- Details
- Written by: አባ ፍቅረ ማርያም መኩሪያ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 3640
ሱባኤ ቃሉ የግእዝ ሲሆን ሰባት ቁጥር ማለት ነው፡፡ ሰባት ቁጥር ደግሞ በዕብራውያን አቆጣጠር ፍጹም ቁጥር ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ በሰባት በሰባት የተጠቀሱ ነገሮችን ተጽፈው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን በስድስት ቀን ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን አርፎአል (ዘፍ.፪፥፪) ፡፡ ሰው ማለትም ሕያውነት፣ ለባዊነት ነባቢነት እና አራቱ ባሕርያተ ነፍስ ማለትም ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃ፣ መሬት የተስማሙለት ማለት ነው፡፡ ሌላም በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ጥበብ ቤትን ሰራች ሰባት ምሶሰዎቿን አቆመች›› (ምሳ.፱፥፩) በማለት ተናግሯል። ጥበብ የተባለው ወልድ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴው ‹‹ጥበብሰ መድኃኒነ ውእቱ፤ ጥበብ ግን መድኃኒታችን ነው›› እንዲል። ቤት የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናት ሰባት ምሰሶዎች ተብለው የተነገሩት በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሰባትን ፍጹምነት የሚያስረዱ ሌሎችም አሉ፡፡ ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት “ስለ እውነት ፍርድህ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ፡፡” (መዝ.፻፲፰፥፻፷፬) ሰባቱ ሊቃነ መላእክት (ራእ. ፰፥፪) በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት ተመለከትኩ እንዲል። እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት የሚያስረዱ ለምሳሌነት የተጠቀሱ ናቸው፡፡
ሌላው ሱባኤ ማለት በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋት፣ ወዘተ… ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ በቁርጥ ኅሊና፣ በተዘጋጀ ልቡና፣ በቤት፣ በገዳም ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ነው፡፡ ሰባቱን ዕለታት አንድ እያለ በመቍጠር ሰው እንደ ፍላጐቱ አንድ ሱባኤ ሰባት ቀን፣ ሁለት ሱባኤ ዐሥራ አራት ቀን፣ ሦስት ሲባኤ ሃያ አንድ ቀን… እግዚአብሔርን ደጅ ለመጽናት በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ሳምንቱን በመንፈሳዊ ትሩፋት የሚጠመድበት ማለት ነው፡፡
- Details
- Written by: በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1682
በቅድሚያ ለሁላችሁም ሰላመ እግዚአብሔር ይድረሳችሁ! ሞት በነገሠበት ቸነፈር ጥላውን በጣለበት ዓለም ውስጥ በሕይወት ጠብቆ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ለእመቤታችን የትንሣኤ እና የዕርገት በዓል በሰላም ስላደረሰን ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን !
ከነሐሴ ፩-፲፮ ጾመ ፍልሰታን ጾመን በነሐሴ ፲፮ የምናከብረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል ነው። ለጾሙ ምክንያት የሆኑት የእመቤታችን እረፍት፣ ትንሣኤ እና ዕርገት ናቸው። ጾሙን የጾሙት ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ የጾሙበት ምክንያት የእመቤታችን ጉዳይ እረፍት፣ ፍልሰት፣ ዕርገት ስለ ሆነ ጾመ ፍልሰታ ለማርያም በሚል ስያሜ ይጠራል። በተጨማሪም በጸዋሚዎች ጾመ ሐዋርያትም ይባላል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አክብራ ከተቀበለቻቸው ሰባት አጽዋማት ሰፍራ ቆጥራ ለምእመናን አስተምራ ከምትጾማቸው አንዱ ጾመ ፍልሰታ ለማርያም የሚባለው ጾም ሲሆን ጾሙ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በልዩ ፍቅር የሚወደድ ጾም ነው ።
ከስያሜው ስንነሣ ጾም እና ፍልሰት የሚሉ ሁለት ቃላትን አጣምሮ ጾሙን እና የጾሙን ምክንያት አስተባብሮ የሚገልጥ ነው ። አሁን የምንመለከተው ጾም የሚለውን ሳይሆን ለጾሙ መነሻ የሆነውን የእመቤታችንን ዕርገት ነው ። ይህን የእመቤታችንን የእረፍት ፣የትንሣኤ እና የዕርገት በዓል ስናስብ በእግረ ኅሊና ወደ ኋላ ተመልሰን ወደ ፵፱ ዓመተ ምሕረት እንጓዛለን። እመቤታችን ያረፈቸው በ፵፱ ዓ.ም ጥር ሃያ አንድ ቀን ሲሆን የተነሣችው እና ያረገችውም በዚያው ዓመት ነሐሴ ወር አሁን ፍልሰታ ለማርያም ብለን በምናከብረው ወቅት ነው። ይህም ማለት የዛሬ ፲፱፻፷፫ ዓመት በዘመነ ማቴዎስ የተከናወነ ነው :: ፍልሰታ የሚለው የግእዝ ቃል ፈለሰ ተሰደደ ከሚል ግሥ የወጣ ቃል ነው ዐውዳዊ ፍችውን ስንመለከት እንደየአገባቡ ልዩ ልዩ ትርጉም ይሰጣል። መፍለስ፣ መሰደድ፣ መለየት፣ ቦታን መልቀቅ፣ መሰወር፣ ከሰው ርቆ መኖር፣ እርገት ወዘተ ••• ተብሎ ይተረጎማል።
ፍልሰታ ለማርያም ሲባል የእመቤታችንን ከዚህ ዓለም በሞት መለየትን በትንሣኤ ከመቃብር መውጣትን በዕርገት ከምድር ወደሰማይ ማረግን የሚገልጽ ቃል ነው :: እመቤታችን በዚህ ዓለም ስድሳ አራት ዓመታትን ኖራለች። በእርግጥ የዚህ ዓለም ኑሮ መኖር አይባልም መኖር ከሚለው መቆየት የሚለው ይስማማዋል መቆየት ጊዜያዊነትን ሲያሳይ መኖር የሚለው ደግሞ :: ዘለዓለማዊነትን ገላጭ ነው ::
የዚህ ዓለም ቆይታዋ በንጽሕና በቅድስና ያጌጠ ንጽሕናን ቅድስናን ለዓለም የገለጠ ክብሯም ከፍጡራን የበለጠ እና ለማንም ያልተሰጠ ነው ::
በዚህች ምድር ላይ “ቀደስኩከ እምከርሰ እምከ፤ በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ” (ኤር.፩፥፭) ከተባለ ከኤርምያስ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ በኤልያስ ግብር ጸንቶ ይኖራል ከተባለለት ከዮሐንስ መጥምቅና ከሌሎችም በቅድስና ከኖሩ በንጽሕና ከከበሩ ቅዱሳን በተለየ ቅዱስ ሕይወት የነበረች ፣ያለችና የምትኖር ናት። ልዩ የሚያደርጋትም ክብሯና ቅድስናዋ እንደ ሌሎች ቅዱሳን ጤዛ ልሶ ደንጊያ ተንተርሶ ድምፀ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ታግሶ እንደ ሰማዕታት ከነደደ እሳት ገብቶ አንገትን ለሰይፍ ስለት፣ ሰውነትን ለእሳት ሰጥቶ በገድል የተገኘ አይደለም። የእግዚአብሔር እናት ለመሆን ሰው ሊያውቀው አእምሮ ሊያራቅቀው በማይችል ድንቅ የእግዚአብሔር ጥበብ በመመረጥ የተገኘ እንጂ። የእመቤታችን ክብሯ ልዩ ነው ከሰማያውያን መላእክት ከምድራውያን ደቂቀ አዳም ይልቅ እጅግ የተለየች እና የተመረጠች ናትና ። ክብሯ ልዩ ነው የመመረጧ ግብርም ድንቅ ነው። የሔዋን ልጆቿ በቁጥር እጅግ ብዙ ናቸው መርገሟን ማስወገድ ዕዳ በደሏን ማሰረዝ የቻለች የሔዋን ዕዳ ከፋይ የሆነች ግን እመቤታችን ብቻ ናት ።
