Wednesday, 10 March 2021 00:00

አክባሪ ያጣው ሕግ

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በጸሎት በትጋት ይመሩ በነበረበት ዘመን በ፲፱፻፸፱ ዓ.ም አንድ የወጣ ሕግ ነበር። በጊዜው በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች መነኮሳት ከገዳም ወጥተው በከተሞች የመመላለስ በዚያም የመቆየት ልማድ እየተንሰራፋ በመምጣቱ ከዚህ በፊት የነበረውን የሲኖዶስ ውሳኔ እና የአባቶች ምክር መነሻ በማድረግ አንድ ሕግ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር።  መነኮሳት የፈቃድ ወረቀት ሳይዙ በከተማ ወይም ከገዳም ውጪ በሆነ ስፍራ እንዳይገኙ ተክከሏል። ከገዳም ከወጡ የፈቃድ ወረቀት መያዝ አለባቸው። ያለፈቃድ የሚገኙ በሕግ አካላትም እንዲጠየቁ መመሪያ ተላልፏል። ቀሳውስትም ከአንዱ ሀገረ ስብከት ወደ ሌላው ሄደው ሀገረ ስብከት ዝውውር ለማድረግ ቢፈልጉ ከነበሩበት ሊቀ ጳጳስ የፈቃድ ወረቀት ማጻፍ አለባቸው። ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስያን በ፲፱፻፵፮ ዓ.ም እና በ፲፱፻፶ ዓ.ም ባወጣችው በሁለተኛው ሲኖዶስ በ፲፩ኛው፣ በ፲፫ኛው፣ በ፲፬ኛው አንቀጽ እንዲሁም በሦስተኛው ሲኖዶስ በ፬ኛው ክፍል የተወሰነውን ውሳኔ መሠረት ያደረገ ነበር ተብሏል።  ይሁን እንጂ ይሄ ሕግና መመሪያ ከወጣበት ጊዜ አነሥቶ ላለፉት  ሦስት ዐሠርት ዓመታት በአግባቡ ሳይተገበር እንደውም ከጊዜ ጊዜ በባሰ ሁኔታ የመነኮሳት ፍልሰትና አግባብ ያልሆነ የከተሞች ቆይታ መስተዋሉን ቀጥሏል። ይህ ሁኔታ መልኩን እየቀየረም በገዳማት በሱባኤና በትጋት በሚቆይባቸው የጾም ወራትም ተከብሮ አለመገኘቱ ደግሞ የበለጠ ያሳስባል። መነኮሳት ወደ ከተማ እንዳይመጡ ፈጽሞ የተከለከለ ባይሆንም ለገዳሙ በመላላክ፣ ወይም የእነሱን ወደ ከተማ መምጣት የሚያስፈልግባቸው የጋራና የግል ጉዳዮች ሲኖሩ የፈቃድ ወረቀት ይዘው እንዲንቀሳቀሱ ይፈቀዳል። ይሁን እንጂ ምክንያቱ በማይታወቅ፣ ጥንቃቄ በጎደለው፣ ድፍረትም በተሞላባት፣ አሰናካይ በሆነ ሁኔታ በአዲስ አበባና በሀገራችን አንቱ በተባሉ ከተሞች በቁጥር በዛ ያሉ መነኮሳትን ማየት እየተለመደ ነው። እነዚህ መነኮሳት በከተሞች የሚያደርጓቸው መመላለሶች ብቻ ሳይሆን በሚፈጽሟቸው ተግባራትም ለምእመናን ሰላም በማይሰጡ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በማይመጥኑ፣ ለገዳማዊ ሥርዓቱ ክብር በነፈጉ ተግባራት ውስጥም ይታያሉ። መነኮሳት ከገዳማት ሲመጡ የሚያርፉባቸው ገዳማት ሊኖሯቸው ሲገባ በየመንደሩ፣ በየሆቴሎች የሚቆዩ መኖራቸው፣ በሆቴሎችና በአደባባዮች ሲመገቡ የሚወሰድባቸው ትዝብቶች፣ አብረዋቸው በሚውሉና በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ምክንያት የሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽእኖ  . . . ወዘተ በቤተ ክርስቲያኒቱ እየፈጠረ ያለው ማሰናካያ ግምቱ እየከበደ ነው።  በከተሞች ያለፈቃድ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ መነኮሳት ቆቡን አስተካክለው፣ መስቀላቸውን ይዘው፣ ቀሚሳቸውን አሳምረው፣ ፈረጅያቸውን ነስንሰው፣ ምንኩስናቸውን የበለጠ በሚገልጽ አለባባስ ስለሚታዩ መነኮሳት መሆናቸውን ማንም በግልጽ የሚረዳው ሆኖ ይታያሉ። ነገር ግን አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች በአውቶብሶች ላይ ባለው ግፊያ ውስጥ የሚደርስባቸው መንገላታት፣ ክብር ማጣት፣ ከዚያም አልፎ ለቁጣና ለክርክር የሚዳርግ ሁኔታ ለምእመናን ትልቅ ቁጭት የሚፈጥር ነው። በታክሲዎች ውስጥ በተሳፋሪ ክብር ማጣት፣ በረዳቶች ማመናጨቅና ከንቱ ክርክሮች ውስጥ መታየት ለሥርኣተ ምንኩስናው የሚሰጠውን ክብር ያቀለዋል።  ከዚያ አልፈው በየመጠጥ ቤቶች አካባቢ፣ በየሥጋ ቤቶች ደጃፍ ተቀምጠው አገልግሎት ለማግኘት ሲውተረተሩ መታየቱም ለቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ሰላም የሚሰጥ አይሆንም። በስመ መነኲሴ የሚነግዱ ፤መነኲሴ ሳይሆኑ በተከበረው ልብስ ውስጥ ተደብቀው ‹‹ ወደ ገዳም ልሄድ ነውና ብር አምጡ›› እያሉ የዋሁን ምእመን ኪስ የሚያራቁቱ ብዙዎችን በየመንገዱ ማየት የተለመደ ከመሆኑም ባሻገር የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የእውነተኞቹን መነኲሳት ክብር የሚነካ ነው።  በስንት ተጋድሎ የሚገኘውን የክብር ልብስ በቀላሉ ከመርካቶ በመግዛት ተጎናጽፈው በቤት የክብር ወንበር፤ በአደባባይ የክብር ስፍራ ለማግኘት የሚሯሯጡ ‹‹የቀበሮ ባህታውያን›› በከተማው እንደ አሸን ፈልተው ሲታይ ደህነኛውን ለመለየት እጅግ አስቸጋሪ የሆነበት ዘመን ነው። ዛሬ ዛሬ ምንኩስና የእነ አባ እንጦንስን ፈለግ በመከተል ይህን ዓለም ንቆ ለእግዚአብሔር ማደሪያ መሆኑ ቀርቶ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለመሄድ ፓስፖርት ማግኛ መንገድም እየሆነ ነው። ያለፈቃድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ መነኮሳት ሌላም ቀዳዳ እየከፈቱ ነው። መነኲሴ ሳይሆኑ መነኲሴ መስለው ለሚንቀሳቀሱ መናፍቃን በአርአያ ምንኩስናው የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ በማበላሸትና የተሳሳተ ትምህርት በመስጠት ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ ያልገቡትን ደግሞ በዚያው ሳይገቡ እንዲቀሩ በማድረግ ወጥመድ ለዘረጉ ክፉዎች በር ከፍተዋል።  የቤተ ክህነቱ አስተዳዳርም ከዚህ በፊት እንደዚህ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለማስተካከል ያወጣው ሕግ እንዳለ እያወቀ ከሚመለከታቸው የሕግ አካላት ጋር በመተባባርም ድርጊቱን ማስቆም አልቻለም። መነኮሳት ከገዳም የሚወጡበትንም ሁኔታ በትክክል ለማስተግበር የሚስችል ግልጽ አሠራር ከገዳማት ጋር በመተባባር አላዳበረም። ስለዚህ ተግባሩ የሁልጊዜም የቤተ ክርስቲያን ሐዘን ሆኖ ቀጥሏል። አጅግ አስገራሚው ነገር ደግሞ ምእመናን ካሉባቸው ብዙ ጭንቀቶች የተነሣ ዕረፍት ይሰጡናል ወደሚሏቸው ገዳማት በስፋት እየተመሙ፣ በጾም በሱባኤ ለመቆየት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ባሉበት በዚህ ዘመን የመነኮሳት ከገዳም ወጥቶ በከተሞች መሰንበት ነገሩን እንዴት በተቃራኒ እየተጓዘ እንደሆነ የሚያመላክት ነው። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳር ከዚህ በፊት ያወጣቻቸውን ሕጎች/መመሪያዎች አሁንም ለማንቃት ቢሞክር መልካም ይሆናል። ገዳማትም እየተጎዳ ያለው ሥርዐተ ምንኩስናው የገዳማዊ ሕይወት ክብር መሆኑንን በውል ተረድተው የውስጥ አስተዳዳር ሥርዐቱን ማርቀቅ ይገባቸዋል። ያሏቸውን ሴትና ወንድ መነኮሳት ቁጥር ማወቅ ማንነታቸውን መለየት ሕጋዊ መታወቂያ መስጠት፣ በገዳሙ ሥርዐት መሠረት የመነኮሳትን እንቅስቃሴ ምን መምሰል እንዳለበት ሥርዐታቸውን በየጊዜው ማጥበቅ ይገባቸዋል።  ምእመናንንም አጓጉል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ መነኮሳት መደበቂያ ዋሻ ከለላና ጠበቃ በመሆን የቤተ ክርስቲያንን ሥርዐታዊ አሠራር ከማወክ ሊቆጠቡ ይገባል። ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት በዚህ ረገድ ያለውን ጥፋት ከግምት ያስገባ እርምጃ መውሰድም ያስፈልጋቸዋል።  ይህ ካልሆነ ገዳማዊ ሥርዐት የማይወደድ የማይፈለግ፣ ከዓለማዊ አኗኗር ያልተለየ እንዲመስል ያደርገዋል። የዋህና ትሑት አባቶች በፈቃድ ሲንቀሳቀሱ የሚገባቸውን ክብርና ነጻነት እንዳያገኙ ወጥመድ ይፈጥራል። ለመናፍቃን እንቅስቃሴ አመቺ መንገድ ይከፈታል። የቤተ ክህነት አስተዳደር አቅምም ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ብሂል ማሰብ ይገባል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር  
Read 501 times