Tuesday, 24 November 2020 00:00

‹‹አክቲቪስቶቹ›› ካህናት 

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ

Overview

ይሄ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚባል ጉድ የስንቱን ጠባይ፣ፍላጎትና ገበና ገለጠው?! ሰው እንዴት ከልብሱ አልፎ ገላውን፣ ከገላው አልፎ ነፍሱን አራቁቶ ያሳያል?! ጎበዞች ሆይ! ማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ክብራቸው በነውራቸው እንዲሆን የመፍቀድ ልምምዳቸው ማሳያ አደባባይ እየሆነ መምጣቱን እንደ እኔ አስተውላችሁ ይሆን! ሞራል፣ ሥነ ምግባር፣ ሕግ በይፋ ሲሰባበሩ የሚታይብት የፍልሚያ ሜዳ አይታያችሁም? ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሳየን የሁሉንም ገመና ሆኗል፤ የሴቱን ብቻ አይደለም፤ የወንዱንም ነው፤ የደቂቁን ብቻ አይደለም የልሂቁንም ነው፤ የኢ-አማኒውን ብቻ አይደለም የምእመኑንም ነው፤ ያልተማረውን ብቻ አይደለም የተማረውንም ነው፡፡ እረ ስንቱን! በየቤቱ ቤተሰብ የቻለው ጉድ አሁን የሁሉም ሕዝብ ሆኖ ማኅበረሰብ እንዲሸከመው ሆኗል፡፡ አሁን በቤተሰብህ ብቻ ሳይሆን በጎረቤትህ አመል ትታወካለህ፡፡ ይሄ ጉድ ሄዶ ሄዶ ከቤተክርስቲያን ቄሱን፣ ዲያቆኑን፤ ከገዳም መነኮሳቱን መንካቱ ደግሞ ‹‹የቤቴው ጉድ›› እንድል አስገድዶኛል፡፡ የዛሬም ትዝብቴ ከብዙ ኃላፊነት ተሰምቷቸው የእግዚአብሔርን አደራ ጠብቀው ቀን ከሌት ስለሕዝባቸው በመንፈስ ሲጋደሉ ከሚኖሩ ካህናት ተርታ ወጥተው ‹‹አክቲቪስት›› ስለሆኑ ጥቂት ካህናት ነው፡፡ ሌት ከቀን በማኅበራዊ ሚዲያ ዕድሎቻቸው መልካሙን ዜና ከሚያወሩና ከሚነግሩን ብርቱ አገልጋይ መምህራን ይልቅ ጥቂት ‹‹አክቲቪስት›› ስለተባሉ አገልጋዮች ነው፡፡ 

 

መቼም ካህናት እና የእግዚአብሔር አገልጋዮች እናንተ ‹‹የምድር ጨው ናችሁ›› ብሎ አልጫውን ዓለም እንዲያጣፍጡ የታዘዙ ሆነው ሳለ፤ እነዚህ ጥቂት ‹‹አክቲቪስት›› ካህናት አልጫነቱ እየባሰበት ከመጣው ዓለም ጋር አብረው የጨውነት ክብርና መዓርጋቸውን ማውለቃቸውን ያየንበት አንዱ መድረክ ይሄው የማኅበራዊ ሚዲያ ከሆነ ሰነባበተ፡፡ ‹‹ጨው አልጫ ቢሆን በምን ይጣፍጣል?›› ይልሃል ይሄው ነው፡፡ 

