- Details
- Written by: ዲ/ን ዐቢይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1192
ድካም በብዙ መንገድ ይገለጻል። በሥጋ መድከምና መሸከም የሚገባውን መሸከም አለመቻል፣ መሥራት በሚገባው መጠን መሥራት አለመቻል፣ መሮጥ በሚገባው መጠን መሮጥ አለመቻል ወዘተ ሁሉ ድካም ይባላል። ሌላው ደግሞ በመንፈስ መድከም ሲሆን ይህም የሚጠበቅበትን ያህል አለመጾም፣ አለመጸለይ፣ አለመስገድ፣ ብሎም በእምነት ጸንቶ አለመኖር ወዘተ የመንፈስ ድክመት ይባላል። አረጋዊው ስምዖን አስቀድሞ በመንፈስ ደክሞ የኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና መወለድ ማመን ተቸግሮ ነበር። በኋላ ግን በዕድሜ ረጅም ዓመታትን በዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ከመኖሩ የተነሣ ሸምግሎ ደክሞ ነበር። በዚህ ዐውድ ደካማው ሽማግሌ ነበልባሉን እንዴት ታቀፈው የሚለው በሥጋ መድከሙን አይደለም። ምክንያቱም ምንም ቢደክም የአርባ ቀን ሕፃን መሸከም አይቸገርምና። እንዲህ ከሆነ የቃሉ ተናጋሪ ኢትዮጳያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ምን ለማለት ነው ይህን የተናገረ የሚለውን ሙሉ ቃሉን እንጥቀስና በዝርዝር እንመለከታለን።
“ለዓለም ዘያዐርፎ በእንቲአነ ሥጋ ሰብእ ተአጺፎ በከመ አቅደመ እምትካት ተጽሕፎ ስምዖን ካህን ነበረ እንዘ ይሴፎ ሰአለ ከመ ያዕርፎ በሕፅኑ ተወክፎ አረጋዊ ድኩም እፎ ለነበልባል ሐቀፎ። ዓለምን የሚያሳርፈው ስለእኛ የሰውን ሥጋ ለብሶ (ተጎናጽፎ) ከጥንት ጀምሮ በመጻፍ መናገርን እዳስቀደመ ካህን ስምዖን ተስፋ እያደረገ ተቀመጠ። እንዲያሳርፈውም ለመነ። በዕቅፉም ታቀፈው። ደካማው ሽማግሌ ነበልባሉን እንዴት ታቀፈው።” (ድጓ ዘስምዖን አረጋዊ) በዚህ ምንባብ የሚከተሉትን ነጥቦች መመልከት ይቻላል።
Read more: ደካማው ሽማግሌ ነበልባሉን እንዴት ታቀፈው? (ቅዱስ ያሬድ ድጓ ዘስምዖን አረጋዊ)
- Details
- Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2045
‹‹ሃያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ። በኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋው ያለ ጦርነት የለም።… በአፍሪካ በኩል ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሣቱ ታወቀ። የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ። ጥቁሩ ዓለም በኤሮፓውያን ላይ ሲያምጽና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል። የኛ ዓለም ገና ቶርና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው። አሁን የኹሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው…››። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ ገጽ ፻፶፱)።
ይህንን የተናገረው ቤርክሊይ የተባለ ጸሐፊ ነው። (Berkeley, George; The Campaign of Adowa and the Rise of Menilik)። ከአድዋ ጦርነት በኋላ ይህና እንዲህ ዓይነቱ የአድናቆት ምስክርነት ከዓለም ዙሪያ ለኢትዮጵያውያን መበርከቱን የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። የአድዋ ድል የዓለም ፖለቲካዊ አካሔድ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ነበረው። እንዲያውም የዚያን ዘመኑን የቅኝ ግዛት ዘመን ከአድዋ በፊትና ከአድዋ በኋላ ብሎ መክፈልና ማጥናት ይቻላል። በዓለም ላይ ከታዩ እጅግ አስገራሚና ወሳኝ ክስተቶች እንደ አንዱም መመደብ የሚችል ነው። ይህ የሆነው ደግሞ በጊዜው አሉ የተባሉትን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቀችና ከጊዜው ኃያላን አንዷ የሆነች አንዲት አውሮፓዊት ሥልጡን ሀገር፣ እዚህ ግባ የሚባል ሥልጣኔ በሌላትና እንደ አውሮፓውያኑ የምታመርተው ቀርቶ የምትገዛውና በእርዳታ የምታገኘው የጦር መሣሪያ እንኳን በቁጥር ውሱንና እጅግ ኋላ ቀር በሆነ፣ ዘመናዊ የጦርነት ስልትን እንደ ሌሎቹ ያልተራቀቀችበት፣ ጦርና ጋሻን በያዙ ዜጎቿ የምትዋጋ እንጂ የወታደሮቿ ቍጥር ጥቂት በሆነባት፣ በአንዲት አፍሪካዊት ሀገር መሸነፏ ነበር።
- Details
- Written by: ሕግና ዕቅበተ እምነት አገልግሎት ማስተባበሪያ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1022
ባለፈው ጽሑፋችን ዕቅበተ እምነትን በተመለከተ በጥቅሉ መጻፋችን ይታወሳል። ይህ ጽሑፍም ካለፈው የቀጠለ ሲኾን በተለይ ዐቃብያነ እምነት ወይም ቀዋምያን ለቤተ ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩ አባቶችን ሕይወትና ጽሑፋቸውን የሚዳስስ ነው።
ኹለተኛው ክፍለ ዘመን በርካታ ፈተናዎችን በቤተ ክርስቲያን ላይ የጋረጠ ክፍለ ዘመን እንደ ነበር ተመልክተናል። የሮም መንግሥት በግዛቶቹ ሁሉ ክርስትናን ሕጋዊነት የሌለው አዲስ እንቅስቃሴ አድርጎ በመቍጠሩ ክርስቲያኖች እንደ ወንጀለኛና የመንግሥት ተቃዋሚ ተደርገው እንዲታዩ መንገድ ከፍቶ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ አዲስ አቀራረብ ያላቸው የዕቅበተ እምነት ጽሑፎች መውጣት ጀመሩ። በዚህ ሂደት የአቴንሱ ዮስጢኖስ የመጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
፩. ሰማዕቱ ዮስጢኖስ /Justin Martyr (፻-፻፷፭ዓ.እ/AD.)
በኹለተኛው ክፍለ ዘመን ከተነሡ ዐቃብያነ እምነት አንዱ የሆነውና በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን ጽሑፎች ጥናት ስሙ በሰፊው የሚነሣው ዮስጢኖስ ነው። (Johannes Quasten, Patrology Vol. I,፻፺፮.) ጥንት የሰማርያ ክፍል በነበረችው፣ ናብሉስ (Neapolis/Nablus) ከኢአማንያን ወላጆች የተወለደ፣ እስከ ሠላሳ ዕድሜው ድረስ የተለያዩ የፍልስፍናና ሌሎችንም የዕውቀት ዘርፎችን ሲያጠና ቆይቶ በ፻፴ ዓ.እ/AD. ክርስትናን የተቀበለ፣ በመጭረሻም ታላቅ የክርስትና ጠበቃ መኾን የቻለ አባት ነው። (Cross, The Oxford Dictionary of the Christian Church, 1974, 770.)
- Details
- Written by: በዲ/ን ደረጀ ጋረደው
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1364
፮. በገዳሙ የተከናወኑ ገቢረ ተአምራት
በገዳሙ ለረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጠበል የሚገኝበት ሲሆን፤ በተጨማሪ ከቅርብ ዓመታት በፊት የበዓታ ለማርያም ጠበል ፈልቋል። አሁን ሁለቱም ጠበሎች በአንድ ላይ የሚፈሱ ሲሆን፤ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ ብዙ ድውያን ተፈውሰዋል እየተፈወሱም ይገኛሉ
ጠበሉ ፈዋሽ እንደመሆኑ መጠን አላግባብ ለሚጠቀሙበት ሰዎችም ደም በመሆን ተአምራቱን ገልጿል።
በጥንት ጊዜ ጫካው የሚጠበቀው በዳልጋ አንበሳ እንደ ነበር አባቶች ያስረዳሉ።
፯. በገዳሙ ተሠርተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የልማት ውጤቶች
፯.፩.የእናቶች እና አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት ማደሪያ
አንድ እናት ፭ እጓለ መውታ (የሙት ልጅ) ሕፃናትን በመንከባከብ እንዲያሳድጉ በማሰብ ፲፮ ክፍሎች ያሉት ባለ አንድ ፎቅ (G+1) ዘመናዊ ሕንጻ ተገንብቶ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ሲሆን የተለያዩ ቁሳቁሶች፣ የገላ መታጠቢያ እና መጸዳጃ ቤቶችም የተሟሉለት ነው። እጓለ ማውታ (የሙት ልጅ) ሕፃናት ገብተው አገልግሎቱ መሰጠት ባይጀምርም ሕንጻው መናንያን እናቶችን በጊዜያዊ በዓትነት እያገለገለ ይገኛል።
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 4034
ውድ አንባብያን በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዐምዳችን የትዳርንና ትዳር የሚፈርሱባቸውን ምክንያቶች በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል አገልጋይ የሆኑትን መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰን ጋብዘናል። መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቪዥን መርሐ ግብር አዘጋጅም ናቸው። ፈቃደኛ ሆነው ከቦታችን ተገኝተውልን ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ንባብ።
ሐመር፡- መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰን ትዳርንና በትዳር መካከል የሚነሡ ችግሮችን መሠረት ያደረጉና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ለምናነሣቸው ሐሳቦች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለ ሆኑልን አስቀድመን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።
መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
፩. ሐመር፡- ትዳር ማለት ምን ማለት ነው?
መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ትዳር፡- ብዙ አጥኚዎች፣ በጋብቻ ዙሪያ የጻፉና የሰበኩ መምህራንም በተለያየ መልኩ ገልጸውታል። እኔ በአለኝ መረዳት ሁለት ተጋቢዎች አንድ ወንድና አንዲት ሴት በጋብቻ አንድ የሚሆኑበት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። በሌላ አገላለጽ ደግሞ ሀብት ንብረት ማፍራት፣ ልጆች ወልዶ፣ በአንድነት ቤተሰብ መሥርቶ መኖር ትዳር ይባላል። አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ትዳር ሀብት ንብረት ተብሎ ተገልጾ እናገኛለን። ተጋቢዎች ሀብት ንብረት አፍርተው የሚኖሩበትን ሕይወት ያስረዳል። ለምሳሌ “ከዐሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት ነበረች፤ ትዳሯንም ሁሉ ለባለ መድኃኒቶች ሰጥታ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም ነበር” (ሉቃ.፰፥፵፫) ተብሎ ተጽፎ እንደምናነበው ትዳር ሀብት ንብረት ተብሎ ተገልጾአል። በአጠቃላይ ትዳር አንድ ወንድና አንዲስ ሴት በጋብቻ ተጣምረውና ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩበት የአንድነት ኑሮ ማለት ነው።
፪. ሐመር፡- ትዳር በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እይታ እንዴት ይገለጻል?
መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ትዳር (ጋብቻ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ቅዱስና ክቡር ነው ተብሎ ይገለጻል። አስቀድሞ መሥራቹ ልዑል እግዚአብሔር ነው። ፈጻሚዎቹ ደግሞ የሰው ልጆች ናቸው። እግዚአብሔር የባረከው፣ የቀደሰውና ሕግ አድርጎ የሰጠው ሁሉ መልካም ነው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት በፍቅር ላይ ተመሥርተው የሚመሠርቱት ጋብቻም ቅዱስ ነው። ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ ጋብቻን ባርኮ የሰጠ እግዚአብሔር ነው። የሰው ልጅ ዕድሜው ሲደርስ በቅዱስ ጋብቻ ወይም በምንኵስና እንዲኖር ይመከራል። ሱባኤ ገብቶ፣ ልቡን መርምሮ፣ ካህናትን አማክሮ አንዱን ሕይወት ይወስናል። ስለዚህ በየትኛውም ሕይወት ማለትም በጋብቻም ሆነ በምንኵና ሕይወት መኖር የተቀደሰና የተባረከ ነው።
አስቀድሞ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ስለሆነ ዛሬም ራሱን መርምሮ ከካህን ጋር ተመካክሮ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቆ በትዳር እንዲወሰን መጽሐፍ ቅዱስ ይመክራል ያስተምራል። አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በማስተማር ዘመኑ የመጀመሪያውን ተአምር በቃና ዘገሊላ ተገኝቶ በሰርግ ቤት ማድረጉ ጋብቻ የተባረከ መሆኑን ያሳየናል። እንዲሁም አስቀድሞ “ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት እንጂ” (ዘፍ.፪፥፲፰) በማለት የተናገረውን አምላካዊ ቃል ሕግ አድርጎ እንደሰጠን ሁሉ በማስተማር ዘመኑም ‹‹ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ሚስቱን ይከተላል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ። እንኪያስ ሁለት አይደሉም፤ አንድ አካል ናቸው እንጂ፤ እግዚአብሔርም አንድ ያደረገውን ሰው አይለይ” (ማቴ.፲፱፥፭-፮) ብሎ ማስተማሩ ትዳር ቅዱስ መሆኑ ይገልጻል።
እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ትዳር ክብረ ንጽሕናቸውን ጠብቀው እስከ ጋብቻቸው በድንግልና ለኖሩ በተክሊል፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ድንግልናቸውን ላልጠበቁ ንስሓ ገብተው፣ በቁርባን በመንፈሳዊ ሥርዓት ሲፈጸም ቅዱስ፣ ክቡር ነው። ልዩ ልዩ ምክንያቶች የተባሉትም በሞት፣ በዝሙትና በመሳሰሉት እንደ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬ ትእዛዝ ድጋሜ ጋብቻ ለሚፈጽሙት በመዓስብ ሥርዓት ይፈጸማል። ማሳረጊያው ግን ቅዱስ ቊርባን ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በንስሓና በመንፈሳዊ ሥርዐት የሚፈጸም ጋብቻ ክቡር ነው፤ ቅዱስ ነው፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበት ነው፤ እያለች ትመሰክራለች።
ጋብቻ ቅዱስ የሚሆነው በመንፈሳዊ ሥርዐት ሲፈጸም ብቻ ነው። ሰው ሁሉ የሥላሴ ፍጡር ነው። ሰው ሁሉ ግን ቅዱስ ነው ማለት አይቻልም። ይህም ቅድስና የተለየ ተጋድሎ ስለሚጠይቅ ነው። ተራሮች ሁሉ የእግዚአብሔር ፍጥረታት ናቸው። ግን ተራሮች ሁሉ መሥዋዕት አይሠዋባቸውም። ቦታዎችን ሁሉ ቅዱሳት መካናት፣ አድባራትና ገዳማት አንላቸውም። ታቦተ ሕጉ ያለበትን፣ ሥጋ ወደሙ የሚፈተትበትን ቅዱሳን ከሰብአ ዓለም ተለይተው ዕድሜ ልካቸውን የጸለዩበትን፣ ሱባኤ የገቡበትን፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉበትን፣ ወዘተ ቅዱሳት መካናት፣ አድባራትና ገዳማት እያልን እንጠራቸዋለን። ከተራራ መርጦ በገዳመ ቆሮንቶስ ጾምና ጸሎት እንደያዘ፣ በደብረ ሲና ጽላተ ኦሪትን እንደሰጠ፣ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጠ ሁሉ በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን፣ በንስሓ ሕይወት፣ በመንፈሳዊ ሥርዐት በቅዱስ ቊርባን የተፈጸመ ጋብቻ ቅዱስ ነው፤ ክቡርም ነው።
፫. ሐመር፡- እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ባልና ሚስት እንዴት ይገለጻሉ? በምንስ ይመሰላሉ?
መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ባልና ሚስ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንዴት ይገለጻሉ በምንስ ይመሰላሉ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ለምሳሌ፡- በኦሪቱ ነቢያት የእስራኤልንና የእግዚአብሔርን ግንኙነት እንደባልና ሚስት መስለው አስተምረውበታል። እስራኤል ከሕገ እግዚአብሔር ፈቀቅ ባሉ ጊዜ ጋለሞታ ተብለው ተሰድበዋል። በድንቅ አጠራሩ ጠርቶ፣ በቸርነቱ ረድቶ ከብዙ መከራ የታደጋቸው ሲበድሉ ግን እግዚአብሔር በነቢዩ በኤርምያስ ላይ አድሮ የተናገረውን እንመልከት።
ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን ወደረዘመው ተራራ ሁሉ ወደለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች፤ በዚያም አመነዘረች። ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደእኔ ተመለሽ አልኋት፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እህቷ ይሁዳም አየች ከዳተኛይቱ እስራኤል እንዳመነዘረች አየሁ። የፍችዋንም ደብዳቤ በእጅዋ ሰጥቼ ሰደድኋት ጎስቋላ እህቷ ይሁዳ ግን በዚያ አልፈራችም፤ እርሷም ደግሞ ሄዳ አመነዘረች ዝሙቷም ከንቱ ሆነ፤ እርሷም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች በዚህም ሁሉ ከዳተኛይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጅ በእውነት ወደእኔ አልተመለሰችም። (ኤር. ፫፥፮-፱)
ጋለሞታ ማለት ባል ፈትታ የምትኖር ሴት ማለት ነው። እስራኤል ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወጥተው በአምልኮተ ጣዖት ወይም ከፈቃደ እግዚአብሔር ውጭ ሆነው መኖር በጀመሩ ጊዜ ባሏን የፈታች ሴት ተብለዋል። ባልና ሚስት አይለያዩም፤ የሰው ልጅም ከአምልኮተ እግዚአብሔር ሊወጣ አይገባውም። አለዚያ ግን ጋለሞታ ወይም ባል አልባ ወይም ሚስት አልባ ይባላል። ስለዚህ እስራኤል ከአምልኮተ እግዚአብሔር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ በኤርምያስ ላይ አድሮ “ጋለሞታ” በማለት ገሠጻቸው።
ነቢዩ እግዚአብሔር በእስራኤል ስለመገለጡ፣ በእስራኤል ድንቅ ምሥጢር ስለማድረጉ እነርሱን እየመገበ በእነርሱ እየተመሰገነ መኖሩን እግዚአብሔር እንደ ባል እስራኤል እንደሚስት ሆነው ቅርርባቸውን የሚያሳይ ነው። ይህም ትዳር መንፈሳዊና ሰማያዊ ምሥጢር ያለው መሆኑን ነው የሚያሳየው።
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የበለጠ ይልቅም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ባልና ሚስትን ይልቁንም በፍቅር የሚዋሐዱ አንድ ወንድና አንድ ሴትን በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መስሎ አስተምሯል። ይህንም በኤፌሶን መልእክቱ ‹‹ዐቢይ ውእቱ ዝ ነገር፤ ወአንሰ እብሎ ላዕለ ክርስቶስ ወላዕለ ቤተ ክርስቲያኑ፤ ይም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገራለሁ›› (ኤፌ.፭፥፴፪) በማለት የምሥጢሩን ታላቅነትና ባልና ሚስት ሊኖሩበት የሚገባውንም ልዩ የአኗኗር ምሥጢር በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መስሎ አስተማረ። ከላይም እንዲሁ “ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቱያንን እንደ ወደዳት ራሱንም ስለ እርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ” ይላል። (ኤፌ.፭፥፳፭) ይህ ማለት ሴትም ለባሏ ትገዛ ባልም ሚስቱን ይውደዳት በማለት ነው።
ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የወደዳት እስከሞት ድረስ ነው። ባልም ሚስቱን እስከሞት ድረስ ሊወዳት ይገባል። ሚስትም ለባሏ ትገዛ ሲል ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ በፍቅር እንዳምትገዛ ሁሉ ሚስት ለባሏ በፍቅር ትገዛ ሲል አስተምሯል። ቤተ ክርስቲያን ስንል ማኅበረ ምእመናንን ማለታችን ነው። ማኅበረ ምእመናን የሚጾሙት፣ የሚጸልዩት፣ ንስሓ የሚገቡት ተገደው አይደለም። ካህናቱ አስገድደዋቸው ገዝተዋቸው አይደለም። በራሳቸው ፈቃድ ነው። ደስ ብሏቸው የሚያደርጉት ነው። አጽዋማቱ መጡ፣ ብለው ሊጾሙ የሚዘጋጁት፣ በዓላቱ መጡ ብለው ገንዘባቸውን አውጥተው ሊያከብሩ የሚዘጋጁት፣ ዐሥራት በኩራታቸውን የሚያወጡት እግዚአብሔርን ወደው ነው። ስለዚህ ሴት ለቧሏ የምትገዛ በፍቅር ነው። ባልም ከመውደድ አልፎ ይሙትላት ተብሏል። እንግዲህ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ባልም ራሱን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ የሚወዱትና ሁለቱም በጽኑ ፍቅር የሚኖሩበት ስለሆነ ባልና ሚስት በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን ተመስለዋል።
በሌላ አንቀጽ እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው የሚኖሩ ናቸው። ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው ሰው የሚለውንና በሰብእና የሚገልጸው ነገር እንደሚያስገኙት ሁሉ ባልና ሚስትም በአንድነት ተዋሕደውና ተስማምተው የመኖር ድንቅ ምሥጢር እንዳለው በልዩ ልዩ የሊቃውንት መጽሐፍ እንረዳለን። ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ አካል ናቸው በማለት ድንቅ ቃል ተናገረ። አንድ አካል ናቸው ሲልም ለምሳሌ፡- ማንም አካሉን እንደሚወድ ሁሉ ከአካሌ ላይ ይቆረጥ፣ ከእግሬ ላይ ይቆረጥ እንደማይል ሁሉ በሌላ አገላለጽም ቅዱስ ጳውሎስ “ሚስቱንም የሚወድ ራሱን ወደደ” (ኤፌ.፭፥፳፰) እንዳለ ሁሉ ባል የሚስት አካል ነው ሚስትም የባል አካል ናት። ማንም ሰው ለዐይኑ እንደሚሳሳ እንዲሁ አንዲት ሴት ለእጇ፣ ለእግሯ፣ ለሰውነቷ ሌላው ቀርቶ ለጌጣጌጧ እንደምትሳሳ ሁሉ ባሏንም እንደሰውነቷ እንደ አካሏ እንድታይ ጌታችን መድኃኒታችን አንድ አካል ናቸው ያለውን መሠረት አድርገው ሐዋርያትና ሊቃውንት ተንትነውታል።
ለምሳሌ፡- ቅዱስ ጳውሎስ በ (፩ቆሮ.፯፥፬) ላይ “ሚስት በራስዋ አካል ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ባል በራሱ አካል ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ” ሲል በእርሱ አካል ላይ ሚስት ሥልጣን አላት። በሚስት አካል ላይ ባል ሥልጣን አለው። ይህም አንድ አካል ናቸው የሚለውን ይበልጥ እንድንረዳው የሚያስገነዝበን ነው። ራስ ወዳድነት የሚጠፋበት፣ መዋደድ፣ መተሳሰብ፣ ባል ለእኔ ሳይሆን ለእርሷ የሚልበት፣ ሚስትም ከራሷ ይልቅ ለባሏ የምታስብበት፣ የባል ችግር ለሚስት፣ የሚስትም ችግር ለባል፣ የባል ደስታ ለሚስት፣ የሚስትም ደስታ ለባል፣ የሚሆንበት ነው። በአንድ የሰውነት ክፍል መታመም የትኛውም የሰውነት ክፍል ምቾት አይስማማውም። ለምሳሌ፡- እግር ቢታመም መላውን ሰውነቱን እንደ ሕመም ይሰማዋል። ይህ ሁሉ የማይነጣጠል ጽኑ አንድነት ያለበት በእስራኤልና በእግዚአብሔር በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን፣ በነፍስና በሥጋ የተመሰለ መሆኑን ያስረዳናል።
፬. ሐመር፡- በዚህ ዘመን የትዳር መፍረስ እየተስፋፋ እንደሆነ ይስተዋላል። ለትዳር መፍረስ ምክንያቶች ናቸው ብለው ከሚያስቧቸው መካከል የተወሰኑትን ቢገልጹልን?
መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ለትዳር መፍረስ ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። አንዳንዶች እንደ እግዚብሔር ፈቃድ በሽምግልና ከመፍረስ ሲድኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በየፍርድ ቤቱ ሰማንያችን ይቀደድልን ብለው ሲሄዱና ትዳራቸውንም ሲያፈርሱ ይስሠተዋላል። ለዚህ ሁሉ ችግሮችና የችግሮቹን ምንጮች ስናነሣ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ከመጀሪያው ለመነሣት፡-
፩. በጠላት ዲያብሎስ ፈተና፡- ጠላታችን ዲያብሎስ በዙሪያችን ሆኖ የእኛን መሰናከልና መውደቅ ይጠባበቃል። በመሆኑም በሥጋ ወደሙ፣ በንስሓ ሕይወት፣ በአጠቃላይ በጥሩ መንፈሳዊ ሕይወት ከብረው የኖሩትን ባልና ሚስቶች ሳይቀር መርዙን እየረጨ ሊፈትናቸው ይችላል። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ ትጉም፤ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና” (፩ጴጥ.፭፥፰) በማለት እንደገለጸው ዲያብሎስ እኛን ለመጣል ስለማያርፍ በዚህ ምክንያት ሊፈርስ ይችላል።
፪. በራስ ደካማ ጐን ፡- ይህ ሲባል በባል ወይም በሚስት በኩል ባለ ድክመት፣ ራስን ለይቅርታ ባለማዘጋጀት በማይረባ ምኞት በመጠለፍ ፈተናቸው እየጠነከረ ሲሄድ ይስተዋላል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “የሚፈተን ሰው ቢኖር እግዚአብሔር ይፈትነኛል አይበል፤ እግዚአብሔር ለክፉ ነገር አይፈትንምና፤ እርሱ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ምኞት ከፀነሰች ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ከተፈጸመች ሞትን ትወልዳለች” (ያዕ.፩፥፲፫-፲፭) በማለት እንደተናገረው ክፉ ምኞታችን ለራሳችን የሕይወት መሰናክል ይሆናል።
እንዲሁ ይህው ሐዋርያ ‹‹በእናንተ ዘንድ ጥልና መጋደል ከወዴት ይመጣሉ? በሰውነታችሁ ውስጥ የሚሠራውን ዝሙት ከመውደድ የተነሣ ከዚህ አይደለምን? ትመኛላችሁ እንጂ አታገኙም፤ ትቀናናላችሁ፤ ትገዳደላላችሁ፤ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ፣ ትዋጉማላችሁ፤ ነገር ግን አትለምኑምና የምትፈልጉትን አታገኙም፤ ትለምናላችሁ ለፍትወታችሁ ትከፍሉ ዘንድ ለክፉ ትለምናላችሁና አታገኙም” (ያዕ.፬፥፩-፫) በማለት እንደተናገረ ከራሳችን ክፉ ምኞት፣ ጸሎት አለማድረግ፣ ብናደርግም እንኳን ለመልካም ነገር ሳይሆን ለክፉው ነገር ስለምንለምን መልካሙን አታገኙም ተባልን። ስለዚህ ራሳችን ያለመገንዘብ፣ ራሳችን ለትዳራችን በአግባቡ ካለመጸለይ፣ ወዘተ ከመሳሰሉት ሁሉ ለትዳር መፈታት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ። ሌሎቹንም ብዙ ጊዜ ለትዳር መፍረስ ምክንያት የሚሆኑትን የተወሰኑትን ለመጥቀስ ልሞክር፡-
፫. ሳይተዋወቁ መጋባት፡- ቀድሞ በሁለቱም በኩል ያለውን ጠንካራና ደካማ ጐን ሳይጠናኑ በችኮላና በአንዳንድ ጊዜያዊ ስሜቶች ወስኖ የሚገቡበት ትዳር በኋላ ለሚፈጠረው የሐሳብ መለያየት “ሳላውቀው ነው፤ ሳላውቃት ነው” መባባል ላይ ስለሚደርሱ የፍች ምክንያት ሲሆን ይታያል። በእርግጥ ሰው ተጠንቶ አያልቅም። ይሁን እንጂ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን መሠረታዊ የሆነ ግንዛቤ በሁለቱም በኩል ሊኖር ይገባል። ይህ ሳይሆን ይቀርና መጋባታቸው ከመሰማቱ መፋታታቸው የሚሰማ ባልና ሚስቶች እየተበራከቱ መጥተዋል።
፬. ስለ ሦስተኛ ወገን ሳያስቡ መጋባት፡- ይህ ማለት ስለ ልጅ፣ ስለ እናትና አባት፣ ስለ ቤተ ሰብ፣ ስለማኅበራዊ ኑሮ ወዘተ ሳያስቡ መጋባት የሚያስከትለው ችግር ነው። ለምሳሌ ከተጋቡ በኋላ ልጅ እንውለድ አንውለድ ተባብለው የሚጋጩ አሉ። በሥራ ጠባይ፣ በሀብት እጥረት፣ በትምህርት ወዘተ ሰበብ ሲሉ ለመውለድ አንዱ ሲፈልግ ሌላኛው ሳይፈልግ ግጭት ይፈጠራል። ይህ ደግሞ ገና መጀመሪያ ሲጋቡ “ሰነፈች፣ ደከመች፣ መከነች፣ ጠቆረች፣ ከሳች፣ ወዘተ” ብዬ ላልፈታት የሚለውን ቃል ኪዳን ልብ አለማለትን ያስረዳል። ከጋብቻ በኋላ ገንዘቡ ሲቀንስ፣ ውበቱ ሲቀንስ፣ ታዋቂነቱ ሲቀንስ ወዘተ የጠባይ መለዋወጥ የፍቅር መቀነስ ይከሠታል። “ራስን መተው፣ ራስን መካድ” የሚለውን ይዘነጉትና በሐሳብ ለመለያየታቸው መሠረታዊ ጉዳይ ባልሆነው ሁሉ ሲጋጩ ይስተዋላሉ። ይህ ሁሉ ትርጉም ሲያጣ ፍቺ ይከሠታል።
፭. ሀብትን መሠረት አድርጐ መጋባት፡- በዚህ ዓለም ሲኖሩ ሀብት ንብረት ያስፈልጋል። ነገር ግን ቀዳሚ ጉዳይ መሆን የለበትም። ሀብትን መሠረት አድርጐ መጋባት ሀብቱ እየጐደለ ሲሄድ ቤት ላይ በሚጐድሉ ነገሮች መለያየት፣ መጨቃጨቅ ይጀምራሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀብት ቢኖርም ሀብት ለጊዜው እንጂ ዘላቂ ፍቅርን አይሰጥም። ሲያውቁበት እንጂ ሳያውቁበት መንግሥተ ሰማያትንም ለመውረስ ፈተና ይሆናል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “ገንዘብ ላለው ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው?” (ማር.፲፥፳፫) በማለት ያስተማረው ወደ ሰማያዊውና ወደ ዘለዓለማዊው ዓለም ለመግባትም መሰናክል የሞሆንበት አጋጣሚ ስላለ ነው። ደግሞም በገንዘቡ እናገኘዋለን ብለው የጠበቁት ነገር አልገኝላቸው ሲል ትዳራቸውን ይፈታሉ።
፮. አለመተማመን፡- በመካከላቸው አለመተማመን፣ ካለ ትዳራቸው ሊፈርስ ይችላል። በሆነ ባልሆነው መጨቃጨቅ ከእገሌ ጋር አየሁህ፤ ከእገሌ ጋር አየሁሽ ወዘተ መባባል የጭቅጭቃቸው መጠን እየሰፋ ይሄዳል። በባልም ሆነ በሚስት በኩል በድብቅ የሚፈጸም ነገር ካለ በጎም ቢሆን መቆም አለበት። በበጎው ላይ መደባበቅ ካለ በመጥፎውም ላይ ሊኖር ይችላል በማለት እርስ በእርሳቸው እንዲጠራጠሩ ይገፋፋቸዋል። አለመተማመን ለወንዶች ወይም ለሴቶች ብቻ ተለይቶ የሚሰጥ አይደለም። ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ነገሮችን ማስወገድ አለመቻል ነው።
፯. ግልጽ አለመሆን፡- በአንዳንዶቹ ዘንድ የሚበሉ፣ የሚጠጡትን፣ የሚለብሱትን ብቻ መናገራቸው ግልነት ሊመስላቸው ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን የውስጥ ስሜታቸውን በተክክል አይናበቡም። በይሉኝታ ተደብቆ፣ በራስ ማንነት ሳይሆን ሚስት ከሆነች ባሏን ባልም ከሆነ ሚስትን ደስ ያሰኙ እየመሰላቸው በትክክለኛ ማንነታቸው መገለጥ አለመቻል ሊገለጡ የሚገባቸውን ጉዳዮች አለመግለጥ፤ ግልጽ የገንዘብ ዝውውር አለመኖር፣ በድብቅ ቤተሰብን መርዳት ወዘተ ለግጭት መንሥኤ ሊሆን ይችላል።
፰. በሩካቤ ሥጋ አለመጣጣም ነው፡- ከጋብቻ በፊት ጤንነታቸውን፣ የውስጥ ስሜታቸውን በሚገባ ማጤን ይኖርባቸዋል። በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከጋብቻ በፊት ባለ የቆይታ ጊዜ ከአላስፈላጊ መነካካት፣ ከመዳራት ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መቆጠብ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ በስነ ልቡና ችግር፣ በፊት በነበራቸው የብቸኝነት እሳቤ በፍርሃት ወዘተ… ባለመነጋገር (ባለመወያየት ወዘተ በሚፈጠር አለመጣጣም ጋብቻ ሲፈርስ ይታያል)
፱. የሌሎች አሉታዊ ጣልቃ ገብነት፡- ይህ በቤተሰብ፣ በጓደኛ፣ በሥራ ባልደረባ ወዘተ አማካኝነት ትዳራቸውን ከሚያጸና ይልቅ የሚያፈርስ ሐሳብ ሊያመጣ ይችላልና የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ካለ ትዳር ሊፈርስ ይችላል። የአንዳንዶቹ ጣልቃ ገብነት በውስጣቸው የሐሳብ መለያየትን ከመፍጠር አልፎ ፍታት ወይም ፍቺው ብለው እስከ መወሰን ድረስ የሚደርስ ነው። በዚህ ጊዜ ባለትዳሮቹ በብሉይ ኪዳን “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ሚስቱንም ይከተላል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” (ዘፍ.፪፥፳፬) እንደተባለ በሐዲስ ኪዳንም ‹‹ስለዚህ ወንድ አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ አካል ናቸው›› (ኤፌ.፭፥፴፩) ተብሏል። ስለዚህ ሰዎች ይህን በአግባቡ በመረዳት ለትዳራቸው ዋስትና ማበጀት ይኖርባቸዋል። ባል የሚስቱን ሐሳብ ሚስት የባሏን ሐሳብ አክብራ ለትዳራቸው እንቅፋት የሚሆነውን የሦስተኛ ወገን ሐሳብ በመተው ዘላቂ የሆነውን ኑሯቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተቃራኒው ግን ከእናትና ከአባቴ አትበልጥብኝም /ጭብኝም በመባባል ትዳራቸው ሲፈርስ ይስተዋላል።
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1224
የሰው ልጅ ፍላጎቱ ገደብ የሌለው፣ አንዱ ሲሟላለት ሌላ የሚያስብ፣ በወቅቱ ያሰበው ሲከናወንለት ደግሞ ሌላ የሚፈልግ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ አሳቢ አእምሮ ተሰጥቶት ስለተፈጠረ እንደሆነ ይታወቃል። ምን አልባትም እንደ አደገበት ሁኔታ፣ እንደተማረው የትምህርት ዓይነት፣ እንደኑሮ ዘይቤው የሚያስበው ነገር ሊለያይ ይችላል እንጂ የማያስብ ሰው ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ይሁንም እንጂ ስላሰበ ያሰበው ሁሉ አይሟላለትም፣ የጀመረውን ሁሉ አይፈጽምም፤ የተመኘውን ሁሉ አያገኝም። ምክንያቱም ፍላጎቱ ገደብ የለሽ ሆኖ የተፈጠረው የሰው ልጅ ፍላጎቱን ለማከናወን ያለው ዐቅም ውሱን ስለ ሆነ ነው። ይህም ሆኖ ለመኖር መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች መሟላት አለባቸው። ከእነዚህ መካከል ፍቅር፣ የእርስ በእርስ መተሳሰብ፣ የተቸገሩትን መርዳት ተጠቃሾች ናቸው። ስለዚህ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቅር ኑሩ” በማለት የተናገረው ለሰው ልጅ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ስለሆነ ነው።
በመሠረቱ ወንድምነት በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። ከሥነ ፍጥረት አንጻር ከተመለከትነው ምንም እንኳን ብዙዎቻችን በዚህ መልኩ ባንረዳውም ሁሉም የአዳምና የሔዋን ልጅ ስለሆነ ሁላችንም ወንድማማቾች ነን። ከምናመልከው አምላክና ከምንከተለው ክርስትና አንጻር ስንመለከተው ደግሞ በክርስቶስ ስም ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በአርባና በሰማንያ ቀን ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ሲቀበል የቤተ ክርስተያን አባል የክርስቶስ አካል ሲሆን ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ተወልዶ ሁሉም የሥላሴ ልጅ ይሆናል። ስለዚህ በዚም በኩል ሁላችንም ወንድማማቾች ነን። ይህን በአግባቡ መረዳት ባንችልም እንኳ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ኑሮ የሚያስፈልገውና ብቻውን ምሉእ እንዳልሆነ ሊገነዘበው ይገባል።
