Tuesday, 23 February 2021 00:00

‹‹ምን አለበት››

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
ክርስትና ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ይጠራል፤ የጠራቸውን ደግሞ አስተምሮ አጥምቆ ይመርጣል፤ የመረጣቸውን ደግሞ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አሳድጎ ያጸድቃል።      ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአንድ ክርስቲያን ጉዞው ቤተ ክርስቲያን በሠራችው ሥርዓት ውስጥ ነው።    ያለሥርዓት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠትም ይሁን መቀበል አይቻልም። በመሆኑም ያለሥርዓት መመላለስ ለቤተ ክርስቲያን አለመታዘዝ ነው። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የክርስቶስ አካል ስለሆነች ለክርስቶስ አለመታዘዝ ይሆናል።    መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን።›› ፩ኛ ቆሮ ፲፬፥፵ ይላል።    ለአንዳንዶች ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አላስፈላጊ፣ ተደራቢ፣ ትርፍ ነገር ይመስላቸዋል።  ለኦርቶዶክሳውያን ግን አግባብ በሆነ መንገድ እግዚአብሔርን ለማምለክ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።    በመሆኑም ቅዳሴው፣ ጥምቀቱ፣ በዓላቱ፣ ጾሙ፣ ትምህርቱ /ስብከቱ/ ወዘተ በሥርዓት የሚከናወን ነው።   

 

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደ አካባቢው ሁኔታ፣ እንደ ማኅበረሰቡ አኗኗርና ልማድ ከኃጢአት ወይም ለኃጢአት ከሚያበረታታ ሁኔታ በጸዳ፣ ቀንበር ሆኖ ለምእመናንም ሆነ ካህናት የማያደናቅፍ ሆኖ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርጎ፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ መመሪያ የሚሆን ነው።     

ይህንን ባለመረዳት አንዳንድ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ውስጥ መከበር ያለባቸውን ሥርዓቶች ‹‹ምን አለበት›› በሚል መንፈስ ሲጥሷቸው፣ ለሌሎችም የስንፍና ምሳሌ እየሆኑ ይታያሉ። ለምሳሌም በቤተ ክርስቲያ ቅዳሴ ሲደረግ መከበር ያለባቸው ሥርዓቶች ከአለማወቅ እስከ መናቅ ችግሮች ይታያሉ። ለዚህም የተወሰኑትን ማስታወስ እንችላላን።   

የመጀመሪያው ችግር ሥርዓተ ቅዳሴ በሚፈጸምበት ጊዜ መግቢያ መውጫ ሰዓቶችን አለማክበር ነው።   የሥርዓተ ቅዳሴ መግቢያ መውጫ ማወቅ በሥርዓቱ በአግባቡ ለመሳተፍ የሚከናወንበትን ጊዜ ማወቅ ያስፈልጋል።    መቼ ቀን በምን ሰዓት ይገባል፤ ይወጣል የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ራስን በሥርዓቱ በተገቢው ጊዜ ጀምሮ በተገቢው ጊዜ በመፈጸም እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ለመሳተፍ ያስችላል።  ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ሌሎች በሚገባው ጊዜ ገብተው በቅዳሴው የሚሳተፉ ትጉሃንን ያለጊዜው በሚገቡና በሚወጡ ሰዎች ሳይታወኩ አገልግሎቱን እንዲሳተፉ ያደርጋል።  በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ አባቶቻችን ለሠሩት ሥርዓት በመታዘዝ ፍቅራችንን እንገልጻለን።  ሌላውና ዋነኛው ነገር ደግሞ የእግዚአብሔር ስሙ በትጉሃን በተመስጦ በሚጠራበት በሚወደስበት የአምልኮት ሰዓት እንደ ሥርዓቱ በመመላለስ አምላካችንን እናከብራለን።   

ሌላው አለባበሳቸውን አንደሥርዓቱ ማድረግ ሲገባቸው ያለሥርዓት ለብሰው በቅዳሴው የሚሳተፉ ሰዎች ምን አለበት የሚል አቋም ሲያራምዱ ይታያሉ።    በቅዳሴ ሥርዓት ጊዜ አካልን የሚያራቁቱ፣ የተለያዩ ትኩረት የሚስቡ ዓላማዊ መልእክት የተጻፈባቸው ልብሶችን፣ ለስግደት ለአንቅስቃሴ የማይመቹ ወዘተ ልበሶችን መልበስ አግባብ አይሆንም።  ሴቶች ራሳቸውን ሸፍነው፣ እንደሴትነታቸው ለብሰው፣ ወንዶችም እንደወንድነታቸው ለብሰው በተቻለ መጠን  ሁላችንም ብርሃናዊ በሆነ አገልግሎት እየተሳተፍን መሆኑን በሚገልጽ መንገድ ነጭ ነጠላ /ለብስ/ መስቀልኛ አጣፍተን መሳተፍ አለብን።    ሴቶችም ወንዶችም በቅዳሴ ለመሳተፍ ሲመጡ ለሥርዓቱ በሚገባ ከማኅበረ ምእመናን አንድ ሆነን በምንታይበት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በምናሳይበት መንገድ መልበስ ያስፈልጋል።     

