በአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ ሲጓዙ ብዙ የሚያስገርም፣ የሚያሳዝን፣ የሚያስፈግግ፣ የሚያስቆጣም ክሥተቶች ያጋጥማሉ። በተለይም ደግሞ ረዘም ያለ ርቀት ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚጓዝ ሰው ከሚኖረው ብዙ የጉዞ ቆይታ አንጻር እንዲህ ዓይነት ክሥተቶች ሊፈራረቁበት ይችላሉ።
እኔም በአንድ አጋጣሚ ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ ሀገር ስጓዝ ያጋጠመኝን እና በጅጉ አዝኜ የታዘብኩትን ላውጋችሁ። አውቶብሱ ሞልቶ የተወሰኑ ቆመው የሚሄዱ ሰዎችንም ጭኗል። ሁሉም አፍና አፍንጫውን በመሸፈኛ ጋርዶ ግማሹ በወንበር ላይ ተክዞ፣ ግማሹ አጠገቡ ካለው የጉዞ ጓዱ ጋር እያወጋ፣ የቆሙት ደግሞ የመኪናውን ወራጅና ቋሚ ብረቶች በእጆቻቸው ይዘው፣ በመኪናው ግፊት ወደ ኋላ ወደ ፊት እየተወዛወዙ ይጓዛሉ። ፌርማታዎች ላይ ሲደረስ ከነበሩት ገሚሶቹ ሲወርዱ አዲስ ተሳፋሪዎች ደግሞ በጉዞው ይስተናገዳሉ።
በዕለቱ በጉዞው በጉልህ መጀመሪያ ላይ ያጋጠመኝ ተሳፋሪ ሆኖ ትኬት ቆርጦ ከገቡት ተጓዦች መካከል አንዱ ተሳፋሪው የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋለት ጮክ ብሎ መጠየቅ ጀመረ። ከተሳፋሪው የተወሰነው ሰውዬው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ በመግባቱ ያጉረመርማል። የተወሰኑ አጠገቡ ያሉ ወጣቶች ደግሞ የህክምና ማስረጃ ብሎ የያዘውን ወረቀት ቀረብ ብለው በማየት ‹‹ማኅተሙ ደብዝዟል፣ የተጭበረበረ ነው›› እያሉ ይሳሳቃሉ። የተወሰነው ሰው ደግሞ ‹‹ካልቸገረው ሰው ፊት አይቆምም፤ መርዳት ነው›› እያለ የሚችለውን እየተቀባበለ ያደርስለታል። ሰውዬው የቻለውን ያህል ለምኖ ፌርማታ ጠብቆ ወረደ።
ትንሽ እንደተጓዝን ከከተማው ወጥተን ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ሳለ በፌርማታ አቅራቢያ አንድ የቤተ ክርስቲያን ልብሰ ተክህኖ ለብሶ፣ መስቀል ጨብጦ፣ ማዕጠንት የያዘ ካህን ይታየኛል። እንደደረስን አውቶብሱ ቆሞ የመሐል በር ተከፈተ። ተሳፋሪው በአብዛኛው በመጨረሻው ፌርማታ የሚወርድ በመሆኑ የወረደ ሰው የለም ከውጪም ከቆመው ባለማዕጠንት ካህን በስተቀር ሌላ ሰው አይታይም።
መኪናው ቆሞ በሩ እንደተከፈተ ማዕጠንት የያዘው ካህን በእጁ የያዘውን ዕጣን በማዕጠንቱ ባለው ፍም ላይ ጨምሮ ጭሱ ደምቆ መውጣት እንደጀመረ ወደ አውቶብሱ ገባ። ካህኑ በተሳፋሪው መካከል ወደ ፊት ወደ ኋላ እየተጓዘ አውቶብሱን አጠኑ። የልብሰ ተክህኖውን ዘርፍ መስቀሉን በያዘበት በግራ እጁ ዘርግቶ ይዞ በቀኝ እጁ ማዕጠንቱን ያወዛውዛል።
በአውቶብሱ ውስጥ ካለው ተሳፋሪ ብዙዎች ብር እያወጡ ካህኑ በግራ እጁ ዘርግቶ በያዘው የልብሰ ተክህኖው ዘርፍ ላይ ይጥላሉ። አንዳንዱ ጠጋ እያለ በግራ እጅ ወደተያዘው መስቀል ቀረብ ብሎ ይሳለማል። አንዳንዱ ደግሞ መስኮት ከፍቶ የእጣኑን ጢስ ለማስወጣት ይውተረተራል። አንዳንዱ ዓይኑን ቁልጭ ቁልጭ እያደረገ ወደፊት ወደኋላ ያያል። አንዳንዱ በአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛው ውስጥ ሆኖ ያጉረመርማል። ሹፌሩም ካህኑ የሚያደርገውን ፈጽሞ እስከሚወርድ ይጠብቃል።
