Friday, 11 December 2020 00:00

የብዙዎች አባት - አቡነ ኢየሱስ ሞዐ

Written by  ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ
የተወዳዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? አሜን፤ የአባቶቻችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!  ልጆች! ዛሬ የብዙ ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን መንፈሳዊ አባት ስለሆኑት ጻድቁ አባታችን አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ የቅዱሳንን ታሪክ በማንበብ ለቅዱሳን ከተሰጠው ቃል ኪዳን ተጠቃሚ መሆን ይቻላልና በጥሞና ታነቡ ዘንድ እንጋብዛችኋለን!  የአቡነ ኢየሱስ ሞዐ አባታቸው ዘክርስቶስ እናታቸው ደግሞ እግዚእ ክብራ ይባላሉ።   በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።  አቡነ ኢየሱስ ሞዓ በጐንደር ክፍለ ሀገር ዳኅና ገብርኤል በሚባል ቦታ  ግንቦት ፳፮ በ፲፪፻፲ ዓ.ም ተወለዱ።   ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በአባታቸው ቤት እና በአካባቢያቸው ጥበብን፣ ትምህርተ ሃይማኖትን እና መልካም ተግባርን ሁሉ እየፈጸሙ አደጉ።  በቅድስና በንጽሕና ሆነው በቤተሰቦቻቸው ቤት እስከ ሠላሳ ዓመት ኖሩ።   አንድ ቀን ስሙ ገብርኤል የተባለ የእግዚአብሔር መልአክ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዐ በሌሊት ታያቸው።  ሦስት ጊዜም ጠራቸውና ‹‹ከአባትህ ቤት ውጣ፤ ወደ ታላቁ አባት ወደ አባ ዮሐኒ መኖሪያ ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ሂድ፤ ደግ አገልጋይ ትሆናለህም›› አላቸው።  ቃሉንም ተቀበሉትና በሠላሳ ዓመታቸው በ፲፪፻፵ ዓ.ም. ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገብተው ከአባ ዮሐኒ ጋር ሰባት ዓመት ኖሩ። 

 

ልጆች! አቡነ ኢየሱስ ሞዐ አባ ዮሐኒን ሌሎች መነኰሳትን እየረዱና መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ለሰባት ዓመት ቈይተው ከደብረ ዳሞ ገዳም አበምኔት ከአባ ዮሐኒ በሠላሳ  ሰባት ዓመታቸዉ በ፲፪፻፵፯ ዓ.ም. መዓረገ ምንኩስናን ተቀበሉ። 

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ በጽድቅ እና የሊቅነት ሕይወት የሚኖሩ  ታላቅ አባት ናቸው።  በዘመናቸው ለቤተክርስቲያንም ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል፤ ይህ ሥራቸውም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል።  

ከዕለታት በአንድ ቀን ደግሞ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ ገድላቸውና ትሩፈታቸው በዓለም ሕዝብ ሁሉ እንደሚታወቅ ነግሯቸው ‹‹የስምህ መከበሪያ ወደ ሆነዉ ሐይቅ ወደ ተባለዉ ሥፍራ ተነሣና ሂድ›› አላቸው።  

የብዙ ወራት መንገድ የሆነውንም እርሱ እየመራ በስድስት ሰዓት ዉስጥ ከሐይቅ ከተማ አደረሳቸውና ተሠወረ።  ከዚያም በኋላ ከሐይቅ ገዳም በስተሰሜን አቅጣጫ ወደ በሚገኘው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ለስድስት ወራት ያህል ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቅ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር።  

ከዚህ የተነሣ በሐይቅ እስጢፋኖስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት መነኰሳት ማታ ማታ የብርሃን ዓምድ ወደ ሐይቁ ሲገባ ማለዳ ደግሞ ሲወጣ ያዩ ነበር።  በዚህ ዓይነት ክብራቸዉ የተገለጠዉ አባታችን አቡነ ኢየሱስ ሞዐ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድና በገዳሙ አባቶች ተማኅጽኖ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም አበምኔት ሆነው ተሾሙ።  

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ ለገዳሙ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የተለያዩ መልካም ተግባራትን እየሠሩ ለ፵፭ ዓመታት አገልገለዋል።  

አባታችን ከሠሯቸው ሥራዎች መካከልም ልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጻፍና በማሰባሰብ በሐይቅ ገዳም በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን መንፈሳዊ የቤተክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት አቋቁመዋል።  

ከዚህ በተጨማሪ የመጀመሪያውን ቋሚ የአብነት ትምህርት ቤት በማቋቋም ስምንት መቶ መነኮሳትን በትምህርተ ሃይማኖት በማነጽ በመላው ኢትዮጵያ አሰማርተዋቸዋል።  ከእነዚህም መነኰሳት መካከል፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አቡነ ኂሩተ አምላክ፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል የመሠሰሉትን እጅግ በጣም ብዙ ደጋግ አባቶችን አፍርተዋል፤ በዚህም የተነሣ ‹‹ወላዴ አእላፍ›› የብዙዎች አባት ተብለው ይጠራሉ። 

በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ‹‹በስምህ ግማሽ እንጀራና ቀዝቃዛ ውኃ ለድሆች የሰጠውን እስከ ሰባት ትውልድ እምርልሃለው›› የሚልን ቃል ኪዳንን ከፈጣሪያቸው ተቀብለው በ፹፪ ዓመታቸው ኅዳር ፳፮ ቀን ፲፪፻፺፪ ዓም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል።  ‹‹በዚያችም ዕለት በቦታው የታየው የብርሃን ዓምድ ሀገሪቱን ሞላት›› በማለት በስማቸው የተጻፈው ገድለ ኢየሱስ ሞዐ ይተርካል። 

ልጆች! ከብዙዎች አባት ከአባታችን ከአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ታሪክ ብዙ ትምህርት እንደተማራችሁ ተስፋ እናደርጋለን።  ወር በገባ በ፳፮ ከአቡነ ሀብተ ማርያም ጋር በዓላቸው ይታሰባልና እናንተም አቡነ ኢየሱስ ሞዐን በመዘከር ረድኤት በረከት እንድታገኙ እናሳስባችኋለን።  

በሚቀጥለው ትምህርታችን እስክንገናኝ 

ደኅና ሰንብቱ! 

የአቡነ ኢየሱስ ሞዐ አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን!

Read 1452 times