Wednesday, 10 March 2021 00:00

ንሰሐ አባቴን የደበቅሁት ምሥጢር፦ ወደ ኋላ መመለስ ፈራሁ ክፍል ሁለት

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። ፫. ቅዱስ ጴጥሮስ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በኃጢአቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ግን ንስሓ በመግባቱ ከታረቁት መካከል በዋናነት ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ተጠቃሽ ነው። ይህ ሐዋርያ ሌሎች እንኳ ቢክዱህ እኔ አልክድህም ሲል የነበረ ቢሆንም ከሌሎቹ ተለይቶ የካደ እርሱ ነበር። ሆኖም ግን በፍጥነት ወደራሱ ተመለሰ። የተነገረው ትንቢት ሳይውል ሳያድር እንደተፈጸመበት አወቀ። ፈጥኖ አለቀሰ፤ ንስሓ ገባ፤ እግዚአብሔርም ይቅር አለው። የጥሉ ግድግዳ በንስሓው አማካኝነት በእግዚአብሔር ቸርነት ተናደ። በዚህም ታማኝ አድርጎ የበጎቹ ጠባቂ አደረገው። (ዮሐ.፳፩፥፲፭-፲፰) ስለዚህ ምንም እንኳ ኃጢአተኛው የሠራው ክፉ ሥራና የሚገባው ንስሓ ማለትም በንስሓ የሚያደርገው ጸሎት፣ ልመና፣ ልቅሶ፣ ስግደት፣ ምጽዋት ወዘተ ለበደለው በደል በትክክል ካሳ ከመሆን አንጻር ባይመጣጠንም እግዚአብሔር ግን በባሕርዩ መሐሪ ነውና ንስሓውን ምክንያት አድርጎ ይቅር አለው ታረቀውም። ፬. ማርያም እንተ ዕፍረት  ማርያም እንተ ዕፍረት ዕድሜ ዘመኗን በኃጢአት ያሳለፈች ሴት ነበረች። ይሁን እንጂ በኃጢአት መኖር ከእግዚአብሔር መለየት አግባብ እንዳልሆነ በተረዳች ጊዜ ፈጥና ወደ ንስሓ ተመለሰች። በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናገኘውም እጅግ ዋጋው የከበረ ሽቶ አቀረበች ጌታችን መድኃኒታችንንም በእንባዋ አጠበችው። የንስሓ ዋጋ የሆነውንም “እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት ቦታ ይህች ሴት ያደረገችው ለእርሷ መታሰቢያ ሆኖ ይነገራል።” በማለት  የማይጠፋ ስም ሰጣት። (ማቴ.፳፮፥፮-፲፫)፤ (ማር.፲፬፥፫-፱)፤ (ዮሐ. ፲፪፥፩-፰) ከማርያም ዕንተ እፍረት የምንማራቸው በርካታ ቁም ነገሮች አሉን እነሱም ለበጎ ነገር መሽቀዳደምን ይልቁንም ለንስሓ ጊዜ መስጠት እንደሌለብን እንረዳለን። ትርጓሜ ወንጌል እንደሚነግረን ማርያም እንተ ዕፍረት ይህ ቀረሽ የማትባል መልከ መልካም ነበረች። ከዕለታት አንድ ቀን መላ ሰውነቷን በሚያሳይ በቁም መስተዋት ራሷን እየተመለከተች ግን ያን የሚመስል ውበት እንደሚያልፍ እንደሚረግፍ ተገነዘበች። ለዚህ መድኃኒቱ ደግሞ ንስሓ መግባት እንደ ሆነ ተረዳችና ዘመኗን ሙሉ በዝሙት የአጠራቀመችውን ገንዘብ በመያዝ ሥርየትን ለሚያድለው፣ ኃጢአትህ/ሽ ተሥርዮልሃል/ሻል ለሚለው ሊቀ ካህናት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ሽቱ ገዝታ ወደ እርሱ ሄደችና ማድረግ የሚገባትን አደረገች። ማርያም እንተ ዕፍረት ልቧ በተመለሰ ጊዜ ሳትውል ሳታድር ፈጥና ነው ንስሓን ወደ ሚቀበለው ሊቀ ካህናት የሄደችው። ይህ ብቻ አይደለም በመንገድ ላይም ሆነ ከደረሰች በኋላ በርካታ መሰናክሎች