አንዳንድ ልጆች ግን በየመንገዱ ታላላቆቻቸው፣ አዛውንቶችንና የታመሙትን ሰዎች በማንጓጠጥ እንዲሁም በማሾፍ የሚሳደቡ አሉ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ኤልሳዕ የሚባል ደግ ነቢይ ነበር፡፡ የታመሙትን ይፈውሳል፤ የሞተ ሰው ያስነሣል፤ በጣም የተከበረ ሰውም ነበር፡፡ ነገር ግን ሕፃናት ገጹንና አካሉን ሲያዩት ተራ ሰው አድርገው ናቁትና ‹አንተ ራሰ በራ (መላጣ) ውጣ! አንተ ራሰ በራ (መላጣ) ውጣ!› ብለው አፌዙበት፡፡ ልጆቹ ማፌዛቸውን እንደጨዋታ ቆጥረው የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሻሩ፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕም ዘወርም ብሎ አያቸው፤ በእግዚአብሔር ስምም ረገማቸው፤ ከዱር (ከጫካ) ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖቹ መካከል አርባ ሁለቱን ለሕፃናት ሰባበሩው በሏቸው፡፡ ስለዚህ ልጆች ከኤልሳው ታሪክ እንደምንማረው እግዚአብሔር አምላክ የሚታዘዙትን ቅዱሳን ስለሚወድ እንዲከበሩ እንጂ እንዲናቁ ወይንም እንዲሾፍባቸው አይፈልግም፡፡ (፪ ነገሥት ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፳፫)
ልጆች! ጠቢቡ ሰሎሞን ምን ብሏል መሰላችሁ፤ ‹አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ በድቅድቅ ጨለማ ማለትም ሲኦል የሚባል ቦታ ውስጥ ለዘለዓለም ሲቀጣ ይኖራል፤› ይህንን ሁል ጊዜ አስታውሰን አባትና እናታችንን ማክበር አለብን፡፡ ጨለማ እንዳይውጠን መብራት እናበራለን፤ በምሽት በመንገድም ስንሄድ መብራት ከሌለ ጉድጓድ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ መቼም ያለ መብራት መንቀሳቀስ አይቻልም፤ በቀንም ቢሆን ፀሐይ ብርሃን ባይሆነን መንቀሳቀስ ይከብዳልና፡፡ (መጽሐፈ ምሳሌ ፳ ቁጥር ፳)
የሃይማኖት አባቶች ቤታችን መጥተው ጠበል የሚረጩን እና መስቀል የሚያሳልሙን አባቶች በመሆናቸው እነርሱንም ማክበር አለብን፡፡ እንዲሁም በትምህርት ቤት የቀለም ትምህርት በጥሩ ሁኔታ የሚያስተምሩንን፣ ስናጠፋ የሚያርሙን፣ ትልቅ ደረጃ እንድንደርስ በመምከር እና ሳንታዘዝ ስንቀር ቀጥተው የሚያስተካክሉን አባቶች አሉን፤ እነርሱንም ልክ እንደ ወላጆቻችን ማክበርና መታዘዝ አለብን፡፡
ልጆች! በአካባቢያችን የተቸገሩ ወይንም በዕድሜያቸው ያረጁ ሰዎችም እናትና አባቶቻችን ናቸው፡፡ ሱቅ ዕቃ ለመግዛት የሚላካቸው እያጡ የሚቸገሩ ከሆነ ሮጥ ብለን ገዝተን ብናመጣላቸው ይመርቁናል፡፡ እግዚአብሔርም ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡ ዓይናቸው የደከመ ሰዎች ማየት ቢከብዳቸው እኛ እጆቻቸውን ይዘን ወደ ቤታቸው ብንወስዳቸው እንዲሁም የተራቡትን ምግብ ብንሰጣቸው እንመረቃለን፡፡
ሌላው ደግሞ ልጆች! አንዳንዴ ከወላጆቻቸው ጋር ሲሄዱ በጣም ደካማ አረጋውያን ሲለምኑ ሲያዩ ‹አባቴ እናቴ! ሳንቲም እርዷቸው ወይንም ሳንቲም እንስጣቸው› በማለት በጎ ነገር እንዲያደርጉላቸው ይለምኗቸዋል፡፡ እነርሱን ለመርዳት ገንዘብ ባይኖራችሁ እንኳን ወላጆቻችሁ እንዲረዱ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ማለት ነው፤ እግዚአብሔር የሚወደን ገንዘብ ስላለን ሳይሆን ለሰዎች ስናዝን እና ስንረዳ ነው፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ሥራ ነው፤ ልጆች ለዛሬ በዚህ ይቆየን፤ ደኅና ሰንብቱ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር