Tuesday, 23 February 2021 00:00

ንሰሐ አባቴን የደበቅሁት ምሥጢር፦ ወደ ኋላ መመለስ ፈራሁ ክፍል አንድ

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ለረጅም ጊዜ በውስጤ ሲመላለስ የቆየ እና ሰላም የነሳኝን ጥያቄ ልጠይቅ ወደድኩ የኅሊና ዕረፍት የሚሰጥ መልስ ትሰጡኛላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።  ስሜ ወለተ ገብርኤል ይባላል ዕድሜዬ በአርባዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለ ትዳርና የሦስት ልጆች እናት ነኝ።  ትዳር ከመመሥረቴ በፊት ከተለያዩ ወንዶች ጋር ተራክቦ እፈጽም ነበር።  የአሁኑን የትዳር አጋሬን ሳገባ ይህንን አልነገርኩትም ነበር።  በጊዜው ከሱ በፊት ከነበረኝ የወንድ ጓደኛዬ ጋር በአጋጣሚ በተፈጠረ ክሥተት ስህተት ላይ መውደቄን ብቻ ነግሬው ነው ያለፍኩት። ለንስሐ አባቴም በወቅቱ ያለፈ ሕይወቴን እና የሠሁትን ኃጢአት በሙሉ ዘርዝሬ አልነገርኳቸውም።  ለአሁኑ ባለቤቴ የነገርኩትን ብቻ ነግሬ ሌሎቹን ‹‹ያለፈ ታሪክ ነው›› በሚል ምክንያት ሸፋፍኜ ነው ያለፍኩት።  በዕድሜ እየበሰልኩ ስመጣ እና ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ውስጤ ይደነግጣል፤ በኅሊናዬም ኃጢአተኛ እንደሆንኩ እያስታወሰኝ በየዕለቱ ይወቅሰኛል።  ከዚህም የተነሣ መልካም ለሆነው ባለቤቴ፣ ለልጆቼ፣ ለንስሐ አባቴ በተለይም ለእግዚአብሔር ታማኝ እንዳልሆንኩ ይሰማኛል።  ውድ የስምዐ ጽድቅ አዘጋጆች! ያለፈውን ኃጢአቴን እያሰብኩ በየዕለቱ ፀፀት ቢሰማኝም በጊዜው የደበቅሁትን ምሥጢር ግን አውጥቼ መናገር ፈራሁ።  ለመሆኑ ያለፈ በደሌን ዛሬ ላይ አለመናዘዜ ኃጢአት ይሆን? ፀፀቴን መሸከም ባለመቻሌ ለባለቤቴ እና ለንስሐ አባቴ መንገር እፈልግና ወደ ኋላ መመለስ ፈራሁ።  ምን ላድርግ ምንስ ትመክሩኛላችሁ እባካችሁ ዘርዘር አድርጋችሁ አስረዱኝ።  

 

እህታችን ወለተ ገብርኤል ‹‹የንስሐ አባቴን የደበቅሁት ምሥጢር ኅሊናዬን ዕረፍት ነሳኝ ወደ ኋላ ተመልሼ መናዘዝን ፈራሁ ምን ይሻለኛል?›› በማለት መፍትሔ ለማግኘት ጥያቄ ፣ማቅረብሽ መልካም ነው እንላለን። ምክንያቱም ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ፤ ለሚያደርጋት ሁሉ ምክር መልካም ናት” (መዝ.፻፲፣፲) በማለት እንደተናገረው ሰው በሥጋው ሲታመም ለመታከም ታክሞም ለመዳን የሚሄደው ወደ ጤና ተቋም እንደሆነ ሁሉ ነፍስም በኃጢአት ደዌ ስትያዝ (ስቴታም) መድኃኒቷ የእግዚአብሔር ቃል ፣ወደ እርሱም በንስሐ መቅረብና በውስጥሽ ረፍት ለነሳሽ የነፍስሽ ሕመም መፍትሔ አገኛለሁ ብለሽ ይህንን ጥያቄ ይዘሽ ወደ ዝግጅት ክፍላችን ቀርበሻል።  ስለሆነም እኛም እንደተለመደው የመምህራን አባቶችንና የቅዱሳት መጻሕፍትን ሐሳብ አብነት አድርገን ለችግርሽ መፍትሔ ይሆናሉ ያልናቸውን ምክረ ሐሳቦች ከዚህ በታች እንደሚከተለው አቅርበናልና በጥሞና እንድትከታተዪን በእግዚአብሔር ስም እናሳስብሻለን።   

ውድ እኅታችን ዕድሜሽ በዐርባዎቹ አጋማሽ ላይ እንደሆነ እና በትዳር ተወስነሽ የሦስት ልጆች እናት እንደሆንሽ ገልጸሽልናል።  ኅሊናሽን ዕረፍት የነሣሽ ጉዳይም ከአሁኑ የትዳር አጋርሽ ጋር ከመጣመርሽ በፊት ከተለያዩ ወንዶች ጋር ተራክቦ መፈጸምሽን ይህንን ጉዳይ ለነፍስ አባትሽም ሆነ ለትዳር አጋርሽ በግልጽ (በዝርዝር) እንዳላስረዳሻቸው ይህም አሁን ላይ ለነፍስ አባትሽ አለመናገርሽ እየረበሸሽ እንደሆነ ገልጸሽልናል።  

እኅታችን ወለተ ገብርኤል ላነሳሽው ጥያቄ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልስ ሊሆን የሚችለውን እንደሚከተለው እንመለከታለን።

ሰው አስቀድሞ ሲፈጠር ለባዊት፣ ነባቢት እና ሕያዊት ነፍስ ተሰጥቶት አዋቂ አእምሮ ታድሎት የተፈጠረ ታላቅና ድንቅ ፍጡር  ነው። ስለዚህ አስቀድሞ ማወቅ የሚገባቸው ነገሮች አሉ። እንደማንኛውም ላለፈውም ሆነ ይልቁንም አሁንም መረዳት የሚኖርብሽ ነገሮች የምንላቸውን እንደሚከተለው እንዘርዝራቸዋለን።

ሀ. የሰይጣንን ሴራ መረዳት፡- ሰይጣን በሰው ልጅ ከመቅናት መቼም አያርፍም። በመጽሐፈ ቀለሚንጦስ “ወሶበ ርእየ ሰይጣን ሀብተ ጸጋ ለአዳም እምኀበ እግዚአብሔር ቀንዓ ላዕሌሁ እይእቲ ሰዓት፤ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ለአዳም የተሰጠውን ጸጋ ባየ ጊዜ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ቀና” (ቀለ.፩፣፵፮) ተብሎ ተጽፎ እንደምናገኘው የሰውን ልጅ በሕይወት መኖር የማይወድ ጥንተ ጠላት ዛሬም ያለማቋረጥ ይከታተለዋል። በመሆኑም መጀመሪያ ኃጢአት እንዲሠራ መገፋፋት ከሠራው በኋላ ደግሞ ራሱን ለንስሓ እንዳያዘጋጅ በመከልከል ግን በሠራው ኃጢአት ከአቅም በላይ እንዲጨነቅ ማድረግ ነው። ስለዚህ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለማግኘት እንዲህ ያለውን የሰይጣንን ክፉ ሴራ በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል።