ገጥመዋታል። ከነዚህም መካከል ጥንት ዝሙት ያሠራት የነበረው ሰይጣን ቀድሞ በግብር ከሚያውቋት ወንድ ባንዱ ተመስሎ ከመንገድ ጠብቆ በርካታ የማሰናከያ ቃላትን እየጠቀሰ ሊያሰናክላት ሞክሯል። እሷ ግን አንድ ጊዜ ስለወሰነች እርሱ በሚያመጣው መሰናክል ሳትሸነፍ ለሚያነሣቸው ጥያቄዎች ሁሉ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድል ነሥተዋለች። ስለዚህ እኛም ወደ መልካም ነገር ስንሄድ በየመንገዱ እየጠበቀ ለዚያውም በምናውቀውና በምንወደው አካል እያደረ እንዳያሰናክለን ትጥቃችንን ልናጠብቅ ይገባናል።  ሌላው ከደቀ መዛሙርቱ የመጣው ፈተና ነበር። አዛኝ ለድሆች በጎ አሳቢ በመምሰል ይህ ተሸጦ ለድሆች በተሰጠ በተገባ ነበር በማለት ያደረገችውን ሥራ እንደጥፋት ቆጥረውት ነበር። ክርስቶስ ግን መልካም አደረገች ለምን ታሰናክሏታላችሁ በማለት ሥራዋን አደነቀላት። እንዲያውም ይህ የእሷ ሥራ በአራቱም ወንጌላውያን ሲነገር እንደሚኖር በመግለጽ አስረዳቸው። ዛሬም እኛ ለንስሓ መፋጠን እንጂ መዘግየት እንደሌለብን፣ እኛ ለንስሓ በተፋጠን ቍጥር እግዚአብሔር አምላካችን ንስሓችንን በቶሎ እንደሚቀበለንና የሚመጡ መሰናክሎችን ሁሉ የምናልፍበትን ኃይል እንደሚሰጠን ያስረዳናል። ምሕረትን ለሚያድለው፣ ኃጢአትህ/ሽ ተሠርዮልሃል/ሻል ለሚለው ሊቀ ካህናት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ሽቱ ገዝታ ወደ እሱ ሄደችና ማድረግ የሚገባትን አደረገች። ውድ እኅታችን ወለተ ገብርኤል ዛሬ ላይ ሁነሽ ይህን ጉዳይ መደበቅሽ የኅሊና ዕረፍት እንደነሣሽ የተደረገበት ምክንያት በዕድሜ የመብሰልሽ ጉዳይ ነው። ሰው በዕድሜ እየበሰለ በሄደ ቁጥር ትላንት ይጓዝበት የነበረው የጨለማ መንገድ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ይሠራቸው የነበሩ ስሕተቶች በጉልህ እየታዩት ራሱን እንዲወቅስ፣ መሳሳቱንም እንዲያይ፣ እግዚአብሔር ኅሊናን ያህል ዳኛ መስጠቱ በዚህ ይታወቃል። የኅሊና ዳኝነት ከባድ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ “በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ፤ ከሥራቸው የተነሣ ይታወቃል፤ ሕሊናቸው ይመሰክርባቸዋል፤ ይፈርድባቸዋልም” (ሮሜ ፪፣፲፭) በማለት እንደተናገረው ኅሊና በራሱ ስለሚጠይቅ ተፈጥሯዊ ጉዳይ መሆኑንም ልብ ማለት ያስፈልጋል።  አንቺም የኅሊና ዳኝነቱ ደርሶሽ መፍትሔ ፍለጋ ጥያቄሽን አቅርበሽልናል።  ወለተ ገብርኤል በቅድሚያ መረዳት የሚገባሽ ዝሙትን መፈጸም ከዐሥርቱ ትዕዛዛት አንዱን መሻር እንደሆነ መገንዘብ ይገባሻል። እግዚአብሔር አምላክ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕግን ሰጠው። በተሰጠው ሕግ ለወቅቱ እስራኤል ዘሥጋ (ያዕቆባውያን) ይተዳደሩበት ዘንድ ሲሆን ለፍጻሜው ደግሞ ለእስራኤል ዘነፍስ (ለክርስቲያኖች) የተሰጠ ሕግ ነው። ከዐሥርቱ ሕግጋት አንዱም ‹‹አታመንዝር›› የሚል ነው (ዘፀ. ፳፥፲፬።) አንቺ ግን በወጣትነትሽ ወቅት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን ሕግ ተላልፈሽ ከተለያዩ ወንዶች ጋር ተራክቦ መፈጸምሽን ነግረሽናል።  ወለተ ገብርኤል ዝሙት ታላቅ ኃጢአት መሆኑን በሰብአ ትካት በኖኅ ዘመን ሰዎች ላይ ያስከተለውን መዓት ምን እንደሆነ ታላቁ መጽሐፍ ይመሰክራል።  በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከዝሙት ይርቁ ዘንድ ‹‹ሥጋ ግን ለእግዚአብሔር ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም ጌታም ለሥጋ ነው። ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደሆኑ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር እንደሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሏልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙት ሽሹ። ሰው  የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋል ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።›› በማለት አስተምሯቸዋል። ፩ቆሮ.፮፥፳—፳፫።  ክርስቲያን በዋጋ የተገዛ መሆኑን ሲዘነጋ ለኃጢአት ይዳረጋል። ክርስቲያኖችን ጌታችን በወርቅ ደሙ እንደዋጀን ሐዋርያው ሲገልጽ “በዋጋ ተገዝታችኋል” አለ። ከዚህም በተጓዳኝ ዝሙትን ስንፈጽም በእኛ ያደረውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ማሳዘን ስለሆነ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በሥጋው እግዚአብርን ማክበር ደግሞ ካልቻለና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በኃጢአት ከወደቀም ፈጥኖ ንስሓ መግባት ይጠበቅበታል።  ወለተ ገብርኤል እንደሚታወቀው ኃጢአት የሥጋም የነፍስም በሽታ ነው። ለዚህ በሽታ ደግሞ እግዚአብሔር የሰጠን መድኃኒት ንስሓ ነው። የንስሓ ሁሉ መጀመሪያ ደግሞ የኅሊና ወቀሳ ነው። ይህም ማለት ኃጢአተኝነትን ማመንና ኃጢአትን ማውገዝና መጥላት ነው። ይህም ተነሳሒው በኅሊናው በአንቺ እንደሆነው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር መናዘዝ ነው። ‹‹ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ በደሌንም አልሸፈንሁም ለእግዚአብሔር መተላለፌን እናገራለሁ›› (መዝ. ፴፩፥፭ ) እንዲል።  ይህ ዓይነቱ የኅሊና ጸፀት ብቻ በራሱ በቂ አለመሆኑን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በለምጽ በሽታ የተያዘውን ሰው ከለምጹ ከፈወሰው በኋላ ‹‹ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ›› (ማቴ.፰፥፬) ብሎታል።  አንድ ኃጢአተኛ ራሱን ለካህን ማሳየት ለምን ያስፈልጋል? የሚል ሰው ካለም መልሱ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ስለሆነ ነው። ‹‹ካህኑ ሁሉን የሚችል የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና  ከንፈሮቹ ዕውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፤ ሕጉንም በልቡ ይመረምር ዘንድ ሚል.፪፥፯ ተብሏልና ነው።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዲስ ኪዳን ለወቅቱ ለቅዱሳን ሐዋርያት ለፍጻሜው በእርሱ እግር ተተክተው ለሚያገለግሉ ሥልጣነ ክህነት ላላቸው ካህናት የሰጠው ሥልጣን እንዲህ የሚል ነው። ‹‹እውነት እላችኋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።›› (ማቴ.፲፰፥፲፰) ይህ ሥልጣን በዘመናት፣ ኃያላን የማይሽሩት አምላካዊ ጸጋ ነው። እኅታችን ወለተ ገብርኤል እስቲ አንቺ አንድ ጥያቄ መልሽልን እንጠይቅሽ። አያድርገው እንጂ አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር በሥጋሽ ታመሽ ትላንት የጤና ባለሙያ ጋር ሄደሽ ሕመምሽን ተናግረሽ መድኃኒት ታዝዞልሽ ነገር ግን የታዘዘልሽን መድኃኒት በአግባቡ ባለመውሰድሽ ሕመሙ ቢጸናብሽ ተመልሰሽ ጤና ባለሙያው ዘንድ መሄድሽ ይቀራል? አይቀርም። ምክንያቱም ፈውስ ስለምትፈልጊ ተመልሰሽ ሄደሽ ተናግረሽ የሚታዘዝልሽን መድኃኒት ወስደሽ እንደምትጠቀሚበት ሁሉ ያለ ምንም ዕፍረትና ይሉኝታ የነፍስ አባቴ ዳግመኛ ስነግራቸው ምን ይሉኛል ሳትይና ሳትሳቀቂ ጉዳዩን በዝርዝር አስረድተሻቸው ያንጊዜ ያልተናገርኩት ዕፍረት ይዞኝ ነው። አሁን ግን ኅሊናዬን ኃጢአቱ እረፍት ስለነሳኝ ነው ብለሽ ተናዘሽ የሚሰጥሽን ቀኖና በተግባር ፈጽሚው።  ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ ‹‹እንድትጸድቅ መጀመሪያ ኃጢአትህን ተናገር›› ኢሳ.፵፫፥፳፮ ብሏልና። ከተለያዩ ወንዶች ጋር በዝሙት ኃጢአት መውደቅሽን መግለጽ ያለብሽ ለነፍስ አባትሽ ብቻ እንጂ ለትዳር አጋርሽ ለልጆችሽ አባት አለመሆኑንም ማወቅ ይገባሻል። ምክንያቱም አንደኛ የቀደመ በደልሽን የሚያስተሠርይልሽ ኃጢአትሽን ለካህኑ መንገርሽ እንጂ ለባለቤትሽ መንገረሽ አይደለም ባለቤትሽ ወደ ኋላ ተመልሰሽ የተደረገውን ድርጊት ስትነግሪው ጎልማሳ በሚስቱ ቀናዒ ነው ስለሚባል ሊከፋውና ሊጠላሽ ይችል ይሆናልና። ስለዚህም አሁን ማድረግ የሚገባሽ ከላይ እንደገለጽንልሸ የተደረገውን ድርጊት ኅሊናሸን ዕረፍት የነሳሽን ጉዳይ ለነፍስ አባትሽ ነግረሽ ንስሐ ግቢበት አይከብድም። በተጓዳኝ ደግሞ በመጽሐፍ ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይልን ታደርጋለች›› (ያዕ.፭፥፲፮) ተብሏልና መብዓ ማለትም (ዕጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብ) ወደ ገዳማት ከስመ ክርስትናሽ ጋር በመላክ  በጸሎት እንዲያስቡሽ አስደርጊ።  በተቀረው በዘመንሽ ሁሉ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በፈጸምሽው ኃጢአት እየተጸጸትሽ መኖር አንዱ የክርስትና ሕይወት መሆኑን ብታውቂም እግዚአብሔር ደግሞ መሐሪ መሆኑን ሳትዘነጊው አምነሽ ኅሊናሽን በፀፀት ከመጉዳት ተጠበቂ። ቸሩ አምላክ በደልሽን ሁሉ ይቅር ብሎሽ ትዳርሽን ባርኮ እንዲቀድስሽ የእርሱ መልካም ፈቃድ ይሁን አሜን።      
Read 685 times