Tuesday, 24 November 2020 00:00

‹‹ከልክ ያለፈ ፍርሀት ሕይወቴን ተፈታተናት››

Written by  ከዝግጅት ክፍሉ

Overview

የተወደደዳችሁ የስምዐ ጽድቅ አዘጋጆች እንደምን አላችሁ? ከሰላምታዬ በመቀጠል የማካፍላችሁ ችግሬ እንዲህ ነው፦ ስሜ ክንፈ ሚካኤል ይባላል፤ ዕድሜዬ ሠላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡  ‹‹ከልክ ያለፈ ፍርሃት ሕይወቴን አስቸጋሪ እያደረገብኝ ነው››፡፡ ምንም እንኳን ንስሓ አስፈላጊ እንደሆነ ባውቅም ወደ አባቶች ቀርቤ ኃጢአቴን መናዘዝ እየፈለኩ ግን በፍራቻዬ የተነሣ አልቻልኩም፡፡ ከሰዎች ጋር አብሬ ጊዜ ለማሳለፍም እፈራለሁ፤ ከዚህ በተጨማሪም ጋብቻን ለመመሥረት ሀሳቡና ፍላጎቱ ቢኖረኝም ግን ሴቶችን መቅረብ እፈራለሁ፡፡ በመሆኑም ፍርሃት በሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወቴ ላይ ተጽእኖ አሳድሮብኛል፡፡ ከዚህ ችግር ነጻ ለመውጣት ብጸልይም መፍትሔ አላገኘሁም፤ አሁን አሁን ጭንቀት እየተሰማኝ ነው፤ ታዲያ ከዚህ ችግር እንዴት መውጣት እችላለሁ፡፡  ውድ ወንድማችን ክንፈ ሚካኤል በቅድሚያ ታሪክህን ስላካፈልከን እናመሰግናለን፤ ይህ ዓይነቱ ታሪክ የሌሎች እኅቶች እንዲሁም ወንድሞች ሊሆን ስለሚችል እና አስተማሪ በመሆኑ ለዚህ ዝግጅት እንዲስማማ አድርገን አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ፡፡ ፍርሃት ስሜት እንደመሆኑ መጠን ሰው ሆኖ የፍርሃት ስሜት የማይሰማው የለም፡፡ ነገር ግን ከልክ ያለፈ ፍርሃት የሰውን ሕይወት አስቸጋሪና ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ከልክ ያለፈ የፍርሃት ስሜት የሚሰማን ከሆነ በሕይወታችን ላይ ከሚያስከተለው ተጽዕኖ ነጻ ለውጣት መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ 

 

የፍርሃት ስሜት ሁሉ በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ አንጻራዊ  መጠነኛ  ፍርሃት  ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ፍርሃት ጠቃሚ  ነው ሲባል ሰው ራሱን  በሕይወቱ ሊያጋጥሙት ከሚችሉ  አሉታዊ ሁኔታዎች ለመከላከል ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችለው ተፈጥሮዊ ስሜት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ የፍርሀት ስሜት የራሱ ጥቅም አለው የሚባለው ሰው በአካባቢው ሊያጋጥሙት ከሚችሉ ውጫዊ እና ውስጣዊ  ችግሮች ራስን ለመጠበቅ የሚያስችል ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ በተለየ  ከልክ ያለፈ ፍርሃት ግን ሰው ሊያጋጥመኝ ይችላል ብሎ ለሚያስበው አሉታዊ ሁኔታ ራሱን እንዳያዘጋጅ ያደርጋለል፡፡ በሰው ሕይወት ላይ አሉታዊ የስሜት ጫና በመፍጠር ጉዳት ያስከትላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ከልክ ያለፈ ፍርሃት ማጣት ደግሞ ሰው ሊመጣብኝ ይችላል ብሎ ለሚገምተው አሉታዊ ሁኔታ ራሱን እንዳያዘጋጅ ስለሚደርገው በሰው ላይ የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የባለታሪካችንን ሕይወት ስንመለከት ከልክ ያለፈ ፍርሃት ሕይወቱን ተቆጣጥሮት እንመለከታለን፡፡ ገና ለገና ኃጢአቴን ብናዘዝ ምን ይሉኛል፤ ከሰዎች ጋር ብቀራረብ መዝነውኝ ብቀልስ፤ልቤ የፈቀዳትን ሴት ለጓደኝነት ጠይቄያት እሺ ባትለኝስ በሚሉ የፍርሃት ስሜቶች መፈጸም ያለበትን ተገቢ ነገር እንዳይፈጽም እያደረገው ነው፡፡ ስለዚህ የትኛው ፍርሃት ተገቢ እንደሆነ የትኛው ፍርሃት ተገቢ እንዳልሆነ መለየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ 

ተገቢ ያልሆነ ፍርሃት

አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ‹‹ሥጋችሁንም የሚገድሉትን አትፍሩአቸው፤ ነፍሳችሁን ግን ሊገዱሉአት አይችሉም፤ ነገር ግን ነፍስንም ሥጋንም አንድ አድርጎ በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን እርሱን ፍሩት›› ብሎአቸዋል (ማቴ፲፥፳፰) ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ይህን የተናገረው ማንን መፍራት አንዳለብን እንድንረዳ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን ግን ሰው እንዲህ ሊለኝ ይችላል ወይም እንዲህ ሊከሰት ይችላል ብለን  ባልተጨበጠ ነገር እንፈራለን፡፡ በእርግጥ እኛ ሙሉ በሙሉ ከፍርሀት ስሜት ነፃ ለመሆን እንቸገር ይሆናል ነገር ግን ከልክ ያለፈ ፍርሃት ሊሰማን ግን አይገባም፡፡ 

ብዙ ጊዜ  በሥጋ የሆነ ፍርሃት ይሰማናል፤ ይህ ፍርሃት ሰው ሕገ እግዚአብሔርን መተላለፉን ተከትሎ የመጣ እንጂ በጥንተ ተፈጥሮ የነበረ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡  ነገር ግን ከዚህ አይነቱ ያልተገባ ፍርሃት ነጻ መውጣት እንደሚቻል ልናምን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እኛ ክርስቶስ በሞቱ የዳንን፤ የሞተልንን አምላክ በእምነት የምናውቅ ክርስቲያኖች ነን ‹‹እመን ብቻ እንጂ አትፍራ›› (ማር. ፭፥፴፮) እንደተባለ ጽኑ እምነት ያለው ሰው ያልተገባ ፍርሃት አይገዛውም፡፡ 

አስቀድሞ ሰዎች እንዲህና አንዲያ ይሉናል፤ አንዲህና እንዲያ ያደርጉናል በሚል ያልተጨበጠ የፍርሃት ስሜት ውስጥ ልንኖር አይገባም፡፡ እኛ በቻልነው መጠን  ምንን እና ማንን መፈራት እንዳለብን ተረድተን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ የፍራቻችን መነሻ ምክንቶች በአስተዳደጋችን ወቅት በሚያጋጥም ጉድለት፤ ከአእምሮ ጤና ጋር የተያያዘ፤ከመንፈሳዊ ሕይወት ጉድለት የተነሳ ሊሆን   ይችላል፡፡ ባለታሪካችን ፍርሃትህ መነሻ የቱም ይሁን ካህናት አባቶችን፤ሴት እኅቶቻችንንና ሌሎች ሰዎችን መፍራትህ ተገቢ ቢሆንም ሰዎችን ማክበር እንጂ መፍራት አይገባም፡፡ ከሁሉ በላይ ተገቢው ፍርሃት የቱ እንደሆነ ልታውቅ ልትረዳ ይገባል፡፡

ተገቢ የሆነ ፍርሃት

ፍርሃታችን ተገቢ የሚሆነው ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን ስንፈራ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ›› (መዝ. ፪፥፲፩) ብሎ የተናገረው ለእግዚአብሔር በፍርሃት በመገዛታቸን ተገቢ ና ዋጋ ያለው በመሆኑና ደስ ሳይሰኙ መገዛት ዋጋ ስለማያሰጥ ደስ ልንሰኝ ይገባል ሲለን ነው፡፡ ነቢዩ ይህንን የተናገረው ተገቢ የሆነው እግዚአብሔርን መፍራት ክፉ ከመስራት እንድንርቅ ፤ መልካም ለመስራት እንድንበረታ ስለሚያደርገን ነው፡፡  

እግዚአብሔርን መፍራት ተገቢና ጥበብም መሆኑን ሰሎሞን ሲናገር ‹‹ነገር ግን እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ናት›› (ምሳ ፩፥፯) ይላል  ፡፡እግዚአብሔርን የምናከብረው አክብሮት፣ የምንፈራው ፍርሃት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው እንጂ እንደ ምድራዊ ንጉሥ ያጠፋኛል፤ ይቀጣኛልም ብለን እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል፡፡  እንዲሁም ደግሞ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም ፍርሃት ቅጣት አለውና የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም ይላል (፩ ዮሐ. ፬፥፲፰፣ ምሳ. ፩፥፯) ፡፡ ባለታሪካችን ኃጢአቱን ለመናገር ፍርሃት አለበት ይህ ደግሞ ተገቢ ፍርሃት አይደለም፡፡ ‹‹ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል፡፡ ›› ምሳ ፳፰፥፩፫

ያልተገባ ፍርሃትን  እንዴት ማስወገድ ይቻላል?

