Friday, 22 January 2021 00:00

በዓል እና ባህል  

Written by  በኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት  በርካታ መንፈሳዊ በዓላት አሉ፡፡ እነዚህም በዓላት በየሀገሩ፣ በየወገኑ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሥርዓት መሠረት ይከበራሉ፡፡ ለምሳሌም በዓለ ልደት፣ በዓለ ጥምቀት፣ በዓለ ሆሳዕና ወዘተ በተለያየ ቀን፣ በተለያየ ሥርዓት፣ በተለያየም የባህል ዐውድ ውስጥ ይከበራሉ፡፡ የግብጹን ከኢትዮጵያ፣ የሶርያውን ከአርመን የሚለየው ብዙ ሥርዓት ሊኖር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የበዓሉን ማእከልና ዓላማ ግን አንድ ነው እርሱም የበዓሉ ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ማመስገን ነው፡፡  አብያተ ክርስቲያናት ክርስቶስን በበዓሉ በመስበክ፣ በማክበር፣ በበዓሉም መባረክን በመፈለግ በኩል አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ዓላማ ስላላቸው የአንድ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ መሆናቸውን ይመሰከራሉ፡፡ በዓላት የሚከበሩበት የባህል ዐውድ ግን ከበዓሉ ዓላማ በላይ ከዋለ፣ በበዓሉ ዕለት ከሚነበበው ወንጌል፣ ከሚነገረው ተኣምር፣ ከሚሰበከው ስብከት በላይ በዓሉን ለማድመቅ ተብለው የገቡ በየጊዜው የዳበሩና እየተጨመሩ ያሉ አላባዎች ከገነኑ፤ የበዓሉም ዓላማ የበዓሉን የአከባባር መንገድና ጌጣጌጦች ማንገሥ ላይ ካተኮረ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ያለውን የበዓል መንፈስ እጅግ እያራራቀው፣ ሌላው ቀርቶ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንኳን በዓሉ ልዩ ልዩ ባህል ባላቸው ማህበረሰቦች መካከል መራራቅን ሊያስከትል ይችላል፡፡

 

ለምሳሌ በዓለ ጥምቀት ሲከበር በየባሕረ ጥምቀቱ በየጊዜው የሚጨመሩ ማድመቂያ ነገሮች የበዓሉን አክባሪዎች ትኩረት ወደሚከብረው ሳይሆን ወደ ማክበሪያው መንገድ እየሳበው ይመስላል፡፡ በየባሕረ ጥምቀቱ ደምቀው የሚከናወኑ የቁማር ጨዋታዎች፣ በየድንኳኑ ያሉ የንግድ ትርዒቶች፣ በየምእመኑ የሚደረገው የባህል ልብስ ትዕይንት፣ ከአርሞሪካው ጭፈራ እስከ ምንጃሩ ረገጣ የሚከናወነው ትርዒት ሁሉ ለበዓሉ አክባሪ ግርዶሽ ሆኖ ወደ ዋናው ዓላማ እንዳያተኩር እንቅፋት እየሆኑት ነው፡፡ 

ባህል መጠበቅ ማክበር መልካም ቢሆንም ምእመናን ከቤታቸው ገና ሲወጡ የክርስቶስን ጥምቀትና በጥምቀቱም የደመሰሰልንን ዕዳና የሰጠንን ጸጋ ሳይሆን ከላይ የተጠቀሱትንና ያልተጠቀሱትን ልዩ ልዩ ክዋኔዎች በዓይነ ኅሊናቸው አዝለው ለመውጣት የሚፈተኑበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ከዝማሬው፣ ከእልልታው ይልቅ በየጥጋጥጉ በሚገኙ ማረፊያ መጠጥ ቤቶች ጎራ ብሎ ቢራና ድራፍት እየጠጡ ስለፖለቲካው፣ ስለኢኮኖሚው፣ ስለኑሮ ውጣ ውረድ ሁሉ ሲያወጉ መቆየት በስፋት እየተለመደ ነው፡፡ ይህም እንደ ባህል ሆኖ ከበዓሉ የጎንዮሸ በስፋት በቅሏል፡፡ መንፈሳዊ በዓላትን በወጉ አክብሮ በመብላት በመጠጣት የበለጠ በዓሉን መዝከር ያለና የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን በዓል ማክበር ቁማሩ፣ ቢራና ድራፍቱ፣ የኮረዶች መሽኮርመም የጎረምሶች ማሽኮርመም ወዘተ እየሆነ ከቀጠለ ሃይማኖታዊው በዓል ሥጋዊ መልኩ ጎልቶ መንፈሳዊ ዓለሙ ደብዝዞ ወደ መጥፋት ይሸጋገራል፡፡

