየቆየን በዕድሜም ሆነ በአእምሮ  እየጎለመስን ስንመጣ ባለቤቴ የቤተሰቤ እምነት የምትለውን እስልምና አጥብቃ በመከታተል  በኔና በልጆቼ ላይም ተጽዕኖ ማድረግ ጀመረች፡፡ ልጆቼን ባላት ትርፍ ጊዜ የእስልምና ትምህርት ማስተማር ፣ ወደ ቁርአን ቤት መላክ ወዘተ የመሳሰሉትን ነገሮች ማከናወን ጀመረች ፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ተነጋግረን መግባባትና መፍትሔ ማምጣት አልቻልንም፡፡ ስለዚህ እኔ ብዙ ዓለማዊ የመፍትሔ አማራጮችን ተጠቅሜ ትዳሬንና ልጆቼን ለማቆየት ሞክሬ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር ቁልቁል ሆነብኝ እናም በእናንተ በኩል መንፈሳዊ ምክርና አስተማሪ መፍትሔ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ ከልጆቼም ከባለቤቴም ተለይቼ ባልኖር ግን እመርጣለሁ ፡፡ ምክንያቱም ብቸኝነት ያስፈራኛል ፡፡    የተከበርክ ውድ ወንድማችን በቅድሚያ በገጠመህ ችግር ብቻህን ከመጨነቅ ይልቅ መፍትሔ አገኛለሁ ብለህ ያስጨነቀህን ጉዳይ ስላካፈልከን እናመሰግንሃለን። እኛም በዝርዝር ያነሳኸውን ታሪክ መነሻ በማድረግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ ለገጠመህ ችግር  መፍትሔ ይሆናሉ  ብለን ያሰብናቸውን ምላሾች ከዚህ በታች ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ። ውድ ጠያቂያችን አብዛኛውን ጊዜ ትዳር አደጋ ውስጥ የሚገባው ወይም ባልና ሚስት የሚፋቱትና ልጆች የሚበተኑት  ቅድመ ጋብቻ ላይ በሚፈጸም የጥንቃቄ ጉድለትና ትክክል ያልሆነ የትዳር አመሠራረት ሂደት ነው፡፡ የቅድመ ጋብቻ የትውውቅ ወቅት ወይም የትውውቅ ጊዜ የጥንዶቹ   የትዳር ሕይወት መሠረት የሚጣልበት ወርቃማ ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት በስሜታዊነት፣ በችኮላ ወይም በግዴለሽነት  በሚደረግ ውሳኔ የሚፈጠሩ ስሕተቶች በስተኋላ ያልተጠበቀ ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀርም።  ትዳር ተቃራኒ ጾታ ባላቸው ጥንዶች የሚመሠረት፣ ለትልቋ ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ስኬታማነት መሠረት የሆነ ቤተሰብን ያቀፈ የተቀደሰ አንድነት ነው። በምድራዊ መንግሥት አንጻር ካየንም ትዳር ትንሹ መንግሥት በመሆን ለትልቁ መንግሥት ግንባታ በመሠረትነት ያገለግላል። ትንሿ ቤተ ክርስቲያንና ትንሹ መንግሥት የሚጀምረው በተቀደሰ ጋብቻ ከሚመሠረት ትዳርና ቤተሰብ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ትዳር ለአመሠራረቱ፣ ለውጤታማነቱና ለዘላቂነቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚገባ ልዩ ተቋም ነው።  ውድ ጠያቂያችን ስለትዳርህ እንደገለጽከው ከሆነ ቀድሞ መሠራት የሚገባውን ቅድመ ዝግጅት ባግባቡ መሥራት ባለመቻልህ የትዳራችሁ መሠረት በመናጋት ላይ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ብዙ ጊዜ የውበትን ትክክለኛ ትርጉም ስለምናዛባው በራሳችን የእይታ ስሕተት በወጥመድ ተይዘን እንሠቃያለን። የአንድ ሰው ትክክለኛ ውበት አፍኣዊና ውሳጣዊ በሚሉ ሁለት ክፍሎች ተከፍሎ ይገለጻል። በሌላም መልኩ የሰው ማንነት ሲጠና በተመሳሳይ ሁኔታ ውጪያዊና ውስጣዊ ማንነት ተብሎ በሁለት ይከፈላል። አፍኣዊ (ውጪያዊ) ውበት (ማንነት) መገለጫው ውጪያዊ ገጽታ ነው። ይህም ተክለ ሰውነትን፣ አኗኗርን፣ አለባበስን፣ አነጋገርን፣ ጠባይን፣ ሥራውንና የመሳሰሉትን ያካትታል። ውሳጣዊ ውበት (ማንነት) ደግሞ ባሕርይውን፣ ፍልስፍናውን ማለትም የሕይወት እይታውን፣ ዕውቀቱን፣ አስተሳሰቡን፣ እምነቱን፣ ምኞቱን፣ ስሜቱንና ማኅበራዊ ዕሴቱን ያጠቃልላል። በአግባቡ ካልተያዘ መረጋጋትንና ማስተዋልን በሚጋርደው የወጣትነት ዕድሜ ጎልቶ የሚታየው ውጪያዊ ውበትና ማንነት ይሆንና ተፈጥሮአዊ በሆነው አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ለውጥ እየታገዘ በስሜት ማዕበል  ይናወጻል። አፍኣዊው ገጽታ ውሳጣዊውን ውበት እንዳናይ አሳውሮ በጭፍን የመንዳት አቅም እንዲያገኝ ዕድል ከሰጠነው ወደማንወጣበት ዐዘቅት ይከተናል። ብዙዎች እኅቶቻችንና ወንድሞቻችንን አታሎ ገደል የሚከታቸው ደግሞ ውስጣዊው ማንነት በውጪያዊው ማንነት በሚደበቅበት ጊዜ ነው። ውስጣዊው ማንነት በውጪያዊው ማንነት ካባ በሚሸፈንበት ጊዜ እጅግ አደገኛ ይኾናል። ምክንያቱም በዚህ ጊዜ የአንድን ሰው ትክክለኛ ማንነት መረዳት አስቸጋሪ ስለሚኾን ነው። አንድ ሰው ውሳጣዊ ማንነቱ በተለይም መንፈሳዊ ሕይወቱ የላላ ከኾነ በሌሎች ውጪያዊ ውበት በቀላሉ የሚማረክ መኾኑ አይቀሬ ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ችግር ብዙ ወጣቶችን  አታሎ  ወደማይጠቅም ሕይወት ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡ ወንድማችን አንተም የችግርህ ምንጭ ከእነዚህ ነጥቦች ውጪ ሊሆን እንደማይችል ከጻፍከልን ጥያቄ መረዳት እንችላለን። ውድ ጠያቂያችን ምንም እንኳን መፍትሔ የሚሰጠው እግዚአብሔር  ቢሆንም በማኅበረሰቡ ውስጥ ስንኖር ለችግሮቻችን መፍትሔ ሰጪ የሚሆኑ ሰዎችና ተቋማት በመኖራቸው እንደ እግዚአብሔር በሰው ላይ አድሮ ችግርን  ይፈታልና እኛም  ካህናትንና ሊቃውንት አባቶችን በማማከር ያገኘነውን ምክረ ሀሳብና  ሃይማኖታዊ መፍትሔዎች ብሎም በኦርቶዶክሳዊ  ሕይወትህ ልትጠቀምባቸው ይገባሉ ያልናቸውን መፍትሔዎች እንደሚከተለው አስቀምጠናል፡፡ ፩. አሁን ያላችሁበትን የትዳር ሁኔታ በጥልቀት መመርመር ውድ ጠያቂያችን እንደገለጽከው ደግሞ በ፲፪ ዓመት የትዳር ቆይታችሁ ፪ ልጆችን እስከ ማፍራት ደርሳችኋል። ባለቤትህ በስተኋላ ባንተና በልጆቻችሁ ላይ እያደረሰች ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ገልጸህ "እንዴት ነው መቋቋምና ማስተካከል የምችለው?" ብለህ ጠይቀኸናል። ይህ የአንተ ዓይነት ችግር በመጽሐፍ ቅዱስም ተመዝገቦ የሚገኝ የነበረ፣ ያለና የሚኖር የብዙዎች ምእመናን ፈተና ነው። ለምሳሌ በመጽሐፈ ዕዝራ እንዲህ የሚል ሃሳብ እናገኛለን"ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ፥ ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። አሁንም የአባቶቻችንን አምላክ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ፤ አላቸው።" (ዕዝ. ፲፥፲-፲፪) የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጥሰው ከእንግዶች ሴቶች ጋር የተጋቡ በርካታ ወንዶች መገኘታቸውን ካህኑ ዕዝራ በስም በስማቸው ዘርዝሮ፦ "እነዚህ ሁሉ እንግዶቹን ሚስቶች አግብተው ነበር፤ ከእነዚህም ሚስቶች ዐያሌዎቹ ልጆችን ወልደው ነበር።" (ዕዝ. ፲፥፵፬) ይላል።  