አንድ ሰው የሚሰማውን ያልተገባ የፍርሃት ስሜት በግልጽ ከተረዳ እና የዚያ ስሜት  መንስኤው ምን እንደሆነ መረዳት ሲችል ችግሩን ለማስወገድ እምብዛም አይቸገርም፡፡ ውድ ወንድማችን ከጽሑፍህ መረዳት እንደቻልነው ከልክ ያለፈ የፍርሃት ስሜት እንዳለብህና ይህ የፍርሃት ስሜት ያስከተለብህ ችግሮች መኖራቸውን ነው፡፡ በእርግጥ የሚሰማህ ተገቢ ያልሆነ የፍርሃት ስሜት ነው፡፡ ከዚህ የፍርሃት ስሜት ለመውጣት ደግሞ ችግሩ አንዳለብህ ማመንህ መልካም ጎን ሲሆን ከዚህ ችግር መውጣት እንደምትችል፣ ለዚህም የእግዚአብሔር ተራዳኢነት በማመን እርሱን ተስፋ ልታደርግ ይገባል፡፡

ውድ ወንድማችን ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ሰው እግዚአብሔርን ከማፍቀር የተነሳ እንደ አባትነቱ ሊፈራው ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ፍርሃት ደግሞ ተገቢ የሆነው ፍርሃት ነው፡፡ ነገር ግን ኃጠአትህን ለመናዘዝ፤ ራስህን ለካህን ለማሳየት መፍራትህ ተገቢ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ መረዳት ያለብህ ኃጢአት ሰውን ከእግዚአብሔር የሚለይ ትልቅ ግድግዳ ነው፡፡ በመሆኑም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ዳግም ኅብረት እንዲኖረው በንስሓ ሊመለስ ይገባል፡፡ 

ወንድማችን ክንፈ ሚካኤል አንተ  በንስሓ መመለስ ተገቢ መሆኑን አውቀህ  ኃጢአትን ለመናዘዝ ግን መፍራትህ የእግዚአብሔርን ቸርነት ርኅራኄ አለመረዳት ነው፡፡  ለዚህ ነው ሐዋርያው ‹‹አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና›› (ሮሜ  ፰፥፲፭)  በማለት የእግዚአብሔርን አባታዊ ፍቅሩን እንድንረዳ የሚስገንዝበን፡፡ አንተም የእግዚአብሔር ፍርዱን ብቻ ሳይሆን አባታዊ ፍቅሩን ዘወትር ልታስብ ያስፈልጋል፡፡ እርሱ የሰጠን እኛም የተቀበልነው መንፈስ ያልተገባ ፍርሃት እንድንፈራ የሚያደርገን አይደለም ‹‹እግዚአብሔር የኃይልና የንጽሕና፥ የፍቅርና የጥበብ መንፈስን እንጂ የፍርሃት መንፈስን አልሰጠንምና።›› ( ፪ኛ ጢሞ. ፩፥፯) ስለዚህ  እግዚአብሔርን ከፍቅር በመነጨ ፍርሃት ልትቀርበው እንጂ ገና ነገና በኃጢአትህ አፍረህና ኃጢአትን መናዘዝ እስከመፍራት በሚያደርስ ከልክ ባለፈ ፍርሃት ውስጥ መኖር የለብህም፡፡ 

አሁን ካለህበት ሁኔታ ለመውጣት የአንተ ጥረት እና መልካም ሐሳብ እንዳለ ሆኖ ሐሳብህ ወደ ተግባር የሚለወጥበትን መንገድ ማመቻቸት አለብህ፡፡ ለዚህም የንስሓ አባት ከሌለህ አንድትይዝ ካለህ ደግሞ ቀርበህ የሚሰማህን የፍርሃት ስሜት ለንሰሐ አባትህ በመንገር ፣ ምክር መቀበል ፣ መጾም እና መጸለይ በሕይወትህ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ ከንስሓ አባትህ ተከታታይ የሆነ የምክር አገልግሎት ብታገኝ ካለህበት ችግር ለማገገም ብሎም ዘለቄታዊ መፍትሔ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ 

ሌላው ባልተገባ ፍርሃት ምክንያት ልብህ የፈቀዳትን ሴት ቀርበህ የልብህን ሐሳብ መናገር እንዳልቻልህ ገልጸህልናል፡፡ ቅድመ ጋብቻ ጓደኝነት ለመጀመር ስታስብ ጋብቻን ዓላማ አድርገህ መጀመር አለብህ፡፡ ትውውቅ፤የጓደኝነት ጥያቄ ማቅረብ ፤መጠናናት፤መተጫጨት በቅድመ ጋብቻ ውስጥ ያሉ ሂደቶች ናቸው፡፡ አንተ ገና በትውውቅ ደረጃ ላይ የተቸገርህ ስትሆን ለዚህም አስቀድመህ የሥነ-ልቡና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብሀል፡፡ አንተ ውስጥ የፍርሃት ስሜት እንዲፈጠር ከሚያደርጉ ሐሳቦች መካከል ምናልባት ጠይቄ እሺታዋን ባላገኝ፤ ጓደኛ ቢኖራትስ፤እሷ በወንድምነት ብቻ ምታስበኝ ከነበረስ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ፍቃዷን ስትጠይቅ መልሷ አሺታ ሊሆንም ላይሆንም እንደሚችል ራስህን በሥነ ልቡና ልታዘጋጅ ይገባል፡፡ስለዚህ ፍቃዷን ማወቅ የምትችለው ደግሞ ስትጠይቅ ብቻ ነው፡፡ ከአንተ የሚጠበቀው በጨዋ ደንብ ጥያቄህን ማቅረብ ብቻ ነው፤ ቀሪው የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ አንድ ጊዜ አልሆነም ማለት ደግሞ ሁልጊዜ አይሆንም ማለት አይደለም፡፡ ልብህ የፈቀዳት ሴት ስታገኝ ከክርስትና መንገድህ የማታሰናክልህ እስከሆነች ድረስ ጥያቄ ለማቅረብ ልትፈራ አይገባም፡፡ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።››  (ኢሳ. ፵፩፥፲) ሐሳብህ በጎ እስከሆነ ድረስ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንደሆነ ካመንህ ካልተገባ የፍርሃት ስሜት ሊሰማህ አይገባም፡፡  መፍራት አንድም የእምነት ጉድለት ነው፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ላይ ያለህ እምነት ሊያድግ  ይገባል ‹‹እግዚአብሔር ያበራልኛል፤ ያድነኛል፤ ምን ያስፈራኛል? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ ምን ያስደነግጠኛል? ... በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሸሽጎኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሰውሮኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና።›› (መዝ. ፳፮፥፩-፭) ብለህ ዘወትር ልትጸልይ ይገባል፡፡ 

ሌላው ባለታሪካችን ያልተገባ የፍርሃት ስሜት ማኅበራዊ ሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮብሀል፡፡ ክርስትና በተግባር ከሚገለጥባቸው ዐውዶች አንዱ ማኅበራዊ ኑሮ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከሰዎች ጋር አብሮ ለመሆን የፍርሃት ስሜት ቢሰማህም ሰውን መፍራት ተገቢ እንዳልሆነ ተረድተህ ዘወትር ‹‹እኔ ግን በአንተም ታመንሁ። በእግዚአብሔር ቃሉን አከብራለሁ፤ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?›› መዝ. ፶፮፥፫-፬ የሚለውን የመዝሙረኛውን ቃል አስብ፡፡ ሰዎች አንተን ምንም እንደማያደርጉህ እመን፤ ቀስ በቀስም ከሰዎች ጋር በመቀራረብ ማኅበራዊ ግንኙነትህን ልታሻሽል ትችላለህ፡፡ 

በአጠቃላይ ፍርሃት በራሱ መልካም ወይም ክፉ አይደለም፤ ማንን ነው የምንፈራው? ለምንድን ነው የምንፈራው? የሚሉት ጥያቄዎች ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ከታሪክህ እንደተረዳነው ፍርሃትህ ተገቢ አንዳልሆነ ነው፡፡ አስቀድሞ ከዚህ ስሜት በቅጽበት ነጻ መውጣት እንደማይቻል ልትረዳ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በሂደት ተስፋ ሳትቆርጥ በእምነት ነጻ መውጣት ትችላለህ፡፡ ለዚህም በእግዚአብሔር ላይ ያለህ እምነት ሊያድግ እንደሚገባ ተረድተህ፤ ዘወትር በሃይማኖት ጸንተህ፤ በምክረ ካህን ተደግፈህ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ እያደረግህ ልትጠባበቅ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር

 

Read 2099 times