ጥበበኛው ሰሎሞን በመኃልዩ ይህን ሲያስረዳ “ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ ንግሥታትና ቍባቶችም አመሰገኑአት።” እንዲል (መኃ. ፮፥፱) የሔዋን ጆሮ ምክረ ከይሲን ሰምቶ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላትን አመጣ የሰው ልጆችን ከገነት አስወጣ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ቦታ፣ ልጅነትን ያህል ክብር ገነት መንግሥተ ሰማያትን ያህል ሀገር አሳጣ ይህ ሁሉ የሆነው በሄዋን ምክንያት ነበር። ይህ የተገለበጠው ደግሞ በቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ነው። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሃይማኖተ አበው ይህን ሲገልጽ “ነገር ግን ሔዋንን ዲያብሎስ አሳታት የሞት ምክንያት የሚሆን ቃየልን ወለደች ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ሁሉን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች። የሔዋን ልብላ ልብላ ማለቷ ዕፀ በለስ የሞት ምክንያት እንደሆነ አስረዳ በዚያም ዕፅ አዳም ተድላ ደስታ ካለበት ከገነት ወጣ ከድንግል የተወለደ አካላዊ ቃል ግን መስቀል የድኅነት ምክንያት እንደሆነ ገለጠ በዚያም መስቀል ቀማኛ ወንበዴ የነበረው ሰው ከአባቱ ከአዳምና ከቀደሙ አባቶች ሁሉ ጋር ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ገባ” (ሃ.አበ. ፷፯፥፬-፭) በማለት አስረድቷል።
ይህም የሚያስረዳን የሔዋን ዕዳ በደል የተወገደው በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማካኝነት ነው። ዓለም በሔዋን ምክንያት ከገነት ሲሰደድ በድንግል ማርያም አማካኝነትም ወደ ገነት ተመልሷል። ሊቃውንቱ መልክአ ውዳሴ በተባለ ድርሰት “ለሔዋን እምነ ከይሲ ዘአስሐታ እግዚአብሔር ናዘዛ ኪያኪ በወሊዶታ፤ ከይሲ ያሳታት እናታችን ሔዋንን አንቺን በመውለዷ እግዚአብሔር አረጋጋት” በማለት የሔዋን ኃዘን የተወገደው፣ ሔዋን ከሞት ወደ ሕይወት ከሲኦል ወደገነት የተመለሰችው ድንግል ማርያምን ያመሰግናሉ።
በቅዱስ መጽሐፍ “አዳምም ለሚስቱ ሔዋን” ብሎ ስም አወጣ። የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም። እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔደን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። አዳምንም አስወጣው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔደን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።” ዘፍ ፫÷፳-፳፬ ተብሎ የተገለጽውን ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም “በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ-በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋብን ዳግመኛ በድንግል ማርያም ተከፈተልን” በማለት በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ እንደገለጸው የሰው ልጆች ጥያቄ መልስ ያገኘው በእመቤታችን ነው። ዳግማይ አዳም ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔር አካላዊ ቃልን ወልዳልናለችና።
ከሔዋን በተለየ ግብር ጸንታ ከሔዋን የተገኘች ስትሆን ከሔዋን ተለይታ ለሰው ልጆች ሕይወትን የሚሰጠውን ወለደችልን። በዚህ ልዩ ምሥጢር እግዚአብሔር ከእርሷ ተወልዶ ተገለጠ ሞት በሕይወት ተለወጠ ። ለዘመናት በሰው ልጆች ላይ ሠልጥኖ የነበረው ዲያብሎስ ደነገጠ ሞት የሰውን ልጅ ገድሎ ወደ መቃብር ይሸኘዋል። በዚህም መንገድ ሥጋ በመቃብር ሲፈርስ ሲበሰብስ ነፍስም በፍዳ ተይዛ በሲኦል ተግዛ ትኖር ነበር ከእርሷ የተወለደው አምላክ ወልደ አምላክ በሞቱ ሞተ ነፍስን ደመሰሰልን የሞተ ነፍስ መነሻ የመከራ ነፍስ መገስገሻ የነበረውን ሞተ ሥጋን የትንሣኤ እና የዕርገት መናገሻ አደረገልን ። አስደንጋጭ የነበረው ሞት የሕይወት መንገድ መሆኑ በክርስቶስ ሞት ተገለጠ። በትንሣኤውና በዕርገቱ ይበልጥ ተረጋገጠ። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያስረዳ “ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ስለዚህ ነገር ሙታንንም ሕያዋንንም ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአልና ሕያውም ሆኖአልና።” (ሮሜ ፲፬ ÷፯-፱) በማለት ገልጾአል።
እመቤታችንም የሞተችው ሞት ይህን መሰል ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የናፈቁት ሞት ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ የነበሩ አበው ከሞቱት ሞት ይለያል። ያኛው ፍዳን ያስከትላል ይህኛው ግን ሕይወትን የሚያስከትል ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የሚያኖር ነውና። እመቤታችንም ደግሞ ከሁሉም ቅዱሳን ይልቅ በሕይወተ ሥጋ ቅድመ ፀኒስ እግዚአብሔር በረድኤት ያልተለያት ጊዜ ፀኒስ ድኅረ ፀኒስ እግዚአብሔር በኩነት ማለት ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኖ አብሯት የኖረ ከቤተ ልሔም እስከ ቀራንዮ ከመካነ ልደቱ እስከ መካነ ሞቱ ያልተለየችው እግዚአብሔርም ያልተለያት ከፅንስቱ እስከ እርገቱ ለኅሊናችን እሩቅ ለልቡናችን ረቂቅ የሆነውን ምሥጢር ተሸከማ ልዩ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆና የኖረች ናት ።
እርሷ የሞተችው ሞት ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር መሆኑ ግልጥ ነው። ይህንን ነው ፍልሰታ ለማርያም የምንለው ከዚህ ዓለም በሞት ከመቃብር በትንሣኤ ከትንሣኤ ቀጥሎ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረውን ሕይወት ለመኖር መለየት፣ መሰደድ፣ መፍለስ፣ መራቅ፣ መሰወር፣ ዕርገት ነው ፍልሰታ ማለት። ከላይ የጽሑፋችን መነሻ ያደረግነው የቅዱስ ያሬድ ዝማሬ ይህን የሚገልጥ ስለ እመቤታችን ዕርገት የሚያስረዳ ነው። “ተለዐለት እምድር በስብሐት ውስተ ሰማያት ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ከምድር በክብር በምስጋና ወደሰማያት ከፍ አለች( ዐረገች) አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጡት ክብር ከልጇ ጋር በዚያ ተቀመጠች” በማለት የእመቤታችን ዕርገቷን የገለጠበት ምስጋና ምስክርነትም ነው። “ተለዐለ” የሚለው ግስ ከፍ ማለትን ወደ ላይ ወደ ሰማይ መውጣትን ማረግን የሚገልጥ ግሥ ነው ይህ ግሥ ለጌታችን ዕርገት መነገሩን ልብ ይሏል “ወዘንተ እንዘ ይብሎሙ ተለዐለ ወነስአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ፤ ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።” (ሐዋ. ፩፥፱)
በዚህ አንጻር “ተለዐለት” ማለት ዐርገት ማለት መሆኑን እናስተውል :: የእመቤታችን ትንሣኤ እና ዕርገት ከቅዱሳት መጻሕፍት የምናገኘው ነው እንጂ ልብ የወለደው አእምሮ የፈጠረው አይደለም። አስቀድሞ በነቢያት የተነገረ ነው እንጂ እንዲህ ተብሎ “አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።” (መዝ. ፻፴፩፥፰) አቤቱ ተነሥ የሚለው የጌታችን ትንሣኤ ገላጭ ሲሆን የመቅደስህ ታቦት የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ።
