- Details
- Written by: ዲ/ን ደረጄ ጋረደው
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1888
መግቢያ
በቅዱስ መጽሐፍ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በኤዶም ገነት አኖረው” (ዘፍ.፪፥፲፭) ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ቦታን ይቀድሳል። በአንጻሩም ሰዎች በቦታ ይቀደሳሉ። ይልቁንም የቅዱሳን የጸሎት በዓታቸው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያለበት፣ የቅዱሳኑ አጽማቸው የረገፈበት ስለሆነ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን ያድለናል። ይህንም መሠረት በማድረግ የጮቢ መካነ ሕይወት በዓታ ለማርያም የአንድነት ገዳም ከምሥረታ አስከ አሁን ያለውን ታሪክ ለአንባብያን ልናስተዋውቃችሁ ጀመርን መልካም ንባብ፡፡
፩. የገዳሙ መገኛ ቦታ፡-
መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የሚገኘው በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዱግዳ ቦራ ወረዳ ሀርቦ አቡኖ ቁሙሮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ እስከ ኬላ ከተማ ድረስ ፻፲፫ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን፤ ከኬላ ከተማ ገዳሙ ድረስ ደግሞ ያለው ጥርጊያ መንገድ ፲፭ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡
"ጮቢ" ማለት በኦሮሚኛ በረከት ማለት ሲሆን፤ የገዳሙ አካባቢ ደግሞ አቡኖ በመባል የሚጠራ ነው፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘበት ምክንያት በጥንት ጊዜ ቦታው ላይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያረፉበት በመሆኑ እንደሆነ የገዳሙ አባቶች ያስረዳሉ፡፡
ከገዳሙ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በተራራ የተከበበ እና የተለያዩ ዕፅዋቶች የሚገኙበት ሲሆን፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ያለበት ሜዳ እና ገደላማ ነው፡፡ በገዳሙ አካባቢ የሚኖሩ ምዕመናን የሶዶ ጉራጌ ሲሆኑ፤ መለያ ስማቸው ግን ሶዶ ክስታኔ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኙት በጣሊያን ጊዜ በመስቃን ጦርነት ከአርሲ ሙስሊሞች ጋር ተዋግተው ብዙዎች ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜም ሃይማኖታቸውን ሳይቀይሩ ፀንተው የቆዩ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ነው፡፡
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1922
፭. ሐመር፡- ‹‹ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ›› ስንል ከላይም እንደ ተገለጸው ልዑለ ባሕርይ መለኮት ትሑቱን ሥጋ ገንዘብ አደረገ ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ “ሁሉ ተካክሎ በደለ አንድ ስንኳን በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም” (መዝ.፲፫፥፫ ፤ መዝ.፶፪፥፫) እንዳለ አንድም ንጹሕ ሰው አልነበረም። ስለዚህ ‹አምላክ የተዋሐደው ሥጋ ጥንተ አብሶ ነበረበት› አያስብልም ወይ?
መምህር ሥሙር፡- እዚህ ላይ መጠንቀቅ የሚያስፈልገው ነገር “ሁሉ” የሚለው ቃል አንጻራዊ ነው። ለምሳሌ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰) ብላ ስትናገር አንጻራዊ በሆነ አገላለጽ እንጂ የማያምን እንዳለ የታወቀ ነው። ሁሉ የሚለው ቃል አማኞችን ብቻ የሚመለከት ነው። ስለዚህ ይህ ዳዊት የተናገረው ቃል በተነገረበት ዘመንና ከተነገረበት ዘመን በፊትም የነበረውን ብንመለከት ሁሉም አልበደሉም። ለምሳሌ፡-
በብሉይ ኪዳን ጽድቅ የመርገም ጨርቅ ቢሆንም እጅግ በርካታ ደጋግና ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሰዎች እንደ ነበሩ መዘንጋት የለብንም። በዘፍ.፬ ስለ አቤል ጽድቅ ተጽፎ እናገኛለን። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ሄኖክ እንደ ተሰወረ እናገኛለን። ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት “አብርሃምም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” (ዘፍ.፲፭፥፮)ተብሏል። እንደ አብርሃም ያሉ ጻድቃን እንደ ይስሐቅ ያሉ ታዛዦች፣ እንደ ያዕቆብ ያሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ። ይህ ሁሉ የነበረው በ፶፻፭፻ ዘመን ውስጥ ነው። በመሆኑም ሁሉ በደለ ከተባለ በሕገ ልቡናም ሆነ በሕገ ኦሪት ብዙ ደጋግ ሰዎች ነበሩና ከመሆናቸው ጋር ይጋጫል። ስለዚህ ሁሉም የሚለው ቃል በደለኞችን ብቻ እንጂ ያልበደሉትን አይጨምርም።
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2717
ጋብቻ የራሱ የሆነ ዝግጅት አለው። ይህ ዝግጅት ደግሞ ሰርግ ይባላል፡፡ ‹‹ሰርግ›› የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹ሰረገ፣ ደገሰ፣ ሰርግ አደረገ፣ የሰርጉን ቤት ሸለመ፣ አስጌጠ፣ አንቆጠቆጠ” በማለት ሲገልጹት አያይዘውም “ሰርግ በቁሙ፣ ከብካብ፣ መርዓ፣ የጋብቻ በዓል ድግስ፣ የሚያጌጡበት፣ የሚሸለሙበት፡፡›› በማለት ያብራሩታል። (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ ፰፻፹፬) ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ከሣቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በተሰኘ መጽሐፋቸው ‹‹አካለ መጠን ያደረሰ ወንድ ልጅና አካለ መጠን ያደረሰች ሴት ልጅ ባልና ሚስት ሊሆኑ የሚጋቡበት ቀንና ተጋብተውም የዚህን ዓለም ኑሮ የሚጀምሩበት የሰርግ ቀን›› (ገጽ ፪፻፴፱) በማለት ይገልጹታል። ከሁለቱም ምሁራን አገላለጽ እንደምንረዳው ሰርግ የዕለት ክንውን ሲሆን ጋብቻውን ምክንያት አድርጎ የሚደገሰውን ድግስ የሚለበሰውን ልብስ፣ የሚታየውን ጌጣጌጥ የሚያካትት የማስተዋወቂያ ዝግጅት ነው፡፡ ማለትም ሰዎች ከብቸኝነት ሕይወት ወደ ጥንድነት የሚሸጋገሩበት ዝግጅት ነው፡፡ ይህ ዝግጅት የሁለቱ አንድነት የሚታወጅበት በሁለታችንም ፍላጎት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለዚህ በቅተናልና የደስታችን ተካፋይ ሁኑ በማለት ሙሽሮች በሚያስተላልፉት ጥሪ መሠረት ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ የሁለቱ ተዋሕዶ የሚታወጅበት ወይም አዋጁ የሚጸድቅበት ልዩ የዝግጅት ጊዜ ነው፡፡
Read more: ኢየሱስ ወደ ሰርግ ቤት ተጠራ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሄደ። (ቅዱስ ያሬድ፣ ድጓ ዘቃና ዘገሊላ)
- Details
- Written by: በመዝሙርና ሥነ ጥበባት አገልግሎት ማስተባበሪ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1950
ሥራዬን አልወደውም፡፡ ፈጣሪ ሆን ብሎ የፈረደብኝ ይመስለኛል፡፡ ሥራዬን ብተወው ደግሞ እቸገራለሁ፤ ይርበኛል፡፡ እንዳልተወው ችግሩ እያስጨነቀኝ እንዳልቀጥል ደግሞ ጠልቼው ሁል ጊዜም እየተማረርኩ ወደ ሥራ ሄዳለሁ፡፡ እሠራለሁ እሠራለሁ…. ወገቤን … ወይኔ ሲያደክም ደሞ… የሆነ ችክ ያለ ሥራ ነው፡፡ እዚያ አንገቴን ደፍቼ ስቆፍር ስቆፍር እውልና… ፌቴን አጨፍግጌ ሲመሽ ወደ ቤቴ እያዘገምሁ እሄዳለሁ፡፡ መንገድ ላይ ሰው አያወራኝም፡፡ ልብሴ አቧራ ስለሆነ ይሁን… ፊቴ ስለተከሰከሰ… እኔ እንጃ ብቻ…ለነገሩ እኔም ቢያወሩኝ የምመልስላቸው አይመስለኝም፡፡ ደህናና ረዘም ያለ ወሬ ካወራሁ ረጅም ጊዜ ሆኖኛል ፡፡
ወደ ቤቴ ስሔድ እግሬ ለምዶበት ራት ወደምበላበት ቤት ይወስደኛል ገብቼ እንደተቀመጥሁ ከአፍታ በኋላ የተለመደችው ልጅ የተለመደውን ምግብ ታመጣልኛለች፡፡ የምበላውን ስለምታውቅ ሳልነግራት ነው የምታመጣልኝ… ለትዕዛዝ እንኳን አላወራም፡፡ እጄን በውኃ አርስና ቆረስ አድርጌ ወደ አፌ ሳስጠጋ ከንፈሬ ይላቀቃል… በቀስታ እበላለሁ፡፡ አላምጨ ስውጥ ራሱ ሔዶ ሆዴ ውስጥ ሲቀመጥ ድምፁ የሚሰማኝ ይመስለኛል፡፡
- Details
- Written by: ዳዊት ደስታ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 3837
ሰላም ምንድን ነው?
ሰላም በስምምነትና በአንድነት አብሮ መኖር ማለት ነው፡፡ የሰው ልጆች በምንኖረው ሕይወት ውስጥ እጅጉን ከሚያስፈልገን ነገር ዋነኛው ሰላም ነው፡፡ ፍጥረታት እንዲኖሩ የሚያስፈልገው በሰላም ነው ያለ ሰላም ልንኖር አንችልም፡፡ ሰላም ማለት ‹‹ፍጹም፣ ጤና፣ ዕረፍት፣ ዕርቅ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ደኅንነት፣ ተድላ፣ ደስታ፣ ሰላምታ፣ የቡራኬ የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝ ሲለያይ የሚለው የሚናገረው ወይም የሚጽፈው›› በማለት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የሰላምን ፍቺ በእንዲህ መልኩ ገልጸውታል፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፰፻፷፰)
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ‹‹የሰላም ግንባታ ማሠልጠኛ›› በተሰኘው ጥናታዊ መድበሉ ስለ ሰላም ምንነት እንደሚከተለው አብራርቷል፡፡ ‹‹ሰላም የሚለው የአማርኛ ቃል የተሸከመው ፅንሰ ሐሳብ ከጦርነትና ከዐመፅ ነፃ መሆን›› ከሚለው የአንዳንድ መዛግብት ቃላት ሰፋ ያለ ትርጉም ይዟል፡፡ ‹‹ሰላም›› ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታና ውድ ጸጋ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔር ሰላም ነው›› (መሳ. ፮፥፳፬) በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል፡፡
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1347
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር አንድነት፣ ሰላም፣ እድገትና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እጅግ ብዙ አስተዋጽዖ ማድረጓን ሁሉም የሚያውቀው እውነታ ነው። ሆኖም ባደረገችው አስተዋጽዖና በዋለችው ውለታ ልክ መከበርና መጠቀም ሲገባት በብዙ ጉዳዮች ገለል ተደርጋ፣ በአንዳንድ ቦታዎችም ስትገፋ ማየቱ በተለይም ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት እየተለመደ መጥቷል። ይህ ሊሆን የቻለውም በአብዛኛው በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ በታየው መጠንን ያለፈ ትዕግሥትና ቸልተኝነት እንዲሁም በዋናነት የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እየበረከቱ በመምጣታቸው ነው።
የዐደባባይ በዓላትን በምሳሌነት ብንወስድ፡ በገቢ ረገድ ከቤተ ክርስቲያን በላይ ተጠቃሚው መንግሥት ነው። ነገር ግን የተጠቃሚነቱን ያክል ለቤተ ክርስቲያን ሀብቶችና ለበዓሉ ድምቀት ቤተ ክርስቲያንን አግዞ ሲሠራ አይታይም። በዚህም ምክንያት ለብዙ ዐሥርት ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች የነበሩ የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች እኩይ ዓላማን ባነገቡ ሰዎች ተጽዕኖ ተነጥቀዋል፤ ምእመናን ተንገላተዋል። አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ይዞታዎችም የይዞታ ማረጋገጫ ያልተሰጠባቸውና በቀጣይ ጊዜያት ተመሳሳይ ፈተና የሚጠብቃቸው ናቸው።
የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ማክበሪያ ይዞታዎችም ብቻ ሳይሆን ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችም ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ናቸው። ለአብነትም ለቤተ እምነት በሚሰጡ ቦታዎች ፍትሐዊነት ላይ መንግሥት ቆም ብሎ ሊያስብባቸውና ብዙ ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ ሊያስተውል ይገባል።
ይህ ሲባል ግን ብዙዎቹ የይዞታ ችግሮች በመንግሥት ቸልተኝነት ብቻ የተፈጠሩ ችግሮች እንዳልሆኑ በእኛ በኩልም ይህን መገንዘብ ይኖርብናል። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን አካላትም አለመቀናጀትና ዝርው አካሄድ የተነሣ የተፈጠሩ መሆናቸውንም ማስተዋል ተገቢ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ በየትኛው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር መመለስ እንደሚገባው ግልጽ አይደለም። የትኛው ኃላፊነት የየትኛው መምሪያ ድርሻ መሆኑን ለመግለጽም ያስቸግራል። ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ጉዳይ ለማቀድም ሆነ የክንውን ዘገባ ለማቅረብ ስለማይቻል ባይሠራ እንኳን ተወቃሽ አካል እንዳይኖረው ያደርጋል። ስለሆነም ይህንን የአሠራር ክፍተት የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር በተቻለ ፍጥነት ማስተካከል ይኖርበታል ብለን እናምናለን።
እዚህ ላይ፡ የአንዳንድ አባቶች፣ ምእመናን፣ ወጣት አገልጋዮችና ማኅበራት እንቅስቃሴ ምስጋና የሚያሻው ነው። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ‹ያገባኛል› በሚል መንፈስ ብዙ ርቀት ተጉዘው ጥቂቶቹን ይዞታዎችም ቢሆን አስመልሰዋል። ለወደፊቱም ቢሆን ለቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴና ኅብረት እጅግ አስፈላጊ ነው።
በየአካባቢው ያሉ የቤተ ክርስቲያን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ይዞታዎች ‹የእኛ ናቸው› ብሎ ዓመቱን ሙሉ ሊከታተላቸው የሚገባ አካል ሊመደብላቸው ያስፈልጋል። አንድ ጊዜ ብቅ ብሎ በዓላቱን ካከበሩ በኋላ ጉዳዩን ርግፍ አድርጎ በመተው እንደገና በዓመቱ ሲመጣ ተሰብስቦ መጯጯሁ ትርፉ ጩኸት ብቻ ነው። ሌሎች አካላትንም ‹ውሰዱልኝ› እንደ ማለት ይቆጠራል። ስለዚህ በዓሉን በአንድነት የሚያከብሩ ተጎራባች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቦታውን በአንድ መዋቅራዊ አሠራር የሚያስከብሩበትና የሚያለሙበት መንገድ ሊቀየስ ይገባል።
በአሁኑ ወቅት በክርስትና ሃይማኖታችን በታላቅ ጉጉት ከሚጠበቁ ዐበይት በዓላት ዋዜማ ላይ እንገኛለን። እነዚህም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደትና ጥምቀት ናቸው። ሁለቱም በዓላት የየራሳቸው ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ የአከባበር ዘዬ ያላቸው ሲሆን፡ በምእመናንም ዘንድ በእጅጉ የሚናፈቁ ናቸው።
በዓለ ልደትን ለማክበር እንደ ሃይማኖታችን ሥርዓት ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ ያለውን ወቅት ሁሉም አማኝ በጾም ማሳለፍ እንደሚገባው የታወቀ ነው። ከጾሙ ባለፈም ምእመናን የብርሃነ ልደቱን ደስታ ለመሳተፍ በተለያዩ መንገዶች ይዘጋጃሉ። ከእነዚህም አንዱ ነዳያንንና ዐቅመ ደካሞችን ለማስፈሰክ የሚደረግ ዝግጅት ነው። በተለይ በሰንበት ትምህርት ቤቶች አስተባባሪነት በጌታችን ልደትና ትንሣኤ በዓላት እየተጠናከረ የመጣው ይህ መልካም ሥራ ዘንድሮም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለ ጥምቀትን ካለ ወጣቶች ተሳትፎ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ማሰብ አስቸጋሪ ሆኗል። በየሠፈሩ የሚታየው ይህ የወጣቶች መነቃቃት እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው፤ ይህን መነቃቃት ያዩ ጥቂት አጥቢያዎችና ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ወጣቶችን ዐቅፎ በማስተማር በዓመት አንዴ ከመምጣት ዘወትር ወደ ማገልገል እንዲያድጉ አስችለዋል። ይህ መልካም ልምድ በሁሉም ቦታ ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው።
ከዚህ ባለፈም ከወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ አንጻር የበዓላቱን ፀጥታ ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሊኖሩ ይችላሉና ገና ካሁኑ ከመንግሥት አካላት ጋር በተለይም ከፖሊስ ጋር በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል።
በመጨረሻም በእነዚህ የዐደባባይ በዓላት መንፈሳዊ ይዘት ላይ እጅግ ሊተኮር ይገባል። በዓላቱ ከመንፈሳዊ ይዘትነታቸው ባለፈ በተለይ በተተኪው ትውልድ እንደ አንድ ዓለማዊ ‹ፌስቲቫል› እየታዩ መምጣታቸው እጅግ አስጊ ነው። በዓላቱ በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ለሀገር ጠቃሚ ሆኖ ሳለ፡ ሚዲያዎች ሁሉ የበዓላቱን መንፈሳዊ እሴት በመዘንጋት ከቅርስነትና ከማኅበራዊ ፋይዳዎቻቸው አንጻር ብቻ መዘገባቸው እጅግ አሳሳቢና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነውና ሊታሰብበት ይገባል እንላለን።
- Details
- Written by: መ/ር ግሩም ወ/መድኅን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 3003
በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ ኦ እግዝእትየ ማርያም ሰላም ለኪ፤ እመቤቴ ሆይ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ።
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳታቋርጥ በምትጸልየው የዘወትር ጸሎት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ካስተማረው አቡነ ዘበሰማያት ቀጥሎ የሚጸለይ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ያቀረበው የምስጋናና የሰላምታ ጸሎት ነው። ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ የአንድነት የሦስትነት ምስጋና ካቀረበች በኋላ ለእመቤታችንም ምስጋና ታቀርባለች ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ - ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድም ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል›› ብላ ካመሰገነች በኋላ ‹‹ስብሐት ለእግዝትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፤ አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና ይገባል›› በማለት ታመሰግናለች።
በስግደትም እንዲሁ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ የአንድነት የሦስትነት የባሕርይ የአምላክነት ስግደት በኋላ ለእመቤታችንም የባለሟልነት፣ የመወደድና የእናትነት ስግደት ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐተ ስግደተ እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት፤ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ለሚሆን አምላክ እሰግዳለሁ።›› በማለት አንድነት ሦስትነትን የሚመሰክረው ኃይለ ቃል ከተነገረ በኋላ፡- ‹‹እሰግድ ለእዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ - አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምም እሰግዳለሁ›› በማለት እንደተገለጸው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በተግባር ትገልጠዋለች።