ካህናት ‹‹የእግዚአብሔር ዓይኖች›› ናቸው፤ ሰውን ሁሉ እንደ ፈጣሪው በእኩልነት የሚያዩ  የእርሱም እንደራሴ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፤ አንዱን ሰው ከአንዱ አስበልጠው ሲያሞግሱ ሲያወድሱ፣ ሲከሱ ሲወቅሱ ያየናቸው  ‹‹አክቲቪስት›› ካህናት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቍጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ በየኪሱ ዘውድ ይዞ ከሚዞረው እገሌ ወይም እገሌ ከሚባለው የፖለቲካ ወገን ጋር እየወገኑ አንዱን ሲያነሡ፣ ሌላውን ሲከሰክሱ አይተናል፡፡ አንዱን ቋንቋ ተናጋሪ ከሌላው ቋንቋ ተናጋሪ ለይተው ሲክቡ ሌላውን ሲያዋክቡ አይተናል፡፡ የአንዱን  ባህልና ታሪክ ከሌላው ባህልና ታሪክ እያበላለጡ ሲያራክሱ ወይም ሲቀድሱ አይተናል፡፡ የእነዚህ ‹‹አክቲቪስቶች›› ዓዕይንተ እግዚአብሔርነት ወዴት አለ! ‹‹እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።›› /ሮሜ 2፥11/ እጅግ አስገራሚው ነገር እነዚህ ወገኖች የእኛ አይደሉም እንዳንላቸው የሃይማኖት ካባ አጥልቀዋል፤ ነገር ግን መሸ፣ ነጋ ብሎ ቤተክርስቲያን የምትናፍቀውን ምእመን የእነሱ የማኅበራዊ ሚዲያ ጩኸት እንዲናፍቀው ይሠራሉ፡፡ ‹‹አክትቪስት›› ካህናቱ ከምእመኑ ፊት ተደንቅረው ቤተ መቅደሱን እንዳያይ፣ ምዕመኑን ከሃይማኖቱ አፋተው የዩቲዩብ የገንዘብ ምንጭ አድርገውታል፤ ሐዋርያው እንዳለ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች እየሆኑብን ነው፡፡ 

አገልጋይና የቤተክርስቲያን ባለውለታ ተደርገው ሲታሰቡ ቆይተው ያገኙትን አንቱታቸውን፣ ታዋቂነታቸውን ተጠቅመው ሕዝበ ክርስቲያኑን ወደ ገደል ስለሚገፉ ዓለምን ከነትብታቧ ጎትተው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስላስገቡ ስለእነዚህ ወገኖች ወይም ‹‹አክቲቪስት›› ካህናት ምን እንበል?

የእግዚአብርሔርን ቃል እንደሚሸቃቅጡት ተብሎ እንደተጻፈ ወንጌልን ሊሰማቸው ልቡን ሰጥቶ ጆሮውን ከፍቶ ለሚያዳምጣቸው የዋህ ምእመን ፖለቲካውን ከወንጌል መሳ ለመሳ አድርጎ በማቅረብ የቤተ ክርስያንን ፍቅር የተሞላበት የአገልግሎት መንገድ በጥላቻና መለያየት እየተኩ ስላሉ አክትቪስት ካህናትስ ምን እንበል? ግራ ገባን እኮ!

ካህናት ለቤተክርስቲያን አንድነት ሲሉ ራሳቸውን ያስጨንቃሉ እንጂ ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል እንዴት ይጨነቃሉ፤ በሚለጥፉት ፎቶ፣በሚጽፉት ጽሑፍ፣በሚናገሩት ቃል፣ በሚሰጡት አስተያየት የአንዱን ቍስል ሲታመሙለት በአንዱ ቍስል ደግሞ እንጨት ሲሰዱበት የሚያዩስ አሕዛብ ስለቤተከክርስቲያን ምን ይላሉ? ‹‹በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ።›› /ሮሜ ፪፥፳፬/፡፡

ስለሰው ሁሉ መከራ ማልቀስ የሚገባቸው እነዚህ ካህናት በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚናገሩት ቃልና ጽሑፍ የሚያስለቅሱት እንዳለ እንዴት አላስተዋሉም፡፡ የሚደግፉት የፖለቲካ ቡድን ጫፉ ከሚነካ ቤተክርስቲያን ብትንካካ የማይገዳቸው መሆናቸውን በሚያነክስ ቃልና ጽሑፎቻቸው ውስጥ ብዙ ታዝበናል፡፡ የሚችሉትን መክረው፣ የማይችሉትን ለእግዚአብሔር በጸሎት አሳስበው መልካሙ እንዲመጣ ማድረግ ሲገባቸው ‹‹እገሌ ይታሰር፣ እገሌ ይሰቀል፣ እገሌ ይውረድ፣ እገሌ ይውጣ፣ እገሌ ይምጣ፣›› ሲሉ የሚውሉ እነዚህ ‹‹አክቲቪስቶች›› እርስ በእርስ እንኳን በሐሳብ አንድ ሆነው አለመገኘታቸው እንደውም በተቃራኒ ጎራ ሆነው መፋለማቸው ምን ያህል ሐሳባቸው ምድራዊ እንደሆ ለትዝብት አይዳረጉም ትላላችሁ!