እኔ አጠገቤ ያለውን ሰው ሁኔታ በጣም እየተከታተልኩ ነበር። በካህኑ ተግባር በጣም ተደስቷል። ለካህኑም ብር ሰጥቷል። ‹‹እሰይ፣ እሰይ እንዲህ ሲያደርጉ ግሸን የምጓዝ ያህል ነው የተሰማኝ›› አለ። እኔም መለስ ብዬ ‹‹ሁሌም እንደዚህ እየገቡ ያጥናሉ እንዴ›› አልኩት። ‹‹እኔ አልፎ አልፎ ስመጣ እንደዚህ ሲያደርጉ አጋጥሞኛል፤ የአውቶብስ ሾፌሮቹም ይተባበሯቸዋል፤ በጣም ደስ ይላል›› አለኝ። የምለው ጠፍቶኝ በዝምታ ተዋጥኩ።
ካህኑ ወረደ። አውቶብሱ መጓዝ ጀመረ። እኔ ከተቀመጥኩበት ወንበር ጀርባ ግን አንድ የሚያጉረመርም ሰው ድምፅ ሰማሁ ‹‹ጥፋተኛው ሾፌሩ ነው፤ ይህ እኮ! የሕዝብ ሁሉ መገልገያ አውቶብስ ነው። ዕጣን መታጠን የማይፈልግ ሰው ቢኖርስ! ለምን እንደዚህ ይሆናል። እኔ እኮ ወንጌላዊ አማኝ ነኝ …እያለ አብሮት ላለው የጉዞ ጓዱ ያወራል። ‹‹እነርሱ ለአገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ነው…›› ክርክሩ ቀጠለ፤ ‹‹ታዲያ እዚህ ሳይገባ በመስኮት መቀበል ይችላልኮ…› ክርክሩ ቀጥሏል።
የእኔም ትልቁ ትዝብት በመንግስት አውቶብሶች ውስጥ ገብቶ ማዕጠንት ይዞ አውቶብሱን እያጠኑ ገንዘብ መሰብሰብ መቼ ነው የተጀመረው? ለመሆኑ ቤተ ክህነትስ ጉዳዩን ያውቀው ይሆን? ይህንን በማድረግ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀማለች ወይስ ትጎዳለች?
በእኔ ትዝብት ግን ተግባሩ በሕግ የሚያስጠይቅ ከመሆን አልፎ ከፍተኛ ግጭት የሚቀሰቅስ ተግባር ነው። እኔ ባየሁት አጋጣሚ የታየው የሙስሊምና ፕሮቴስታንቶች ማጉረምረም፣ የኦርቶዶክሱ ወገን ደስታ ውጤቱ መልካም እንደማይሆን ነው።
በአውቶብስ ውስጥ ማዕጠንት ይዞ ወጣ ገባ ማለቱስ ከሃይማኖታችን ሥርዓት አንጻር ምን ያህል ተቀባነት አለው። ሁሉም አማኝ ባልሆነበት፣ ፈቃዱ ባልተጠየቀበት፣ በማን አለብኝነት የሚፈጸም ሥርዓት ውጤቱ የማረ ይሆናል ብዬ አላስብም። ምእመናን የማዕጠንት ሥርዓት በሚፈጸምበት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው በመሳተፍ ከአገልግሎቱ ሊጠቀሙ ሲገባ ወደማይገባ ስፍራ አገልግሎቱን በመውሰድ የንትርክ አጀንዳ መፍጠር አግባብ አይደለም።
ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳዮች ኖረውት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በወቅቱና በጊዜው ተግባሩን ለመፈጸም እየተጣደፈ ላለ ተሳፋሪ ለአምስትም ይሁን ለዐሥር ደቂቃ ቆሞ ባላቀደው አጋጣሚ ውስጥ መቆየት ላይዋጥለት ይችላል። ቤተ ክርስቲያንን በማክበርና በመውደድ ተባባሪ የሆኑ አውቶቡስ ሾፌሮችም ለሕግ ተጠያቂነት መጋለጥ የለባቸውም።
ስለዚህ ምእመናን የምንወዳቸው እና የምንፈልጋቸው አገልግሎቶች ከጊዜና ከቦታቸው ሲወጡ ለምን ማለት ይገባናል እንጂ ግፋ በለው በማለት ለሀገራችን ሰላም እጦት ምክንያት መሆን የለብንም። የሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርም በየአካባቢዎቹ ያሉ ለፈተና ሊዳርጉን የሚችሉ የካህናት እንቅስቃሴዎችን በምክር ሊያስተካከል ይገባል።
በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን የሚመስሉ (በትክክል ልመናው ለቤተ ክርስቲያን ቢሆን እንኳ) ነገር ግን በብዙ መንገድ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያፈነገጡ እና የሚያስተቹ ድርጊቶች ናቸው። በመሆኑም ሁሉም የሚመለከተው አካል እንዲህ ዓይነት በቤተ ክርስቲያን ስም የሚደረጉ ከሥርዓት የወጡ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ሲያይ በቸልታ ሊያልፈው አይገባም እላለሁ።