Monday, 11 January 2021 00:00

የዝክራችን መልክ

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ

Overview

ዝክር አንድን ቅዱስ የተወለደበትን፣ ያረፈበትን፣ ተአምራት የሠራበትን፣ መከራ የተቀበለበትን የክብር አክሊል የተቀዳጀበትን….ወዘተ በመሰባሰብ ወይም በተናጠል ማሰብ ማለት ነው። ኦርዶክሳውያን ቅዱሱን ከማሰብ ጀምሮ፣ በጸሎትና ምስጋና እንዲሁም በቅዳሴና በውዳሴ ይዘክሩታል። በቅዱሱ ስም ከሚጠራ ሩቅ ወይም ቅርብ ቤተ ክርስቲያን ወይም ገዳም ሄዶ በመሳለምም ይዘክራሉ። ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ከማጠጣት፣ ቆሎ ከማዘገን ጀምሮ ሰፋ ያለ ድግስ ደግሶ ነድያንን፣ ጎረቤትን ወዳጆችን ጠርቶ ‹‹ብሉልኝ ጠጡልኝ›› በማለትም ይዘክራሉ።…..  ዛሬ ዛሬ ግን ነባሩን የዝክር መልክ የቀየሩ ክዋኔዎች እየመጡ ነው። በቅዱሱ/በቅድስቷ ስም ተጠራርተው ባልተቀደሱ መንገዶች እየሄዱ ብቻቸውን አብዝተው እየበሉ እየጠጡ ዝክር እንዳደረጉ የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ቆርሰው ለድሆች የማያጎርሱበት፣ ቀድተው ለምስኪኖች የማያጠጡበት ዝክር በርክቷል። ጥቂቶች ከመንደር ተጠራርተው ዛሬ ቅዱስ ‹‹እገሌ›› ነው ብለው በልተው ጠጥተው ከመለያየት በስተቀር ስመ አምላክ ሳይጠራ፣ ስለቅዱሱም ሳይወራ፣ ጸሎት ሳይደረግ፣ ሳይመሰገን በመብል ተጀምሮ በመብል የሚያልቅ ዝክር አለ። ለእነዚህ ወገኖች ዋናው አጀንዳ ተሰብስቦ መብላት ብቻ ነው። 

 

ተሰብስበው በልተው ከመለያየት ተሻግሮ ደግሞ በዝክር ስም በተደረገው ሰብሰባ የባጥ የቆጡን ማውራት፣ በሐሜት መሙላት፣ በሌላው ላይ በመፍረድ መሰልጠን ይታይበታል። በዚሁ አጋጣሚ ተከራክረው ተካረው፣ ክፉ ደግ ተነጋግረውም የሚወጡ ይኖራሉ። ማን ምን አለ? ብለው ታዝበው ከሚወጡት ጀምሮ ‹‹ለካ እገሌ እንደዚህ ዓይነት ሰው ነው›› ብለው ቂም የሚይዙ፣ የሚያኮርፉም ይኖራሉ።

ሌላው አስከፊ ገጽታ ደግሞ ዝክር ብለው ጠርተው የዘፈን ድግስ ሲያቀርቡም የሚታዩ አሉ። ዘፈን እያማረጡ በጂፓስ በታዳሚው ጆሮ ሲያፈሱ የሚቆዩ ይታያሉ፤ የቴሌቪዥን ስክሪኖቻውም ተመሳሳይ ትዕይቶችን በማሳየት ስለሚቆዩ ለአፍታም ክርስያናዊ ዝክር ሳይመስላቸው ‹‹ያክብርልን›› ብለው የሚወጡ ሰዎች ብዙ ናቸው። ከከንቱ ድምፅና ምስል አጀቡ በተጨማሪ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸውን አውጥተው በመጎርጎር በፌስቡክና በቴሌግራም የተለቀቁ ልዩ ልዩ ዓለማዊ ጉዳዮችን እያዩና እያሳዩ የት ገብተው  እንደወጡ እንኳን እስከማያስታውሱት ድረስ አእምሯቸውን አባክነው የሚለያዩም የዝክር ተሳታፊዎች በርካቶች ናቸው። በዝክሮቻቸው ነዳያን ብቻ ሳይሆን የካህን ዘር የማይገኝበት ኦርቶዶክሳዊ ለመሆኑ ምስክር የሚሆኑ ምልክቶች የማይታይበትም ዝክር ያጋጥማል። 