ለ.የንስሓን ምንነትና አስፈላጊነት በአግባቡ መረዳት፡- ንስሓ መጸጸት መመለስ ፊት በሠሩት መጥፎ ሥራ ማልቀስ ፊት የሠሩትን ሥራ ላለመሥራት መወሰን ማለት ነው።  ንስሐ የተሰበረ መንፈስ ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‹‹መሥዋዕቱ ለእግዚአብሔር መንፈስ የዋሕ ልበ ትሑተ ወየዋሐ ኢይሜንን እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሐር መስዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው የተሰበረውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።›› (መዝ. ፶፥፲፯) በማለት እንደገለጸው ሰው የተሰበረ ልብ ሲኖረውና የቀና መንፈስ ሲላበስ ያኔ ነው የንስሓ ሰው ሆነ የሚባል።  የንስሓ ጀማሪ የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነው አዳም ነው ።  አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በበላና ከክብር በተዋረደ ጊዜ እጅግ አብዝቶ አነባ እንባው አልቆ እዥ እስከሚወጣው ድረስ አለቀሰ።  ኃጢአትን መናዘዝ የተጀመረውም በብሉይ ኪዳን ይልቁንም በሕገ ልቡና ነው፡

ንስሓ  ከእግዚአብሔር የምንታረቅበት፡- አባቱ ‹‹ይህ ልጄ ሞቶ ነበር አሁን ግን ሕያው ሆኗልና ጠፍቶም ነበር ተገኝቷልና። ›› (ሉቃ. ፲፭፥፳፬) ፤ ከሞት የምንድንበት ሉቃ.፲፫፣፩-፭፣ ሁለተኛ የምንወለድበት ነው ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው ሦስት ልደታት ብሎ ከሚዘረዝራቸው መካከል አንዱ ንስሓ ነው። “ንሕነኒ እለ ተወለድነ በሥጋ ከማሆሙ ብነ ሠለስቱ ልደታት። አሐቲ ጥምቀት ቅደስት እንተ ትሬስየነ አምሳለ ክርስቶስ። ወአሐዱ ሥጋሁ ወደሙ ለክርስቶስ ዘይሠሪ አበሳ ወኃጢአተ። ወአሐዱ አንብዕ ዘበንስሓ ዘይወጽእ እምውስጥ በአምሳለ ዮርዳኖስ ዘያቀርብ ንጹሐ ቅድመ እግዚአብሔር፤ እኛም እንደነሱ በሥጋ የተወለድን ሦስት ልደታት አሉን። አንዲቱ የክርስቶስ ምሳሌ የምታደርገን ቅድስት ጥምቀት ናት። ሁለተኛው ኃጢአትንና አበሳን የሚደመስስ የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ ነው። ሦስተኛው በዮርዳኖስ አምሳል ከውስጣችን የሚወጣው በንስሓ የሚገኝ ዕንባ ነው፤ ይህም በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ አድርጎ የሚያቀርብ ነው” (ቅዳሴ አትናቴዎስ እንዲል። ንስሓ እንደ አባቶቻችን አስተምህሮ የበደለውን እንዳልበደለ፣ ዘማዊውን እንድ ድንግል፣ ኃጢአተኛውን እንደ ጻድቅ የምታድርግ ናት።

ሐ. ከንስሓ አባት ምንም ሊደበቅ የሚችል ነገር እንደሌለ መገንዘብ፦ የንስሓን አስፈላጊነት በተመለከተ ከላይ የተዘረዘሩትን ከላይ በሚገባ የተረዳ ሰው ንስሓ ለመግባት ወደኋላ አይልም። ከንስሓ አባቱ ፊት ቀርቦም ይህን ልናገር ይህን ደግሞ አልናገር ብሎ የሚመርጠውና የሚያስቀረው አንዳች ነገር ሊኖረው አይችልም። 

እግዚአብሔር መሐሪ ስለሆነ ዕድሜ ለንስሓ እየሰጠን እንጂ የንስሓ አባትን መዋሸት እግዚአብሔርን መዋሸት ስለሆነ ያስቀጣል። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው ተጽፎ የምናገኘው ሐናንያና ሰጲራ ቅዱስ ጴጥሮስን ባታለሉት ጊዜ ተቀጥተዋል። (ሐዋ. ፭፣፩-፲፩) ከካህኑ መደበቅ ከመንፈስ ቅዱስ መደበቅ ማለት ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም ሐናንያን ሲወቅሰው “ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅዱስን ታታልል ዘንድ የመሬቷንም ዋጋ ከፍለህ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ እንዴት አደረ?”  (ሐዋ. ፭፣፫) በማለት የተናገረው ካህኑን ማታለል መንፈስ ቅዱስን ማታለል ስለሆነ ነው። ስለዚህ ዛሬም ምን አልባት አረፈድሽ እንጂ እንዳልመሸብሽ ማወቅና ፈጥነሽ ወደ ንስሓ አባትሽ መሄድ ዋነኛ መፍትሔው መሆኑን ነው።

መ. በንስሓ ሕይወት የተጠቀሙ ሰዎችን ማሰብ፡- ንስሓ እግዚአብሔር አምላካችን የሰውን ልጅ በምን ያህል መጠን እንደሚወደው የገለጸበት ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር ንስሓቸውን ተቀብሎላቸው ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ የታደጋቸው በርካታ አባቶችን መዘርዝር ይቻላል። ይሁን እንጂ ለዚህ ጉዳይ ብቻ የተወሰኑትን እንጥቀስ።

፩. አዳም

ንስሓ በመግባታቸው ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁ ብዙ ቅዱሳንን ማንሣት ይቻላል።  ለምሳሌ ያህል ብንጠቅስ ከዘመነ አበው አባታችን አዳም ከእግዚአብሔር ተጣልቶ ከልጅነት ወጥቶ ከገነት ተባሮ የነበረው በድሎ ሳለ ተክሦለት ወደቀደመ ክብሩ ልጅነት ወደቀደመ ቦታው ወደ ገነት የተመለሰው በንስሓ ነው።  ‹‹ወኮነ አራቄ ለሐዲስ ኪዳን፤ ለሐዲስ ኪዳን አስታራቂ ሆነን። ›› በማለት ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እንደገለጸው አስታራቂው ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከራሱና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በደሙ ፈሳሽነት ያስታረቀን ሲሆን ለዚህ እንድንበቃ ምክንያት የሆነን  አዳም የገባው ንስሓ ነበር። 

፪. ነቢዩ ዳዊት

በዘመነ ነቢያት በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሱ ታላላቅ አባቶች መካከል ነቢዩ ዳዊትን መጥቀስ ይቻላል።  ዳዊት የጎልማሳ ሚስት ቀምቶ ጎልማሳ አስገድሎ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ነበር።  እግዚአብሔርም እጅግ ተቀይሞት ነበር።  በነቢዩ በናታን አማካኝነትም እንዲህ ሲል ወቀሰው።  “በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፤ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶህ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር።  አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልክ ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መተሃል፤ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል።” (፪ሳሙ. ፲፪፥፮-፲) እንዲል።

ከላይ ባነበብነው አንቀጽ ነቢዩ ዳዊት በእግዚአብሔር ዘንድ ተወቀሰ።  ዳዊትም ወቀሳው ሲመጣበት እንዲሁ ዛሬ ነገ እያለ ጊዜ አላባከነም። ምሕረት የባሕርዩ የሆነ አምላክ የውስጡን እንደሚያውቅና ምሕረትን እንደሚያደርግለት በማመን በፍጥነት ንስሐ ገባ።  የዳዊት ንስሓ በዕንባ የተሞላ እውነተኛ ጸጸት ያለበት እንደነበር አበው ያስረዳሉ። እርሱም በመዝሙሩ ‹‹ወአሐጽብ ኵሎ ሌሊተ አራትየ ወበአንብዕየ አርሐስኩ ምስካብየ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ›› (መዝ. ፮፥፮) በማለት ተናገረ። ምሕረት የባሕርዩ የሆነው እግዚአብሔርም ታረቀው።  ለእኛ የሚያስፈልገንን ሁሉ እኛ ሳንለምነው ያዘጋጅልናል። የተሰጠንን ጸጋ ባለመረዳትና በደካማ ባሕርያችን እንኳን ብንበድለው ስንመለስ ንስሓችንን ለመቀበል ቸር አባት ነው።

 

Read 773 times