መቅደስ የተባለ ሰውነቱ ነው። ይህም በቅዱስ ወንጌል “ንሥትዎ ለዝንቱ ቤተ መቅደስ ወበሠሉስ ዕለት አነሥኦ ወውእቱሰ ይቤሎሙ በእንተ ቤተ ሥጋሁ፤ ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። … እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር።” (ዮሐ. ፪÷፲፱-፳፩) ተብሎ ተገልጾአል። ስለዚህ አንተ ተነሥ በማለት የትንሣኤያችን በኩር የሆነ የጌታችንን ትንሣኤ ትእዛዛዊ በሆነ እንደማይቀር በሚያስረግጥ መልኩ የተነገረበት ሲሆን “የመቅደስህ ታቦት” ሰው ሆነህ ያደርክባት የተገለጥክባት እርሷም እመቤታችን ትነሣ በሚል ምልዐተ ንባብ የእመቤታችን ትንሣኤ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳይጠብቅ ከእርሱ ቀጥሎ የሚፈጸም መሆኑ የተነገረበት ትንቢት እና ምስክርነት ነው::
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተነሣች ካልን ዐረገች ማለት ግድ ነው። ምክንያቱም ትንሣኤ የዕርገት ዋዜማ ነውና። እመቤታችን በጥር ፳፩ አረፈች፤ በነሐሴ ፲፬ ተቀበረች፤ ዕለቱን በነሐሴ ፲፬ ተነሣች፤ በነሐሴ ፲፬ በዕለተ እሑድ ዐረገች። ከመ ትንሣኤ ወልዳ እንደ ልጇ ፍጹም ትንሣኤ ተነሣች ከመ ትንሣኤ ወልዳ ማለት ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊትን አያመለክትም ዕለተ እሑድ መሆኑንና የትንሣኤዋን ፍጹምነት ዳግም ሞት የሌለበት ትንሣኤ መነሣቷን እንጂ። ያን ጊዜ ዕርገቷን ያየ ቶማስ ብቻ ነበር ሌሎች ሐዋርያት አላዩም ነበርና በነሐሴ አስራ ስድስት በዓመቱ ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችን ዕርገቷን የገለጠበት ዜና ትንሣኤዋንና ዜና ዕርገቷን እንዲሰብኩ ያዘዘበት “ዘፀውዐ ስመኪ ወዘገብረ ተዝካረኪ እምሕር ለኪ፤ ስምሽን የጠራውን መታሰቢያሽን ያደረገውን እምርልሻለሁ” ብሎ ለእመቤታችን ጽኑእ የሆነ ቃል ኪዳን ገብቶላታል።
እንዲሁም “ዘፀውዐ ስመክሙ ወዘገብረ ተዝካረክሙ እምሕር ለክሙ፤ ስማችሁን የጠራውን መታሰቢያችሁን ያደረገውን እምርላችሁአለሁ” ብሎ ለሐዋርያትም ተናግሮ የማያስቀረውን ጽኑእ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ነሐሴ ዐሥራ አራት ትንሣኤዋ እና ዕርገቷ ሲሆን ዐሥራ ስድስት የትንሣኤዋ እና የዕርገቷ መታሰቢያ በዓል የሚከበርበት፣ ትንሣኤዋንና ዕረገቷን ላላዩ ሐዋርያት ጌችንና መድኃኒታችን ለሐዋርያት የተገለጠበት፣ ቃል ኪዳን የሰጠበትነው።
ዕርገቷም እንደ ትንሣኤዋ ሁሉ በመጻሕፍት የተነገረ ሲጠበቅ የኖረ ነው:: “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” (መዝ. ፵፭፥፱) ትቀውም የሚለውን መተርጉማን ትነብር ይሉታል ንግሥት በቀኝህ ትቀመጣለች ማለት ነው። “ትቀውም፤ ትቆማለች” ማለት ለፍጡራን ሁሉ ይልቁንም በአማላጅነቷ ለሚያምኑ በቃል ኪዳኗ ለሚማፀኑ አማላጅነቷን አስረጂ ነው። “ትነብር፤ ትቀመጣለች” ማለት ደግሞ ከዚህ ዓለም ድካመ ሥጋ በዕርገት ማረፏን የተሰጣትን ፍጹም ክብር የሚያስረዳ ነው። መቆም ተልእኮን፣ መቀመጥ ደግሞ ክብርን ገላጭ ነው። በቀኝህ ትቀመጣለች የሚለው ቅዱስ ያሬድ በዝማሬው ካነሣው ሐሳብ ጋር አንድ ነው። “ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ፤ ከልጇ ጋር በዚያ ተቀመጠች” ይላል በዚያ ያለው በመንግሥተ ሰማያት ነው እርሷ በወራሽነት ልጇ በምልዓት ይኖሩባታልና ነው::
የመጀመሪያዋ የገነት ኗሪ ከቀዳማዊው አዳም ጋር ሔዋን ነበረች። የመንግሥተ ሰማያት ጀማሪ ደግሞ ከዳግማይ አዳም ክርስቶስ ጋር ዳግሚት ሔዋን እመቤታችን ናት። “ይቤ ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም አፈበረከት ወመምህር ሦርያዊ በእንተ እግዝእትነ ማርያም ድንግል ወትረ በኩሉ ጊዜ እምአመ ልደታ እስከ አመ እረፍታ ወፍልሰታ፤ አፈ በረከት የሦርያው መምህር ቅዱስ ኤፍሬም ዘወትር ድንግል ስለሆነች ስለእመቤታችን ከልደቷ እስከእረፍቷ እና ፍልሰቷ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ::” ( ሃ.አበ. ፵፯፥፩)
ይህ ፍልሰት የሥጋ ብቻ አይደለም ነፍስና ሥጋዋ ተዋሕደው እንደ ልጇ ትንሣኤ እና ዕርገት ነው እንጂ። (ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ ምስለ ነፍስኪ ኢመዋቲ በተሰናዕዎ አሐቲ፤ ከማትሞት ነፍስሽ ጋር በአንዲት መስማማት ለተደረገ ለስጋሽ ፍልሰት ሰላም እላለሁ) ፤ “ሰላም ለዕርገተ ሥጋኪ ዘተወጥነ ቦቱ:: ዕርገተ ቅዱሳን ሰብእ ዘበኀቤኪ ተአኲቱ፤ በአንቺ ዘንድ የተመሰገኑ የቅዱሳን ሰዎች ዕርገት ለተጀመረበት ለሥጋሽ እርገት ሰላም እላለሁ:: (መልክአ ፍልሰታ) ተብሎ እንደተገለጸው ፍልሰቷ ነፍስና ሥጋዋ ተዋሕዶ ዳግም ትንሣኤን ሳይጠብቅ መንግሠተ ሰማያትን መውረሷን የሚያመለክት ነው።
ከፍጡራን የሞት እና የውርደት ጀማሪ ሔዋን ስትሆን የትንሣኤና የዕርገት ጀማሪ እመቤታችን ናት:: ልጇን መስለን እርሷን ተከትለን ሁላችን እንደምንነሣና እንደምናርግ የታወቀ ነው:: ተስፋ ምናደርገው ትንሣኤ ዘጉባኤ ለሁላችን አለ። ጸሎታችን የእምነት መግለጫችንም ይህ ነው “የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ” ለዘለዓለሙ የሚመጣው ሕይወት በትንሣኤ የምናገኘው በዕርገት የምናረጋግጠው አይደለምን? ይህም አምላካችን የሰጠን የተስፋ ፍጻሜ ነው:: “በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁና እላችሁ ነበር። ከሄድሁና ቦታ ካዘጋጀሁላችሁም ዳግመኛ እመጣለሁ፤ እናንተ እኔ ባለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።” (ዮሐ. ፲፬÷፪) በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ጽኑእ ተስፋ ለዘለዓለም የጸና ምእመናንም ይህን ተስፋ ሰንቀው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው ነው።
ይህ ለሰው የተሰጠው ተስፋ ማለትም መንግሥተ ሰማያትን ወርሶ መኖር አስቀድሞ የተሰጠው ለእመቤታችን ነው ኋላ ለሁላችን ይሆናል:: “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።” (፩ኛ ተሰ. ፬ ÷፲፮-፲፰) ተብሎ እንደተነገረው።
ባጠቃላይ “ተለዐለት እምድር በስብሐት ውስተ ሰማያት ወበህየ ነበረት፤ በክብር በምስጋና ከምድር ወደሰማይ ዐረገች በዚያም ተቀመጠች” በማለት ቅዱስ ያሬድ የገለጸው እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደልጇ እንደወዳጇ በይባቤ መላእክት በክብር፣ በምስጋና ከሙታን ተለይታ መነሣቷን፣ እንዲሁም ወደሰማይ ማረጓን፣ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ፣ ድካም፣ እንግልት ማረፏን፣ በክብር መንግሥተ ሰማያትን መውረሷን የሚያስረዳን ነው። እንደ ልጇ ትንሣኤና ዕርገት የእርሷንም ትንሣኤና ዕርገት በማመን ከትንሣኤዋና ከዕርገቷ በረከትን እንዲያሳትፈን እግዚአብሔር ይፍቀድልን፤ የእመቤታችን ቃል ኪዳን ረድኤት ይደረግልን አሜን !!