ለእመቤታችን የምንሰግድበት ምክንያት መስተብቁዕ ዘመስቀል በተባለው የቤተ ክርስቲያን የጸሎት ክፍል ‹‹ለማርያምሰ ዘንሰግድ ላቲ እስመ ነሥአ ሥጋ እምሥጋሃ እግዚአብሔር ፈጣሪሃ ወረከብነ ንሕነ መድኀኒት እምኔሃ - ለማርያምስ የምንሰግድላት እግዚአብሔር ፈጣሪዋ ከእርሷ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ስለነሳ ከእርሷም መድኀኒትን ስላገኘን ነው›› በማለት ይገልጻል። ወደ ጥንተ ነገራችን (የገብርኤል ሰላምታ) እንመለስ ቅዱስ ሉቃስ ይህንን ሲዘግብ ከላኪው ከተላኪው ከተላከበት ቦታ የተላከላትንም በማስረዳት ነው። የተላከበትን ጊዜ ሲገልጽ ‹‹ወበሳድስ ወርኅ ተፈነወ ገብርኤል መልአክ እምኀበ እግዚአብሔር፤ በስድሰተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተላከ›› (ሉቃ.፩፥፳፮) እንዲል። ስድስተኛ ወር የተባለው ቅዱስ ገብርኤል ለዘካርያስ ኤልሳቤጥ እንደምትፀንስ፣ ዮሐንስ እንደሚፀነስ በመሠዊያው አጠገብ ተገልጾ ባናገረበት በስድስተኛው ወር ሲል ነው። ወይም በአዳም በደል ምክንያት ዓለም በድቅድቅ ጨለማ በኖረበት ለአዳም ተስፋ በተሰጠበት የሰው ልጅ የኀጢአትና የዲያብሎስ ባርያ በሆነበት በስድስተኛው ሺህ ቅዱስ ገብርኤል መልእክተኛ ሆኖ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ አንዲት ድንግል ተላከ ማለት ነው።
ይህንን ጽንሰ ሐሳብ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹ወሶበ ርእየ ንጽሕናኪ ለሊሁ እግዚአብሔር አብ ፈነወ ኀቤኪ መልአኮ ብርሃናዌ ዘስሙ ገብርኤል፤ እርሱ ቅሉ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የተባለ ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንቺ ላከ›› (ቅዳሴ ማርያም) በማለት የተናገረውን መተርጕማኑ ደግሞ “ተርታ መልአክ ያይደለ ባለሟሉን፣ ያልታወቀውን ያይደለ የታወቀውን፣ መልአከ ጽልመት ያይደለ ብርሃናዊውን መልአክ ወደ አንቺ ሰደደው” በማለት አብራርተውታል።
ድንግልን እንዲያበሥር የተላከው ቅዱስ ገብርኤል መልአክ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲገልጽ ‹‹ሶበ ተወልደ እምድንግል ዐቀበ ድንግልናሃ እንበለ ሙስና እስመ ቀዳሚ ሔዋን ኮነት ድንግለ ወአስሐታ ዲያብሎስ ለማርያም ድንግል አብሠራ ገብርኤል፤ ከድንግል በተወለደ ጊዜ ድንግልናዋን ባለመለወጥ አጸናው ቀድሞ ሔዋን ድንግል ነበረችና ዲያብሎስ አሳታት እንጂ ድንግል ማርያምን ግን ገብርኤል አበሠራት›› (ሃ.አ.ዮ.አፈ. ምዕ.፷፯ ክፍ ፲፩፥፫፤ ዘፍ. ፫፥፩-፪፤ ሉቃ. ፩፥፳፮) ሔዋን የዲያብሎስን ቃል ሰምታ መቀበሏ እና ድንግል ማርያም ደግሞ የመልአኩን ቃል ሰምታ መቀበሏ ያመጣውንም ውጤት ሲገልጥ እንዲህ ይላል ‹‹ወባሕቱ ለሔዋንሰ አስሐታ ዲያብሎስ ወወለደት ቃየልሃ ዘውእቱ ምክንያተ ሞት ወማርያምሰ ሶበ አብሠራ መልአክ ወለደት ቃለ በሥጋ ዘውእቱ መራሔ ኵሉ ኀበ ሕይወት ዘለዓለም፤ ነገር ግን ሔዋንን ዲያብሎስ አሳታት የሞት ምክንያት የሚሆን ቃየልን ወለደች ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች›› (ሃ.አ.ዮ.አፈ. ምዕ.፷፯ ክፍ ፲፩፥፬)
ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ ንጽሕት፣ ቅድስትና ብፅዕት ወደ ሆነችው ድንግል ማርያም የያዘውን መልእክት ያመጣ ዘንድ በአምሳለ ብእሲ ተገለጠ፤ እሳታዊው መልአክ ከእግዚአብሔር ተላከ፤ የተሠወረ ምሥጢር ይዞ ከእግዚአብሔር የተላከው መንፈሳዊው መልአክ ከሰማይ ሠራዊት መካከል መጣ። እርሱም ብላቴናይቱን አግኝቶ ሰላምታ ሰጣት በላይ በሰማይ በሚኖረው በእግዚአብሔር እንደታዘዘው ምሥጢሩን ገለጠው።
የንጉሡ እናት በሆነችው በድንግል ፊት ጎንበስ ብሎ ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ሊገባትና ልትቀበለው በምትችል ንግግር አነጋገራት። በመለኮታዊ ጸጋ ውበት የተመላሽ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን፤ የጽድቅ ፀሐይ እናት የሆንሽ ማርያም ሆይ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ የተቀደሱ ነገሮች መናገሻ የሆንሽና በበጎነት የተመላሽ ሆይ ሰላም ባንቺ ላይ ይሁን፤ የምሥጢራት መሸሸጊያ በከበረ ጸጋ የተመላሽ መርከብ ነሽ፤ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሸ የተባረክሽ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን፤ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ። እያለ የምስጋና ነጠብጣብን በፊቷ ያወርድ ጀመረ። ይህንን የመልአኩን ድንቅ የሰላምታ ቃል ወንጌላዊው ‹‹በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባለው ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር መልአኩም ወደ እርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ካንቺ ጋር ነው ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት›› (ሉቃ. ፩፥፳፮-፳፱) በማለት ይገልጻል።
መልአኩ የተላከው ከእግዚአብሔር ነው ‹‹ዘእግዚአብሔር ፈነዎ ይነግር ቃለ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል›› (ዮሐ.፫፥፴፬) ተብሎ እንደተጻፈ የሚናገረው የእግዚአብሔርን ነገር ነው መልአኩ ወደ እርሷ ገብቶ ከተናገረው ጀምሮ ያለውን ባጭሩ እንይ መልአኩ እመቤታችንን ያናገራትና ሰላምታ ያቀረበበት ሦስት ጊዜና ሦስት ቦታ ላይ ነው። እመቤታችን በቤተ ዮሴፍ ሳለች የዮሴፍን ልጆች ዘመድ ዘመድ ለማለት ባጭር ታጥቃ ውኃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ወርዳ ውኃ ቀድታ ስትመለስ መንገድ ላይ የመጀመሪያውን ድምፅ (ሰላምታ) ሰምታለች። ይህንንም ዘወር ብላ አንዳች እናቴን ሔዋንን ያሳትክ ሰይጣን ትሆን ብላ ትታው ሄደች። ሁለተኛው እንስራዋን ስታወርድ ከቤት ውስጥ ያንኑ ቃል ደገመላት። ይህ ነገር የመንፈስ ቅዱስ ይሁን ወይስ የሰይጣን ነገሩን ከቤተ መቅደስ (ከቤተ እግዚአብሔር) ሆኖ ሊረዱት ይገባል ብላ ሳትዘገይ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሄዳለች። ከደናግለ እስራኤል የተካፈለችውን ሐርና ወርቅ እያስማማች ስትፈትል መልአኩ ወደ እርሷ ገብቶ (ወደ እርሷ ባሕርይ ተመልሶ እየወደቀ እየተነሣ እየታጠቀ እየፈታ በአምሳለ ሰያብ አረጋዊ ሰውነቱ ክት አንደበቱ ነገር አያሳትት በሚባል ሽማግሌ ሰላምታ አቀረበላት። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ወእንዘ ትፈትል ወርቀ ወሜላተ አስተርአያ ገብርኤል ግብተ፤ ሐርና ወርቁን እያስማማች ስትፈትል ወደ እርሷ ገብቶ ታያት›› በማለት ገልጾታል የቦታ ነው ቢሉ እርሷ ወዳለችበት ቤት ገባ የመገለጥ ነው ቢሉ ባሕርይዋን መሰለላት፤ መስሎም ታያት ሲል ቦአ መልአክ ኀቤሃ አለ።
በሰላምታው አራት ድንቅ ድንቅ ነገሮችን አካቷል። እነርሱም፡-
- ተፈሥሒ ፍሥሕት
- ኦ ምልዕተ ጸጋ
- እግዚአብሔር ምስሌኪ
- ቡርክት አንቲ እምአንስት
እነዚህን የሰላምታ ቃላት እያንዳንዳቸውን እናያቸዋለን ከመልአኩ ለእመቤታችን የቀረቡ ወንጌላዊው በጥንቃቄ ያሰፈራቸው በዚህ መነሻነት ብዙ ሊቃውንት የተረጎሙአቸው የተነተኑአቸው ናቸው።
፩. ተፈሥሒ ፍሥሕት፤ ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ
የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር በመለየታቸው ደስታ ከራቃቸው አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናትን ቈጥረው ባሉበት ዘመን “ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ” በማለት ለድንግል ማርያም መልካም ዜናን ተናገረ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የእመቤታችንን ነገር በተናገረበት አንቀጹ በምዕራፍ ስልሳ ስምንት በክፍል ሃያ ስድስት ላይ እመቤታችንን ደስ ይበልሽ እያልን የምናመሰግንበትን ነገር እንዲህ ይገልጸዋል። ‹‹የጠፋ በግ አዳምን የፈለገው ባገኘውም ጊዜ የተሸከመው እውነተኛ ቸር ጠባቂ ካንቺ የተወለደ እመቤቴ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ›› እንዲል። ሊቁ ለእመቤታችን ከሚያቀርበው ሰላምታ በተጨማሪ ሰላምታውን የሚያቀርብላት ቅድስት ድንግል ማርያም የወለደችው ቸር ጠባቂ መሆኑንም ያስረዳናል። በቅዱስ ወንጌል ‹‹የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግ የሞተውን ሊያድን መጥቷል›› (ሉቃ. ፲፬፥፲) ፤ ‹‹እውነተኛ እረኛ እኔ ነኝ እውነተኛ እረኛ ራሱን ስለ በጎቹ ይሰጣል›› (ዮሐ. ፲፥፲፩) ተብሎ እንደተጻፈ ቅድስት ድንግል ማርያም የወለደችው እራሱን ለበጎቹ የሚሰጥ፣ እውነተኛና ቸር እረኛ ነው። ስለዚህ ይህን ቸር እረኛ የወለደች እናቱ ድንግል ማርያምን ደስ ይበልሽ እያልን እናመሰግናታለን።
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አያይዞም ‹‹እግዚአብሔር በሲኦል የጣላት የሔዋን ጽኑ ፍዳ ባንቺ የጠፋ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ›› በማለት ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ፤ በሔዋን ምክንያት የገነት በር ተዘጋብን በድንግል ማርያም ምክንያት ተከፈተልን›› (ውዳሴ ማርያም) ብሎ የገለጸውን ያጠነክርልናል። ገነት ሲዘጋ ሔዋንና ልጆቿ ሁሉ ወደ ሲኦል ተጥለዋል፤ በጽኑ ፍዳ ውስጥም ኖረዋል። ይህ ጽኑ ፍዳ የተወገደልን አምላክ ከእመቤታችን ሰው በመሆኑ ነውና ለእንዲህ ያለው ክብር ምክንያት የሆነች ድንግል ማርያምን ሊቃውንቱ ተባብረው ደስ ይበልሽ አሏት።
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምንሰግድለት ቃል ካንቺ ይወለድ ዘንድ ዓለም ሳይፈጠር የነበረ እግዚአብሔር አንቺን የወደደ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ። እኔ ሐዋርያ የሆንኩለት የጌታ እናቱ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ማኅተመ ድንግልናሽን ያለመለወጥ የጠበቀውን አማኑኤልን የወለድሽ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ። እያለ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ተከትሎ ያመሰግናታል፤ እኛም ደስ ይበልሽ እንላታለን። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የጀመረውን ሰላምታ መሠረት አድርገው ያመሰገኑት ሊቃውንት በርካታ ናቸው። ለማሳያ ያህል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን እንደጠቀስን ከሌሎችም የተወሰነ እንጥቀስ።
ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው “ኦ ምልዕተ ጸጋ ኦ ሙኀዘ ፍሥሐ፤ ጸጋን የተመላሽ የተድላ የደስታ መፍሰሻ” (ቅዳሴ ማርያም) እያለ ያመሰግናታል። ሊቁ እርሷ ደስታን የተመላች ናትና የተድላ የደስታ መፍሰሻ በማለት ገለጻት። እርሷ ምልዕተ ጸጋ ሁና በአማላጅነቷ ለሚያምን ሁሉ ጸጋን ታሰጣለችና የተድላ የደስታ መፍሰሻ አላት።
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም ‹‹ተፈሥሒ ኦ ወላዲተ እግዚእ ሐሤቶሙ ለመላእክት፤ የመላእክት ተድላ ደስታቸው አምላክን የወለድሽ ደስ ይበልሽ፤ የመላእክት ዜና ትንቢታቸው ንፅሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ የዓለሙን ሁሉ ተድላ ደስታ የሆነውን የመልአኩን ቃል ተቀብለሽዋልና ደስ ይበልሽ›› (ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ) እያለ የተድላ የደስታ የሰላም የፍቅር መገኛ የሆነችውን እመ ብርሃንን ያመሰግናታል። እኛም እነሱን አብነት አድርገን በዘወትር ጸሎታችን ‹‹ተፈሥሒ ፍሥሕት›› እያልን እናመሰግናታለን።
፪. ኦ ምልዕተ ጸጋ፤ ጸጋን የተመላሽ
ጠቢቡ ሰሎሞን በመኀልዩ ‹‹ኵለንታኪ ሠናይት እንተ ኀቤየ አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ፤ ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ ምንም ነውር የለብሽም” (መኃ. ፬፥፯) በማለት የነቢብም የኀልዮም የገቢርም ኃጢአት የሌለባትን የእመቤታችንን ንጽሕና ቅድስና ፍጽምና መስክሯል። በሌላ ቦታም ‹‹መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ አንቺ ግን ከሁሉ ትልቂአለሽ እጅግም ትበልጫለሽ›› (ምሳ. ፴፩፥፳፱) ይላል። ከሁሉ መብለጧ መላቋ ደግሞ ምልዕተ ጸጋ በመሆኗ ነው። ሊቁ አባ ሕርያቆስ ‹‹ኦ ምልዕተ ጸጋ ኦ ሙኀዘ ፍሥሐ፤ ጸጋን የተመላሽ የተድላ የደስታ መፍሰሻ ሆይ›› በማለት እንደመሰከረላት። ጸጋ ማለት ሀብት ስጦታ ማለት ነው ለእመቤታችን ተከፍሎ የቀረባት ጸጋ የለም በወንጌል እንደተገለጸው እግዚአብሔር ጸጋውን ሰፍሮ አይሰጥም። ይህ ማለት ለእያንዳንዱ በልክ በልኩ ጸጋ ተቀባዩ የሚችለውን ያክል ይሰጣል እንጂ ማለት ነው። ለቅዱሳኑ ሁሉ የተሰጣቸው በሚችሉትና በሚገባቸው ልክ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው›› (፩ቆሮ. ፲፪፥፬) ብሎ እደተናገረ። እመቤታችን ግን በመልአኩ አንደበት ‹‹ምልዕተ ጸጋ›› ተብሎ እንደተነገረው ጸጋ ያልተከፈለባት ናት።
ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹አይ ልቡና ወአይ ነቢብ ወአይ ሰሚዕ ዘይክል አእምሮ ዝንቱ ምሥጢር መንክራተ ዘይትነበብ ላዕሌሃ፤ ስለ እርሷ ድንቅ ሆኖ የሚነገረው ይህንን ምሥጢር ማወቅ የሚቻለው ምን ልብ ነው መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው›› በማለት በምልዕተ ጸጋነቷ ያገኘችውን ክብርና ባለሟልነት ይገልጻል።
፫. እግዚአብሔር ምስሌኪ (እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው)
እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው የሚለው አገላለጽ “የቀድሞ አባቶችም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብፅ ሀገር ሸጡት፣ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበር” (ሐዋ.፯፥፱-፲) እንደተባለው አይደለም። ወይም መልአኩ ለጌዴዎን ተገልጦ “አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነው” (መሳ.፮፥፲፪) እንዳለው አይደለም። እንዲሁ ጌታም ለሐዋርያቱ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” (ማቴ.፳፰፥፳) ብሎ እንደተናገረው አይደለም።
እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ሲል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ በማሕፀኗ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አድሮ ሐሊበ ድንግልናዋን እየጠባ ያደገበት ፍጹም ሰው የሆነበትን ምሥጢር ሲገልጥ “እግዚአብሔር ምስሌኪ” አለ ይህንንም ቅዱስ ቄርሎስ በሃይማኖተ አበው ‹‹እግዚአብሔር አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው እርሱ ቀምቶ እግዚአብሔር የሆነ አይደለም እራሱን አዋርዶ የተገዥ ባሕርይን ገንዘብ አደረገ።
መለኮትስ እንደ ሰው በድንግል ማሕፀን የዕለት ፅንስ በመሆን በድንግል ማሕፀን ሳለ በሰማይም በምድርም ምሉዕ ነው ለፅንሱ ወራት ዘጠኝ ወር እስኪፈጸም ድረስ እንደሰው ሁሉ በየጥቂቱ አደገ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ከእርሷ በነሳው ሥጋ ወለደችው በጨርቅም ጠቅልላ በበረት አስተኛችው ፍጹም መለኮቱ የሰውን ሥጋ ተዋሐደ ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ሆኖ ሠላሳ ዘመን እስኪሞላው ድረስ በአካል በጥበብ በሕዋሳት መጽናት በየጥቂቱ አደገ›› (ሃ.አ.ዘቄ ም ፸፩ ክ ፫ ቁ ፮-፯) በማለት እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ጋር የሆነው በተዋሕዶ ማለትም ሥጋዋንና ነፍሷን በመዋሐድ መሆኑን ያስረዳል።
አባ ጊዮርጊስም ይህንን ድንቅ ምሥጢር በሰዓታቱ እንዲህ ይገልጸዋል ‹‹በእንተ ሥጋ ወነፍስ አጽም ወደም ጸጉር ወአስራው ዘነሳእከ እምኔሃ ወረሰይኮ አሐደ ምስለ መለኮትከ ዘእንበለ ፍልጠት ኢ ውላጤ ወዘእንበለ ቱስሕት ኢ ቡአዴ በከመ መሀሩነ አበው፤ አባቶቻችን እንዳስተማሩን ከእርሷ የነሳኸውን ሥጋና ነፍስ አጥንትና ደም ጸጉርና ጅማት ከመለኮትህ ጋር ያለመለየት ያለመለወጥ ያለመጨመር ያለመነጠል አንድ አደረግኸው›› በማለት ፍጹም የሆነውን ተዋሕዶ ይገልጻል። ስለዚህ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ማለት በኅድረት ሳይሆን በኵነት፣ ማለትም በረድኤት፣ በጸጋ ሳይሆን በተዋሕዶ መሆኑን እንረዳለን።
፬. ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ
ይህ ቃል ሰማያዊው ቅዱስ ገብርኤልና ምድራዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ የተባበሩበት ቃል ነው። ከሴቶች ተለይተሽ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለብሽ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እያማለድሽ የምታሰጭ ነሽ ሲሏት ‹‹ቡርክት አንቲ እም አንስት›› ብለዋታል። ይህንንም ቅዱስ ቄርሎስ በሃ.አበው ‹‹ለዘመዶቹ ታዘዘ ይህችውም ያለ ዘርአ ብእሲ የወለደችው እናቱ ናት በሥጋ ከእርሷ መወለዱም እንደ ሴቶች መፅነስ ሥርዓት ልማድ አይደለም ከሴቶች መፅነስ ሥርዓት ልማድ የተለየ ነው እንጂ ድንግል በሥጋ ያለ ዘርአ ብእሲ ወለደችው›› (ሃ.ዘቄ ም.፸ ክ.፪ ቁ.፳፭) ብሎ እንደተናገረ እናትነትን ከድንግልና ድንግልናን ከእናትነት አስተባብራ የያዘች ብቸኛ ሴት ድንግል ማርያም ብቻ ናት። ስለዚህ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ ተባለች።
ጠቢቡ ሰሎሞንም በመኃልዩ ‹‹ርግቤ መደምደሚያዬ አንዲት ናት›› (መኃ.፮፥፱) ብሎ እንዳመሰገነ እመቤታችን በኀልዮ፣ በነቢብ በገቢር ንጽሕት ናትና ‹‹የዓቢ ክብራ ለማርያም እምኩሎሙ ቅዱሳን፤ የእመቤታችን ክብር ከቅዱሳን ክብር ሁሉ ይበልጣል፣ ይእቲ ተዓቢ እምኪሩቤል ወትፈደፍድ እምሱራፌል፤ ይቺ ከኪሩቤል ትበልጣለች ከሱራፌልም ትልቃለች››፤ ‹‹ቡርክት አንቲ አምአንስት ወቡሩክ ፍሬ ከርስኪ፤ አንቺ ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው›› እያልን ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር እናመሰግናታለን።
በአጠቃላይ እመቤታችን ቅደስት ድንግል ማርያም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ እንደተሰጣት ፍጥረታት ሁሉ ያመሰግኗታል። እርሷም “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰) ብላ እንደተናገረችው ትውልድ ሁሉ ያመሰግኗታል። እኛም መልአኩን፣ ሊቃውንቱን ሁሉ አብነት አድርገን ሰላም እልሻለሁ ልንላት ይገባል። ወላዲተ አምላክነቷን አምነን፣ በአማላጅነቷ ተማፅነን ርስተ መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ እግዚአብሔር ይፍቀድልን።
ምልጃ በረከቷን ለሁላችን ያድለን። አሜን!!!
