ሐመረ ጽድቅ
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ሐመር
    • የማኅበሩ መልእክት
    • ትምህርተ ሃይማኖት
    • እናስተዋውቃችሁ
    • የጥያቄዎቻችሁ መልስ
    • ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት
    • ኪነ ጥበብ
    • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን
    • ከዓለም ማእዘናት
    • ዐውደ ስብከት
    • ዐቢይ ጉዳይ
  • ስምዓ ጽድቅ
    • ርእሰ አንቀጽ
    • አጫጭር ዜናዎች
    • ሪፖርታዥ
    • ቤተ አብርሃም
    • ፍሬ ከናፍር
    • የሕፃናት ዓምድ
    • ትዝብት
    • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ
  • ሙሉ ሕትመቶች
    • ሐመር በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • ሐመር በ ዓ.ም.
      • 1985
      • 1986
      • 1987
      • 1988
      • 1989
      • 1990
      • 1991
      • 1992
      • 1993
      • 1994
      • 1995
      • 1996
      • 1997
      • 1998
      • 1999
      • 2000
      • 2001
      • 2002
      • 2003
      • 2004
    • ሐመር በዓመት
      • 1ኛ ዓመት
      • 2ኛ ዓመት
      • 3ኛ ዓመት
      • 4ኛ ዓመት
      • 5ኛ ዓመት
      • 6ኛ ዓመት
      • 7ኛ ዓመት
      • 8ኛ ዓመት
      • 9ኛ ዓመት
      • 10ኛ ዓመት
      • 11ኛ ዓመት
      • 12ኛ ዓመት
      • 13ኛ ዓመት
      • 14ኛ ዓመት
      • 15ኛ ዓመት
      • 16ኛ ዓመት
      • 17ኛ ዓመት
      • 18ኛ ዓመት
      • 19ኛ ዓመት
      • 20ኛ ዓመት
    • ስምዓ ጽድቅ በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • አዳዲስ ሙሉ ሕትመቶች
      • አዲስ ሐመር
      • አዲስ ስምዐ ጽድቅ
  • ያግኙን

ሐመር መጽሔት *

ጾመ ነቢያት በዓለም ማዕዘናት

Details
Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1352
  • ከዓለም ማእዘናት

ከኅዳር 15 ጀምሮ የሚገባውን የነቢያት ጾምን መጾም፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚታወቅ ሥርዓት አይደለም። ሁሉም የኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ጾም ይጾሙታል። ጾሙን የሚጾሙት ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ይህን ጾም ለመጾማቸው እንደ ዋና መሠረት የሚጠቅሱት ለጾሙ ፋሲካ የሆነውን የክርስቶስን ልደት በጾም ተዘጋጅቶ መቀበልን ነው።

አብዛኞቹ ‹‹Nativity Fast›› ይሉታል፤ ‹‹ጾመ ልደት›› እንደ ማለት ነው። የቅዱስ ፊሊጶስ በዓል ከተከበረ በኋላ በመግባቱም ‹‹ጾመ ፊሊጶስ›› ተብሎ መጠራቱም የተለመደ ነው። በተለያየ አጠራር ብንጠራውም፡ ነቢያት የጌታችንን መውረዱንና መወለዱን ተስፋ በማድረግ አስቀድመው የጾሙት ጾም በመሆኑ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ስያሜው ‹‹ጾመ ነቢያት›› መባሉ የሚታወቅ እውነታ ነው።

የባይዛንታይን አብያተ ክርስቲያናት ከኅዳር ፮ (Nov. 15) እስከ ታኅሣሥ ፲፭ (Dec. 24) በመጾም ልደተ እግዚእን በታኅሣሥ ፲፮ (Dec. 25) ያከብራሉ። የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ አንዳንዶቹ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ግን ጾሙን ኅዳር ፲፱ (Nov. 28) ይጀምራሉ። የኅዳር ፲፱ ስንክሳርም ‹‹ወበዛቲ ዕለት ኮነ ጥንተ ጾመ ስብከተ ጌና ዘሮም ወአፍርንጊ ወሶርያ ወአርማንያ ዘእንበለ ግብጽ ወኢትዮጵያ ወኖባ - በዚችም ዕለት የሮም፣ የአፍርንጊ፣ የሶርያ፣ የአርማንያ ክርስቲያን ከግብጽ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኖባ በቀር የስብከተ ጌና ጾምን የሚጀምሩበት ነው›› ብሎ የተጠቀሱት አብያተ ክርስቲያናት ጾሙን በኅዳር ፲፱ የሚጀምሩ መሆናቸውን ያስረዳል። አስቀድመን በጽሑፉ መጀመሪያ እንደ ገለጽነው ይህን የተመለከተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጾሙ በኅዳር ፲፭ እንዲጀመር ያዛል።

Read more: ጾመ ነቢያት በዓለም ማዕዘናት

ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ሕመምተኞች ያላት አስተዋጽኦ

Details
Written by: በዶ/ር እንግዳ ግርማ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1529
  • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን

፩. መግቢያ

የአእምሮ ጤንነት ችግር የአስተሳሰብ፣ የስሜት፣ የጠባይ እንዲሁም ሌሎች የአእምሮ ተግባራት መዛባት የሚያመጡት የጤና እክል ነው። ይህም በአንጻሩ ቀላልና ጊዜያዊ ከምንላቸው የውጥረት ስሜቶች እስከ ከባድ የአእምሮ መቃወስ የሚያካትት ነው። ምንም እንኳን ከፍተኛ የአእምሮ ሕመም ደረጃ ባይደርሱም ሌሎች የውጥረት፣ የጭንቀት፣ የእንቅልፍ ማጣት ወይም የጠባይ መቀየሮችም በጊዜያዊነት ወይም ከፍ ባለ መጠን በተደጋጋሚ ይከሠታሉ። 

የአእምሮ ችግር መንሥኤዎች ብዙና የተለያዩ ናቸው። ሥነ ሕይወታዊ (Biological)፣ ስነ ልቡናዊ (Psychological)፣ ማኅበራዊ (Social) መንስኤዎች ብሎ መክፈል የተለመደና እስካሁን ተቀባይነት ያለው የአስተሳሰብ ማቀፍ ነው። ማኅበራዊ (social) መንሥኤ በሚለው ውስጥ ባህላዊ (cultural) እና መንፈሳዊ (Spiritual/Religious) ሁኔታዎችም ይካተታሉ። 

የአእምሮ ሕመም ሲባል ራሱን የጣለ፣ የተዳደፈ፣ ቆሻሻ የሚለቅም፣ አደገኛ ሰው ማሰብ የተለመደ ነው። በርግጥ እጅግ በጣም ጥቂቱ የአእምሮ ሕሙማን ብቻ እንዲያ ያለውን የአእምሮ መቃወስ ምልክቶች ያሳያሉ። የሚበዙት ሕመሞች ምክንያት አልባ ጭንቀት፣ ድባቴ፣ እንቅልፍ ማጣት ወይም ከአእምሮ ዕድገት ጋር የተገናኙ ችግሮች ናቸው። በዐይን አይቶ ለመለየትም አይቻልም። ሁሉም ሊባሉ በሚችል ደረጃ ዘመናዊ የንግግር ወይም የመድኀኒት ሕክምና ያላቸው ቢሆንም አብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል ወደ ጤና ተደራሽ አይደለም። በሀገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የአእምሮ ሕመም ካላቸው ሰዎች መካከል ከመቶ ውስጥ ሰማንያ ዘጠኝ  የሚሆኑት ህክምና አያገኙም። (ምንጭ) በቂ ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው የአእምሮ ሕሙማን በጣም ብዙ የሕይወታቸውን ዘመናት በመታሰር፣ ተስፋ በመቁረጥና በመደብደብ እንዲሁም በብቸኝነት ያለሥራ ያሳልፏቸዋል። የቤተሰብ ኑሮና ብዙ የሀገር ንዋይ እንዲሁ እንደባከነ ያልፋል። 

Read more: ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ሕመምተኞች ያላት አስተዋጽኦ

ቅጽል

Details
Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1195
  • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን

ውድ አንባብያን በባለፈው ዕትማችን ስለ ወገን አመልካች ቅጽልና ስለ አኃዝ ቅጽል ምንነት ተመልክተናል። የቤት ሥራ መስጠታችንም ይታወሳል፤ በአግባቡ እንደሠራችሁትም ተስፋ እናደርጋለን። ለማረጋገጥ ያህል እንደሚከተለው መልሱን አስቀምጠናል።

፩. በሚከተሉት ቃላት ምዕላድን  በመጨመር በነጠላና በብዙ፣ በሴትና በወንድ ወገን አመልካች ቃላትን (ቅጽሎችን) መሥርቱ።

ተ.ቁ ስም ለነጠላ ወንድ ለነጠላ ሴት ለብዙ ወንድ ለብዙ ሴት
፩ ገሊላ ገሊላዊ ገሊላዊት ገሊላውያን ገሊላውያት
፪ ቅድም ቀዳማዊ/ ይ ቀዳማዊት/ይት ቀዳማውያን ቀዳማውያት
፫ ሣልስ ሣልሳዊ/ይ ሣልሳዊት/ይት ሣልሳውያን ሣልሳውያት
፬ ሀገር ሀገራዊ ሀገራዊት ሀገራውያን ሀገራውያት
፭ ሐሳብ ሐሳባዊ ሐሳባዊት ሐሳባውያን ሐሳባውያት


፪. ውድ አንባብያን የሚከተሉትን  ቁጥሮች ለዕለታት ሲሆን እንዴት መጠቀም እንደምንችል በፊደል በመጠቀም (አኀዝ ቅጽሎችን) መሥርቱ። 

፲፮፣ ፲፯፣ ፲፰፣ ፲፱፣ ፳፣ ፳፩፣ ፳፪፣ ፳፫፣ ፳፬፣ ፳፭፣ ፳፮፣ ፳፯፣ ፳፰፣ ፳፱፣ ፴

፲፮= ዐሥሩ ወሰዱሱ፤ ፲፯- ዐሥሩ ወሰብዑ፤ ፲፰- ዐሥሩ ወሰሙኑ፤ ፲፱- ዐሥሩ ወተሥዑ፤ ፳- እስራ፤ ፳፩-እስራ ወአሚሩ፤ ፳፪-እስራ ወሰኑዩ፤ ፳፫-እስራ ወሠሉሱ፤ ፳፬-እስራ ወረብዑ፤  ፳፭-እስራ ወሐሙሱ፤ ፳፮-እስራ ወሰዱሱ፤ ፳፯-እስራ ወሰብዑ፤ ፳፰-እስራ ወሰሙኑ፤ ፳፱-እስራ ወተሥዑ፤ ፴-ሠላሳ።

ውድ አንባብያን  የቤት ሥራውን በዚህ መልኩ ሠርታችሁት ከሆነ ትክክል ናችሁ። በዚህ ዕትማችን ደግሞ ለዚህ ክፍል የመጨረሻ የሆነውን ግልጠ ዘ ቅጽልን እንመለከታለን።

ግልጠ ዘ ቅጽል ፡- ይህ የቅጽል ዓይነት ግልጠ ዘ የተባለው “የ” ተብለው የሚፈቱትና፣ በግስ ላይ ተጨምረው ስምን እንዲገልጽ በግስ ላይ የሚቀጸሉት  ወይም ግስን ቅጽል እንዲሆን የሚያደርጉት አገባቦች በግልጥ ስለሚታዩ ነው።

ግልጠ ዘ ቅጽል የሚባሉት ዘ፣ እንተ እና እለ ናቸው። ባለፉት ዕትሞቻችን የቅጽል ዓይነቶችን ስንመለከት  መምህር አስበ ድንግል ግእዝ ልሳነ ኢትዮጵያ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፳ ላይ የውስጠ ዘ ዓይነቶችን  “ግልጠ ዘ እና ውስጠ ዘ”  ብለው እንደሚከፍሏቸውና በውስጠ ዘ ቅጽል ምድብ ውስጥም  የሚዘረዘሩትን ተመልክተናል። ግልጠ ዘ ቅጽሎች በሚለው ምድባቸው ደግሞ የሚዘረዝሯቸውም  ከላይ የተገለጹትን  ማለትም  “ዘ” ን፣ “እንተ” ን እና “እለ” ን ነው።

አለቃ ኪዳነ ወልድም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘ መጽሐፋቸው (ገጽ ፹፱-፺፩) በመጀመሪያ ዘርና ነባር ብለው በሁለት ከከፈሏቸው በኋላ በእያንዳንዳቸው ደግሞ ሌሎች ንኡሳን ክፍሎች እንደሚዘረዝሩ ጠቁመናል። ነባር ቅጽሎች ብለው ከሚዘረዝሯቸው መካከል ግልጠ ዘ የሚባሉት ቅጽሎች ይገኛሉ። እነዚህ ግልጠ ዘ የሚባሉት “ዘ” ፣ “እንተ” እና “እለ” እንደሆኑ ይዘረዝራሉ።

መምህር ኀይለ ኢየሱስ መንግሥት የልሳነ ግእዝ መማሪያ ብለው ባዘጋጁት መጽሐፋቸው ግልጠ ዘን ግልጠ (የ) ብለው ይሰይሙትና ሲገልጹትም  “ዝንቱ ዘመደ ቅጽል እንዘ ይወድቅ መልዕልተ ግስ ይከሥትዎ ለስም። (ስሞችን የሚገልጽ ማለት ነው።) ብለው ያስረዱና በዝርዝር ሲያስቀምጧቸውም “ግልጠ (የ) ቅጽላት ዘይትበሀሉ “እንተ” ፣ “ዘ” ወ “እለ” ውእቶሙ።”  (ገጽ ፺፭) በማለት ይጠቅሷቸዋል።

ከላይ መምህራኑ በገለጹት መሠረት ግልጠ ዘ የሚባሉት “እንተ”፣ “ዘ” እና “እለ” ናቸው። ግልጠ ዘ የተባሉበት ምክንያት አንድ ግስ ቅጽል እንዲሆን የሚያደርጉት እነዚህ አገባቦች ወይም ቃላት በአካል ግሱ ላይ ተጨምረው ስለሚታዩ ነው። በአገልግሎት ደረጃ የተወሰነ ልዩነት ስላላቸው ልዩነታቸውን አንድ በአንድ እንመለከታለን።

“ዘ” ይህ ቅጽል ለአንድ ለብዙ ለሴት ለወንድ ይቀጸላል። ወይም ይህ አገባብ የተጨመረበት ግስ ለአንድና ለብዙ፣ ለሴትና ለወንድ መቀጸል ይችላል። ምሳሌ፡-

- ዘተንሥአ እሙታን አምላክ ውእቱ።

- ዘነሥአት ዕፍረተ ብእሲት ተመይጠት መንገለ ቤታ።

- ዘነበቡ ትንቢተ ነቢያት ውእቶሙ።

- ዘይቀድሓ ማየ አንስት ወረዳ መንገለ ቀላይ።

“እንተ”  ይህ ቅጽል ከቍጥር አንጻር ለአንድ  ብቻ ሲሆን ከጾታ አንጻር ግን ለሴትና ለወንድ ይቀጸላል። ወይም ይህ አገባብ የተጨመረበት ግስ ለአንድ (ለነጠላ ቁጥር) ብቻ ሆኖ ለሴት ለወንድ መቀጸል ይችላል። ምሳሌ፡-

- ዝ ውእቱ ሕፃን እንተ ያፈቅሮ አቡሁ።

-ዛቲ ይእቲ መርዓት እንተ ታፈቅር ብእሴሃ።

“እለ” ይህ ቅጽል ከቍጥር አንጻር ለብዙ  ብቻ ሲሆን ከጾታ አንጻር ግን ለሴቶችም ለወንዶችም ይቀጸላል። ወይም ይህ አገባብ የተጨመረበት ግስ ለብዙ ቁጥር ብቻ ሆኖ ለሴቶች ለወንዶች መቀጸል ይችላል። ምሳሌ፡-

-ቡሩካን ውእቶሙ አበው እለ ሠርዑ ለነ ሥርዐተ።

-አንስት እለ ነሥኣ መኃትዊሆን ተሰብሓ በፈጣሪሆን።

ውድ አንባብያን ከላይ የቀረበው ትምህርት ግልጽ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን። ከላይ የቀረበውን ትምህርት መሠረት አድርጋችሁ ግልጠ ዘ ብለን በዘረዘርናቸው ቅጽሎች በእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዐረፍተ ነገሮችን ሥሩባቸው።

“ዘ”

“እንተ”

“እለ”

ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት

Details
Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 1620
  • የማኅበሩ መልእክት

ቤተ ክርስቲያን ከዓለመ መላእክት ጀምራ የውስጥም ሆነ የውጭ ፈተናዎችን እንደ አመጣጣቸው እያስተናገደች ኖራለች፤ ዛሬም አለች፤ ወደ ፊትም ትኖራለች። በሐዲስ ኪዳንም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ  በደሙ የመሠረታት አማናዊት ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በመከራ ነውና መከራ መስቀሉን ተሸክማ አለች፤ ወደ ፊትም ትኖራለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መከራን እየሸሸች ሳይሆን በመከራም እያለፈች ለሀገር ያበረከተችው አስተዋጽኦ በየትኛውም ምድራዊ ሚዛን ሊለካ አይችልም። የምህንድስና ጥበብን፣ የትምህርት ማእከልን፣ የሥነ ጽሑፍ ሙያን፣ የዘመን አቆጣጠርን፣ የፍልስፍና ጥበብን ወዘተ. ከሁሉ  አስቀድማ  ለዓለም አበርክታለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ሁሉ አስተዋጽኦ አበርክታም፣ ፍትሕ በተጓደለበት ዓለም ነውና የምትኖረው ሊያጠፏት ሌት ከቀን የሚደክሙት በርካቶች ናቸው። ለዘመናት መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ጥቃቶችን እያስተናገደች አልፋለች፤ ዛሬም የግፍ ጽዋዕን እየተጎነጨች ትገኛለች።

ይሁን እንጂ  ዕለት ዕለት ምእመናኗን “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት” ባለው በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ እያጽናናችና እያበረታች የምትገኝ እናት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ጥበብና ማስተዋል በተሞላበት አኪያሄድ ይህን የመከራ ዘመን በትዕግሥት እንድናልፍ አደራዋን ታስተላልፋለች።

አሁን ያለንበት ዘመን  እጅግ የከፋ ነው። ሰው በሰውነቱ መኖር የማይችልበት፣ በማንነቱ ማለትም በሃይማኖቱና በዘሩ (በጎሣው) እየተለየ የግፍ ግፍ የሚፈጸምበት፣ የተገደለ ሰው የቀብር ቦታ እንኳን የሚከለከልበት፣ ሰውን ሰው የሚበላበት ዘመን ላይ እንገኛለን። በዚህም ሁሉ ግን “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት” ያለንን የሐዋርያውን ቃል በማስተዋል ወቅቱን የጠበቀ ራስን የመጠበቅና የመከላከል ሥራን ልንሠራ ይገባል። ለዚህም ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ አካል ድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። ለምሳሌ፡-

በአባቶች በኩል ከመንግሥት ጋር ጥብቅ የሆነ ውይይት በማድረግ መንግሥት በራሱ አደጋውን እንዲከላከል ያላሠለሰ ጥረት ማድረግ ይገባል። ይህ ካልሆነም ለምእመናኑ አግባብነት ያለው መመሪያ መስጠት ይገባል። መዋቅሩን ጠብቆ ወጣቱ እንዲደራጅ ማድረግ፣ በስሜት ሳይሆን ጥበብና ማስተዋል በተሞላበት መንገድ እንዲጓዝ ከፊት እየሆኑ መምራት የግድ ነው።

አባቶቻችን ከውጭ ላለ ጠላት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ጠላት አሳልፎ የሰጠንን የእርስ በእርስ መለያየት፣ የውስጥ የአሠራር ብልሹነት፣ የአስተዳደር ክፍተት ወዘተ. አጥብቀው ማውገዝና የውስጥ ሰላም መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። የውስጥ ሰላም ሳይኖርና የእርስ በእርስ መበላላት ሰፍኖ ባለበት ሰዓት የውጭ ጠላትን እመክታለሁ ማለት ሞኝነት መሆኑን መረዳትና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማምጣት ይኖርባቸዋል። ዕለት ዕለት ‹‹ጸልዩ በእንተ ሰላም፤ ስለ ሰላም ጸልዩ›› እያለች የምታስተምርና የምትጸልይ ቤተ ክርስቲያን ሰላሟን ሊነፍጓት የሚሯሯጡትን አካላት ዘመኑን በዋጀ፣ ጥበብና ማስተዋል በሞላበት ኃይል መመከት ይኖርባታል። ለዚህም አባቶቻችን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉና ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።

በየጊዜው እየተወሰነ ነገር ግን ተግባራዊ መሆን ያልቻለውን መሪ ዕቅድ በአግባቡ ትኩረት በመስጠትና ወደ ተግባር በመለወጥ የቤተ ክርስቲያን ችግር እንዲፈታ መታገል ያስፈልጋል። በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል በየወቅቱ ጥሩ ጥሩ የሆኑ ውሳኔዎች ይወሰናሉ፤ ይህም ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ መሆኑን እንድናምን የሚያስችል መሆኑን እንረዳለን። ይሁን እንጂ በውሳኔው ደስ ሲለን ወደ ተግባር ባለመለወጡ ውሳኔ ባገኘው ችግር ሁሉ በተደጋጋሚ እንሠቃይበታለን። ይህ እንዳይሆን ከውሳኔው ጋር የተግባር ሰው ለመሆንም ቆርጦ መነሣት ይገባል።

ምእመኑ የአባቶችን ትእዛዝ ከዐይኑ ብሌን ባልተናነሰ እየጠበቀ ከስሜት የወጣ የውስጥ አንድነት መፍጠር፣ ጥበብ የተሞላበትን ጉዞ መጓዝ፣ በሆነው ሁሉ የሚሸበረውን ግያዝን ሳይሆን ‹‹ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ›› (፪ነገ.፮፡፲፮) ያለውን ኤልሳዕን በዐይነ ልቡና መቃኘት፣ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የሚመጣበትን አቅጣጫ መምረጥ ይኖርበታል። ሀገሩን፣ ቤተ ክርስቲያኑን፣ ሃይማኖቱን መጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ መተባበርና መደራጀት እንደሚያስፈልግ ተረድቶ ጥቃቅን ከሆኑት መለያየት ወጥቶ የጠነከረ ኅብረት መፍጠር ይኖርበታል።

ወጣቱ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደ ተባለው ከአካባቢ፣ ከአጥቢያ፣ ከጎጥ ወዘተ በወጣ እና ሰፊ በሆነ አንድነት መተባበር ይኖርበታል። እንደ ሀገር የሚስተዋለው መለያየት እንደ አጥቢያም ይስተዋላል። ለምሳሌ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ከማኅበረ ካህናቱ፣ ማኅበረ ካህናቱ ከስብከተ ወንጌል ክፍሉ፣ ስብከተ ወንጌል ክፍሉ ከሰንበት ትምህርት ቤቱ፣ … ወዘተ ተናቦ አገልግሎት የሚፈጸምባቸው አጥቢያዎች በጭራሽ የሉም ማለት ባይቻልም ግን ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ እንደዚህ ያለውን መለያየት በማስወገድ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን፣ ሁሉም በፍቅርና በመደማመጥ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዘብ ሊቆም ይገባዋል።

መንግሥትም በሕዝብና፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ ይህ ሁሉ መከራ እየተፈራረቀ ዝም ብሎ ማየት አግባብነት እንደሌለው ተገንዝቦ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል። በሚመራው ሕዝብና በሚያስተዳድራት ሀገር ሰዎች በማንነታቸው እየተመረጡ መታረዳቸው፣ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው፣ ከተጎጂዎች ባልተናነሰ ሕመሙ ሊሰማው ይገባል። ሕገ ወጥነት ሰፈነ ሲባል ማጣፊያው የሚያጥረው ለራሱ እንደ ሆነ በመረዳት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የሚመጣበትን መንገድ መቀየስ አለበት።

በመንግሥት መዋቅር ሆነው ለሕዝብ ሰላምና ለሀገር ሉዓላዊነት ከመትጋት ይልቅ የግል ጉዳያቸውን ብቻ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱትን ራሱ መንግሥት አትወክሉኝም ሊላቸው ይገባል። ጥፋተኞችም ከእንዲህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር ተቆጥበው ዘመኑን የዋጀ የአመራር ጥበብን፣ የአስተዳደር ስልትን፣ ለእነርሱም ቢሆን የሚጠቅም የኑሮ ዘይቤን ሊከተሉ ይገባል።

 

''ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ፤ የማትረግፍ አበባ''

Details
Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 1834
  • ዐውደ ስብከት

በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ሃያ ስድስት እስከ ኅዳር አምስት ያለው ዓርባ ቀናትን የያዘው ጊዜ ዘመነ ጽጌ፣ ወርኃ ጽጌ በመባል የሚታወቅ ነው። ከዋክብትን ለሰማይ ውበት የፈጠራቸው አምላካችን እግዚአብሔር አበቦችን ደግሞ ምድርን ያስጌጧት ዘንድ ፈጥሯቸዋል። አበቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ላይ መታየት የጀመሩት በዕለተ ሠሉስ፣ በሦስተኛው የፍጥረት ዕለት ነው። ይህንን የመዘገበልን ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንዲህ ይለናል፡ ‹‹ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ››። (ዘፍ.፩፡፲፪)። ጊዜን በወቅቶች ከፍሎ፡ በየትኛው ጊዜ ምን ዓይነት ምስጋናን ማቅረብ እንደሚገባን ሥርዓትን በመጻሕፍቱ የሠራልን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፡ በዚህ የሙሴ ቃል ላይ ተነሥቶ በድጓ ዘጽጌ እንዲህ ይለናል፡- ‹‹በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ ወሤሞ ለፀሐይ ውስተ ጠፈረ ሰማይ ወርእየ ከመ ሠናይ ወካዕበ ይቤ ለታውፅዕ ምድር ጽጌያተ ዘበድዱ ወፍሬያተ ዘበበዘመዱ - በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ሠራ፤ ፀሐይንም በጠፈር ላይ አሠለጠነው፤ የሠራው ሁሉ መልካም እንደ ሆነ እግዚአብሔር አየ። ዳግመኛ ምድር አበቦችን በየግንዱ ፍሬዎችን በየነገዱ ታውጣ እንዳለ››። (ድጓ ዘጽጌ)።

እግዚአብሔር ሰውን በዕለተ ዓርብ የፈጠረው ሰማይን በከዋክብት፣ ምድርን በዕፅዋት አስጊጦ ከፈጸመ በኋላ ነው። ቅዱስ ያሬድ በዚሁ በጽጌ ድጓው እንዳለውም  ‹‹ወወሀበ ገነተ ምስለ ጽጌያት - ገነትንም በአበቦች እንዳሸበረቀች ሰጠው››። አንድ ደጋሽ ምግቡን አዘጋጅቶ፣ መጠጡን አሰናድቶ፣ ቤቱን አስውቦ የከበረ እንግዳውን በመጨረሻ እንደሚጠራው፡ እግዚአብሔር አምላክም ከፍጥረታት ይልቅ የከበረውን ሰው ሁሉን አሰናድቶ ከፈጸመ በኋላ ፈጠረውና በሁሉ ላይ ሾመው። አዳም ይኖርባት ዘንድ የተሰጠችው ገነትም ያማረችና የተዋበች ነበረች። ለዚህ ነው አምላካችን ‹‹ወይቤሎ ለአዳም ወሀብኩከ ርስተ ገነተ ትፍሥሕት በጽጌ ሥርጉተ ወበፍሬ ክልልተ- ለአዳም ‹አዳም ሆይ በፍሬ የተከበበች በአበባ የተሸለመች የደስታ ገነትን ለአንተና ለልጆችህ ርስት ትሆንህ ዘንድ ለርስትነት ሰጠሁህ›› በማለት ገነትን ‹‹የደስታ ገነት›› ብሎ የሰጠው። (ድጓ ዘጽጌ)።

አዳም በበደለ ጊዜ ግን ባሕርይው ጎሰቆለ። ከገነት ወጣ፤ ስደተኛ ሆነ፤ ምድርም በአዳም ምክንያት ተረገመች። 

ዕፀ በለስን በመብላት መዋቲነትን መረጠ። ምንም እንኳን ለዘላለም ሕይወት ቢፈጠርም በበደሉ ምክንያት የሚሞት ሆነ። እንደ አበባ ሊያብብ ቢፈጠርም ባለመታመኑ ምክንያት  ጠወለገ። አበባ እሳት ሲያቃጥለው፣ ፀሐይን ሲያጣ ወይም ሙቀቷ ሲበረታበት፣ ውኃን ሲጠማ፣ ውጫዊ ኃይል ሲያርፍበትና ከግንዱ ሲለይ ይጠወልጋል፣ ይረግፋል። አዳምም ከጕንደ ወይኑ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ጠወለገ፤ ሥጋው በመቃብር ነፍሱ በሲኦል ረገፈ። መልሶ እንዲያብብ ‹‹የሕይወት ውኃ›› የተባለ ‹‹ፀሐየ ጽድቅ›› ክርስቶስ ያስፈልገው ነበር። ለዚህ ደግሞ ለድኅነቱ ምክንያት የሆነችው ንጽሕት እመቤት ድንግል ማርያም ታስፈልገው ነበር። ለዚህ ነው ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል የገለጻት፡-

‹‹እስመ ርእየ ሕማማ ለአመቱ ወገብረ ኃይለ በመዝራዕቱ… መዝገቡ ለቃል ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ መድኃኒተ ሕዝብ - የባርያይቱን መዋረድ አይቷልና ኃይልን በክንዱ አደረገ፤ የማትረግፈውን አበባ የዓለም መድኃኒት የቅዱሳን መዓዛ እንድትሆን አደላት›› (ድጓ ዘጽጌ)።

የማይረግፉ አበቦች

ቅዱስ ያሬድ ‹‹የማትረግፈው አበባ›› ያላት የማይረግፍ ዘላለማዊ ክብርና ቅድስና ያላትን እመቤታችንን ነው። ስለ እርሷ ‹የማይረግፍ አበባነት› ከማየታችን በፊት ግን፡ ሊቁ በአበባ ከመሰላቸው መካከል ከእመቤታችን ጋር ዐቢያን አምሳላት የሚባሉት መስቀሉ እና ቤተ ክርስቲያንም ይህ ቅጽል ይገባቸዋልና የእነርሱንም ‹የማይረግፍ አበባነት› በጥቂቱ ልናይ ይገባናል። ይልቁንስ ከጠቀስናቸው ከሦስቱም ይልቅ በአበባ ከሚመሰሉት ከዐራቱ ዐቢያን አንዱ የሆነው ጌታችን፡ ‹‹የማይረግፍ አበባ›› ነው፤ ሌሎቹም ይህን ጸጋ ያገኙት ከእርሱ ሥር ተጠልለው ነውና ከሁሉ አስቀድሞ የእርሱን አበባነት ማየቱ ተገቢ ነው።

የጌታችን አበባነት

ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ‹‹ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል›› ሲል የጌታችንን ከእመቤታችን መወለድ ገልጾአል። (ኢሳ. ፲፩፡፩)። ‹‹በትር›› የተባለችው ያለ ዘር የጸነሰችውና ከእሴይ የዘር ሐረግ ሥር የተገኘችው ድንግል ማርያም ስትኾን ከበትሩ ላይ ያቆጠቆጠው አበባ ደግሞ ጌታችን ነው። ይህንን ሲያስረዳ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ትወፅዕ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ… ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም ቅድስት ይእቲ ወጽጌ ዘወፅአ እምኔሃ አምሳሉ ለወልድ - ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ያቆጠቁጣል፤ ይህች በትር ቅድስት ማርያም ናት፤ ከእርሷ የወጣው አበባም የወልድ ምሳሌ ነው››።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማርያም አበባ ነው። ከእርሷ በትርነት የተገኘ አበባ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን በመኃልየ መኃልይ ‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› ማለቱን ሊቃውንት ከጌታችን ጋር አያይዘው ተርጉመውታል። (መኃ.፪፡፩)። ሳሮን (Sharon) በይሁዳ የሚገኝ ሸለቆ ነው። ብዙ ውኃ ያለበትና መለምለም የሚችል ሥፍራ ነው። ነገር ግን በግብፅና በሶሪያ መካከል እንደ መንገድ የሚጠቀሙበት ጠባብ ሥፍራ በመኾኑ አበቦች የሉበትም። ‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› በሚለው ጥቅስ ላይ ሳሮን የሕዝበ እስራኤል፣ ቆላ ደግሞ የአሕዛብ ምሳሌ ናቸው። በእስራኤልም ሆነ በሕዝብ መካከል ፍሬ ድኅነት አልተገኘባቸውም ነበር፤ ድኅነትን የሚሰጠውን አበባ፣ ማለትም ክርስቶስን አላገኙም ነበርና። የማርያም አበባ የሆነው ጌታችን በተወለደ ጊዜ ግን በሳሮን ለተመሰሉት ለእስራኤላውያን ጽጌረዳ፣ በቆላ ለተመሰሉት አሕዛብም አበባ ሆነላቸው። ያውም በጊዜ ብዛት የማያልፍና የማይጠወልግ፣ የማይረግፍም አበባ።

‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› ያለው ጌታችን በጠቢቡ አንደበት ቀጥሎም ‹‹በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት›› ይላል። (መኃ.፪፡፪)። ይህን ያብራሩ ሊቃውንት ‹‹እርሱ የቆላ አበባ እንደ ሆነው ሁሉ የሚወዳቸው ሁሉ የእርሱን ምሳሌነት ተከትለው አበባ እንዲኾኑ ይፈልጋል። ማለትም የእርሱን መንገድና ምሳሌነት የሚከተል ነፍስ ሁሉ አበባ ይኾናል›› ይላሉ። በእሾህ እንደ ተከበበች የሱፍ አበባ ወዳጄ ብሎ የገለጻት የሰው ነፍስን ነው። ይህን ክፍል በተረጎመበት ትምህርቱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ‹‹ነፍስ ወደ መሲሁ የምትናፍቅ አበባ ናት፤ የዚህን ዓለም ፈተና ሁሉ ድል አድርጋ ወደ እርሱ የምትጓጓ አበባ ናት›› ይላል። (A Patristic Commentary on The Song of Songs; Fr. Tadros Y. Malaty;)

የቅዱስ መስቀሉ አበባነት

አበው ‹‹በሴት ጠፋን በሴት ዳን›› እንደሚሉት ሁሉ ‹‹በዕፅ ጠፋን በዕፅ ዳን››ም ይላሉ። ያጠፋን ዕፅ ዕፀ በለስ ሲኾን ያዳነን ዕፅ ደግሞ ዕፀ መስቀሉ ነው። የመስቀሉ ጠላቶች የሚበሰብስ መስሏቸው ዕፀ መስቀሉን ከመሬት ሥር ለሦስት መቶ ዓመታት ቀብረውት ቢቆዩም ‹‹የማይረግፈው አበባ›› መስቀሉ ግን ምንም ሳይኾን በቅድሰት ዕሌኒ ምክንያት ተገኝቷል። ዛሬም ማዕተብና መስቀሉ የሚወክለው ክርስትናን ጨርሶ ለመቅበር የሚጥሩ ሰዎች የማይሳካላቸው መስቀሉ ‹‹የማይረግፍ አበባ›› ስለ ሆነ ነው። ውኃ የማይጠጣ ተክል ይጠወልጋል፤ መስቀሉ ግን ‹‹እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ›› ያለውን የክርስቶስን ደም ‹ጠጥቶ› ስለ ለመለመ የሚጠወልግ አይደለም - የማይረግፍ አበባ ነው እንጂ። (ዮሐ.፬፡፲፬)።

ቅዱስ ያሬድም ‹‹በከመ ይቤ ሰሎሞን በእንተ ማርያም ንዑ ንትፈጋዕ ወኢይኅልፈነ ጽጌ ደመና መስቀል ዘዮም አብርሃ በሥነ ማርያም - ሰሎሞን ስለ ድንግል ማርያም ሲናገር እነሆ ክረምቱ አልፎ በረከት ተተካ እንዳለ የክርስቶስ መስቀል ከድንግል ማርያም ባሕርይ በተገኘው (በተወለደው በክርስቶስ) ዛሬ አብርቷልና የበረከት አበባ ሳያልፈን ኑ እንደሰት›› ይላል። (ድጓ ዘጽጌ)። ለዚህም ነው መዘምራን የመስቀል በዓል ሲደርስ ‹‹መስቀል አበባ ነህ ውብ አበባ አደይ አበባ ነህ ውብ አበባ›› እያሉ የሚዘምሩት።

የቤተ ክርስቲያን አበባነት

ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያንን አበባነት ሲመሰክር እንዲህ አለ፡- ‹‹ልዑለ ረሰዮ ለመሠረትኪ አረፋትኪ ዘመረግድ ደቂቅኪ ምሁራን በኀበ እግዚአብሔር…- የተለየሽ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሆይ መሠረትሽን ከፍ ከፍ አደረገው። ግድግዳዎችሽን በመረግድ በወርቀ ደማቸው። ልጆችሽ በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠኑ ናቸው። በምድረ በዳ እንዳለች የሱፍ አበባ ለጋ የሆነ የወይን አበባ ሽታን ትሸቻለሽ። የበረከትንም ፍሬ ታፈሪያለሽ››።

ዳግመኛም በዚሁ በድጓ ዘጽጌው ‹‹ሐረገ ወይን እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕፁቂሃ እንተ በሥሉስ ትትገመድ  ወታፈሪ ለነ አስካለ በረከት ሲሳዮሙ ለቅዱሳን - ሥሯ በምድር ጫፏ በሰማይ የሆነች በፈቃደ ሥላሴ ተገርዛ የምትለቀም የበረከት ፍሬን የምታፈራልን የወይን ሐረግ የተለየች ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ናት›› ይላል።

ቤተ ክርስቲያን ‹‹ፍሬ›› የተባለ የክርስቶስን ሥጋ ወደሙን ዘወትር የምትሰጠን የማትረግፍ አበባ ናት። ብዙዎች ሊያረግፏትና ሊያጠወልጓት ለዘመናት ቢዘምቱባትም፣ ዲያቢሎስ ጦሩን ሁሉ ቢወረውርባትም፡ ልክ ለምለም አበባ በረጅም ሥሩ ውኃን ከመሬት እየሳበ የበለጠ እንደሚያብበው ‹‹የውኃ ግድግዳ የደም መሠረት›› እያልን የምንዘምርላት ቤተ ክርስቲያንም የበለጠ አበበች እንጂ አልጠወለገችም። አትጠወልግምም።

የእመቤታችን አበባነት

‹‹የማኅጸንሽ ፍሬ ቡሩክ ነው›› ለተባለው ለእውነተኛው ፍሬ መገኛ የሆነችው እመቤታችን የማትረግፍና ዘወትር የምታብብ አበባ ናት። እመቤታችን በማይጠወልግና በለምለም ተክል መመሰሏ ነገረ ማርያምን ለተማረ ሰው አዲስ አይደለም።

ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እሳቱ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም እሳቱን ሳያጠፋው ያየው ምሥጢር ለእሳተ መለኮትና ለትሥብእት ተዋሕዶ ምሳሌ ነው። ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ››። (ዘፀ. ፫፡፪)። እሳት ተዋሕዶት ያልጠወለገው ሐመልማል ለእመቤታችን ምሳሌ እንደ ሆነ ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ሲያስረዳ ‹‹ጌታችን ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ ከእርሷ ወደ ሰው ሕይወት የበራው የመለኮት ብርሃን ሐመልማሉን አላቃጠለውም። በተመሳሳይም በእርሷ ውስጥ ያለው የድንግልናዋ አበባም አምላክን በወለደችው ጊዜ አልረገፈም›› ይላል። ሌሎች እናቶች ሲያገቡና ሲወልዱ ጽጌ ድንግልናቸው ይወገዳል፤ የማትረግፈው አበባ ድንግል ማርያም ግን ወልዳም ጽጌድንግልናዋ አልተለወጠም።

የኢየሩሳሌምን ጥፋት እንዳያይ እግዚአብሔር በእንቅልፍ ምክንያት የሠወረው አቤሜሌክ፡ ከቀጠፋት ከስልሳ ስድስት ዓመት በኋላ ሳትጠወልግና ሳትደርቅ ወተቷ ሲንጠባጠብ የተገኘችው የበለስ ቅጠል ምሳሌነቷ ለእመቤታችን እንደ ሆነ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አመሥጥረው ያስረዳሉ። (ተረ.ባሮ. ፫)። ይህች ቅጠል ተቀጥፋ ከስልሳ ስድስት  ዓመታት በኋላም ከነ ልምላሜዋ መገኘቷ የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና፣ ንጽሕናና ቅድስና  የሚያሳይ ነው። 

የካህኑ አሮን የደረቀ በትር መለምለሙም ለእመቤታችን ሌላው ምሳሌ ነው። ‹‹እንዲህም ሆነ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፥ ለመለመችም፥ አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች››። (ዘኁ. ፲፯፡፰)። ይህም አስቀድመን እንዳየናቸው ምሳሌዎች ሁሉ መጠቀስ የሚችል ነው።

‹‹በሰላመ ገብርኤልን›› አዘውትሮ የሚጸልይና ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር የነበረው አንድ አስቴራስ የተባለ ዲያቆን ነበር። ይህም ዲያቆን ወደ ሩቅ አገር እየሔደ ሳለ ጨካኞች በመንገድ አገኙትና ገድለውት ሳይቀብሩት ከመንገድ ዳር ትተውት ሔዱ። ነገር ግን ሌሎች መንገደኞች ሲያልፉ አይተውት ከዚያው ከመንገዱ ዳር ቀብረውት ሔዱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በዚያ አቅራቢያ ባለ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያገለግል አንድ መልካም ዲያቆን እመቤታችን በራእይ ትገለጣለች። ጓደኞቹን አስተባብሮም የዲያቆን አስቴራስን አስከሬን ከመንገዱ ዳር በማውጣት በቤተ ክርስቲያን ግቢ እንዲቀብሩት ታዛቸዋለች። ዲያቆኑም እመቤታችን እንዳዘዘችው ሌሎች ዲያቆናትን ይዞ ወደ ቦታው በመጓዝ አስከሬኑን ቢያወጡት ርሔ እንደሚባል ሽቱ መዓዛው እጅግ ደስ የሚያሰኝ ከአስከሬኑ የበቀለ  የጽጌሬዳ አበባን አገኙ። በዚህም እየተደነቁ አስከሬኑን በክብር ገንዘውት በታዘዙት ሥፍራ ቀበሩት። ይህን የተአምረ ማርያም ታሪክ አባ ጽጌ ድንግል እንዲህ ተቀኝቶበታል፡- (ሊቀ ጠበብት አስራደ ባያብል፣ የማሕሌተ ጽጌ ትርጉምና ታሪክ፣ ፳፻፬፣ ፳)

ጽጌ አስተርአየ ሠሪጾ እምዐፅሙ፣

ለዘአምኀኪ ጽጌ ለገብርኤል ምስለ ሰላሙ፣

ወበእንተዝ ማርያም ሶበ ሐወዘኒ መዓዛ ጣዕሙ፣

ለተዐምርኪ አሐሊ እሙ፣

ማሕሌተ ጽጌ ዘይሰመይ ስሙ።

ትርጉም፡-

የክርስቶስ እናቱ የሆንሽ ድንግል ማርያም ሆይ

መልአኩ ገብርኤል ደስ ይበልሽ እያለ ካቀረበልሽ ሰላምታ ጋር

አበባን ይዞ እጅ ከነሣሽ ሰው ዐፅም የጽጌሬዳ አበባ በቅሎ ታየ

ስለዚህም የተአምርሽ ዜና ባስደሰተኝ ጊዜ ስሙ ማኅሌተ ጽጌ የሚባል ምስጋናን አመሰግንሻለሁ። (ማኅሌተ ጽጌ)

አንድ ሌላ የእመቤታችን ወዳጅ የሆነ ዲያቆንም እንዲሁ በግፍ ተገድሎ በተቀበረ በአራተኛ ቀኑ፡ በመቃብሩ ላይ ፈርከሊሳ የተባለ አበባ ይበቅላል። የአበባው ቅጠል ላይም ዲያቆኑ በሕይወት እያለ ዘወትር ይጸልየው የነበረው ‹‹በሰላመ ገብርኤል›› ጸሎት ተጽፎበት ተገኝቷል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በመልክአ ውዳሴው፡-

ማርያም ጽጌ ዘትምዕዚ እምፈርከሊሳ፣

ይማዖ ጽድቀ ዚአኪ ለዘዚአየ አበሳ፣

ከመአራዊተ ይመውእ አንበሳ።

ትርጉም፡-

ፈርከሊሳ ከምትባል የሽቱ እንጨት መዓዛ ይልቅ

አንበሳ አራዊትን እንደሚያሸንፍ

ጽድቅሽ፣ መዓዛ ቅድስናሽ የኔን በደል ያጥፋው። (መልክአ ውዳሴ)

በማሕሌተ ጽጌም ይህንና ይህን የመሰለውን ሁሉ በማንሣት እመቤታችንንና ጌታችንን በአበባ እየመሰሉ ካህናቱና ምዕመናኑ ሲያመሰግኑ ያድራሉ።

ማጠቃለያ፡- የዚህ ዓለም ሀብትና ጊዜ እንደ ጤዛ የሚረግፉ፣ እንደዚህ ዓለም አበባ የሚጠወልጉ ናቸው። የሰው ልጅ በዚህ ምድር ቢያዝን ኀዘኑ ዘላለማዊ አይደለም። ቢደሰትም የዚህ ምድር ደስታና ፈንጠዝያ የሚያልፍ ነው። የሰው የጉብዝና ዘመንና የምድር ሕይወት እንኳን የሚረግፍ ነው። ነቢዩ የሰው ልጅን እንደ ሣር መጠውለግ ሲገልጽ ‹‹የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፥ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ?›› ይላል። (ኢሳ.፶፩፡፲፪)።

የሰው ልጅ ከሚጠወልግ ከዚህ ምድር ሕይወቱ ይልቅ ዘላለማዊውን የማይረግፍ ሕይወት ያገኝ ዘንድ ‹‹የማይረግፉ አበቦች›› ያልናቸውን ሊጠጋ ይገባዋል። የጌታችንን ሥጋውን ሊበላ ደሙን ሊጠጣ፣ ጌታችን ራስ ለሆነላት ለአካሉ ለቤተ ክርስቲያን ብልት ለመኾን ሊፋጠን፣ በእመቤታችን አማላጅነትና በመስቀሉ መማጸኛነት አምኖና ተመርኩዞ መንፈሳዊ ሕይወቱን ሊያበረታ ይገባዋል። ይህን በማድረግም ‹‹የክርስቶስ አበባ›› የተባለች ነፍሱን ከመጠውለግና ከመርገፍ ይታደጋታል።

‹‹ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ - የማትረግፍ አበባ›› ብሎ ቅዱስ ያሬድ የጠራት እመቤታችን ሁላችንንም ከመከራ ትጠብቀን።

ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ “ሰቈቃወ ድንግል”

Details
Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 1431
  • ትምህርተ ሃይማኖት

የቃሉ ተናጋሪ አባ ጽጌ ድንግል ነው። ቃሉን የተናገረውም የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደቷን፣ በስደቷ ጊዜም የደረሰባትን መከራና ኃዘን አምልቶና አስፍቶ በገለጸበትና በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና አምላክን የወለደች ድንግል ማርያምንም ባመሰገነበት ክፍሉ ነው። ሙሉ ቃሉን እንደሚከተለው እንመልከተው።

“ሰሚዖ ሕፃን ለእሙ ገአራ፤ ባረከ ኰኵሐ ወአንቅዐ ማየ እምታሕተ እግራ፤ ወእምኔሁ ለጽምዓ ትስተይ አመራ፤ ከመ ኢይስተይዋ ሰብአ ሀገር ለይእቲ ማይ አምረራ፤ ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ፤  ሕፃኑ የእናቱን ጩኸት (ለቅሶ) ሰምቶ፤ ዐለቱን ባርኮ ከቆመችበት ቦታ ውኃ አፈለቀ፤ ከውኃውም ትጠጣ ዘንድ አመለከታት፤ የዚያች ሀገር ሰዎች እንዳይጠጧት ያችን ምንጭ አመረራት፤ ከሩቅ  ለመጡት ግን መድኃኒት የጣፈጠችም አደረጋት።” (ሰቈቃወ ድንግል)

ይህ ኀይለ ቃል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ የደረሰባትን መከራና ሁሉን የሚችለው አምላክ ወልደ አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት መካከል አንዱን የሚያስታውሰን ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው ሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ይዘው “የተወለደው የአይሁድን ንጉሥ የት አለ” እያሉ ሲመጡ በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ በቅንዐት ተነሳሳና ሊገድለው ፈለገ። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ ነገረውና በሌሊት እናቱንና ሕፃኑን ይዞ ወደ ግብፅ ሸሸ። ወንጌላዊው ማቴዎስ ይህን ታሪክ “እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ገብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ኑር አለው። እርሱም በሌሊት ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ።” (ማቴ.፪፥፲፫-፲፬) በማለት እንደጻፈው ሁሉን የሚችል ፣ ሁሉ የእርሱ የሆነ አምላክ ጠላት ተነሣበትና ስደተኛ ሆነ። 

ሰው ከሀገሩ ወጥቶ ስደተኛ ሲሆን ስንቁ ያልቃል፤ ይራባል፤ ይጠማል፤ የሚሰጠው ሊያገኝም ላያገኝም ይችላል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም በሄሮድስ ላይ አድሮ በጠላትነት እንዲነሣሣ ያደረገ ሰይጣን በሰዎች ላይ እያደረ የሚያዝንላቸው አጥተው ስለነበረ ተራበ፤ ተጠማ፣ ዐለት ሰንጥቆ ውኃ አፍልቆ የሚያጠጣው አምላክ በተዋሐደው ሥጋ ተጠማና አለቀሰ። የልጇን ልቅሶ ስትሰማ እናቱም ምርር ብላ አለቀሰች። ሁሉን የሚችል አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ቢወሰንም አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን ሲያስረዳ፣ ዐለቱን ባርኮ ውኃ አፈለቀ።  ማፍለቁ ብቻ ሳይሆን ያፈለቀው ውኃ ለስደተኞች የሚጥምና የሚጣፍጥ በአካባቢው ላሉትና በክፋት ለተሞሉት ሰዎች ደግሞ የሚመር ሁለት ዓይነተ ጣዕም ያለው ውኃ ሆነ።

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይህን ምሥጢር የገለጸለት ደግ አባት አባ ጽጌ ድንግልም  ከእግዚአብአብሔር ሁሉን ቻይነት አንጻር የማያስደንቅ ቢሆንም ከፍጡራን ባሕርይና ችሎታ አንጻር ግን እንዲህ እጅግ የሚያስደንቀውን ምሥጢር ገለጸልን። ሰዎች እርሱ የሰጣቸውን ውኃ ሲከለክሉት እርሱ ግን ከአንድ ምንጭ ተገኝቶ ለአንዱ ጣፋጭ ለሌላው መራራ የሆነ ተአምረኛ ውኃ አፈለቀ። ይህ እጀግ የሚያስደንቅና ልዩ የሆነ ምሥጢር ያን ጊዜ እንደ አዲስ የተጀመረ ሳይሆን ጥንትም ሀልወቱን፣ መግቦቱን፣ አምላካዊ ጥበቃውን ሲገልጽበት የኖረ፣ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ የሚኖርም ነው። ለማሳያ የሚሆነን ታሪክ እንመለከታለን።

እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት በከፋ አገዛዝ ሁለት መቶ ዐሥራ አምስት ዓመታት ያህል ኖረዋል። የገዢዎቻቸው ጭካኔ ልኩን ሲያልፍና እነርሱም አብዝተው ሲጮኹ ጩኸታቸውን ሰምቶ በሙሴ አማካኝነት ከግብፅ ምድር አውጥቷቸዋል። በጉዟቸውም ጊዜ መና ከሰማይ እያወረደ ሲመግባቸው፣ ውኃ ከዐለት ላይ እያፈለቀ ሲያጠጣቸው የነበረ መሆኑ የእስራኤልን ታሪክ የጻፈለን ሊቀ ነቢያት ሙሴ መዝግቦት እናገኛለን። በመጽሐፍ ቅዱስም “ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ከኤርትራ ባሕር አውጥቶ ወደ ሱር ምድረ በዳ ወሰዳቸው። በምድረ በዳም ሦስት ቀን ተጓዙ፤ ይጠጡም ዘንድ ውኃ አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ ከማራም ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም፤ ውኃው መራራ ነበርና፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም “መሪር” ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡሙ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፤ በውኃውም ላይ ጣለው፤ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዐትንና ፍርድን አደረገላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እርሱም “አንተ የአምላክህን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም መልካምን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታደምጥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብፀውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ።” (ዘፀ.፲፭፥፳፪-፳፮) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናነበው በዚህ ጥቅስም እንደተመለከትነው በወቅቱ መራራ የነበረው ውኃ በሙሴ ጸሎትና ልመና አማካኝነት በእግዚአብሔር ቸርነት ጣፍጦላቸው ጠጥተዋል። በጊዜው መጠጣታቸው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የሕይወታቸው መመሪያ የሚሆናቸውን አምላካዊ ቃል በሙሴ አማካኝነት አስተላልፏል። እርሱም “አንተ የአምላክህን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም መልካምን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታደምጥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብፀውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ።” እንዲል። እስራኤላውያን ሕጉን ጠብቀው፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው፣ እንደሥርዓቱ ቢጓዙ በግብፅ ላይ የወረደው መቅሰፍት እንደማይደርስባቸው እንደተነገራቸው ሁሉ ዛሬም በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር እየሠራን የተፈቀደልንን እያደረግን ያልተፈቀደልንን እየተውን ብንኖር አምላካዊ ጥበቃው ሳይለየን እንደምንኖር ያስረዳናል። 

በወቅቱ መራራ የነበረውን ውኃ አጣፍጦ እንዳጠጣቸው ሁሉ በሙሴ ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ለእስራኤል ከዐለት ላይ ውኃ ፈልቆላቸው ጠጥተዋል። (ዘፀ.፲፯፥፩-፯) እግዚአብሔር ያለውን ማጣፈጥ ብቻ ሳይሆን ከሌለበት ማምጣትና መስጠትም እንደሚችል እንረዳለን። የእግዚአብሔር ቸርነት ካልተከተለን በቀር ከዐለት ላይ ውኃ ማፍለቅ አይቻለንም። እርሱ ግን የማንም ረዳት ሳያስፈልገው ከዐለት ላይ ውኃ ማፍለቅ ይቻለዋል። የኤርትራን ባሕር ከፍሎ እስራኤላውያንን ማሻገር፣ ግብፃውያንን ደግሞ በባሕር ተሰጥመው እንዲቀሩ ማድረግ ችሏል። አሁንም ሁሉን ማድረግ ይችላል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ዕብን ዘመነንዋ ነደቅት ወይእቲ ኮነት ውስተ ርእሰ ማዕዘንት፤ ግንበኞች የናቋት ድንጋይ እርሷ የማዕዘን ራስ ሆነች።” (መዝ.፻፲፯፥፳፪) በማለት የተናገረውን መተርጉማኑ የተናቀች ደንጊያ የተባለችው ዕብነ ሙሴ እንደሆነች አስረድተዋል። ይቺ ዕብነ ሙሴ  ዐሥራ ሁለት ምንጭ ያላት ለዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል እያፈለቀች የምታጠጣ፣ በፊት በኋላ በቀኝ በግራ ሁና ከለላ የምትሆን፣ ጠላት ሲመጣ ረግረግ እየሆነች የምታሰጥም፣ ቀን እንደደመና እየሆነች ከቀን ሐሩር የምትከላከልላቸው፣ ሌሊት የብርሃን ዐምድ እየሆነች የምትመራቸው እንደነበረች በትርጓሜ አስረድተዋል። (መዝ.፻፲፯፥፳፪ አንድምታ ትርጓሜ)

ለእስራኤል የተደረገውን ድንቅ ተአምር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉም ያን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ። ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ።” (፩ቆሮ.፲፥፫-፬) በማለት ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ አስረድቷል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይከተላቸው የነበረ መንፈሳዊ ዐለት በማለት የገለጸውን ይህም ዐለት ክርስቶስ ነበረ በማለት ተርጕሞታል።  ሁሉን የሚችለው አምላክ ዐለቱን የውኃ መፍለቂያ ምንጭ አድርጎ የተጠማውን ያጠጣበታል፤ የተራበውን ኅብስተ መና አድርጎ ይመግብበታል፤ ለጠላት መከላከያ መሣሪያም ያደርገዋል። ይሁን እንጂ መለስ ብለን በታሪክ እንደምናስታውሰው ይህ ሁሉ የቸርነት ሥራ ለክፉዎች  አይመችም ነበር። አንዲ ሲድንበት ሌላው ሲጠፋበት ኖሯል። በስደቱ ወቅት ያደረገው ተአምርም የሚያስረዳን እንዲህ ያለውን ጉዳይ ነው።

ዛሬም ለአንዱ መራራ ለሌው ጣፋጭ የሚሆን ብዙ ነገር አለ። በእርግጥ መራራም ሆነ ጣፋጭ የሚሆነው ተቀባዩ ለዚያ ነገር ከመብቃትና ካለመብቃት፣ ወዶ ፈቅዶ ከመቀበልና ካለመቀበል፣ ለሚሰጠው ነገር አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግና ካለማድረግ ወዘተ የሚመጣ ነው እንጂ ስጦታው በተፈጥሮው መራራ ሆኖ አይደለም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ክፉ ነገር አይሰጥም። ሰዎች ግን በአጠቃቀም ስሕተት በመድኃኒቱም ይሞቱበታል። ይህን በተመለከተ የተወሰኑትን እንጥቀስ፡-

፩. የእግዚአብሔር ቃል

ከላይ እነምደተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል የሚመር ሆኖ አይደለም። ከአቀባበል መለያየት የተነሣ ግን የመረራቸው፣ አሁንም የሚመራቸው አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። የጣፈጣቸውም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ ወደፊትም ይኖራሉ። የሚጣፍጣቸውንም ሆነ የሚመራቸውን እንመልከት።

ሀ. የሚጣፍጣቸው

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ጥዑም ለጕርዔየ ነቢብከ እምዓር ወሦከር ጥዕመኒ ለአፉየ፤ ቃልህ ለጕረሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ” (መዝ.፻፲፯፥፻፫) በማለት እንደገለጸው የእግዚአብሔር ቃል የሚጣፍጥ ለሕይወትም መሠረት ነው። ለዚህም ነው “ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው” ካለ በኋላ በምድር ላይ ጣፋጭ ከሚባለው “ከማርና ከወለላ ይልቅ ጣፈጠኝ” በማለት እኛ ልንረዳውና ልንገነዘበው በምንችለው አገላለጽ ነገረን። የቃሉን ጣፋጭነትና መድኃኒትነት የተረዳው የመቶ አለቃው “በቃልህ እዘዝ፤  ልጄም ይድናል” (ማቴ.፰፥፰) በማለት ፍጹም የሆነ ሃይማኖቱን ገለጠ።

መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ጊዜም ቃሉ የሚጣፍጣቸው በርካታ ሰዎች ነበሩ። በቅዱስ ወንጌል “በየምኵራቦቻቸውም ሁሉ ያስተምራቸው ነበር፤ ትምህርቱንም ያደንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።” (ሉቃ.፬፥፲፭) ተብሎ ተጽፎ እናነባለን። እንዲሁም በቅዱስ ወንጌል “ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆምም ወረደ፤ በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር። አነጋገሩም በትእዛዝ ነበርና ትምህርቱን ያደንቁ በር።” (ሉቃ.፬፥፴፩) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ቃሉን በደስታ የተቀበሉት እንዳሉ ነው።

በመሆኑም “ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ” እንደተባለው ቃሉን ለሚሹት፣ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ፈልገው ሲለምኑት ለኖሩት ለአበው ቀደምት፣ ለነቢያት፣ ለቅዱሳን ጣፋጭ አደረጋት። እንዲሁም ከአሕዛብ ወገን ለሆኑት፣ ከሩቅ ለመጡት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ላልተባሉት ጣፋጭ አደረጋት። 

በሌላ አገላለጽ ትንቢት ለተነገረላቸው ሱባኤ ለተቈጠረላቸው ወገኖቹ ለተባሉት እስራኤላውያን መራራ አደረጋት። ማለት እንዳይቀበሉት ዐይነ ልቡናቸው ታወረ። “ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም” (ዮሐ.፩፥፲፩-፲፫) እንዲል የተቀበሉት እንዳሉ ሁሉ ያልተቀበሉትም እንደነበሩ ልንገነዘብ ይገባል። 

ለ. የሚመራቸው

በዚህ አገላለጽ አምነው ባለመቀበላቸው አለመጠቀማቸውንና መጎዳታቸውን ለማስረዳት ነው። በመሆኑም ከአብርሃም ዘር በመወለዳቸው የሚመኩትን አይሁድን “እውነት እውነት እላችኋለሁ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑስ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር)” (ዮሐ.፰፥፴፱) በማለት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የወቀሳቸው እውነተኛውን ቃሉን ሲነግራቸው ማመን ባለመቻላቸው ነበር። ቃሉን አምነው ከመቀበል ይልቅ ሊገድሉት ይሹ ነበር። በእውነት መንገድ ለማይጓዝ፣ እውነትን ገንዘብ የማያደርግ አካል ምንጊዜም ቢሆን እውነት ይመረዋል። እውነቱን ስለነገራቸው ስለኃጢአታቸውም ስለዘለፋቸው ጋኔን አድሮበታል ይሉትም ነበር። “አይሁድም አንተ ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ መናገራችን በሚገባ አይደለምን? ብለው ጠየቁት” (ዮሐ.፰፥፵፰) እንዲል።  

ቃሉ ሕይወት መድኃኒት ሲሆን በሚገባ ባለመቀበላቸውና የሕይወታቸው መመሪያም ባለማድረጋቸው የተነሣ ተፈርዶባቸዋል። በዕለተ ምጽአትም መፈራረጃ ይሆንባቸዋል። ይህን አስመልክቶ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “አመ ይመጽእ ንጉሥ በግርማ መንግሥት ኵነኔ ድልው ቅድሜሁ ነፍስ ትርእድ ወመጻሕፍት ይትከሠታ ለስምዕ፤ ንጉሡ በግርማ መንግሥት በክበበ ትስብእት በመጣ ጊዜ ፍርዱ በፊቱ ነው፤ ነፍስ ትንቀጠቀጣለች መጻሕፍትም ለምስክርነት ይረቀርባሉ” (ጾመ ድጓ ዘደብረ ዘይት) በማለት ያስረዳናል። ቃሉን ሰምተው አለመጠቀማቸው ለፍርድ ይሆንባቸዋል።

፪.ሥርዐቱ

ሕጉን ጠብቀው፣ እንደ ሥርዓቱ ተጉዘው ሰማያዊውን ርስት ለመውረስ ለሚመኙት እግዚአብሔር ያስቀመጠልን ሕግና ሥርዓት የሚመች፣ የሚጥም ነው። ነገር ግን መሠረታዊ ዓላማቸው ይህ ላልሆነው፣ ጽድቁን ቢያስቡም ያለመከራ ለሥጋዊ ምኞታቸው ቅድሚያ በመስጠት ለመጽደቅ ለሚያስቡት ሕጉና ሥርዓቱ ላይመቻቸው ይችላል። ሕግና ሥርዓት ለእውነተኛ ሰው አይጎራብጥም፤ የሚጎራብጠው እውነትን መከተል ለማይፈልግ፣ ከእውነት ጎዳና አፈንግጦ በራሱ ሐሳብና ምኞት ለሚጓዝ ግን አይመችም። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝ.፻፲፰፥፻፭) በማለት የገለጸው ለእውነተኞች የእግዚአብሔር ሕግ የሕይወት መሠረት ስለሆነ ነው። በአንጻሩ በሕግ መኖር ለማይፈልግ ግን ይመረዋል፤ ይጠፋበታልም።

፫. መንፈሳዊ ተጋድሎ 

ሰው በልዩ ልዩ ምክንያቶች አብሮት ከሚኖረውም ሆነ ከማይኖረው ጋር ይጋጫል፣ ይጋደላል። ለምድራዊ ርስት፣ ለምድራዊ ሀብት ንብረት ብሎ የሚጛደል ይኖራል። ለመንፈሳዊው ርስት ብሎ ደግሞ ከሚታየውም ከማይታየውም ጋር ይጋደላል። ምድራዊውን ርስት ፈጽሞ አያስፈልግም ባይባልም ሰማያዊውንነ ርስት አስቦ የሚታየውን ዓለም በማይታየው ዓለም ለውጦ የሚያደርጉት ተጋድሎ መንፈሳዊ ተጋድሎ ተብሎ ይጠራል። ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚጥማቸውም የማይጥማቸውም  አካላት አሉ። 

ሀ.የሚጣፍጣቸው

ቅዱሳን አባቶቻችን እውነተኛውንና መንፈሳዊውን ተጋድሎ በተግባር ፈጽመው አሳይተውናል። እየጣፈጣቸውም ተቀብለውት አልፈዋል። በሃይማኖት ጸንተው የሚቀበሉት መከራ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያስገኝ ክብርን የሚያጎናጽፍ በመሆኑ ይጣፍጣል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ “ስለዚህም ቢሆን  በብዙ ራእይ እንዳልታበይ ሰውነቴን የሚወጋ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። ስለዚህም ከእኔ ያርቀው ዘንድ ጌታዬን ሦስት ጊዜ ማለድሁት። እርሱም ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይልስ በደዌ ያልቃል አለኝ፤ የክርስቶስም ኃይል በእኔ ላይ ያድር ዘንድ በመከራዬ ልመካ ወደድሁ። ስለዚህም ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልን፣ መሰደብን፣ መጨነቅን፣ መሰደድን፣ መቸገርንም ወደድሁ፤ መከራ በተቀበልሁ ጊዜ ወዲያውኑ እበረታለሁና። (፪ቆሮ ፲፪፥፰) በማለት በእርሱ ላይ ያደረው ደዌ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደሆነና ለምንም እንደተሰጠው ሲናገር በመከራው (በደዌው) ምክንያት የሚያገኘው ጸጋ እንዳለ ያስረዳል። ስለዚህ ጸጋ የሚያስገኝ  መከራ ይጣፍጣል።

በሃይማኖት ጸንተን ምግባራችንን አቅንተን እየኖርን የሚመጣብን ቅጣት ክብር የሚያሰጥ ነው። ሐዋርያው ያዕቆብ “በመከራ የሚታገሥ ሰው ብፁዕ ነው፤ ተፈትኖ እግዚአብሔር ለሚወዱት ተስፋ ያደረገላቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና።” (ያዕ.፩፥፲፪) በማለት እንዳስተማረን መከራችን፣ ተጋድሏችን ሰማያዊ ክብርን የሚያሰጥ፣ ዘለዓለማዊ ደስታን የሚያጎናጽፍ ነው። ስለዚህ እንደዚህ ያለውን ተጋድሎ ባንጋደል ሰማያዊው ክብር ይቀርብናል። ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ  የማያልፈውን፣ የማይጠፋውን፣ ዘለዓለማዊ ክብር የሚያሰጠን ስለሆነ በዚህ መንፈሳዊ ተጋድሎ አለመጽናታችን የምናስበውንና የምንመኘውን ክብር እንዳናገኝ ያደርገናል።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ሞዕዎ ለእኩይ ኅሊና በእምነቶሙ እስመ ሠናየ ገድለ ተጋደሉ፤ መልካሙን ገድል ተጋድለዋልና በእምነታቸው ክፉውን ሐሳብ ድል አደረጉት” በማለት እንደገለጸው ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ ክፉውን ሐሳብ ድል የምናደርግበት ነውና እጅግ ይጥማል። ቅዱሳኑም ሰማያዊውን ዓለም እያሰቡ ተጋድሎውን ሳይሳቀቁት ይልቁንም እየጣፈጣቸውና እየተመቻቸው መከራውን በመቀበላቸውም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ተግባራዊ ክርስትናን አሳይተውናል።

ለ.የሚመራቸው፡-

ከላይ የተገለጸው መንፈሳዊ ተጋድሎ ለእነ ቅዱስ ጳውሎስ እንደጣማቸው ለነዴማስ አልጣማቸውም። እነ ቅዱስ ጳውሎስ “አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወከዐዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት፤ ሰማዕታት በእውነት የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን  አፈሰሱ፣ ስለመንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) እንደተባለው በመከራው ሲደሰቱ እነዴማስ ግን እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ሳይሆን የተሰሎንቄን ከተማ መረጡ። ስለዚህ በመልካም ተጋድሎ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ መቻልን፣ ወይም መንፈሳዊውን ተጋድሎ በጸጋ መቀበልንና በሕይወት መተርጎምን ከሩቅ ለመጡት ጣፋጭ ለቅርብ ሰዎች ግን መራራ አደረገው ማለት በተጋድሎ ሰማያዊውን ዓለም እንደሚወርሱ የተሰበከላቸው የእግዚአብሔር ሕዝቦች የተባሉት እስራኤል ጸንተው መቀበል ሲያቅታቸው ከአሕዛብ ወገን የነበሩት ግን አምነው መልካሙን ተጋድሎ ተጋድለው ይህ ዓይነት ሕይወትም ጣፍጧቸው እንደተጠቀሙበት ለመግለጽ ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል” (ማቴ.፳፩፥፴፩) በማለት የተናገረው ትንቢቱ የተነገረላቸው ሱባኤው የተቈጠረላቸው አምነው መቀበል ሲቸገሩ ትንቢት ያልተነገረላቸው ሱባዔ ያልተቈጠረላቸው አሕዛብ አምነው በመቀበላቸው ለክብር መብቃታቸውን ያስረዳናል።

፬. ንስሓው

ንስሓ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቅበት፣ ከቅዱሳን ኅብረት አንድ የሚሆንበት ታላቅ ስጦታ ነው። የመልካም አባት ስጦታ፣ የፍቅር ስጦታ እየተባለም በሊቃውንት ዘንድ ይነገራል። ይህን ታላቅ ስጦታ ተረድተውት ለሚጠቀሙበት የሚጣፍጥ ነው። ለማይጠቀሙበት ግን ፍርድን ያስከትላል። ኃጢአታቸውን እያሰቡ ያለቀሱት፣ ዘመናቸውን በአግባቡ የተጠቀሙትን ለምሳሌ ብንጠቅስ አዳም፣ ዳዊት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ እናገኛለን። ይሁን እንጂ የንስሓ ዕድሜ ተሰጥቷቸው ያልተጠቀሙበት ደግሞ እንደ ይሁዳና ሌሎችም የይሁዳን መንገድ የተከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሉን አምነው ባለመቀበላቸውና ንስሓም ባለመግባታቸው እንዲህ ይወቅሳቸው ነበር። “ኮራዚ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ ወዮልሽ በእናንተ የተደረገ አምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው አስቀድመው ንስሓ በገቡ ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ጢሮስና ሲዶና ዕረፍትን ያገኛሉ። ቅፍርናሆም አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺም የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን እስከ ዛሬ በኖረች ነበር። ነገር ግን እልሻለሁ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ የሰዶም ምድር ዕረፍትን ታገኛለች።” (ማቴ.፲፩፥፳፩-፳፬) 

ይህ ኀይለ ምንባብ የሚያስረደሳን መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በአካል ተገልጦ ቢያስተምራቸው አንመለስም ብለው የንስሓ ሕይወትን ገንዘብ አለማድረጋቸውን ነው። አባ ጽጌ ድንግም “ለሀገሩ ሰዎች መራራ አደረጋት” ብሎ የገለጸው እንዲህ ያለውን በቅርብ የተገኘ ጸጋ በአግባቡ አለመጠቀምን ሲያስረዳን ነው።

፭. ሥጋ ወደሙ

በሰው ልጅ ሕይወት የሚገድልም የሚያድንም ምግብ አለ። አዳም ከአንዲት ዕፀ በለስ በቀር በገነት ያለው ሁሉ ሲፈቀድለት ዕፀ በለስን ግን ተከልክሏል። የተፈቀደለት ነገር በሕይወት እንዲኖር የሚያስችለው ሲሆን የተከለከለው ግን ሞትን የሚያመጣበት ነበር። የተፈቀደለት ነገርና የተከለከለው ዕፀ በለስ እንዳለ ሆኖ ብላም አትብላም የሚል ትእዛዝ ያልተላለፈበት ዕፀ ሕይወትም ነበረ። አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን ሲበላ ሞት ተፈረደበትና ዕፀ ሕይወትን ተከለከለ። “አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ስለዚህ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ደስታ ከሚገኝባት ገነት አስወጣው” (ዘፍ.፫፥፳፪-፳፫) እንዲል።

አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በመብላቱ ዕፀ ሕይወትን ተከለከለው። በአዳም ሕይወት ዕፀ በለስ የሚገድል ዕፀ ሕይወት ደግሞ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያስገኝ ነበር። በሐዲስ ኪዳን ላለን ምእመናን በዕፀ ሕይወት ፈንታ የታደለን ሥጋ ወደሙ ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ቅድስት ማርያምን ባመሰገነበት በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ ከፈለነ ንብላዕ እም ዕፀ ሕይወት ዘውእቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር በእንተ ፍቅረ ዚአነ፤ ከሕይወት እንጨት እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም ሰውን ስለመውደዱ ያደለን ሥውና ደሙ ነው” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት እንደገለጸው ሕይወትን የሚሰጠን ዘለዓለማዊ ሕይወትን ገንዘብ አድርገን እንድንኖር የተሰጠን ሥጋውና ደሙ ነው። 

የተለያዩ ነገሮች የተለያየ ጠባይና ተፈጥሮ መኖራቸው ላያስደንቅ ይችላል። ዕፀ በለስና ዕፀ ሕይወት የሞትና የሕይወት እንጨት መሆናቸው ብዙ ላይገርመን ይችላል። ነገር ግን አንዱ ዕፀ ሕይወት ለአንዱ ሕይወትን የሚያድል ለሌላው ደግሞ ሞትን የሚያመጣ መሆኑ የረቀቀ ምሥጢር። ሥጋ ወደሙ ሕይወትን የሚያድላቸው እንዳሉ ሁሉ  ሞትን የሚያመጣባቸው ወገኖች አሉ። እነርሱ እንማን ናቸው? የሚለውን እንመለከታለን።

ሀ. የሚጣፍጣቸው፡-

ፈቅደውና ወደው ንስሓ ገብተው የሚችሉትን ዝግጅት አድርገው ለሚቀበሉት ሕይወት መድኃኒት ነው። ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “እሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ፤ ፈቃዱን ለሚፈጽሙ የሚያድን እሳት ነው” (ቅዳሴ ማርያም) በማለት እንደገለጸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ለሚመላለሱት እንድንበታለን ብለው አምነው ለሚቀበሉት ሕይወት መድኃኒት ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን አስፈላጊ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ያለዚያ ሰማያዊ መንግሥትን መውረስ እንደማይቻልም አስተምሮናል። “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛይቱ ቀን አነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛመጠጥ ነውና” (ዮሐ.፮፥፶፫-፶፭)

ለ. የሚመራቸው

ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ ብሎ ሲያስተምር በእምነት መቀበል የተቸገሩት አይሁድ “ይህ እንበላ ዘንድ ሥጋውን ሊሰጠን እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በእርሳቸው ተከራከሩ” (ዮሐ.፮፥፶፪) በእርግጥም አምነው ለማይቀበሉት፣ ሳይገባቸው ለሚቀበሉት የማይቻል ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከላቸው መልእክቱ “አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ ይህንም ጽዋ የጠጣ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ስለሆነ ዕዳ አለበት” (፩ቆሮ.፲፫፥፳፯) በማለት ሳያምኑበትና ያድነኛል ሳይሉ ንስሓም ሳይገቡ ለሚቀበሉት ዕዳ እንደሚሆናቸው፣ እንደማይመቻቸው ያስረዳል። ሊቁ አባ ሕርያቆስም መድኃኒትነቱን ብቻ ሳይሆን የሚያጠፋ መሆኑንም  “እሳት በላዒ ለአማጽያን ለእለ ይክህዱ ስሞ” ስሙን ለሚክዱት ለአመጸኞች የሚባላ እሳት ነው። በማለት ከማን አንሼ ብለው፣ እገሌ ሲቈርብ አየን ብለው የሚቀበሉት እንዳልሆነ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ላይ ሆነው ቢቀበሉት ደግሞ መፈራረጃ እንደሚሆን አስረድቷል።

በአጠቃላይ በማይመረመር ጥበቡና በልዩ ፍቅሩ የፈጠረን እግዚአብሔር አምላካችን የሚሰጠን ሁሉ መልካም ነው። ይሁን እንጂ የተሰጠንን ነገር በአግባቡ ባለመጠቀማችን ስንጎዳበት እንስተዋላለን። አንዳንዶቹ በቤቱ እየኖሩ፣ በክህነት አገልግሎት እየተመላለሱ፣ ግን ለቤቱ የሚገባና የሚመች አገልግሎት ባለመፈጸማቸው ሲጠፉበት ይስተዋላሉ። በአንጻሩ ደግሞ ከውጭ ሆነው እግዚአብሔርን በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የሚኖሩ ግን ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው መንፈሳዊ ማንነታቸው የማይገለጥ በርካታ ሰዎች አሉ። ለዚህ ነው “ከሩቅ ለመጡት የሚጣፍጥ ለሀገሩ ሰዎች ደግሞ መራራ አደረጋት” በማለት አባ ጽጌ ድንግል የገለጸልን። በቤቱ ኖረን ለቤቱም የሚገባውን ክብር በመስጠት አገልግሎታችንን ፈጽመን ሰማያዊውን ዓለም እንዲያወርሰን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን። 

ክብረ ክህነት (ክፍል አራት)

Details
Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 2182
  • ዐቢይ ጉዳይ

የካህናት ኀላፊነት 

በክህነት አገልግሎት ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ማዕረጋት አሉ። እነርሱም ጵጵስና፣ ቅስና እና ዲቁና ናቸው። የየራሳቸው ዋና ዋና የአገልግሎት ድርሻም አላቸው። ለምሳሌ፡- 

ጳጳሱ፡- አንብሮ እድ ላዕለ ጳጳስ ማለት ጳጳሳት ሲሾሙ እጁን በመጫን መሳተፍ፣ ቀሳውስትን መሾም፣ ዲያቆናትን መሾም፣ ማጥመቅና ቀድሶ ማቍረብ ናቸው።

ቄሱ ፡- ማጥመቅና ቀድሶ ማቍረብ ናቸው።

ዲያቆኑ፡- መላላክ ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ያስተማረው ትምህርት ይህን ያስረዳል። “መንገድ እንደሚሄድ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ” (ማቴ.፳፭፥፲፬-፲፭) ይህን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት መተርጕማኑ ባለአምስት ጳጳስ ባለሁለት ቄስ፣ ባለአንድ ዲያቆን ብለው ተርጕመውታል። ባለአምሰት ባለሁለትና ባለአንድ ብለው ለጳጳስ፣ ለቄስና ለዲያቆን የሰጧቸውም ካላቸው ድርሻ አንጻር ነው። 

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የአገልግሎት ድርሻዎች በእያንዳንዱ የክህነት ማዕረግ የሚከናወኑ ናቸው። ከላይ ወደታች መጥቶ ማገልገል ይቻላል። ለምሳሌ ጳጳሱ ዝቅ ብሎ የቄሱንም የዲያቆኑም አገልግሎት ማከናወን ይችላል። ቄሱም ዝቅ ብሎ የዲያቆኑን አገልግሎት ማከናወን ይችላል። ከታች ወደላይ ግን አይቻልም። ለምሳሌ ዲያቆኑ የቄሱን አገልግሎት ማከናወን አይችልም። ቄሱም እንዲሁ የጳጳሱን አገልግሎት ማለትም ከእርሱ የአገልግሎት በላይ የሆኑትን አገልግሎቶችን ማከናወን አይችልም። ለምሳሌ ካህናትን መሾም የጳጳስ እንጂ የቄስ ድርሻ አይደለም። ቄስ ክህነት መሾም አይችልም። 

ከማሰር ከመፍታት ሥልጣን አንጻርም ፍትሕ መንፈሳዊ በየማዕረጉ ያለውን ሁኔታ  “ወኢይደሉ ለአሐዱሂ እምሊቃነ ጳጳሳት፣ ወጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት ከመ ይፍታሕ ዘአሠሮ ካልኡ ዘእንበለ እምድኅረ ሞቱ፤ ከሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳት ለአንዱስ እንኳን አንዱ ያወገዘውን አንዱ መፍታት አይገባውም ከመሞቱ በኋላ ቢሆን ነው እንጂ” (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፬ ቁጥር ፵፩) በማለት ያስረዳንና “ወሊቀ ጳጳሳትሰ ብውሕ ውእቱ ከመ ይፍታሕ ማእሠሮሙ ለእሉ ኵሎሙ ሶበ ርእየ ዝክተ፤ ሊቀ ጳጳሳት ግን ነገሩን መርምሮ ካወቀ በኋላ እሊህ ሁሉ ያወገዙትን መፍታት ይገባዋል። እስመ ውእቱ ከመ እግዚአ ቤት በላዕሌሆሙ፤ እርሱ በእነርሱ ላይ የሹመት ባለቤት ነውና” ብሎ ያለውን የሥልጣን ደረጃ ያብራራልናል።

ይህን ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜው የበለጠ ግልጽ ሆኖ ተብራርቶ እናገኘዋለን። “ሊቀ ጳጳስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፤ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ቄስ ሳለም ከሞተም በኋላ አይፈታውም። ቄስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፣ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ሊቀ ጳጳስ ሳለም ከሞተም በኋላ ይፈታዋል። ሊቀ ጳጳስ ያወገዘውን ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፣ ቄስ ያወገዘውን ቄስ በሕይወት እያለ መፍታት አይችልም ከሞተ በኋላ ግን ይፈተዋል።” እንዲል። ይህ የክህነት ማዕረግ የቤተ ክርስቲያንን ጽኑዕ የሆነ መዋቅራዊ አደረጃጀትና “እናት አባትህን አክብር” ብላ የምታስተምር ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ደረጃውን የጠበቀ አደረጃጀት እንዳላት ያስረዳናል። 

ይህ በእያንዳንዱ የክህነት ማዕረግ የሚከናወን የአገልግሎት ድርሻ ነው። በአጠቃላይ ግን ካህናት በክህነት አገልግሎት ሲኖሩ ምን ምን ኀላፊነቶች አሉባቸው ቢባል የሚዘረዘሩት በርከት ያሉ ቢሆኑም በዚህ ጽሑፍ የሚከተሉትን ብቻ እንመለከታለን።

ጠባቂ  ናቸው፡- ካህኑ መንጋዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገቡ ዘንድ ቁልፉ በእጁ ያለ በረኛ ነው። ምእመናን ዘለዓለማዊውን ርስት ይወርሱ ዘንድ ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል። “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል” (ማቴ.፲፮፥፲፱) ተብሎ ይህን ያህል ኃላፊነት የተሰጠው ካህን ምእመናን መንግሥተ ሰማያት ቢዘጋባቸው የእርሱ ድርሻ እንዳለበት ማመን ይኖርበታል። ምክንያቱም መክፈቻው በእጁ አለና። ስለዚህ ካህን ይህን ያህል ኃላፊነት ያለበት ነው። 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው ትምህርት እና አንቀጸ አባግዕ ተብሎ በሚጠራው የወንጌል ክፍል “እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደበጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ ወንበዴም ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎቹ ጠባቂ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል።) (ዮሐ.፲፥፩-፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን።

በዚህ ምንባብ ጠባቂው በጎችን ከመጠበቅ ባለፈ በጎችን የሚጠብቀው እረኛ በበሩ የሚገባ፣ በጎቹን በየስማቸው የሚጠራቸው፣ በጎቹ የሚከተሉት፣ በጎቹን የሚያሰማራ እየተባለ ተገልጾ እናገኘዋለን። በበሩ የሚገባ ሲል በር የተባለው ሃይማኖት፣ ወንጌል፣ ንስሓ ነው፤ በሃይማኖት የሚኖር፣ በአማናዊት ሕግ በሕገ ወንጌል አምኖ የሚኖር እንደሰውነቱ የንስሓን አስፈላጊነት የተረዳና በንስሓ የሚመላለስ ማለት ነው። በጎቹን በየስማቸው የሚጠራቸው የተባለው ደግሞ የሚጠብቃቸውን ምእመናን በትክክል የሚያውቃቸውና አስፈላጊውን ጥበቃ የሚያደርግላቸው ማለት ነው። በጎቹ የሚከተሉት ሲልም ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት የሚያስተምራቸው፣ በሃይማኖት እርሱን መስለው እንዲኖሩ የሚያደርግ በጎቹ በትክክል በአባትነቱ አምነውበት የሚከተሉት ሲል ነው። 

ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በሃይማኖተ አበው “የካህኑን ምክሩን፣ ትእዛዙን፣ ተግሣጹን አንሰቀቅ፤ ነፍስን የሚያድን ባለመድኃኒት ነውና፤ የነፍስን ደዌ የሚያርቅ ይቅርና የሥጋ በሽታ የሚያድን ባለመድኃኒትስ ወደ ሥጋዊ በሽተኛ በመጣ ጊዜ ለመድኃኒቱ ከማይስማሙ ምግቦችን ከመመገብ ይከለከል ዘንድ ያዝዘዋል፤ መራራ መራራ ቅጠልን ምረቱ ጭንቅ ሽታው ክፉ የሚሆን ከብዙ ወገን የተቀመመ መድኃኒትን ያጠጣዋል። በድውዩ አካል የተለያየ ሕዋሳትን አንድ ያደርግለት ዘንድ። (ሃ.አበ.፴፯፥፫) በማለት እንደገለጸው ቃሉን በትክክል ሰምተው የሚከተሉት መሆን አለበት። በጎቹን የሚያሰማራ ሲልም  የበጎች መሠማሪያ የተባለች ቤተ ክርስቲያን፣ መንግሥተ ሰማያት ናትና ወደቤተ ክርስቲያን የሚያቀርባቸው በቤተ ክርስቲያን እንዲኖሩ የሚያደርግ ማለት ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸው ጽኑ አደራ በመጽሐፍ ቅዱስ “አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (ሐዋ.፳፥፳፰) ተብሎ ተጽፎ እናገኘዋለን። ስለዚህ ካህናት የምእመናን ጠባቂዎች ናቸው።

ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው ‹‹ኦ ካህናት አንትሙ ውእቱ አዕይንተ እግዚአብሔር ብሩሃት፤ እናንተ ካህናት ሆይ የእግዚአብሔር ዐይኖች ናችሁና ኃጢአተኛውን እንደ ወንድማችሁ ገሥጹት።” በማለት በቅዳሴው ገልጾት እናገኛለን። ይህም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም ፤ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ በማለት የሰጣቸውን ክህነት እንዳይዘነጉ በማስታወስ ያላቸውን ልዕልና ያስረዳል።

ከላይ በገለጽነው ሐሳብ ልዕልናቸውን ብቻ ሳይሆን ኀላፊነታቸውንም ያስረዳል። ምክንያቱም ካሀናት ባያስተምህሩ በሚጠፉት ነፍሳት ሁሉ የመጀመሪያ ተጠያቂዎች እነሱ ናቸውና። የእግዚአብሔር ዐይኖች ከፈጠሯቸው ፍጥረታት ለቅጽበት ያህል እንኳ በጥበቃቸው አይለዩም። ካህናትም ከንስሓ ልጆቻቸው መለየት እንደሌለባቸው ሲያስረዳ አዕይንተ እግዚአብሔር ይላቸዋል።  

ሊቁ ካህናትን ብቻም ሳይሆን ዲያቆናትንም እንዲህ ይላቸዋል። “ኦ ዲያቆናት ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ወላዕካኒሃ ምልሑ ውስቴታ ኢየሀሉ ተኵላ ምስለ በግዕ አንቄ ምስለ ርግብ፤ የቤተ ክርስቲያን ፋና የምትሆኑ ዲያቆናት አገልጋዮቿም የሆናችሁ ተኵላ ከበግ ጭልፊትም ከርግብ ጋር እንዳይኖር ለዩ።›› ተኵላ የተባሉ መናፍቃን ናቸው። እነዚህ ከምእመናን ጋር ጭልፊት የተባሉት ደግሞ ኃጥኣን ናቸው። እነዚህም ከጻድቃን ጋር ተቀላቅለው እንዳይኖሩ ለዩ እያለ ዲያቆናትም እንደ አቅማቸው ያስተምራሉና የየድርሻቸውን በትጋት መወጣት እንዳለባቸው ሲያስረዳ እናገኛለን።

በቅዱስ ወንጌል “ምሳም ከበሉ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው እርሱም አዎን ጌታዬ ሆይ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው ፤ ጌታችን ኢየሱስም በጎቼን ጠብቅ አለው። ዳግመኛም የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን አለው፤ እርሱም አዎን ጌታዬ ሆይ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ አለው። ሦስተኛ ጊዜ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን? አለው፤ ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን ስላለው ተከዘ ጌታየ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው፤ እንኪያስ ግልገሎቼን ጠብቅ አለው።” (ዮሐ.፳፩፥፲፭-፲፯) የሚል ኀይለ ምንባብ እናገኛለን።

በዚህ ምንባብ ለቅዱስ ጴጥሮስ ከተሰጠው የጠባቂነት ድርሻ በተጨማሪ ልብ የምንለው ጉዳይ አለ። እርሱም አደራውን ለመስጠት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ነው። በጎቹን በአደራ ለመቀበል የበጎቹን ባለቤት መውደድ መቻል አለበት። እርሱን ደግሞ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስላላወቀ አይደለም የጠየቀው። እንደሚያውቅማ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስም  “እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” በማለት ወዳጅነቱን ገልጾአል። ይሁን እንጂ የእርሱን አሰረ ፍኖት ተከትለው በእርሱ መንበር ተቀምጠው ለመንጋው እረኛ የሚሆኑ ካህናት አደራው እጅግ ጥብቅ እንደሆነ እንዲረዱት፣ አስቀድመውም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች መሆን እንዳለባቸው እንዲያውቁት ነው። ምክንያቱም በጎች የደም ዋጋ የተከፈለላቸው ናቸው። በወርቅ በብር ሳይሆን በደም የተገዙ ናቸውና ኀላፊነቱን በትጋት የሚወጣና የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች መሆን ይኖርባቸዋል።

መንጋውን ይጠብቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር በአደራ የተቀበለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቋቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን” (፩ጴጥ.፭፥፪) በማለት እርሱም እረኞች እንዲጠብቁ ብቻ ሳይሆን በምን መንገድ መጠበቅ እንዳለባቸውም ይናገራል።

መሪ ናቸው፡- ጌታቸን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው የእረኝነት ትምህርት “ሁሉንም አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል በጎቹም ይከተሉታል ቃሉን ያውቃሉና” (ዮሐ.፲፥፬) የሚል ኀይለ ምንባብ እናገኛለን። በዕብራውያን ባህል እረኛ በፊት በፊት እየሄደ በጎቹ ይከተሉታል። እረኛው ካልተንቀሳቀሰ እነርሱም አይንቀሳቀሱም። ካህኑ የምእመናን እረኛ ነውና ከምእመናን ቀድሞ መገኘት አለበት። 

እረኛው መሪ ነው ሲባል እንዲሁ በፊት ሆኖ ተከተሉኝ የሚል ብቻ አይደም። ሲከተሉት ተከታዮቹን ወስዶ በመልካም መሰማሪያ ላይ የሚያደርስ ማለት ነው። መልካም መሰማሪያ የተባለች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም መንግሥተ ሰማያት ናት። ስለዚህ መልካም ሥራ ሠርቶ እርሱም የሚጸድቅ መንጋውንም ወደ መልካም ነገር እየመራ የሚያጸድቅ መሆን አለበት።

ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠውና በቅዱስ ወንጌል የተጻፈው የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ኀላፊነት “ጠቦቶቼን አሰማራ” የሚል ትእዛዝ ነበረበት። አሰማራ የሚለው ትእዛዝ ከመጠበቅ ባለፈ አቅጣጫ ማሳየትን፣ መምራትን፣ መዋያቸውን፣ ማደሪያቸውን፣ ምግባቸውን፣ አጠቃላይ ለሕይወታቸው አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሙሉ ከማሰብና ከማዘጋጀት ጋር የተያያዘ ነው።  

ካህኑ መሪ ነው ሲባል ክርስቲያናዊ ሕይወትን በተግባር እየኖረ የሚያሳይ መሆን አለበት። እንዲህ ከሆነ ሕዝቡም የእርሱን ፈለግ የሚከተል ይሆናል። ይህን አስመልክቶ በፍትሕ መንፈሳዊ “በከመ ይቤ ሆሴዕ ነቢይ እስመ ከመ ይከውን ካህን ከማሁ ካዕበ ሕዝብኒ፤ ነቢዩ ሆሴዕ መምህሩ ደግ ቢሆን ሕዝቡም እንደርሱ ደጋግ ይሆናሉ ብሎ እንደተናገረ ደግ መሆን አለበት” የሚል ኀይለ ቃል እናገኛለን። ይህንም ሲያጠነክር “ ወዓዲ መምህርነ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነ ወጠነ ቅድመ ከመ ይግበር ወይምሀር፤ ዳግመኛም ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ሠርቶ ያስተምር ዘንድ ጀመረ። ወይቤ እስመ ዘይገብር ወይሜህር ዐቢየ ይሰመይ በመንግሥተ ሰማያት፤ ሠርቶ የሚያስተምህር መምህር በመንግሥተ ሰማያት ደገኛ እንዲሆን ተናገረ” ተብሎ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተግባራዊ አስተምህሮ በማስረጃነት ተጠቅሶ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ካህኑ በተግባር እያሳየ መንጋውም እርሱን እንዲከተል ማድረግ እንደአለበት ነው። 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልም በተግባርም አስተምሯል። የቅደም ተከተል ጉዳይ ካልሆነ በቀር በተግባር ያልፈጸመውን እኛ እንድንፈጽመው አላዘዘንም። ለዚህም ነው ከላይ በጠቀስነው በፍትሕ መንፈሳዊ “ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ሠርቶ ያስተምር ዘንድ ጀመረ።” የተባለው። ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የሾማቸው ካህናትም እንዲሁ ምእመናንን ሲመሩ እነርሱ በተግባር እያከናወኑ መሆን አለበት። 

መጋቢ ናቸው፡- በክህነት አገልግሎት መኖር የክርስቶስ እንደራሴ ሁኖ የክርስቶስን ጸጋ ለምእመናን ማድረስ ነው። በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፬ ቍጥር ፵፯ “ሊቀ ጵጵስና ህየንተ ክርስቶስ ውስተ ዓለም፤ በዚህ ዓለም ሊቀ ጵጵስና መሾም እንደ ክርስቶስ መሆን ወይም የክርስቶስ ምስለኔ መሆን ነው። በእንተ ዐቂበ ሃይማኖት፤ ሃይማኖትን ለማጽናት፣ ወመግቦተ መሃይምናን፤ ምእመናንንም ለመመገብ” ተብሎ ተገልጾ እናገኘዋለን። ስለዚህ ሃይማኖትን አጽንቶ ምእመናንን ከነጣቂ ተኵላ ጠብቆ፣ የሚያሻቸውን ምግብ እየመገበ ይኖራል። 

ካህኑ የሚጠብቃቸውን መንጋዎቹን መመገብ የግድ ይለዋል። ጠባቂነቱ፣ አባትነቱ መንፈሳዊ ነውና መንፈሳዊውን ምግብ የእግዚአብሔርን ቃል ዕለት ዕለት እየመገበ ማኖር አለበት። በቅዱስ ወንጌል “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ፣ ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን? ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው” (ሉቃ.፲፪፥፵፪-፵፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ካህኑ እግዚአብሔር በምእመናኑ ላይ የሾመው መጋቢ ነው። በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው ተግቶ የሚመግብ ደግሞ እጅግ የላቀ ዋጋ ያገኛል።

የሰው ልጅ በባሕርዩ ምግበ ሥጋም ምግበ ነፍስም የሚያሻው ሆኖ ተፈጥሯል። የተለየ ጸጋ ኖሮት ያለ ምግበ ሥጋ መኖር ቢችል ያለምግበ ነፍስ መኖር አይችልም። ካህኑ እንዲጠብቃቸው በአደራ የተሰጠውን መንጋዎቹን ምግበ ሥጋቸውንም  ምግበ ነፍሳቸውንም ማዘጋጀትና መመገብ ግዴታው ነው። ምን አልባት ምግበ ሥቻውን በተመለከተ እርሱ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ማገዝ ባይችል እንኳን ልጆቹን እያስተባበረ በማኅበራዊ ኑሯቸው እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ እያደረገ ችግራቸውን እንዲፈቱ ማድረግ አለበት። 

ምክንያቱም በሥጋዊ ችግራቸውም አቅሙ በፈቀደ መጠን መሳተፍ አለበት። ይህን በተመለከተ በመጽሐፈ ዲድስቅልያ “ሰውን ወዳጅ፣ እንግዳን የሚቀበል፣ ፊት አይቶ የማያዳላ፣ ለባለጸጋና ደሃ የማያዳላ፣ ፈራጅ፣ ጥበብ ያለው፣ ለመስጠት እጁን የሚዘረጋ፣ ረዳት የሌለውን የሚቀበል፣ ድሆችን፣ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን የሚወድ ይሁን፤ ዳግመኛም ልጆች ያሏቸውን ይመግብ” (ዲድስቅልያ አንቀጽ ፬ ቍጥር ፲፬) የሚል የሐዋርያትን ትእዛዝ እናገኛለን። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም በመልክቱ “ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቀቡት” (ያዕ.፭፥፲፬) በማለት የገለጸው በደዌ ነፍሳቸው ብቻ ሳይሆን በደዌ ሥጋቸውም መጨነቅ እንዳለባቸው፣ በነፍስ ረኀባቸው ብቻ ሳይሆን በሥጋዊ ረኀባቸውም እንዲጨነቅ ሲያስረዳን ነው። መሪ ነው ሲባልም እንዲህ ያለውን ሁሉ እያስተባበረ የመፍትሔ አካል መሆን እንዲችል ነው።

ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ ካህኑ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግን የመንፈስ ልጆቹ ናቸውና ለመንፈሳዊ ምግባቸው ነው። ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ምግባቸው ምንድን ነው? ከተባለ ተፈጥሯቸው በአንድ በኩል ከባሕርየ እንስሳ ነውና  ምግበ ሥጋ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ በሌላ በኩል ደግሞ በባሕርየ መላእክት ነውና እንደ መላእክት ምግባቸውም ቃለ እግዚአብሔር ነው። የመላእክትን ምግብ በተመለከተ ሊቁ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ “ወሲሳዮሙ ለመላእክት ቅዳሴ ወስብሐት ወስቴሆሙ ፍቅረ መለኮት፤ የመላእክት ምግባቸው የእግዚአብሔር ቃል መጠጣቸውም የመለኮት ፍቅር ነው” (አክሲማሮስ ዘዕለተ እሑድ ክፍል ፬ ቍጥር ፲፮) በማለት ያስረዳናል። እንደ መላእክት የእግዚአብሔርን ቃል የሚመገቡ መሆናቸውን ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወኅብስተ መላእክት በልዑ እጓለ እመሕያው፤ የመላእክትንም እንጀራ የሰው ልጆች በሉ” (መዝ.፸፯፥፳፭) በማለት ያስረዳናል።

ስለዚህ ካህኑ የመንጋዎቹ መጋቢ ነው። ሲባል ሊመግባቸው የሚገባው የእግዚአብሔርን ቃል ነው። በእግዚአብሔር ቃል ኮትኩቶ ማሳደግ ቃለ እግዚአብሔር የዕለት ተዕለት ምግባቸው እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል። በቅዱስ ወንጌልም “ ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተጽፏል” (ማቴ.፬፥፬) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ካህኑ ለምእመናን የእግዚአብሔርን ቃል እየመገበ ከቤቱ እንዲኖሩ ማድረግ፣ በንስሓ ሕይወት እንዲመላለሱም ማስቻል፣ መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰውን፣ የተዘጋችውን የገነትን በር የከፈተውን ሥጋ ወደሙ ማቀበል ዋነኛ ድርሻውና ኃላፊነቱ መሆኑን  ነው።

የጠፉትን የሚፈልጉ ናቸው፡- በቅዱስ ወንጌል የዐመፅ ጥያቄን ያዥጎደጉዱት ለነበሩት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ኃጢኣተኞችን ይቀበላል ከኃጢኣተኞችም ጋር ይበላል ብለው ላቀረቡለት ጥያቄ የሚሆን መልስ “ከእናንተ መካከል መቶ በጎች ያሉት ሰው ቢኖር ከእነርሱ አንዲቱ ብትጠፋው ዘጠና ዘጠኙን በምድረ በዳ ትቶ እስኪያገኛት ድረስ ይፈልጋት ዘንድ ወደጠፋችው በግ ይሄድ የለምን? በአገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በትከሻው ይሸከማታል” (ሉቃ.፲፭፥፬) ተብሎ እንደተጻፈ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን አዳምን ይፈልግ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ። የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን አዳምን እንደፈለገ ሁሉ እርሱ የሾማቸው ካህናትም ዋነኛ ተግባራቸው የጠፋውን የአዳምን ልጅ መፈለግ ነው።

መጥፋት በአካል ብቻ ላይሆን ይችላል። በመንፈስም መጥፋት አለ። ካህናት መንፈሳዊ ጠባቂዎች ናቸውና በመንፈስ የጠፋውን ፈልጎ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። ጌታችን ጠፍተው ስለተገኙ ሦስት ነገሮች እና ጠፍተው በመገኘታቸው በባለቤቶቹ ዘንድ ምን ያህል ደስታ እንደሚደረግ ሲያስተምር ጠፍተው ከተገኙት ከሦስቱ ነገሮች መካከል አንዱ በቤት ውስጥ የጠፋ ነበር። ጠፍታ የተገኘችው በግ በጠባቂው ግዴለሽነት የጠፋች ናት፤ የጠፋው ልጅ ደግሞ በጥጋቡ ከቤት ኮብልሎ የወጣና ከአባቱ ቤት መለየቱ አላዋጣህ ሲለው በራሱ ጊዜ ተመልሶ የመጣ ነው። ጠፍቶ የተገኘው ድሪም ግን በቤት ውስጥ ከቆሻሻ ጋር ተቀላቅሎ የነበርና ባለድሪሟ በመብራት ፈልጋ ያገኘችው ነው። (ሉቃ.፲፭፥፩-፳፬)

ካህናት እረኞች ናቸውና ቢቻል አስቀድመው መንጋቸው እንዳይጠፋ ተግቶ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ካልተቻለ የጠፋበትን ምክንያት፣ የት እንደጠፋ ማለት እንደበጊቱ በእረኛው ግዴለሽነት ነው? ወይስ እንደጠፋው ልጅ በራሱ ጥጋብ ነው? ወይስ ደግሞ በቤት ውስጥ ከጥራጊ ወይም ቆሻሻ ጋር የተደበቀ ነው? በማለት መለየትና ፈልጎ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

እንደ ዲናሩ ከቤቱ እያለ ግን በዓለም ቆሻሻ ተውጦ ይሆን፣ በቤተ ክርስቲያን እየተመላለሰ፣ በሚገባ የማይጸልይ ከሆነ፣ የማይጾም ከሆነ፣ ንስሓ የማይገባ ከሆነ፣ ሥጋ ወደሙ የማይቀበል ከሆነ በቤቱ አለ ግን በኃጢያት ቆሻሻ ተውጦ መገኘት አልቻለም ማለት ነው። ስለዚህ እንደባለዲናሯ መብራት ማብራትና መፈለግ የካህኑ ድርሻ ይሆናል።

ካህናት እነዚህንና የመሳሰሉትን ኃላፊነቶች ለመቀበል በቅድሚያ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መረዳት፣ ለዚህ ኃላፊነት የሚያበቃ ዝግጅት ማድረግ፣ ማለትም በትምህርትም፣ በምግባርም፣ በቁርጠኝነትም ወዘተ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲሁ የክርስቶስ ወዳጅ መሆን አለባቸው። ምክንያቱም በኃላፊነት የሚቀበሏቸው መንጋዎች በምድራዊ ወርቅና ብር የተገዙ ሳይሆኑ በደም የተገዙ ናቸው። ይህን በተመለከተ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ። ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ” (፩ጴጥ. ፩፥፲፰-፲፱) በማለት ያስረዳናል። ስለዚህ እንደዚህ የከበረ ዋጋ የተከፈለላቸውን ምእመናን ለመጠበቅ የሚያበቃ ትጋት ያስፈልጋል። 

በአጠቃላይ በክህነት አገልግሎት የሚኖሩ ካህናት ኃላፊነታቸው እጅግ ከባድና በአግባቡ ከተወጡት ግን ሰማያዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ መሆኑን መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም መንጋውን በአግባቡ ሊጠብቁት፣ ወደሚፈለገው ቦታ ሊመሩት፣ የሚያስፈልገውን ምግብ ሊመግቡትና ቢጠፋ እንኳን ፈልገው ከጠፋበት ሊመልሱት እንደሚገባቸው ራሳቸው ካህናቱም መረዳት አለባቸው ምእመናንም እንዲሁ ይህን ጥብቅ አደራ ተረድተው በተቻለ መጠን የካህናት ትእዛዝ ሊቀበሏቸው ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ ኀላፊነቱን በሚገባ የሚወጣ ጠንካራ አባት እንዲያድለን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን።

 

የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም (ክፍል አንድ)

Details
Written by: በወግደረስ አዳል
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 2691
  • እናስተዋውቃችሁ
የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም  (ክፍል አንድ)

መግቢያ

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ውስጥ ፴፩ ገዳማት የሚገኙ ሲሆን ተከዜ ኪዳነ ምሕረት ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ገዳም አንዱ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ለወዳጆቹ በሰጣቸው ቃል ኪዳን መሠረት ምእመናን በቅዱሳኑ ስም ከተመሠረቱ ገዳማት በረከትን ያገኛሉና እኛም ሁሉም ምእመናን ወደ ገዳሙ በመሄድ በረከትን ይሳተፉ ዘንድ በዚህ የእናስተዋውቃችሁ ዐምድ የዚህን ገዳም ታሪክ ከነሥርዐቱ አቅርበናል። መልካም ንባብ። 

የገዳሙ መገኛ

ገዳሙ የሚገኘው በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በላስታ ወረዳ  በዜሮ ሰባት ቀበሌ እና በመቄት ወረዳ ነው።  የአባቶች ገዳም ተከዜን ተሻግሮ ከወንዝ ማዶ የሚገኝ ሲሆን የእናቶች ገዳም ላስታ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ነው። 

ገዳሙ የተከዜን ወንዝ በሥሩ እየጠጣ የቅዱሳን መነሀሪያ የሆነ በቆላማው የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የተከዜን ወንዝ መሠረት አድርጎ የተሠራ ነው። በስተ ሰሜን የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በደቡብ የአቡነ አሮን ገዳም በቅርብ ርቀት የሚያዋስኑት ገዳም ነው።

ወደ ገዳሙ ለመድረስ በወልዲያ ወይ በባሕር ዳር በጋሸና አድርጎ ወደ ላሊበላ በሚወስደው መንገድ ላይ በተለምዶ ግራኝ አምባ (አዲስ አምባ) በመባል የምትታወቀው ከተማ ሲደርሱ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ታጥፎ እስከ ገዳሙ ክልል ድረስ በተጠረገው መንገድ በእግር ወይም በመኪና መጓዝ ይቻላል። በገዳሙ ውስጥ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን እነሱም የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በእናቶች ገዳም፣ የመድኃኔ ዓለም በአባቶች ገዳምና የቀጭን አበባ ሥላሴ ናቸው።

አመሠራረትና እስካሁን ያለው ታሪክ

የገዳሙ መሥራች በጽኑዕ ተጋድሏቸው የሚታወቁት አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ሲሆኑ የተመሠረተውም በቅዱስ ገብረ ማርያም (ሐርቤ) ዘመነ መንግሥት በ፲፪ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው። የአባታችን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ትውልዳቸው ሸዋ ቡልጋ ሲሆን አባታቸው ንዋየ ጽዮን እናታቸው ፍቅርተ ክርስቶስ የሚባሉ ደጋግ  በተለይም ለምጽዋት እና እንግዳ ለመቀበል የተጉ ክርስቲያኖች ነበሩ። በዘመናቸውም እመቤታችን በእንግድነት ተገልጻላቸው ይህን ቅዱስ አባት እንደሚወልዱ አብሥራቸዋለች። 

የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው ዲቁና እንደ ተቀበሉ ወደ ታላቁ የአየለነ (እየላ) ሚካኤል መጥተው በዲቁና እያገለገሉ በጽኑ ተጋድሎ እየተጋደሉ ቆይተው ምንኵስናን ለመቀበል ወደ ደብረ በንኰል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ሄዱ። በዛም በብዙ ተጋድሎ ከቆዩ በኋላ በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ ምንኵስናን ተቀብለው በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከእመቤታችን እጅ የተቀበሏትን የቃል ኪዳን መታሰቢያዋ የሆነችውን ታቦተ ኪዳነ ምሕረት ይዘው መሃል ተከዜ ወደሚገኘው ወደዚህ ገዳም መጥተዋል። ወደ ገዳሙ ሲደርሱም በአናምርትና በአናብስት ተከቦ በረድኤተ እግዚአብሔር ሲጠበቅ አግኝተውታል። ለታቦተ ኪዳነ ምሕረት ማደሪያ የሚሆን ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ ሌሊት ተከዜ ወንዝ ውስጥ ሲጸልዩ እያደሩ ቀን ቀን አሜከላ አንጥፈው ሲሰግዱ በመዋል አብዝተው እየተጋደሉ መኖራቸውን ቀጠሉ። ገዳሙም የብዙ መናንያን መሰባሰቢያና ትልቅ ገዳም ሆነ። 

የተከዜ ኪዳነ ምሕረት ገዳም በቅዱስ ገብረ ማርያም (ሐርቤ) ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ ሲሆን ገዳሙን ከምሥረታ ጀምሮ ወደ ተሻለ ደረጃ እስከ ማሳደግ ድረስ የደረሱት ታላቁ አባት ሐዋርያ ክርስቶስ ናቸው። እኒህ አባት በእግዚአብሔር ጥሪ የኦሪት መሥዋዕት ይሠዋበት በነበረው ከእየላ ሚካኤል ተነሥተው ወደዚህ ገዳም የተከዜን ወንዝ ተከትለው በመምጣት ዙሪያዋን አንበሶች እና ነብሮች አጥሯን ፤ ቅጥሯን እየጠበቁ አገኟት። ወደ ገዳሙ ሲገቡ ሰማይ ተከፍቶ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ ታያቸው። ጌታችን “ወዳጄ ሐዋርያ ክርስቶስ እንኳን ደኅና መጣህ፤ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ትኖራለህ” አላቸው። ከዚህ ጋር አያይዞም “ይህ ቦታ ምዕራፈ ቅዱሳን ተብሎ ይጠራል” አላቸው። እርሳቸውም ከእመቤታችን በተቀበሉት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ኪዳኗ መታሰቢያ በሆነው በቅድስት ኪዳነ ምሕረት ታቦት ስም የመሠረቱትን ገዳም ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና መድኃኔ ዓለም አንድነጽ ገዳም ብለው ከጌታችን በተነገራቸው ቃል ኪዳን መሠረት መጥራት ጀመሩ። ሐዋርያ ክርስቶስም  በዚህ ገዳም እየጸለዩ እና እየሰገዱ ለዓለም ምሕረትን እየለመኑ ለሕሙማን ፈውስን እያሰጡ የምንኵስና ሕይወት በገዳሙ እንዲሰፋ እና እንዲጠናከር አድርገዋል። 

በመጨረሻም እግዚአብሔር አምላክ እስከ ዳግም ምጽአት ‘‘ሞት የለብህም’’ ብሎ  ስለ ፍቅራቸውና ስለ ጽኑ ተጋድሏቸው ዐሥራ ሁለት ክንፍ ተሰጥቷቸዋል። ሐዋርያ ክርስቶስም ቃል ኪዳን ተቀብለው በ፲፩፻፲፭ ዓ.ም. ግንቦት ፲፮ ቀን ተሠውረዋል። 

አፄ ምኒልክ ለገዳሙ መገልገያ የሚሆኑ የተለያዩ ንዋየ ቅዱሳትን አበርክተዋል። ልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱ ከባላምባራስ ጉግሳ ወሌ ጋር በየገዳማቱ እየሄዱ ይረዱና ለሕይወታቸው ይማፀኑ ነበር። ብዙ ተኣምራትንም አድርጋላቸዋለች። ገዳሙ ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ  በሳቸው እግር በተተኩ አባቶች ፈተናዎችን እያለፈ በጽኑ ገዳማዊ ሕይወትና ሥርዓት ቢቆይም በ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. በነበረው ድርቅ ምክንያት ተፈቷል። ከሦስት በማይበልጡ መነኰሳት እየተጠበቀ ያለ ምንም የውስጥ አገልግሎት እስከ ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ቆይቷል። በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. በአባ ኪዳነ ማርያም አማካኝነት በርካታ መናንያን ተሰባስበው ድጋሚ ተጠናክሮ በአሁኑ ሰዓት ፮፻፲፮ መናንያንና ከ፴ የሚበልጡ የአብነት ተማሪዎች የሚገኙበት ገዳም ሆኗል። (ምንጭ በገዳሙ ከሚገኙ አባቶች)

፩. ሥርዓተ ገዳም

፩.፩.አንድነት

ገዳሙ የአንድነት ገዳም በመሆኑ ጥብቅ የአንድነት ሥርዓት ያለው ነው። በዚህ ገዳም ቁሪት፣ ዘረኝነት፣ ነገረ ሠሪነት ክልክል ከመሆኑም አልፎ ውጉዝ ነው። ማንም በገዳሙ በምናኔ የሚኖርም ሆነ በእንግድነት የመጣ ሰው የገዳሙን የአንድነት  ሥርዓት የማክበር ግዴታ አለበት ። ምግብንም የገዳሙ መጋቢ ከቆነነው ውጭ መጠቀም ፈጽሞ ክልክል ነው። እንግዳ ወደ ገዳሙ  ለሥራ፣ ለጠበል፣ ለጸሎትና ለሱባኤ ሲመጣ ከመናንያን  በዓት ማረፍ ከተመደበለት ሊቀ አበው ውጭ ያለ ሥራና ያለ መጋቢው ፈቃድ ከሌሎች ጋር መገናኘት ክልክል ነው። ይህ እና ይህን የመሳሰሉት ሥርዓቶች በመናንያኑ ዘንድ (ከሥር በፎቶው እንደሚታየው) የአንድነት ገዳማዊ መንፈሳዊ ሕይወት ቃል ኪዳን ውስጥ ተካትተው የሚታወቁ ናቸው።

፩.፪.ሥርዓተ ምንኵስና

በገዳሙ ለምናኔ የሚመጣ ሰው ስለ መጣበት ምክንያት ተጠይቆ ያስረዳል። ቤተሰቡን ትዳሩን ልጆቹን በትኖ አለመምጣቱን፣ ወንጀል ሠርቶ ለመደበቅ አለመምጣቱን፣ ገዳሙን በማንኛውም መንገድ ሊጎዳ አለመምጣቱን፣ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ  እና መሰል ሁኔታዎችን ተጠይቆ ለ፺ ቀናት (ለሦስት ወራት) ደጅ እንዲጠና ይደረጋል። ከዚያም በሰላም ለኪ ወደ ገዳመ ማኅበሩ ገብቶ ለሦስት ዓመት የአመክሮ ጊዜ ይሰጠዋል።  ከሌላ ገዳም ፈልሶ የመጣ እንደ ሆነ በምን ምክንያት ከነበረበት ገዳም እንደ ወጣ፣ በምግባር ችግርም ተባሮ እንደ ሆነ ይጠየቃል። ‹ነበርኩበት› ወዳለው ገዳም ተደውሎ ስለ እርሱ ይጠየቃል። ፈተና ጸንቶበት የመጣ እንደ ሆነ ይቀበሉታል። በምግባር ብልሹነትና ሁከት በማስነሣት የተባረረም ከሆነ ተለይቶ እንዲመከርና በጥንቃቄ ገዳመ ማኅበሩን በማይበጠብጥበት ሁኔታ እንዲታረም ይደረጋል። ምክንያቱም ሁከት ይፈጥራል በሚል ሥጋት ብቻ እንደ መጣ ቢባረር ወደ ዓለም ተመልሶ ይወድቃልና የመታረሚያና የጽሞና ጊዜ ይሰጠዋል። የማይመለስ ከሆነና ለገዳማዊ ሕይወት እንቅፋት የሚሆን ሆኖ የተገኘ እንደ ሆነ 

ገዳሙን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል። ምንፍቅናንና ሁከትን ሊዘራ የመጣ ከሆነ ግን ሳይውል ሳያድር ገዳሙን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል።

በገዳሙ ውስጥ የአመክሮ ጊዜያቸውን በጥሩ ገዳማዊ ሕይወት ላሳለፉ አባቶችና እናቶች አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ የልደታቸው መታሰቢያ በሚከበርበት ሐምሌ ፲፮ እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከስደት ተመልሳ ደብረ ቍስቋም በገባችበት በኅዳር ፮ የምንኵስና ሥርዓታቸው ይፈጸማል። ሐምሌ ፲፮ የጻድቁ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ በዓለ ንግሥ ሲሆን በኅዳር ፮ ደግሞ እመቤታችን ከስደት ተመልሳ ደብረ ቍስቋም የገባችበት ዓመታዊ በዓል ነው። ስለዚህ ወደ መርንኵስና ሕይወት ለሚቀላቀሉ አባቶችና እናቶች ከቅድስት ድንግል ማርያም እና ከአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ቃል ኪዳን ለመቀበል ነው። 

በገዳሙ ሥርዓት መሠረት ከወላጅ አልባዎች ውጭ ለምናኔ የሚመጡ ዕድሜያቸው ከ፲፰ ዓመት በታች የሆኑትን አይቀበልም። ይልቁንም ውስጣቸው ያለው መንፈሳዊነት ልምላሜው የማይቋረጥበትን መንገድ አመላክቶና ምክር ሰጥቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመልሳል።

፩.፫.የአመጋገብ ሥርዓት

አመጋገብን በተመለከተም ገዳሙ ሥርዓት አለው። በበዓለ ሃምሳ በቅዳሜና እሑድ ከጧቱ  ሦስት ከሃያ እና ዘጠኝ ሰዓት ከሃያ ላይ፣ ሥራ በማይሠራባቸው በዓላትና በፍልሰታ በቀን አንድ ጊዜ ዘጠኝ ሰዓት ፣ በሰሙነ ሕማማት ከዋክብት ሲታዩ፤ በሌሎች ቀናት ለአረጋውያንና ለካህናት ዘጠኝ ሰዓት በቀን አንድ ጊዜ ሲሆን ለሚወጡት ለሚወርዱት (ሥራ ለሚሠሩ) አርድእት በሰባት ሰዓት የመቁንን ሥርዓት ተሠርቷል።

በገዳሙ አንድነት በ፳፻፰ ዓ.ም. በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ዐበይት በዓላትንና ዓመታዊ የቅዱሳን መታሰቢያ በዓላትን ጨምሮ በየትኛውም ጊዜ በገዳሙ ውስጥ አስካሪ መጠጥ አይዘጋጅም፤ ሥጋ አይበላም፤ ከውጭም ይዞ መግባት ፈጽሞ ክልክል ነው።

በገዳሙ ሕመምተኞች የሚረዱበት በአባቶችም በእናቶችም ቤተ ሕሙማን ያለ ሲሆን እነሱን የሚንከባከቡ ትራስ ቀና የሚያደርጉ የሚያጎርሱ ልብሳቸውን የሚያጥቡ አረጋውያንንም የሚጦሩ ሊቀ አበው አሉ።

በገዳሙ ውስጥ አእምሮውን ላጣ፣ ሂድ ሂድ ለሚለው ሰው ለ፫ ቀን፣ ለ፯ ቀን ጸሎተ ማርያም ይደረግለታል በሁሉም ጸሎቶች ያታሰባል፤ የንስሓ አባቱ እንዲጎበኙትና እንዲመክሩት ይደረጋል። የማይተወው ከሆነና የሚጸናበት ከሆነ እግረ ሙቅ ይደረግለታል። ከዚህም በተጨማሪ የምክርና የሕክምና እርዳታ የሚያገኝበት በገዳሙ አባቶችና እናቶች የሚገለገል መለስተኛ ክሊኒክም አለ።

፩.፬.የቤተ ሰብ ጉብኝት ሥርዓት

ዘመድ ጥየቃንም በተመለከተ ገዳሙ ሥርዓት አለው። ማንኛውም የመናኝ ቤተሰብ ዘመድ ‹በዚህ ገዳም ይገኛልና ልጠይቀው መጥቻለሁ› ካለ የገዳሙን ህልውና የሚፈታተን ሰው አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠቅሙ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እንዲሁም ስለ መናኙ ማንነትና ስም ይጠየቅና “የተባለው ሰው በገዳሙ ስለ መኖሩ እናጣራለን” ተብሎ በእንግዶች ማረፊያ እንዲያርፍ ይደረጋል። ከዚያም የተባለው ሰው በገዳሙ ያለ ከሆነ እከሌ የሚባል ሰው ያውቅ እንደ ሆነ ተጠይቆ “አውቀዋለሁ” ካለ “ሊጠይቅህ መጥቷልና ልታገኘው ትፈልጋለህ ወይ” ተብሎ ይጠየቃል። “አዎ አግኝቸው ስለ ደኅንነቴ እንዲያውቅና ስለ ሁሉም ነገር ልነግረው እፈልጋለሁ” ካለ እንዲገናኙ ይደረጋል። “አይ ላገኘው አልፈልግም ደኅና መሆኔን ነግራችሁ ሸኙት” ካለ ወይም “አይ ለምናኔ ሕይወቴ ፈተና ስለሚሆንብኝ ላገኘውም አልፈልግም እዚህ መኖሬንም አትንገሩት በጥሩ የእንግዳ አሸኛኘት አስተናግዳችሁ ሸኙት” ካለ በጥሩ ሁኔታ ተስተናግዶ ይሸኛል።

፪.የገዳሙ አስተዳደር የአገልግሎት መዋቅር

ገዳሙን የተመለከተ ማንኛውም ሕግና ሥርዓት ሲወጣና ሲወሰን ሁሉም የገዳሙ አንድነት በተገኙበት ነው። ከዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ቀጥሎ የገዳሙን የትኛውንም እንቅስቃሴ የሚቆጣጠርና የገዳሙ ሥርዓተ ገዳም በትክክል እየተተገበረ መሆኑን የሚከታተል ውይይት አድርጎ ለችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የአበው መማክርት አስተዳደር ጉባኤ የሚባል ፲፫ አባላት ያሉት አበ ምኔቱ፣ እመ ምኔቷ፣ አፈ መምህሩ፣ ጸሓፊው፣ መጋቢው፣ ሊቀ አርድእቱ እና የሰባቱ ዘርፎች ተጠሪዎች ያሉበት ነው።

፪. የሥራ ዘርፎች

ሀ.የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘርፍ፦

ይህ ዘርፍ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልግሎት፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና የአብነት ትምህርት ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ነው።

ለ.የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት ዘርፍ፦ 

በዚህ ዘርፍ ውስጥ የማኅበር መቁነን ዝግጅት ክፍል እና የቁሳቁስ አቅርቦት አገልግሎት ክፍል ይገኛሉ። በውስጡ እንጨት ፈላጮች፣ አህያ ጫኞች ፣ ሊቀ አበው ፣ ባለ ተስፋዎች፣ እጓል መጋቢዎች እና አረጋውያንን ያካተተ ነው። የአገልግሎት ዘርፉ ሥያሜ (የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት) የሚለው በገዳሙ ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያካትት ቢሆንም  ሥያሜው ግን በዚህ ክፍል ለተጠቀሱት የአገልግሎት ዘርፎች ብቻ ስተለተሰጠ እኛም ሥያሜውን እንዳለ ወስደነዋል። 

ሐ.የእጅ ሥራ ዘርፍ፦ 

በውስጡም የጥሬ ዕቃና ምርት ማደራጃ፣ የሽመና፣ የሹራብ ሥራ፣ የጥልፍ ሥራና የኅትመት ሥራ ክፍሎችን በሥሩ የያዘ ነው። በእደ ጥበብ ሥራ ያለውን ከምርት እስከ ጥራት ፍተሻና ቁጥጥር ያለው በዚሁ ዘርፍ ሥር ነው። 

መ.የግብርና ልማት ዘርፍ፦

በውስጡም የእርሻ፣ የደንና የአትክልት ልማት እና የርባታ ክፍሎችን የያዘ ነው።

ሠ.የግንባታ ልማት ዘርፍ፦ 

የቤቶች ግንባታ፣ የመንገድ ሥራና የውኃ ሥራ ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ዘርፍ ነው።

ረ.የቴክኒክና የኢንዱስትሪ ዘርፍ፦

የተሽከርካሪ አገልግሎት፣ የወፍጮና ሌሎች የሞተር ነክ አገልግሎቶች እና የብረታ ብረትና የእንጨት ሥራ ክፍሎችን የያዘ ዘርፍ ነው።

ሰ.የሥነ ጽሑፍና ቅንብር ሥራዎች ዘርፍ፦

የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፣ የድምፅና የምስል ቅንብር ሥራዎች እና የድምፅና ምስል ቀረጻ ክፍሎችን የያዘ ዘርፍ ነው።

ሁሉም የገዳሙ ማኅበረሰብ ከላይ ከተጠቀሱት የሥራና የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የተካተተ ነው። የዘርፎቹም ተጠሪዎች የአበው መማክርት ጉባኤ አባላት ናቸው።

የጥያቄዎቻችሁ መልስ

Details
Written by: በዲ/ን ኃይለማርያም
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 1254
  • የጥያቄያዎቻችሁ መልስ
የጥያቄዎቻችሁ መልስ

ቅዱስ ሲኖዶስ “የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የማስጠበቅ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ራስን የመከላከል እንቅስቃሴ በሰንበት ት/ቤቶች ይመራል” የሚል መግለጫን መስጠቱ ይታወሳል። እኛም በዚህና በተለያዩ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት  ምክትል ሰብሳቢ ከሆኑት አቶ መንክር ግርማ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ሐመር፡- “የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የማስጠበቅ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ራስን የመከላከል እንቅስቃሴ በሰንበት ት/ቤቶች ይመራል” የሚል የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል። ይህ አፈጻጸሙ እንዴት ነው የሚሆነው?

መንክር፡- አፈጻጸሙን በተመለከተ የቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ውሳኔ እና በሚያስቀምጠው አቅጣጫ ይሆናል ብለን እናምናለን። በዝግጁነት ደረጃ በሁለት ከፍለን እንየው። 

ሀ. በአወቃቀር፡- ወጣቶችንም ሆነ ምእመናንን ለማስተባበር አወቃቀሩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ደረጃ የተዋቀረ እና ወጣቶችን የያዘ ሌላ መዋቅር የለም። በዚህ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሕግ አዋቅሮ በቃለ ዐዋዲ ደንግጎ ሕፃናትና ወጣቶችን ዐቅፎ እንዲያገለግል የተዋቀረ አካል ከመሆኑ አንፃር በኔ ግምት ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ  የለም።

ለ. በመሪነት ደረጃም፡- ከወሰድን መዋቅሩ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እና በአብዛኛው አጥቢያ ከመገኘቱ አንጻር የተወሰነ ሥራ ከተሠራ አንጻራዊ እድል አለ ብዬ አስባለሁ። ከዚያም ባሻገር በተለይ በርካታ ነዋሪዎች ባሉበት ከተሞች በአቅም ደረጃም ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች አሉ። ይህ ማለት የተዋጣለት በሁሉ ነገር የተደራጀ ሰው እና ግብአት (ሪሶርስ) አለ ለማለት ሳይሆን በአንጻራዊነት ሕዝቡ ጋር ለመድረስ ከሰንበት ትምህርት ቤት የተሻለ አደረጃጀት የለም። ይህን በአቅሙ ሁሉም ከተረባረበ በአጭር ጊዜ ያለንን የሰው ኃይል እና መዋቅር ተጠቅመን ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠው አቅጣጫ የጉዳቱን መጠን መቀነስ የምንችልበት ዕድል አለ ብዬ አምናለሁ።  

ሐመር፡- መደራጀት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ከመጠበቅ አንፃር ምን ትርጉም አለው? 

መንክር፡- እንደ እምነታችን ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተመሠረተች በመሆኗ ባለቤቱ አይተዋትም፤ ፈታኞችም ድል ይነሣሉ፤ ቤተ ክርስቲያንን ታግሎ ያሸነፈ የለምና። አምላክ ይህን ከፈቀደ እኛ መሣሪያ እንሆናለን የሚለውን ታሳቢ አድርገን ከኛ የሚጠበቀውን ማድረግ ይጠበቅብናል። በዚህም መሠረት፡- መደራጀት በሃይማኖታዊም በዓለማዊም አስተምህሮ ውጤታማ ያደርጋል። ለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን መከራ ከበዛበት ካራን ተስፋ ወደሚያደርጓት ከነዓን ሲጓዙ ሕዝቡን ለመምራት ተቸግሮ ነበር። በአማቱ ዮቶር ምክር የሺህ አለቆችን፣ የመቶ አለቆችን፣ የአምሳ አለቆችን አድርገህ ሹማቸው ባለው መሠረት በዚያ አደራጅቶ በተሰጠው ጊዜና ሰዓት ሕዝቡ ፍትሕን እንዲያገኝ አድርጓል። ‹‹አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ የታመኑ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው።›› እንዲል። (ዘጸ.፲፰፥፳፩)።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአምሳ ሚሊዮን ያላነሰ አማኝና ተከታይ አላት ይህን ሕዝብ በተገቢ መልኩ ብታደራጅ፡ እንኳን ለራሷ በዓለም ደረጃም ከፍተኛ ተፅዕኖን መፍጠር ትችላለች። ስለዚህ ‹‹ካልተደራጀ ዐሥር ሺህ ወታደር የተደራጀ መቶ ወታደር ይሻላል›› እንደሚባለው እኛም በተገቢው መልኩ ብንደራጅ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። መደራጀቱ ጥቃት ሲደርስ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን፡ አስቀድሞም ለማጥቃት የሚያስቡ እኩያንን ለማጋለጥ ይጠቅማል። በአንድነት ተደራጅተን ስንቆም ማንም ሊያጠቃን አይሞክርም። ምክንያቱም የዚህ የተደራጀ ኃይል ሰላማዊ ምላሽ ለአጥቂው ከፍተኛ ኪሳራ የሚያደርስ ይሆናልና ነው። 

ሐመር፡- እስካሁን ባለ መደራጀታችን ምን አጣን? 

መንክር፡- ለዚህ መልሱ ቀላል ነው። አሁን የምናየው በየቦታው ያለው ኦርቶዶክሳዊ በሃይማኖቱ ምክንያት ሲገደል፤ ሲዘረፍ፣ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ከጊዜያዊ የሚዲያ ጩኸት የዘለለ ይህ ነው የሚባል የተደራጀ አካሔድ አይስተዋልም። በመሆኑም ተደጋጋሚ እና የማያቋርጥ የሆነውን  ጥቃት በመደራጀት ልንመክተው ይገባል። 

በሌላ በኩል አሁን አሁን ሁሉም እንደ ፈለገ ቤተ ክርስቲያንን የሚዘልፈው፣ እንደ ፈለገ ቦታዋን የሚቀማው፣ በዓላቷ እንዳይከበሩ እንቅፋት የሚሆነው፣ የበዓላት ማክበሪያ ይዞታዎቻችን በመንግሥት ትኩረት የማያገኙትና በተገቢ መልኩ ለማስከበር አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጣቸው በተገቢው መልኩ ባለመደራጀታችን ነው። 

ሐመር፡- ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ጥቅም የተመሠረቱ ብዙ ማኅብራት እያሉ፡ የቤተ ክርስቲያንን ፈተና ማቃለል ለምን አልተቻለም?

መንክር፡- ቤተ ክርስቲያናችን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አንድ ምእመን ድረስ የሚደርስ መዋቅር ያላት ተቋም ናት። ይሁንና ተቋሟ በተገቢው ሁኔታ በሰው ኃይልና በበጀት ተጠናክሮ ባለ መሥራቱ ብዙ ዋጋ አስክፍሏታል። ይህም ከወለዳቸው አገልግሎቶች መካከል በማኅበራት ተደራጅቶ ቤተ ክርስቲያንን በተቻለ መጠንና አቅም በፈቀደ መልኩ ለማገልገል የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው። በዚህ ዓይነት ዓላማ ተመሥርተው ዘወትር ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የሚደክሙ ማኅበራትና ምእመናን አሉ። ነገር ግን ይህም ከቤተክርስቲያን ሰፊ አገልግሎት  አንጻር ያልተደራጀና ያልተማከለ አሠራር ስለሆነ ማኅበራቱ የሚለኮስ እሳትን ከማጥፋት በዘለለ ዘለቄታዊ መፍትሔን ለማምጣት ተቸግረዋል። አሁንም ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲመጣና የቤተ ክርስቲያን ችግር እንዲፈታ፡ የአቅማቸውን የሚሠሩ ማኅብራትን ቤተ ክርስቲያን ባሏት መዋቅሮች ሁሉ ማሳተፍ ያስፈልጋል። እንዲህ ሲሆን፡ ያለውን የሰውና የገንዘብ ሀብት በተደራጀ መልኩ መጠቀም ይቻላል። መዋቅሩን አቅም ባላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች በማጠናከርና በመደገፍ ሁሉም በአንድነት መንቀሳቀሱ ጥቅሙ ብዙ ነው። በተናጠል ከመዋቅሩ ርቀው የሚመሠረቱ ማኅበራት ግን ጊዜያዊ እና በጣም አናሳ አስተዋጽኦ ከማድረግ የዘለለ የቤተ ክርስቲያንን ችግር በዘላቂነት ሊፈቱ አይችሉም። 

ሐመር፡- የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተደራጅቶ ከመሥራት አንፃር ምን ያህል እየተንቀሳቀሰ ነው? 

መንክር፡- በሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ከመደራጀት አንፃር ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፤ ከአዲስ አበባ ብንነሣ፡ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በንቃት አገልግሎታቸውን የሚሰጡበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ከዚያም ባለፈ ከ፬-፮ አጥቢያዎች በጋራ የሚያስተባብር አደረጃጀት ላለፉት 4 ዓመታት ተሠርቶበት ጥሩ ውጤት እያመጣ ይገኛል። ከዚያም ባለፈ አጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን ከማደራጀት አልፈው የቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን እንዲያደራጁ ኃላፊነት የሰጠቻቸው አካላት በመሆናቸው፡ ኦርቶዶክሳዊ ወጣቶችን ወደ መዋቅር የማደራጀት ሥራ በስፋት እየተሠራ ይገኛል። በሌሎች በተለያዩ ዘርፎችም፡ ማለትም በሀገራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ወጣቱ እንዲሳተፍ በማደራጀት ላይ እንገኛለን።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ስናይም ካሉት ፶፮ አህጉረ ስብከቶች ፴፰ቱን አህጉረ ስብከቶች የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በቅርበት መረጃ የመለዋዋጥና የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በዚህ ዓመት ከፍተኛ ሥራ ይሠራበታል ተብሎ ይታሰባል። 

ሐመር፡- ከማደራጃ መምሪያው ጋር ምን ያህል ተናባችሁ ትሠራላችሁ? 

መንክር፡- ማደራጃ መምሪያው ከመቼውም ጊዜ በላይ አገልግሎታችንን እያገዘ ይገኛል። ለዚህም ዋናው መገለጫ በጣም ጥሩ ይዘት ያለው የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ በእኛው አባላት ከመምሪያው ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፡ ዕቅዱን መሠረት በማድረግም የሀገረ ስብከት ዕቅድ ተዘጋጅቷል። ሀገረ ስብከቶችም ይህን ዕቅድ ከክፍለ ከተማ/ወረዳ አንድነት ጋር በመተባበርና ከዚሁ መሪ ዕቅድ ጋር እንዲናበብ ሆኖ እንዲሠራ አቅጣጫ ተሰጥቶ በዛ መሠረት ከላይ እስከ ታች በዕቅድ ተናበን እየሠራን እንገኛለን። በዚህም ማደራጃ መምሪያው ተገቢውን ድጋፍ አድርጎልናል። ይህን ለማድረግም የሚያስፈልገውን አመራር ለማምጣት ክፍለ ከተሞች በሙሉ ነጻነት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ልጆች ወደ አመራር እንዲመጡ ተደርጓል። በዚህም የማደራጃ መምሪያው የውስጥ መመሪያዎች ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሆኑት በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ መልካም ፈቃድ እና አባታዊ መመሪያ ተሻሽሎ በጥሩ ሁኔታ የተናበበ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። 

ሐመር፡- ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ያቀረባችሁት ጥያቄ ምን ነበር? ምንስ ለውጥ ያመጣል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?

መንክር፡- ጥያቄዎቹ በዋናነት፡-

፩. በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ስላለው ጥቃት፣

፪. የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች አለመፈጸም፣

፫. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ አደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ፣

፬. የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ፣ 

፭. የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ 

፮. የቤተ ክርስቲያን የአእመሮ ሀብት ንብረት ምዝገባ እና የመሳሰሉት ሲሆኑ፡ ቅዱስ ሲኖዶስ አሁን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ያቀረብናቸውን አሳቦች ተወያይቶበታል።  

በነዚህ ፍሬ አሳቦች ላይ ተወያይቶም መመሪያ ሰጥቶባቸዋል።  ራሱ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸው ውሳኔዎች ለብዙ የቤተክርስቲያን ችግሮች መፍትሔ መሆን የሚችሉ ቢሆኑም ውሳኔዎቹ ለዓመታት አለመፈጸማቸው ዋጋ አስከፍሎናል። ይህንን የማስታወሱን ሥራ ነው የሠራነው።

ምን ለውጥ ያመጣል ለተባለው፡ ከዚህ በኋላ ለውጥን ለሆነ አካል የምንተወው አይደለም። ይልቁኑ በተግባር ተሳትፈን የምናመጣው ነው በሚል እንደእኛ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህ መሠረት ጥያቄያችንና ቀጣይ አካሔዳችንን ለቅዱስ ሲኖዶስ አሳውቀናል። ይህንንም በተዋረድ እስከ አጥቢያ ውይይት እየተካሔደበት ነው። ስለዚህ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የለውጡ እንቅፋቶችን የሚጋፈጡ የለውጡ አራማጆችን የሚታዘዙ የሚያግዙ ይሆናሉ። በቀጣይ በዓመት ሁለት ጊዜ የሲኖዶስ ስብሰባ ሲመጣ ጥያቄ የማቅረብ ብቻ ሳይሆን አስፈጻሚውን ‹ለምን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አልተፈጸመም› ብሎ የሚጠይቅና ሲጠይቅም በሙያና በዕውቀት ማገዝ በሚያስችል መልኩ ለማድረግ አንድነቱ ተዘጋጅቷል። ትልቁ ለውጥ ብለን ያስቀመጥነው እኛ ለለውጥ የድርሻችንን ለማበርከት መነሣታችን እና ቅዱስ ሲኖዶስም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መመሪያ መስጠቱን ነው። 

ሐመር፡- ሒደቱ የተገታው የመሪ ዕቅድ ትግበራን ከወቅቱ ጋራ አስማምቶ በማስቀጠል፣ ቤተ ክርስቲያንን ለአስከፊ ጥቃት ያጋለጣት የአሠራር ጉድለት መስተካከል እንዳለበትም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አስተላልፏልና ራስን ከመከላከል አንጻር ምን ዓይነት ፋይዳ አለው ብለው ያምናሉ? 

 መንክር፡- የመሪ ዕቅድ አለመተግበር ብዙ ኪሣራ አድርሷል። መሪ ዕቅዱ ፳፻፮ ዓ.ም. ላይ ጸድቆ ከ፯ ዓመት በኋላ ይፈጸም እያልን እጠየቅን ነው። ይህ መሪ ዕቅድ ቤተ ክርስቲያናችን በስትራቴጂና በዕቅድ እንድትመራ ከማድረጉ በተጨማሪ እንደ ተቋም መዋቅሮቿን በደንብ የሚፈትሽና በተገቢው የሰው ኃይል እና በጀት እንዲጠናከር መንገድ የሚከፍት ነበር። ይህ ማለት የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ላይ ያሉ መመሪያዎች በተገቢው ደረጃ እና የሰው ኃይል ተጠናክረው እንዲሠሩ ያስችላል። ይህም ቤተ ክርስቲያናችንን በስብከተ ወንጌል፣ በወጣቶች፣ በገዳማትና አድባራት፣ በሕግ፣ በሚዲያ፣ በሰበካ ጉባኤ ባሏት በሁሉም መመሪያ የተደራጀና የታቀደ ሥራ እንድትሠራ ያስችላት ነበር። ይህ ተፈጻሚ ሆኖ ቢሆን አሁን ላይ 

ከሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሕዝቧን 

በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ወጣቶቿን 

በገዳማት መምሪያ ገዳማቷንና አድባራቷን   

በሕግ መምሪያ የአእምሮ ንብረቷን፤ ያሏትን ንብረቶቿን አስከብራ እንድትሔድ እና አሁን የገጠመንን ችግር ከግማሽ በላይ መቀነስ ይቻል ነበር። 

ሐመር፡- በስተመጨረሻ ያልተነሣ ጉዳይ አለ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ቢገልጹልን?

መንክር፡- በቀጣይ የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ምንም እንኳን ጥምቀት የቤተ ክርስቲያኗ ሀብት ብቻ ሳይሆን በዩኔስኮ ተመዝግቦ በዓለም ቅርስ የሆነ ቢሆንም፡ መንግሥትንና ባለ ድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት አለመስጠታቸው እንደ ሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት ሥጋት ፈጥሮብናል። ለዚህም ማሳያ የጃንሜዳ ነጋዴዎችን የማንሣት ሥራ አለመጀመር፣ ብዙ የጥምቀት ማክበሪያዎች የይዞታ ማረጋገጫ አለማግኘት፣ ይዞታዎች ከተሰጡ በኋላ መወረራቸው እና ሌሎችም በዚህ በአጭር ጊዜ ሊገለጡ የማይችሉ ፈተናዎች የተጋረጡበት መሆኑ ሁሉ አሳሳቢነው። በቀጣይ በስፋት ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ከግንዛቤ ተወስዶ እኛም እንደ አንድነት ማሰረጃ አደራጅተን እንቅስቃሴ እየጀመርን ስለ ሆነ የእናንተም ሚዲያ ተገቢውን ሽፋን እንዲሰጥ ከወዲሁ ጥያቄያችንን እናቀርባለን።

ሐመር፡- ጊዜዎን ሠውተው ለቃለ መጠይቁ ማብራሪያ ሐሳብ ስለሰጡን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።

መንክር፡- እኔም ለዚህ ጉዳይ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። 

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን። አሜን!

ግብረ ሰዶማዊነት

Details
Written by: ዲ/ን ተስፋዬ አሰፋ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 3062
  • ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር በማይመረመር ጥበቡ ካለመኖር ወደ መኖር በአርአያው እና በአምሳሉ ተፈጥሯል። ሠለስቱ ምዕት በሃይማኖተ አበው «ወኵሉ ሰብእ ዘበአርአያ እግዚአብሔር ወበአምሳሉ እሙንቱ ተፈጥሩ፤ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አርአያ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ናቸው።» (ሃ.አ.፲፱÷፴፫) በማለት እንደ ገለጹት።

የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን የሚታወቀው ከአካላዊ ተፈጥሯችን ባለፈ በለባዊት፣ በነባቢትና በሕያዊት ነፍሳችን ነው። ይኸውም በዚህ ድንቅ የእግዚአብሔር ሥራ ከሸክላው ይልቅ ሸክላ ሠሪውን የምናደንቅበት አንዱ ምክንያት ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ መፍጠሩ ነው። እንዲሁም ወንድና ሴት አድርጐ መፍጠሩም እጅግ ድንቅ  ነው። የሁለቱ ጾታ የራሱ የሆነ የወንድነት ባሕርይ ከሴትነት ተፈጥሮ ጋር ፈጽሞ መለያየት፣ እርስ በእርስ የመፈላለግ እና መሳሳብ፣ የጾታ ልዩነትን መርምረን በመረዳት ፈጣሪን ማድነቅ ይገባል።  ቅዱስ ዳዊት «ግሩም እና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬያለሁና አመሰግንሃለሁ ሥራህ ድንቅ ነው ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች» (መዝ.፻፴፱÷፲፬) ብሎ የተናገረውም ይህን ለማስረዳት ነው።

የሰው ጾታ ምንነት ዐቅድ ወይም ንድፍ ተኮር (Teleological or design focused) የሆነው በእግዚአብሔር ውሳኔ ነው። ወንድ እና ሴት የመሆን ልዩነት ማለት ወንድ በአካልም በመንፈስም የወንድነትን፣ የአባትነትን፣ የወንድምነትን የባልነትን ድርሻ ሲይዝ ከዚህ፣ በተቃራኒ ሴት የሴትነትን፣ የእኅትነትን የሚስትነትን፣ የእናትነትን ሚና ትወስዳለች። ይህ የሚወስደን «ወንድ እና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው» ይልና «እግዚአብሔርም ባረካቸው እንዲህም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት» የሚለው የተፈጥሮ ልዩነታቸውን የሚያስታርቀው ጋብቻ እንደ ኾነ፣ የጾታ ልዩነት ተፈጥሯችን ዘር ለመተካት፣ ከዝሙት ለመከልከል እና ለመረዳዳት እንደ ሆነ ያስረዳናል። (ዘፍ.፩፥፳፮፤ ፪፥፳-፳፭)::

በጋብቻ የሚደረግ መኝታ የወንድ እና ሴት ውሕደታቸው ማሳያ ነው። ይህ ከጽንሰ ሐሳብ የዘለለ ተግባራዊ እውነት ሆኖ እያለ ግብረ ሰዶማዊነት የምዕራቡን ዓለም አሸንፎ በትምህርት ሥርዓታቸው ሳይቀር ተቀርፆ አንድ ሕፃን እስኪያድግ ድረስ ጾታውን አያውቅም ወይም ጾታ የለውም ሲያድግ እርሱ ራሱ ፆታውን ይወስናል እስከ ማለት ደርሰዋል። 

ምዕራባውያኑ ይህም  ሳይበቃቸው የሀገራትን ወንዝ ተሻግረው ውቅያኖሶችን አቋርጠው የሌሎች ሀገራትን  መንግሥታት በብድርና በዕዳ ስረዛ ስም እጆቻቸውን እየጠመዘዙ ግብረ ሰዶማዊነትን በሕገ መንግሥት ደረጃ ካልተቀበላችሁ ርዳታ አንሰጥም፤ የዕዳ ስረዛ አናደርግም፤ የሚሉ ምክንያቶችን በመፍጠር እንደ መብት ሲከራከሩ ብሎም ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል። በዚህም ቤታቸው ውስጥ እያሉ በግብረ ሰዶማውያኑ የተደፈሩ ሕፃናትና ወጣቶችን ሥቃይ ሰምተናል ይሁን እንጂ ፊርማ ከማሰባሰብ በዘለለ የፈየድነው ነገር የለም። 

ይህ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተቆራኛቸው ኢትዮጵያውያንም የፈጸሙት አሳፋሪ ሰዶማዊ  ተግባር ይፋ ወጥቷል። እንግዲህ ስለ ችግሩ አስከፊነት ይበልጥ ለመረዳትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማዊነትን የፈረጀበትን እውነት ማወቅ የመጀመሪያው መነሻ ሐሳብ ነው። ከግብረ ገብነት (moral/ethics) አንጻር መመልከትም ተገቢ ነው። የማስፋፊያ መንገዳቸውን ተረድቶ ለመጠንቀቅ በመቀጠልም በዚህ ጉዳይ ላይ የቤተ ክርስቲያን ሚና ምን መሆን አለበት? እንደ ክርስቲያን ከእኔስ  ምን ይጠበቅብኛል? የሚሉትን ጉዳዮችም አብሮ መመልከት ተገቢ ነው። በዚሀ መሠረት ግብረ ሰዶማዊነት፦  

፩. የተፈጥሮ ሕግን ይቃረናል

ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈሪሳውያን ስለፍቺ በጠየቁት ጊዜ «ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድ እና ሴትን ፈጠረ፤ ስለዚህ ሰው አባት እና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደፊት ሁለት አይደሉም» ብሎ አስረግጦ ራሱ ፈጣሪ ተናግሯል።(ማር.፲፥፮-፱፤ማቴ.፲፱፥፬-፮)  

አንድ ሰው ግብረ ሰዶማዊ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ ወይም የዘር ሐረጎቼ (ancestors) ግብረ ሰዶማዊ ነበሩ ማለት አይችልም። ወንድ ወይም ሴት መሆን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የፈጣሪ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ሴትነት እና ወንድነት ዘር በመተካት የሚመጣ የእግዚአብሔር ጸጋ ከመሆኑም ባለፈ ወንድ ወይም ሴት መሆን እፈልጋለሁ ብሎ የተወለደም የለም። ጋብቻ አዳም  ለሔዋን ሔዋን ለአዳም ከእግዚአብሔር የተሰጠ በመሆኑ ጌታችን ‹ትንሣኤ ሙታን የለም› የሚሉ ሰዱቃውያንን ጥያቄ በመለሰበት የማርቆስ ወንጌል ላይ ሰባት ወንዶች አግብታ የፈታች ሴት በመንግሥተ ሰማያት ለማን ትሆናለች የሚል ጥያቄ ሲያነሡ «ሙታን ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፣ አይጋቡምም» በማለት መልሶላቸዋል  (ማር.፲፪፥፲፰-፳፭)።

እንስሳት ከተቃራኒ ጾታዎቻቸው ጋር ሆነው ድንበር አበጅተው ቤተሰብ መሥርተው የሚኖሩት ከእግዚአብሔር በተሰጠ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ብርሃን ካለ ጨለማ፣ ቀኝ ግራ፣ ፊት ኋላ፣ አጭር ረጅም፣ ክፋት ደግነት፣ ወንድ ሴት እነዚህ ሁሉ በተቃራኒ የሚቆሙ ናቸው።

ይህ የተፈጥሮ ሕግ ያልገዛቸው ለሥጋ ፈቃድ እና ምኞት የተገዙት የሰዶም ሰዎች ምንም እንኳን ጻድቅ ሎጥ ከክፋት ድርጊታቸው እንዲመለሱ ቢለምናቸውም ባለመስማታቸው ከእግዚአብሔር ቅጣት አላመለጡም። ከሎጥ በስተቀር የእሳት ድኝ ከሰማይ ዘንቦ ስለ ኀጢአታቸው አጠፋቸው። መጽሐፍ «ወሰብአ ሰዶምሰ እኩያን፣ ወኃጥአን ጥቀ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎች እና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኀጢአተኞች ነበሩ» እንዲል። (ዘፍ.፲፫፥፲፫፤ዘፍ.፲፱፥፩-፲፬)

አሁን ያለንበት ጊዜ ከሎጥ ጋር አልያም ከሰዶማውያን ጋር መቆማችንን የምናስተውልበት ጊዜ ነው። አንዳች ጥቅም አገኝበታለሁ ብሎ ወይም ግብረሰዶማዊ መሆን አይደለም ማሰብ በራሱ ግብረ ሰዶማዊነት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ «ኢትአምሩኑ ከመ አማፅያን ኢይሬእይዋ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ወንድሞቻቸውን የሚበድሉ ሰዎች መንግሥተ ሰማይን እንዳይወርሱ አታውቁምን? ኢያስሕቱከሙ፣ ይወርሳሉ የሚሉ ሰዎች አያስቷችሁ፣ ኢዘማውያን ዘማውያንም ሆኑ ወኢእለ ያጣዕዉ ጣዖት የሚያመልኩም ሆኑ ወኢእለ ይኤብሱ በነፍስቶሙ ታንቀው የሚሞቱም ወኢእለ የሐውሩ ግብረ ሰዶም የሚሠሩ ወኢእለ የሐውርዎሙ ግብረ ሰዶም የሚሠሩባቸው….. ወኢኀያድያን የሰው ከብት የሚቀሙ ኢይወርስዋ ለመንግሥተ እግዚአብሔር የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም» ብሏል። (፩ቆሮ.፮፥፱ አንድምታ)

ግብረ ሰዶማዊነትን ለማውገዝ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃል ፈጽሞ ያወግዛቸዋል። ይህንንም ከቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት እንረዳለን። ቅዱስ ጳውሎስ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ለተመለሱ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሰዶማዊነት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ጸያፍ እና የከፋ ኀጢአት እንደ ሆነ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ መስክሯል። በተለይ ለሮማውያን በፌበን እጅ በላከው ክታቡ በሰዶማዊ ኀጢአት በሥጋ ፍትወት ስለ ወደቁ ሰዎች በግልጽ «ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሰፍትን አመጣባቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባቸውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን ሠሩ። ወንዶች እንዲሁ  ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ እርስ በእርሳቸውም እየተመላለሱ ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን  ነውር ሠሩ። ነገር ግን ፍዳቸውን ያገኛሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን እንዲሁ እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮን  ሰጣቸው» (ሮሜ ፩፥፳፮-፳፰) ብሏል።

‹የዚህ ሁሉ ምክንያት እግዚአብሔርን ለማወቅ አለመፈለግ ነው› ይላል ሐዋርያው። እግዚአብሔርን ለማወቅ የጓጓ አእምሮ ቅዱስ ዳዊት  «ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» እንዳለ እንደ አብርሃም፣ እንደ ሙሴ ጸሊም በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ ያውቀዋል። (መዝ.፲፰፥፩) እሱን የሚያውቅ ለማይረባ አእምሮ ተላልፎ አይሰጥም። ምክንያቱም ግብረ ሰዶማዊነት የሚረባ አእምሮ ያለው ሰው የሚያደርገው አይደለምና። የሚረባ አእምሮ አዳማዊ ሔዋናዊ ሕግን በአእምሮ ተመራምሮ ይደርስበታል፣ ይረዳልም። ከሐዲስ ኪዳን ዘመንም በፊት እግዚአብሔር ለሙሴ በኦሪት ዘሌዋውያን የድርጊቱን አእምሮ የለሽ አስነዋሪነት «ፀያፍ» ብሎ ነው የገለጸው «የአምላክህን ስም አታርክስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ፀያፍ ነገር ነውና» (ዘሌ.፲፰፥፳፪) እንዲል።

ይህን ድርጊት ስናወግዝ ከእግዚአብሔር ጋር እንደምንተባበር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቅዱስ ጳውሎስ በአጽንዖት ቃል ሲገልጽ «ወንድሞች ሆይ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተማርሁትምም» ብሏል። (ገላ. ፩፥፲፩) ድርጊቱን ማውገዝ መለኮታዊ ትእዛዝ እንጂ ሰው ስላለን ወይም መቃወም ስለ ፈለግን ብቻ አይደለም መቃወማችንም የአንድ ሰሞን ፉከራ መሆን የለበትም። ይህ ጉዳይ ፈጽሞ ከቅዱሳት መጻሕፍት ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ከቅዱሳን አበው ትምህርት እና ሕይወት ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ ነውና። 

እግዚአብሔር ለወንድ እና ለሴት በከበረ ጋብቻ አንድ  ሥጋ እንዲኾኑ በፍቅርና በመተሳሰብ በአንድነትም እንዲኖሩ ተፈጥሯዊ ዝንባሌን ሰጥቷቸዋል። በተፈጥሮ የተሰጠንን ትክክለኛ ስሜት አለማግኘታችንን በእሱ አለመደሰት መቻላችን በውስጣችን እንስሳዊ ስሜትን መግራት አለመቻል እና የሰውነት ስሜታችን በልጦብን የመንፈስ ልዕልናችን ለማሳደግ አለመፈለጋችን በከፋ ኀጢአት እንድን ወድቅ ሆነናል። በራሳችን ላይ ጦርነት አውጀናል። ሰው ጨካኝ እና የተፈጥሮን ሕግ የሚጥስ ብሎም ተፈጥሮን የሚያጠፋ ከንቱ ፍጡር ሆኗል። እንስሳት እንኳን  የማያደርጉትን ነገር መድፈር አሁን፣ አሁን የተለመደ ነገር ሆኗል። ኀጢአት የውስጥ ሰላማችንን ስለሚያዛባው መረጋጋት እና ሰላም ማግኘት አልቻልንም። ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ሳይሆን በራሳችን የምንኮራ፣ ተሳዳቢዎች፣ ለፀብ እና ክርክር የተመቸን አድርጎናል። 

«ሴት የወንድን ልብስ አትልበስ ፥ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ ፤ይህን የሚያደርግ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና»።  ዘዳ ፳፪፥፭። ከዚህ በተፃራሪ ዘመኑ የደረሰበትን የሕክምና ጥበብ ተጠቅሞ ወንድ ልጅ፡ ሴት ሆኖ፤ ቀሚስ አድርጎ እንደ ሴት እያወራ እየተራመደ፤ ኩል ተቀብቶ ሲመጣ ማየትን ኅሊና እንዴት ሊቀበለው ይችላል? ይህ ማለት በሰው ዘር ማንነት (ተፈጥሮ ) ላይ የተነሣ ፀረ-ሰብእ ድርጊት ነው።

እነዚህን ሁሉ የኀጢአት ዓይነቶች ስናስብ የሰው ልጅ ምን ያህል በፈቃዱ ያለ ማንም አስገዳጅነት የሕይወት ምንጭ በሆነው እግዚአብሔር ላይ ማመፁን እንረዳለን። እያንዳንዱ ኀጢአት ሌላ ኀጢአት ይወልዳል። ግብረ ሰዶማዊነትም በባሕርዩ ከአንድ ኀጢአት ወደ ሌላ ኀጢአት የመሸጋገርና  ለከፋ ኀጢአት የሚያጋለጥ ነው። 

፪. ግብረ ሰዶማዊነት በእግዚአብሔር ሕግ ላይ ማመፅ ነው

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ በተደጋጋሚ ዐምጿል፤ ይህኛው የፈጠረውን አምላኩን ከተቃወመበት የስሕተት መንገድ በጣም የከፋው ነው። «ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ… ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ...» (፩ቆሮ.፮፥፱-፲) ብሎ ነው ያስቀመጠው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ንስሓ ቢገቡ እና ቢመለሱ ይቅርታው ሰፊ ነው። «ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን» (ሮሜ፰፥፲፯) ብሏልና። ነገር ግን ንስሓ ለመግባት ፈቃደኛ ካልሆኑ መንግሥቱን እንደማይወርሱ ሐዋርያው በሁለት ወሳኝ ሐሳቦች አሳስቧል። የመጀመሪያው የእግዚአብሔርን መንግሥት ማጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ወደ ገሃነመ እሳት መግባት ናቸው።

፫.ግብረ ሰዶማዊነት ግብረ ገባዊነትን (morality) ይፃረራል

ግብረ ገብነት (morality) በሕግና በኅሊና ሚዛን እውነት ወይም ሐሰት ለማለት የሚያስችለን ከቤተ ሰቦቻችን ፤ ከአካባቢያችን የምንማረው ነው። ሁሉም ሰው የሚስማማባቸው ግብረ ገባዊ ሕግጋት (moral laws) አሉ። ሰውን መግደልን እና ሌሎች መሠል ድርጊቶች ኅሊና አይቀበላቸውም ። ከዚህ አንጸር  ግብረ ሰዶማዊነትም በግብረ ገባዊ ሕግ ሚዛን ሲታይ ተቀባይነትም የለውም።  ግብረ ገባዊነትን በሚፃረር ሁኔታ  በራስ አስተሳሰብ ለራሳችን በምንፈልገው መንገድ መቀየር ከጀመርን ሰነባብተናል። ለምሳሌ “ግብረ ሰዶማዊነት ኀጢአት አይደለም” ብሎ እንደ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት በሕገ መንግሥት ደረጃ ተቀብሎ ማርቀቅ ለአድራጊዎቹ ለጊዜው ትክክል ቢመስላቸው ሕጉን ስለቀየርነው በእውነታዊው ዓለም ያለው ግብረ ገባዊ የኅሊና ሕግ  ትክክል ነው ማለት አይደለም። መሠረታዊ የግብረ ገብ ዕውቀቶች እኛ ስንቀየር እነሱ አይቀየሩም። እኛ ተቀይረናል ማለት መሬት ላይ ያለው ግብረ ገባዊ (moralilty) እውነት ተቀይሯል ማለትም አይደለም። ጥንቱንም ሕፃናትን መድፈር፣ ሰውን መግደል፣ መስረቅ አስነዋሪ ኀጢአት ነው ዛሬም ያው ነው። የሚቀየረው በእነሱ ላይ ያለን አመለካከት ነው። ይህን አመለካከት በጊዜ ሂደት ባለንበት የሕይወት ደረጃ ልክ እንመዝነዋለን። 

ኀጢአትን ቀን ተቀን ልምምዱ እያደረገ ያለ ሰው ስለዚህ ነገር ማውራት በራሱ ትርጉም አይሰጠውም። ነገር ግን ሥነ ምግባሩ አይቀየርም። ለምሳሌ ስለ ፍቅር ያለን አመለካከት ላለፉት ጊዜያት ሊቀየር ይችላል፤ ነገር ግን እኛ ልንቀየር ብንችል እንኳን ፍቅር አልተቀየረም። ይህም ግብረ ሰዶማዊነት መብት አይደለም ወደሚል መደምደምያ ይወስደናል። ይህን ድርጊት መፈጸም ከግብረ ገብነት (morality)  አኳያ ትክክል ካልሆነ ትክክል ያልሆነ ነገርን የሚፈቅድ መብት የለም ማለት ነው። እንደ መብት ለመከራከር ጉዳዩ ትክክል መሆን ያሻዋል። የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ሕጎችም መሠረት የሚያደርጓቸው ዐሥርቱ የሙሴ ሕግጋትንና ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን የማኅበረ ሰብን ቅቡል የሆኑ ግብረ ገባዊ ሕጎችን በመጠበቅ ላይ ነው። ግብረ ሰዶማዊነትም ከግብረ ገብነት አኳያ ስሕተት ስለ ሆነ ተቀባይነት የለውም። ይህን የምንቀበል ከሆነ ሕፃናትን የደፈሩ፣ የሰው ነፍስ ያጠፉ፣ በሕግ ደረጃ ትክክል ናችሁ ብለን እነሱንም መቀበል አለብን ማለት ነው። በግብረ ገብም፣ በፍትሐ ብሔርም ሕግ በእግዚአብሔር ሕግም ተቀባይነት ስለሌለው፡ ቤተ ክርስቲያንም አትቀበለውም። 

፬. እንስሳዊ አፈንጋጭ ባሕርያት በሰው ዘንድ ቅቡል (normative) አይደሉም

ግብረ ሰዶማዊነት እንስሳዊ ባሕርይ ነው። (moral)፣ አመዛዛኝ አሳቢ (rational) አይደሉም። በተሰጠው ነፃ ፈቃድ ሠናይ ወይም እኩይ ተግባራትን እንዲመርጥ የተፈጠረ ፍጡር ከሰውነት ወደእንስሳነት ከወረደ እንስሳ እንጂ ሰው ሊባል አይችልም።    

፭. ሳይንሳዊ መሠረትነት የለውም 

ሌላኛው በሳይንሱ ዓለም ወንድ ከ፵፮ ሃብለ በራሂ (chromosom) ሴትም ከ፵፮ ሃብለ በራሂ (chromosom) እንደ ተፈጠሩ ያትታል። ዕፅዋት የወንዴ እና ሴቴ ዘር በመጣመር ይራባሉ። አበቦች የሚራቡት በእንስሳት ወይም ነፋስ ተሸካሚነት የወንዴ ጽጌ ከሴቴ ጽጌ ጋር ሲገናኝ ብቻ ነው። ግብረ ሰዶማዊነት ከዚህ የተፈጥሮ ሕግ የተለየ ነው። 

፮. በጤና ረገድ ገዳይ ነው

ተፈጥሮን ያልተከተለ በመሆኑ በጤንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። HIV virusን ጨምሮ ለአንጀት ካንሰር እና መሰል በሽታ ተጋልጠዋል። በስተመጨረሻም ከሕክምና የመቆጣጠር ደረጃ በላይ ሆኖ ከሰውነት ደረጃ ወጥተው ለመኖር ይገደዳሉ። በተለይ በመደፈር ተጎጂ የሆኑ ከሆኑ እኛም ቀርበን ሕክምና እንዲከታተሉ ከመግፋት ይልቅ ስለምናገላቸው ለከፍተኛ የሥነ ልቡና ጫና ይጋለጣሉ፤ መማር፤ መሥራት ስለማይችሉ ራሳቸውን ለማጥፋት ሊገደዱ ይችላሉ። 

የአደራ ደብዳቤ

Details
Written by: ዲ/ን አሸናፊ ደሳለኝ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 1668
  • ኪነ ጥበብ

ታላቁ የሕይወት መምህሬ አለቃ ዜና በሕይወተ ሥጋ በግዙፉና በተዳሳሹ ኑባሬ  ዛሬን የሉም ልበል እንጂ ‹‹ሞቱ›› የሚለውን ገዳይ ቃል ለእርሳቸዉ መጠቀም ታላቅ በደል ሆኖ ይሰማኛል።  ምክንያቱም ምንም እንኳን በአካለ ሥጋ በላገኛቸዉም ዘወትር በየዕለቱ ምክርና ተግሣጻቸዉን እንደ ተናፋቂ ዘመድ በመንፈስ ደብዳቤ ከትበው በዐጸደ ነፍስ ይልኩልኛልና። እነዚያን ልዩ የሕይወት ደብዳቤዎች ባነበብኩ ቁጥር  መንፈሴ ይበረታል፤ በወንዝ ዳር እንደ በቀለች፣ ፍሬዋንም በየጊዜው እንደምትቸር ተክል (መዝ. ፩፥፫) ልምላሜ ይሰማኛል። ለዛሬ  ከእነዚህ ልቤን ከሚያበረቱት ጦማሮች አንዱ የሆነውን አካፍላችሁ ዘንድ እሻለሁ ።

ቀን /፲፪/፪/፳፻፲፪ ዓ.ም

የተላከ ከአለቃ ዜና 

ይድረስ ለመንፈስ ልጄ ……….

ልጄ ሆይ እንደ ምን አለህ? ጤናህስ እንዴት ይዞሃል? በትጋት ከሐኪምህ ዘንድ ዕለት ዕለት   እየተከታተልህ ነዉን? አየ. . . ልጄ አንተ እኮ የዋሕ ነህ። አሁን ይህንን ባልኩህ ጊዜ  አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ስለ ክቡር ሞቱና  ትንሣኤዉ ለመንገር በሕንጻ ቤተ መቅደስ እንደ መሰለላቸዉ (ዮሐ.፪፥፲፱)፣ አይሁድም ስለ ሕንጻ ቤተ መቅደስ የሚናገር እንደ መሰላቸው ሁሉ፡ አንተም ይህን ደዌ ሥጋን የጠየኩህ መስሎህ ስለ ራስ ምታትና ቁርጠት እያሰብክ ይሆናል . .    እንዲያም አይደል ልጄ፤  እርግጥ ነው እንበለ ሥጋ …  እንዲሉ አበው  የሥጋ ጤንነትህ ቢያሳስበኝም . .  እኔን የበለጠ የሚያስጨንቀኝና የሚያሳስበኝ፣ የጠየኩህም የነፍስህን፣ የመንፈስህን ደኅንነት ነዉ። ሐኪሙም መምህረ ንስሓህ (የንስሓ አባትህ) ነው። እናም  የቀለም ልጄ የመከርኩህንና ያሰተማርኩህን አደራ፤ ዘወትር  የነፍስህ ሐኪም ወደ ሆነዉ የንሰሐ አባትህ ብቅ እያልክ እራስህን በኑዛዜ አስመርምረህ የፈውስህ ምክንያት ይሆን ዘንድ ቀኖና መድኃኒትህን በሚገባ ትከታተል ዘንድ አደራ እልሃለሁ።  ይህንን ለሰላምታ ያህል ካልኩህ ዘንዳ  ዛሬ  ነፍሴ የታዘበችህንና ላስታውስህ  የምሻውን ቁም ነገር  ልጽፍልህ ወደድኩ።  ሰላመ እግዚአብሔር አይለይህ ።

Read more: የአደራ ደብዳቤ

በናጎርኖ-ካራባኽ የሚገኘው የመድኃኔዓለም ካቴድራል በከባድ መሣሪያ ተመታ

Details
Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 06 November 2020
Hits: 1181
  • ከዓለም ማእዘናት
በናጎርኖ-ካራባኽ የሚገኘው የመድኃኔዓለም ካቴድራል በከባድ መሣሪያ ተመታ

ናጎርኖ-ካራባኽ (Nagorno-Karabakh) በአርመንና በአዘርባጃን መካከል ለተከሰተው ጦርነት ምክንያት የሆነች አካባቢ ናት።

አካባቢው በአዘርባጃን የአስተዳደር ወሰን ሥር ያለ ሲሆን፡ የሚኖሩበት ግን አርመናውያን ክርስቲያኖች ናቸው። በዚህ አካባቢ ላይ ውጥረትን ያነገሠው ቆየት ያለው ግጭት የተፈጠረው፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹እኛ ዝርያችን አርመን፣ እምነታችንም ክርስትና ነውና ከማትመስለን ከአዘርባጃን ጋር አንኖርም›› በማለት የፈጠሩት እንቅስቃሴ ነበር። በዚህም ምክንያት ከ1981 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ በኹለቱ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ተከሰተ። በቀጣዮቹ ዓመታትም በአውዳሚ ጦርነት እርስ በእርሳቸው ተዋግተው ከባድ ዋጋን ከፈሉ።

ከዚህ በኋላ የአካባቢው አማጽያን ራሳቸውን ‹‹የአርትሳክ ሪፐብሊክ (Republic of Artsak)›› በማለት ሰይመው ለአዘርባጃን መንግሥት ያላቸውን እምቢተኝነት ገፉበት። የናጎርኖ-ካራባኽ አማጽያን የሚባሉት እነዚህ ኃይሎች ዋና ዓላማቸው ከአርመኖች ጋር መዋሐድ ነበር።

ከሰሙኑ እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነትም፡ የአዘርባጃን የራስ ገዝ ግዛቱን በኃይል ጠቅልላ ለመያዝ ያደረገችው ጥረት ነበር። በዚህም የራስ ገዙ ጦር የአዘርባጃንን ጥቃት ለመመከት የሚያደርገውን ጥረት የአርመን ጦር ሙሉ በሙሉ ስለ ደገፈው፡ ሁለቱ ሀገራት ወደ ሙሉ ጦርነት ለመግባት ተገድደዋል። አዘርባጃን ‹‹በግዛቴ ውስጥ በማያገባት ገብታ ወረራ ፈጽማብኛለች›› በማለት አርመንን ስትከስ፤ አርመንም ‹‹በናጎርኖ-ካራባክ ግዛት ውስጥ በሚገኙ አርመናውያን ላይ ከፍተኛ ጭቆናና በኃይል የመያዝ ግፍን እየፈጸመች ነው›› ስትል አዘርባጃንን ትከሳለች።

በናጎርኖ ካራባክ የሚገኘው በአርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥር ያለው የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ባለፈው የፈረንጆቹ ወር በከባድ መሣሪያ ሊመታ የቻለውም በዚህ ሰሞንኛ ግጭት ምክንያት ነው። አርመን እንደ ገለጸችው፡- ይህ ጋዛንቼትሶትስ ካቴድራል (Ghazanchetsots Cathedral) በመባልም የሚታወቀው ይህ የመድኃኔዓለም ካቴድራል፡ በመጀመሪያ ጉልላቱ በከባድ መሣሪያ ተመታና በከፊል ፈረሰ። የውስጥ አካሉም በዚህ ጥቃት ጉዳት ደረሰበት። ሌሎች ዘገባዎችም አያይዘው ሕፃናትና ጎልማሶች በካቴድራሉ ውስጥ ተጠልለው እንደ ነበር ይገልጹና፡ በመጀመሪያው ጥቃት ማንም የተጎዳ እንዳልነበር ያክላሉ።

ከብዙ ሰዓታት በኋላ ካቴድራሉ በድጋሚ ተመታ፤ በውስጡ የነበሩት ሁለት ራሺያውያን ጋዜጠኞችም በጥቃቱ ቆሰሉ። የአርመን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ‹‹ጥቃቱ አውሬአዊ ወንጀልና ለሰው ልጅም ትልቅ ተግዳሮት ነው›› ሲሉ የገለጹ ሲሆን፡ የሃይማኖት ተቋማትን ዒላማ ማድረግ የጦርነት ወንጀል መሆኑንም አክለው ተናግረዋል። ሆኖም አዘርባጃን ታሪካዊ፣ ባሕላዊና በተለይም ሃይማኖታዊ ሕንጻዎችንና ሐውልቶችን ዒላማ እንደማታደርግ በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል በመግለጽ ጥቃቱን ክዳለች።

በጥቃቱ ጊዜ እጅግ ተጨንቀው እንደ ነበር የገለጹት አባ እንድርያስ የተባሉ የካቴድራሉ ካህን ‹‹የውቡ ካቴድራላችን ግድግዳዎች የመፍረሳቸው ሕመም ይሰማኛል፤ ዛሬ እዚህ እየተከሰተ ስላለው ነገርና እናት መሬታቸውን እየጠበቁ ልጆቻችን እየሞቱ ዓለም ዝም የማለቷ ሕመምም ይሰማኛል›› ሲሉ መሪር ኀዘናቸውን ገልጸዋል።

ሹሻ በተባለችው የግዛቱ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ይህ ካቴድራል በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታነጸ ሲሆን፡ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1920ዓ.ም. አካባቢ በዘር ምክንያት በተነሣ ግጭት ጉዳት ደርሶበት የነበረ ሲሆን፡ በ1980ዎቹ ከነበሩት ግጭቶች በኋላም ታድሶ ነበር።

የሁለቱ ሀገራት ግጭትና በካቴድራሉ ላይ የደረሰውም ጉዳት፡ ጦርነት እጅግ አውዳሚና ክፉ መሆኑን የሚያስተምር ነው። (ምንጭ፡- AP, AFP, Reuters)

 

Page 6 of 9

  • 1
  • 2
  • 3
  • 4
  • 5
  • 6
  • 7
  • 8
  • 9

የቅጅ መብት © ማኅበረ ቅዱሳን 2012 ዓ.ም.

ዋናው ማዕከል | Afaan Oromoo | English |አሜሪካ ማዕከል | አውሮፓ ማዕከል | ካናዳ ማዕከል | ትሩፋት
MK Facebook MK Telegram MK Youtube
አጫጭር ዜናዎች የሕፃናት ዓምድ ትዝብት ሪፖርታዥ ቤተ አብርሃም ፍሬ ከናፍር ምሥጢሬን ላካፍላችሁ ርዕሰ አንቀጽ Oct ኪነ ጥበብ June ዐውደ ስብከት sept እናስተዋውቃችሁ ትምህርተ ሃይማኖት Nov Mar Apr ዐቢይ ጉዳይ ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት የነገዋ ቤተ ክርስቲያን የጥያቄያዎቻችሁ መልስ July የማኅበሩ መልእክት Jan Aug May 1997 13 ከዓለም ማእዘናት