Tuesday, 09 February 2021 00:00

አስተርእዮ ማርያም

Written by  በእህተ ሚካኤል
የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከርማችኋል? በእግዚአብሔር ጥበቃ በሰላምና በጤና እንደቆያችሁን ተስፋ እናደርጋለን፤ በቤታችሁ ሆናችሁ ትምህርታችሁን በንቃት እየተከታተላችሁ ነው? በጣም ጎበዞች! በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋልና በርቱ!  ልጆች! ዛሬ የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናልና ተከታተሉን! ልጆች! በመጀመሪያ ‹‹አስተርእዮ›› ማለት መገለጥ ማለት ነው። ‹‹አስተርእዮ›› ቃሉ ‹‹አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ›› ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው።  ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢሱስ ክስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት (የታየበት) አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ዋዜማ ጊዜ ‹‹ዘመነ አስተርእዮ›› ይባላል።

 

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍት ጥር ፳፩ ስለሆነ እና በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር ‹‹በዓሉ አስተርእዮ ማርያም›› ይባላል። 

ልጆች! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአባቷ ከቅዱስ ኢያቄምና ከእናቷ ከቅድስት ሐና ከተወለደችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዐረፈችበት ጊዜ ድረስ በምድር ላይ ፷፬ ዓመታትን ኖራለች።  እመቤታችን ከተወለደች በኋላ በእናት በአባቷ ቤት ፫ ዓመት፣ በቤተ መቅደስ ውስጥ ፲፪ ዓመት ፣በቤተ ዮሴፍ ፱ ወር ከልጅዋ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ፴፫ ዓመት ከ፫ ወር እንዲሁም ከጌታ ዕርገት በኋላ ከወንጌላዊው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ደግሞ ፲፭ ዓመት በድምሩ ፷፬ ዓመታትን በዚህ ዓለም ኖራ ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በክብር ዐርፋለች። 

ልጆች! የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ አባቶቻችን በጾመ ፍልሰታ ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያም ሲተረጉሙ ዕረፍቷ በጥር ፳፩ በዕለተ እሑድ ነው።  እመቤታችን በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመት ኖራ ጥር ፳፩ ቀን በዕለተ በእሑድ ጌታ እልፍ አእላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ ‹‹እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ›› አላት።  

እመቤታችንም ‹‹ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማሕጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን?›› አለችው።

ጌታም በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ ‹‹እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል›› አላት። እመቤታችንም ‹‹እኒህን ከማርክልኝስ ይሁን›› አለችው። ጌታም ቅዱስ ሥጋዋን ከቅድስት ነፍሷ ለይቶ በዝማሬ መላእክት ዐሳረጋት። ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ሥጋዋን በክብር ዐሳርፉ አላቸው።

ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሴማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ ቀድሞ ልጇን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሡ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም ተራምዶ የእመቤታችን አስከሬን ያለበትን አጎበር ጨበጠው። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ የታውፋንያን እጆች በሰይፍ ሰየፋቸው እጆቹም ከአጎበሩ ላይ  ተንጠልጥለው ቀሩ። ታውፋንያ በዚህ ጊዜ‹ ‹‹በእውነት የአምላክ እናት ናት›› በማለት ስለአመነ እጆቹ ተመለስው እንደነበሩ ሆኑለት። 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የእናቱን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋ ተቀብሎ ከሐዋርያት ቅዱስ ዮሐንስን በማስከተል  በደመና ነጥቆ ከገነት በማስገባት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት። ቅዱስ ዮሐንስ ወደ እነሱ ሲመለስም ሐዋርያት ስለ እመቤታችን ጠየቁት እርሱም ‹‹ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች›› አላቸው።  ሐዋርያትም ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው እመቤታችንን እንዲያሳያቸው በነሐሴ መጀመሪያ  ጾም ጀመሩ ሁለት ሱባዔ (ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፬) እንደጾሙ ጾሙ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ የእመቤታችንን ሥጋ ሰጣቸው ሐዋርያትም በክብር ተቀብለው ቀበሯት። 

እመቤታችንም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ተነሥታለች። እመቤታችን በተነሣች ጊዜ ቅዱስ ቶማስ አልነበረም በደመና ተጭኖ ከሚሰብክበት ሀገረ ስብከቱ ሲመጣ እመቤታችን ወደ ሰማይ ስታርግ አገኛት።  እሱም ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ዛሬ ደግሞ የአንችን ትንሣኤ ሳላይ ልቀርነውን?›› ብሎ ሲያዝን እመቤታችን ‹‹አይዞህ አትዘን እነርሱ ትንሣኤዬን ዕርገቴንም አላዩም አንተ ግን አይተሃልና ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው›› ብላ የያዘችውን (የተገነዘችበትን) ሰበን ሰጥታ ላከችው። 

ከዚህ በኋላ ሐዋርያው ቶማስ ወደ ሐዋርያት በመሄድ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ? በማለት ጠየቃቸው።  እነርሱም አግኝተን ቀበርናት አሉት።  እርሱም ‹‹ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተው ይህ ነገር አይመስለኝም›› አላቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም አንተ ሁል ጊዜ ለምን ትጠራጠራለህ?  ብሎ በመገሠጽ እመቤታችን የተቀበረችበትን ሊያሳየው ወደ መቃብሩ ይዞት ሄደ።  ከመቃብሩም ደርሰው ቢከፍተው እመቤታችንን አጣት በዚህን ጊዜ ደንግጦ ቆመ።  

ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች፤ ዐረገች አላቸው የያዘውንም ሰበን ሰጣቸው ሐዋርያትም ለበረከትም ተካፈሉት። በዓመቱ ደግሞ ሐዋርያት ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው መጾም ጀመሩ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጾምና ጸሎታችውን ተቀብሎ በ፲፮ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን ቅዱስ እስጢፋኖስን ደግሞ ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቈረባቸው። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መታሰቢያ አድርጋ በዓለ ዕረፍቷን በየዓመቱ ታከብረዋለች።  

ልጆች! እናንተም በጥር ፳፩ የአስተርእዮ ማርያም  በዓል ከቤተ ሰቦቻችሁ ጋር ሆናችሁ እንዳከበራችሁ ተስፋ እናደርጋለን።  በሉ የዛሬን  ትምህርት በዚሁ እንጨርሳለን፤ በደኅና ሰንብቱ! 

ከእመቤታችን ረድኤት፣ በረከት ያሳትፈን! አሜን። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Read 624 times