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2081
የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር እጅግ የሚረቅ፣ የሚደንቅ፣ ከኅሊና በላይ የሆነ ነው። ሊቃውንቱንም እጅግ እያስደነቃቸው በተቻላቸው መጠን ለመግለጽ ይሞክሩና ከኅሊናቸው በላይ ሲሆን ዕፁብ ድንቅ እያሉት ያልፋሉ። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ውዳሴው “ኦ ዝ መንክር ልደተ አምላክ እማርያም ቅድስት ድንግል አግመረቶ ለቃል ኢቀደሞ ዘርዕ ለልደቱ፤ ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ፣ ቃልን ወሰነችው ልደቱንም ዘር አልቀደመውም” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት በኅሊናው ላይ የተፈጠረውን አግራሞት ይገልጻል። እንዲህ ያለው ልዩ ምሥጢር የተገለጸለትና በአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የኖረው ሊቁ ቅዱስ ሳዊሮስም “ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ሰማይ ዓለምን ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ” በማለት ተናገረ። እስኪ ምን ማለት እንደሆነ የተወሰነውን ምንባብ ጠቅሰን ዘርዘር አድርገን እንመልከተው።
“ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ወኮነ እግዚአብሔር ሰብአ በታሕቱ፤ ወረሰዮ ለሰብእ ውስተ አርያም በላዕሉ። ወስብሐተኒ ዘውስተ ሰማይ ኮነ ዲበ ምድር፤ ዘሀሎ በሕጽነ አቡሁ ኮነ በሕፅነ ማርያም፤ ወለዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት፤ ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት፤ ሰማይ ዓለም ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ተገኘ ሰውንም በላይ በአርያም አደረገው፤ በሰማይ የሚቀርበው ምስጋና በዚህ ዓለም ተደረገ (መላእክትና ደቂቀ አዳም በአንድ ቦታ ተገልጠው አመሰገኑ) ። በአብ እሪና ያለ እርሱ በእመቤታችን ክንድ ተይዞ ታየ። እግዚአብሔር አብ በማይመረመር ምሥጢር ያለ እናት የወለደውን ማርያም በማይመረመር ምሥጢር ያለ ዘርዐ ብእሲ በሥጋ ወለደችው።” (ሃ.አበ. ዘሳዊሮስ ፹፭፥፴፯)
ከዚህ ምንባብ በርከት ያሉ ነጥቦችን ማንሣት ቢቻልም። ጉዳዩ ሰፊ በመሆኑ በዚህ ጽሑፍ የተወሰኑትን ብቻ እንደሚከተለው እንመለከታለን።
፩. አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ
ሊቁ የአምላክን ሰው መሆን የሰውን አምላክ መሆን “ወኮነ እግዚአብሔር ሰብአ በታሕቱ፤ ወረሰዮ ለሰብእ ውስተ አርያም በላዕሉ፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ተገኘ ሰውንም በላይ በአርያም አደረገው” በማለት ገለጸልን። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ለማዳን ሰው ሆነ፤ አምላክ ሰው በሆነ ጊዜ ሰውም አምላክ ሆነ። ጥንት እግዚአብሔር የእርሱን የባሕርይ አምላክነት፣ ገዢነት፤ ልጅነት ወዘተ በጸጋ አድሎት፣ ፍጥረቱን ሁሉ እንዲገዛ ፈቀደለት። ግን አታድርግ የተባለውን ሲያደርግ የተሰጠውን ጸጋ ሁሉ ተነጠቀ። ይህ የተነጠቀው ጸጋ ይመለስለት ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ።
የሰው ልጅ ይድን ዘንድ አምላክ ሰው መሆኑን አስመልክቶ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ምሥጢር በተሰኘ መጽሐፉ የሚከተለውን ይነግረናል። “ባለመድኃኒቱ በድውዮች ሴት ልጅ አደረ ከእርሷም ምድራዊት ሥጋን ተዋሐደ ለድውዮችም ፈውስ በሚሆን ገንዘብ ከመለኮቱ ጋር ገንዘብ አደረገው። ባለመድኃኒት ከሰማየ ሰማያት መጥቷልና የፈውስ እንጨትም በዳዊት ቤት ተገኘ። መለኮት ከሥጋ ጋር ሳይዋሐድ ፈውስ እንደማይሆን ባለመድኃኒቱ አወቀ። ስለዚህ ራሱን ሰው ለመሆን ሰጠ።” (መጽሐፈ ምሥጢር ፳፥፯) ሁሉን የሚያድን አምላክ ለሰው ልጅ መድኃኒት ያደረገው ራሱ ሰው መሆንን ነበር። በመሆኑም አምላክ ሰው ሲሆን ሰውም አምላክ ሆነ። ሊቁም የነገረን ይህን ነው።
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ውዳሴ ማርያም “ወኮነ ሰብአ ከማነ ዘእንበለ ኀጢአት ባሕቲታ፤ ከኀጢአት ብቻ በቀር እንደኛ ሰው ሆነ።” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት የተናገረውን መተርጕማኑ “ባሕርያችንን እንደተዋሐደ ሲናገር እንደኛ ሰው ሆነ አለ። ከግብራችን እንደለየው ሲናገር ደግሞ ከኀጢአት ብቻ በቀር አለ” በማለት አብራርተውታል። ሰው የሚባለው አራቱ ባሕርያተ ሥጋና ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ በተዋሕዶ አንድ ሆነው ነውና። አምላክ ሰው ሲሆን ሰው አምላክ ሲሆን ባሕርየ ሥጋን ባሕርየ ነፍስን ሲነሣ ሥጋም ባሕርየ መለኮትን ገንዘብ ሲያደርግ ረቂቁ መለኮት ገዘፈ ግዙፉ ሥጋ ረቀቀ፤ ውሱኑ ሥጋ መላ ምሉእ መለኮት ተወሰነ። አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ይህ ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን ልዩ ምሥጢር “ኑ ይህን ድንቅ ምሥጢር እዩ ሰው የማይሆን ሰው ሆነ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት የማይታይ ታየ የማይታወቅ ታወቀ።” (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ) በማለት ከአድናቆት ጋር ያስረዳል።
ስለዚህ ሰማይ ዓለምን ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ” ማለት ልዑለ ባሕርይ ሰማያዊ አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሰው ሆነ፤ በዚህ ዓለም ተገለጠና ለሰው ሁሉ ታየ፤ ምድራዊው ሰው በተዋሕዶ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘብ አድርጎ ሰማያዊ አምላክ ሆነ ማለት ነው። ይህ ምሥጢር በተዋሕዶ የተፈጸመ መሆኑን ሲያስረዳ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “በእንተ ሥጋ ወነፍስ ዐፅም ወደም ፀጕር ወአሥራው ዘነሣእከ እምኔሃ ወረሰይኮን አሐደ ምስለ መለኮትከ ዘእንበለ ፍልጠት ወኢውላጤ ዘእንበለ ቱስሕት ወኢቡአዴ በከመ መሐሩነ አበው፤ ከእርሷ የነሣሃቸውን ሥጋና ነፍስ፣ አጥንትና ደም፣ የሰውነት ክፍሎችም አባቶቻችን እንዳስተማሩን ያለመለየት፣ ያለመለወጥ፣ ያለመጨመር፣ በተዋሕዶ ከመለኮትህ ጋር አንድ አደረግሃቸው። (መጽሐፈ ሰዓታት) በማለት ያስረዳል።
፪. አብ የወለደውን ድንግል ማርያም ወለደችው
ሊቁ ከላይ በገለጽነው ምንባብ ከሚናገራቸው ነጥቦች መካከል አንዱ አብ የወለደውን ድንግል ማርያም ወለደችው የሚለው ነው። ይህን ሲገልጽ “ወለዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት፤ ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት፤ በማይመረመር ግብር አብ ያለ እናት የወለደው እርሱን፤ በማይመረመር ተዋሕዶ እመቤታችን ያለ አባት ወለደችው” በማለት ልደቱን ብቻ ሳይሆን ልደቱ የማይመረመር እና ረቂቅ ምሥጢር እንደሆነም ይነግረናል።
የሰውን ልጅ ለማዳን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው ነው። ይህን በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ፤ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ” (መዝ.፻፱፥፫) በማለት ነገረን። መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞንም “ተራሮች ሳይመሠረቱ ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ በታች የሚታደርባቸውን ሀገሮችንና ዳርቻዎችን ሳይፈጥር ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬው ነበርሁ። ዙፋኑን በነፋሳት ላይ ባጸና ጊዜ፣ የቀላያትን ምንጮች ባጸና ጊዜ፣ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ እኔ ከእርሱ ጋር እሠራ ነበር” (ምሳ.፰፥፳፭-፴) በማለት ቅድመ ዓለም መወለዱን፣ እንዲሁም በአንዲት ሥልጣን ከባሕርይ አባቱ ጋር ዓለምን የፈጠረ መሆኑን ያስረዳናል።
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ” (ዕብ.፩፥፩) በማለት እንደነገረን ጥንት በአበው ምሳሌ ሲያስተምር በነቢያት ትንቢት ሲያናግር የነበረው አምላክ በኋላም በሐዋርያት እንደተመሰከረለት ሊቃውንቱም አምልተውና አስፍተው አስረዱን። ረቂቁን ምሥጢር እግዚአብሔር በገለጸላቸው መጠን ገለጹልን። ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት የተወለደው ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን ወልደ አብ ወልደ ማርያም መሆኑን አባቶቻችን ሊቃውንት በስፋት ገልጸው ነገሩን።
የተዋሕዶ መዶሻ እየተባለ የሚጠራው ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ “ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይመረመር ተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነውና ቀዳማዊ ሲሆን ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ ነው፤ ዳግመኛም ከድንግል በሥጋ የተወለደ ነው ተብሎ ስለ እርሱ እንዲህ ይነገራል።” (ሃ.አበ.ምዕ ፸፫ ክፍል ፲፩ ቁ. ፬) በማለት ያስረዳል።
ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “በምድራዊ ልደቱ አባት አለው አትበሉ፤ በሰማያዊ ልደቱም እናት አለችው አትበሉ፤ እርሱ በምድር አባት የሌለው ነው፤ በሰማይም እናት የሌለችው ነው።” በማለት ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን አስረዳን። ሊቁ እንዲሁ ተወለደ በሚል ቃል ብቻ አይደለም የገለጸው በሰማይ እናት አትፈልጉለት፣ በምድር ደግሞ አባት አትፈልጉለት በማለት በውስጣችንም ሊነሣ የሚችለውን ጥያቄ ግሩም የሆነ መልስ በመስጠት መጨነቅም እንደሌለብን ያስረዳል።
አንድ ሰው ተወልዶ እስኪያድግ ድረስ ጡት እያጠባች የምታሳድገው እናት፣ ከእናቱ ጋር እየተንከባከበ የአባት ፍቅር ሰጥቶ የሚለብሰውንና የሚጎርሰውን እያዘጋጀ የሚያሳድገው አባት ይፈልጋል። ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱ አባት እንደማያስፈልገው ሊቁ ጎርጎርዮስ “በሰማያዊ ልደቱ ጡት አጥብታ በወተት የምታሳድገው እናት አትሹለት፤ በሰማያዊ ልደቱ እናት የለችውምና መለኮቱን ከትስብእቱ ልዩ ነው አትበሉ፤ መለየት በሌለበት በእርሱ ክፉ መለየት እንዳይመጣ። (ሃ.አበ ምዕ.፴፭ ክፍል ፪ ከ፲፮-፲፰) በማለት ምሥጢረ ሥጋዌን በአግባቡ እንድንረዳ አምልቶና አስፍቶ ይነግረናል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ ልደቱ የወለደችው እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ጡት አጥብታ አሳደገችው። ይህን አስመልክቶ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “ሰብእ ወእንስሳ ወኵሉ ዘሥጋ ያስተበፅዑኪ እስመ ለዘይሴስዮሙ በሐሊበ አጥባትኪ ሐፀንኪዮ፤ ሰው እንስሳና ሥጋዊ ፍጥረት ሁሉ ያመሰግኑሻል። የሚመግባቸውን በጡትሽ ወተት አሳድገሽዋልና” (አርጋኖን ዘሰኑይ) በማለት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፍጥረታት ሁሉ እንደሚያመሰግኗት ከገለጸ በኋላ ለምን እንደሚያመሰግኗት ምክንያቱን ሲያብራራ ደግሞ ፍጥረታትን ሁሉ የሚመግበውን አምላክ ጡቷን አጥብታ በማሳደጓ እንደሆነ ያስረዳል። ከዚህ ላይ ከርእሰ ጉዳዩ አንጻር ልብ እንዲባል የሚፈለገው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋዊ ልደቱ ጡት አጥብታ ያሳደገችው መሆንዋን እንድንረዳው ነው።
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም “በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ የሚኖረውን ጌታን በመሀል እጅሽ ይዘሽዋልና በቸርነቱ ብዛት ሥጋዊ ፍጥረትን ሁሉ የሚመግብ እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ” (ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ) ብሎ እንደገለጸው በምድራዊ ልደቱ የእናቱን የድንግል ማርያምን ጡት ጠባ። ለምድራዊ ልደቱ አጥብታ ያሳደገችው እናት ቅድስት ድንግል ማርያም እንዳለች ሁሉ ለሰማያዊ ልደቱ ግን እንዲህ የምታጠባውና የምታሳድገው እናት አትሹለት በማለት ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስና ሌሎችም ሊቃውንት ነገረ ክርስቶስን አምልተውና አስፍተው ይነግሩናል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ደግሞ ከድንግል ማርያም ያለ አባት በመወለዱ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተብሎ ይጠራል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ድጓ በተሰኘው መጽሐፉ “ወይቤላ እግዚአብሔር ለማርያም አዝማንየ አዝማንኪ አምጣንየ አምጣንኪ ማርያም ሐቀፍኪዮ ወአነ ዮም ወለድክዎ፤ እግዚአብሔር ማርያምን ዘመኔ ዘመንሽ መጠኔ መጠነሽ ነው፤ አንቺ ታቀፍሽው እኔም ዛሬ ወለድሁት” (ድጓ ዘልደት) በማለት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና የወለደችው በእቅፏም የታቀፈችው ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት የተወለደ ወልደ አብ ወልደ ማርያም መሆኑን ያስረዳናል።
ሊቁ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ ደግሞ “ወመሀረነ ወልድከ እግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ አንተ ባሕቲትከ አቡሁ ሎቱ ወውእቱ ባሕቲቱ ወልድ ለከ ከመዝ ነአምን ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር እንዘ አልቦ ዘየአምር ምጽአቶ ዘእንበለ አቡሁ ባሕቲቱ ወጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ፤ ልጅህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንተ ብቻ አባቱ እንደሆንህ፣ እርሱ ብቻም ልጅህ እንደሆነ አስተማረን። አመጣጡን ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ብቻ በቀር ማንም የሚያውቅ እንደሌለ፤ በሰማይ እናት እንደሌለችው በምድር አባት እንደሌለው እናምናለን።” (አንቀጸ ብርሃን) በማለት የአብ ልጅ የማርያም ልጅ የማርያም ልጅ የአብ ልጅ መሆኑን፣ አብ ያለእናት መውለዱን በሰማይ እናት እንደሌለችው በማለት፣ ድንግል ማርያም ያለ አባት እንደወለደችው ደግሞ በምድርም አባት እንደሌለው እናምናለን በማለት ያስረዳል።
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና እንደወለደችውና ምድራዊ አባት እንደሌለው ሲያስረዳን “ሶበ ተወልደ እምድንግል ዐቀበ ድንግልናሃ እንበለ ሙስና፤ ከድንገል በተወለደ ጊዜ ድንግልናዋን ያለ መለወጥ አጸናው። (ሃ.አበ.ምዕ.፷፯ ክፍል፲፩ ቍ.፫) በማለት ከድንግል መወለዱን ብቻም ሳይሆን ሲወለድም ማኅተመ ድንግልናዋን እንዳልለወጠው ይናገራል። በሰው ባሕርይ በመጀመሪያ ድንግሊቱ ልትወልድ አትችልም በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከወለደች በኋላ ድንግል ተብላ ልትጠራ አትችልም። ድንግል ማርያም ግን ከመውለዷ በፊት፣ በወለደችውም ጊዜ ከወለደችውም በኋላ ድንግል ናት። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ የሚነግረን ይህን ነው።
፫. በአብ እሪና ያለ እርሱ በእመቤታችን ክንድ ተይዞ ታየ።
ይህን ዓለም ለማዳን ወዶና ፈቅዶ ወደዚህ ዓለማ የመጣው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ቅድመ ዓለም በአብ እሪና የነበረ ዛሬም ያለ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር አምላክ ነው። ይህ ቅድመ ዓለም በአብ እሪና የነበረው፣ ዛሬም ያለው በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ተወለደ። ስለዚህ ረቂቁ አምላክ በአብ እሪና እንዳለ በድንግል ማርያም ክንድ ተይዞ ታየ። የጌታ ወዳጅ የተባለውና ወንጌላዊው ዮሐንስ “ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዐይናችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን። (፩ዮሐ. ፩፥፩) በማለት ቅድመ ዓለም የነበረ መሆኑን፣ ሥጋ ማርያምን ገንዘብ አድርጎ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ መገለጡን በዐይናችን ያየነውን በእጆቻችን የዳሰስነውን የሕይወት ቃል እንነግራችኋለን በማለት አስረዳን።
ወንጌላዊው ዮሐንስ የጌታን ነገረ ሥጋዌ አምልቶና አስፍቶ በጻፈበት በቅዱስ ወንጌል “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ሁሉ በእርሱ ሆነ። (ዮሐ. ፩፥፩) ይለንና ይህ ቅድመ ዓለም የነበረው ዓለምን የፈጠረው አካላዊ ቃል ሥጋ ማርያምን ነሥቶ ተዋሕዶ ወደዚህ ዓለም መምጣቱንና መገለጡን ሲያስረዳን “ቃል ሥጋ ሆነ።” (ዮሐ.፩፥፲፬) በማለት ነገረን።
ስለዚህ በአብ እሪና ያለው አካላዊ ቃል የእኛን አካልና ባሕርይ ገንዘብ አድርጎ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ረቂቁ ሲገዝፍ፣ ሥውሩ ሲገለጥ በድንግል ማርያም ክንድ ተይዞ ታየ። “ዘሀሎ በሕጽነ አቡሁ ኮነ በሕፅነ ማርያም ፤ በአብ እሪና ያለ እርሱ በእመቤታችን ክንድ ተይዞ ታየ።” ያለው ለዚህ ነው።
፬. መላእክትና ደቂቀ አዳም በአንድ ቦታ ተገልጠው አመሰገኑ፡-
ሊቁ “ወስብሐተኒ ዘውስተ ሰማይ ኮነ ዲበ ምድር፤ በሰማይ የሚመሰገነውም ምስጋና በምድር ተደረገ።” በማለት በምሥጢረ ሥጋዌ ጊዜ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ሰውና መላእክት አንድ ላይ መዘመር መቻላቸውን ገለጸልን።
በጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ “የጌታ ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል” (ዳን.፫፥፴፭) ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር ባወቀ ሳያመሰግን የሚውል የሚያድር ፍጥረት የለም። ይልቁንም ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው ሕያዋን ሁነው ይኖሩ ዘንድ የተፈጠሩ ፍጥረታት ደግሞ ያለማቋረጥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። ማክሰኞ በሚጸለየው የሊጦን ጸሎት “ዘኪያከ ያንቀዐዱ ኵሉ ዘበሰማይ ወዘበምድር ዘፈጠርከ ለስምከ ይሰብሑ ወያእኩቱ፤ ስምህን ያመሰግኑ ዘንድ የፈጠርሃቸው ፍጥረታት ሁሉ በሰማይም በምድርም ወዳንተ ያንጋጥጣሉ” (ሊጦን ዘሠሉስ) ተብሎ እንደተጻፈ ሥራቸው እግዚአብሔርን ማመስገን የሆነላቸው ፍጥረታት ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። እነዚህም መላእክትና የሰው ልጆች ናቸው።
መላእክትና የሰው ልጅ ጥንቱንም ሲፈጠሩ እግዚአብሔርን ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው እንዲኖሩ ነው። ይህን በተመለከተ በመጽሐፍ “ረቂቅ የምትሆን አንተ ከእሳት ነበልባልና ከነፋስ የፈጠረህን ፈጣሪ ነኝ በማለት በታበይህ ጊዜ አንተም በተመካህ ጊዜ እግዚአብሔር ክፉ ሥራህን ተመለከተ፤ ሳያጓድል ስሙን ያመሰግን ዘንድ በአንተ ፋንታ የሚያመሰግን አዳምን ፈጠረው።” (፫መቃ.፪፥፲-፲፩) ተብሎ ተመዝግቧል። እንዲሁም “ምስጋናው በአንተ ጉድለት ይመላ ዘንድ በእጁ በፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ላይ ሾመው። የመሬታዊውም ምስጋና ከሰማያውያኑ ምስጋና ጋር ተጨመረ፤ ምስጋናቸውም እኩል ሆነ” (፫መቃ.፬፥፲፩) የሚል ምንባብ እናገኛለን።
ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች መላእክትም ሆኑ የሰው ልጅ የተፈጠሩት ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው ሊኖሩ እንደሆነ ነው። እግዚአብሔር አመስጋኝ ጎድሎት፣ የሚያመሰግነው መፍጠር ግድ ሆኖበት አይደለም። የክብሩ መገለጫ ይሆን ዘንድ ይህን ዓለም እንዴት እንደወደደው ይልቁንም ለሰው ልጅ ያለውን ጥልቅ ፍቅር እንረዳ ዘንድ ነው እንጂ። ዛሬም አመስጋኙ ለራሱ ይከብራል እንጂ እግዚአብሔር ባያመሰግኑት የሚጎድልበት ቢያመሰግኑት ደግሞ የሚጨመርለት ነገር ኑሮ አይደለም።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ዓለም ያድን ዘንድ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ መላእክት ከሰው ልጅ ጋር አመስግነዋል። አዳም አትብላ የተባለውን በልቶ ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣላ ከመላእክት ጋርም ተጣላ፣ አንድነቱን አጣ። በክርስቶስ መወለድ የሰው ልጅ ካገኛቸው ጸጋዎች አንዱ ከመላእክት ጋር በአንድነት እግዚአብሔርን ማመስገን መቻል ነው። ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በሃይማኖተ አበው “ወረሰዮ ድልወ ይትቀነይ ሎቱ ወይትለአኮ ከመ መላእክት እንዘ ሀሎ ውስተ ምድር በምግባር ሠናይ ወበሃይማኖት ርትዕት ዘሥላሴ ቅድስት፤ በዚህ ዓለም ሳለ በበጎ ምግባር ሥላሴንም በማመን እንደ መላእክት ያገለግለው ዘንድ ለእርሱም ይገዛለት ዘንድ የበቃ አደረገው” “ሃ.አበ. ፳፰፥፴፭) በማለት እንደገለጸው ሰውና መላእክት ዋናው የተፈጠሩለት ዓላማ እግዚአብሔርን አመስግነው ክብሩን ወርሰው ለመኖር ነው። ስለዚህ መላእክት ከሰው ጋር ማመስገን ቻሉ።
ይህን በተመለከተ በቅዱስ ወንጌል “ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ ይሉ ነበር” (ሉቃ.፪፥፲፫-፲፬) ተብሎ መላእክት በክርስቶስ ልደት ከሰው ልጅ ጋር ያመሰገኑት ምስጋና ተመዝግቦልን እናገኛለን። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን፤ ዛሬ መላእክትና ሰው ሃይማኖታዊት በሆነች ቃል ክርስቶስን ያመሰግኑት ዘንድ አንድ ሆኑ።” (ድጓ ዘፋሲካ) በማለት አስረዳን። ስለዚህ ከሊቁ አገላለጽ የምንረዳው በብዙ መንገድ የተገለጸውና መጻሕፍት አምልተውና አስፍተው የሚነግሩን የሰው ልጅ ከመላእክት ጋር ማመስገናቸውን ነው።
በአጠቃላይ “ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ሰማይ ዓለምን ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ” ማለት አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ፤ አብ ቅድመ ዓለም ያለ እናት የወለደውን ድንግል ማርያም ያለ አባት ወለደችው፤ በአብ ዕሪና ያለ በድንግል ማርያም እቅፍ ተይዞ ታየ፤ ሰማያውያን መላእክት ከምድራውያኑ የሰው ልጆች ጋር አመሰገኑ፤ በሰማይ የሚነገረው የመላእክት ምስጋና በምድር፣ በምድር የሚነገረው የሰው ልጅ ምስጋና በሰማይ ተነገረ፤ የሚለውና ከላይ በሰፊው እየተነተነው የመጣነውን የሚያስረዳን ነው። ከበረከተ ልደቱ ያሳትፈን አሜን።
- Details
- Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1532
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ካበረከተቻቸው ዘርፈ ብዙ አስተዋጽዖዎቿ መካከል ሀገር በወራሪ ኃይል እንዳትደፈርና መሬቷ እንዳይወሰድ በቁርጠኝነት መታገሏ እንደ አንዱ ይጠቀሳል። ‹‹ሀገር ከሌለ በማን ላይ ኖረን እግዚአብሔርን እናመልካለን?›› በሚል የኔነት ስሜትና ‹‹ለሀገሬና ለቤተ ክርስቲያኔ ብሞት በሰማይ ዋጋ አለኝ›› በሚል በጎ አስተሳሰብ የየዘመናቱን ትውልድ ቀርጻ ለአርበኝነት አብቅታለች። ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በሰማያዊ ተስፋ አንጻ ትውልድን ባታፈራ ኖሮ ሰይፍ ይዞ ለሃይማኖቱና ለሀገሩ የሚዋደቅ በእንቢ ባይነት መድፍን የመማረክ ወኔ ያለውን ጀግና፡ ሀገራችን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ ላታፈራ ትችል ነበር።
በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርቲያናችን የተቃኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ያለ መለያየት ሁሉም በአንድነት የፈጣሪ ክቡር ፍጡርና የአምላክ ባሪያ ነው›› ብሎ ያምናል። ይህ ትልቅ ሥነ ልቡናዊ ዐቅም ነው፤ ከነጮችና ከወራሪዎች በታች ያልጣለው የሞራል ልዕልናው ነው። በእጅ ከሚዳሰሱ፣ በዐይን ከሚታዩና በጆሮ ከሚሰሙ የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ እኩል ሊነሣ የሚገባው ትልቅ አበርክቶ ነው። ከዚህም ባለፈ የሀገር ግዛት እንዳይወረር፣ መሬቷ እንዳይደፈርና ቅርሶቿ እንዳይመዘበሩ ቤተ ክርስቲያን ካህናቷን ታቦት አስይዛ፣ ምእመናኗንም ከያሉበት ጠርታ አብራ ዘምታለች። በውጤቱም ኢትዮጵያን ከብዙ አፅራረ ሀገር አድናለች። ርስቷንም ጠብቃለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በልጆቿ ደም ከጠላት ሁሉ ጠብቃ ባቆየቻት ሀገር ውስጥ፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምእመን ላይ እስከ መሠዋት ድረስ የሚያደርስ መከራ፤ በሀብት ንብረቷ ላይም የመውደምና የመነጠቅ አደጋ በተቀናጀ መልኩ ሲደርስባት ቆይቷል። በመሬት ይዞታዎቿ ላይ እየታየ ያለው ባለ ይዞታነቷን ያለማረጋገጥና የመንፈግ ተግባርም ከዚሁ ጋር በአንድነት ሊታይ የሚችል፤ መመስገንና መሸለም የሚገባትን በአንጻሩ የማንገላታት ተግባር ነው።
በሀገሪቱ ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሕጋዊ መንገድ ይዘው ለረጅም ጊዜ የተገለገሉባቸውን መሬቶች ዛሬም የባለ ይዞታነት መብት እየተጠየቀባቸው ነው። የባሕረ ጥምቀትና የመስቀል አደባባዮች፡ በዓላቱ ለብዙ ዐሥርት ዓመታት ሲከበሩባቸው ቢቆይም፡ አብዛኞቹ የይዞታ ማረጋገጫ ለቤተ ክርስቲያን ያልተሰጠባቸው ናቸው። በምእመናን በሕጋዊ መንገድ ለዓመታት የተጠየቁ የ‹‹ቤተ ክርስቲያን ቦታ ይሰጠን›› ጥያቄዎች የመንግሥት የቢሮ ኃላፊ በመጣ ቁጥር እንደ አዲስ ሲታዩና አንዳንዴም ቦታዎቹ ለሌሎች የእምነት ተቋማት ሲሰጡ ዛሬም ይስተዋላል። ለምሳሌ፡-
ለ፪ ወጣቶች ሞት ምክንያት የሆነው ቦታ - እንደ ማሳያ
በቅርቡ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ፳፬ ቀበሌ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ለ፪ ወጣቶች መሠዋት ምክንያት የሆነውን ክስተት በምሳሌነት ማንሣት እንችላለን። በአካባቢው ቅርብ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ የአካባቢው ምእመናን በተለይም ሕፃናትና አረጋውያን ጠዋት ኪዳን ለማድረስና ማታም በሠርክ ጸሎትና ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ እጅግ ከአካባቢ ርቀው በመሄድ እንደሚቸገሩ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ ከ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ፲፬ ዓመታት በሕጋዊ መንገድ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል። የሚመለከተው የመንግሥት አካል በቦታው ቤተ ክርስቲያን እንዳይሠራ ለመከልከል ምንም ሕጋዊ ምክንያት አልነበረውም። ይባስ ብሎ የቤተ ክርስቲያንን የዓመታት ጥያቄ ችላ በማለት ለሌላ የእምነት ተቋም ከኋላ ለመጣ ጥያቄ ቦታውን ሊሰጥ መሆኑን የአካባቢው ምእመናን ደረሱበት።
ይህንን የሚያስረዱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ስም በተሰየመው በጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን መብትና ጥቅም አስከባሪ ማኅበር (ጴጥሮሳውያን ኅብረት)፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የመረጃ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ተክሉ ‹‹በአንዳንድ አካላት ቤተ ክርስቲያን መሬቱን እንደ ወረረች ተደርጎ መነገሩ አግባብ አይደለም። እዚያ አካባቢ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አልነበራትም። የአጥቢያ ምእመን ማልዶ ቤተ ክርስቲያን መሔድ ከፈለገ ወይ ወደ ቅዱስ ዑራኤል፣ ወይም ወደ ቦሌ ኆኅተ ብርሃን ማርያም፣ አሊያም ወደ ቦሌ መድኃኔ ዓለም፣ ወይም ደግሞ መገናኛ አካባቢ ወዳለው ወደ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ረጅም መንገድን እንዲሄድ ይገደዳል።
በእነዚህ ቦታዎች መካከል ደግሞ ከፍተኛ ርቀት አለ። ዐቅመ ደካሞች ሁሉ ወደነዚህ ቦታዎች ለመሔድ እጅግ ይቸገራሉ። በዚህም ምክንያት ከ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. አንሥቶ የአምልኮ ቦታ ጥያቄው ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ ቀርቧል። በኋላም በ፳፻፰ ዓ.ም. ምእመናኑ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ጥያቄ አቅርበው፡ ፓትርያርኩም መስከረም ፳፻፱ ዓ.ም. ላይ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ጥያቄውን በደብዳቤ አቅርበዋል። ለጥያቄው አስረጅ የሆኑ ከ፶ (አምሳ) ገጽ በላይ ሰነዶች ከጥያቄው ጋር አብረው ለከተማ አስተዳደሩ ደርሶት ነበር። ነገር ግን መልስ አልተሰጠበትም። ምእመናኑ ግን ጥያቄያቸውን ፈጽሞ አላቋረጡም ነበር። ከመነሻው ጀምሮ የሚንቀሳቀሱት በተደራጀ መልኩ ነበር። ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ የቆዩት ከሰባት ሺህ ሰዎች በላይ የፈረሙበት ሰነድን ከብዙ ማስረጃዎች ጋር ይዘው ነበር›› በማለት አስረድተዋል።
በቦታው ላይ ስለተከሰተው የደም መፍሰስ አቶ ግርማ ተክሉ አያይዘው ሲያስረዱም ‹‹ይህ የተከሰተው ፍትሕ በአግባቡ ባለመሰጠቱ ምክንያት ነው። በቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያንን ለመሥራት ለብዙ ዓመታት የቆየ ጥያቄ እያለ ከክስተቱ ከአንድ ወር በፊት ለጠየቀ ለሌላ የእምነት ተቋም ቦታውን ሊሰጡት ነበር። ለዚህም ማስረጃው አለን። ደብዳቤው በእጃችን ላይ አለ። የአካባቢው ምእመን በዚህ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት በመገፋፋት ትዕግሥቱ አልቆ ነው ቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያንን የሠራው። ከዚህ በኋላም እንኳን የከፋ ጥፋት ሳይከሰት ችግሩን መፍታት እየተቻለ፡ የሁለት ወንድሞቻችን ደም እንዲፈስ ሆነ›› ብለዋል። አቶ ግርማ ተክሉ ከዚህ ሁሉ በኋላ፡ ዘግይቶም ቢሆን የከተማው አስተዳደር ቦታውን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠቱ አመስግነዋል።
ይህ በተለምዶ ፳፬ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ የተፈጠረው ሁኔታንና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያን የይዞታ ጥያቄዎችን በተመለከተ፡ የመንግሥት የአፈጻጸም መመሪያና ሕግጋቱ ምን እንደሚሉ መገንዘብም ተገቢ ነው። አንድ የእምነት ተቋም የአምልኮ ቦታን ለማግኘት ምን ምን ማሟላት እንደሚገባው መገንዘብም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ግንዛቤ መያዝ ‹‹ይህ ጥያቄ ልክ ነው፤ ይህኛው ልክ አይደለም›› ለማለት ያመቻልና፡ እስኪ ጠቅለል አድርገን እንመልከተው።
የአምልኮ ማካሄጃ ቦታን ለመመደብ የሚሟሉ መስፈርቶች
በ፳፻፲ ዓ.ም. በወጣው መመሪያ መሠረት፡ አንድ የእምነት ተቋም በከተማ ውስጥ የአምልኮ ቦታን ለማግኘት በቅድሚያ ሊያሟላቸው የሚገቡ ወይም ጥያቄውን ትክክለኛ የሚያደርጉት መሥፈርቶች አሉ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡-
፩ኛ. ለአምልኮ ማካሄጃ ሊመደብ የሚችለው ቦታ ቅይጥ የመኖሪያ መሬት አጠቃቀም ውስጥ ሆኖ የመዳረሻ መንገዱ ስፋት ቢያንስ ፲፭ ሜትር መሆን ይኖርበታል።
፪ኛ. በአካባቢው ከሚገኘው ከራሱ ነባር የአምልኮ ቦታ አዲስ የተጠየቀው የአምልኮ ቦታ ቢያንስ በሁሉም አቅጣጫ ፫ ኪሎ ሜትር ሬድየስ የሚርቅ መሆን አለበት።
፫ኛ. በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት ፭ መቶ ሜትር ሬድየስ ይሆናል።
፬ኛ. ለአምልኮ ማካሄጃ አገልግሎት ቦታ የሚጠይቅ የሃይማኖት ተቋም በሚጠይቅበት አካባቢ ማለትም በሁሉም አቅጣጫ በ፩.፭ (በአንድ ነጥብ አምስት) ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ባለ በወረዳው ውስጥ የተመዘገቡ ቢያንስ ሰባት ሺህ ነዋሪ ምእመናን መኖር አለባቸው። በተጨማሪም በአካባቢው ተመሳሳይ የሃይማኖት ተቋም ካለ በሁሉም አቅጣጫ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ባለው ክልል ውስጥ ያሉት ምእመናን በአዲሱ የሃይማኖት ተቋም ሊመዘገቡ አይችሉም።
፭ኛ. ከአምልኮ ማካሄጃ አገልግሎት ጋር አብረው የማይሄዱ ማለትም ከአህጉር ዐቀፍና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት፣ ከጦር ካምፖች፤ ከዋና ዋና የንግድ ቦታዎች፤ ከቆሻሻ መጣያ ቦታዎች፤ ከደኅንነት ተቋማት እና ከሌሎች የአምልኮ ሁኔታን ሊያውኩ ከሚችሉ የመሬት አጠቃቀም ቦታዎች ያለው ርቀት ቢያንስ ከ፭ መቶ ሜትር በላይ ርቀት ያለው መሆን አለበት። ነገር ግን በሥራ ላይ የዋሉ ሌሎች ሕጎች ካሉ በሕጎቹ ላይ የሰፈረው ርቀት ገዢ ይሆናል።
እነዚህን መስፈርቶች መሠረት አድርገን ቀደም ሲል ያነሣነውን ደም ያፋሰሰውን የቤተ ክርስቲያን ቦታ ይሰጠን ጥያቄን ስናየው፡ በሁሉም መንገድ ሕጋዊና ተገቢ ጥያቄ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህን ዓይነት ብዙ ሌሎች መልስ ያልተሰጠባቸው ጥያቄዎችም አሉ። እንደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነትና እንደ ጴጥሮሳውያን ኅብረት ገለጻ፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የይዞታ ማረጋጋጫ እንዲሰጣቸው የተጠየቀባቸው የአድባራት እና ገዳማት እንዲሁም የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎች ብዛት ፻፹ (አንድ መቶ ሰማንያ) ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ለ፵ (አርባ) የአድባራት እና የገዳማት፣ እንዲሁም ለ፴፰ የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጥቷል። ቀሪዎቹ ግን እስከ አሁን ገና በጥያቄ ላይ ናቸው።
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን የረጅም ጊዜ ይዞታዎች ደግሞ ለሌላ አካል ካርታ ተሰጥቶባቸው ይገኛሉ። በተለይ የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች የዚህ ዓይነቱ ንጥቂያ ሰለባዎች ሆነዋል። እስኪ የሚከተሉትን ለዚህ በምሳሌነት እናንሣ፡-
ጃንሜዳ፣ ሆሣዕናና መሎ ኮዛ ወረዳ እንደ ማሳያ
ጃንሜዳ
አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ‹‹ጃን ሜዳ›› የሚለውን ቃል ሲተረጉሙት ‹‹ትልቅና ሰፊ ሜዳ፤ የንጉሥ ሜዳ፤ ንጉሡ የጦር ሠራዊት ሰልፍ የሚያይበት ከባለሟሎቹ ጋር ጉግስ የሚጫወትበት ሜዳ›› ይሉታል። በዋናነት በጥምቀት በዓል ማክበሪያነት የሚታወቀው ይህ ቦታ የተቀየሰው በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው።
