Monday, 09 November 2020 00:00

«በሃይማኖት መለያየት ምክንያት የምወዳትን ባለቤቴንና ልጆቼን እንዳላጣቸው እፈራለሁ››ክፍል ሁለት

Written by  ዝግጅት ክፍሉ
«በሃይማኖት መለያየት ምክንያት የምወዳትን ባለቤቴንና ልጆቼን እንዳላጣቸው እፈራለሁ›› ክፍል ሁለት   ፪. በራስህ እምነት ጠንካራ ሆነህ መገኘት  ክርስቲያን የማያምነውን የትዳር አጋሩን የሚቀድሰው እንዴት ነው? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ክርስቲያን አማኙ በሃይማኖቱና በምግባሩ ከሌሎች እምነት አማኞች ተሸሎ ሲገኝ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ አንድ ክርስቲያን ሦስት መሰረታዊ ቁም ነገሮች ሊኖሩት ይገባል እነዚህም፡- ሀ.  ክርስቲያን የእምነት ጥንካሬ ሊኖረው ይገባል። እግዚአብሔር የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን ሁሉ እንደሚችልና እንደሚቀይር አምኖ የሚያሰጨንቀውን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ መሆን አለበት። "በሰው ዘንድ ይህ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል።" (ማቴ. ፲፱፥፳፮) "ቢቻልህ ብለሃል፤ ብታምንስ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል።" (ማር. ፱፥፳፫) "ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ድል ይነሣዋልና፤ ድል መንሣቱም ይህች ናት፤ ዓለምን ድል የሚነሣውም እምነታችሁ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን ድል የሚነሣው ማን ነው?" (፩ ዮሐ. ፭፥፬-፮) ተብሎ እንደተገለጸው። ለ.  ክርስቲያን ስለ እምነቱ ማስተማርና መመስከር ይኖርበታል። አማኙ የማታምን የትዳር አጋሩን ሊቀድሳትና ከዘለዓለም ሞት ሊያድናት ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ ስለ ሃይማኖቱ የሚሰጠው ምስክርነት ነው። "በሰው ፊት የሚያምንብኝን (የሚመሰክርልኝን) ሁሉ እኔም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት አምነዋለሁ። በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት እክደዋለሁ።" (ሉቃ. ፲፪፥፰-፲) እንዲል። ክርስቲያን በሃይማኖቱ ሳያፍርና ሳይፈራ በየትኛውም ጊዜና ቦታ የሚያምነውን የሚመሰክር መሆን ይገባዋል። በተለይም እንዲህ ዓይነቱ በጋብቻ የመተሳሰር ክሥተት ሲፈጠር አጋጣሚውን ተጠቅሞ በፍቅርና በጥበብ የማያምነውን አጋር ለማዳን እምነትን መመስከር ከአማኙ ይጠበቃል። ሐ. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መላበስ ይገባል፡፡ ማንኛውም ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከሚገልጽባቸው መንገዶች አንዱ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መላበስ ነው። አንዳንድ ሰነፎች ክርስትናን በሕይወት ማሳየት ባለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ከክርስትናው በተቃራኒ ስለሚጓዙ እንኳንስ ኢአማንያንን ሊማርኩ ይቅርና አምላካቸውን የሚያሰድቡ ይሆናሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዚህ ነው "እነሆ፥ በእናንተ ምክንያት አሕዛብ የእግዚብሔርን ስም ይሰድባሉ።" (ሮሜ ፪፥፳፬) በማለት ነው