ቅዱስ መጽሐፋችን ባልና ሚስት አንድ አካል መሆናቸውን ያስተምረናል። አንድ አካል መሆን እውን የሚሆነው ደግሞ ጥንዶቹ በሁሉም ነገር ፍጹም የሆነ ተዋሕዶ ሲኖራቸው ነው። "ከወንድሞቻችን መካከል የማታምን፥ ባልዋንም የምታፈቅር ከእርሱም ጋር ለመኖር የምትወድ ሚስት ያለችው ሰው ቢኖር ሚስቱን አይፍታ። ሴቲቱም የማያምንና ሚስቱን የሚያፈቅር ከእርስዋም ጋር ሊኖር የሚወድ ባል ቢኖራት ባልዋን አትፍታ። የማያምን ባል በሚስቱ ይቀደሳልና፤ የማታምን ሚስትም በባልዋ ትቀደሳለችና፤ ያለዚያማ ልጆቻችው ርኵሳን ይሆናሉ፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው።. . . ሚስትም ባልዋን ታድነው እንደ ሆነ አታውቅምና፤ ባልም ሚስቱን ያድናት እንደ ሆነ አያውቅምና።" (፩ ቆሮ. ፯፥፲፪-፲፯) በቅድሚያ የምናነሣው ነጥብ የማታምን ሚስትን ፥ ወይም የማያምን ባልን መፍታት አይገባም የሚለው ነው። መረሳት የሌለበት ጉዳይ ሐዋርያው ኢአማኒ የትዳር አጋርን አትፍቱ ሲል ያስቀመጣቸውን  መሠረታዊ መሥፈርቶች የሚያሟላ/የምታሟላ ከሆነ/ች ነው፡፡ እነዚህም የማታምን ሚስት ባልዋን የምታፈቅርና  ከእርሱ ጋር ለመኖር የምትወድ ከኾነች የሚለው ነው። የማያምን ባልም በተመሳሳይ ሚስቱን የሚያፈቅርና  ከእርስዋ ጋር ሊኖር የሚወድ ከሆነ ከሆነች አይፍታት፤ አትፍታው ብሏል። እዚህ ላይ በጥንቃቄ መታየት ያለበት አንዱ ጉዳይ ሐዋርያው በመልእክቱ የሚያምን ክርስቲያን እምነቱ የማትመስለውን እንዲያገባ ፈቃድ እየሰጠ ነው ማለት አይደለም። የማያምን ባል ስላላት ሚስት ወይም የማታምን ሚስት ስላለችው ባል ነው እየተናገረ ያለው እንጂ ወደፊት በዚህ መስመር ስለሚጋቡት አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተመሥርቶ ችግር ውስጥ ስላሉት ነው እያስተማረ ያለው።  ውድ ወንድማችን አንዱ መመርመር ያለብህ ነጥብ ይህ ነው። ሚስትህ እነዚህን ነጥቦች የምታሟላ ካልሆነ አብራ ልትኖር የምትችልባቸውን ዕድሎች ልታጣ ትችላለች። የዚህም ምክንያቱ ራሷ ነች። ዳሩ ግን መሥፈርቶቹን የምታሟላ ከሆነች አንተም በተመሳሳይ የምታፈቅራትና አብረሃት ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ልትፈታ አይገባትም። እንዳየነውም ሐዋርያው አብሮ የመኖርንና ያለመኖርን መብትና ነፃነት በባልና በሚስት ፍላጎትና ውሳኔ ላይ ነው ያኖረው። ሐዋርያው ለምንድነው አማኙ ባል ከማታምነው ሚስቱ ጋር እንዲኖር የፈቀደው? ለሚለው ጥያቄም፦ "የማታምን ሚስት በባሏ ትቀደሳለች፤. . .ባልም ሚስቱን ያድናት እንደኾነ አያውቅምና።" በማለት ተገቢውን ምላሽ ሰጥቷል።  ክርስቲያን በእምነት የማትመስለውን ሚስቱን ይቀድሳል የሚለው ኀይለ ቃል የሚያሳየው አማኙ ባል የማታምን ሚስቱን የሚቀድስበት ኀይል እንዳለው ነው። ምንድን ነው ያ ኀይል? የክርስትና ሃይማኖት ፍጹም እምነት በመሆኑ የዚህ እምነት ባለቤት (ክርስቲያን) እንደተገለጸው በኢአማኒው እምነት እስካልተጠለፈ ድረስ በማንኛውም ዓይነት እምነት መሰል አስተሳሰብ አይረክስም። በተቃራኒው ይህ እውነተኛውን የባሕርይ አምላክ (እግዚአብሔርን) የሚያመልክና ሀብተ ወልድና ተቀብሎ በስሙ የተጠራ ክርስቲያን ማንኛውንም ዓይነት ከክርስትና የተለየ አማኝን ይቀድሳል።   
Read 731 times