- Details
- Written by: በመዝሙርና ሥነ ጥበባት አገልግሎት ማስተባበሪያ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2293
“አብዬ…”
“አንተ…” ትለኛለች።
አያቴ ናት። የቤቱ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብየ ከራሴ ጋር ብይ እየተጫወትኩ ነበር። ቅዳሜ ከቀኑ አሥር ሰዓት ገደማ ይሆናል። ከቤት ውስጥ መስኮቱ ባለበት ግድግዳ በኩል የተሠራ መደብ ላይ ተኝታ ነው ምትጠራኝ። የመጀመሪያውን ጥሪዋንም ሰምቸዋለሁ… ለምን እንደሆነ አላውቅም ብዙ ጊዜ በሁለተኛው ጥሪ ነው መልስ የምሰጠው። የጠራኝ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ተጣርቶ ካቆመ በቃ እኔም እየሰማሁት ሳልመልስ እሱም ሳይደግም እንለያያለን። ለዚህ ነው አያቴ ስትጠራኝ መጀመሪያ ስሜን አቆላምጣ ትጠራኝና እንደሰማሁ ስለገባት በሁለተኛው “አንተ..” ትለኛለች። ለምን እንደዚህ እንደማደርግ ለኔም አይገባኝም።
“ኧ ኧ ኧ…” የተለመደ መልሴ ነው። አቤት የምለው ለማላውቀው ሰው ነው። ለምን? እንደሆነ እኔ እንጃ!
“ነገ ጠዋት በተስኪያን ህደህ የቅዳሴ ጸበል እንድታመጣልኝ እኔ አሞኛል እግሬ እሽ አይለኝም።” አለች።
“እሽ።” አልኩ። ቀዝቀዝ አድርጌ ህጄ ብይ ማንከባለሉን ሳላቆም።
- Details
- Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1223
በዓለም ላይ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት አብዛኞቹ ምእመኖቻቸው ዐቢይ ጾምን እንዲጾሙ ያዛሉ። በተለይ የምሥራቅና የኦሪየንታል ኦርቶዶክሶች በጉጉት ከሚጠብቋቸው ጊዜያት አንዱ ይህ ወቅት ነው። የሶሪያ አብያተ ክርስቲያናት ይህን ታላቁን ጾም ‹‹Sawma Rabba›› ይሉታል - ጾመ ረቢ - ጾመ ኢየሱስ እንደ ማለት ነው። ጾሙን የሚቀበሉት ከበዓለ ትንሣኤው ከአምሳ ቀናት በፊት ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዐቢይ ጾም ሥርዓት ሳምንታቱ የየራሳቸው ስያሜ እንዳላቸው ኹሉ በሶሪያውያንና በሌሎችም የምሥራቅና የኦሪየንታል ኦርቶዶክሶች ዘንድ ስያሜያቸው የሚታወቁ ዕለታት አሉ። ከእነዚህም አንዱ ‹‹ንጹሕ ሰኞ›› (Clean Monday) ነው። ‹‹ንጹሕ ሰኞ›› የሚሉት ዐቢይ ጾምን የሚጀምሩበት ዕለተ ሰኞን ነው። እንደሚታወቀው የጾሙ የመጀመሪያ ዕለት ሰኞ ሲሆን፡ ጾም ከብዙ ኃጢአት የምንታቀብበት፣ በንስሐ ሳሙና
የምንታጠብበትና የንጽሕና ምግባራትን የምንፈጽምበት በመሆኑ፡ ይህን ያመለክት ዘንድ የመጀመሪያውን የጾሙን መግቢያ ዕለት ንጹሕ ሰኞ ብለውታል።
በሶሪያ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት የዐቢይ ጾምን ስድስተኛ ዓርብ ‹‹የአልዓዛር ዓርብ›› ይሏታል። ሰባተኛዋን ሰንበት ደግሞ ‹‹ሰንበተ ኦሻና›› (የሆሣዕና ሰንበት) ብለው ይጠሯታል። ምሴተ ሐሙስ፣ የስቅለቱ ዓርብና ቀዳም ስዑርም ከበዓለ ትንሣኤ በፊት የሚታሰቡ ዕለታት ናቸው። (የተጠቀምናቸው ምንጮች ሌሎቹ ዓርቦችና ሰንበታት ስያሜ ይኑራቸው፣ አይኑራቸው አይገልጹም)።
አንዳንዶች የምዕራባውያኑ አጠራር ተጽዕኖ አድርጎባቸው ‹‹ንጹሕ ሰኞ››ን፡ ‹‹የአመድ ሰኞ›› (Ash Monday) ብለው ይጠሩታል።
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 888
የጌታችን ዐበይት በዓላት የቤተ ክርስቲያናችን ዐበይት በዓላት ናቸው፡፡ ሌሎች የቅዱሳን ጻድቃንና የቅዱሳን መላእክት በዓላት ትርጕም ኖሯቸው ሊከበሩ የቻሉት በጌታችን በዓላት የሚታሰቡ ምሥጢራት በመኖራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የቅዱሳን በዓለ ልደት እንደ በዓል የሚከበረው ጌታችን በልደቱ ልደተ ሰብእን በመቀደሱ ነው፡፡ ሰማዕታት የተሠዉበት ቀንም ልዩ ተደርጎ የሚከበረው ጌታችን በሞቱ ሞታቸውን ስለ ቀደሰው ነው፡፡ እርሱ ተወልዶ ልደታችንን ባይቀድስልን የቅዱሳን ልደት የሚያስደስት፣ ሞቶም ሞታችን ዕረፍት እንዲሆን ባይባርክልን የሰማዕታት መሠዋትም ከንቱ በሆነ ነበር፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን የጌታ በዓላት በልዩ ትኩረትና ድምቀት ይከበራሉ፡፡
ከጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል ደግሞ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ስቅለቱና ትንሣኤው፣ ዕርገቱ፣ ዳግም ምጽአቱ፣ ወዘተ. በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ከሌሎችም ይልቅ እጅግ ደምቀው የሚከበሩ በዓላት ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በዓለ ጥምቀት ታቦተ ሕጉ ከመንበሩ ወጥቶ በተለየ ሁኔታ በዐደባባይ የሚከበር በዓል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ የበዓሉ ባሕርይ ከሌሎች በዓላት ይልቅ ብዙ የኅብረተሰብ አካላት የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚጋብዝና፡ ብዙዎችን በአከባበሩ ለማካተትም የተመቸ ነው፡፡