ያስተማረው። የክርስቲያን ሕይወት የሚነበብ ወንጌል በመሆን ብዙዎችን ስቦና ማርኮ የሚቀድስ መሆን አለበት። ክርስቲያን ባል ለማታምን ሚስቱ ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ ታዛዥነትን፣ ርኅራኄን፣ ትዕግሥትን፣ ርጋታን፣ . . . ያለማስመሰል በቋሚነት ካሳያት በሃይማኖቱ መሳቧ አይቀርም። ክርስቲያን አልጫውን ዓለም እንዲያጣፍጥ የተጠራ የእግዚአብሔር መልእክተኛ መኾኑን ማመንና በተግባርም ተልእኮውን መወጣት ይጠበቅበታል። ክርስቲያን ባል የማታምን ሚስቱን አልጫ ሕይወት በቅዱስ ቃሉና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባሩ ለማጣፈጥ እግዚአብሔር የሰጠውን ዕድል መጠቀም ይገባዋል። "ሥነ ምግባራቸው እንዲህ ያማረ ሃይማኖታቸው ምንኛ ቢያምር ይኾን?" እያሉ በክርስቲያኖች ሕይወት ተማርከው ለቅድስና የበቁ ሰዎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። የእውነተኛ ክርስቲያኖች የጾም፣ የጸሎት፣ የስግደት፣ የምጽዋት፣. . . ክርስቲያናዊ ሕይወት  ብዙዎችን ካለማመን ወደ ማመን አምጥቶ በምግባር በሃይማኖት አጽንቶ የመንግሥተ ሰማያት ምርኮኞች አድርጓቸዋል፡፡ ውድ ወንድማችን ባለቤትህን እንደምትወዳት እንገነዘባለን። ክርስቲያን የሆነ ሰው ደግሞ እስከ ሞት ድረስ ደርሶ  የሰጠለትን ክርስቶስን እንዲመስል ተጠርቷል። ራስን ከመስጠት የሚበልጥ ስጦታ የለምና እሱ እኛን በመውደዱ ራሱን ነው የሰጠን። እኛም ለምንወደው ሰው የምንሰጠው ስጦታ ለእኛ የምንመኘውንና ውዱን ሀብት ሊኾን ይገባል። ለክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ ከመኾንና ያዘጋጀለትን ሰማያዊ መንግሥቱን ወርሶ ከመኖር የሚበልጥ ምን ሀብትና ስጦታ ይኖረዋል? እወዳታለሁ፤ እወደዋለሁ፤ ለሚለው ሰው ይህን እንዲያገኝ ካልተመኘና እንዲያገኘውም ማንኛውንም መሥዕዋትነት ካልከፈለላት፥ ካልከፈለችለት እንዴት እወደዋለሁ ሊል/ልትል ይችላል/ትችላለች?  የትዳር አጋሩ፣ ልጆቹ፣ ቤተሰቡ፣. . . በጨለማ ውስጥ እየኖሩና ወደ ዘለዓለማዊ ቅጣት እየተጓዙ በግዴለሽነት ማየት ፈጽሞ የሚገባ አይደለም ለዚህም የማይከፍለው ምንም ዓይነት ሰማዕትነት አይኖርም። ከጻፍክልን ጥያቄ እንደተረዳነው ባለቤትህ ይጠቅመኛል ብላ በያዘችው "እምነቷ" በሥራ  ቀድማሃለች። ከልጆችህም አልፎ ተርፎ አንተንም ክርስትናህ ልታወጣህ መንገድ ጀምራለች። በዚህም ምክንያት አብረህ ለመኖር በምታደርገው ግብ ግብ ከውዝፍ ሥራህ ጋራ ተደምሮ የቤት ሥራህን አክብዳብሃለች። ይሁን እንጂ የዘረዘርናቸውን መሠረታዊ ነጥቦች ያለ መነጣጠል ይዘህ ከተነሣህ ጊዜ ሊፈጅብህ ቢችልም ባለቤትህንና ልጆችህን  ወደ ሕይወት መመለስህ አይቀርም። መጠንቀቅ የሚገባህ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለባለቤትህ ክፉ ወይም ያልተለመደ ደረቅ ቃል እንዳትናገራትና ፊትህንም እንዳታጠቁርባት ነው። ፫.  በእምነትህ ተስፋ ሳትቆርጥ ለቀጣይ ሕይወታችሁ መፍትሔ ማበጀት የእግዚአብሔር ቃል  "ዘመኑን እየዋጃችሁ ከሃይማኖት ወደ ተለዩ ሰዎች በማስተዋል ሂዱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንደምትመልሱ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን።" ይላል (ቈላስ. ፬፥፭-፯) እንደሚታወቀው ምንም እንኳን ጨለማ በአዳራሹ ውስጥ በአስፈሪነት ሞገሱ ነግሦ ቢኖርም ብርሃን ሲመጣበት ሥፍራውን ለቆ መሸሹ አይቀርም። ጨለማው ቀድሞ ቦታ ይዞ በመቀመጡ ፈርቶና ተስፋ ቆርጦ ሻማውን