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2874
ክህነት እንዴት ይሾማል
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ኢኀደጋ ለምድር እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፣ እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም፤ ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር ለዘለዓለም እስከ ለዓለም ምድርን ያለ ካህናትና ዲያቆናት አልተዋትም’’ (ዚቅ ዘኅዳር ጽዮን) በማለት እንደገለጸው ክህነት ከጥንት ከአዳም ጀምሮ እንደነበረ በክፍል አንድ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ክህነት እንዴት ይሾማል የሚለውን እንመለከታለን፡፡
የክህነት አሿሿም ሥርዓት በየዘመናቱ ይለያያል፡፡ ሿሚው ራሱ እግዚአብሔር ሁኖ የሚሾምበት ሥርዓት ግን እንደዘመናቱ ነባራዊ ሁኔታ የተለያየ እንደነበር መገንዘብ ይገባል፡፡ ለምሳሌ አዳምን በቀጥታ እግዚአብሔር ሾመው፤ መልከ ጼዴቅንም እንዲሁ በቀጥታ እግዚአብሔር ሾመው፡፡ አሮንና ከእርሱ በኋላ የነበረውን የክህነት አሿሿም ስንመለከት ደግሞ በሙሴ አማካኝነት ተሾሙ:: ከዚያ በኋላ በዘር ማለትም ከሌዊ ወገን የሆነውን በዘመኑ የሚኖረው ሊቀ ካህን ሲሾም ኖሯል፤ ሐዋርያትን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሾማቸው፤ ከእነርሱ በኋላ ደግሞ ተከታዮቻቸውን እነርሱ እንዲሾሙ ታዝዘዋልና ሐዋርያት ሲሾሙ ኖረዋል፤ የእነርሱ ተከታዮችም እንዲሁ እየሾሙ ኖረዋል፡፡ የሐዲስ ኪዳኑ አማናዊ ክህነት ከሐዋርያት ጀምሮ ሐዋርያዊ ቅብብሎሹ ሳይቋረጥ እየተላለፈ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
- Details
- Written by: ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 3110
በቶማስ ስም የሚጠሩ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የሚታወቁ በርካታ ቅዱሳን ቢኖሩም የዚህ ዓምድ ዋና ትኩረቱ የክርስቶስ ምስክሩና ሐዋርያው የሆነ የመርዓስ ኤጲስ ቆጶስ ተጋዳይ ቶማስ ላይ አድርጎ ዘመናችንን ይፈትሻል፡፡
የቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ትሩፋትና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይቻልም እርሱ አስቀድሞ ከልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን የተማረ፣ ገና በወጣትነቱ መንኖ ገዳም የኖረ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰጊድ፣ ቀን እና ሌሊትም በመትጋት ለድኆችና ለምስኪኖችም በመራራት ተጠምዶ የኖረ ነበር፡፡
ቅዱስ ቶማስ "መርዓስ" በምትባል አገር የወጣ የንጋት ኮከብ፣ ጻድቅ፣ ገዳማዊ፣ ጳጳስ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕትና ሊቅ ነው፡፡ የእርሱ ሕይወት ኦርቶዶክሳዊ የክርስትና ሕይወትና የጵጵስና የሹመት ሕይወት ምን እንደ ሆነ በትክክል የሚያሳይ ነው፡፡ መርዓስ በምትባል ሀገር ጳጳስ ሆኖ ተሹሞ በእረኝነት ያገለገል ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መረጠው መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ፡፡
በሹመት ዘመኑ በሰላሙም በመከራውም ዘመን ‹‹ መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ ፤ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?›› (ሮሜ ፰፥፴፭-፴፯) እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ለክርስቶስ ያለውን ፍቅር መከራ፣ ጭንቀት፣ ስደት፣ ራብ፣ ራቁትነት፣ ፍርሃት፣ ሰይፍ ሳይለየው ለአርባ ዓመታት ስለ ክርስቶስ ቀኑን ሁሉ እንደሚታረድ በግ ሆኖ እግዚአብሔርን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አገለገለ፡፡
- Details
- Written by: መ/ር ተስፋ ማርያም ቢሰጥ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2052
በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ አንዳችን ለአንዳችን እንዴት መኖር እንዳለብን የቅዱስ ጳውሎስንና የሌሎችን ቅዱሳን ሕይወት መሠረት በማድረግ ለመዳሰስ እንሞክራለን ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የቀደመ ማንነቱን በመተው ምርጥ ዕቃ ከተባለ በኋላ ወንጌል በማስተማር የተበተኑትን በመሰብሰብ የደካሞችን ድካም ተሸክሟል ፡፡ ክርስቶስ የእኛን ድካም ተሸክሞ በዚህ ዓለም ሲኖር በኋላም በመስቀል ሲገልጸው አንድም ቀን ራሱን ደስ እንዳላሰኝ ይህም ሐዋርያ በተመሳሳይ የክርስቶስን ፈለግ በመከተል እንዲህ አለ፡፡ “የሚገባስ እኛ ብርቱዎች ደካሞችን በድካማቸው እንድንረዳቸው ነው፤ ለራሳችንም አናድላ። ሁላችንም በእውነትና በመልካም ሥራ ይታነጽ ዘንድ ለባለንጀራችን እናድላ ፡፡ ክርስቶስም አንተን የነቀፉበት ነቀፋ በእኔ ላይ ደረሰ ብሎ መጽሐፍ እንደተናገረ ለራሱ ያደላ አይደለም ፡፡›› (ሮሜ ፲፭፥፩-፪) ብሏል፡፡
የክርስትናን አኗኗር ስንኖር ራሳችንን ለመጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌላውን ለመጥቀምና ለማስደሰት መሆን አለበት ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳን የራሱን ጥቅም አይፈልግ” (፩ቆሮ.፲፥፳፬) በማለት እንዳስተማረን ከራሳችን ይልቅ ሌላውን ለመጥቀምና ለማስደሰት መትጋት ይኖርብናል። ገታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን በተግባር አሳይቶናል ፡፡ እሱ ተሰዶ እኛን ከተሰደድንበት መለሰን፡፡ የማይራበው እሱ ተርቦ የተራብነው እኛን ሥጋውንና ደሙን በመስጠት አጠገበ፡፡ የማይጠማው ተጠምቶ የተጠማነውን እኛን ደሙን በመስጠት አረካን ፤ የማይታመመው ታሞ የታመምን እኛን ከሕማመ ሥጋ በተአምራት ከሕማመ ነፍስ በትምህርት ፈወሰ፡፡
መከራ በባሕርይው የማይስማማው መከራን ተቀብሎ እኛን ከመከራ አዳነ፡፡ በፍርድ አደባባይ መቆም፣ መወቀስ፣ መከሰስ የማይገባው አምላክ በፍርድ አደባባይ በጲላጦስ ፊት ቆሞ በመወቀስ፣ በመከሰስ፣ በመገረፍ በፊቱ መቆም የማይገባን እኛን በቸርነቱ ብዛት በፊቱ እንድንቆም በማድረግ ከዘለዓለም ፍርድ በማውጣት ደስ አሰኘን ቸርነቱ ያራራዋልና ለርሱ ግን ደስታ ጎሎበት ይህን በማድረግ ደስታን አላተረፈም ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፡፡ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የእኛን ደስታ አጸናልን። ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ‹‹ እኔን የምትሹ ከሆነ እነዚህን ተዋቸው ይሂዱ›› (ዮሐ. ፲፰፥፰) በማለት በከፈለው ዋጋ እኛን ነፃ አወጣን ፡፡ እጅና እግሩን ታስሮ እኛ የታሰርንበትን የኃጢአት ሰንሰለት ቆረጠ፡፡ የእኛን ኃጢአት ፤ ድካም ፤. . . .በመስቀል ላይ በመሸከም ዕዳችንን ፤ ሸክማችንን አቀለለ፡፡ የውርደት ሞትን በፈቃዱም ቢሆን ሞቶ እኛን ለክብር አበቃን ፡፡ በአጠቃላይ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ የፈፀማቸው ሁሉ እኛ የከበርንባቸው ናቸው፡፡
