- Details
- Written by: በዝግጅት ክፍሉ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1214
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ የሰላም እጦት እንደ ውኃ ጥም እያንገበገባት ትገኛለች። ምክንያቱን በተመለከተ እንኳንስ ችግሩ በቀጥታ የደረሰበት አካል ችግሩን ያደረሰውም ቢሆን ጉዳዩን ወደ ሌላ አካል መግፋት እንጂ የራሱ ችግር እንደሆነ አምኖ አይቀበልም። ይባስ ብሎም ቀድሞ በመጮኽ የተበደለና የተገፋ አድርጎ ለዓለም ያውጃል። ዓለም ደግሞ ቀድሞ የሚሰማውና ባይችልም መፍትሔ አመጣለሁ ብሎ የሚሞክረው ቀድሞ ለጮኸለት አካል ነው። ይህ ደግሞ እንደምንመለከተው ችግሩን የሚያባብስ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ አይደለም።
በዋናነት ግን ሀገራችን እየተከተለችው ያለው የፖለቲካ ርእዮትና፣ ዓለማቀፋዊው የተሳሳተ ትርክት ሲሆን ከዚህም ባሻገር ሀገር በቀሎቹ እኩያን ወይም ጡት ነካሾች በሀገራችን ለሠላሳና ለአርባ ዓመታት የጥላቻ ንግግርና የሐሰት ትርክት፣ እንክርዳድን በትውልድ አእምሮ ላይ ሲዘሩ ኖረዋል። እኩያኑ የዘሩትን ራሳቸው ቢያጭዱት መልካም ነበር። የሚያሳዝነው እኩያኑ የዘሩትን ንጹሐኑ ያንኑ ማጨዳቸው ነው። ይህ ደግሞ አንዱ ሌላውን በጠላትነት እንዲመለከተው እያደረገ ወደ እርስ በእርስ ግድያና እልቂት አስገብቶናል። ለችግሩም መሠረታዊና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማምጣት ከማንችልበት ሁኔታ ላይ እንድንገኝ አድርጎናል።
- Details
- Written by: ዲ/ን ደረጄ ድንቄ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 7001
መከራ ምንድን ነው?
መከራ ማለት ፈተና፣ ጭንቅ ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ተርጕመውት እናገኛለን። (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፭፻፺፩) እንዲሁም ሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን ትንሣኤ አማርኛ-ግእዝ መዝገበ ቃላት በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ፈተና፣ ሀውክ፣ ሥቃይ የሚል አቻ ትርጉም ሰጥተውት እናገኛለን። (ትንሣኤ አማርኛ-ግእዝ መዝገበ ቃላት ገጽ ፳) ክርስቲያን ማለት ከውኃ እና ከመንፈስ በመጠመቅ ክርስቶስን የለበሰ ፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆነ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።›› (ገላ. ፫፥፳፯) እንዲል። ክርስቶስ ይህን ዓለም የወደደው ወይም ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር የገለጠው ደግሞ ራሱን ለመከራ አሳልፎ በመስጠትና በሥቃይ ውስጥ ነው። ጌታም ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፤ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› (ማቴ. ፲፮፥፳፬) ሲል በሰጠው ትእዛዝ ውስጥ ክርስቲያኖች በጥምቀት ለለበሱት አምላክ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጡበት መንገድም መከራ እንደሆነ ልብ ይሏል! በአጠቃላይ የክርስትና ሕይወት ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ደስታ የሚገኝበት ምድራዊ መከራ በዚህ ዓለም ሳለ የማይለየው ሕይወት ነው።
- Details
- Written by: በመ/ሐ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 4441
የሰው ልጅ የመጀመሪያ ተስፋ የወልደ እግዚአብሔር አካላዊ ቃል ቀዳማዊ ምጽአቱ ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም ልኡካነ ቃል ነቢያትን አስነሥቶ በሥጋ እንደሚመጣ አናገረ፤ ነቢያት የወልደ እግዚአብሔርን መምጣት በብዙ ኅብረ ትንቢት እና ኅብረ ምሳሌ አስተማሩ፤ ስለቀዳማዊ ምጽአቱ ትንቢት ተናገሩ፤ ሱባኤ ቆጠሩ፤ የሰው ልጅ ልቡና የፈጣሪውን መምጣት በተስፋ ሰነቀ። በምጽአቱ የሚያገኘውን ድኅነት በተስፋ ጠበቀ። የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር አምላክ ዘመኑ ሲደርስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በብሥራተ መልአክ ተወለደ፤ ይህ የመጀመሪያ ምጽአት ይባላል። ‹‹ዘመኑ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ›› እንዲል ገላ.፬፥፬።
ይህ አመጣጥ የዓለምን ገጽታ የቀየረ ለዘመናት በሰው ልጅ ላይ ጸንቶ የነበረውን መርገም የሻረ ከገነት ተሰዶ የነበረውን የሰው ልጅ ወደገነት የመለሰ የአረጀውን ዓለም ያደሰ የረከሰውን የሰው ልጅ ሕይወት የቀደሰ ልጅነትን በሃይማኖት የሰጠ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን ያጠፋ ሞትን የገደለ የሰው ልጆችን ክብር የገለጠ ምጽአት ነው። በዚህ ግሩም ትሕትናውን አሳይቶ አምላክ በሥጋ በተገለጠበት ቀዳማዊ ምጽአቱ ሰው ሆኖ በመወለዱ ዓለም ያገኘውን ሕይወት መዘርዘር ያገኘውን ጸጋ መናገር በቁጥር የሚወሰን ስላልሆነ ይህን ያህል ነው ማለት አንችልም። እንዲያው በጥቅሉ የሰው ልጅ ከሞት ባርነት ከኃጢአት ተገዥነት በመቃብር ፈርሶ በስብሶ ከመቅረት ነጻ የወጣው በቀዳማዊው ምጽአተ ወልደ እግዚአብሔር ነው።
- Details
- Written by: ዳዊት ደስታ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 3260
እንደ መግቢያ
የሰው ልጅ አብሮ ለመኖር እንዲችል አካሄዱን የሚቆጣጠሩትና የሚመሩት ወደ ተፈለገውም ዕድገትና ብልጽግና እንዲደርስ የሚያስችሉት ሁለት የሥልጣን ተቋማት (ቤተ-መንግሥት እና ቤተ-ክህነት) አሉ። እነዚህ ተቋማት አንዱ ለመንፈሳዊ፣ ዘላለማዊና ሰማያዊ ጉዞውና ፍላጎቱ ሌላው ለሥጋዊ ጊዜያዊና ምድራዊ ጥቅሙና ዕድገቱ ላይ ተመሥርተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት በጥብቅ ግንኙነት ለረጅም ዓመታት አብረው ዘልቀዋል፤ ትስስሩም በሁለቱም መፈላለግ ላይ የተመሠረተ ነበር። መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለው መርሕ ተግባራዊ አፈጻጸሙ አጠያያቂ ነው፤ ሁለቱም በተመሳሳይ ሕዝብ ላይ ስለሚያተኩሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ‹‹መነካካታቸው›› አይቀሬ ነውና። በሀገራዊ ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር መተባበር በየትኛውም አኳኋን ‹‹ፖለቲከኛ›› ሊያሰኝ አይገባም፤ ለሃይማኖቱም ምድራዊ ህልውና የሀገር ሰላምና ልማት ያስፈልጋልና። የሁለቱም ህልውና የተመሠረተው በሕዝቡ ላይ መሆኑ ያገናኛቸዋል ብቻ ሳይሆን ወደ የራሳቸው ፍልስፍና በመሳብ ሂደት ውስጥ ያነታርካቸዋል። ቤተ ክርስቲያን ‹‹በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት›› ናት፤ ምድራዊው መንግሥትም በሕዝብ ተመሥርቶ፣ ለሕዝብ የሚሠራ፣ ሕዝባዊ ነው። እናም ሁለቱም ያለ ሕዝብ (ሰዎች) ሀልዎታቸው ሊነገር አይችልም።
- Details
- Written by: ቀሲስ ዐቢይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1906
ልደት
አባ ተከሥተ ብርሃን ከአባታቸው መልከ ጼዴቅ እና ከእናታቸው ድል በኢየሱስ በሰሜን ሸዋ አካባቢ የተወለዱ በ፲፫ኛውና በ፲፬ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ አባት ናቸው። አባ ተከሥተ ብርሃን የቀድሞ ስማቸው በኪሞስ ይባል የነበረ ሲሆን የደብረ ሊባኖሱ የእጨጌ ፊልጶስ ደቀ መዝሙርም ነበሩ። ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ባዘጋጁት የአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ግን ልደታቸው በ፲፬ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ተጽፏል።
የአገልግሎት ሕይወት
አባ ተከሥተ ብርሃን ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ወደ ጎጃም በመሄድ፣ ወንጌልን አስተምረዋል። በዚያም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርገዋል። በርካታ ምእመናንን በማሳመንና በማጥመቅም ዕድሜያቸውን ሙሉ እግዚአብሔርን አገልግለዋል። ከደብረ ሊባኖስ ወደ ጎጃም የሄዱበት ምክንያትም ንጉሡ አፄ አምደ ጽዮን የእንጀራ እናቱን ማግባቱን እጨጌ ፊልጶስ ስለተቃወሙት እርሳቸው ማለትም አባ ተከሥተ ብርሃንም ደግሞ በወቅቱ የእጨጌ ፊልጶስ ደቀ መዝሙር ስለነበሩ የንጉሡ ሰዎች የእጨጌ ፍልጶስ ተባባሪ ናችሁ ብለው ካደረሱባቸው መከራ የተነሣ በስደት ነበር። አፄ አምደ ጽዮን መነኰሳቱን ሲያሳድዳቸው አባ ፊልጶስ አባ በኪሞስን አንተ ወደ ምድረ ጎጃም ሂድ እኔ ክፍሌ በመንዝ አካባቢ በምትገኘው ደብረ ዕንቍ ነው” ብለዋቸው ወደ ጎጃም እንዲመጡ ሆኗል።
- Details
- Written by: ቀሲስ ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1989
ውድ አንባብያን ባለፈው ወር ዕትማችን በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዐምዳችን የትዳርንና ትዳር የሚፈርሱባቸውን ምክንያቶች በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል አገልጋይ የሆኑትን መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰን ጋብዘን አንደነበርና መልሳቸውንም ለእናንተ ማካፈላችን ይታወሳል። ቀጣዩን ክፍል ደግሞ በዚህ ወር ዕትማችን እናቀርባለን መልካም ንባብ።
፭.ሐመር፡- በአሁኑ ጊዜ የብዙዎች ትዳር ከሚፈርሱባቸው ምክንያቶች አንዱ በሩካቤ ሥጋ ጊዜ የስሜት አለመጣጣም ችግር እየተፈጠረባቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል? ለዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን መፍትሔውስ?
መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ለዚህም ጥያቄ በርከት ያሉ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ዋና ዋና የምላቸውን ለመጥቀስ ልሞክር፡-
- Details
- Written by: ቀሲስ ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1554
ቃሉን የተናገረው ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የተናገረበት ምክንያት ከየአቅጣጫው የተሰበሰቡት ሕዝብ ለተለያየ ፍላጎት እንደሆነ ያውቃልና ከፍላጎታቸው አንዱ ደግሞ አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት “በሉ እጅግም ጠገቡ ለምኞታቸውም ሰጣቸው። ከወደዱትም አላሳጣቸውም” (መዝ.፸፯፥፳፱) ተብሎ እንደተነገረ ኅብስት አበርክቶ ያበላናል ብለው የመጡ ነበሩ። እነዚህ ከየሰፈሩ የተሰበሰቡት ሰዎች እንደተራቡ ያውቃልና ደቀ መዛሙርቱ ቀድሞ እንዲያሰናብታቸው ሲጠይቁት “የሚበሉትን ስጧቸው እንጂ እንደራባቸው ሊሄዱ አይገባም” በማለት ተናገረ። ሙሉ ፅንሰ ሐሳቡን እንጥቀስና ዝርዝር ጉዳዩንም እንመለከታለን።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው በቅዱስ ወንጌል “ጌታችን ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ በታንኳ ሆኖ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከየመንደሩ በእግር ተከተሉት። በወጣም ጊዜ ብዙ ሰዎችን አይቶ አዘነላቸው፤ ድውዮቻቸውንም አዳነላቸው። በመሸ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው ቦታው ምድረ በዳ ነው ሰዓቱም አልፏል፤ ወደ መንደር ገብተው ምግባቸውን ይገዙ ዘንድ ሕዝቡን አሰናብታቸው አሉት። ጌታችን ኢየሱስም እንደራባቸው ሊሄዱ አይገባም እናንተ የሚበሉትን ስጧቸው እንጂ አላቸው።” (ማቴ.፲፬፥፲፫-፲፮) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን።
- Details
- Written by: እንዳለ ደምስስ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2177
የቀኑ ሐሩር አናት ይበሳል፣ ከአስፋልቱ ግለት የሚወጣው ወላፈን ፊትን ከመለብለብ አልፎ ልብ ይሰልባል። በዚያ ጠራራ ፀሐይ እመቤት ከንስሓ አባቷ ጋር ለያዘችው ቀጠሮ በሰዓቱ ለመድረስ እየተጣደፈች ከአራት ኪሎ ቁልቁል በመውረድ፣ በፓርላማ በኩል አድርጋ ወደ ታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም አቀናች። ቁና ቁና እየተነፈሰች ታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ስትደርስ አማትባ ወደ ውስጥ በመግባት በስተቀኝ ካለው ዛፍ ሥር ድንጋይ ላይ ዐረፍ አለች። ቀይ ፊቷ ብስል ቲማቲም መስሏል፤ በነጠላዋ ጫፍ የፊቷን ላብ ጠርጋ በረጅሙ “ኡፍፍፍፍ…” ብላ የድካም አየር አስወጥታ ዛፎቹና ንፋሱ ከሚፈጥሩት ቀዝቃዛ አየር ወደ ውስጥ ሳበች። ጥቂት ዕረፍት አድርጋ አስፋልቱን ይዛ በቀዝቃዛ አየር ታጅባ ወደ ቤተ ክርሰቲያኑ አመራች። የታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ግቢ በጥንታዊ ሀገር በቀል ዛፎች እንደተከበበ ግርማ ሞገሱን ተላብሶ ይታያል፣ ነፋሻማው አየር ደግሞ ለነፍስ ሐሤትን ያጎናጽፋል፣ የአዕዋፋቱ ዝማሬ በተመስጦ ሰማየ ሰማያት አድርሶ ይመልሳል።
እመቤት ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለደረሰች ግቢው ውስጥ የሰው ዘር አይታይም። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንዳቀናች በሴቶች መግቢያ በኩል በማምራት ተንበርክካ በመሳለም የልቡናዋን መሻት ይፈጽምላት ዘንድ ፈጣሪዋን፣ እንዲሁም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በምልጃዋ እንድትረዳት ስትማጸን ቆየች።
- Details
- Written by: ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ እንደሰበከው
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2720
ውድ አንባብያን በዚህ ዓምድ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ነገ ምን መሆን እንዳለባት የሚያሳይ፣ ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባል ቤተ ክርስቲያን ልትደርስበት የሚገባትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ፣ አኮኖሚያዊና ልማታዊ አቅጣጫዎችን ማሳየት፣ ትውልዱም የድርሻውን እንዲወጣ ማመላከት ነው። በመሆኑም አስቀድመን ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? የሚለውን መሠረታውዊ ዕውቀት መረዳት ይቻል ዘንድ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የሰበከውን በተከታታይ አቅርበንላችኋል መልካም ንባብ።
እንደ እግዚአብሔር ቸርነት በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው "አሐቲ ቤተ ክርስቲያን፤ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፤" የሚል ይሆናል።
- Details
- Written by: እህተ ሚካኤል
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2731
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከረማችሁ? ደህና ናችሁ? አሜን እግዚአብሔር ይመስገን!
