Tuesday, 23 February 2021 00:00

አባ ገላስዮስ

Written by  እህተ ሚካኤል
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከረማችሁ? አሜን የአባቶቻችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!  ልጆች ትምህርታችሁን በንቃት እየተከታተላችሁ ነው? እያጠናችሁስ ነው? በርቱ ትምህርታችሁን በተገቢው መንገድ በመከታትል በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋል! ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው አባ ገላስዮስ ስለሚባል ቅዱስ አባት ታሪክ ነው፤ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!                                                                       ልጆች አባ ገላስዮስ እግዚአብሔርን ከሚያመልኩና ከሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያን ወላጆች የተገኘ ቅዱስ አባት ነው።    ቤተ ሰቦቹም ልጃቸው ገላስዮስን ከሕፃንነቱ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩት በምግባርና በሃይማኖት ኮትኩተው አሳደጉት።    በኋላም ገላስዮስ የዲቁና ማእረግ ተቀበለ።    ቅዱስ ገላስዮስም ከትንሽነቱ ጀምሮ ይህንን ዓለም በመናቅ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር የሚተጋ መነኩሴ ሆነ።    በምንኩስና ሆኖ በጾም በጸሎት እየተጋደለ መኖር ጀመረ።    እግዚአብሔር አምላክም የቅዱስ ገላስዮስን ትጋት ተመልክቶ በአስቄጥስ ገዳም ባሉ መነኮሳት ላይ ቅስና ተሾመ።    በአስቄጥስ ገዳም ሆኖ በታላቅ ተጋድሎ የገዳሙን ማኅበረ መነኮሳት እያገለገለ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ለአባ ጳኩሚስ እንደተገለጠ ለአባ ገላስዮስም ተገለጠለት።    በገዳሙ ያሉ መነኮሳትንም ሰብስቦ እግዚአብሔርን መፍራትንና የምንኩስናን ሕግ እንዲያስተምራቸው አዘዘው። በገዳሙ የሚገኙ መነኮሳትን በመሰብሰብም መንፈሳዊ የሆነ የአንድነት ማኅበራዊ የኑሮን ሥርዓት ሠራላቸው።  አባ ገላስዮስም በመነኮሳቱ መካከል ሲኖር እጅግ ትሑት ከመሆኑ የተነሳ እንደ መምህራቸው ሳይሆን ከእነርሱ እንደሚያንስ እንደ አገልጋያቸው ይሆን ነበር።    አባ ገላስዮስ በአስቄጥስ ገዳም መነኮሳቱን በፍጾም የዋህነት፣ ቸርነትና በመታዘዝ ያገለግላቸው ነበር።    በዚያም ሳለ የብሉይ ኪዳን እና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በአንድነት ሰብስቦ አንድ ታላቅ መጽሐፍ ጻፈ። ይህን ታላቅ መጽሐፍ ለማጻፍም ፲፰ የወርቅ ዲናር አወጣ።    ያንንም ታላቅ መጽሐፍ መነኮሳቱ ለማንበብ በሚፈልጉ ጊዜ እንዲያገኙት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአትሮንስ ላይ አኖረላቸው።    አንድ ሰውም ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋዊ አባ ገላስዮስን ሊጎበኝ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጣ። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሲዘልቅም ማንም አልነበረም፤ ነገር ግን ያንን ታላቅ መጽሐፍ በአትሮንስ ላይ ተቀምጦ አየና ሊወስደው ፈለገ። ጨለማ በሆነ ጊዜም ተመልሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጣና ማንም ሰው ሳያየው መጽሐፉን ሰርቆ ወጣ ሊሸጠውም ወደ ከተማ ይዦት ሄደ።    አንድ ሰውም መጽሐፉን ሊገዛው ፈልጎ ‹‹የመጽሐፉ ዋጋ ምን ያህል ነው? አለው።    ሌባውም ‹‹ ፲፯ የወርቅ ዲናር ስጠኝና ውስደው›› አለው።    ገዢውም ‹‹ያልከውን ፲፯ የወርቅ ዲናር እሰጥሃለሁ ነገር ግን ለወዳጄ ወስጄ እስካሳየው ድረስ ጥቂት ታገሰኝ›› አለው።    ሌባውም በዚህ ስለተስማማ ገዚው መጽሐፉን ወደ አባ ገላስዮስ ዘንድ ይዞ በመሄድ ‹‹ አባቴ ሆይ! ይህ መጽሐፍ ተመልከትልኝ፤ መልካም ከሆነ እገዛዋለሁ›› አለው።    አባ ገላስዮስም መጽሐፉን ሊገዛ የመጣውን ሰው ‹‹ መጽሐፉን ሊሸጥልህ ያለው ሰው ምን ያህል ገንዘብ ጠየቀህ?›› አለው።    ገዥውም ‹‹ ፲፯ የወርቅ ዲናር ጠየቀኝ›› በማለት ነገረው።    አባ ገላስዮስም ‹‹መጽሐፉ መልካም ነው ዋጋው ቀላል ነው ግዛው›› አለው።     ገዥውም ወደ ሌባው ተመልሶ እና አባ ገላስዮስ የነገረውን ደብቆ ‹‹ ለአባ ገላስዮስ አሳየሁት እርሱም ዋጋው በዝቷል አለኝ ›› አለው።     ሌባውም ‹‹ያ ሽማግሌ ሌላ የተናገረህ ነገር የለም? ››  በማለት ገዢውን ጠየቀው።    ገዢውም ‹‹አዎን ሌላ ምንም ነገር አልተናገረኝም›› አለው።    በዚህ ጊዜ ያ መጻተኛ ሌባ ‹‹ ይህን መጽሐፍ በፍጹም አልሸጠውም›› ብሎ ወደ አባ ገላስዮስ ሄደ።    ከእግሩ በታች ወድቆም ‹‹ ሰይጣን አስቶኛልና ይቅር በለኝ ፤ መጽሐፍህንም ውሰድ›› ብሎ ለመነው።     የከበረ አባ ገላስዮስ ግን ‹‹ እኔ መጽሐፉን መውሰድ አልሻም ሽጠህ የወርቁን ዲናር ለምትፈልገው ተግባር አውለው›› አለው።    ሌባውም በፊቱ እያለቀሰ እና እየሰገደ ብዙ ለመነው፤ ከብዙ ድካም በኋላ አባ ገላስዮስ መጽሐፉን ተቀበለው።    ይህንንም ምሥጢር ከሁለቱ በስተቀር ማንም አያውቅም ነበር።     ልጆች የአባ ገላስዮስን ደግነት አያችሁ? መጽሐፉን ሊገዛው የነበረው ሰው ይዞለት ሲመጣ ‹‹የኔ ነው፤ ተሰርቆ ነው›› ብሎ አላጋለጠውም ይህን ማድረጉ ሌባው የአባ ገላስዮስን መጽሐፍ በመስረቁ ተጸጽቶ እንደመለሰለት አስተውሉ።     ልጆች! ከዚህ በኋላ ለአባ ገላስዮስ ትንቢት የመናገር ሀብት ተሰጠው፡፤ ብዙ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ያደርግ ነበር።    በአንዲት ዕለትም የገዳሙ ወጥ ቤት የሚሠራው ሰው ለገዳሙ መነኮሳት ዓሳ ወጥ ሰርቶ አንዱን ልጅ በመጥራት ‹‹ እስክመለስ ድረስ ጠብቅ›› ብሎት ወደ ሥራው ሄደ።    እንዲጠብቅ የታዘዘው ልጅ ግን ለገዳሙ መነኮሳት ከተቀመጠው ዓሳ በላ።     ወጥ ቤት ሠራተኛውም ተመልሶ ሲመጣ ወጡ ተበልቶ በማግኘቱ ልጁን ‹‹ አረጋውያን አባቶች ሳይባርኩት እንዴት ደፍረህ ትበላለህ? አለው።    የቁጣ መንፈስም በልቡ አደረና ልጁን ረግጦ ገደለው፤ ልጁ ፈጽሞ እንደሞተ አይቶ እጅግ ደነገጠ።     ታላቅ ፍርሃትም ፈራና ወደ አባ ገላስዮስ ሄዶ የሆነውን ሁሉ ነገረው።    አባ ገላስዮስም ወጥ ቤት ሠራተኛውን ‹‹የልጁን ሬሣ ወስደህ ከቤተ መቅደሱ ፊት አስተኛው›› በማለት አዘዘው።    ወጥ ቤት ሠራተኛውም አባ ገላስዮስ እንዳዘዘው አደረገ።    ማታም በሆነ ጊዜ አረጋውያን መነኵሳት በቤተ ክርስቲያን ጸሎት አድርገው ወጡ።    አረጋዊ አባ ገላስዮስም ከእነርሱ ጋር በወጣ ጊዜ የሞተው ልጅ ተነሥቶ ከኋላው ተከተለው ይህንን ማንም አላወቀም ነበር።     እርሱም የገደለውን ባለወጥ ለማንም እንዳይናገር አዘዘው።    የተመሰገነ አባ ገላስዮስም ያማረ ትሩፋቱንና ተጋድሎውን ፈጽሞ ፤ እግዚአብሔርን አገልግሎ ፤ይህንንም በጎ ተግባር መታሰቢያ ትቶ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሰላም ዐረፈ።    ልጆች ከታሪኩ ብዙ መንፈሳዊ እውቀት እንደቀሰማችሁ ተስፋ እናደርጋለን።    በሚቀጥለው ትምህርታችን እስክንገናኝ በትምህርታችሁ ጎብዛችሁ እንድታጠኑ ደግሞም በጸሎትና በጾም እንድትበረቱ እንመክራችኋለን፤ ደኅና ሰንብቱ!  ልጆች! የአባ ገላስዮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን አሜን! ምንጭ ፦ ስንክሳር የካቲት ፲፪  
Read 503 times