ውድ እኅታችን ወለተ መድኅን ምክር አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት በብዙ ቦታ ተጽፎ እናገኛለን። “ብልህ ሰው ያለ ምክር የሚሠራው ሥራ የለም፤ የሚሠራውም ሥራ የበጀ ይሆንለታል። ” (ሲራክ. ፴፭፥፲፰ ) የሚለው ከእነርሱ መካከል አንዱ ነው። አንቺም ለገጠመሽ ፈተና መሻትሽ መልካም ነው ።
ውድ እኅታችን ብቸኝነት በተለያየ መንገድ በሰዎች ላይ ሊከሠት ይችላል። ሰዎች የሚወዱአቸው ሰዎች በሞትም ሆነ በሕይወት ሲለዩአቸው፣ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ በቤተሰብ መሀል ፍቺ ሲኖር እና ቤተሰብ ሲለያይ፣ በሰዎች መካከል የአመለካከት እና የአስተሳሰብ ልዩነት ሲኖር እና ያንን አቻችሎ መኖር ሲያቅት አንደኛው ወገን ከሌሎች ጋር ላለመገናኘት በመወሰን ለመሸሽ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ወደ ብቸኝነት ሊገባ ይችላል።
አንዳንዶች ከደረሰባቸው ክፉ ነገር ተነሥተው የቀደመውን ዓይነት ችግር ውስጥ ደግመው ላለመግባት ከሰዎች ጋር መገናኘቱን በመተው ብቸኝነትን ይመርጣሉ። ሆኖም ሰዎች ከሰዎች እየራቁ በሄዱ ቁጥር ባዶነት እየተሰማቸው ይሄድና በመጨረሻ ለከፋ የሥነ ልቡና ችግር ሊያጋልጣቸው ይችላል።
ከሰዎች ጋር ባለው ግኙኝነት ከሚመጣባቸው የብቸኝነት ተጽእኖ ውጪ በራሳቸው አማካይነት ሊከሠትም ይቻላል። ለምሳሌ ሰዎች የአእምሮ ሕመም ሲያጋጥማቸው፣
ሥራ አጥነት ሲከሠት፣ የአካል ጉዳተኝነት . . . ወዘተ የመሳሰሉት ለብቸኝነት ሊጋለጡ ይችላሉ።
ወደ እኅታችን ወደ አንቺ ጥያቄ ስንመጣ ችግርሽን በጽሑፍ እንደገለጽሽው ከልጅነት ጀምሮ ተጫዋችና በትምህርት ቤትም ብዙ ጓደኞች እንደነበሩሽ፤ ወደ ሥራ ዓለም ገብተሸ የቀረብሻቸው ሰዎች ግን’፦
፩ኛ. ለግል ጥቅማቸው ብቻ የሚያተኩሩ፣ ለፍተው ከማግኘት ይልቅ በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ፣ በሥልጣናቸው ጭምር ተጠቅመው ሌሎችን የሚበድሉ መሆናቸው፤
፪ኛ. ለጓደኝነት የምትቀርቢያቸው ሴቶችም፤ እውነተኞች ባለመሆናቸው ጓደኛ በማጣት መቸገርሽን፤
፫ኛ. በሥራና በግል ሕይወትሽ ስሜትሽን የሚጎዱ አስተያየት በመስጠትና በመዝለፍ፤ ሕይወትሽን አስቸጋሪ እንዳደረጉብሽ፤
፬ኛ. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራና የግል ሕይወትን የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶች ከመፈጸም አልፎ፤ ለትዳር ያለሽን አመለካከት እስከማበላሸት መድረሳቸው፤ በዚህም የተነሣ ትዳር ለመመሥረት መቸገርሽን፤
፭ኛ. በመጨረሻም ከሰዎች ርቀሽ በብቸኝነት ለመኖር መወሰንሽንና የዕረፍት ጊዜሽን በብቸኝነት እያሳለፍሽ መሆኑን፤ ነገር ግን ብቸኝነቱ እየጎዳሽ ስለሆነ፤ ሰው የግድ እንደሚያስፈልግሽ ስለተረዳሽ፤ ምክር እንድናካፍልሽ ጠይቀሻል። በዚህም መሠረት እኛ ጥያቄሽን ተመልክተን ችግርሽን ተረድተን ለጥያቄዎችሽ መልስ ይሆናሉ ያልናቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከአባቶች አስተምህሮ ጥቂቶቹን የመፍትሔ ሐሳቦች እንጠቁምሻለን።
፩. በመሥሪያ ቤት ውሎሽ የገለጽሽው ሐሳብ በተለይ በሠራተኞች አካባቢየተመለከትሽው መጥፎ ባሕርያት በተለይ በዘመናችን በብዙዎች ላይ የሚታይ መሆኑ ነው። ባንቺ በኩል የሚሰሙሽ ከሆነ ለመምከር መሞከር ነው፤ የማይሰሙሽ ከሆነ ግን ከክፉ ሥራቸው መለየት ነው። “ከክፉ ሽሽ መልካሙን አድርግ፤” ይላልና (መዝ. ፴፮፥፳፯) እኛ የሰው ልጆች የተፈጠርነው፤ አምላካችን የሚወደውን፣ የሚፈቅደውን ፈጽመን የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን ነበር። ነገር ግን የጠላት ዲያብሎስን ምክር በመከተል፣ ለፈቃደ ሥጋ በመሸነፍ፤ ራሳችንንም ሌሎችንም በመጥፎ ሥነ ምግባራችን በመፈተንን ላይ እንገኛለን።
እኅታችን ወለተ መድኅን ሰዎች አንቺን በበጎ ማየት አቁመው በምትሠሪው ሥራ ሲመቀኙሽ፣ መጥፎም ሊያደርጉብሽ ቢሞክሩ የተሻለ ነገር በመሥራት ከቀድሞው በበለጠ ሥራሽን በማሻሻል እና በክፉ የሚያዩሽን ሰዎች በቅንነት በመቀበል በአንቺ ላይ ያላቸውን አመለካከት መቀየር ትችያለሽ። በተሰለፍሽበት የሥራ መስክ ውጤታማ ለመሆን በምታደርጊው እንቅስቃሴ ባንቺ ጉዳይ ጣልቃ ይገቡ የነበሩ ሰዎች ተስፋ ቆርጠው ሊተዉ ይቻላሉ። በተለይ በራስሽ የምትተማመኚ ሆነሽ ከተገኘሽ ሌሎችን በመልካም ወደራስሽ መሳብ ትችያለሽ።
እኅታችን ወለተ መድኅን ከላይ የተነሠት ምክረ ሐሳቦች እንደተጠበቁ ሆነው የመድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ልጅ እንደመሆንሽ እርሱን አርአያና ምሳሌ በማድረግ የምትጠይው ሰዎቹን ሳይሆን ክፉ ተግባራቸውን መሆን አለበት። በዘወትር ጸሎትሽም “በክፉዎች ግብር እንዳልሳብ ጠብቀኝ፤ ክፉ ከሚያሠራቸው ከፈቃደ ሥጋ፣ ከሰው ልጆች ባላጋራ ሰይጣን ነፃ አውጣኝ” በማለት ጸልዪ። ይህን ስታደርጊ በእነሱ አድሮ የሚፈትንሽ ሰይጣን ገለል ይልልሻል፤ ጠላት ሰይጣን በግልጽ ሊፈትነን አይመጣም፤ ሕይወታችን ሰላማዊ እንዳይሆን፤ በደካማ ጎናችን እየገባ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠርን ሰዎች ስምምነት እንዳይኖረን፣ እንዳንግባባ፣ አንዳችን በሌላው እንድንፈርድ እያደረገ ይዋጋናል። ይህን እውነተኛ ጠላታችንን ልናውቅበት ይገባል። ይቀጥላል...