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1582
ይህ ዓለም ድካም፣ ውጣ ውረድ፣ ጊዜያዊ ሀብት፣ ወዘተ የበዛበት ኃላፊ ዓለም ነው። ይህ ዓለም ምንም ኃላፊ፣ ጠፊ ቢሆንም የማይታየውንና የማያልፈውን ሰማያዊውን ዓለም ተስፋ አድርገን ወደ ዘለዓለማዊው ሕይወት የሚያስገባን ሥራ እየሠራን የምንኖርበት ዓለም ነው። ይህ ዓለም ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ “ዓለሙ ያልፋል፤ ምኞቱም ያልፋል” (፩ዮሐ. ፪፥፲፯) በማለት እንደገለጸልን የሚያልፍ የሚጠፋ እንጂ ለዘለዓለም የምንኖርበት ቦታ አይደለም።
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የእመቤታችንን ዕረፍት በአዘከረበት ድጓው “ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ፤ ወአግዐዛ እምእኵይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ ወረሰየ ይዝክሩ ስማ ውስተ ኵሉ ምድር፤ ለዚች ሴት የአብ ብዕለ ጸጋው በእርሷ ላይ ወጣ፤ ከክፉ ወደ መልካም፣ ከሞት ወደ ሕይወት ነጻ አወጣት ወይም ወሰዳት፤ በምድር ሁሉ ስሟን ይጠሩ ዘንድም አደረገ ” በማለት አስረዳን። በዚህ ምንባብ ሊቁ ሊነግረን የፈለገው በእናታችን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የአብ ጸጋው እንዳደረባት፣ ከክፉ ወደ መልካም፣ ከሞት ወደ ሕይወት እንዳሸጋገራት፣ እንዲሁም በምድር ሁሉ ሰዎች ስሟን ሲዘክሩ እንደሚኖሩ ነው። ዘርዘር ያለውን ጉዳይ እንደሚከተለው እንመለከታለን።
- Details
- Written by: ዲ/ን ተስፋዬ ምትኩ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1616
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን ባመሰገነበት በዕለተ ሰኑይ ውዳሴ ማርያም ላይ በወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ፍጥረታት በሙሉ ደስ እንዳላቸው ይናገራል፡፡ እንደሚታወቀው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ በተለየ አካሉ ከሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ደንግል ማርያም ሥጋና ነፍስ ነሥቶ ፍጹም ሰው የሆነው የሰው ልጆችን ለማዳን ነው፡፡ በዚህ ደስ ሊለን የሚገባን እኛ የሰው ልጆች ነን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ግን ፍጥረት ሁሉ ደስ አለው ብሎናል፡፡ ለመሆኑ ፍጥረታት የተባሉት እነ ማን ናቸው፤ ለምንስ ደስ አላቸው ብለን ስንጠይቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፍጥረታት የተባሉት መላእክት፣ እንስሳትና አራዊት፣እንዲሁም ደቂቀ አዳም ናቸው። ብለው በሦስት ከፍለው አስቀምጠውልናል፡፡
ሀ. መላእክት፡-
መላእክት የሚለው ስም ግብራቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ቃሉ የግእዝ ሲሆን በግሪክ አንጌሎስ (Angelos)፣ በዕብራይስጡ ደግሞ መለክ፣ “Mal’ak” ከሚሉት ቃላት የአቻነት ትርጕም ያለው ነው፡፡ የተላከ (messenger) የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ በግእዙም መላእክት የሚለው ቃል፡- ለአከ፣ ተልእከ፣ ላከ፣ ተላከ ልኡክ ከሚሉ ግሶች የሚገኝ ሲሆን መላላክን፣ ማገልገልን፣ መልእከተኛ መሆንን ያመለክታል፡፡ ( ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ፲፱፻፵፰ ዓ.ም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፭፻፶፬)
- Details
- Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1538
ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ
ከላይ ካነሣናቸው ጋር በሚመሳሰል መልኩ በጎፋ ዞን በመሎ ኮዛ ወረዳ የተከሰተው ክስተትም ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጫናና በደል ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
በወረዳው የሚገኘው የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ይዞታው ከ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፡ እስከ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ድረስ ቦታው የሚገኝባት ከተማ በገጠር ከተማነት ቆይታ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. በማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ሥር የሆነች ናት፡፡
ታዲያ በዚሁ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. የከተማዋ አስተዳደር ወደ ማዘጋጃነት ሲቀየር የሃይማኖት ተቋማት ይዞታ ‹‹ባለበት ይቀጥላል›› ተብሎ ነበር፡፡ ከዓመታት ቆይታ በኋላ በ፳፻፲፪ ዓ.ም. ባለ ሥልጣናቱ ሁለተኛ ዙር ጥናት በማለት፡ የቀድሞውን ውሳኔ ችላ ብለው የቤተ ክርስቲያንን የጥምቀት ይዞታ ነጠቁ፡፡
Read more: የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችና ሌሎች ይዞታዎቿ ወቅታዊ ፈተናዎች ክፍል ሁለት