Tuesday, 24 November 2020 00:00

ደጉ ሳምራዊ

Written by  ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ
የተወዳዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከርማችኋል? በእግዚአብሔር ቸርነት በሰላምና በጤና እንደቆያችሁን ተስፋ እናደርጋለን፤ ትምህርታችሁን በንቃት በመከታትል በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋልና በርቱ! ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ታሪክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አንድ ደግ ሳምራዊ ለአንድ ሕግ አዋቂ በምሳሌ ያስተማረውን ትምህርት ነው፤ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!        አንድ ቀን አንድ የሕግ ባለሙያ ጌታችን ኢየሱስን ሊፈትነው ቀርቦ «መምህር ሆይ የዘላለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ልሥራ (ላድርግ)? ሲል ጠየቀው፡፡»  ጌታችንም ለሕግ ዐዋቂው «በሕግ በመጽሐፍ የተጻፈውን አንተ እንዴት ታነባለህ?» ብሎ ጠየቀው፤ ሕግ ዐዋቂውም ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣  በፍጹም ኃይልህም፣  በፍጹም ሐሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም  እንደራስህ ውደድ»  በማለት መለሰለት፡፡ ጌታችንም ለሕግ ዐዋቂው «እውነት መለስህ፡፡ የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት በሕይወትም ለመኖር ከፈለክ ጌታ አምላክህን በፍጹም ነፍስህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ» አለው፡፡   

 

በዚህን ጊዜ ጌታችን ራሱን ከፍ አድርጎ ሌላውን ንቆ ጥያቄ ላቀረበው ሕግ ዐዋቂ ባልንጀራው ማን እንደሆነ እንዲረዳ እና ምን ማድረግ እንዳለበት የሚከተለውን ታሪክ በምሳሌ ሊነግረው እንዲህ  በማለት ጀመረ፡፡ 

በአንድ ወቅት አንድ ሰዉ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ተጓዘ፡፡ በጒዞውም ሳለ በድንገት ወንበዴዎችና ሽፍቶች አገኝተውት መጥተዉ አስቆሙት:: ገንዘቡን ወሰዱ፤ ልብሱንም ገፈፉበት፤ ደብድበዉም፤ አቊስለው ሊሞት ሲቃረብ በመንገድ ላይ ጥለውት ሔዱ፡፡                                          

አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲሔድ ያን ተደብድቦ የወደቀውን ሰው ቀርቦም ቢያየው ተጎድቷል፤ ነገር ግን ሳይረዳዉ አልፎ ጥሎት ሔደ፡፡

ከካህኑ ቀጥሎ ደግሞ አንድ ከሌዊ ወገን የሆነ ሰው በዚያ መንገድ ሲያልፍ በወንበዴዎች ተደብድቦ የወደቀዉን ሰዉ አገኘው እና አየዉ:: ነገር ግን እርሱም ሳይረዳዉ ዝም ብሎ በመንገድ ላይ እንዳየው እንደቀደመው ካህን ሌዋዊውም ገለል ብሎ አልፎት ሔደ::

ሦስተኛ አንድ ሳምራዊ በዚያች መንገድ ሲሄድ አገኘው፤ አይቶም አዘነለት፤ ወደ ቈሰለው ቀርቦ በቊስሉ ላይ እንዲያደርቅለት ወይን አደረገለት፤ እንዲያለሰልስለት ደግሞ ዘይት በቊስሉ ላይ አፈሰሰለት፡፡    

ደጉ ሳምራዊው የተደበደበውን ተጓዥ ሰው ቅርብ ወዳለው እንግዳ ማረፊያ ስፍራም ከአስገባው በኋላ እየተንከባከበዉ፣ እያስታመመውና የሚፈልገውን እያደረገለት አብሮት በሰላም አደሩ፡፡

በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዶች ማረፊያ ማደሪያ ወይም ማደሪያ ቤት ባለቤት ኃላፊ ለሆነው ሰው ሰጠዉ፡፡ ከሰጠዉም በኋላ ይህን ሰው ተንከባከብልኝ «የምትከስረዉን ሁለ እኔ ስመለስ እከፍልኀለው» ብሎ የተደበደበውን ሰው አደራ ሰጥቶት ወደ ሌላ ስፍራ ሔደ፡፡                                

ልጆች! የጌታችንን ምሳሌውን እየተከታተላችሁ ነው አይደል? መልካም! ታዲያ ለዚህ ተደብድቦ በመንገድ ላይ ለወደቀዉ ሰዉ ባልንጀራዉ የሆነለት የትኛዉ ሰው  ይመስላችኀኋል?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሳሌውን ታሪክ የእግዚአብሔርን ሕግ ዐዋቂ ለሆነው ሰው ነግሮ ከጨረሰ በኋላ «ከእነዚህ ከሦስቱ ከካህኑ፣ ከሌዋዊዉ እና ከሳምራዊዉ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀዉ  ባልንጀራ የሆነዉ ማንኛዉም ይመስልሃል?» ሲል የሕግ ዐዋቂዉን ጥያቄ ጠየቀዉ:: 

እርሱም «ምሕረት ያደረገለት ነው» ብሎ መለሰለት፡፡

ጌታችን ኢየሱስም ሕግ አዋቂ ለሆነው ሰው እንዲህ አለው «አንተም የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ፣ በሕይወት ለመኖር ሕግን ማወቅ፣ ስለ ፈጣሪ ሕግ መናገር ፣ለሚጠየቁ ጥያቄዎች መልስን መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሳምራዊዉ ሰዉ የአንተን እርዳታ ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው መልካምን አድርግ» በማለት ነገረው፡፡ 

«የወደቁ ሰዎችን እርዳ፣ ምሕረት አድርግ፣ ተንከባከብ፡፡ ባልንጀርነት ማለት ምሕረት ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሒድ አንተም እንደ ሳምራዊው ምሕረት አድርግ በሕይወት ትኖራለህ» አለው፡፡ (ሉቃ. ፲፥፴፫-፴፯) 

ልጆች!  ሳምራዊው እንደተመለከትነው በመንገድ ላይ ወድቆ ያገኘውን ቊስለኛ አንስቶ መልካም ነገር ስላደረገለት፣ ከወንበዴዎች እጅ ስላዳነው፣ ምሕረትም ቸርነትም ስለአደረገለት ደግ ሰው  ይባላል፡፡ 

ልጆች! እናንተም እንደ ደጉ ሳምራዊዉ ደግ ሁኑ፤ በጎም አድርጉ፤ የተቸገረ ማንኛዉንም ሰዉ መርዳት ይገባችኋል:: ሰዎች የእናንተን እርዳታ በሚፈልጉበት ጊዜ ደጉ ሳምራዊውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ በማንኛዉም ጊዜ ለሰዎች በጎ  አድርጉ፡፡ «እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ» ብሎም እንዳስተማረን ደግ ሰዎች ስትሆኑ ሰላማዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር ይሆናል!!! (ማቴ.፳፰፥፳) 

ልጆች! ለዛሬ በዚህ ላይ ይብቃን፤ በሚቀጥለው ትምህርታችን እስክንገናኝ ደኅና ሰንብቱ!    

                                                     እግዚአብሔር ይባርካችሁ!

ምንጭ፦ «ደጉ ሳምራዊ» ከ፯-፲፩ ዓመት ላሉ ልጆች ከተዘጋጀ የሕፃናት መጽሐፍ፤ ፳፻፲ ዓ.ም የተወሰደ።

 

 

Read 705 times