Saturday, 26 December 2020 00:00

ብቸኝነት እየጎዳኝ ነው ክፍል ሁለት

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን

Overview

፪. ጓደኛ የማጣት የብቸኝነት ፈተናን በተመለከተ በርግጥ ነው ሰው ያለሰው መኖር አይችልም።  ግን ምን አይነት ሰው፣ ከየት ማግኘት ይቻላል? ለሚለው መድኃኔ ዓለም አባታችን በወንጌል “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ወይን፥ ከአሜኬላም በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬ ያፈራል” (ማቴ.፯፥፲፮-፲፱) በማለት ክፉ ሰዎችን እና መልካም ሰዎችን በክፉ ዛፍና በመልካም ዛፍ መስሎ እንዳስተማረ ልንቀርባቸውና ጓደኛ ልናደርጋቸው የሚገባን መልካሞቹን እንደሆነ እንረዳለን።  እነዚህን የምናገኘው ደግሞ ዘወትር ወደ ቤተ እግዚአብሔር ለጸሎትና ለአገልግሎት ከሚገሠግሡት መካከል ነው።  ከእነዚህ ውስጥ መልካሞቹ የሚታወቁት ደግሞ በበጎ ሥራቸው ነው።  ወለተ መድኅን ወደ መድኃኔ ዓለም፣ ወደ እናቱ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወደ ቅዱሳን መላእክትና ጻድቃን ሰማዕታት በጸሎት ደጅ በመጥናት፤ መንፈሳዊ ጓደኞችን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይገባሻል።  በጽሑፍሽ ስለ መንፈሳዊ ሕይወትሽ የገለጥሽው ነገር ባይኖርም ከሥራ ውጪ  ባለሽ ትርፍ ጊዜ ጠዋት እና ማታ ቅዳሜና እሑድ ወደ ቤተ ክርስቲያን መገሠገሥ በመንፈሳውያን ማኅበራት አባል ሆኖ ማገልገል፣ ወደ ገዳማት መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ መንፈሳውያን ጓደኞችን ለማግኘት ይጠቅምሻል።  ፫.በሥራና በግል ሕይወትሽ፤ ስሜትን የሚጎዱ አስተያየት በመስጠትና በመዝለፍ የሚፈትኑሽን በተመለከተም፦ ጠቢቡ ሰሎሞን “ተግሣጽን የሚወድ ዕውቀትን ይወዳል፤ተግሣጽን የሚጠላ ግን ሰነፍ ነው።  የተሻለ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኛል።  ዐመፀኛ ሰው ግን ቸል ይባላል።  ከዐመፃ የማይርቅ ሰው ይጠፋል፤የጻድቃን ሥር ግን አይነቀልም።” (ምሳ. ፲፪፥፩ )እንዳለ በዚህች ምደር ላይ ሁለት ዓይነት ሰዎች ማለትም ጽድቅን የሚከተሉና ክፋትን የሚፈጽሙ እንዳሉ በሚከተሉት እና በሚፈጽሙት አንፃር የሚገጥማቸውን ያብራራል።   እኛ ምንም ነገር ቢገጥመን ተግሣጽን ከሚወዱት ወገን ልንሆን ይገባል።  የሚጠሉሽና የሚዘልፉሽ ስለ ሃይማኖትሽ እና ስለ በጎ ሥነ ምግባርሽ ከሆነ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  “ሰዎች ስለሰው ልጅ ቢጠሉአችሁ፥ ከሰው ለይተው ቢአሳድዱአችሁ ቢሰድቡአችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአወጡላችሁ ብፁዓን ናችሁ።” (ሉቃ. ፮፥ ፳፪) በማለት እንደተናገረው ክብር ታገኚበታለሽ እንጂ ስለማትጎጂበት ደስ ሊልሽ ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለክፋትና ስለክፉዎች፤  “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ከክፉ ራቁ፤ በጎውንም ያዙ፤ ለጽድቅ አድሉ፤ እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ ተዋደዱ፤ የምትራሩም ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ።  . . .  የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ . . . ክፉ ላደረገባችሁም ክፉ አትመልሱለት፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ።  ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ. . . ክፉውን በመልካም ሥራ ድል ንሣው እንጂ ክፉውን በክፉ ድል አትንሣው።” (ሮሜ ፲፪፥፲፬-፳፩) እያለ የመከረንን በሕይወታችን ከተጠቀምንበት የክፉ ሰዎች ባሕርይ አይፈትነንም፤ በትዕግሥት እናሳልፈዋለን።  ትዕግሥት ደግሞ በፈተና ወቅት ለመሸጋገሪያ ዋና መሣሪያ ናት።  ጻድቁ ኢዮብ የታገሠው ደዌውን ብቻ አይደለም፤ ጓደኞቹ በእርሱ ላይ የተናገሩትን ነቀፌታም ጭምር ነው።  በዚህ ምክንያት ልዑል እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ክፉ የተናገሩትን ተቆጥቶ ጻድቁ ኢዮብ ካልጸለየላቸው ምሕረት እንደማያገኙ በነገራቸው መሠረት  በቅዱሱ ጸሎት ይቅርታ ተደርጎላቸዋል።  የእኛን ሕይወት ለመጉዳት ፈተና የሚያመጡብንን ሁሉ በትዕግሥት ካሳለፍናቸው፣ ከጸለይንላቸው ለጊዜው ፈተናቸው ሊያስጨንቀን ቢችልም፤ በኋላ ጸጋና ክብር የምናገኝበት ይሆናል። (ያዕ. ፭፥፲፩፤ኢዮ. ፵፪፥፯-፲)  ፬. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራና የግል ሕይወት የሚያሰናክሉ ድርጊቶች ከመፈጸም አልፎ፤ የትዳር ሕይወትሽን እስከማበላሸት በመድረሳቸው ትዳር መመሥረት መቸገርሽን በተመለከተ፦ የፈጸሙብሽ ድርጊቶች ምን እንደሆኑ፤ ጾታዊ ግንኙነት ማበላሸት ማለት ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ ያለ ፈቃድ ወይም በማታለል የተፈጸመ መሆኑ ስላልተገለጸ፤ በቂ ምክር ለመስጠት ቢያስቸግርም፤  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራና የግል ሕይወትን የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶች ያጋጠሙሽ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በድላችሁ የመጣባችሁን ብትታገሡ፥ ምስጋናችሁ ምንድነው? ነገር ግን መልካም እየሠራችሁ፥ የደረሰባችሁን ግፍ ብትታገሡ፥ በእዚአብሔር ዘንድ የምታስመሰግን ይህቺ ናት። ” (፩ኛጴጥ. ፪፥፳) እንዳለው በዚህ ሁኔታ የሚያገኝሽ መከራ ዋጋ የሚያሰጥሽ ስለሆነ፤ ተስፋ ልትቆርጭ አይገባም።  ጾታዊ ግንኙነትን በተመለከተ ያለ ፈቃድ ወይም በመታለል የተፈጸመ ከሆነ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፤  ወደ መምህረ ንስሓሽ ቀርበሽ፤ በሚሰጡሽ ምክርና መመሪያ መሠረት ላንቺ የሚሆንሽን እስክታገኚ፤ በንጽሕና፣ በጾም፣ በጸሎት ተጠብቀሽ፤ የሚስማማሽ፣ የምትስማሚው የትዳር አጋር ስታገኚ፤ በጸሎተ መዓስባን በሥጋ ወደሙ ለማግባት እድሉ ስላለ፤ ተስፋ መቁረጥ የለብሽም።   በሥራሽ ጣልቃ የሚገቡ ሰዎች ቢኖሩም አንቺ ግን በተፈጠረው ጣልቃ ገብነት ሳትደናገጪ እና ሳትረበሺ በሥራ ቦታሽ ላይ ሥራሽ ካንቺ የሚፈልገውን አቅም ሁሉ በመጠቀም የሰዎችን ባሕርይ መቀየር ትችያለሽ።  