ይህም ታላቅ የወንጌል መምህር ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ እኔ ክርስቶስን እንደመሰልኩ እናንተም እኔን ምሰሉ›› (፩ቆሮ. ፲፩፥፩) ብሎ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመልእክቱ የጻፈው ለሌሎች እንደመኖርና የሌሎቹን ድኅነት እንደማሰብ ድካማቸውንም እንደመሸከም የሚያስደስት የለምና ነው። አንድ ሰው ብዙ ቢጾም፤ ቢጸልይ ፤ ቢሰግድ፤ አርምሞ ቢይዝ የሌሎች ወገኖች ጉዳይ መራብ፣ መጠማት፣መታመምና መጎስቆል፣ በኃጢአት መውደቅ… የማያሳስበው ከሆነ ከክርስቶስ ብዙ ርቋል ፡፡ ሐዋርያውም “ወንድሞቼ ሆይ የልቤ ምኞት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርበው ጸሎትም እስራኤል እንዲድኑ ነው ፡፡” (ሮሜ ፲፥፩) በማለት ምኞቱና ጸሎቱ ስለሌሎች መዳን መሆኑን በአጽንኦት ይነግረናል። ሐዋርያው በልቡ እንዲህ አይነት በጎ ፈቃድ ስላለው የቆሮንቶስንም ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት አስተማሯል “እኔ ከሁሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እሰበስባቸው ዘንድ እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ ፡፡ አይሁድን እጠቅም ዘንድ ለአይሁድ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁላቸው፤ ከኦሪት በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ እኔ ራሴ ከኦሪት በታች ሳልሆን ከኦሪት በታች ላሉት ከኦሪት በታች እንዳለ ሰው ሆንሁላቸው፤ የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋሁ ሳልሆን በክርስቶስ ሕግም ሳለሁ ሕግ የሌላቸውን እጠቅማቸው ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሆንሁላቸው፤ ደካሞችንም እጠቅማቸው ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶቹን አድን ዘንድ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደነርሱ ሆንሁ፡፡ በወንጌልም ትምህርት አንድነት ይኖረኝ ዘንድ ስለወንጌል ትምህርት ሁሉን አደርጋለሁ፡፡ (፩ቆሮ. ፱፥፲፱-፳፫)
ይህ ታላቅ ሐዋርያ ሰዎችን ይረዳ ይጠቅም ድካማቸውንም ይሸከም ዘንድ ፤ ለአይሁዳዊውም ሕግ ለሌለውም ከሕግ በታች ላሉትም ለደካሞችም የሚያድንበትን መንገድ ለማስፋት የቻለውን አድርጓል፡፡ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ›› (፩ቆሮ. ፲፩፥፩)ያለበት ዋነኛው ምክንያትም ይህ ነው። ክርስቶስ እኛን ከወደቅንበት ለማንሣት እያሳደድነው፣ እየደበደብነው፣ እየገፋነው እርሱ ግን እስከ ሞት ድረስ ወደደን። በመንጸፈ ደይን መውደቃችንን በእግረ አጋንንት መጠቅጠቃችንን አይቶ ልዑል ባሕርይውን ዝቅ በማድረግ እኛን ከወደቅንበት ለማንሣት ወደኛ መጥቷል ፡፡ እርሱ በባሕርዩ የማይስማማውን መራብን፣ መጠማትን፣ መሰደብን፣ መገረፍን መሞትን ለኛ ሲል እንደተቀበለ እኛም ለሌሎች መዳን የቻልነውን ማደረግ ይጠበቅብናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሌሎችን ለመጥቀም ሲል ለኅሊና የማይመቹ ብዙ ነገሮችን አድርጓል ፡፡
ሀ. ራስን መላጨት ፡- ቆሮንቶስ የአካይያ ዋና መዲና ስትሆን ጋልዮስ በአካይያ አገረ ገዥ በነበረበት ጊዜ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ . . ..ጋልዮስም ‹‹በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድም በማለት ከፍርድ ወንበር አስወጥቷቸዋል . . . . ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጅግ ቀን ተቀምጦ ወንድሞቹንም ተሰናብቶ በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ ስለትም ነበረበትና ራሱን በክርንክራአስ ተላጨ ድርስቅላና አቂላም ከእነርሱ ጋር ነበሩ፡፡ (ሐዋ.፲፰፥፲፪-፲፰) ብፅዐት ያለበት ሰው ስድስት ቀን ከሰው ተለይቶ በሰባተኛው ቀን ጠጉሩን ተላጭቶ ገላውን ታጥቦ ልብሱን አንፅቶ መሥዋዕት አሠውቶ ማየ ምንዛህ (ውኃ) ተረጭቶ ከሰው ይገናኝ ነበር ፡፡ (ዘኊ.፮፥፱) ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን መላጨቱ ለእሱ ምንም ጥቅም ሳይኖረው ሌሎችን ለመሳብ አድርጓል ይህ ሐዋርያ እየተራበም እየተጠማም፤ እየተገፋም ሌሎችን ለመሳብ የሚያደርገው ጥረት እጅግ የሚደንቅ ነው ፡፡
ለ. ግዝረት ፡- ቅዱስ ጳውሎስ ስለግዝረት ምንነት በሰወፊው አስተምሯል “ኦሪትንም ብትፈጽም ግዝረት ትጠቅምሃለች ኦሪትን ባትፈጽም ግን ግዝረትህ አለመገረዝ ትሆንብሃለች። አንተ ሳትገዘር ብትኖር ኦሪትንም ብትጠብቅ አለመገዘርህ መገዘር ትሆንልሃለች። ተገዝረህ ኦሪትን ከምታፈርስ በተፈጥሮ ያገኘሃት አለመገዘርህ አብራህ ብትኖር ይሻልሃል፤ ኦሪት ከምታፈርስ ካንተ ከተገዘርኸው ያ ያልተገዘረው ኦሪትን የሚፈጽመው ይሻላል።… ›› (ሮሜ ፪፥፳፭-፳፱) በማለት በሐዲስ ኪዳን ግዝረት ማለት በመንፈስ ቅዱስ ምላጭነት በልብ ያለውን የኃጢአት ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣልና ሕገ እግዚአብሔርን መፈፀም እንደሆነ በግልፅ አስረዳ ፡፡
በመሆኑም መገረዝም አለመገረዝም ምንም ዓይነት ጥቅም ባይኖረውም ሌሎቹን ለመጥቀምና ድካማቸውን ለመሸከም ክርስቶስም ተገርዟል፡፡ ክርስቶስ የግዝረትን ሥርዓት የፈጸመው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሥርዓቱን ግን የፈጸመው የአባቶቻችን ሥርዓት አይፈጽምም ብለው በእርሱ እንዳይሰናከሉ ሠራዔ ሕግ ሲሆን ፈጻሜ ሕግም ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ደርቤንና ልሳጥልን በሚባል ቦታ በግሪክ አገር ከሲላስ ጋር በደረሰ ጊዜ ወደፊት ታማኝና ተወዳጅ ልጅ የሚሆነውን ጢሞቲዎስን አገኘና ከእርሱ ጋር ይወስደው ዘንድ ወደደ ነገር ግን በዚያ ሥፍራ አይሁድ ስለነበሩ እነርሱ ደግሞ ያልተገዘረን ሰው ደቀ መዝሙር አድርጎ ሲወስድ ቢያዩ የኦሪት ግዝረት ምንም ዋጋ የሌለው መሆኑን ተምረው እስኪያውቁ ድረስ እንዳይሰናከሉና በዚህም ምክንያት ወንጌልን ከመስማትና ሰምተውም ከማመንና ከመዳን ራሳቸውን እንዳያርቁ ለእነርሱ ሲል ገዘረው፡፡ ‹‹በዚያም ስለነበሩ አይሁድ ጢሞቲዎስን ይዞ ገዘረው›› (ሐዋ.፲፮፥፩-፬)
ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ጉባዔ አድርገው በወሰኑት ውሳኔ “ሥርዓት እንዳናከብድ ሌላም ሸክም እንዳንጨምር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ነውና፤ ነገር ግን ይህን በግድ ትተው ዘንድ እናዝዛችኋለን።ለአማልክት የተሠዋውን ፣ ሞቶ የተገኘውን፣ ደምንም አትብሉ ፤ ከዝሙትም ራቁ፤ በራሳችሁ የምትጠሉትንም በወንድሞቻችሁ ላይ አታድርጉ ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ በሰላም ትኖራላችሁ ደኅና ሁኑ” (ሐዋ. ፲፭፥፳፰-፳፱) ብለው ወስነዋል። በዚህም ውሳኔያቸው ከአሕዛብና ከአይሁድ ወደ ክርስትና የሚመጡትን ወገኖች ሲያወዛግቡ የነበሩትን ግዝረትን በኦሪት የታዘዘውን ይህን ካሉ ይህን አትብሉ የሚለውን ገለጹ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም አላስፈላጊነቱን እርሱም ባለበት በኢየሩሳሌም ጉባዔ የተወሰነውንና ብዙ ጊዜም በመልእክታቱ ምንም ጥቅም እንደሌለው የተናገረበትን ግዝረትን ለጊዜው ከሰዎች ደካማነት የተነሣ የእነርሱን ድካም በመሸከም ይህን ፈጽሟል ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ለራሱ ሳይሆን ለሌላው በመኖር ጨውም ቅመምም በመሆኑ መራራ በነበሩ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ክርስትናውን አጣፍጦታል ፡፡
ሐ. ገንዘብ አለመውደድ (አለመቀበል) ፡- አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሲልካቸው ምንም ነገር መያዝ እንደሌለባቸው “በመቀነታችሁ ወርቅ ወይም ብር ወይም መሐለቅ አትያዙ። ለመንገድም ስልቻ ወይም ሁለት ልብስ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ ለሠራተኛ ዋጋው ይገበዋልና ›› (ማቴ.፲፥፲) በማለት በሔዱበት የዕለት ምግባቸውን እንዲያገኙ እንጂ ሌላ ነገር እንዳይዙ አዟል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን ቃለ እግዚአብሔርን ከሚመግባቸው ምእመናን ለዕለት ኑሮው የሚያስፈልገውን ምግብ ማግኘት መብቱ ቢሆንም ከእነርሱ ምንም ገንዘብ ሳይቀበል ድንኳን እየሰፋ ይተዳደር ነበር። ምክንያቱም ሰው ገንዘብ አምጣ ሲሉት ፊቱ ይጠቁራል ውስጡም ይቀየማል ፡፡ ስለዚህ ገንዘብ ወዳድ ሆኖ የነርሱን ቢቀበል የሚያስተምረውን ወንጌል በንጹሕ ልብ እንዳይቀበሉ እንቅፋት ይሆንብኛል ብሎ ወንጌልን መስበክ ወደደ፡፡
በተለይም ለቆሮንቶስ ሰዎች ‹‹ እነሆ ወደ እናንተ ልመጣ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ነገር ግን አልተፋጠንሁም ገንዘባችሁን ያይደለ እናንተን እሻለሁና፤ ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና እኔ ግን ስለነፍሳችሁ ገንዘቤን በብዙ ደስታ እከፍላለሁ፡፡›› (፪ቆሮ.፲፪፥፲፬-፲፭) በማለት እንኳንስ የእነርሱን ገንዘብ ሊቀበል ድንኳን ሰፍቶ የሚያገኘውን ገንዘቡንና ራሱንም ጭምር ለእነሱ እንደሚከፍል በግልጽ ነግሯቸዋል ፡፡ ይህንም የተናገረበት ምክንያት የቆሮንቶስ ምእመናን ገንዘብን ከመውደዳቸው የተነሣ ብዙዎች ዳኞች ባለሥልጣናት ገና አረማውያን በነበሩበትና ክርስትና ገና እየተስፋፋ በነበረበት ጊዜ እነዚህ ክርስቲያኖች ‹‹ ክርስቶስ አባታችን መንግሥተ ሰማይ ርስታችን ሀገራችን በሰማይ እያሉ በዚህ ዓለም ገንዘብ እየተጨቃጨቁ ይካሰሳሉ›› እያሉ ክርስትናን ያስነቀፉ ስለነበር ነው፡፡ “ይህንም የምላችሁ ስዘልፋችሁ ነው፤ እንግዲህ ከመካከላችሁ ወንድማማቾችን ከወንድሞቻቸው ጋር ማስታረቅ የሚችል ሽማግሌ የለምን? ነገር ግን ወንድም ከወንድሙ ጋር ይካሰሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል። እንግዲህ ጸብና ክርክር ካላችሁ ከመጀመሪያው ጀምሮ ውርደት እንደሚሆንባችሁ ዕወቁ፤ እንግዲያማ እንዴት አትነጠቁም? እንዴትስ አትገፉም? አሁንም ቢሆን እናንተ ዐመፀኞችና ቀማኞች ናችሁ፤ እንደዚህም ወንድሞቻችሁን ትበድላላችሁ፡፡›› ያለበት ምክንያት ይህን ለመግለጽነው (፩ቆሮ.፮፥፭-፰)
በኃላፊ ጠፊ ገንዘብ ምክንያት ከወንድም ጋር መካሰስ ተገቢ እንዳልሆነ በግልፅ ጻፈ፡፡ የዋሁ ጳውሊም ከወንድሙ ጋር በገንዘብ ተካሶ ሲሄድ ሬሳ ለቀብር ሰዎች ተሸክመውት በማየት ለዚህ ነው ወንድሜን የምከሰው ወንድሜ ተመለስ ሁሉ ላንተ ይሁን ብሎ ይችን ዓለም በምናኔ ተሰናብቶታል ፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስም በገንዘብ ፍቅር ከሚቃጠሉና ከሚካሰሱ ሰዎች ምንም ነገር መቀበል ያልፈለገው ፡፡ ይልቁንም እርሱ ወንጌልን እያስተማራቸው ልጅነት፤ ጥምቀት፤ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር እየመራቸው የድካሙን ዋጋ የዕለት ጉርሱን ቢቀበል መብቱ እንደሆነም አስረድቷቸዋል ፡፡ ‹‹ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንም ? ወይስ ሥራ ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን? ከቶ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማነው ?ወይስ ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማነው ? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማነው ? ይህን በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁ ? ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ በሙሴ ሕግ ተጽፏል፡፡ እግዚአብሔር ስለበሬዎች ይገደዋልን ?ይህን የሚለው ስለ እኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲከፍል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው በእውነት ስለኛ ተጽፏል፡፡ እኛ መንፈሳዊ ነገር የዘራንላችሁ ብንሆን የእናንተን ሥጋዊ ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን በመቅደስ የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሚሆነውን ነገር እንዲመገቡ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠውያው እንዲካፈሉ አታውቁምን ?እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጓል ፡፡ እኔ ግን በዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምኩም እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፡፡” (፩ቆሮ.፱፥፮-፲፩፤፲፫-፲፭)
ይህን ካለ በኋላ ለምን በዚህ መብት እንዳልተጠቀመ ሲገልጽ “በእኛ ሹመት ሌላ የሚቀድመን ከሆነ የሚሻላችሁን እናንተ ታውቃላችሁ እኔ ይህን አልፈለግሁትም። ነገር ግን የክርስቶስን ትምህርት እንዳላሰናክል በሁሉ እታገሣለሁ” አለ፡፡ (፩ቆሮ.፱፥፲፪) ይህ ታላቅ ሐዋርያ ለእርሱ የተፈቀደውን እንኳ ሳይጠቀም አሁን እኛ ባለንበት ዘመን ጓደኛ ጓደኛውን አላምን ብሎ በሩን ዘግቶ ለራሱ ብቻ ከመኖር ይልቅ በዚህ በክፉ ወቅት አንዱ የአንዱን ድካም ቢሸከም እጅግ መልካም ነበር ፡፡ ምክንያቱም የአንዱ መኖር ለሌላው እጅግ ወሳኝ ነውና። መቼም ሕዝብ ሳይኖር ወታደር፤ ወታደር ሳይኖር መንግሥት ለማን ይነግሣል፡፡ ሕዝብ ሳይኖር ሀገር፤ ሀገር ሳይኖር ሕዝብ ምን ይሆናል? ገበሬ ሳይኖር በሬ ማርባት ለእርድ ብቻ ነው የሚሆነው ስለዚህ ምርት የለም ማለት ነው ፡፡ ምርት ሳይኖር ገበሬው ኑሮ ፤ ገበሬ ሳይኖር የከተማ ኑሮ የእምቧይ ካብ ነው የሚሆነው ፡፡ ስለዚህ የአንዱ መኖር ለሌላው መኖር መሠረት ማለት ነው ፡፡ ለምሳሌ፡-
የትንሹ ዓሣ በትልቁ ዓሣ ነባሪ በሻርኩ ላይ መኖር፡- ዓሣ ነባሪው ሲመገብ የሚተርፈውን እርሱ ይመገባል፤ ለዓሣ ነባሪው የፅዳት ሥራ ይሠራል፤ ለራሱ ደግሞ የዕለት ምግቡን ከማግኘት በዘለለ በሌሎቹ ምግብ ፈላጊዎች እንዳይዋጥ ጉዳት እንዳይደርስበት ይረዳዋል ፡፡ ይህም ሂደት የጋራ ጥቅም ተብሏል ፡፡ ይህም እርስ በርስ መጠቃቀም ማለት ሲሆን የትንሹን ዓሣ ድካም ዓሣ ነባሪው ተሸክሞ ሲኖር ድካም ተሰምቶት አያውቅም፡፡ ምክንያቱም ስንት ኪሎ ግራም የሚመዝን የራሱን ክብደት ተሸክሞ ይኖራል ፡፡ ስለዚህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የደካሞችን ድካም ተሸክሞ ማለፍ በዓላማው ዝለት ልዩ ልዩ የዓለማችን ድክመት ያፈራረሰውን የሰው ልጅ ልቦና ማነጽ ማለት ነው ፡፡
በአጠቃላይ የክርስትና ሕይወት ለራስ ብቻ ሳይሆን በራስ መኖር ውስጥ ስለሌላውም ጭምር የሚኖርበት ሕይወት ነው። ክርስቶስ እከብር አይል ክቡር፣ እነግሥ አይል ንጉሥ፣ እጸድቅ አይል ጻድቅ ሲሆን ክብር ያጣውን ሊያከብር፣ በጠላት እግር ሥር የወደቀውን ከጠላት አገዛዝ ነጻ ሊያወጣ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ይህን ዓለም እንዳዳነ ሁሉ እርሱን አብነት አድርገው የኖሩት ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሁሉ ለሰው ሲሉ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ትተው ሰዎች ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የሚያገኙበትን ተግባር አከናውነዋል። እነርሱ እየተራቡ ለሌላው ሲያበሉ፣ እነርሱ እየተጠሙ ለሌላውን ሲያጠጡ ኑረዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው” (፩ቆሮ.፱፥፳፪) በማለት የገለጸው እንዲህ ያለውን ተግባር እንድንረዳ ነው። እኛም በእንደዚህ ያለው መልካም ተግባር እንድንኖር እግዚአብሔር ይፍቀድልን።
ወስበሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 603
በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዓምዳችን ወርኀ ጳጕሜንና የዘመን መለወጫ (ዕንቁዕጣጣሽን) በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልጋይ የሆኑትን አባ ዐሥራተ ማርያም ደስታን ጋብዘናቸዋል። ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ቆይታ፡፡
ሐመር፡- አባታችን የምናነሣቸው ጥያቄዎች ከጳጕሜንና ከዘመን መለወጫ ጋር የተያያዙ ይሆናሉ፡፡ ለመሆኑ ጳጉሜን ማለት ምን ማለት ነው?