ልጆች የአንደኛ ሰሚስተር ውጤት እንዴት ነው? መቼም ባለፈው ባስተላለፍንላችሁ ምክር መሠረት በደንብ አጥንታችሁ ጥሩ ውጤት እንዳመጣችሁ ተስፋ እናደርጋለን። በርቱ እሺ! ነገ አድጋችሁ የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ተረካቢ የምትሆኑት እናንተ ናችሁ፤ ለዚህ ደግሞ በመንፈሳዊውም በዓለማዊውም እውቀት ማደግ አለባችሁ።
ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ስለ ዐቢይ ጾም ወይም ስለ ጾመ ሁዳዴ ነው፤መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!
ልጆች! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በዓመት ውስጥ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ። እነዚህን አጽዋማት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ የሆነ ምእመን ሁሉ ከልጅ እስከ አዋቂ የሚጾማቸው ነው። ልጆች! በቤተ ክርስቲያን ሕፃናት ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ መጾም እንዳለባቸው ፤እንዲሁም አጽዋማት የአዋጅ እና የፈቃድ ተብለው እንደሚከፈሉ ከዚህ በፊት በጻፍነው ጽሑፍ ውስጥ ገልጠንላችሁ ነበር አስታወሳችሁ? ደህና።
ልጆች ዐቢይ ጾም(ጾመ ሁዳዴ) ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ጾም ዐቢይ ጾም የተባለበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ስለሆነ ነው። ሌላው ደግሞ ከሌሎቹ አጽዋማት ብዙ ቀናት የሚጾም ጾም በመሆኑ ነው። ጾመ ሁዳዴ መባሉም ‹‹ሁዳድ›› ማለት ሰፊ የእርሻ ቦታ ወይም ማንኛውም ብዙ ሕዝብ የሚሳተፍበት ሥራ ማለት ነው። ይህም ጾም ታላቅ ጾም በመሆኑ እና ብዙዎች የሚጾሙት ጾም በመሆኑ ምክንያት ጾመ ሁዳዴም ይባላል።
ዐቢይ ጾም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ዕለቱኑ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት የጾመው ጾም ነው። ልጆች! ጌታችን የጾመው ኃጢአት ኖሮበት ሳይሆን ለኛ አብነት ለመሆን ነው። በዚህም መሠረት ዐቢይ ጾምን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በኋላ ሐዋርያት ጾመውታል፤ እኛም ክርስቲያኖች እነሱን አብነት በማድረግ እንጾማለን።
ልጆች! የዐቢይ ጾም ወይም ጾመ ሁዳዴ ስምንት ሳምንታት እና ሃምሳ አምስት ቀናትን የያዘ ነው። እነዚህ ቀናት ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሑድን ሲይዙ በአጠቃላይ አሥራ አምስት ቀን ይሆናሉ ማለት ነው። የዐቢይ ጾም ሃምሳ አምስት ቀናት ናቸው ስንል ጌታ የጾመው ፵ ቀናት ነው። ለምን ሃምሳ አምስት ቀን ሆነ? ሲባል ከጾሙ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ የተጨመሩ ሁለት ሳምንታት ወይም አሥራ አምስት ቀናት ስላሉ ነው። እነሱም የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ሲባል ፤ የመጨረሻው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በመባል የሚታወቅ ነው። እነዚህ ሁለት ሳምንታት የተጨመሩበት የራሳቸው ታሪክ እና ምክንያት አላቸው።
ልጆች የዐቢይ ጾም ሳምንታት የየራሳቸው መጠሪያም አላቸው። እነዚህንም የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሰየመው የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ ሊቅ የሆነው ቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ በሚለው መጽሐፉ ነው። ስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት መጠሪያዎችም፡-
1. ዘወረደ
2. ቅድስት
3. ምኩራብ
4. መጻጉዕ
5. ደብረ ዘይት
6. ገብርኄር
7. ኒቆዲሞስ
8. ሆሣዕና በመባል ይታወቃሉ።
በዚህ ክፍል ከስምንቱ ሳምንታት ስያሜዎች ሁለቱን ማለትም ‹‹ዘወረደ››ን እና ‹‹ቅድስት››ን አንስተን ለምን ይህ ስያሜ እንደተሰጣቸው በዝርዝር እናያለን።
1. ዘወረደ ፡- ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ ዘወረደ›› በመባል ይጠራል። ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ለማዳን ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም መምጣቱን፤ ለሰው ልጆች ሲል መከራ ሞት መቀበሉን፣ እንዲሁም በመስቀል ተሰቅሎ ዓለሙን ማዳኑን ያመለክታል። ‹‹ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው›› ዮሐ ፫፥፲፫ ካለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሳት ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል። ይህ ሳምንት ‹‹ጾመ ሕርቃል›› በመባልም ይታወቃል።
ልጆች ሕርቃል የሚባል የቤዛንታይን ንጉሥ ነበር። እርሱ ንጉሥ በነበረበት ዘመን ፋርሶች ኢየሩሳሌምን በመውረር የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ማርከው ወደ ሀገራቸው ወስደውት ነበር። ንጉሡ ሕርቃልም ወደ ፋርስ በመዝመት የጌታን መስቀል ለማስመለስ ተነሣ፤ ነገር ግን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ‹‹ነፍስ የገደለ ሰው እስከ ዕድሜ ልኩ ይጹም›› ብለው ሥርዓት ሠርተው ነበርና ፈራ። ይህን ፍርሃቱን የተረዱት የኢየሩሳሌም ምእመናንም ‹‹ጠላታችንን አጥፍተህ መስቀሉን አስመልስልን እንጂ ጾሙን አምስት አምስት ቀን ተከፋፍለን እኛ እንጾምልሃለን›› በማለታቸው ፋርስ ድረስ ዘምቶ መስቀሉን አስመልሷል። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ሥርዓት መሠረት በማድረግ እንዲሁም ሐዋርያትን አብነት በማድረግ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት ‹‹ጾመ ሕርቃል›› በሚል ሰይማ እንዲጾም አድርጋዋለች። (ስንክሳር መጋቢት ፲፪)
2. ቅድስት፡- የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት ‹‹ቅድስት›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ከርኩስነታችን የምንቀደስበትን ሥርዓት ሊሠራልን በገዳመ ቆሮንቶስ መጾም መጀመሩን ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች። ልጆች ቅድስት ማለት ጽኑዕ፣ ክቡር ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ጾሙን የጀመረበት ሳምንት በመሆኑ ቅድስት ተብሎ ይጠራል።
ይህ ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ቅድስና የሚነገርበት ሳምንት ነው። ሰንበት የእረፍት ቀን እንድትሆን በኦሪትም በሐዲስም እግዚአብሔር አምላክ የቀደሳት ዕለት መሆንዋን የሚናገር፤ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ የፈጠረው ሰውም ቅድስናን መያዝ እንደሚገባው የሚያሳስብም ነው። ዘፍ ፪፥፫፤ ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፭—፲፮። ባጠቃላይ ቅድስት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ የጾምን ጥቅምና ሥርዓት ሊያሥተምረን መጾም የጀመረበት ሳምንት ነው።
ልጆች! ስለተቀሩት የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜና ትርጉም በሚቀጥለው እትማችን እናስተምራኋለን፤በሚቀጥለው ትምህርት እስከምንገናኝ ጾሙን እንድትጾሙና እንደትጸልዩ እንመክራችኋለን።
ደኅና ሰንብቱ ጾሙን የበረከት ያድርግላችሁ!
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 904
ነቢዩ ሳሙኤል የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በሳኦል ራስ ላይ ካፈሰሰ በኋላ ከፊቱ ስለሚገጥመው ነገር እየገለጸ መክሮት ነበር። ከእርሱ ተለይቶ ወደ ፊት በመሄድ ወደ ታቦር ወደ ትልቁ ዛፍ በደረሰ ጊዜ ሦስት ሰዎችን እንደሚያገኝ ነገረው። እነርሱም ‹‹ሰላምታም ይሰጡሃል ሁለትም ዳቦ ይሰጡሃል›› አለው። (፩ ሳሙ. ፲፥፬)። መንገድን ለጀመረ ተጓዥ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ሰላምና ስንቅ ዋነኞቹ ናቸው። በመንገድ ሰላም ከሌለ መንገደኛ ሊጓዝ አይችልም፤ ስንቅ ካልያዘም እንዲሁ። እነዚህ ሁለቱ ለተጓዥ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። የሰው ልጅ ተረጋግቶ ይኖር ዘንድ የሀገር ሰላምና በልቶ የማደር ጉዳይ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው።
እነዚህ ሁለት ነገሮች ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት በጸሎቷ የምታስታውሳቸው ጉዳዮች ናቸው። የምእመኖቿ ሰላምና በልቶ የማደር ጉዳይ ዘወትር ቤተ ክርስቲያንን ያስጨንቃታል። የምእመኖቿ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ ብሎም የዓለም ሰላምና የዕለት ምግብም ያሳስባታል። ቤተ ክርስቲያን የሁሉም እንደ መሆኗም ስለ ሀገርና ስለ ዓለም ሰላም ትጸልያለች። መጋቢ እግዚአብሔር ነውና በመግቦቱ ያስበን ዘንድ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን›› ብለን ወደ እርሱ እንድናንጋጥጥም ታስተምራለች።
- Details
- Written by: ዲ/ን ተስፋዬ ምትኩ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 927
ቸርነት፣ ደግነት፣ ምሕረትና ይቅር ባይነት የባሕርይ ገንዘቦቹ የሆኑለት አምላካችን እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠራቸው የሰው ልጆችን ከመንገዱ በመውጣት በጠላት ወጥመድ ተይዘው እንዳይቀሩ “ወደ እኔ ተመለሱ” እያለ ዘወትር ይጣራል። ይህ ጥሪ የንስሓ ጥሪ ነው። ንስሓ የቃሉ ትርጒም መጸጸት መቆጨት፣ በሠሩት ክፉ ተግባር ማዘን ማለት ነው። (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፰፻፸፰) በሌላ በኩል ደግሞ ንስሓ በሙሉ ልብ መመለስንና መለወጥን ያመለክታል። የሰው ልጅ ድካም የሚስማማውን ሥጋ እንደ መልበሱ ይደክማል፤ ይዝላልም። ከእውነት መንገድ፣ ከጽድቅ፣ ከሕይወት፣ ወጥቶ ይስታል። ይሁን እንጂ የሚያስብ አእምሮና የሚያመዛዝን ኅሊና ያለው ፍጡር እንደመሆኑ የሠራውን ስሕተት አስተውሎ መጸጸቱ የማይቀር ነው። ጸጸቱ የሐሳብ ለውጥ መኖሩን ያመለክታላል። ነገር ግን የሐሳብ ለውጥ ብቻ መፍትሔ አይሆንምና በተግባር መለወጥ አለበት። በሐሳብም በተግባርም መለወጥ ማለት ደግሞ አጠቃላይ የሕይወት ለውጥ መሆኑን ያስገነዝበናል። ንስሓ የሚባለውም ይህ ነው። ማለትም በመጀምሪያ ያለንበትን ሁኔታ ቆም ብለን ማሰብ፤ ያለንበት ሁኔታ ከትክክለኛው የሕይወት መስመር የወጣ እንደሆነ መጸጸትና መቆጨት፤ ቀጥሎም የበደልነውና የተጣላነው ሰው ካለ ይቅርታ መጠየቅና መታረቅ፣ ከሁሉ በላይ ሕጉን በመተላለፍ ያሳዘንነው አምላካችን ይቅር እንዲለን ደጅ መጥናት ንስሓ ይባላል። ከንስሓ በኋላም ወደ ትትክለኛው መንገድ በመመለስ አዲስ ሕይወት መጀመር ይጠበቅብናል።