Monday, 10 August 2020 00:00

ትንኝን የምታጠሩ ፥ ግልገልንም የምትውጡ፣ ማቴ . ፳፫፥፳፬

Written by  ረቂቅ መቻል

Overview

  የተከበራችሁ አንባብያን መቼም በዕለት ዕለት እንቅስቃሴያችን ልብ ብለን ካስተዋልን የሚደንቁ እና የሚያስገርሙ የሚያስደስቱና የሚያዝናኑ የሚያበሳጩ ነገሮችን  በአግራሞት ተመልክተን ወይም ሰምተን ማለፋችን አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንዴም አስተማሪ የሆኑ ትርኢቶችን ልናይ እንችላለን፡፡ እኔም በአንዲት ዕለት ካስተዋልኳቸው ትዝብቶቼ መካከል ለእናንተ ለማካፈል ወደድሁ፡፡  ወሩ ሰኔ ዕለቱ ዐርብ ቀኑ ዐሥራ ሁለት  ሰዓቱ  ደግሞ በግምት ከዐሥራ ሁለት  ተኩል እስከ አንድ  ሰዓት ባለው  አካባቢ ይሆናል፡፡ ቦታው ስድስት ኪሎ ቅዱስ  ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን  ነው፡፡ በዚህ ዕለት ዐይኖቼ ያዩትን በጆሮዬ የሰማሁትን እና በልቤ ያወጣሁ ያወረድሁትን እንዲሁም የተሰማኝን በትዝብት ቅኝቴ ውስጥ ላሳያችሁ ስወድ ከመንፈሳዊ ቅንዓት ተነሥቼ ነው ፡፡ ለትዝብት ቅኝቴ አትኩሮት እንድሰጥ ምክንያት የሆነኝ በክርስቲያን ወገኖቼ ዘንድ የዕለቱ  በዓል ታላቅነት ሰፊ ስፍራ የሚሰጠው በመሆኑ ተከብሮ የሚውለውን የበዓሉን ምንነት በጥቂቱ ለማስታወስ ያህል እግረ መንገዴን ታሪኩን እያወሳሁ የትዝብት ቅኝቴን ልገልጽላችሁ እወድዳለሁ፡፡ወቅቱ ዓለምን እያስጨነቀ ያለው ኮቪድ ፲፱ ወረርሽኝን አስመልክቶ በሚወጡ የመንግሥት አዋጆች እና  አተገባበራቸውን ስታዘብ በአብያተ ክርስቲያኖች ላይ አብዝቶ  የሚደርሰው አሉታዊ ጫናና ግፍ ከዕለት ዕለት የሚያሳዝንና የሚያበሳጭ ሆኖ ስላየሁት ነው፡፡  በዚህ ቀን ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ ማልዶ በመነሣት ወደ ቅዱስ ሚካኤል  ወዳለበት ቤተ ክርስቲያን   ይተማል፡፡ ከባድ የሚባል ችግር ካልገጠመው በቀር ሁሉም በሚባል ደረጃ ደጁን ሳይረግጥ ቤተ ክርስቲያንን ሰላም ለኪ ብሎ በሮቿን ስሞ ቅዱስ ሚካኤልን አማልደኝ ርዳኝ ረድኤትህ በረከትህ ይደርብኝ ሳይል የሚውልና ወደ ተሰማራበት የዕለት ሥራ የማይሄድ  ክርስቲያን የለም ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ዐይኖቼ ለሕዝብ ደኅንነት የተመደቡትን የፖሊስ አካላት ብቻ ሳይሆን በበጎ ምግባር ተሰማርተው ቤተክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያኑን በቅንነትና በማስተዋል  ሲያገለግሉ የነበሩትን ወጣቶች በማየት ማድነቅ ጀመርኩ፡፡

 

ወጣቶቹ እጅ በማስታጠብ ፣ አልኮልና ሳኒታይዘር በማቀበል ምእመናን ርቀታቸውን ጠብቀው  የዕለቱ የበረከት ተካፋይ እንዲሆኑ ከወዲያ ወዲህ ሲራወጡ ያየኋቸውን የቤተክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች ሳላመሰግን እንዳላልፍ ተገደድኩ፡፡ 