ለቅዳሴ መጥተው የራሳቸውን የጸሎት መጽሐፍ አንብበው የሚመለሱ ሰዎችም ያጋጥማሉ።    በቅዳሴው ጸሎት በንቃት እንዲሳተፉ በግል ከምንጸልየው ጸሎት በላይ በኅብረት በፍቅር የምንሳተፍበት የቅዳሴ ጸሎት እንደሚበልጥ ሲነገራቸው ‹‹ምን አለበት›› የሚሉ ወገኖችም አሉ።    እነዚህ ወገኖች የቅዳሴውን ጣዕምና መልእክት ካለመረዳት፣ በውስጡም ያለውን የምስጢርና አገልግሎት ታላቅነት ካለመረዳት ሊሆን ይችላል።    ይህ ጉዳይ ‹‹ለምን?›› ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ‹‹ምን አለበት!›› የሚለውን አስተሳሰብ መከተል ሥርዓተ አምልኮን አለመረዳትና መናቅ ነው።    

የቅዳሴ ጸሎት ከሁሉ ጸሎት የሚበልጥ የወንጌል መልእክት ያለው፣ ምክር፣ ተግሳጽና ትምህርት የያዘ ነው።    ከትንሽ እስከ ትልቅ ከአካባቢ እስከ ዓለም ላለው ሕዝብና ተፈጥሮ ሁሉ የምጸልይበት ነው።    የምንወደውን እግዚአብሔርን በታላቅ ትሕትና ስሙን እየጠራን የምናከብርብት፣ የምናመልክበት ጸሎትና ምስጋና ያለው ነው።    ከሁሉም በላይ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውና ደሙ የሚፈተትበት ንስሐ ለገቡ ምእመናን የሚሰጥበት ታላቅ ጸሎት ነው። ስለዚህ የራሳችን የግል ጸሎት በምናደርስበት ጊዜ በቤትም ይሁን በቤተ ክርስቲያን በሚገባው የግል የጸሎት ሥርት መደረግ ያለበት ነው።   

ሌላው ዘመን አመጣሹ ፈተና ደግሞ የሞባይል ስልኮች አጠቃቀም ነው።    በቅዳሴ ጊዜ ስልኮቻቸውን የማያጠፉ፣ ወይም ድምፀ አልባ የማያደርጉ ከዚያም አልፈው የፌስ ቡክና የቴሌግራም ገጾችን ከፍተው የሚጠቀሙ፣ መልእክት የሚለዋወጡ፣ ወዘተ ሰዎች አሉ።    እንዲህ ያሉት ወገኖች ሲመከሩ አንዳንዶቹ ‹‹ምን አለበት፤ ከዘመኑ ጋር መራመድ ነው›› ብለው የሚያስቡ አሉ።    

ይህ ግን በቅዳሴ ጊዜ ያለንን ተመስጦ የሚሰልብ፣ ‹‹እናስተውል›› ከሚለው የሥርዓተ ቅዳሴ ትእዛዝ ጋር የሚቃረን ነው። የቅዳሴ ጊዜ ለእግዚአብሔር ብለን ለይተን የሰጠነው ጊዜ ከሆነ በዚያን ጊዜ ከእርሱ የሚበልጥ የምናከብረውና የምናተኩርብት ነገር ሊኖር አይገባም።     

በአጠቃላይ ሲታይ አንዳንድ ምእመናን በአለማወቅ የሚፈጽሟቸው የሥርዓት ጥሰቶች አሉ። እንዲህ ያሉትን ምእመናን በልዩ ልዩ መንገድ ሥርዓትን እንዲያውቁ ማስተማር አግባብ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ በዚያው ሥርዓተ ቅዳሴ በሚፈጸምበት ዕለት ከሚሰጡ ትምህርቶች ጋር አጣምሮ መምከር አስፈላጊ ይሆናል።   እጅግ አስቸጋሪው ግን ነገሩን በአለማወቅ ብቻ ሳይሆን እንዲያውቁት ሲነገራቸው ‹‹ምን አለበት!›› ለሚሉ ወገኖች በተደጋጋሚ ምክርና ትምህርት መስጠት የሁሉም ምእመናንና አገልጋዮች ድርሻ ነው እንላለን።   

 

Read 623 times