‹‹የጃንሜዳ ባሕላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች›› በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ያዘጋጁት አቶ ዓባይነህ ታደሰ ጃንሜዳ የመንግሥት ጉዳዮች ማስፈጸሚያ የሹመትና ሽረት አዋጅ መንገሪያ እንደ ነበረ የልጅ ኢያሱ ንግሥና በኋላም ሽረት ሁሉ የተነገረበትና የተደገሰበት እንደ ነበረ ያወሳሉ።
በጃንሜዳ ላይ ብዙ የዘመቻ የሰልፍ ትርኢቶች ተደርገውበታል። በ፲፱፻፵ዎቹ የክብር ዘበኛ ቃኘው ሻለቃ ጦር ወደ ኮርያ ሲዘምት፣ በ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. ለዕድገት በኅብረት የዕውቀትና ሥራ ዘመቻ፣ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲዘምቱ ሰልፋቸውን የጀመሩት ከጃንሜዳ ነበር። በዘመነ ደርግ ለተደረጉ ልዩ ልዩ ዘመቻዎች የክተት መነሻም የነበሩበት አጋጣሚም እንደ መኖሩ ሁሉ በኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ዘመን በማዕከላዊ መንግሥት ሥር የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች ወደየ ክልሉ እንዲዛወሩ ሲደረግ መነሻቸውን ያደረጉት ጃንሜዳ ነበር። በቅርብ ጊዜ ታሪኩም የገና ጨዋታን ጨምሮ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ተመራጭ መሆኑ ይታወቃል።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (፲፱፻፳፫-፲፱፻፷፯) በጃንሜዳ ስለ ነበረው የጥምቀት በዓል አከባበር አቶ ዓባይነህ ከላይ በተጠቀሰው ጥናታቸው ከጻፉት ውስጥ በጥቂቱ እዚህ ላይ አስፍረነዋል።
‹‹በከፍተኛ ደረጃ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ የሚያከብረው የክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ በዓል ዓመታዊው የጥምቀት በዓል እንደ ሆነ ይታወቃል። በዓሉ በድምቀት የሚከበርበት ቦታ ከ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ጀምሮ በጃንሜዳ እንዲሆን በመወሰኑ በዚሁ ሥፍራ ያለማቋረጥ ሲካሄድ ቆይቷል።
‹‹የጥምቀት በዓል የሚከበርባቸው ሌሎች ጥምቀተ ባሕሮች በአዲስ አበባ ከተማ ቢኖሩም የጃንሜዳው ጥምቀተ ባሕር በየዓመቱ ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱና ሚኒስትሮች ከሕዝብ ጋር ተገኝተው የሚያከብሩበት፣ የኦርቶዶክስ ፓትርያርኩም ሥነ ሥርዓቱን የሚመሩበት በመሆኑም የተለየ ዝና ሊያገኝ ችሏል።
‹‹በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ዓመታዊው የጥምቀት በዓል በጃንሜዳ ሲከበር በተለየ ችግር ምክንያት ካልሆነ ንጉሡ በሥፍራው መገኘታቸው የተለመደ ሥርዓት ነበር። ይህም ሁኔታ በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል የቆየውን መተሳሰር ያመለክታል። በ፲፱፻፳፬ ዓ.ም. በጤና መጓደል ምክንያት፣ ከ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ወደ አውሮፓ በስደት ምክንያት በመሄዳቸው በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር ጉብኝት በመሄዳቸው ምክንያት ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ንጉሡ በዓሉን ሳያከብሩ መቅረታቸው ተመዝግቧል።
‹‹በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ላይ የተለያዩ የሀገር መሪዎች ከንጉሡ ጋር መገኘታቸው የዚህን ሥፍራ ታሪካዊ ገጽታ የሚያጎላ ሆኖ እናገኘዋለን። በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. በዓሉ ሲከበር ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የነበሩት የዴንማርክ ንጉሥና ንግሥት በጃንሜዳ ተገኝተው ነበር። በ፲፱፻፷፭ ዓ.ም. የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ፖምፒዱ በጃንሜዳ ተገኝተው የጥምቀት በዓልን አከባበር ተመልክተውታል።
‹‹የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ከሌሎቹ በተለየ ትኩረትን የሳበው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።
አንደኛው፦ የታቦታት ብዛት በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ላይ አሥራ ሁለት ታቦታት ባንድ ላይ ውለው ስለሚያድሩ ከተለያዩ የከተማው ክፍሎች አጅቧቸው የሚመጣው የሕዝብ ቁጥር ስለሚበዛ በዓሉን ሊያደምቀው ችሏል።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፡- ንጉሡና ንጉሣውያን ቤተሰቦች ሚኒስትሮች፣ፓትርያርኩ በጃንሜዳ በዓሉን ማክበራቸው ስፍራው ከሌሎች ባሕረ ጥምቀቶች የበለጠ ደረጃ እንዲያገኝ አስችሎታል። ጃንሜዳ የተመረጠበት ምክንያት የማዕከላዊው መንግሥትና ቤተ ክህነት ኃላፊዎች የጥምቀት በዓል ማክበሪያና በንጉሡ /በጃንሆይ/ ማዕርግ ስለ ተሰየመ መሆኑ ታውቋል። ንጉሡ ከሥልጣን ከወረዱም በኋላ ዋናው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ሆኖ ለመቀጠል ችሏል።›› (ዓባይነህ ታደሰ፣ የጃንሜዳ ባሕላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች፣ retrived from: http://m.facebook.com/architectyohannis/posts/2938117996198309?local2=ms_MY)
ጃንሜዳ ከሰማንያ ዓመታት በላይ (ከ፲፱፻፴፫ ጀምሮ) በጥምቀት በዓል ማክበሪያነት ያገለገለ ቦታ ነው። በርካታ የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የባሕል እና ሃይማኖታዊ እሴቶች የተሰናሰኑበት ራሱ ታሪክ የሆነ ሥፍራ ነው።
ጃንሜዳ የጥምቀት በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርት እና የባሕል ማዕከል ጥምቀትን የዓለም ቅርስ አድርጎ ሲመዘግብ በርካታ ማስረጃዎች እና የሃይማኖታዊ ኩነቶች ናሙና ከተወሰደባቸው ታሪካዊ ቦታዎችም አንዱ ነው። ይህ ታላቅ ቦታ በቀደሙት ዘመናት፡ አሁን ካለው ይዞታ በላይ የነበረው ቢሆንም በተለያየ ዘመን ልዩ ልዩ አካላት ተናጥቀውት አሁን ላይ የሚገኘው ፴፫ ጋሻ ገደማ ነው። የቦታው ታሪካዊ ባለ ይዞታም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ሀገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው።
ነገር ግን ይህች ታሪካዊት የቦታው ባለ ይዞታ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባላወቀችበት ሁኔታ ከዘጠና ከመቶ በላይ ይዞታው የአዲስ አበባ ስፓርት ኮሚሽን ካርታ አውጥቶበት ‹‹ባለ ይዞታ ነኝ›› እያለበት ይገኛል። ይህ ባለ ይዞታነቱን የሰጠውንም ሆነ የተቀበለውን አካል ከታሪክም ሆነ ከሞራል አንጻር የሚያስነቅፍ ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያንን የማግለል ተግባር ነው። የቦታውን ቅርስነትም የሚጎዳ አስተዋይነት የጎደለው ውሳኔ ነው።
በመሆኑም ይህን አግባብ ያልሆነ ውሳኔን ቤተ ክርስቲያናችን ለከተማው አስተዳደር ስሞታ አቅርባ በመከታተል ላይ ትገኛለች።
ታሪካዊው ጃንሜዳ የዓለም ቅርስ፣ የሀገር ሀብት እና የገቢ ምንጭ ሆኖ፤ በዋናነት ሃይማኖታዊ አከባበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት እንዲቀጥል የከተማው አስተዳደር ሊያስብበት ይገባል። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአትክልት ተራ ሆኖ እጅግ መቆሸሹ ለጥምቀት በዓል አከባበር እንደማያመች በመረዳት ለማጽዳት በከተማው አስተዳደር እየተደረገ ያለው ርብርብ፡ የቦታውን ባለ ይዞታነት ለቤተ ክርስቲያን መልሶ ፍትሕን በማረጋገጥ ሊደገም ይገባል። የከተማ አስተዳደሩ ይህንና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎችን በሕግ አግባብ ፈጥኖ የሚመልስ ከሆነ በእውነቱ የታሪክና የቅርስ አለኝታነቱን ማስመስከር የሚችል ይሆናል።
ሆሣዕና
በሆሣዕና ከተማ የጥምቀተ ባሕር ቦታው ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተይዞ አገልግሎት ሲሰጥበት የቆየ ጥንታዊ ይዞታ ነው።
ይህ ጥንታዊ ይዞታ እስከ ፳፻፲፩ ዓ.ም. ድረስ ስድሳ ሺህ ካሬ ሙሉ ነበር። በዞኑ አሁን ባለው ኢ-ፍትሕዊነት ጥንታዊው የጥምቀት ማክበሪያ ይዞታ ተነጥቋል።
አሁን በከተማው ውስጥ የገበያ ቦታ የሆነው የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ የነበረና የተነጠቀ ነው። ከብዙ ጥረት በኋላ ሃያ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታን ብቻ ለመስጠት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም እርሱንም መልሰው ከልክለዋል።
በዚህ ላይም አስተያየት የሰጡን አቶ ግርማ ‹‹የዞኑ አመራሮች ሲፈልጉ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ለይቶ የሚያጠቃ መመሪያ ያጸድቃሉ። እንዲሁም ፍትሕ በመንፈግ የግል ሃይማኖታቸው ተከታይ ለሆኑት ፓስተሮች ከሠላሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ካሬ ያድላሉ። የቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊ ይዞታ ግን ይነጥቃሉ›› ሲሉ የምእመናኑን ምሬት አስተጋብተዋል።
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስም በተመሳሳይ ባለ ሥልጣናቱ ለቤተ ክርስቲያን ካላቸው ጥላቻ የተነሣ ቤተ ክርስቲያኗ ያነሣችውን ተገቢ ጥያቄ በሕግ አግባብ ከመመለስ ይልቅ ነገሩን የፖለቲካ ቅርጽ በመስጠት ከማወሳሰባቸው ባሻገር ‹‹ወራሪ›› እያሉ መሳደብ የሚቀናቸው መሆናቸውን በጉዳዩ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መግለጻቸው ይታወሳል።
ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ
ከላይ ካነሣናቸው ጋር በሚመሳሰል መልኩ በጎፋ ዞን በመሎ ኮዛ ወረዳ የተከሰተው ክስተትም ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጫናና በደል ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።
በወረዳው የሚገኘው የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ይዞታው ከ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፡ እስከ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ድረስ ቦታው የሚገኝባት ከተማ በገጠር ከተማነት ቆይታ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. በማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ሥር የሆነች ናት።
ታዲያ በዚሁ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. የከተማዋ አስተዳደር ወደ ማዘጋጃነት ሲቀየር የሃይማኖት ተቋማት ይዞታ ‹‹ባለበት ይቀጥላል›› ተብሎ ነበር። ከዓመታት ቆይታ በኋላ በ፳፻፲፪ ዓ.ም. ባለ ሥልጣናቱ ሁለተኛ ዙር ጥናት በማለት፡ የቀድሞውን ውሳኔ ችላ ብለው የቤተ ክርስቲያንን የጥምቀት ይዞታ ነጠቁ።
ገና ከተማው ሳይቆረቆር ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአምሳ ዓመታት ትጠቀምበት የነበረውን ይህን ይዞታ ከተማው ከኋላ መጥቶ በመስፋፋቱ ምክንያት፡ የአስተዳደር አካላቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ፣ ለበዓሉ ቅርስነት ሳይጨነቁ ቦታውን ከቤተ ክርስቲያን ላይ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነጠቁ። ይህን ሲያደርጉ ቢያንስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከበዓል አከባበሩ ጋር በማይጣረስ መልኩ እንድታለማ እንኳን ዕድል አልተሰጣትም።
ከዚህ የሚከፋው ደግሞ የጉዳዩን ሕገ ወጥነት እና ኢ-ፍትሐዊነት አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረቡት ምእመናን፣ ለአምሳ ዓመታት ሲገለገሉበት በነበረው የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ላይ የመጠመቂያ ገንዳ በመሥራት እና መስቀል በመትከል በዓለ ጥምቀትን በማክበራቸው፡ በተለይ ጉዳዩን በዋናነት የሚከታተሉትን ክርስቲያኖች፡ የከተማው አስተደደር ክስ መሠረተባቸው። በሚያሳዝን መልኩም ከ፯-፱ ዓመታት ድረስ የእስር ፍርድ እንዲበየንባቸው ተደረገ። ያቀረቡት ጥያቄ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መልስ ባላገኘበት ሁኔታ ዘወትር በዓሉን በሚያከብሩበት መልኩ ለማክበር በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ለዓመታት በእስር እንዲቆዩ ፈረዱባቸው።
ስለ ጉዳዩ አስተያየት የሰጡን ቀደም ሲል ያነሣናቸው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አመራር የሆኑት አቶ ግርማ ተክሉ ‹‹ይህን ያደረጉት ሙሉ ለሙሉ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ የአስተዳደር አካላት ናቸው። ድርጊቱ ቤተ ክርስቲያን ላይ ባለ ጥላቻ ብቻ የተፈጸመ ነው›› ያሉ ሲሆን፡ ቤተ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ ባደረገችው ጫናም ክልሉ እስረኞቹ ካለ አግባብ መታሰራቸውን በማመን በቅርቡ እንዲፈቱ ማዘዙንም ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ‹‹በዞኑ የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ብዙ መከራ እየደረሰባቸው ነው። መስቀል ያለበት ቲሸርት እንኳን መልበስ አልተቻለም›› ብለው ቤተ ክርስቲያን እና አማኞቿ ላይ እየደረሰ ያለው ፈተና ዘርፈ ብዙ መልክ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
እነዚህን በምሳሌነት አነሣናቸው እንጂ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች ለዘመናት መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥባቸው የኖሩ እስከ ዛሬም ያሉ ሆነው ሳለ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰፊ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የዘመቻ ዒላማ እንደ ሆኑና በዚህና በእኛም ቸልተኝነት ምክንያት ለፈተና የተጋለጡ እንደ ሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ይቀጥላል
- Details
- Written by: በክፍለ ማርያም
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2338
መግቢያ
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል” (መዝ.፻፲፩፥፮) በማለት እንደተናገረው በሃይማኖት ጸንተው በምግባር በትሩፋት ተጸምደው በተሰጣቸው ውስን የዚህ ዓለም ዕድሜ እግዚአብሔርን ያገለገሉ ቅዱሳን ሁሉ መታሰቢያቸው ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል። በዚህ ዓለም የነበረ የተጋድሎ ቆይታቸው የተወሰነ ቢሆንም የተጋድሎ ዋጋቸው ግን ጊዜ የማይሽረው ዘለዓለማዊ ነው። በዚህ ወር የእናስተዋውቃችሁ ዓምዳችን በ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን በድንቅ ተጋድሏቸው እግዚአብሔርን ካስደሰቱትና ዘለዓለማዊ መታሰቢያ ከታደላቸው ቅዱሳን አንዱን አባ ተክለ አልፋን አቅርበናል።
ልደት
አባ ተክለ አልፋ ከአባታቸው ከአሮንና ከእናታቸው ከኦርኒ በዕለተ ሐሙስ ጥር ፳፩ በ፲፭፻፫ ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ደብረ ኤልያስ ወረዳ ጎፍጭማ ከምትባል ቦታ ተወለዱ። አባታቸው ከሸዋ ምድር ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ጎጃም የደብረ ኤልያስ አካባቢ ሰው ናቸው። አባታቸው በንጉሥ ይስሐቅ ዘመን ከሸዋ ተሰደው ደብረ ኤልያስ ጎፍጭማ ከምትባል ቦታ ከወሰን አምባ ምድር ደረሱ፤ በውስጧም ተቀመጡ። በእግዚአብሔር ፈቃድ በንጹሕና በከበረ ጋብቻ አንድ ሁነው ወንድና ሴት ልጆችንም ወለዱ። አባ ተክለ አልፋ ከመወለዳቸው በፊት እናታቸው ኦርኒ ራእይ አይተው “ፀሐይ ስትወጣ በሆዴም እንደ መብረቅ ሲያበራ አየሁ” ብለው ለባለቤታቸው ነገሯቸው። ባዩትም ራእይ እየተደነቁ ሳለ ዕለተ ሐሙስ ጥር ፳፩ በ፲፭፻፫ ዓ.ም በእመቤታችን በዓለ ዕረፍት ተወለዱ።
የስማቸው ትርጓሜ
ተክለ አልፋ ማለት የአልፋ ተክል ማለት ነው። አልፋ ማለት ስመ አምላክ ሲሆን ተክለ አልፋ ማለትም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ተክል፣ የጽድቅ ፍሬን የሚያፈራ እንጨት፣ ከኃጢአት ሐሩር መጠለያ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም ወዘተ ማለት ነው።
የትምህርት ሕይወት
አባ ተክለ አልፋ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወላጆቻቸው በአካባቢያቸው ለሚገኙ መምህር ሰጧቸው። በአካባቢ ከሚገኙ መማህራንና ከሌሎችም መምህራን ዘንድ እየተዘዋወሩ የብሉያትና የሐዲሳትን ትርጓሜ ተምረዋል። ወደ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደመጡ በወቅቱ የገዳሙ አበ ምኔት ከነበሩት ከአባ ማቴዎስ ሥርዓተ ገዳምን ተምረዋል።
የምናኔ ሕይወት
ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወላጆቻቸው ሊያጋቧቸው አስበው ሚስት እንዳጩላቸው በሰሙ ጊዜ ከዚህ ዓለም ሙሽርነት ይልቅ ሰማያዊ ሙሽርነትን በመምረጥ እግዚአብሔርን የሕይወትን መንገድ ምራኝ በማለት ጸለዩ። ሰርጉ ሦስት ቀን ሲቀረውም መልአከ ገጻቸው (ጠባቂ መልአካቸው) እየመራ ወደ ዲማ ገዳም አደረሻቸው።
ከተወለዱበት ቦታ ወደ ዲማ ገዳም ሲሄዱ መንገድ ላይ መሸባቸውና የሰንበት ከምትባል ቦታ አደሩ። ዕለቱ ዐርብ ነበርና በሰንበት መንገድ አልሄድም ብለው ከዚያው ቦታ ሰነበቱ። በዚህ ጊዜ ለጸሎት ሲቆሙ ዐሥሩ ጣቶቻቸው ሲያበሩ ለካባቢው ምእመናን ይታዩ ነበር። በዚህም የአካባቢው ምእመናን እግዚአብሔርን አመስግነዋል። የቦታው ስያሜም የሰንበት የተባለው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ከቀድሞ አባቶች የተገኘው ትውፊት ያስረዳል።
ወደ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደመጡም በወቅቱ የገዳሙ አበ ምኔት ከነበሩት ከአባ ማቴዎስ ሥርዓተ ገዳምን ከተማሩ በኋላ አባ ማቴዎስ የአባ ተክለ አልፋን መንፈሳዊ ጽናት አይተው አመነኰሷቸው። በመቀጠልም በአባ ተክለ አልፋ ተጋድሎና ደግነት ስለተደሰቱ የገዳሙ አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው።
በዚህ ጊዜ የገዳሙ አበምኔት የሚሆን ሰው ከግሸና ተክለ ሃይማኖት ይመጣ ስለነበር እንደ አዲስ ሥርዐት ተቆጥሮ በግሸና መነኰሳትና በዲማ መነኰሳት መካከል ጠብና ክርክር ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሡ ልብነ ድንግልና ሹማምንቱ በእርሱ ላይ ያደረውን ጸጋ እግዚአብሔር አይተው ለዲማ መነኰሳት ፈርደውላቸው የአባ ተክለ አልፋን ሹመት አጽድቀውላቸዋል።
ይህ ግሸና የሚባለው ቦታ የዲማን ገዳም የመሠረቱት አቡነ ተከሥተ ብርሃ ወደ ዲማ ከመምጣታቸው በፊት ለተወሰነ ጊዜ ቆይተውበት ስለነበርና እርሳቸው ከዚህ ቦታ ስለመጡ እንደ አንድ ይቆጠራልና እስከ አቡነ ማቴዎስ ድረስ የገዳሙ አበምኔት የሚመጣው ከዚህ ቦታ ነበር። ከአቡነ ማቴዎስ በኋላ ግን ማለትም ከአቡነ ተክለ አልፋ ጀምሮ ከዚሁ ከዲማ የሚሾም ሆኗል። የጠቡና የክርክሩ መነሻም ይህው ነበር።
ጻድቁ አባት አባ ተክለ አልፋ ግን ለተመረጡለት ሹመት ፈቃደኛ አልነበሩም። በንጉሡም ፊት አይሆንም ለማለት ሞክረው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ኃላፊነት በጸጋ እንዲቀበሉና ገዳሙን በቅንነት እንዲያገለግሉ፣ የሹመቱንም ወንበር ትተው ከገዳሙ እንዳይወጡ አባ ማርቆስ የተባሉ ጳጳስ አወገዟቸው፤ የጳጳሱንም ቃል ይሽሩ ዘንድ አልቻሉምና በእሽታ ተቀበሉት።
ጻድቁ አባ ተክለ አልፋ ምስማር ያለው ጫማ በመጫማት ከእግራቸው ደምና ዕዥ ይወርድ ነበር። በዚያ ደምና ዕዥም በሽተኞች ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር። በሚሄዱበት መንገድም ደምና ዕዥ ከእግራቸው ይፈስ ስለነበር ሕፃኑም አዋቂውም አባ ተክለ አልፋ ዛሬ በዚህ በኩል አልፏል ይላቸው ነበር። ዕለተ ሞታቸው እንደተቃረበ ተረድተው ከገዳሙ በስተደቡብ በኩል ባለውና ሱባኤ ይይዙበት በነበረው ዋሻ ጸሎት ማድረግ ጀመሩ።
በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አበ ምኔት ሁነው ለ፵፭ ዓመታት ያህል ገዳሙን በሥርዓትና በሕግ ካገለገሉ በኋላ በ፸፭ ዓመታቸው ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ታኅሣሥ ፰ ቀን ሐሙስ ማታ ለዐርብ አጥቢያ ከምሽቱ ፫ ሰዓት አርፈዋል። በዚህ ጊዜ መላ ዘመናቸውን ይዘዋት ትኖር የነበረች መቋሚያቸው ወደ መነኰሳቱ መጥታ አባታችን አርፈዋልና ቅበሯቸው ብላ በሰው አንደበት ተናግራለች። እስከ አሁንም ድረስ በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትገኛለች ሕሙማንም ይፈወሱባታል።
ለገዳሙ የሠሩት ሥርዐት
ከአቡነ ተከሥተ ብርሃን እስከ አቡነ ተክለ አልፋ ድረስ መነኰሳቱ በአንድ ቤት በአንድ ቅጽር ይሰበሰቡ፣ በአንድ በርም ይገቡ ይወጡ ነበር፤ እንደየማዕረጋቸውም መጀመሪያ አስኬማና ቆብ የተቀበሉት፣ ከዚህ በኋላ ደግሞ ባለ ቀሚስና ባለ ቅስና በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ ሰዴቃ ይበሉ ይጠጡ ነበር። በእንደዚህ ያለ ሥርዐት እያሉ ግራኝ ኢትዮጵያን ወረራት፤ ቤተ ክርስቲያንም ተዘጋች። አባታችን አቡነ ተክለ አልፋም የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ይዘው ወደ በጌ ምድር ተሰደዱ። ጥቂት መነኰሳትም አብረው ተሰደዱ። የቀሩት መነኰሳትም በዋሻ ውስጥ ገብተው መኖር ጀመሩ። ከዐሥራ አምስት ዓመት በኋላ ግራኝ ሲሞት ሞት ስደት ፀጥ አለ። ያን ጊዜም አባታችን አቡነ ተክለ አልፋ ከተሰደዱበት ተመለሱ፡ መነኰሳቱም ከተበተኑበት ተሰበሰቡ። ከዚህ በኋላ መነኰሳቱ ስደት አማቶናልና በአንድ ቤት ተሰብሰቡ አይበሉን፤ መቅኑናችንንም በየቤታችን እንብላ ብለው አባ ተክለ አልፋን ለመኗቸው።
አባ ተክለ አልፋም የመነኰሳቱን ልመና ተቀብለው በተለያየ ቤት እንዲኖሩ መቅኑናቸውም በየቤታቸው እንዲሰጣቸው ፈቀዱላቸው። እነርሱም እየተከፋፈሉ በየግላቸው መውሰድና መብላት ያን ጊዜ ጀመሩ።
ቃል ኪዳን
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለታት አንድ ቀን ተገልጾ በዚህ ዓለም እንዳከበርከኝ እኔም በወዲያኛው ዓለም አከብርሃለሁ። ስለ ስሜም እንደደከምክ የምሕረት ቃል ኪዳን እሰጥሃለሁ በመንግሥተ ሰማያትም ዋጋህ እጽፍ ድርብ ይሆንልሃል። ስምህን የጠራውን በጸሎትህ የታመነውን መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። በተለየ ሁኔታ ለአባ ተክለ አልፋ የተሰጧቸው በርከት ያሉ ቃል ኪዳኖች አሉ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡-
፩. በአንድ ወቅት ረኀብ ሆኖ አንዲት ድሀ ለተከታታይ ስድስት ቀናት እየመጣች ለመነቻቸውና ስድስቱንም ቀናት የእርሳቸውን የዕለት ምግብ ሰጧት። በሰባተኛውም ቀን እንደ ለመደችው መጥታ ቆመች። በዚህ ጊዜ ረኀብ ቢሰማቸውም “ተርቤ አላበላችሁኝምና” (ማቴ.፳፭፥፵፪) የሚለው የወንጌል ቃል ሊፈርስብኝ አይደለም እንዴ በማለት ሰጧት። ከዚህ በኋላ ጠይቋቸው የማያውቅ ባለጸጋ ምግባቸውን ይዞላቸው መጥቷል። ጌታም ተገልጦ ከእንግዲህ ወዲህ በዘመንህ ረኀብ አላመጠብህም ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።
፪. በገዳሙ ክልል ጅብና እባብ ሰውንም ሆነ እንስሳ እንዳይተናኮል ስለገዘቱት በእነዚህ አውሬዎች ምእመናን ፍራቻ የለባቸውም። ዛሬም እንስሳቱ ሌሊት በሜዳው ሲያድሩ ምንም ሳይነካቸው ያድራሉ። እባቡም ከመታየት በዘለል ምንም ሰው አይናከስም።
፫.ሚያዝያ ፳፫ ቀን የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ሲከበር ታቦቱ ከዋሻው ወጥቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን እስከሚገባበት ጊዜ ድረስ በሚያርፍበትና በሚነሣበት ጊዜ ሁሉ ከፊት ለፊት የሚሄድ ጥቅል አውሎ ነፋስ አለ። ከዚህም በተጨማሪ ከሚያዝያ ፩ በዓሉ እስከሚከበርበት ሚያዝያ ፳፫ ድረስ በስድስት በስድስት ሰዓት በጉልላቱ ገብቶ ቤተ መቅደስ ቆይቶ ተመልሶ የሚወጣበት ምልክት አለ። ይህም ቦታውን በረድኤት አልለየውም ብሎ ለጻድቁ የገባላቸው ቃል ኪዳን ምልክት ሁኖ ይኖራል።
፬.ሀገሪቱ (ዲማ) እንደመቃብሬ እንደኢየሩሳሌም ትሆንልሃለች የሚል ቃል ኪዳንም ገብቶላቸዋል።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ቃል ኪዳኖች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቁ ከገባላቸው ጥቂቶች ናቸው።
በአጠቃላይ ጻድቁ አቡነ ተክለ አልፋ በሃይማኖት ጸንተው በምግባር በትሩፋት ተጸምደው በሕይወት ዘመናቸው እግዚአብሔርን አስደስተው ጽኑዕ የሆነ ቃል ኪዳን ከእግዚአብሔር ተቀብለው ታኅሣሥ ፰ ዐርፈዋል። ዛሬም ተጋድሏቸውን በፈጸሙበትና እግዚአብሔርን ባገለገሉበት ቦታ በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታኅሣሥ ፰ ዓመታዊ በዓላቸው፣ በየወሩም ማለትም ወር በገባ በ፰ ደግሞ ወርኃዊ መታሰቢያቸው ይከበራል። ከጻድቁ በረከት ያድለን አሜን።
(ምንጭ ገድለ ተክለ አልፋና በገዳሙ የተዘጋጀ የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ገዳም አጭር ታሪክ የሚዘክር መጽሔት)
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 3199
ውድ አንባብያን በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዐምዳችን የነገረ ሥጋዌን ጉዳይ በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊና የመጻሕፍት መምህር የሆኑትን መምህር ሥሙር አላምረውን ጋብዘናል። መምህር ሥሙር የመጻሕፍተ ሐዲሳትና የመጻሕፍተ ሊቃውንት ትርጓሜ መምህር ሲሆኑ፡ ፈቃደኛ ሆነው ከቦታችን ተገኝተውልን ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ንባብ።
ሐመር፡- መምህር ነገረ ሥጋዌን መሠረት ያደረጉና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ለምናነሣቸው ሐሳቦች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለ ሆኑልን አስቀድመን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።
መምህር ሥሙር አላምረው፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
፩. ሐመር፡-በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከሚዘመሩት መዝሙራት መካከል አንዱ ነቢዩ ዳዊት “በኃይል ቀን በቅዱሳን ብርሃን ከአንተ ጋር ነበርሁ” (መዝ.፻፱፥፫) የሚለው ነው። ነቢዩ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህ የኃይል ቀን የተባለውስ መቼ ነው?
መምህር ሥሙር አላምረው፡- ይህ ዕለተ ኀይል የተባለው በርካታ ዝርዝሮች አሉት። የተወሰኑትንና በተለይም ከነገረ ሥጋዌው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ብቻ እንመለከታለን። ይህ ዕለተ ኀይል የተባለው፡-
ሀ.የመጀመሪያው ዕለተ ፍጥረት ነው። ማለትም ይህ ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር የተፈጠረበት ዕለት ነው። በቅዱሳን ብርሃን የሚለው ደግሞ በቅዳሴሆሙ ለመላእክት ብለው ሊቃውንቱ ይተረጉሙታል። ቅዱሳን መላእክት ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ ያመሰገኑበት ቀን የኃይል ቀን ይባላል። በዚህች ቀን ቀዳማዊ ወልድ ከቀዳማዊ አብ ጋር ነበር ብሎ ነቢዩ ቀዳማዊነትን ለእግዚአብሔር አብም ለእግዚአብሔር ወልድም ሰጥቶ ይናገራል። ተናጋሪው እግዚአብሔር ወልድም እግዚአብሔር አብም ይሆናል።
ይህ ዕለት የኀይል ቀን የተባለበት ምክንያት የዚህ ዓለም ጠበብት ምንም ነገር ቢሠሩ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥተው ሊፈጥሩ አይችሉም። እግዚአብሔር ግን ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሮታልና የኀይል ቀን ይባላል። በዚህ ዓለም ጠበብት የተፈጠሩ በርካታ ነገሮች አሉ። ግን ሰዎች የፈጠሯቸው ከተፈጠረ ነገር ነው። ለምሳሌ- መብራትን ቢፈጥሩ መብራትን ለመፍጠር የሚያስችል ቅንጣት፤ መኪና፣ አውሮፕላን፣ ወዘተ. ቢያዘጋጁ እነዚህን ሁሉ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ቁስ አካላት ያስፈልጓቸዋል። እግዚአብሔር ግን በመጽሐፈ ቅዳሴያችን “ዘእንበለ እሳት አንደደ ወዘእንበለ ማይ አብረደ፤ ያለእሳት እሳትን ፈጠረ፤ ያለ ውኃ ውኃን ፈጠረ” ተብሎ እንደ ተገለጸው ዓለምን ካለመኖር ፈጠረ። ስለዚህ እንዲህ ያለው ድንቅ ተግባር ተከናውኖበታልና ይህ ቀን የኃይል ቀን ተብሏል።
በዚህ በኀይል ቀን እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ነበረ። ለምን ከተባለ በመፍጠር አንድ ናቸውና። ወንጌላዊው ዮሐንስም “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም።” (ዮሐ.፩፥፩) በማለት እንደ ገለጸው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በአንዲት ህልውና የነበሩ ሥላሴ ይህን ዓለም በአንዲት ሥልጣን፣ በአንዲት ፈቃድ ፈጥረዋል። ስለዚህ ‹‹ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ለመፍጠር አብሬው ነበርሁ›› ብሎ እግዚአብሔር ወልድም እግዚአብሔር አብም ይናገራል።
ለ. ዕለተ ፅንስ፡- ይህ ዕለት ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በኅቱም ድንግልና የተፀነሰበት ዕለት ነው። ይህ ዕለት የኀይል ቀን ተብሏል ምክንያቱም ፅንሰቱ ያለ ዘርአ ብእሲ ስለ ሆነ ነው። አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህን ድንቅ ነገር ሲናገር “ለቀዳማዊ ልደቱ አመሥጠሮ ወለደኃራዊ ልደቱ አመንከሮ፤ ቀዳማዊ ልደቱን አረቀቀው፣ ደኃራዊ ልደቱን ደግሞ አስደነቀው” (መጽሐፈ ምሥጢር) በማለት በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን በአድናቆት ይገልጻል።
ይህ ነገር ለምን ተደነቀ ከተባለ ፅንሱ ከአጋንንት የተሠወረ ነው። እንኳንስ ከአጋንንት ከዮሴፍም የተሠወረ ስለ ነበር ዮሴፍ እጅግ ተጨንቆ ነበር። እመቤታችንም ተደንቃበታለች። እንዲሁ የቅዱስ ገብርኤልን ቃል አልተቀበለችውም። እንዴት ይሆናል ወንድ የማታውቅ አንዲት ድንግል እንዴት ልትፀንስ ትችላለች በማለት ጥያቄ አቅርባ ነበር። ነገር ግን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” ሲላት “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” ብላ ተቀበለች። ይህንም ምክንያት አድርጎ ከቅዱስ ገብርኤል የሰማችው ቃል በማኅፀነ ማርያም ተፀነሰ።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የቅዱስ ገብርኤል ቃል ተፀነሰ ማለት አይደለም። ራሱ ባለቤቱ “ላእከ ኮንኩ ለርእስየ ወአብሠርክዋ ለወላዲትየ በአምሳለ ገብርኤል ላእክ፤ ለራሴ መልእክተኛ ሆንኩ ለእናቴም በገብርኤል አምሳል አበሠርኳት” በማለት ተናግሯል። ስለዚህ በገብርኤል አምሳል እናቱን ያበሥር የነበረው እግዚአብሔር ቃል ወይም በገብርኤል ላይ አድሮ ድንግል ማርያምን ያበሠራት እግዚአብሔር ቃል በኅቱም ድንግልና ተፀነሰ። ይህ ዕፁብ ድንቅ የሆነው ምሥጢር ስለ ተፈጸመበት የኃይል ቀን ተባለ። በዚህ ዕለት ‹‹ከአንተ ጋር ነበርሁ›› የሚለው እግዚአብሔር አብ ለማጽናት፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለጠበቅ እግዚአብሔር ወልድ ደግሞ በተለየ አካሉ ለመፀነስ፣ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ለመዋሐድ አድረውባታልና ‹‹ከአንተ ጋር ነበርሁ›› ይላል።
ሐ. ዕለተ ልደት፡- ዕለተ ልደት ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት፤ አምላክ ሰው መሆኑ ሰው አምላክ መሆኑ የተገለጠበት ዕለት ነው። በዚህም ጊዜ “ከአንተ ጋር ነበርሁ” ያለው ከእግዚአብሔር አብ የተለየበት ጊዜ አለመኖሩን ያስረዳል። እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ስለ ተወለደ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተለየ የተባለበት ጊዜ የለም። ይህ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ የተወለደበት ቀን እጅግ ድንቅ ስለ ሆነ የኃይል ቀን ተባለ።
ሌላው የኀይል ቀን የተባለበት ምክንያት እርሱ በተወለደ ጊዜ ጣኦታት ተሰባብረዋል፣ አጋንንት በጣኦታት ላይ ማደር ተስኗቸው ተጨንቀዋል። እንዲያውም አጋንንት እየሄዱ ለአለቃቸው ለዲያብሎስ ጣኦታቱም ተሰባበሩ እኛም በጣኦታት ላይ ማደር አልተቻለንም ብለው ነገሩት። በዚህ ጊዜ “ያ ኢሳይያስ ‘እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች’ (ኢሳ.፯፥፲፬) ብሎ ትንቢት የተናገረለት፣ ሚኪያስም ‘አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆንከአንቺ ይወጣልኛል’ (ሚክ.፭፥፪) ሲል የሰማሁት ሌሎችም ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ተወልዶ ይሆናል” ብሎ ተናገረ። በዚያም ጊዜ በምናሴ ላይ አድሮ ነቢያቱን አስገደላቸው።
መላእክት ከእረኞች ጋር ዘምረዋል፤ እረኛ ዘፈን እንጂ ምስጋና አያውቅም በዚያ ዕለት ግን ከመላእክት ጋር አብረው ዘመሩ። የኃይል ቀን ያስባለው ይህ ሁሉ ነው። በአጭሩ የኀይል ቀን ማለት ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር መጥቶ የተፈጠረበት፣ አምላክ ሰው የሆነበት ሰው አምላክ የሆነበት ዕለተ ፅንስ፤ አምላክ ሰው መሆኑ ሰው አምላክ መሆኑ የተገለጠበት ማለትም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደበት ዕለተ ልደት ነው። ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም ዕለተ ስቅለቱ፣ ዕለተ ትንሣኤው፣ ዕለተ ዕርገቱ፣ ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ዕለት፣ ዕለተ ምጽአቱ ሁሉ የኃይል ቀን ይባላል። በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በአንዲት ፈቃድና በአንዲት ሥልጣን አባታዊና አምላካዊ ሥራውን ይሠራልና በኀይል ቀን ከአንተ ጋር ነበርሁ የሚለው እንዲህ ይተረጎማል።
፪.ሐመር፡- ከላይ እንደ ተመለከትነው የኃይል ቀን ከተባሉት መካከል አንዱ አምላክ ሰው የሆነበት ሰው አምላክ የሆነበት ነው ብለናልና ለመሆኑ አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ስንል ምን ማለታችን ነው?