ከእነርሱ በተለየ መልኩ ደግሞ እንጀራ ሆኖባቸው ይሁን ሌላ ተልእኮ ለማስፈጸም ግልጽ ባይሆንልኝም ምእመኑ ባለበት ቆሞ እንኳን መሳለምና ጸሎት ማድረስ ፈልጎ እያለ በዱላ የሚያራውጡትን አይቼ ምናለ ለዛሬ  ብዬ ልማጸን ወደድኩ ግን ሰሚ የለም፡፡ የሰው ልጆች በትሕትና ራሳቸውን ዝቅ ማድረግ እንደሚገባቸው እና እርስ በእርሳችን መከባበርን ገንዘብ ልናደርጋት የሚያስፈልግ ሲሆን በዚያ በከበረ ዕለት ግን በአንዳንድ የጸጥታ አስከባሪዎች የተመለከትኩት እና የታዘብኩት በዓሉን ለማክበር የመጡ በዕድሜ የገፉ አረጋውያን አባቶችን እና እናቶችን ሳይቀር እየገፈተሩ ለጆሮ የማይመጥን ቃል እየተናገሩ ከፍ ዝቅ አድርጎ በማመናጨቅ ከኢትዮጵያዊነት ባሕል ወግና ልማድ ውጪ በሆነ መንገድ ቀልባቸውን እየገፈፉ ሲያዳፉዋቸው ማየቱ ልብ ይነካል፡፡ 

በሁሉም ዘንድ የሚታወቀውና የማይካደው የወቅቱ ችግር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት መሆኑ እሙን ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ያን በዓል ምክንያት አድርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለጸሎት የሚመጣው አማኝ ለቫይረሱ እንዳይጋለጥ ራሱን እንዲጠብቅ መከባበር ባለበት መንገድ ማስተማርና ግንዛቤ እንዲወስዱ በሰለጠነ መንገድ ማድረግ ሲቻል በበሽታው እያመካኙ ለይምሰል ብቻ ነጠላ የለበሰን ክርስቲያን  አድኖ ማንገላታቱ ዓላማው ምንድን ነው ብሎ ለመጠየቅ የሚያስችል ድርጊት መሆኑ የትዝብቴ ዋና አትኩሮት ነው፡፡     

ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዱ ለራሱና ስለ ሀገር ደኅንነት ለመጸለይ እንጂ ለሌላ ጉዳይ እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ቢሆንም በአንዳንዶች ዘንድ ግን ይህ ያልተዋጠላቸው አካላት ወንጀል እንደ ፈጸመ አስመስለው በአጋጣሚው ተጠቅመው የግል ተልእኮአቸውን ለማስፈጸም መሞከሩ ያስተዛዝባል፡፡ 

እኔም በዚህች በከበረች እና ለምስጋና በተመረጠች ዕለት እንደ እናት አባቶቼ እንደ እኅት ወንድሞቼ ከበረከቱ ለመሳተፍ ምንም እንኳን ሌሊቱን እንደ አባቶቼ ካህናት በማኅሌቱ ለመሳተፍ ዕድሉን ባላገኝም ኪዳኑን አስደርሼ የጾም ወራት ስለሆነና ቀኑም ዐርብ በመሆኑ ቀሪ የአምልኮ ሥርዓቶችን ተሳትፌ የመልአኩን ረድኤት ለማግኘት ከቤቴ ወጥቻለሁ፡፡ 

በዚያውም የቃል ኪዳኑ ታቦት ከመንበረ ክብሩ ተነሥቶ በዝማሬና በውዳሴ በዕልልታም ታጅቦ ሲወጣ ተባርኬ ቅዳሴውንም አስቀድሼ በአጠቃላይ በዕለቱ የሚከናወኑትን ምሥጢራት ሁሉ ተሳትፌ በረከቱን ለማግኘት ነጠላዬን መስቀልኛ አጣፍቼ የጸሎት መጽሐፌን ይዤ አንበሳ ግቢ ከሚባለው መስመር የሰማዕታት መታሰቢያ አደባባዩን ልሻገርና በያሬድ ዜማ ወረቡ ወደሚንቆረቆርባት በዓሉን ለማክበር ቅጥሮቿን በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ተውባ ከሩቅ ወደምትጣራው በበዓሉም የአምልኮ የምስጋና ሥርዓት አሸብርቃ ወደምትታየው ቤተ ክርስቲያን ለመግባት ጉዞዬ ሲቃረብ የጸጥታ አስከባሪዎችን በብዛት ሆነው  አየሁ፡፡ 

አደባባይ እንደ መሆኑ ወደ አራቱም ማዕዘን የሚተላለፈውን ሰው በትኩረት ስመለከት ዘርዘር ብለው ቆመዋል፡፡ ነጠላቸውን መስቀልኛ የለበሱ ኦርቶዶክሳውያን የአደባባዩን መሻገሪያዎች ሞልተዋቸዋል፡፡ ምክንያቱም አደባባዩን ተሻግረው እንዳያልፉና ቀረብ ብለው እንዳይሳለሙ በመደረጋቸው ነው፡፡ 

ራቅ ብለው በብዛት በአንድ አካባቢ ሰብሰብ ብለው ቆመዋል፡፡ ምክንያቱም  ወደ ቤተ ክርስቲያን በሮች መግባት ቀርቶ ቀረብ ብሎም አማትቦ መሳለም እንዳይችል ተከልክሏል፡፡  እኔም እስኪ ካስገቡኝ ልሞክር ብዬ ወደ ተለያየ ጉዳያቸው ለመድረስ ከሚተላለፉት ሰዎች ጋር አደባባዩን ለመሻገር ስሞክር በእኔ በኩል የነበረው  የጸጥታ አስከባሪ ነጠላ መልበሴን እንዳየ አስቆመኝና “ወዴት ነው”? አለኝ እኔም በትሕትና እባክህ ርቀቴን ጠብቄ ወደ ቤተ ክርስቲያን ልግባ ስእለቴንም ላስገባ አልኩት፡፡ ይሁን እንጂ በሥርዓት የምለውን እንኳ መስማት አልፈለገም፡፡ ከሁኔታው እንደ ተረዳሁት ስእለት ምን እንደ ሆነም የሚያውቅ እንዳልሆነ ያስታውቃል፡፡ በቁጣ ሆኖ ተመለሽ ከዚህ ማለፍ አይቻልም አለኝ፡፡ 

 

እኔም ዘወር ዘወር በዬ ዙሪዬን ስመለከት እንደኔ እንዳያልፉ የተከለከሉ ክርስቲያኖች ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለተባለው ለወረርሽኙ በሚያጋልጥ ሁኔታ ተፋፍኖ የተሰበሰበው ሰው ብዛቱ ያስደነግጣል፡፡ የጸጥታ አስከባሪዎችም ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ መከልከላቸውን እንጂ ተከልክለው በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በአንድ ላይ መቆማቸውና የነበረውን ትርምስ እያዩ ከምንም አልቆጠሩትም፡፡ 

ያን በውስጤ እየታዘብኩ በዐይነ ኅሊናዬ ሌሎችን ቦታች ሰዎች በብዛት የሚሰበሰቡባቸውን ስፍራዎች መቃኘት ጀመርኩ፡፡ የገበያ ስፍራዎች፣ መጠጥ ቤቶች፣ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት መሸጫ ስፍራዎች በተለመደው እንቅስቃሴ መሆናቸው በተለይም ጃን ሜዳ በቅርቡ የተቀየረው አትክልት ተራ፣ መነኻሪያዎች ወዘተ በነበረው አይነት እንቅስቃሴ መሆናቸው ግድ ሳይሰጣቸው እንዲሁም በነዚህ ስፍራዎች ለምልክት እንኳ የፖሊስ አባላት  የማይታዩ ሆኖ ሳለ የፊት መሸፈኛ አድርጎ፣ አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እጅ የሚታጠቡበትን እና አልኮሎችን በር ላይ አዘጋጅተው በማኖር ከወረርሽኙ ለመጠበቅ እነዚህ ሁሉ በተሟሉባትና ጥንቃቄ በሚደረግባት ቤተ ክርስቲያን ምንም አይነት ሰው ዝር እንዳይል  የሚል በሚመስል  መልኩያለ የሌለ ኃይል በመጠቀም ክልከላ  ማድረግ  ምን ታስቦ ነው ያስብላል፡፡ 

ወደ ተለያዩ ቦታዎችና ሕዝብ ወደሚበዛባቸው ስፍራዎች ለመሄድ ምንም አይነት ጥያቄ የለም፡፡ ለዓለም ጸሎት ወደሚደርስባት ቤተ ክርስቲያን የምትሄድ መስሎ ከታያቸው ግን ወዴት ነው የሚል ጥያቄ ይቀርብልሃል፡፡ አንዳንድ አጥቢያዎች ላይ የሚቆሙ የፖሊስ አባላትማ  በቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ ቆመህ አማትበህ እንዳትሳለም እንኳ ይከለክሉሃል፡፡ የእኔ ትዝብት ያስተዋለው በወረርሽኙ እያመካኙ የቤተ ክርስቲያንን መዘጋት እንደ ስኬት የሚቆጥሩ አካላት መኖራቸውን ነው፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ማስተዋልና ሕግን በአግባቡ የማስከበር ልምድን ሊተገብሩና ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱን ሕግ አክብራ ሥርዓተ አምልኮዋን እንዳትፈጽም መከልከል አግባብነት የለውም፡፡ ስለሆነም ሰላምን አስከብራለሁ የሚለው የፀጥታ ኀይል የሃይማኖት ነጻነትን ማክበር ቢችል መልካም ነው፡፡ 

እግዚአብሔር ልብ እንዲሰጣቸው እየለመንን እኛም  ከተኛንበት መንቃት እና ቤተ ክርስቲናችንን መጠበቅ ልባችን ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር እንዳይርቅ መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር የተሻለ ዘመን ያምጣልን የቤተ ክርስቲያንን ጠላቶች ያስታግሥልን፡፡ 

አሜን

 

Read 734 times