በዓሉ የንግድ ትርዒት መጥሪያ እየሆነ መምጣቱ በበዓሉ አደባባይና ዐውድ ከእምነቱ ውጪ የሆኑ ወገኖች ጭምር የሚሳተፉበት ክፍተኛ የንግድ ክንውን ይታያል፡፡ አሁን አሁን በዓሉ  መንፈሳዊውን ነገር በማጉላት ከሌላ እምነት የመጡ ወገኖችን እንኳን ሊሰብክና ሊያስተምር በሚችል መንገድ እየተካሄደ አይደለም፡፡ ስለዚህ ብዙዎች ነግደው አትርፈው ለመሄድ በጉጉት የሚጠብቁት በዓል እንጂ በምናንጸባርቀው መንፈሳዊ ትዕይንት ተገርመው ‹‹ምን ማለት ነው?›› ብለው እንዲጠይቁን የሚያደርግ አይደለም፡፡ 

ካህናቱና መዘምራን የበዓሉን ዓላማ ማእከል አድርገው አገልግሎታቸውን መፈጸማቸው እነሱን ተከትሎ ምእመናን ሁሉ አሜን እንዲሉ በማሰብ ነው፡፡ ነገር ግን የካህናቱ ሽብሸባ የመዘምራኑ እልልታ ተቀባይና አጃቢ እያጣ ምእመናን በሌላ የባህል ድንኳኖች ውስጥ ገብተው መለያየቱ ከሰፋ የቤተ ክርስቲያን በዓላት የካህናትና የሰንበት ተማሪዎች ብቻ ሆነው ሊንሳፈፉ ይችላሉ፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም የባህል ፈጠራ ማስፋፋቱ በየአህጉራቱ ልዩ ልዩ መልክ እየያዘ ስለመጣ የትኩረት ማእከሉ ባህል በሆነ መጠን በመንፈሳዊው በዓል ማእከልነት አንድነታችንን ማጽናት እንቸገራለን፡፡ በመላው ምእመናን መካከል አንድ መንፈስ ይዞ ክርስቶስን በማሰብ መመላለስ ይቀራል፡፡

በበዓለ ጥምቀት ብቻ ሳይሆን በሌሎች መንፈሳዊ በዓላት ከቤተ ክርስቲያናዊ ሥርዓቱ ይልቅ በቤት ውስጥ መስተንግዶ፣ በዳቦው በቅርጫው በዶሮ ገበያው ወዘተ ነፍሳት ተይዘው በዓሉ ገብቶ እስኪወጣ የበዓሉን ባለቤት በወጉ ሳያስቡ የሚያልፍባቸው በርካቶች ሆነዋል፡፡ ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ጸሎቱ…ወዘተ የጥቂቶች ብቻ እየሆነ እየቀረ ነው፡፡ 

በዓላችንን የሚመሩት ሚዲያዎች እንጂ ቤተ ክርስቲያን መሆኗ እየቀረ ነው፡፡ ሚዲያዎች ደግሞ ባህላዊ ይዞታዎች ላይ፣ ንግድ ትርዒትና ባዛሮች፣ የሙዚቃ ድግሶች ላይ፣ በዓሉን ተከትለው በሚዘጋጁ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚያዘጋጇቸው ልዩ ልዩ ክዋኔዎች ላይ አተኩረው ነው፡፡ ስለዚህ በዓላችን በአዲስና በነባር የባህል እሴቶች እየተደፈቀ ነው፤ ከቀደመው በባሰ መልኩ የመንፈሳዊው በዓል ዓላማና ተግባር ተሳታፊዎች ጥቂት ምእመናን እንዲሆኑ እያስገደደ ነው፡፡ በዓላችን እየመራ ካልሄደ ባህል የሚመራው ከሆነ ሃይማኖታዊ መልኩ ይጠፋል፡፡ 

በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ሌሎችም ወገኖች እስከሚታዘቡት ድረስ ሥጋዊ መልኮቻቸው እየጎሉ የመጡትን የበዓላት አከባበራችን ወደ ቀደመ ክብርና ለዛቸው መመለስ የዘመናችን አገልጋይ ካህናት ኃላፊነት ይሆናል፡፡  ሊቃውንቱ በበዓላቱ መድረኮች ሁሉ ከዚህ አንጻር ምክርና ተግሳጽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምእመናንም የሊቃውንቱን ምክር ሰምተው ነገሮቻቸው ሁሉ የበዓሉን መንፈሳዊ ዓላማ የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ መትጋት ይገባቸዋል፡፡ 

 

 

Read 694 times