አባ ዐሥራተ ማርያም፡- ጳጕሜን ማለት ቃሉ የጽርዕ ወይም የግሪክ ሲሆን ሄፓጎሜን ይባላል፡፡ ትርጓሜውም ጭማሪ ማለት ነው። በግእዝ ተውሳክ ይባላል። በሌላ አገላለጽ ከዐውደ ወርኅ ስለተረፈና በዓመት መጨረሻ ስለተገኘ ተረፈ ዓመት ይባላል። በዓመተ ዑደተ ፀሐይ አንድ ዓመት ፫፻፷፭ ቀናት ነው። ይህን ለ፴ ስናካፍል ፲፪ ይደርስና ፭ ይቀራል። እነዚህ ፭ ቀናት ጳጕሜን ተብለው ስለሚጠሩ ጳጕሜን ማለት ጭማሪ ወይም ተረፈ ዓመት ተብሎ ይጠራል።
ሐመር፡- አባታችን ከዚህ ጋር ተያይዞ ጳጒሜን ሦስቱን ዓመታት አምስት አምስት ቀናት ሆነው ሲውሉ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ ምክንያቱን ቢያብራሩልን?
አባ ዐሥራተ ማርያም፡- ይህ የሚሆንበት ምክንያት ከእያንዳንዱ ዓመት ተጨማሪ ስድስት ስድስት ሰዓት ትርፍ አለ። ይህ ስድስት ሰዓት በዐራተኛው ዓመት ፳፬ ሰዓት (አንድ ቀን) ይሆናል። በዘመነ ሉቃስ ጳጕሜን ስድስት የሚሆነው በየዓመቱ የተረፉት ስድስት ስድስት ሰዓታት ተደምረው አንድ ቀን ሲለሚሞሉ ነው።
- Details
- Written by: ዲ/ን አሸናፊ ደሳለኝ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2219
“አጥብቄ ፈለግሁ . . . ደከምሁ፤ እጅግም ባዘንሁ፤ ዙሪያ ገባውን ሁሉ እየቃኘሁ የዓለምን ዳርቻዎች ሁሉ አማተርሁ፤ . . . ነገር ግን ነፍሴን እፎይ ብየ አሳርፋት ዘንድ እሸሸግበት ጥግ አጣሁ የደከመ መንፈሴን ሰላም አሰፍንበት ዘንድ ማረፊያ ወደብ አጣሁ . . አዎ እጅግ ባተትሁ ነፍሴን ከደካማው ሥጋየ እሥር አላቅቄ ነጻነትን አጎናጽፋት ዘንድ ማረፊያው የሥጋ ሸክም ማራገፊያው ከቶ ወዴት ነው? “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል” (ማር. ፰፥፴፮) እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ በዚህ ምድራዊ ዓለም የሚዳሰስ፣ የሚላስ፣ የሚቀመስ ይጣፍጥ ዘንድ ግን ከቶ በማይቻለው የዓለም ግሳንግስ የተወረረችና ዝላ የደከመች ነፍሴን ምኞት፣ ዝሙትና ፍቅረ ንዋይ የተሰኙ ወንበዴዎች ደብድበው ያቆሰሏትን ድኩም ነፍሴን ዘይቱን አፍስሶ ቁስሌን ወደሚያክምልኝ ያ ደግና ርኅሩኅ ሳምራዊ አደርሳት ዘንድ ከቶ የት ልሂድ፡፡” (ሉቃ. ፲፥፴፫) እያሉ አባ ሞገሴ ረዘም ባለ ንግግራቸው ድምፃቸውን ጎላ አድርገው ያወራሉ፡፡
አባ ሞገሴ ከሰው ጋር ያሉ መስሎኝ ትቻቸው ልሄድ ስል ብቻቸውን ናቸው። አመማቸው እንዴ ብየ ልጠይቃቸው ስል ዐይናቸውን ወደሰማይ ቀና አድርገው ከነበሩበት ስሜት ማንም የሚያናውጻቸው ያለ አይመስልም። አባ ሞገሴ በአንድ ታዋቂና ታላቅ ደብር ጸሎት አሳራጊ አባት ናቸው። በዚህ ታላቅ ደብር ቄሰ ገበዝ ሆነው ለረጅም ጊዜ ካገለገሉ በኋላ የጸሎት አሳራጊ አባት እንዲሆኑ በካህናቱ ፈቃድ ከሰሞነኛነት ተለይተው የሚኖሩ አባት ናቸው። ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቅዱስ አባት ለአርባ ዓመት ቆመው የጸለዩበት ቦታ ነው ከሚባል ጫካ ቆመው እየጸለዩ ነው። እኔም ስሜታቸውን ከምረብሽ በጽሞና ማዳመጡና ከጸሎታቸው በረከት መቀበሉ የተሻለ ነው ብየ ማዳመጥ ጀመርሁ። አባ ከብሉያት ከሐዲሳት እየጠቃቀሱ ልመናቸውን ቀጠሉ።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1464
የቱርክ መንግሥት ታላቁንና ጥንታዊውን የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ ወደ መስጅድነት መቀየሩን ተከትሎ ዐሥራ አራቱ የአውሮፓ ሀገራት መንግሥታት ድርጊተን እንዲያወግዙ የግሪኳ ፕሬዘዳንት ካተሪና ሳከላሮፖውሎው (Katerina Sakellarouplou) ጥሪ እንዳቀረቡላቸው ኦርቶዶክስ ታይምስ ዘግቧል፡፡ ፕሬዘዳንቷ ለዐሥራ አራት አውሮፓ ሀገራት መንግሥታት ደብዳቤ የጻፉ ሲሆን በደብዳቤያቸውም ጥንታዊውና በአውሮፓ የቀደመ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለውን የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ ወደ መስጅድነት የመቀየር የቱርክ መንግሥት ውሳኔን እንዲታገሉና እንዲያወግዙት አሳስበዋል፡፡
ታላቁ የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ የአውሮፓውያንን የጋራ ማንነት፤ እሴትና ልዩነት ለወደፊቱ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ያሉ ሲሆን ፕሬዘዳንቷ ቤተ መቅደሱ የአውሮፓውያን የጋራ ታሪካዊ ቅርስ፣ ልዩ ጥበብና እምነትን ያጣመረ እንደሆነም ገልጠዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ቤተ መቅደሱ እንደ እ.ኤ.አ. ፲፱፻፸፪ ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ ሳይንስና ባህል ድርጅት የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በመሆኑም የቱርክ መንግሥት ቤተ መቅደሱን የመቻቻል፣ የሰላም፣ የአብሮ መኖር፣ በባህሎችና በሃይማኖት ተቋማት መካከል የመነጋገሪያ ምልክት ሆኖ እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ የግጭት፣ ያለመቻቻል፣ የመገፋፋትና የጥርጣሬ ምልክት እንዲሆን ማድረጉ እንዳስከፋቸው ፕሬዘዳንቷ ተናግረዋል፡፡
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1563
በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዓምዳችን ወርኀ ጳጕሜንና የዘመን መለወጫ (ዕንቁዕጣጣሽን) በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልጋይ የሆኑትን አባ ዐሥራተ ማርያም ደስታን ጋብዘናቸዋል። ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ቆይታ፡፡
ሐመር፡- አባታችን የምናነሣቸው ጥያቄዎች ከጳጕሜንና ከዘመን መለወጫ ጋር የተያያዙ ይሆናሉ፡፡ ለመሆኑ ጳጉሜን ማለት ምን ማለት ነው?
