Monday, 11 January 2021 00:00

ከጋብቻ በፊት የሚኖር ግንኙነት ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር እንዴት ይታያል?

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን

Overview

ወደ ቤተክርስቲያን መጣ ሔድ በማለት በበዓል፣ በመንፈሳዊ ጉባኤያት፣ በዕለተ ሰንበት በመገኘት “ክርስቲያን ነኝ” ለማለት በማልደፍርበት አካሔድ እመጣለሁ (እመላለሳለሁ)። በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ እገኛለሁ። በእግዚብሔር ቤት መኖር የምመኝ የመንግሥት መስሪያ ቤት ሠራተኛ ነኝ፤ እናም ለማግባት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። ብዙ ወንዶች ለጋብቻ ይጠይቁኛል። ለብዙዎቹ ‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን›› ብዬ እንዲጸልዩ እንዲተጉ ምክር እሰጣቸዋለሁ። አንድ ቀን ወደ መሥሪያ ቤት ስሔድ ታክሲ ውስጥ ከአንድ ወንድም ጋር ተዋወቅንና ስልክ ተለዋወጥን ከዚህ በኋላ እየተቀራረብን መጣን። ወደ ሥራ ቦታ ስንሄድም ሆነ ስንመለስ እየተጠባበቅን መሄድ ጀመርን በዚህ መሀል አንድ ቀን ወደ ሥራ እየሄድን ሳለ ስለትዳር ጉዳይ ተነስቶ እንድንጋባ ጠየቀኝ።  ጥያቄውን ከመመለሴ በፊት እርሱ በጋብቻ ላይ ያለው አመለካከት ምን እንደሆነ ጠየቅሁት  እርሱም ከጋብቻ በፊት ግንኙነት መፈጸም መልካም እንደሆነና ለጋብቻም ጥሩ መተዋወቅን እንደሚፈጥር፤ በአንጻሩ በምዕራባውያን ፺ ከመቶ  በላይ የሚሆኑት ሰዎች ጋብቻቸውን የሚያፈርሱት በግብረ ሥጋ ግንኙነት አለመጣጣም የተነሳ እንደሆነ አክሎ ነገረኝ። እኔም እግዚአብሔር ባቀበለኝ መንገድ ‹‹ምዕራባውያኑ በቅድመ ጋብቻ ውስጥ በመኖራቸው ለምን ፍቺን መቀነስ ብሎም ማጥፋት አልቻሉም? እኔ ቅድመ ጋብቻን ዝሙት እንደሆነ ነው የማስበው›› ብዬ በጊዜው መለስ  ሰጠሁት። ለመሆኑ ይህንን ጉዳይ ከቤተ ክርስቲያን አስተምሮ አንጻር ምን ትሉኛላችሁ?  ወለተ ማርያም 

 

ውድ እኅታችን ወለተ ማርያም ለችግርሽ መፍትሔ አገኛለሁ ብለሽ ወደ ዝግጅት ክፍላችን በመምጣትሽ በቅድሚያ እናመሰግናለን። በመቀጠልም ከጥያቄሽ በተረዳነው መሠረት ስለ ትዳር የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በጥቂቱ እንደሚከተለው እናቀርባለን ተከታተይን ትዳር የሚመሠረተው ስለ ሦስት ነገር ነው። 

ትዳር ሰው ቤተሰቡን ትቶ ወይም ወላጆቹን ትቶ ከሚስቱ ወይም ከባሏ ጋር አንድ የሚሆኑበት ታላቅ ምሥጢር ነው። ትዳር የሚመሠረተው በሦስቱ ዋና ዋና ምክንያቶች በተለይ ከአምላክ ለሰው ልጅ በተሠጠው ትልቅ ስጦታ ውስጥ ነው። ‹‹ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚብሔር ዘንድ ናት።›› (ምሳሌ ፲፱፥፲፬) እንዲል ጠቢቡ ሰለሞን ይህን ድንቅ ሥጦታ አምላክ ለሰው የሰጠውን ከቤተሰብ ሥጦታ ይልቅ የተሻለና የበለጠ መሆኑን ያስገነዝበናል። እግዚአብሔር አምላክ በብሉይ ኪዳን  የአዳምና የሔዋንን እንዲሁም የሌሎች ቅዱሳን አባቶች እና እናቶች ጋብቻ መባረኩ፤ በሐዲስ ኪዳን በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን መቀየሩ ብሎም በሰርግ ቤት መገኘቱ የጋብቻን ክቡርነት የሚያረጋግጥ ነው። ጋብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ምሥጢር ነውና። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ምሥጢር ትዳር ለሰው ልጅ ስለ ሦስት ነገሮች ያስፈልጉታል።

