ከዚሁ በተጓዳኝ ለአቅመ ሔዋንም በደረስኩ ጊዜ ለሕይወት አጋር ሊሆኑኝ ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸው ወንዶች ለትዳር ሳይሆን ለሥጋዊ ፍላጎት ብቻ የሚፈልጉኝ ሆኑብኝ፤ ይህም ጥላቻዬን አባባሰው፡፡ በሥራም ሆነ ማኅበራዊ ሕይወቴ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በተደጋጋሚ ጉዳት አድርሰውብኛል፡፡ ከቤተሰብ ጋርም ያለው ሁኔታ እየባሰ በመምጣቱ ከእነርሱ ጋር መኖር የማልችልበት ደረጃ ላይ ደረስኩኝ፡፡ ምንም እንኳን ያጠራቀምኩት ገንዘብ ባይኖረኝም የራሴን ሕይወት ለመመሥረት ከበቤተሰቦቼ ወጥቼ ብቻዬን መኖር ጀመረኩ፡፡ በዚህም ተጽዕኖ ሰዎች በሕይወቴ ቦታ እንዲኖራቸው አልፈልግም፡፡ አዳዲስ ሰዎችንም የመቅረብ ምንም ዓይነት ፍላጎት የለኝም፡፡ በአጋጣሚዎች የማገኛቸውንም ከአንገት በላይ በሆነ ቀረቤታ እቀርባቸዋለሁ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተዋወኳቸውንም ደግሞ ለሴት ጓደኝነትም ሆነ የሕይወት አጋርነት ማሰብ እየተሳነኝ እቸገራለሁ፡፡ እውነተኛ የሴት ጓደኛም ሆነ ጥሩ ወንድ የለም እስከማለት ደርሻለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ አመለካከት በእኔ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አምጥቷል፤ ማኅበራዊ ሕይወትም እንዳይኖረኝም አድርጓል፤ ጥላቻዬም እያደረ ክፋት አሳስቦ ወደ ጥፋት እንዳይመራኝ እባካችሁ እርዱኝ እላለሁ፡፡
ውድ የምሥጢሬን ላካፍላችሁ ጠያቂያችን በቅድሚያ መንፈሳዊ መፍትሔ አገኛለሁ ብለሽ ጥያቄውን ስላቀረብሽ እያመሰገንን ለጥያቄው የሚከተለውን ምላሽ አቅርበናል፡፡
ወድ ጠያቂያችን ከጥያቄሽ ለመረዳት እንደቻልነው በገዛ ቤተ ሰብሽ ውስጥ የተለያዩ የአንቺን ፍላጎት የሚጋፉ ፣ብሎም አካላዊ ጥቃት እንዳደረሱብሽ ገልጸሻል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው ‹‹ በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን?›› ኢዮ ፯፥፩ ይላል፡፡ እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› ዮሐ ፲፮፥፴፩ ብሏል፡፡ ስለዚህ የሰው ሕይወት ፈተና እና ውጣ ውረድ እንደማይለየው በመጀመሪያ መረዳት ተገቢ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደገለጸው በምድር ላይ የኢዮብን ያህል ፈተና የተፈራረቀበት ሰው ማግኘት ይከብዳል፡፡ ጻድቁ ኢዮብ ዐሥር ልጆቹን በአንድ ቀን ያጣ፣ ሀብቱ ሁሉ በአንድ ቀን የወደመበት፣አካሉ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ በክፉ ቁስል የተመታ ነበር፡፡ በትዳር አጋሩ (በሚስቱ) እና በጓደኞቹ ሳይቀር የተለያየ መከራን በጸጋ የተቀበለ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን ኢዮብ ይህን ፈተና ሁሉ በትዕግሥት ከተቀበለ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ የጻድቁ ኢዮብ ጽናቱን አይቶ ሀብቱን እጥፍ ድርብ አድርጎ መለሰለት፡፡
ሐዋርያው ያዕቆብ ይህን ሲመሰክር ‹‹ወንድሞች ሆይ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ፡፡ እነሆ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን ኢዮብ እንደታገሠ ሰምታችኋል ጌታም እንደፈጸመለት አይታችኋል፡፡ ›› ያዕ ፭፥፲፩ በማለት ጻድቁ ፈተናውን በጽናት ከተወጣ በኋላ የተደረገለትን በረከት ይነግረናል፡፡ ‹‹ እግዚአብሔርም ቀድሞ በነበረው ገንዘቡ ሁሉ ፋንታ ከዚያ በላይ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው›› (ኢዮ ፵፪፥፥፲) በማለት ያረጋግጥልናል፡፡
ይህ ሁሉ ፈተና የደረሰበት እርሱ ጻድቁ ኢዮብ ማነው? ብለን በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጻድቁ ኢዮብ የተጻፈውን ስናይ ኢዮብ ፩ኛ. ፍጹም ነው
፪ኛ. ቅን ነው
፫ኛ. እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው
፬ኛ. ከክፋትም የራቀ መሆኑ የተመሰከረለት ጻድቅ ሰው ነው ኢዮ ፩፥፩‐፪፡፡
ውድ ጠያቂያችን በጻድቁ ኢዮብ ሕይወት አንጻር ፈተና ደርሶብኝ ቤተሰቦቼን እስክጠላቸውና እስክጠራጠራቸው ያደረሰኝ ሕይወት ላይ ነኝ ፤ እንዲሁም የአካል ጉዳት ደርሶብኛል የሚለውን ኃሳብ ጻድቁ ከደረሰበት ፈተና አንጻር የእኔ ሕይወት እንዴት ነው ብለሽ መመልከቱ በተወሰነ መልኩ ለጥያቄሽ መልሽ ይሰጥሻል፡፡
ከላይ እንደገለጽነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› በማለት ማስተማሩ የዚህን ዓለም መከራና ሥቃይ አስቀድመን እንድናውቀውና አዲስ ነገርም እንዳይሆንብን ጭምር ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ እኔን መከተል ቢወድ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› ማቴ ፲፮፥፳፬ ብሎ ማስተማሩን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡ ለመሆኑ ራስን መካድ ማለት ምን ማለት ነው? እኔ ሰው አይደለሁም ማለት ነውን? በእርግጥ እንዲህ ማለት አይደለም፡፡ ውድ ጠያቂያችን ራስን መካድ ማለት እውቀት፣ ሀብት ፣ ሥልጣን ፣ዘመድ ቢኖር በእርሱ አይመካ ማለቱ ነው፡፡ ‹‹ የሚመካ ቢኖር በእግዚአብሔር ይመካ እንዲል ›› ፩ኛ ቆሮ ፩፥፴፩ ፡፡
ከላይ እንዳየነው መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ ማለት ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› ተብሏልና የደረሰብንን ግፍና መከራ በአኮቴት (በምስጋና) ተቀብሎ እንደ ኢዮብ በፈተና መጽናት ማለት ነው፡፡ ‹‹ወንድሞች ሆይ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደሙሉ ደስታ ቁጠሩት›› (ያዕ ፩፥፪‐፫) እንዳለ ቅዱስ ያዕቆብ በደረሰብሽ ፈተና ሳትማረሪና ተስፋ ሳትቆርጪ እንደ ሙሉ ደስታ ልትቆጥሪው ይገባል፡፡
ይህ ፈተና በቅድሚያ የደረሰብሽ ከቤተሰቦችሽ በመሆኑ የእምነትሽን ጽናት ለማየት የቀረበልሽ ፈተና መሆኑን መገንዘብ ይገባሻል፡፡ በመጽሐፈ ኢዮብ ‹‹ ዓለም ሁሉ ዞርኳት›. ያለው ጥንተ ጠላታችን ቤተሰቦችሽ በአንቺ ላይ እንዲነሳሱ እና የአካል ጉዳትም ጭምር እንዲያደርሱብሽ ያደረገው ፈታኝ (ዲያቢሎስ)መሆኑን ልታወቂበት ይገባል፡፡ ‹‹ ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ››(ያዕ ፭፥፲፫) እንዳለው በቤተሰቦችሽ ላይም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ ቶሎ ተስፋ ወደ መቁረጥ ሳትሄጂ ‹‹ የደረሰብኝ መከራ ለበጎ ነው›› ብለሽ ኅሊናሽን አሳምነሽ ከሁሉ በፊት ጸሎትን የሕይወትሽ አንድ ገጽታ አድርገሽ ልትጓዢ ይገባል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልዕክቱ ‹‹በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ›› (ፊል ፬፥፯) እንዳለው በነገር ሁሉ ሲል በጥቂትም በብዙም ፣ በውስጥም በውጪም ፤ በሚታየውም ሆነ በማይታየው ሁሉ ነገር ሲያጋጥማችሁ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ እንድናስታውቅ ያዛልና ይህን የሕይወት መመሪያ ልታደርጊው ይገባል፡፡
ለደረሰብሽ ነገር ሁሉ በቅድሚያ በጸሎት እግዚአብሔርን መጠየቅ ይገባሻል፡፡ ስትጸልይ ደግሞ ሐዋርያው በምልጃ እንዳለ ስለናትህ ቅድስት ድንግል ማርያም ብሎም ስለቅዱሳንህ ሁሉ ብለህ የዚህን ፈተና መውጫ መንገዱን አመልክተኝ ብለሽ መለመን ይገባሻል፡፡ ስለደረሰብሽ ነገር ሁሉ ደግሞ ሳትማረሪ እግዚአብሔርን አመስግኝ፡፡ ‘’እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን’’ (ሮሜ ፰፥፳፰) ተብሎ ተጽፏል፡፡
ከዚህም በተጓዳኝ ከቤተሰቤ ተለይቼ ብቻዬን እየኖርኩ እገኛለሁ ብለሻል፡፡ ለመሆኑ አንቺ የዘረዘርሻቸውን ፈተና ያደርሱብሽ ቤተሰቦችሽ ወደው ይመስልሻል? ስለሆነው ነገር ሁሉም ለቤተሰቦችሽም ጸልይላቸው፡፡ እንኳን ቤተሰቦችሽ ይቅርና ሌላም አካል ይህንን ፈተና ቢያደርስብሽ ልትጸልይለት ይገባል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘’በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁንም መርቁ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ ስለሚያሰድዷችሁም ጸልዩ’’ (ማቴ ፵፬፥፵፭ ) ብሏልና፡፡
አበው ‘’እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል’’ እንዲሁ እንጂ በቤተሰቦችሽ ከደረሰብሽ ፈተና የተነሳ ሰውን ሁሉ ወደ መጠራጠር ተጉዘሻል፡፡ እኔ ለትዳር ያሰብኳቸውም እንኳን ቢሆኑ እነርሱ ግን ለሥጋዊ ፍላጎት ብቻ የሚፈልጉኝ ሆነብኝ ምን ይሻለኛል? ላልሽው በመጀመሪያ ከትዳሩ በፊት አንቺ ሕይወትሽ በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን የታነጸ ይሆን ዘንድ ቅድሚያ የነፍስ አባት ይዘሽ ዘወትርም በፀሎት እየተጋሽ ተጓዥ፡፡ ጌታችን ለምጻሙን ሰው ካዳነው በኋላ ‘’ሂድ ራስህን ለካህን አሳይ’’ (ማቴ ፰፥፬) በማለት እንዳዘዘው አበነፍስ ይዘሽ የተሰጠሽን ቀኖና በተግባር ፈጽሚ፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ ወደ ቅዱሳት መካናት እየተጓዝሽ አበው በጸሎታቸው እንዲያስቡሽ አስደርጊ ‘’የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች’’ (ያዕ ፭፥፲፮) ይላልና፡፡
እውነተኛ የሴት ጓደኛም ሆነ ጥሩ ወንድ የለም እስከ ማለት ደርሻለሁኝ ያልሽውም ስሕተት መሆኑን በቅድሚያ ለኅሊናሽ ንገሪው ምክንያቱም ሁሉም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ስሑታን ናቸው ብሎ ለመቀበል ይከብዳልና፡፡ በመጽሐፍ ‘’ከቸር ሰው ጋር ቸር ሁነህ፣ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሁነህ፣ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሁነህ ትገኛለህ፣ ከጠማማ ሰው ጋር ጠማማ ሁነህ ትገኛለህ’’ (መዝ ፲፯፥፳፭-፳፮ )ተብሏልና፡፡
ከወንድም ሆነ ከሴት ጓደኞችሽ ቸር ፣ ቅን ፣ ንጹሕ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ ጠማማ የሆኑም ሊኖሩ እንደሚችሉ እንጂ ሁሉንም ሰው አንድ ዓይነት ጠባይ አላቸው ብለሽ አትራቂያቸው፡፡ ከመንፈሳውያን ጓደኞችሽ የምታገኚው ጠቃሚ ምክር መኖሩንም አትዘንጊ፡፡
አበው‹‹ ሰይጣን ተስፋ የለውም ፤ግን ተስፋ አይቆርጥም›› የሚል ብሂል አላቸው፡፡ ክርስቲያን ደግሞ ተስፋ እያለው ተስፋን መቁረጥ አይገባውም ይልቁንም ‹‹ አሁንስ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥትም ከአንተ ዘንድ ነው››(መዝ ፴፱፥፯) በማለት እንደ ቅዱስ ዳዊት ተስፋሽን በእግዚአብሔር ላይ አድርገሽ በትዕግሥት ነገሮችን ሁሉ እንደአመጣጣቸው ትቀበዪ ዘንድ ይገባል፡፡
ውድ ጠያቂያችን በዚህ ሰዓት ከሁሉ ማስቀደም ያለብሽ ጉዳይ ከቤተሰብሽ፣ የትዳር አጋር ከመፈለግሽ ፣ ከጓደኛም በፊት ሕይወትሽ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ያማረ ይሆን ዘንድ ዘወትር ስለነፍስሽ አስቢ፣ ንሰሓ ግቢ፣ በጸሎት በርቺ ፣ በጸሎት እንዲያስቡሽ ወደ ቅዱሳን መካናት ስመ ክርስትናሽን ከመብአ ጋር ላኪ፡፡ በተጨማሪም ስለደረሰብሽ ነገር ሁሉ ሳታማርሪ እግዚአብሔርን አመስግኚው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ኤርምያስ አድሮ ‹‹ ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም›› (ኤር ፳፱፥፲፩) ብሏልና የሰላም አምላክ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአንቺ የሚያስፈልግሽን እንደሚሰጥሽ አምነሽ በጸሎት ተማፀኚ፡፡ ከላይ በመግቢያሽ የዘረዘርሻቸውን ፈተናዎች እንድትቋቋሚው ኃይል የሰጠሸ አማላክ ካንቺ ጋር መሆኑን እመኚ፡፡
ጌታችን በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ሆኖ ለሰቃዮቹ እንዳዘነላቸውና እንደራራላቸው በአንቺ ላይ ክፉ ነገር ላደረሱብሽ ሁሉ ‹‹ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› እያልሽ ጸልይላቸው፡፡ ሊቀ ዲያቆናት ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም በድንጋይ እየወገሩት እርሱ ግን ወደ አምላኩ እንደጸለየላቸው አንቺም አውቀሽ ጸልይላቸው፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ፣ ሐሳብ ተሳክቶ ለምስጋና የምትቆሚበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እመኚ፡፡ ስለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት ካንቺ ጋር ይሁን፡፡