ተወዳጅ የሆናችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከርማችኋል? በእግዚአብሔር ጥበቃ በሰላምና በጤና እንደቆያችሁን ተስፋ እናደርጋለን፤ በቤታችሁ ሆናችሁ ትምህርታችሁን በንቃት እየተከታተላችሁ ነው? በጣም ጎበዞች! በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋልና በርቱ!
ልጆች! ዛሬ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ታሪክ ይዘልላችሁ ቀርበናልና ተከታተሉን!
አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ንጉሥ በነገሠበት ዘመን በግዛቱ ያሉ ሕዘቦቹን ለማወቅ በእስራኤል ሀገር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ይቆጠር ዘንድ አዘዘ። በትእዛዙ መሠረትም ሰው ሁሉ ሊቆጠር ወደ የትውልድ ከተማው ሄደ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በዚያን ወቅት ጌታችንን አርግዛ ስለነበር ከአረጋዊው ዮሴፍ ጋር ሆና ለመቆጠር ከናዝሬት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ቤተ ልሔም ሄዱ። በቤተ ልሔም ሳሉም
እመቤታችን ማርያም የምትወልድበት ቀን ደረሰ። በዚያ ሥፍራም ብዙ ሰው ስለነበር እነ ዮሴፍ የሚያርፉበት ቦታ አላገኙም። ማደርያም ስላልነበራቸው በከብቶች በረት ውስጥ ዐርፈው ሳለ እመቤታችን የመውለጃዋ ጊዜ በመድረሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችው። በጨርቅ ጠቅልላ እዛው በበረት ውስጥ አስተኛችው፤
በዚያ ሀገር ይኖሩ የነበሩ እረኞችም ሌሊት ከብቶቻቸውን ይጠብቁ ነበር፤ የእግዚአብሔር መልአክም በእረኞቹ አጠገብ ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው በራ፤ በጣምም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው ‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል። ይኸውም ጌታ እና እግዚአብሔር የሆነ መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ነው። እናንተም ባገኛችሁት ጊዜ ምልክቱ እንዲህ ነው። ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ፤ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ።›› (ሉቃ.፪፥፲-፲፫)
ከዚህም በኋላ እነዚህ እረኞች እርስ በርሳቸው ‹‹እስከ ቤተ ልሔም እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ›› አሉ፤ ፈጥነውም ሄዱ። ድንግል ማርያምንና ዮሴፍንም በከብቶቹ በረት አገኙአቸው። ሕፃኑንም በአዩት ጊዜ የነገሩአቸው እውን መሆኑን ስላዩ በጣም ተደነቁ። እረኞቹም እንደነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› ብለው እያመሰገኑና እያከበሩ ወደመጡበት ተመለሱ። ሰብአ ሰገልም በኮከብ ተመርተው ወደ ሕፃኑ ገብተው አምላክነቱን በመረዳት ሰገዱለት፤ ዕጣን፣ ወርቅና ከርቤንም የእጅ መንሻ አድርገው አቀረቡለት። (ሉቃ.፪፥፲፭-፲፰)
ልጆች! እነዚህ ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊያዩ የመጡ ሰዎች በደስታ የጌታችንን መወለድ አክብረዋል። ስለዚህ እናንተም በቤተ ክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በደስታ ልታከብሩ ይገባል። አንድ ላይም ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን›› እያልን እንዘምር፤ እንግዲህ ለዛሬ በዚህ ይብቃን፤ ልጆች! መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ እንመኝላችኋለን!። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፤ የሰብአ ሰገሉ ረድኤት አይለያችሁ!