፩. ለመረዳዳት፦ ባልና ሚስት በአንድ ጐጆ ሲኖሩ የሚረዳዱበትን የሚተጋገዙበትን መንገድ ለማመቻቸት እርሱ ለእርሷ እርሷ ለእርሱ የሚያደርጉትን መተሳሰብ መመካከር ለማጠናከር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ  ‹‹እግዚአብሔር አምላክም አለ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚረዳውን ረዳት እንፍጠርለት›› ዘፍ.፪፥፲፰ ይላልና። የእግዚአብሔር ሥጦታ ልዩ ከሚያደርጉት አንዱ ርዳታ ብቻ አይደለም የሚመች ጭምር ነው።  እርሷ ለእርሱ ረዳት ስትሆን ልትመቸው እርሱ ለእርሷ ረዳት ሲሆናት የሚመቻትና ብቸኛነቷን የምትረሳበት መሆን እንዳለበት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ያገባ ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል… የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለም ነገር ታስባለች›› ፩ኛቆሮ.፯፥፴፫-፴፬ እንዲል ባል ለሚስቱ ለአካሉ የሚያደርገው ርዳታና ሐሳብ እርሷን ለማስደሰት የሚያደርገውን ጥረት እርሷም ለርሱ ለባልዋ በምታደርገው የፍቅር መግለጫ በመተጋገዝ ማስደሰት እንደሆነም ሲገልጥ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ከልጅነት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ›› ይላል ምሳ. ፭፥፲፰ ደስታው የመረዳዳት የመተሳሰብ መሆኑንም ይገልጽልናል። መረዳዳት ባለትዳሮች በአንድ ጣሪያ ሥር የሚኖሩበት ብዙ ነገሮችን በጋራ የሚፈጽሙበት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንዳለው ‹‹በቤት ውስጥ ያለች ትንሿ ቤተ ክርስቲያን›› ናት። 

፪. ዘር ለመተካት፡- እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፤ግዙአትም›› እንዳለ ዘፍ ፩፥፳፪-፳፰  ሰዎች ዘራቸውን እየተኩ ይበዙ ዘንድ አዝዟቸዋል። በትዳር ሒደት ውስጥ የአምላክ ሥጦታ ሆኖ የሚገኘው ታላቁ ተወዳዳሪና መተኪያ የሌለው ከእግዚአብሔር ብቻ የሚሰጠው የሁለቱ ፍሬ ልጅ ነው ‹‹መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው ለመኝታቸውም ርኩሰት የለውም›› እንዳለ ሐዋርያው በዕብ.፲፫፥፬። ጋብቻ መልካም መኝታው ንጹሕ ነው ዘር ለመተካት እግዚአብሔር በተቀደሰ ጋብቻ ውስጥ የሚኖረው የልጅ በረከት ሥጦታው የርሱ ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ‹‹እነሆ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው›› ይላል (መዝ. ፮፥፫።) ይህ የሁለቱም ዘር የሚሆን ልጅ የሚገኘው እግዚአብሔር በፈቀደው የትዳር ውጤት ነውና ስለዚህ ነገር ትዳር ይመሠረታል። 

፫. ከዝሙት ለመዳን፦ የጋብቻ ሌላው ዓላማ ፍትወተ ሥጋን ለማሸነፍ ወይም ለመከላከል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ከዝሙት ጠንቅ ለመከላከል ‹‹ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው፤ለእያንዳንዲቱም ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት›› በማለት ያስተምረናል (፩ኛ ቆሮ ፯፥፪‐፱።) 

በየቦታው ዓይኑ እየተቅበዘበዘ  እንዳይፈተን የተሠራለት ሕግ በአንዲቱ እርሷም በአንዱ ወንድ ሊጸኑ ያስፈልጋል። ወደ ሌላ  መመልከት ግን ዝሙት ነውና እንደሚያስቀጣ ፍርድ እንሚያመጣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይላል ‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል›› ማቴ.፭፥፳፰ በማለት የቀደመውን ትእዛዝ ያጸናዋል። ፍትሐ ነገሥትም ሕግ ወደማፍረስ የሚያደርስ የፈቲውጾር በብዙ ሰዎች ቢጸና ጋብቻ መፈጸም እንዲገባ በአንቀጽ ፳፬፣ ክፍል ፩ ላይ ይነግረናል። 

ስለዚህ የትዳር ትልቁ ሦስቱ ሀብት ሆነው የሰው ልጅ የሚጠቀምባቸው የሚያተርፍባቸው ከበሽታ ጤናን ከመርገም በረከትን የሚያገኝባቸው በተለይም ከአምላኩ ጋር ከሚያጠላው ይልቅ የሚያፋቅረውና የሚያስማማው በእንዲህ አይነት መንገድ በተመሠረተ የትዳር ሕይወት ሲኖር ነው። 

ትዳር የአንድ ቀን ደስታ የሚበሉት ምሳ፣ ቁርስ፣ እራት የግብዣ ምሽት አይደለም እስከ ሕይወት ፍጻሜ ያለ አንድነት ነው እንጂ። ‹‹ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ›› እንዳለ ማቴ.፲፱፥፮። ይህ ማለት ድንቅና ሰማያዊ ምሥጢር እንጂ በአካልም በመንፈስም የተለያዩ ሰዎች በአንድ ላይ የሚኖሩበት የደባልነት ኑሮ አይደለም።

ዛሬ ዛሬ የሚታዩት አንዳንድ ትዳሮች መሠረታቸው አንድነታቸውም ሥጋዊ መግባባት ላይ ብቻ ይሆንና በኋላ ላይ መሰለቻቸት አልፎ ተርፎ ታኝኮ እንደተጣለ ማስቲካ እስከ መርገጥ የሚደርስ ጥላቻ ውስጥ ይገባሉ።  ብዙዎች መጀመሪያ የቸኮሉበትን ነገር ሲያገኙ ፈተናው ይጠነክርና አንድነቱ ይፈራርሳል።  ስለዚህ እህታችን እንደገለጽሽው በቅድመ ጋብቻ የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት በማድረግ የተመሠረቱ ትዳሮች መጨረሻቸው ፍቺ ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ በዚህ ዘመን በሁለቱም ላይ የሚታየው ትልቅ ችግር ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የጾታ ግኑኝነት ሲሆን ውሎ ሲያድር ሁለቱንም ለተለያየ ችግር ሲዳርግ ይታያል። እነሱም የሚከተሉት ናቸው።

፩. በመንፈሳዊ ሕይወት ላይ ሞትን ያስከትልባቸዋል 

የቅድመ ጋብቻ ግንኙነት በእግዚአብሔር ዘንድ ዝሙት ነው፤ ኃጢአት ነው፤ ሞትም ነው። ምክንያቱም የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና›› ሲል ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮናል።  ‹‹ሴሰኞችና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል›› ይላል  ዕብ.፲፫፥፬። ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ ከዝሙት ራቁ›› ፩ኛ ተሰሎ ፬፥፫ ማለቱ ‹‹ዝሙት›› ቃሉ ራሱ ከትዳር ውጪ የሚፈጸምን ማንኛውንም የጾታ ግንኙነት የሚያመለክት ነው። አንድ ወንድና ሴት ለመጋባት እቅድ ቢኖራቸውም  ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የጾታ ግንኙነት ኃጢአት መሆኑን ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስረግጥልን። ከዚህ ሌላ እንዲህ ዓይነት ግንኙነት በሥነ ልቡና ምሁራን ዘንድም ተቀባይነት እያጣ መምጣቱን ማስተዋልም ይገባል። ቤተ ክርስቲያንም ከትዳር በፊት የሚፈጠረውን የሩካቤ ሥጋ ግንኙነቶች እጅግ ታወግዛለች በመድረኳም ቦታ የለውም። 

፪. ማኅበራዊ ኑሮ ላይ የሚያስከትለው ችግር  

ቅድመ ጋብቻ የሚፈጸም የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት መሠረቱ በስሜት፣ በአካላዊ ቁመና መማረክ ላይ የተመሠረተ ይሆንና የጾታ ግንኙነቱ ከተፈጸመ በኋላ ችግሩ በተለይ በሴቶች ላይ ገዝፎ ይታያል። ለምሳሌ በሴቷ ላይ በሚከተለው እርግዝና ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። በዚህም ምክንያት ከማኅበረሰቡ ሐሜት እና ወቀሳ ለመሸሽ ያልተፈለገውንም ፅንስ ለማስወረድ በሚደረግ ጥረት ወደ ሕገ ወጥ ውርጃ ውስጥ ይገባል ነፍስንም ወደ ማጥፋት ይደረሳል። ይህ ደግሞ ሕይወትን እስከማጣት ሊያደርስ ይችላል። ከውርጃ ተርፎ ሕፃኑ ቢወለድ እንኳ አባት የሌለው ልጅ ባል የሌላት እናት የሚለው የማኅበረሰቡ ሐሜት በሕፃኑ የወደፊት ሕይወትም ሆነ በእናቲቱ ሥነ ልቦና ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። 

ስለዚህ ውድ እህታችን እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነትሽ ‹‹ምዕራባውያን›› ስለፈጸሙት ብቻ ትክክል ነው የሚልን ማስተባበያ ልትቀበይ አይገባም። እንደ ሥልጣኔ ቆጥረውት እና ተቀብለው የተጓዙበት ራሳቸው ምዕራባውያኑ ምን ያህል የማኅበራዊና የመንፈሳዊ ኑሮ ቀውስ ደርሶባቸው እየተቸገሩ እንደሆነ ልታውቂ ይገባል።

በተጨማሪም የእውነተኛ ትዳር መሠረቱ ቅድመ ጋብቻ የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት አይደለም። ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት የጀመሩ ሰዎች ከጋብቻ በኋላ የሚኖራቸው ሕይወት በእጅጉ ፈተና በዛበት ነው። ነገር ግን ወደ ተቀደሰው ጋብቻ መቅረብ በኋለኛው ዘመንም በረከት ነውና ከቅድመ ጋብቻ የጾታ ግኑኝነት ርቀሽ ንጽሕናሽን ጠብቀሽ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አክብረሽ ጋብቻ ልትፈጽሚ ይገባል። ውድ እህታችን ለሁሉም እግዚአብሔር ዓላማሽን በልብሽ አጽንቶ ከተቀደሰው ሥርዓተ ጋብቻ ያድርስሽ። እመቤታችን አትለይሽ።

 

Read 1516 times