ገንዘብ እንጂ ምግብ የማይፈልጉ ነዳያን
ምጽዋት ለሌሎች ቸርነትን ማድረግ በኢትዮጵያ በተለይም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስያን ምእመን እጅግ የለመደ ነው፡፡ “ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ በደቀ መዝሙሬ ስም ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ የሚያጠጣ እውነት እላችኃለሁ ዋጋውን አያጣም” ማቴ ፲፥፵፪ የሚለውን አምላካዊ ቃል ተግባራዊ በማድረግ በእመቤታችን፣ በቅዱሳን፣ በሰማዕታት፣በመላእክት ስም ጠበል ጸዲቅ አዘጋጅተው ለነዳያን በማብላት እና በማጠጣት ከእመቤታችን፣ ከቅዱሳኑ፣ ከጻድቃኑ በረከት ይሳተፋሉ፡፡ የተቸገሩትን መርዳት በእግዚአብሔርም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ምእመኑ ያለውን በማካፈል ከሌለው ላይ እንኳ ቀንሶ በመስጠት የታወቀ ነው፡፡ ምግብ፣ ልብስ ገንዘብ የመሳሰሉትን ለሌላቸው ይሰጣል፡፡ “ለድሃ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ እንደ ስጦታውም መልሶ ይከፍለዋል ” ምሳ ፲፱፥፲፯ እንዳለ ጠቢቡ ሀብታም ደሀ ሳይል ለድሆች ይመፀውታል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ እና ዘርፈ ብዙ ችግር ያለባቸውን ነዳያን ከነሱ የተሻለው የመርዳት ባህል በእጅጉ የተለመደ ነው፡፡
ለዛሬው የትዝብት ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወደ አራት ኪሎ በሚወስደው መንገድ ላይ ያየሁት እና የሰማሁት አጋጣሚ ነው፡፡ መንገዱ የዘወትር መንገዴ ስለሆነ በዚያ ሳልፍ መንገዱ ጠርዝ ላይ ተቀምጠው የሚለምኑ አንድ አዛውንት አያለሁ፡፡ ሁሌም ሳያቸው ያሳዝኑኛል ለራሴም “እኚህ አዛውንት በዚህ እድሜአቸው እዚህ ጎዳና ላይ መቀመጥ አልነበረባቸውም፤ ሲሆን ቤታቸው ተቀምጠው በስርዓት ቤተ ክርስቲያን እየተሳለሙ ሥጋ ወደሙን እየተቀበሉ መኖር ነበረባቸው” እላለሁ፡፡ ሁሌም ባይሆን አልፎ አልፎ ገንዘብ እሰጣቸዋለሁ፡፡ ያን የማደርገው ቢያንስ ምግብ ገዝተው ይበሉበታል ብዬ ስለማስብ ነው፡፡
አንድ ቀን ግን ከዚህ የተለየ ነገር ሲያደርጉ አየኋቸው፡፡ አንድ ሰው በፌስታል በፌስታል የተቋጠረ ምግም ይዞ ከዘንቢል እያወጣ በአካባቢው ለነበሩ ነዳያን ያድላል፡፡ የራሱን ድርሻ የተቀበለ አንድ ወጣት ድጋሚ ተቀበለና ወደ አዛውንቷ እየሮጠ መጣና “ይኸው አመጣሁልዎት” በማለት እጁን ወደ ርሳቸው ዘረጋ ከአዛውንቷ የተሰጠው መልስ ግን እጅግ አስደንጋጭ ነበረ፡፡ “ውሰድልኝ ወደዚያ አሁን በምኔ ልይዘው ነው” ብለው ተቆጡት፡፡ ጥሩ ነገር ያደረገ የመሰለው ወጣት በሀፍረት ሽምቅቅ ብሎ ሲመለስ አየሁት፡፡
ከአዛውንቷ በተሰነዘረው ቁጣ ያዘለ መልስ ወጣቱ ብቻ ሳይሆን እኔም አስደነገጠኝ፡፡ እኒህ ሴት ገፋፍቶ ጎዳና ላይ ያወጣቸው አንዳች ነገር አለ እሱም ችግራቸው ነው፡፡ ሰዎች ከሚቸገሩባቸው ነገሮች ውስጥ በተለይ ጊዜ ከማይሠጡ የሰው ፍላጎቶች ውስጥ አንዱና ዋንኛው ደግሞ ምግብ ነው፡፡ በእርግጥ ሰው የተለያየ ችግር ሊኖርበት ይችላል ነገር ግን ሚዛን የሚደፋው የምግብ ችግር ነው፡፡ ምግብ የሚገፋ ነዳይ ግን ምን ዓይነት ነዳይ ነው፡፡ ሊረዳው የሚፈልገውስ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ሰው እንዴት ነው ሊረዳው የሚችለው?
የኒህ አዛውንት ገጠመኝ መነሻ ሆነ እንጂ እንዲህ ዓይነት ትዕይንቶችን በየመንገዱ በተለይም በቤተ ክርስቲያን ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በዓላት በሚከበሩበት ቀን ምእመኑ በእመቤታችን፣ በቅዱሳን ፣ በመላእክት ስም ጠበል ጸዲቅ አድርጎ የሚመጣበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ምግብ ከሆነ ላለመቀበል የሚሸሹ አሊያም ተቀብለው እዚያው ጥለውት የሚሄዱ ነዳያን ጥቂት አይደሉም፡፡
በቀድሞው ዘመን ነዳያን ከረጢት ይዘው መንደር ለመንደር እየዞሩ በመልአኩ ወይም በቅዱሳኑ ስም የሚበላ እና የሚጠጣ ነገር ነበር የሚለምኑት፡፡ በምእመን ደጅ ቆመው ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው የተሰጣቸውን በከረጢታቸው ከተው ምእመኑን አመስግነውና መርቀው ነው የሚሄዱት፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ እንደነዚህ ዓይነት ነዳያንን መንደር ውስጥ ሲለምኑ ማየት አሁን አሁን ብርቅ እየሆነ ሄዷል ጭራሽ የሉም ማለት ይቀላል፡፡
እውነት ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ነች እናም ዛሬ ዛሬ በርከት ያሉ ነዳያንን በቤተ ክርስቲያን ደጅ ተኮልኩሎ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የሚመጡትም ከመጽዋቹ ደግ ሕዝብ ምጽዋትን ሊቀበሉ ነው፡፡ ሆኖም የተቸገረ ነው ብሎ ምግብ መስጠት ለአንዳንዱ ነዳይ እንደነውር የሚቆጠር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነዳያንን ማየት ደግሞ ለቸገረው ነዳይ ለመመጽወት እስኪያስቸግር ድረስ ሰውን ጥርጣሬ ውስጥ ይከታል፡፡ ደህነኛውን ከችግረኛው ለመለየት ያስቸግራል፡፡ በእነደዚህ ዓይነቶቹና ከምግብ ይልቅ ትኩረታቸውን በሙሉ ገንዘብ ላይ ባደረጉ ነዳያን ምክንያት ሊመጸወቱ የሚገባቸው ሰዎች ሳይመጸወቱ ይቀራሉ፡፡
እንዲህ ዓይነት ነገር ሲነሳ የሞላ ኑሮ ያላቸው ትርፍ ነገር ፍለጋ አደባባይ የሚወጡ ሀብታም ለማኞችም አሉ ፣ ዛሬ ዛሬ መለመን ሱስ ሆኖባቸው እግረ መንገዳቸውን የሚለምኑ ሰዎችንም እያየን ነው፡፡ የውሸት ምክንያት እየደረደሩ የሚለምኑ፣ የውሸት የህክምና ወረቀት ይዘው ለመድኃኒት መግዣ የሚሉ አልፎም በልመና ገንዘብ ጠርቀም አድርገው ወደ ሀገራቸው ለመመለስም ከጎዳና የወጡ አዛውንቶችን ማየት ዘወትራዊ ሆኗል፡፡ ከነዚህ መሀከል የትኛው ነው ትክክለኛ ነዳይ ብሎ ለመመጽወት ሰዎችን እየፈተነ ያለበት ዘመን ነው፡፡
ከነዳያን ጋር ተያይዞ ከዘጠኝ ዓመት በፊት አንድ ወዳጄ ያጫወተችኝን ገጠመኝ እዚህ ላይ ላንሳ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የሰሚስተር ወረቀቷን በልመና ግጥም ላይ ለመሥራት ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ አንድ ነዳይ ትቀርብና የልመና ግጥሞች እንዲነግራት እና በመቅረጸ ድምጽ ልትቀዳው ትጠይቀዋለች፡፡ “በአንድ ግጥም ስንት ትከፍዪኛለሽ ?”የሚል ፈጣን ጥቀያቄ ነበር የሰነዘረላት፡፡ ነገሩ የውጤት ጉዳይ በመሆኑ በግጥም ፳ ብር ልትከፍለው ተስማምተው ቤቱ ይቀጥራታል፡፡ በዕለቱ ምግብ አዘጋጅቶ ቡና አስፈልቶ ነበር የጠበቃት፡፡ ይህ አይደለም የገረማት ቤቱ ውስጥ ቴሌቭዥን ሳይቀር ሁሉ ነገር የተሟላ ነው፡፡ በጊዜው መንገድ ላይ የተደረተ ቡትቶ ለብሶ የሚለምነውን ይኽ ነዳይ ከኑሮው ጋር አልገናኝ ብሎአት ተገርማ ነበር ያጫወተችኝ፡፡
የኒህ አአዛውንት ገጠመኝ መነሻ ሆኖ አንዳንድ ገጠመኞችን አልፎ አልፎ አነሳን እንጂ ነዳያን አካባቢ ብዙ ነገሮች ይነሳሉ የዋሁ ምእመን የመጽሐፍ ቅዱሱን “ሁለት ልብስ ያለው ለሌላው ይስጥ፤ ምግብም ያለውም እንዲሁ ያድርግ፡፡” ሉቃ ፫፥፲፩ የሚለውን ቃል በማሰብ እና ጽድቅን ፍለጋ በግልም በሕብረትም ብዙ ነገር ያደርጋል ሆኖም ለምን ዓይነት ሰው ነው መመጽወት ያለብን የሚል ነው ጥያቄው፡፡
በዚያው መጠን የሚላስ የሚቀመስ ያጡ እየቸገራቸው ኢትዮጵያዊው ባህል ይዞአቸው እጃቸውን ለልመና ለመዘርጋት አፍረው በችግር የሚማቅቁ ብዙ ሰዎች በየቤቱ መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም ፤ በንጹህ ልብስ ውሰጥ ችግር ያቆራመዳቸው ፤ በእውነት ሊረዱ የሚገባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ የቸገረውን ከደኽነኛው ለመለየት እጅግ አስቸጋሪ ወቅት መሆኑን የምናየው እንዲህ ገሀድ የወጡ ገጠመኞችን ስናይ ነው፡፡ ሆኖም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ስላሉ በጅምላ በመፈረጅ እጃችንን ከምጽዋት ፣ ልባችንን ከመራራት ልንመልስ አይገባም፡፡