በዙሪያሽ ባሉ ሰዎች እና በቅርብ አለቃሽ ዘንድ መልካም የሆነውን ነገር በማድረግ፣ ሥራሽን በቅልጥፍና በመሥራት ማንነትሽንና በሥራሽ አካባቢ ለሁሉም ሰው ቀና አመለካከት በማሳየት ከሌሎች ጋር የሚኖርሽን ግኑኝነት ከበፊቱ የበለጠ ማጠናከር ትችያለሽ።  ፭. በመጨረሻም ብቸኝነቱ የጎዳሽ በመሆኑ፤ ሰው የግድ እንደሚያስፈልግሽ፤ ለዚህም ምክር እንድንለግስሽ ጠይቀሻል።  በእርግጥ ሰዎች ሁሉ አንድ አይደሉም እንደ መልካቸው ሁሉ ባሕሪያቸው ሊለያይ ይችላል።  አንቺም ከአንድ ወይም ከሁለት ሰው ጋር በነበረሽ ግኙኝነት ሁሉም ሰው እንደዚያ ዓይነት ባሕርይ ይኖረዋል ብለሽ መገመት የለብሽም።  ከጥቂት ሰዎች ጋር በነበረሽ ግኑኝነት ሁሉም ሰው እንደዚያ ዓይነት ነው ብለሽ መገመትሽ ሰዎችን ሁሉ እንድትርቂ እና ብቸኛ እንድትሆኚ አድርጎሻል።  ይህ ደግሞ እየዋለ ሲያድር በራስሽ ላይ ያመጣውን ተጽዕኖ ከሐሳብሽ ተረድተናል።  ከሰዎች ጋር መቀራረብ ብትጀምሪ ብዙ መልካም ሰዎች በምድር ላይ እንዳሉ ታያለሽና።  በተጨማሪም ከብቸኝነት ለመዳን ግዴታ መሥሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን በማኅበራት፣ በሰንበቴ፣ በዕድር፣ በሰንበት ት/ቤት፣ በሠፈር ወ.ዘ.ተ. ጓደኛ ማፍራት ይቻላል።  እኅታችን አንችም በነዚህ ማኅበራዊ ተቋማት በመሳተፍ ማኅበራዊ ሕይወትሽን ማጠናከር ትችያለሽ።  ጋብቻን በተመለከተ ምንም እንኳን ቀጥተኛ ጥያቄ ባይሆንም ጠቢቡ ሰሎሞን “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል።  አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ያነሣዋልና፥ አንድ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት።  ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ አንድ ብቻውን ግን  እንዴት ይሞቀዋል? አንዱም ሌላውን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ፤ በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም። ” (መክ. ፬፥፱-፲፪) በማለት እንደገለጸው አንቺም በተግባር በማየትሽ ጓደኛ እንዴት ማግኘት እችላለሁ በማለት ላቀረብሽው ጥያቄ ከላይ በቁጥር ፪ ከሰጠነው ምክር በተጨማሪ ጓደኛ ወይም ወዳጅ ስንይዝ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊሆን ይገባዋል።  ከጠላቶቻችን ይልቅ ወዳጅ መስለው የሚመጡብን ጠላቶች ስላሉ መጠንቀቅ ተገቢ እንደሆነ ጠቢቡ ሰለሞን “ ከጠላቶችህ ራቅ፤ ወዳጆችህንም ተጠባበቃቸው።  . . .የታመነ ወዳጅ የሕይወት መድኃኒት ነው፤ እግዚአብሔርንም የሚፈሩ ያገኙታል” (ሲራ.፮፥፲፫-፲፮ ) በማለት ምክር ተሰጥቶናል።  ስለዚህ ሕጉን ትእዛዙን በማክበር ለእርሱ በመገዛት በጸሎት ደጅ በመጥናት እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት ይቻላል።  ተጨማሪ ምክር የሚያስፈልግሽ ከሆነ በዝግጅት ክፍላችን ስልክ ቁጥር ብትደውዪ ከመምህራን ጋር ልናገናኝሽ እንችላለን።   ውድ እኅታችን ወለተ መድኅን እነዚህን ምክሮች ተጠቅመሽ ከገጠመሽ ፈተና ነፃ ለመውጣት፤ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳሽ፤ የወላዲተ አምላክ አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን የሰማዕታት ቃል ኪዳን አይለይሽ። 
Read 713 times