መምህር ሥሙር አላምረው፡- ‹አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ› ስንል እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ‹ከኃጢአት ብቻ በቀር አምላክ የእኛን ባሕርይ፣ የእኛን ጠባይ፣ የእኛን አካል ገንዘቡ አደረገ› ማለታችን ነው። በሌላ መንገድ ‹አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ› ማለት ‹ልዑሉ አምላክ የትሑቱን ሥጋ ባሕርይና አካል ገንዘብ አደረገ፤ ትሑት የነበረው ሥጋ ደግሞ ባሕርየ መለኮትን፣ አካለ መለኮትን ገንዘቡ አደረገ› ማለታችን ነው።
፫. ሐመር፡- አምላክ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው?
መምህር ሥሙር አላምረው፡- የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ልዩ ልዩ ነጥቦችን ይናገራሉ። የተወሰኑትን ለማየት ያህል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምራት “እስመ አሕዛብ አፍቀሩ አርአያ ወአምሳል እምዕፀው ዘፀረብዎሙ ፀረብት ወበእንተዝ ኮነ ሥጋ ወልድከ፤ አሕዛብ የለዘበ ድንጋይ የተጠረበ እንጨት እያመለኩ የሚታይ አምላክ እንጂ የማይታይ አምላክ ማምለክ አልፈለጉም በዚህም ልጅህ ሥጋን ተዋሐደ” (ሃይ.አበው ዘጎርጎርዮስ ፲፭፥፮) በማለት አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያት ያስረዳል። ሰዎች የሚታይ አምላክ ከፈለጉ ብሎ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ ወዘተ አምላክ ሆኖ መጣ። ስለዚህ አምላክ ሰው የሆነው የሰው ልጅ የማያየውን፣ በእምነት ብቻ የሚከተለውንና የሚያመልከውን አምላክ ማምለክ ስላልቻለ ግዙፍ አምላክ ለግዙፍ አስተሳሰባችን የሚመች ሆኖ መጣ።
ያዕቆብ ዘሥሩግ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችንም ሊቅ “መላ ሕዋሳትን ከእኛ ገንዘብ አደረገ” ይልና ይህን ሲያብራራው ለራሱ ደረትን ገንዘብ አደረገ፤ድንግል ትታቀፈው ዘንድ፤ በኋላም ደግሞ የፈጠረውን አዳምን ይታቀፍበት ዘንድ፣ ለራሱ ጀርባን ገንዘብ አደረገ፤ ለጊዜው የጠፋውን በግ ይሸከምበት ዘንድ በኋላም በዕለተ ዐርብ ተገርፎ፣ ቆስሎ፣ መከራን ተቀብሎ፣ በቁስሉ ቁስላችንን ያድን ዘንድ፤ ለራሱ አፍና ምራቅን ገንዘብ አደረገ፤ የዕውራንን ዐይን ያበራ ዘንድ”(ሃ. አበው ፹፰፥፭-፯) በማለት ያብራራል። ስለዚህ በድንግል ማርያም እቅፍ ላይ ተቀምጦ የሚታይ አካል፣ የሚገረፍ ጀርባ፣ በዕውራን ዐይን ላይ እንትፍ ተብሎ ዕውራንን የሚያበራ ምራቅ፣ ያስፈልገው ነበርና አምላክ ሰው ሆነ።
ሌላው አምላክ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው የሚለውን ስንመለከት ከጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ሴራና ተንኮል እንድንመለከት ያስገድደናል። ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን ሲያስታቸው በእባብ ላይ አድሮ ነው። ስለዚህ ‹‹እሾህን በእሾህ” እንዲሉ ስሕተቱን በመጣበት መንገድ ለመመለስ ነበር። ዲያብሎስ በእባብ ገላ አድሮ አዳምንና ሔዋንን እንዳሳተ እግዚአብሔር ወልድም በሥጋ ተገልጦ ዲያብሎስን ድል ያደርግና አዳምን ነጻ ያወጣ ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ “ወበከመ ተሀብአ ሰይጣን በጕህሉት ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትን በተሠውሮተ ቃለ እግዚአብሔር በዘመድነ፤ ሰይጣን በተንኮሉ በሥጋ ከይሲ እንደ ተሠወረ ድኅነታችንም ቃለ እግዚአብሔር በሥጋችን በማደሩ ተፈጸመልን።” (መቅድመ ወንጌል) እንደ ተባለ የእኛ ድኅነት በዚህ መንገድ ይሆን ዘንድ ፈቅዷልና አምላክ ሰው ሆነ።
በሌላ መንገድ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው የሚለውን ቄርሎስ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅና አረጋዊ መንፈሳዊ የተባለ ሊቅ የተባበሩበት “በሕፃን አምሳል ተገለጠ አንተን ሕፃን ያደርግህ ዘንድ” ይላል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ የተባለ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅም እኛ በመጀመሪያ “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” (ዘፍ.፩፥፳፮) ያለውን ይጠቅስና ‹‹የሰው ልጅ ሁሉ እግዚአብሔርን መስሎ ተፈጥሮ ነበር። ነገር ግን አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ ሲበላ እግዚአብሔርን መምሰሉ ተበላሸ፣ መነሻ ግብራችን ከእኛ ተለይቶን ነበር። ስለዚህ ያ እግዚአብሔርን የመሰለበት ተፈጥሮ ሲበላሽ ራሱ እግዚአብሔር ሰውን መሰለ›› በማለት ያብራራል።
እዚህ ላይ ሁለት መመሳሰሎች ይታያሉ። የመጀመሪያው ‹እግዚአብሔር ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው›ና ‹ሰው እግዚአብሔርን መሰለ›። ሁለተኛው ግን የአምላክ ሰው መሆን ራሱ አምላክ ሰውን ሆኖ መጣ ማለት ነው። ሳዊሮስ የተባለ ሊቅ “ቀዳሚሰ ወሀበነ አርአያሁ ክብርተ ወደኃሪሰ ነሥአ ሥጋነ ህሥርተ፤ በመጀመሪያ ክብርት የሆነች አርአያውን ሰጠን፤ በኋላ ግን የእኛን የጎሰቆለ ባሕርያችንን ከኃጢአት ንጹሕ አድርጎ ገንዘቡ አደረገ።” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ) በማለት ያስረዳል። ስለዚህ ለእኛ ሁለተኛ ልደት ይሰጠን ዘንድ እርሱ ሁለተኛ ተወለደ፤ እርሱ ሁለተኛ ባይወለድ እኛም ሁለተኛ አንወለድም ነበር። እርሱ ፈራሽ በሆነ ሥጋ ተወልዶ እኛ ዘለዓለማዊ የሆነ ልደትን እንድንወለድ አደረገን። አምላክ ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት ይህ ነው።
፬. ሐመር፡- አምላክ ሰው መሆን ያስፈለገው ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ለማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች በሙሉ ለማድረግ ነው ከተባለ ሁሉን የሚችል አምላክ ሰው ሳይሆን ማድረግ አይችልም ነበር ወይ?
መምህር ሥሙር አላምረው፡- ይህን ጥያቄ ከእኛ በፊት የነበሩ ሊቃውንት ጠይቀው መልሱንም መልሰውታል። ኀይለኛ ደካማውን ቢያሸንፍ አይደንቅም። “አኮ መንክር እመ ሞዖ ኃያል ለድኩም መንክርሰ እመ ሞዖ ድኩም ለኀያል፤ ኀይለኛ ደካማውን ድል ቢያደርግ አይደንቅም የሚያስደንቅ ግን ደካማ ኀይለኛውን ድል ማድረጉ ነው። ይህም ደካማ ሥጋ ኀይለኛውን ዲያብሎስ ድል ማድረጉ ነው እንጂ ኀያሉ መለኮት ደካማውን ዲያብሎስ ድል ማድረጉ አያስደንቅም። ስለዚህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሔዋንን ከዲያብሎስ ግዞት ነፃ ያወጣቸው በደካማ ሥጋ እንጂ በኀያል መለኮት አይደለም። በእርግጥ ደካማ ሥጋ ከኀያል መለኮት ጋር ተዋሕዷል።
በመሆኑም የዲያብሎስ መሸነፍ የክርስቶስ ማሸነፍ በደካማ ሥጋ መሆኑ ነው እንጂ የሚያስደንቀው በኃያል መለኮት ቢሆን አያስደንቅም ነበር። ስለዚህ በዚህ ድንቅ በሆነ ጥበቡ እኛን ያድነን ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ።
በሌላ መልኩ ደግሞ ኪዳን ወይም ትምህርተ ኅቡአት በተባለ መጽሐፍ ላይ እንደ ተገለጸው “አርአያ ዘኢይማስን ዘቦቱ በአርአያ ዘይማስን ተነሥተ፤ የማይሞት አካል ያለው ዲያብሎስ በሚሞት ሥጋ ድል ተነሣ” (ትምህርተ ኅቡአት) ይላል። ስለዚህ የማይሞተው መለኮት ዲያብሎስን ድል አድርጎት ቢሆን አይደንቅም ነበር።
እንዲሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ፍቅር አይታወቅም ነበር። ፍቅሩ ድንቅ ይሆን ዘንድ ከሚራብ፣ ከሚጠማ፣ ከሚታመም፣ ከሚሞት ሥጋ ጋር ተዋሐደና ረሀብ፣ ጥም፣ ሕማም፣ ሞት ወዘተ. የማይስማማውን ዲያብሎስን ድል አደረገው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ፍጹም ፍቅር በቅዱስ ወንጌልም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና” (ዮሐ.፫፥፲፮) ተብሎ እንደ ተገለጸው እንዲሁ መውደዱን ይገልጽልን ዘንድ ዋጋ ከፈለልን። ስለ ወደደን ተወለደልን፣ ስለ ወደደን ተገረፈልን፣ ስለ ወደደን ተሰቀለልን፣ ዋጋ ከፍሎ መውደድና ዋጋ ሳይከፍሉ መውደድ የተለያየ ስለ ሆነ እጅግ የሚያስደንቅ ዋጋ ከፈለልን።
ይህን በተመለከተ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “ፍቅር ሰሀቦ ለወልድ ኀያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት፤ ኀያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው” (ቅዳሴ ማርያም) በማለት እንደ ገለጸው የጽንዐ ፍቅሩ መገለጫ ይሆን ዘንድ የማይሞት መለኮት ከሚሞት ሥጋ ጋር ተዋሐደ፤ የማይራበው መለኮት በሚራብ ሥጋ ተራበ፣ የማይሞተው መለኮት በሚሞት ሥጋ ሞተ።
ቄርሎስ የተባለ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ደግሞ “ወረደ ከመ ያዕርገነ ለነ ኀበ ሀገሩ አርያማዊ ኀበ ሀሎ አቡሁ፤ የባሕርይ አባቱ ካለበት ሰማያዊ ሀገሩ ያገባን ዘንድ እርሱ ወደ እኛ ወረደ” (ሃ/አበው) በማለት ተናገረ። ይህን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “ልባችሁ አይደንግጥ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ” (ዮሐ.፲፬፥፩) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ነገራቸው ሰማያዊውን ርስት ያወርሰን ዘንድ ሰው ሆነ።
እንግዲህ ጽንዐ ፍቅሩን ይገልጽልን ዘንድ በሚደክም፣ በሚታመም፣ በሚራብ ሥጋ ተገለጠ፣ በተዋሐደው ሥጋ ተራበ፤ ተጠማ፤ ተገረፈ። መለኮት የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚታመም፣ የሚሞት ባሕርይ የለውም ስለዚህ ሰው ሆነ የሚታመም፣ የሚገረፍ፣ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚሞት አካል ያለውን ገንዘብ ሁሉ ገንዘቡ ለማድረግ አምላክ ሰው ሆነ።
በዚህ ክፍል ‹አምላክ ሰው ሆኖ ያደረጋቸውን የማዳን ሥራዎች ሁሉ ሰው ሳይሆን ማድረግ አይችልም ነበር ወይ?› ለሚለው ጥያቄ መልሱ ‹ይችላል› ነው። ነገር ግን ከላይ በዘረዘርናቸው ምክንያቶች ሰው ሆነ እንዳልን ሁሉ ለመጨረሻ አረአያነቱን ሊያድለን ሰው ሆነ። አረአያነት በተግባር የሚገለጽ ነው። መለኮት የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚቸገር፣ የሚታመም፣ የሚሞት ባሕርይ የለውም። ጹሞ ‹‹ጹሙ›› ሊለን፣ ተርቦ ‹‹ተራቡ›› ሊለን፣ ተጠምቶ ‹‹ተጠሙ›› ሊለን ሰው ሆነ። በቅዱስ ወንጌልም “ቀንበሬን በላያችሁ ላይ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ።” (ማቴ.፲፩፥፳፱) እንዳለን እኛ እንድንጠቀምበት የምንሠራውን ሁሉ አስቀድሞ እርሱ ፈጽሞልናል። ስለዚህ ጹሞ ‹‹ጹሙ›› ለማለት ተርቦ ‹‹ተራቡ›› ለማለት፣ ተሰዶ ‹‹ተሰደዱ›› ለማለት፣ ተገርፎ ‹‹ተገረፉ›› ለማለት የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚሰደድ፣ የሚገረፍ፣ የሚሞት ሥጋ ያስፈልገው ስለ ነበር አምላክ ሰው ሆነ።
- Details
- Written by: በክፍለ ማርያም
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1634
የበዓል ምንነት
በዓል፡- “አብዐለ አከበረ፣ አስከበረ፣ አበለጠገ፣ ሰውን ባዕል፣ ዕለትን በዓል አደረገ” በማለት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በሚል መጽሐፋቸው ይፈቱታል። (ኪዳነ ወልድ፣ገጽ ፪፻፸፰) እርሳቸው አክለውም “በዓል፡- በቁሙ የደስታ የዕረፍት ቀን፣ በዓመት፣ በወር፣ በሳምንት የሚከበር ያለፈ ነገር የሚታሰብበት ተዝካር፣ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎትና ለብሶ፣ አጊጦ የሚዘፍንበት፣ የሚዘምርበት፣ ዕልል የሚልበት፣ ሽብሸባ ጭብጨባ፣ … የሚያደርግበት፣ …” በማለት ሰፊ ማብራሪያ ይሰጡበታል። (ዝኒ ከማሁ)። ከዚህ ገለጻ የምንረዳው በዓል በደስታ የሚከበር የሚያጌጡበት፣ የሚደሰቱበት፣ የሚዘምሩበት፣ ወዘተ እንደሆነ ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም በመዝሙሩ “ግበሩ በዓለ በትፍሥሕት፤ በደስታ በዓልን አድርጉ” (መዝ.፻፲፯፥፳፯) በማለት እንደገለጸው በዓል ሰዎች ደስ ብሏቸው የተደረገላቸውን እያስታወሱ የሚያከብሩት ዕለት ነው።
በዓል የደስታ ዕለት በመሆኑ ምክንያት ሰዎች ለበዓሉ የሚገባውን ድግስ በማዘጋጀት ለመብላት ለመጠጣት ደስታን ለማድረግ ይሰባሰባሉ። ይህ ማለት ግን ለሥጋዊ መብልና መጠጥ ብቻ የሚጨነቁበት፣ ሥጋቸውን ብቻ ደስ የሚያሰኙበት ነው ማለት አይደለም። መንፈሳዊውን ምግብም ተመግበው መንፈሳቸውን ደስ የሚያሰኙበት፤ መሆንም ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ከላይ በርእሱ “በዓል በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን ጥራ” (ሉቃ.፲፬፥፲፫) ተብሎ እንደተገለጸው በዓል የሚያደርገው ሰው እነማንን መጥራት አለበት? እነማንንስ መጥራት የለበትም? የሚለውን ሙሉ ቃሉን በመጥቀስ ለማብራራት እንሞክራለን።
“በበዓል ምሳ ወይም ራት በምታደርግበት ጊዜ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን፣ ዘመዶችህንና ጎረቤቶችህን፣ ባለጸጎች ባልንጀሮችህንም አትጥራ፤ እነርሱም ይጠሩሃልና፤ ብድርም ይሆንብሃልና። ነገር ግን በበዓል ምሳ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፤ ዕውሮችን፣ እጅና እግርም የሌላቸውን ጥራ። አንተም ብፁዕ ትሆናለህ የሚከፍሉህ የላቸውምና፤ ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ” (ሉቃ.፲፬፥፲፪-፲፬) እንዲል። ይህ ቃል የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምሳ ግብዣ ከተጠሩት አንዱን ሰው በዚህ መልኩ አስተምሮታል። ለጊዜው ለሰውየው የተሰጠው ይህ ትምህርት ሰዎች እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ሲማሩበት ይኖራል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምንባብ በተናገራቸው መሠረታዊ ነጥቦች ውስጥ ብድር መመለስ የሚችሉና የማይችሉ ሁለት አካላት ይገኛሉ።