የእነዚህ ‹‹አክቲቪስቶች›› ክህነታቸው ከአንድ ቤት ከአንድ መንፈስ ይቀዳል፤ የተሰጣቸውን ጸጋና ኃላፊነት ግን ስለረሱ አንድ ሐሳብ አንድ ልብ የላቸውም፤ አንዱ ከሰሜን ሆኖ የደቡቡን ያሳምማል፤ አንዱ ከምሥራቁ ሆኖ የምዕራቡን ያቃልላል፡፡ ያነሣሣል፤ ያጋግላል፤ ያጋድላል፡፡ ፍቅርን ከሚያመነጭ ከክርስቶስ የክህነት ጸጋ ጥላቻ እንዴት መነጨ! አንድነትን ከሚያመንጭ ከክርስቶስ የክህነት ጸጋ መለያየት እንዴት መነጨ? ‹‹እኛስ የክርስቶስ ልብ አለን›› ብለው ሰብከው ሲያበቁ፤ ዓለምን በሚያዩበት መነጽር ግን እንዴት በውስጠቸው ያለውን የክርስቶስን ልብ ከፋፈሉት? ‹‹ ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ›› /፩ኛ ቆሮ ፩፥ ፲፫/ 

እውነትን አይተው እንደሚፈርዱ፣ ስለእውነትና ስለፍትህ እንደሚቆሙ እያስመሰሉ የሥጋ መሻታቸውን በፌስ ቡክ ገጾቻቸው፣ በቴሌግራም ቻናላቸው ሲለቁ ማየት እጀግ ያሳዝናል፡፡ ሰዎችን ማጣላታችን አንድ በደል ነው፤ መታረቅ እስከማይችሉበት ጥግ ወስዶ፣ በክፉ ሐሳብ ግራና ቀኝ ሆኖ መረጫጨት ግን የበለጠ አሳዛኝ ነው፡፡ ካህናት እስከ ደም ድረስ ለማስታረቅ ይጋደላሉ እንጂ እንደ እነዚህ ጥቂት ብልጣብልጦች ለማጣላት አይተጉም፡፡ ካህናት የሰውን ክፉ መንፈስ ያሳድዳሉ እንጂ በእነርሱ ምክንያት ሰው ከቤተክርስቲን እንዲሰደድ ማድረግ ሌላ ነገር ነው፡፡ ይህ በእውነት ምን እንለዋለን? ጀግንነት ነውን? ሰማዕትነት ነውን? ፍርድ አዋቂነት ነውን? የሰላም ሰባኪነት ነውን? በእነዚህ ጥቂት ‹‹አክቲቪስት›› ካህናት ምክንያትስ የሚጎድፈው የካህናት መልክ ታስቧቸው ያውቅ ይሆን? እነዚህ ጨለምተኛ ካህናትስ ተስፋን ከምትሰብክ ቤተክርስያን ማሳያ ሆነው መገለጣቸው ለምን ያህል ጊዜ ዕዳ ሆኖ ያቆይብን ይሆን? እርሱ ይወቀው፡፡

እና ምን እናድርግ ለሚሉንም ያለን የመፍትሔ ሐሳብ እንደ እውነተኛ ካህን ሁሉን እናገልግል፤ በማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀምን መሸሽ ሳይሆን ለሁሉ የሚጠቅም ሁሉን የሚገዛ ሐሳቦችን እናንሸራሽር፤ የሚዲያ ዕድላችንን ለሁሉ መድኃኒት የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ በየቋንቋው እናድርስ፡፡ ከሥጋ ለባሽ ሰው ይልቅ መንፈስ ከሆነው ሰይጣን ሥራና ሐሳብ ጋር እንዋጋ፡፡

 

መነሻዬ እነርሱን መጥላት አይደለም፤ ምኞቴ የእነርሱ ጥፋት አይደለም፤ ሐሳቤ ለእነዚህ አክቲቪስት ካህናት ‹‹ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም።›› /፪ኛ ጢሞ ፬፥ ፭/፤ ዳግመኛም ‹‹የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም።›› /፪ኛ ጢሞ ፪፥ ፳፬/  ያለውን የሐዋርያውን ቃል ማስታወስ ብቻ ነው፡፡ ሰላሙን ይስጠን፡፡ 

 

Read 931 times