መለኮስ የሚያቆም የለም። አንተም ምንም እንኳን በቸልተኝነትህ ብትቀደምና ቢረፍድብህም አልመሸም። በቁጭት ከንፈር በመምጠጥ ያለፈውን በማማረር የሚባክን ጊዜ ሳይኾን ጠንክረህ በቁርጠኝነት ከሠራህ ዛሬም ገና ዕድሉና ተስፋው አለህ። ማንንም ሊቀድስ የሚችል፣ በምንም ነገር የማይረክስ፣ እውነት የኾነ፣ በማንኛውም ነገር የማይሸነፍ፣ ጨለማውን ሁሉ የሚገፍ፣ የሰይጣንን ወጥመድ የሚሰባብርና ከኀያሉ እግዚአብሔር ፊት የሚያቆም ሃይማኖት ባለቤት መሆንህን ማመን አለብህ። ከነቢዩ ከቅዱስ ዳዊትም ጋር አብረህ፦ "እግዚአብሔር ያበራልኛል፤ ያድነኛልም፤ ምን ያስፈራኛል? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ ምን ያስደነግጠኛል?" (መዝ. ፳፮፥፩) በማለት እየዘመርህ በኀይል ሳይኾን በጥበብ ሚስትህንና ልጆችህን ለመታደግና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመምራት የምትጀምርበት ጊዜ ሩቅ አይኾንም። እንደዚህ ያለ የትድግና መንፈሳዊ ተግባር ሲፈጸም መረሳት የሌለበት አንዱ ቁም ነገር አልጋ በአልጋ የሆነ መንገድ እንደሌለና ያለ ፈተናም አለመፈጸሙ ነው። ሰይጣን ዝም ብሎ ስለማያይህ የጠበቅሃቸውንና ያልጠበቅሃቸውን ልዩ ልዩ ፈተናዎች እያመጣ ተስፋ ቆርጠህ እንድትተወው ያለመሰልቸት ይዋጋሃል። በጸሎት፣ በጾም፣ በስግደትና በምጽዋት እግዚአብሔርን እየለመንክ፣  ወደ ገዳማት መባዕ በመላክ ገዳማውያን አባቶች በጸሎታቸው እንዲያስቡህ ማድረግና አንተም በጽናት መጋደል ይጠበቅብሃል። ፬. ንስሓ አባት በመያዝ በንስሓ መመላለስ የንስሓ አባት ከሌለህ ከአካባቢህ አጥቢያ የተሻለውን  ካህን በማድረግ በካህኑ ምክርና በጸሎቱ ከመጠቀም ጋር የአሸናፊነትን መንፈስና ኀይለ እግዚአብሔርን ለመታጠቅ ትችል ዘንድ ንስሓ ገብተህ ራስህን አንጻ። በቅርብ የምታገኛቸውን የቤተ ክርስቲያን መምህራን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የጠነከሩና ሊያግዙህ የሚችሉ የቤተ ዘመድ አባላትንና ጓደኞችህን በአጋርነት መጠቀም ብልህነት ነው። አቅም በፈቀደ መጠን በፍቅር ሆነህ በጉብኝት ስምም ቢሆን እያግባባህ ወደ ልዩ ልዩ ገዳማትና አድባራት ይዘህ በመሄድ በረከት እንዲቀበሉና የሚያዩትና የሚሰሙትም በልባቸው ጽላት እንዲታተም ዕድል መፍጠር ይገባል። ከምንም ነገር በፊት ግን አንተ በሃይማኖትህ ጸንተህ መቆም ይጠበቅብሃል። አሁንም ያ ቆሜአለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።" (፩ ቆሮ. ፲፥፲፪) እንደተባለ የሚቀድመው የአንተ በሃይማኖት ጸንቶ መገኘት ነው። ለዚህም በቃለ እግዚአብሔር ራስህን መገንባትና በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋት እንዲሁም ከላይ በተገለጹት መልካም ምግባራት ሁሉ መጠንከር ይኖርብሃል። ከእነዚህ ምግባራት ጋራ እግዚአብሔር በጥረትህ ውስጥ እንዲረዳህ በተቻለ መጠን በዕንባ (በለቅሶ) ድንግል ማርያምን በመማጸን ወደ እግዚአብሔር መጮህን አዘውትር። ለጊዜው ፈተናዎች ተነባብረው ቢያውኩህም በምንም ነገር ተስፋ ሳትቆርጥ ጸንተህ ከታገልክ የኋላ ኋላ ራስህን፣ ባለቤትህን. ልጆችህንና ቤተሰብህን የቅድስና ሕይወት ባለቤት ማድረግህ አይቀርም። እኛም ሐሳብህንና ፍላጎትህን ለማሳካት የምታደርገው ጥረትህ ለፍሬ ክብር እንዲበቃ ቅዱሳን በጸሎታቸው፥ እመቤታችን በአማላጅነቷ፥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በቸርነቱ ከአንተ ጋር ሆነው ይረዱህ ዘንድ ፈቃዳቸው እንዲሆን እንመኛለን።  
Read 683 times