ሌላው ዝክር ደግሞ ከቤተ ዘመድ ጉባኤ ያልተለየ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ከቤተ ዘመዱ ያልተሻገረ፣ ቤተሰባዊ ወግ ናኝቶበት የሚውል ስመ ዝክርም አልፎ አልፎ እናገኛለን። አስገራሚው ከዚህ ሰፋሁ ብሎ ቢገኝ በቋንቋ ወይም በትውልድ ሀገር ተመራርጦ የጎጥ ዕድር የሚመስል ዝክርም እናገኛለን። በዚህ ዓይነት ቤተሰባዊ እና ጎጠኛ ስመ ዝክር ውስጥ የሚጠሩበትን የወገን መስፈርት ብቻ በመመልከት የሚታደሙ መናፍቃን የቤተዘመዱ አባላትና የጎጥ ስብስቦችም ስለሚያጋጥሙ ለክርስቲያን ግራ ሊያጋባ ይችላል።   

በጥቅል ሲታይ አጉል የሆነው የዝክር መልክ አጉል ያሰኘውን መልክ የሚላበሰው በዝክሩ ዘካሪዎች ብቻ ሳይሆን በዝክሩም ተሳታፊዎች መሆኑን ማስተዋል እንችላለን። 

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ዝክርን ከዓላማው ጋር የሚያስማሙ ከመስመር ሳይወጡ የሚፈጽሙ አሉ። ቃለ እግዚአብሔርን በድምፅ ወይም በድምፅ ወምስል እያቀረቡ ሰዎችን በዚያ አጋጣሚ ወደ እግዚአብሔር ቃል የሚያቀርቡ ምስጉኖች አሉ። መዝሙሮችን በማሰማት የሰዎችን መንፈስ ወደ መንፈሳዊው ዓለም የሚስቡ ለንስሓ የሚያነቃቁ፣ለበጎ ቅናት የሚያደርሱ ብዙዎች ናቸው።

በዝክሮቻቸው አጋጣሚ የአካባቢዎቻችን ችግረኞች እንዴት አድርገው እንደሚረዱ፣ ለዚያ የሚያገለግል ማኅበር ስለማቋቋም የሚመክሩ አሉ። በአካባቢያቸው ያሉ የአእምሮ ሕሙማንን፣ ወላጆቻውን ያጡ ሕፃናትን፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያንን የሚደግፉ ለችግረኞች ርዳታ የሚያደርጉ  ድርጅቶችን ስለማቋቋም የሚመክሩ አሉ። በሌላም በዕለቱ ስሙ በሚጠራው ቅዱስ ስም ያለ አጥቢያን ስለመደገፍ፣ የጎደለውን ስለማሟላት የሚነጋገሩም ይገኛሉ። በዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠው የሚነጋገሩ፣ የቅዱሱን ተአምራት ወይም ገድላት የሚያነቡ፣ አንሥተው የሚመሰክሩ የዝክሩ ተሳታፊዎችም ሊገኙ ይችላሉ። ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እናገልግል ብለው የሚጠበቡ፣ በወቅታዊ ጉዳዮቿ ላይ ተወያይተው ምን እናድርግ የሚሉ ወገኖችም የዝክርን መንፈሳዊ መልክ ጠባቂዎች ሆነው እናገኛቸዋለን።     

በአጠቃላይ ሲታይም አሁን አሁን የሚታየው አጓጉል የሆነው የዝክር አዘካከር በየጊዜው እየተፈታተነን ያለው ዓላማዊነት ምን ያህል እየሸረሸረን መሆኑን የምናስተውልበት ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ ፍጹም መንፈሳዊ መልክ ለማስያዝ የሚተጉ በርካታ ክርስቲያኖች ሲታዩ ደግሞ ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርግ የመልካሙ ዝክር መልክ እንዳይለወጥ አብነት የሚያስቀርልን ሆኖ እናገኘዋለን።

በመሆኑም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሳናውቅ ወይም ተገደን በምንሳተፍባቸው አጓጉል መልክ ያላቸው ዝክሮች መንፈሳዊ መልክ እንዲይዙ  ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ዝክር ጠሪዎቻችን ዝክራቸውን ከጊዜ ጊዜ በጎውን መልክ እንዲያላብሱት ማገዝ አለብን። አንዳንዴም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሳያውቁ የሚፈጽሙት ስለሚሆን በዝግጅታቸው ትሑት ሆነን በመሳተፍ ጭምር መርዳት አስፈላጊ ነው።     

 

Read 1967 times