Friday, 22 January 2021 00:00

የጥምቀት በዓል   

Written by  ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ

Overview

የተወዳዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ሕፃናት! እንደምን ከርማችኋል? በእግዚአብሔር ቸርነት በሰላምና በጤና እንደቆያችሁን ተስፋ እናደርጋለን፤ ትምህርታችሁን በንቃት በመከታትል በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋልና በርቱ! ልጆች! ዛሬ ስለጥምቀት በዓል እናስተምራችኋለንና በጥሞና ተከታተሉ!  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ዕለት የምናከብረው በዓል የጥምቀት በዓል ይባላል፡፡ ጥምቀት የሚለው ቃል ‹‹ተጠምቀ፣ ተጠመቀ›› ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲሆን ትርጕሙም በውኃ ‹‹መነከር፣ በገዛ እጁ ወይም በሰው እጅ ሥርየት ወይንም ልጅነት ለማግኘት መጠመቅ›› ማለት ነው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፭፻፪) ጥምቀት በተቀደሰ ውኃ መጠመቅ ማለት ነው፤ ይኸውም ቀሳውስት በጸሎት ሥርዓት ከቀደሱት በኋላ ምእመናንን (ክርስቲያኖችን) በተቀደሰው ውኃ ያጠምቋቸዋል፡፡ ካህናቱ ሕዝቡን ጸበል ከረጩ በኋላ ልዩ ልዩ ሥርዓቶች ይደረጋሉ፤ ከዚያም ታቦታቱ ከድንኳን ወጥተው ወደ የመጡበት ቤተ ክርስቲያን ይሔዳሉ፡፡ ‹‹ጥሩ ውኃንም ረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ›› (ሕዝ. ፳፮፥፳፭) ተብሎ እንደተነገረው፡፡ ውኃ ለሰው ልጆች በሙሉ አስፈላጊ ነው፤ ያለ ውኃ መኖር አይቻልም፡፡ ጥምቀትም ለሁሉም የሚያስፈልግ በመሆኑ ያለ ጥምቀት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ውኃ መልክ ያሳያል፤ መልክ ያለመልማል (ያጠራል)፡፡ ጥምቀትም መልክአ ነፍስን ያሳያል፤ መልክአ ነፍስን ያለመልማልና (ያጠራልና) ጌታችን  በውኃ ተጠመቀ፡፡

 

በጥምቀት በዓል ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ እንደተጠመቀ ለማስታወስ ጥር ፲ (ዐሥር) ቀን ሁሉም ታቦታት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ውኃ ወዳለበት ሥፍራ በመሔድ በድንኳን ውስጥ ያድራሉ፤ ይህም ዕለት ከተራ ይባላል፡፡ ከተራ የተባለው በአካባቢው ያለው ውኃ እንዳይፈስ ተገድቦ ሕዝቡ እንዲጠመቅበት ስለሚዘጋጅ ነው፡፡ ታቦታቱ ወደ ድንኳኑ ከገቡ በኋላ ሌሊቱን ካህናቱ ሲያመሰግኑ፣ ሲዘምሩና ሲቀድሱ እንዲሁም በዓሉን የተመለከተ ትምህርት ለሕዝቡ ሲያስተምሩ ያድራሉ፡፡ ከጥዋቱ ፲፪ (ዐሥራ ሁለት) ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ወደመጠመቂያው ውኃ  በመሄድ በውኃው ላይ ጸሎት ከተደረገ እና ከተባረከ በኋላ የተሰበሰበው ሕዝብ በተጸለየበት ጸበል ይረጫል፡፡  

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት ምክንያት እርሱ ተጠምቆ ለነፍሳችን ድኅነት መሆኑን ሊያሳየንና ኃጢአታችን በጥምቀት እንደሚነጻ ለማመልከት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ከተወለደ በኋላ ፴ (ሠላሳ) ዓመቱ ነው፡፡ የዚህም ምክንያት አባታችን አዳም የሠላሳ ዓመት ፤ እናታችን ሔዋን ደግሞ የዐሥራ አምስት ዓመት ሆነው ሲፈጠሩ አዳም በ፵ (ዐርባ) ቀን፣ ሔዋን በ፹ (ሰማንያ) ቀን ከሥላሴ የተቀበሉትን ልጅነት ጠላታችን ዲያብሎስ  ዕፀ በለስን በልተው እንዲሳሳቱ ባደረጋቸው ሰዓት የሥላሴን ልጅነት በማጣታቸው ጌታችን በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቆ መልሶላቸዋል፡፡ ዛሬ ወንዶች በዐርባ ቀን፣ ሴቶች በሰማንያ ቀን በዕለተ ዓርብ ከቀኝ ጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ የምንወለድበት ምክንያትም አዳም በዐርባ ቀኑ፣ ሔዋን ደግሞ በሰማንያ ቀኗ ከሥላሴ ያገኙትን ልጅነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ (ኩፋ. ፬፥፱)  የምንጠመቀውም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ‹‹ወእንዘ  ታጠምቅዎሙ  በሉ በስመ አብ  ወወልድ  ወመንፈስ  ቅዱስ፤  ስታጠምቋቸውም  በአብ  በወልድና  በመንፈስ  ቅዱስ  ስም  አጥምቋቸው›› እንዲል፡፡ (ማቴ. ፳፰፥፲፱)  

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ሖረ ኢየሱስ እምገሊላ ኀበ ዮሐንስ ከመያጥምቆ በፈለገ ዮርዳኖስ›› በማለት እንደተናገረ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመሄድ በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ የተጠመቀበት ሰዓትም ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት ላይ ሲሆን ዕለቱም ዕለተ ሠሉስ ወይም ማክሰኞ ነበር፡፡ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት ምክንያት ደግሞ ጠላት ዲያቢሎስ የዕዳ (የበደል) ደብዳቤያችንን በዚያ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ቀብሮት ስለነበር በጥምቀቱ የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ ነው፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ ከሰማይ አብ በደመና ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት›› በማለት የባሕርይ አባትነቱን መሰከረ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ አረፈ፡፡ (ማቴ.፫፥፲፫-፲፯)

በዚህም መሠረት በዓለ ጥምቀት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀበት ከ፴ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሲከበር ይኖራል፡፡

እኛም የበዓሉን መታሰቢያ የምናደርገው እርሱ ጥምቀትን ስለባረከልን ጥምቀት ድኅነታችን መሆኑን አምነን ተጠምቀን እንድን ዘንድ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ሁላችን በሞቱ እንደተጠመቅን ሁላችሁ ይህን ዕወቁ፤ እኛ ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛ በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› በማለት በጥምቀት ክርስቶስን እንደምንመስለው ተናግሯል፡፡ ይህም ማለት ጌታችን እንደተጠመቀ እርሱን ክርስቶስን መስለን ክርስቲያኖች እንድንባል መጠመቅ እንዳለብን መረዳት ያስፈልጋል፡፡  (ሮሜ ፮፥፫-፬)

ልጆች! እናንተም በጥምቀት በዓል ከቤተ ሰቦቻችሁ ጋር ሆናችሁ በሥርዓቱ መሠረት እንድታከብሩ እየመከርናችሁ የዛሬን ትምህርት በዚሁ እንጨርሳለን፤ በደኅና ሰንብቱ! 

ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት፣ በረከት ያሳትፈን! አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

Read 808 times