አባ ዐሥራተ ማርያም፡- ጳጕሜን ማለት ቃሉ የጽርዕ ወይም የግሪክ ሲሆን ሄፓጎሜን ይባላል፡፡ ትርጓሜውም ጭማሪ ማለት ነው። በግእዝ ተውሳክ ይባላል። በሌላ አገላለጽ ከዐውደ ወርኅ ስለተረፈና በዓመት መጨረሻ ስለተገኘ ተረፈ ዓመት ይባላል። በዓመተ ዑደተ ፀሐይ አንድ ዓመት ፫፻፷፭ ቀናት ነው። ይህን ለ፴ ስናካፍል ፲፪ ይደርስና ፭ ይቀራል። እነዚህ ፭ ቀናት ጳጕሜን ተብለው ስለሚጠሩ ጳጕሜን ማለት ጭማሪ ወይም ተረፈ ዓመት ተብሎ ይጠራል።
ሐመር፡- አባታችን ከዚህ ጋር ተያይዞ ጳጒሜን ሦስቱን ዓመታት አምስት አምስት ቀናት ሆነው ሲውሉ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ ምክንያቱን ቢያብራሩልን?
አባ ዐሥራተ ማርያም፡- ይህ የሚሆንበት ምክንያት ከእያንዳንዱ ዓመት ተጨማሪ ስድስት ስድስት ሰዓት ትርፍ አለ። ይህ ስድስት ሰዓት በዐራተኛው ዓመት ፳፬ ሰዓት (አንድ ቀን) ይሆናል። በዘመነ ሉቃስ ጳጕሜን ስድስት የሚሆነው በየዓመቱ የተረፉት ስድስት ስድስት ሰዓታት ተደምረው አንድ ቀን ሲለሚሞሉ ነው።
- Details
- Written by: ዲ/ን አሸናፊ ደሳለኝ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1493
እምነተ ጎደሎው ሰንከልካላው ልቤ፤
የኀጢአት አውድማ ደካማው ሐሳቤ።
ለሠላሳ ዘመን ደግሞም ከዛ በላይ ፤
በደዌ ተይዞ ተኝቷል አልጋ ላይ ።
ውኃውን ሲያናውጥ ቃልህ ቀስቃሽ ሆኖ ሕይወትን ሊያለብሰኝ፤
ወደ ፈዋሹ ምንጭ የሕይወት እንጀራ በፍቅር ሲጠራኝ፤
እሽ ብየ ለመሄድ መንፈሳዊ ወኔ አቅም ስላጠረኝ።
አልጋህን ተሸከም በንስሓ ታጠብ፤
ከእንግዲህ በኋላ በደልን አታስብ፤
ብለህ አበረትተህ ልዳን ፍቀድልኝ፤
አልጋህን ተሸከም ተመላለስ በለኝ።
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 3680
ክፍል አንድ
መግቢያ
“ቤተ ክርስቲያን አካለ ክርስቶስ ወይም ቤተ ክርስቲያን ልትባል የምትችለው ቢያንስ አራት ነገሮን ከራሱ ከክርስቶስ ከተማርነውና ከሐዋርያት ባገኘነው ላይ ብቻ ጠብቃ ስትገኝ ነው። እነዚህም ሐዋርያዊ ትውፊት፣ ሐዋርያዊ ትምህርት፣ ሐዋርያዊ ክህነትና ሐዋርያዊ ሥርዓተ አምልኮን ጠብቃ ስትገኝ ነው። ትምህርቱና ትውፊቱ ለሥርዓተ አምልኮ መሠረቶች ናቸው። ክህነቱ ደግሞ የአምልኮቱ መፈጸሚያ ነው። ያለ እውነተኛ ሃይማኖትና ሥርዓተ አምልኮት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ወይም መንፈሳዊ ውሕደት እንደማይቻል ሁሉ ያለ ሐዋርያዊ ክህነት ደግሞ ትክክለኛ አምልኮትን መፈጸም አይቻልም። ይህ ማለት ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖራቸው የሚችለው መንፈሳዊ ግንኙነትም እንበለው ውሕደት ያለ እውነተኛ ክህነት ሊፈጸም አይችልም ማለት ነው።”
(የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ፓትርያሪክ፣ ቀዳሜ ቃል)
ከላይ የተወሰደው ጽንሰ ሐሳብ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ በተሰኘው መጽሐፍ በቀዳሜ ቃል ላይ ያስቀመጠው መልእክት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በቦታና በጊዜ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሁኔታዎች አይወሰንም፡፡ ፍጥረታቱን በቀጥታ ለመገናኘትም እርሱን የሚያግደው ነገር የለም፡፡ እርሱ እንደወደደና እንደፈቀደ ፈጥሮ በመግቦቱና በአምላካዊ ጥበቃው እየተገናኘም ይኖራል፡፡ እርሱ ፈቅዶና ወዶም የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበትን መንገድ እጅግ አብዝቶታል፡፡ ከዚህ ከብዙው መገናኛ መንገዱ መካከል ክህነት አንዱ ነው፡፡ ይህ የክህነት አገልግሎት ከህገ ልቡና ጀምሮ እስከ አሁን አለ ወደፊትም ይኖራል፡፡ ከላይ በዲያቆን ብርሃኑ የተጠቀሰው ጽንሰ ሐሳብ የሚያስረዳን እግዚአብሔር በዚህ የክህነት አገልግሎት አማካኝነት ከሰው ልጆች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ሲያደርግ እንደኖረ ወደፊትም እንደሚኖር ነው፡፡ ዲያቆን ብርሃኑ በመቀጠልም “አንዳንድ ሰዎችን የልቡናቸውን ቅንነት አይቶ እግዚአብሔር ቢቀበልላቸው እንኳን ለድኅነት ይበቁ ዘንድ መንገዳቸውን ወደ ትክክለኛው እምነትና ሥርዓተ አምልኮት ይመራቸዋል። ለምሳሌ ያህል ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቆርነሌዎስን ጸሎቱን፣ ምጽዋቱንና የልቡን ቅንነት አይቶ ተቀብሎ ጠርቶታል። ቅዱስ ጳውሎስን ደግሞ ቀናዒነቱንና ለአመነበት ነገር ራሱን አሳልፎ መስጠቱን አይቶ ጠርቶታል። ሁለቱንም በተአምራት ከመለሳቸው በኋላ መጀመሪያ ያደረገው ግን ከካህናት ጋር ማገናኘትና ከቤተ ክርስቲያን ሊያገኙት የሚገባቸውን እንዲያገኙ ማስቻል ነው። መልሶ ከራሱ ያዋሐዳቸው በዚህ ሐዋርያዊ መንገድ ነው።” (ዝኒ ከማሁ) በማለት ያስረዳል፡፡
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 3523
ነቢያት በትንቢታቸው፣ ሐዋርያት በስብከታቸው ሕይወት፣ መድኃኒት እንደሆነ የመሰከሩለት፣ የስሙ ትርጓሜም መድኃኒት የሆነ ሁሉ የሚቻለው አምላክ በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህ ዓለም ሲመላለስ በዋናነት ዓለምን የማዳን እና ለዓለም አርአያ የመሆን ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት አድኗል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን በዚህ ዓለም ያከናወነውን ተግባር ሁሉ ጠቅሶ መጨረስ አይቻልም። በመጽሐፍም ሁሉ ተዘርዝሮ አልተጻፈም። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ጌታችን ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልጻፈ ብዙ ሌላ ተአምራት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ። ነገር ግን ይህ የተጻፈ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እናንተ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ የዘለዓለም ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ነው” (ዮሐ.፳፥፴-፴፩) በማለት እንደመሰከረለት የተጻፈው ጥቂቱ ብቻ ነው።
ጊዜ ገጥሟቸው ከመዋዕለ ሥጋዌው ደርሰው በስብከቱ፣ በተአምራቱ አምነው የዳኑት እጅግ ብዙ ናቸው። ነገር ግን እርሱ የማዳን ተግባሩን ፈጽሞ በክብር ወደ ባሕርይ አባቱ እና ወደ ባሕርይ ሕይወቱ ካረገ በኋላ እርሱ የሾማቸውን መምህራን ሰምተን፣ የፈጸማቸውን ተግባራት ከመጻሕፍት ተረድተን ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንወርስ ዘንድ እግዚአብሔር ባወቀ ለእኛ የሚሆነን ያህል ተጻፈልን። ሐዋርያትን፣ ሊቃውንትን መምህራንን የሾመልን፣ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ አካላዊ ቃል በሥጋ ተገልጦ ወደዚህ ዓለም የመጣ፣ ዓለምን ያዳነ የሕይወት ቃል ነው።