ሀ. ብድር መመለስ የሚችሉ፡- እነዚህ አካላት በወዳጅነት፣ በቤተ ሰብነት፣ በባለጸግነት፣ በጎረቤትነት መልኩ የሚጠሩ ናቸው። እነዚህን አትጥራ ተብሏል። ምክንያቱ ደግሞ እነርሱ ብድር ይመልሳሉና የሚለው ነው። “ወዳጆችህንና ወንድሞችህን፣ ዘመዶችህንና ጎረቤቶችህን፣ ባለጸጎች ባልንጀሮችህንም አትጥራ፤ እነርሱም ይጠሩሃልና፤ ብድርም ይሆንብሃልና።” (ሉቃ.፲፬፥፲፪) እንዲል። ይህ ሐሳብ የሚያስረዳው ሰዎች ብድር የሚመልሱ ከሆነ ስጦታው ለሌላው ቀን እንዲሆን ማበደር እንጂ ስጦታ አይሆንም። ስለዚህ “ብድር የሚከፍሉህን አትጥራ” በማለት ተናገረ።
ይህ ሲባል ግን መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች እርስ በእርስ እየተጠራሩ መብላት መጠጣትን፣ በአንድነት መኖርን እየነቀፈ አይደለም። ሆኖም ይህን የተናገረው ስጦታ እንዲሆን ብድሩን ሳያስብ፣ ምን ይመልሳሉ፣ ምን አይመልሱም የሚለውን ሳያስብ በነፃ ሰጥቶ መንግሥቱን መውረስ የሚያስችል ሥራ እንዲሠራ ለማስተማር ነው።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ፍቅር ባስተማረበት አንቀጽም “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁንም መርቁ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሏችሁና ስለሚያሳድዷችሁ መልካም አድርጉ።…የሚወዷችሁንማ ብትወዱ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንደዚህማ ቀራጮችስ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን?” (ማቴ.፭፥፵፫-፵፯) በማለት እንዳስተማረ ክርስትናችን ከአሕዛብና ከቀራጮች የተለየና እውነተኛ ይሆን ዘንድ ብድራት ሳንጠብቅ፣ ውለታ ይመልሱልናል ሳንል በነጻ እንድናደርገው በዓል ስናከብርም ብድር የሚመልሱትን አትጥራ በማለት አስተማረ።
ለ. ብድር መመለስ የማይችሉ፡- እነዚህ አካላት፣ በድህነት፣ በችግር፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ ያሉ ድሆችና ጦም አዳሪዎች ናቸው። ድሆችና ጦም አዳሪዎች ድግሞ ብድር መመለስ አይችሉም። “ነገር ግን በበዓል ምሳ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፤ ዕውሮችን፣ እጅና እግርም የሌላቸውን ጥራ። አንተም ብፁዕ ትሆናለህ የሚከፍሉህ የላቸውምና፤ ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ” (ሉቃ.፲፬፥፲፫-፲፬) እንዲል።
ድሆችና ችግረኞች፣ ዕውሮች፣ እጅና እግርም የሌላቸው ወዘተ ተብለው የተዘረዘሩት አንዳንዶቹ ሊለምኑ ያፈሩ፣ ሊሠሩ የተቸገሩ የሕይወት መንገዱ የጠፋባቸው ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ የአካል ጉዳተኛ ሁነው መሥራት የማይችሉ ሕይወታቸውን በልመና ብቻ እንመራለን ብለው የሚያስቡ ናቸው። ስለዚህ ለእነዚህ ወገኖቻችን ቋሚ የሆነ መተዳደሪያ የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር ባይቻል እንኳን በበዓል ወቅት የምሳ ወይም የራት ግብዣ በሚዘጋጅበት ጊዜ ቅድሚያ ለእነዚህ አካላት መስጠት አስፈላጊ ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብድር የሚከፍሉትን ሳይሆን ብድር መክፈል የማይችሉትን ጥራ በማለት ያስተማረው ለዚህ ነው።
ሰው ምጽዋት ሲሰጥ ብድሩን ከእግዚአብሔር አገኘዋለሁ ብሎ መስጠት እንዳለበት ያስተምረናል። በመጨረሻም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው “ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ” (ሉቃ.፲፬፥፲፬) የሚለውን ነው። ዋጋውን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰዎች አይደለም። ወይም ካበላቸውና ካጠጣቸው፣ በወቅቱ ምሳ ወይም ራት ከጋበዛቸው የሚያገኘው የእራት ወይም የምሳ ግብዣ አይደለም። ስለዚህ “እንዲህ ማድረግ የማይችሉትን ጥራ” በማለት አስተማረ።
መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ እንደ ስጦታውም መልሶ ይከፍለዋል” (ምሳ.፲፱፥፲፯) በማለት እንደተናገረው ሰዎች ድሆችን በችግራቸው ሁሉ ሲረዱ ተበዳሪው እግዚአብሔር መሆኑን ልናስተውል ይገባል። በትምህርተ ኅቡአት “ዘየአሢ ተወካፊ፤ የሚሰጥ ተቀባይ” ተብሎ እንደተገለጸ በባለጸጋዎች ላይ አድሮ ይሰጣል፤ በድሆች ላይ አድሮ ይቀበላል። ስለዚህ የቸርነት ሥራ የሚሠራ ሰው ለእግዚአብሔር እንዳደረገ ተበዳሪውም እግዚአብሔር እንደሆነ ቆጥሮ ላላቸው ሳይሆን ለሌላቸው መርዳት አለበት።
መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ ወንጌል “ሀብታችሁን ሸጣችሁ ምጽዋት ስጡ፤ ሌባ በማያገኝበት ነቀዝም በማያበላሽበት የማያረጅ ከረጢት የማያልቅም መዝገብ በሰማያት ለእናንተ አድርጉ” (ሉቃ.፲፪፥፴፫) በማለት ያስተማረው ዋጋው ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነ ሲያስረዳን ነው። ሰማያዊው ዋጋ ደግሞ አያልቅም፤ አያረጅም፤ ሌባ ወንበዴ የሚያገኘው አይደለም። ይህ የማያልቀው፣ የማያረጀው፣ ሌባ ወይም ወንበዴ የማይወስደው ሰማያዊ ዋጋ ደግሞ የሚገኘው ለባለጸጎችና ለቤተ ዘመድ በማብላትና በማጠጣት ሳይሆን ለድሆችና ለአካል ጉዳተኞች ወይም ለጦም አዳሪዎች በማብላትና በማጠጣት ነው።
ቆርነሌዎስ የተባለው የመቶ አለቃም ምጽዋት የሚያደርግ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር። በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሁኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል” (ሐዋ.፲፥፬) በማለት ያደረገውን ምጽዋትና ጸሎት እግዚአብሔር እንደተቀበለለት፣ መልካም ዋጋውንም እንደሚያገኝ አስረዳው። እንግዲህ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሁኖ ወደ እግዚአብሔር አዐርጓል” ማለት ዋጋው በሰማይ ታላቅ ሆኖ እግዚአብሔርም ተቀብሎለት መልካምና ሰማያዊ ዋጋን ልታገኝበት እግዚአብሔር ፈቅዷል ማለት ነው።
ነባራዊ ሁኔታው ምን ይመስላል?
ዛሬ ዛሬ የበዓል አከባበር ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ሰዎች በዓል ያደርጋሉ፣ ይደግሳሉ፣ ሰውም ይጠራሉ። ይሁን እንጂ የሚጠሩት ዘመዶቻቸውን እየፈለጉ፤ ምን አልባትም እነርሱ በዓል ከማድረጋቸው በፊትም ሆነ በኋላ እየጠሩ ያበሏቸውና ያጠጧቸውን ይጠራሉ እንጂ ድሆችን እየፈለጉ አይጠሩም። ከዚህም እልፍ ሲል በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጁ ነገሮች ከበዓሉ ምንነት ጋር የማይሄዱ ናቸው። ለምሳሌ የምሽት ክበቦች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የዳንስና የጭፈራ ዝግጅቶች በዓሉን ምክንያት በማድረግ እየተባሉ ማስታወቂያ የሚነገርላቸው ለእንደነዚህ ያሉት ተግባራት ነው። ይህ ደግሞ ሰው በዓሉን ምክንያት በማድረግ ወደቤተ ክርስቲያን ልሂድ ሳይሆን ወደተዘጋጀው ጭፈራ ቤትና ዝሙት ወደሚስፋፋበት ቦታ ልሂድ እንዲል ያደርገዋል።
በዓል በመጣ ቍጥር ሰዎች ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሳይሆን ለሥጋዊ ደስታቸው እንዲጨነቁ ለድኅነተ ነፍሳችን ስለሚሠዋው አማናዊ መሥዋዕት ሳይሆን ለሥጋዊው ድግስ እንዲጨነቁ ያውም ከዘመድ ዘመድ አማርጠው ለመጥራት፣ ታላቅ የሚሉት ሰው ቤታቸውን ስላላየላቸው የሚያስቡበት ሁኔታ እንደ ሥርዐት ወይም እንደባህል እየተቆጠረ ሲመጣ ይስተዋላል።
በበዓል ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን የተወሰደው ምግብም ቢሆን በመጀመሪያ ታላላቅ የተባሉ ሰዎች ተመግበው ሲተርፍ ችግረኞች ሊታሰቡ ይችላሉ። ምን አልባትም ሲተርፍ ይሰጣችኋል ሲባሉ ቆይተው አልተርፍ ብሎ አለቀ የሚባሉበትና ምንም ነገር ሳይቀምሱ እንደለመደባቸው ረኀባቸውን መጠጊያ አድርገው የሚመለሱበት ጊዜም ይስተዋላል። የሚበላውና የሚጠጣው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ አይተው ረኀባችንን እናስታግሣለን ብለው ተስፋ ሲያደርጉ ግን ከቤታቸው የሚበሉትና የሚጠጡት ያልጎደለባቸው ሰዎች በልተውትና ጠጥተውት ያልቅና ምንም ሳይቀምሱ ይመለሳሉ።
መፍትሔው ምን መሆን አለበት?
ከላይም እንደተገለጸው ሰዎች ባንድነት ተሰብስበው እግዚአብሔርን እያመሰግኑ የተገኘውን ቢበሉና ቢጠጡ ጥፋት ነው ማለት አይደለም። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው።” (መዝ.፻፴፪፥፩) በማለት እንደገለጸው በአንድነት ተሰባስበው የእግዚአብሔርን ስም የእመቤታችንን ስም፣ የቅዱሳንን ስም፣ ወዘተ እየጠሩ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የተገኘውን እየበሉና እየጠጡ ቢኖሩ ጥፋት አይደለም።
ዋናው ትኩረት መሰጠት ያለበት ጉዳይ በሚሰበሰቡበት ጊዜ የተዘጋጀው ምግብ ከማለቁ አስቀድሞ ለድሆች መታደል ይኖርበታል። ምክንያቱ ደግሞ ባለጸጎች ከቤታቸውም ሄደው የሚበሉትና የሚጠጡት ስለ አላቸው ነው። ስለዚህ ቅድሚያ ለድሆችና ለችግረኞች ሊሰጥ ይገባል። ቤተ ክርስቲያንን መጠጊያ አድርገው እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የተጠለሉት ችግረኞች ቢያንስ በዚህ ጊዜ መመገብ አለባቸው።
በዓለ ልደት ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን የሰው ልጆች አንድ ላይ የዘመሩበት ነው። ባለጸጎች ቤት አናስገባም ሲሏቸው እንስሳት ትንፋሻቸውን ገብረው የተወለደውን ሕፃን ያሟሟቁበት በዓል ነው። ስለዚህ ዛሬም በዓለ ልደትን ማክበር ያለብን ልዑላኑ መላእክት ከትሑታኑ እረኞች ጋር አብረው እንደዘመሩ ሁሉ ባለጸጎችና ድሆች አብረው የሚያከብሩት በዓል መሆን አለበት። በዓለ ልደትን ያላቸው ባለጸጎች ደግሰው የሚያበሉት የሚያጠጡት ድሆች ደግሞ በክብር ተጠርተው አብረው ከባለ ጸጎች ጋር ተቀምጠው መብላት መጠጣት የሚችሉበት መሆን አለበት።
በዓል ስናከብር ድሆችን መጠየቅ እንዳለብን የሚያስረዳን ተጨማሪ መረጃ እንጥቀስ። በድርሳነ ሚካኤል “በዚህ በዓል ብቻውን የሚበላ የሚጠጣ ደስ የሚለው እየራባቸው እየጠማቸው ድሆችን ጦም አዳሪዎችን ቸል የሚላቸው አይፈለግምና። በዚህ በዓል ደሀው ከሜዳ ወድቆ በብርድ እየተሠቃየ በክብር ልብስ የሚያጌጥ አይፈለግም። ይህ በዓል ደሀው በሜዳ ወድቆ ባጌጡ ቤቶች የሚቀመጡለትን ሰዎች አይፈልግም። ይህ በዓል ደሀው በእስር ቤት እየተጨነቀ በተድላ በደስታ ያለ ልክ የሚበላ የሚጠጣ ሰውን አይፈቅድም። ይህ በዓል ደሀው ታሞ የሚረዳው የሚጎበኘው አጥቶ ሲጨነቅ ብቻውን ራት ወይም ምሳ የሚያደርገውን አይሻም። በወንጌል የተጻፉት ትእዛዛት የሚሉት ይህ ነው” (ድርሳነ ሚካኤል ዘወርኃ መጋቢት ገጽ ፪፻፵፭-፪፻፵፯) እንዲል።
ከላይ የተጠቀሰው ምንባብ በዓል በሚከበርበት ጊዜ ድሆችን መጎብኘት የግድ እንደሆነ ይህ ካልሆነ ግን የበዓሉ ሥርዓት ድሆችን የማይጎበኘውን፣ የማያበላውን፣ የማያጠጣውን፣ የማያልብሰውን እንደማይፈልግ ያስረዳናል። ስለዚህ ከላይ በርእሳችን እንደተገለጸው ከባለጸጎች ይልቅ ድሆችን፣ ከዘመዶቻችን ይልቅ የማያውቁንን፣ ጉልበት ካላቸው ይልቅ አካል ጉዳተኞችን መርዳት ይኖርብናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ብድር ሊከፍሉ የሚችሉትን ሳይሆን ብድር መክፈል የማይችሉትን እንድንረዳም ያስተምረናል።
ይህ ተግባር ዋጋው በሰማይ እንደሆነና ለዚህም በትጋት መሥራት እንዳለብን ሲያስረዳ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔም እላችኋለሁ፤ ባለቀባችሁ ጊዜ እነርሱ በዘለዓለም ቤታቸው ይቀበሏችሁ ዘንድ በዐመፃ ገንዘብ ለእናንተ ወዳጆች አድርጉበት” (ሉቃ.፲፮፥፱) በማለት እኛ ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን የምናደርገው ድሆችንና ችግረኞችን የመጎብኘት ሥራ እነርሱ ደግሞ በዘለዓለም ቤታቸው ይቀበሉናል። እኛ ዛሬ እነርሱን ማብላታችን እነርሱ ደግሞ በሰማያዊው ቤታቸው ያበሉናል፤ ያጠጡናልም።
ባለጸጎችንና ጎረቤቶቻችንን ብንቀበል፣ ብናበላና ብናጠጣ እነርሱም በተራቸው የሚቀበሉን፣ የሚያበሉንና የሚያጠጡን በዚህ ዓለም ነው። ድሆችና ችግረኞች ግን የሚቀበሉን፣ የሚያበሉንና የሚያጠጡን በሰማያዊ ቤታቸው ነው። ስለዚህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓል በምናደርግ ጊዜ በዚህ ዓለም ብድር የሚከፍሉትን ሳይሆን በዚህ ዓለም ብድር መክፈል የማይችሉትን መጥራት እንዳለብን አስተማረን።
ባጠቃላይ በዓል የደስታ ዕለት ያለፈን ነገር እያስታወስን የምንደሰትበትና የተደረገልንን ነገር እያስታወስን እግዚአብሔርን የምናመሰግንምበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለትም መብል መጠጥ ይዘጋጃል። ሰዎች ይሰበሰባሉ፣ በእግዚአብሔር ስም፣ በእመቤታችን በቅድሰት ድንግል ማርያም ስም፣ በቅዱሳን ስም እየተሰበሰቡ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይበላሉ ይጠጣሉ። በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልም እንዲሁ ሰዎች እየተጠራሩ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ፤ ዘመድ ከዘመድ ይጠያየቃሉ። ይሁን እንጂ የዘመድ መጠያየቂያ ከመሆን ባሻገር ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፣ ዕውሮችን፣ እጅና እግር የሌላቸውን ብድር መመለስ የማይችሉትን እንዳንዘነጋ መዘንጋት ብቻ ሳይሆን ብድር መመለስ ከሚችሉት ከዘመዶቻችንና ከባለጸጎች ይልቅ ቅድሚያ ሰጥተን እንድናበላቸውና እንድናጠጣቸው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል። በተማርነው ትምህርት ተጠቅመን፣ ከባለጸጎችና ከዘመዶቻችን ይልቅ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፣ ዕውሮችን፣ እጅና እግር የሌላቸውን አስበናቸው የተቻለንንም አድርገንላቸው የበዓሉን በረከት እንዲያድለን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን።