- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1346
ውድ አንባብያን ባለፈው ትምህርታችን የመስም ቅጽልና የመድበል ቅጽልን ምንነት ተምረናል። የቤት ሥራም መስጠታችን ይታወሳል። እናንተም እንደሠራችሁት ተስፋ እናደርጋለን።
ለማረጋገጥ በሚከተለው መንገድ መልሱን እናስቀምጣለን።
| ተ.ቁ | ግስ | መስም ሳድስ ቅጽል | መስም ሣልስ ቅጽል | መድበል ቅጽል |
| ፩ | ከሠተ | መክሥት | ከሠት | |
| ፪ | ተለወ | መትልው | ተለውት | |
| ፫ | ተንበለ | መተንብል | ተንበልት | |
| ፬ | ነበረ | መንብር | ነበርት | |
| ፭ | ሜጠ | መመይጥ | መየጥ | |
| ፮ | ሰፈነ | መስፍን | መስፈኒ | ሰፈንት |
| ፯ | ነገደ | መንግድ | ነገድ |
ውድ አንባብያን መልሱን በዚህ መልክ ከሠራችሁት ጥሩ ሠርታችኋል። በዚህ ዕትማችን ደግሞ ስለ ወገን ቅጽልና ስለ አኀዝ ቅጽል እንመለከታለን።ማስታወሻ አንዳንድ ግሶች መስም ሳድስ ቅጽል እንጅ መስም ሣልስ ቅጽል ላይኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ የቀተለ መስም ሳድስ ቅጽሉ መቅትል መስም ሣልስ ቅጽሉ መቅተሊ ይሆናል። ጠበ የሚለው ግስ መስም ሳድስ ቅጽሉ መጥብብ ሲሆን መስም ሣልስ ቅጽሉ ደግሞ መጥበቢ ይሆናል። የጸንዐ ደግሞ መስም ሣልስ ቅጽሉ መጽንዒ ይሆናል። ስለዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ግሶች መስም ሣልስ ቅጽል ያልተጻፈላቸው በመጽሐፍ የማይገኝላቸው ስለሆነ ነው።
ወገን ቅጽል
ይህ የቅጽል ዓይነት ወገንነትን፣ ዝምድናን የሚያመለክት ሲሆን በሀገር ስም ላይ ለተባዕታይ ጾታ ዊ/ ይ እና ለአንስታይ ጾታ ደግሞ ዊት/ ይት በመጨመር ይመሠረታል። ይህን በተመለከተ መምህር ዕንባቆም የግእዝ ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ ለተማሪዎች በልዩ አቀራረብ የተዘጋጀ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፸ ላይ “ወገን ቅጽል ማለት አባትነትን፣ ወገንነትን፣ ጎሳነትን የሚያሳይ ሲሆን የሀገርና የትውልድ ስሞች መድረሻ ፊደላቸውን ራብዕ እያደረገ ምዕላድ ፊደላት “ዊ”፣ ”ዊት”፣ “ይ” ፣ “ይት” ን በመጨመር የሚቀጸል ነው” በማለት ያስረዳሉ።
መምህር አስበ ድንግል ደግሞ ግእዝ ልሳነ ኢትዮጵያ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፴፫ ላይ ጾታ ቅጽል በማለት ይጠሩትና ሲያብራሩት ግን “ጾታ ቅጽል ማለት ወገን ቅጽል ማለት ነው። በስም ላይ አርፎ ወገንነትን የሚገልጽ ነው በመድረሻው ላይ፡- ለነጠላ ወንድ “ዊ”፣ ለነጠላ ሴት “ዊት”፣ ለብዙ ወንድ “ውያን”፣ ለብዙ ሴት “ውያት” በቅጽልነት የሚገኝበት ነው። በማለት ጾታ ቅጽል ብለው የጠሩት ወገን ቅጽል ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ።
የሁለቱም መምህራን ከስያሜ ያለፈ ልዩነት የለውም። በዚህም ወገን ቅጽል ማለት በስሞች ላይ “ዊ/ይ”፣ “ዊት/ ይት” የሚሉ ምዕላዶችን በመቀጠል ዝምድናን የሚያስረዳ የቅጽል ዓይነት ነው። የተሻለ ግልጽ ለማድረግ በምሳሌ እንመልከተው።
| ተ.ቁ | ስም | መስም ሳድስ ቅጽል | መስም ሣልስ ቅጽል | መድበል ቅጽል | አንስታይ ብዙ |
| ፩ | ሰማይ | ሰማያዊ | ሰማያዊት | ሰማያውያን | ሰማያውያት |
| ፪ | ኢትዮጵያ | ኢትዮጵያዊ | ኢትዮጵያዊት | ኢትዮጵያውያን | ኢትዮጵያውያት |
| ፫ | ድኅር | ደኃራዊ/ይ | ደኃራዊት/ይት | ደኃራውያን/ ይያን | ደኃራውያት/ይያት |
| ፬ | ምድር | ምድራዊ | ምድራዊት | ምድራውያን | ምድራውያት |
| ፭ | ግብፅ | ግብፃዊ | ግብፃዊት | ግብፃውያን | ግብፃውያት |
አኀዝ ቅጽል
አኀዝ ቅጽል የሚባለው ቁጥር ሲሆን የነገሮችንና የስሞችን መጠን ወይም ብዛት ለመለካት የሚያገለግል ነው። ይህ ቅጽል ለነገር፣ ለሰው ስሞች ሲሆን እና ለዕለታት ሲሆን የተለያየ ቅርጽ አለው።
ለምሳሌ፡- ለሰው ወይም ለነገር ሲሆን አሐዱ፣ ክልኤቱ፣ ሠለስቱ፣ ዐርባዕቱ፣ ኀመስቱ፣ ስድስቱ፣ ሰብዓቱ፣ ሰመንቱ፣ ተስዓቱ፣ ዐሠርቱ
ዐሠርቱ ወአሐዱ፣ ዐሠርቱ ወክልኤቱ፣ ዐሠርቱ ወሠለስቱ፣ ዐሠርቱ ወዐርባዕቱ፣ ዐሠርቱ ወኀመስቱ፣… እያለ ይገለጻል።
ለዕለታት ሲሆን፡- አሚሩ፣ ሰኑዩ፣ ሠሉሱ፣ ረብዑ፣ ሐሙሱ፣ ሰዱሱ፣ ሰብዑኡ፣ ሰሙኑ፣ ተስዑ፣ ዐሥሩ
ዐሥሩ ወአሚሩ፣ ዐሥሩ ወሰኑዩ፣ ዐሥሩ፣ ወሠሉሱ፣ ዐሥሩ ወረብዑ፣ ዐሥሩ ወሐሙሱ፣ … እያለ ይቀጥላል።
በአጠቃላይ አኀዝ ቅጽል በነገሮች ስም፣ በሰዎች ስም፣ በዕለታት ላይ ወዘተ እየተጨመረ ብዛትን የሚያመለክት የቅጽል ዓይነት ነው።
ውድን አንባብያን ከላይ የቀረበው ትምህርት ግልጽ ከሆነ የቤት ሠራ እንስጣችሁ።
፩. ውድ አንባብያን በሚከተሉት ቃላት ወገን አመልካች ምዕላድን በመጨመር በነጠላና በብዙ፣ በሴትና በወንድ ወገን አመልካች ቃላትን መሥርቱ።
| ተ.ቁ | ስም | መስም ሳድስ ቅጽል | መስም ሣልስ ቅጽል | መድበል ቅጽል | አንስታይ ብዙ |
| ፩ | ገሊላ | ||||
| ፪ | ቅድም | ||||
| ፫ | ሣልስ | ||||
| ፬ | ሀገር | ||||
| ፭ | ሐሳብ |
፪. ውድ አንባብያን የሚከተሉትን ቁጥሮች ለዕለታት ሲሆን እንዴት መጠቀም እንደምንችል በፊደል በመጠቀም (አኀዝ ቅጽሎችን) መሥርቱ።
፲፮፣ ፲፯፣ ፲፰፣ ፲፱፣ ፳፣ ፳፩፣ ፳፪፣ ፳፫፣ ፳፬፣ ፳፭፣ ፳፮፣ ፳፯፣ ፳፰፣ ፳፱፣ ፴
- Details
- Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1498
ዶክተር ጆሲ ጄኮብ (ቀሲስ) በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ውስጥ ለአሥራ ስድስት ዓመታት ያስተማሩ የሕንድ የማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህንና መምህር ናቸው። መምህሩ ከኮሌጁ የመምህርነት አገልግሎታቸው በተጨማሪ እዚህ በቆዩባቸው ዓመታት በሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠነክርም በትጋት ሠርተዋል። ታዲያ ይህን ቆያታቸውን እና በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት Orthodoxy Cognate Page የተባለ ሚዲያ አጭር ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር።
ዶክተሩ በቃለመጠይቁ ላይ በመንፈሳዊ ኮሌጁ የነበራቸውን የአሥራ ስድስት ዓመት ቆይታ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፡-
‹‹ከሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ነገረ መለኮትን እንዳስተምር ወደ ኢትዮጵያ የተላኩት ጥቅምት ፳፰፣ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ነበር። በዚያም ለ፲፮ ዓመታት ያክል ቆይቼ ወደ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተመለስኩት በ፳፻፲፩ ዓ.ም. ነበር። በዚህም ብዙ ልምዶችን አግኝቼበታለሁ። ከተለያዩ ቦታዎች፣ ከተለያዩ የሥራ ዘርፎች፣ ከተለያዩ የሕይወት ዳራዎች ከሚመጡ ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝቼአለሁ። ብዙ ተምሬአለሁ። እንደውም በኢትዮጵያ ‹መምህር ነበርኩ› ከምል ይልቅ ‹ተማሪ ነበርኩ› ብል ይቀለኛል።››
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በተመለከተም ‹‹ውብ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፤ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮት ውብ ነው። ነገር ግን በዓለም ላይ ብዙም አልታወቀም። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት የተጻፉት በሀገር ውስጥ ቋንቋ፡ በተለይም በግእዝ ነው እንጂ በውጪ ቋንቋዎች አይደለም። ግእዝ በተለይም ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ የመነጋገሪያ ቋንቋ አልነበረም። ብዙ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት የሚገኙት ግን አሁንም በግእዝ ነው። ባሕሉ ራሱ የግእዝ ባሕል ነው።››
በቅድስት ሥላሴ በሚያስተምሩበት ጊዜ በኮሌጁ ማኅበረሰብ ‹‹ፋዘር ጆሲ›› በሚል አጠራር የሚታወቁት እኚህ መምህር በሀገራችን ስላለው ወቅታዊ አለመረጋጋትም ሲገልጹ ሕዝቡ በጣም ሰላማዊ እንደ ሆነና ችግሮችን እየፈጠሩ ያሉት አንድን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ጽንፈኞች እንደ ሆኑም አብራርተዋል።
ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በምን ዓይነት መሪዎችና የአመራር ስልት እንደ ቆየች በጥቂቱ የገለጹት ዶክተር ጆሲ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በማቆሙና በመጠበቁ ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልነበርም አጽንዖት ሰጥተው መስክረዋል።
ሆኖም አሁን በሀገሪቱ ያሉ ጽንፈኞች ቤተ ክርስቲያንን አብዝተው መክሰሳቸውና ከብሔር ጋር ማያያዛቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ዋነኛ ተጠቂ እንዳደረጋትም አስረድተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠልና የኦርቶዶክሳውያን መሠዋትም የጥቂት ጽንፈኞች የተሳሳተ የስብከት ፍረጃ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።
‹‹ቤተ ክርስቲያን ኩላዊት ናት እንጂ የአንድ ብሔር ብቻ አይደለችም›› ካሉ በኋላም ‹‹እባካችሁ ቤተ ክርስቲያን የኹሉም ናትና ከአንድ ብሔር ጋር ብቻ አታያይዟት›› ሲሉም መክረዋል።
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1300
በ፳፻፲፫ ዓ.ም በዓለ መስቀል ተከብሮ የዋለው በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት ሰማዕትነትን የተቀበሉ ምእመናን በእንዴት ዓይነት መከራ እንዳለፉ በተግባር ባየንበት ሁኔታ ነው። መከራ መስቀሉ የሚታሰበው በልቅሶ፣ በመከራ፣ በኀዘን፣ በመሳደድ መሆኑን በዐይናችን አይተናል፤ በጆሯችን ሰምተናል። መንግሥት ባለበት ሀገር ክርስቲያኖች በዓለ መስቀልን በኀዘን እንዲያሳልፉ ማድረግ “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ” የተባለውን በተግባር ተተግብሮ አይተነዋል። ይህ ድርጊት የቤተ ክርስቲያንን ክብር የበለጠ የሚገልጥ ቢሆንም ሃይማኖትን ተገን አድርገው ግፍ ለሚፈጽሙ ግን በአባቶቻችን ዘመን የዓላውያን ነገሥታትና መኳንንትን የግፍ አገዳደል ዳግም እያሳየን ነው።
በክርስቲያኖች ላይ ገሀድ የወጣ አድልዎ ተፈጽሞባቸው ሲያለቅሱ መዋላቸው መንግሥትን ትዝብት ላይ የሚጥል ሲሆን በሌላ በኩል ዘመን ሰጠን ብለው ከልክ የሚያልፉ አካላት ከማይችሉት አምላክ ጋር እየተገዳደሩ፣ ሞታቸውን እያፋጠኑ መሆኑን እንድንረዳ የሚያደርግ እኩይ ድርጊት ነው። ቤተ ክርስቲያንን ምክንያት እየፈለጉ መግፋት ለ፳፻ ዘመናት የዘለቀ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሀገራችን ተከሥቶ ማየታችን እጅግ የሚያሳዝን ነው። በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን መከራ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር ከመማጸን በተጨማሪ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅን ተግባር መፈጸም ይገባል። በሃይማኖታችን ምክንያት መንግሥታዊ ጥቃት ሲፈጸምብን ከክርስቲያኖች የሚጠበቀው ቢያንስ ሁለት ወይም ሦስት ተግባራትን መፈጸም ነው።
የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያናችን “የሰማዕትነትን ክብር ይሰጠን ዘንድ ስለ ሰማዕታት እንማልዳለን” በማለት ዕለት ዕለት የምትጸልየውን ሰምቶ ለክብር እንዲያበቃን አምላካችንን መማጸን ነው። ሁለተኛው እጃችንን አጣጥፈን፣ አንድ ቦታ ተቀምጠን እስከምናልቅ ከመጠበቅ በክርስትና ሃይማኖታችን የሚተኩትን እግዚአብሔር እንዲያበዛቸው ሐዋርያዊ አገልግሎታችንን ማጠናከር ነው። ይህም በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ የሮማ ክርስቲያኖች ከሞት የተረፉበትን መንፈሳዊ ጥበብ መተግበርን ያካትታል። የሮማ ክርስቲያኖች ከሞት የተረፉት ከብረት የጠነከረ አንድነት የነበራቸው በመሆኑ ጭምር እንደነበር መረዳት ይገባል። እርስ በርስ እየተተቻቸንና መልካም ሥራ ለሚሠሩት የማሰናከያ ድንጋይ እየሆንን ይህንን የመከራ ዘመን እንደማናልፈው መረዳት ይኖርብናል። በመለያየትና በመተቻቸታችን ለጠላት የተመቸን እንሆናለን እንጂ ለራሳችንም ለቤተ ክርስቲያንም ስለማንጠቅም የመጥፊያ መንገዳችንን እንዳናዘጋጅ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
ላለፉት አርባና ኀምሳ ዓመታት ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ከኢትዮጵያ አጥፍቶ ታሪክ ለማድረግ በዕቅድ ሲሠራበት የኖረውን እኩይ ድርጊት በማልቀስና በማኅበራዊ ሚዲያ በመንጫጫት ብቻ ማስቆም እንደማንችልም መረዳት ያስፈልጋል። የቅዝምዝሙን አመጣጥ አይቶ ጎንበስ ብሎ ለማሳለፍ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ክርስቲያናዊ ፈሊጦችን በመጠቀም ዘመኑን መዋጀት የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች የቤት ሥራ መሆኑን መረዳትም ያስፈልጋል። በመናገርና ለዓለም ማኅበረሰብ በማሳወቅ ብቻም በዕቅድ የሚፈጸመውን የጠላትን ጥቃት ማስቆም አይቻልም። ክርስቲያኖችን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እኩይ ዓላማ ይዞ እያሠለጠነ ለሚያስፈጀን አካል ጥያቄ ማቅረብ ንብረታችንን ከሰረቀ ሰው ጋር ፍለጋ መውጣት ነው።
በዚህ ዘመን በሌሎች መሥዋዕትነት ለክርስቲያኖች መልካም ዘመን ይመጣላቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት በመሆኑም ከስሜታዊነት ርቀን በአስተዋይነት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ መሥራት ይኖርብናል። ከአባቶቻችን የተቀበልናት መክሊት (ክርስትናችን) በእኛ ዘመን እንዳትቀበር እግዚአብሔርን ይዘን የምንችለውን ሁሉ ለመፈጸም መዘጋጀት ታላቅነት ነው። ዘመኑ ክፉ በመሆኑ ወደ ፊትም በዓለ መስቀልን ስናከብር እንደዚህ ዓይነቱ መከራ እንደሚጠብቀን እያሰብን መዘጋጀት እንጂ በክፉ ወሬ መፈታት ተሸናፊነት ነው።
ፀረ ኦርቶዶክስ የሆኑ የዞንና የከተማ ባለሥልጣናት ኦርቶዶክሳውያን መስቀልንና ጥምቀትን እንዳያከብሩ ሲከለክሉ ቆይተዋል። ዘንድሮም በዓሉ ሳምንት ሲቀረው ልማደኞቹ የሆሣዕና ባለሥልጣናት ወገኖቻችን በዓለ መስቀልን እንዳያከብሩ ከልክለዋል። አንድ ቦታ እየከለከሉ ሌላ ቦታ እየፈቀዱ ያሉትን ባለሥልጣናት ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እኩል ማገልገል እስከምትጀምሩ ሰላማዊ ትግላችንን አናቋርጥም ልንላቸው ይገባል።
እነዚህ ሰዎች መደበቂያቸው ሃይማኖት ወይም ጎሳ ነው። ዓላማቸው ባይሳካ እንኳ ሕዝብ ጎራ ለይቶ ደም ሲፋሰስ በሰው ኀዘን የሚደሰቱ ብዙ ከንቱ ሰዎች ስላሉ እነርሱ በሄዱበት መንገድ መጓዝ ሽንፈት መሆኑን ዐውቀን በመንፈስ ልዕልና ላይ በመቆም ማሸነፍ ይገባል። ሀገርን በሥራ ከመለወጥ ይልቅ ተንኮል በመሸረብ ውለው የሚያድሩ ሰዎች ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው እንዳይጠየቁ በማዘናጋት ችግር እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
ባለሥልጣናቱ ይህን የሚፈጽሙት ሕዝብን ሁሉ እኩል ሊያገለግሉ የተቀበሉትን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የእኛ ለሚሉት ሃይማኖት በማድላት ነው። የሆሣዕና ከተማ ክርስቲያኖች ፍትሕ ማጣት የመላው ሕዝበ ክርስቲያን ፍትሕ ማጣት መሆኑን መረዳት ነበረባቸው። እነዚህ ባለሥልጣናት ራሳቸውን ከሕግ በላይ ማድረጋቸው በመላ ሀገሪቱ የምንገኝ ኦርቶዶክሳውያን እንድንተባበር ያደርገናል እንጂ አያለያየንም።
መፍትሔውም መንግሥት የሕግ የበላይነትን አስከብሮ ጉዳት ደርሶባቸው ሜዳ ላይ ተበትነው የሚገኙትን፣ በየቤተ ክርስቲያኑና በየግለሰቦች ቤት ተጠልለው ያሉትን ክርስቲያኖች ሰብስቦ ወደቀያቸው መመለስ በቀደመው ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲኖሩ ማድረግ፣ በቀጣይም እንዲህ ያለ ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከልና መጠበቅ ይገባል። ይህንም ሁሉ መከራ ለመከላከል ሰላማዊና ቤተ ክርስቲያን በምትፈቅደው መሠረት እየታገሉ በትዕግሥት ማለፍንም የዕለት ተለት ተግባራችን ማድረግ ይኖርብናል። በሃይማኖት ጸንተን የምንቀበለው መከራ መስቀልም ሰማዕትነትን በተግባር መፈጸም ነውና መሳቀቅ የለብንም።
- Details
- Written by: ዲ/ን ተስፋዬ አሰፋ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2396
ይህን ቃል የተናገረው ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል ነው። ሕዝቅኤል ማለት ጽኑዕ፣ ጽንዐ እግዚአብሔር ማለት ነው። ቃሉን የተናገረውም በኢኮንያን ተማርኮ ባቢሎን ከሕዝቡ ጋር በወረደበት ጊዜ ነው። በዚህ ርእስ ሊተላለፍ የተፈለገው የፈረሰችው ኢየሩሳሌም ለጣዖት ሰገደች፤ ሌባ፣ ቀማኛ በዛብሽ፤ ልጆችሽ ወላጆቻቸውን የማያከብሩ ሆነዋል፤ የንጹሓንን ደም አፈሰስሽ፤ እንደ ነዌ ዝናመ ምሕረት የማዘንብባት የነበረሽው ኀጢአትሽ ከሰዶም በልጧልና ዳግማዊት ሰዶም ተባልሽ፤ ካህናቶችሽ ሕጌን ጣሱ፣ ቤተ መቅደሴን አረከሱ፤ እናም አምባውን አጽንቶ በፊቴ የሚቆም አርበኛ ሰው ከመካከላችሁ ፈለግሁ። ይኸውም እንደ ሙሴ እስራኤልን በንስሓ አድሶ፣ በረድኤት ተካሶ ለማማለድ በፊቴ የሚቆም ጻድቅ ሰው ፈለግሁ። ሕዝቡም ወንበዴዎች ቀማኖች ሆኑ ይህ ሁሉ ሆነ፤ የፈረሰውን ቅጽር የሚሠራ፣ በፈረሰበት በኩል የሚቆምላትን ሰው እፈልጋለሁ አለ እግዚአብሔር። ዛሬም እግዚአብሔር ሰው ይፈልጋል። በዚህ ርእስ ውስጥ አስፈላጊ የሆነ ጻድቅ ሰው እናያለን ስሙም ነህምያ ይባላል። (ሕዝ.፳፪፥፴ አንድምታ)
ኢየሩሳሌም በጠላቶቿ ፈርሳ፣ ቋያ በቅሎባት እና አራዊት ሰፍሮባት በተበተነችበት ዘመን ቅጥሯን ሊሠራ የበረታው ነህምያ ነበር። ለመኾኑ ኢየሩሳሌም የተባለች ማን ነች? የፈረሰ ግንቡዋ ምንድን ነው? እኔ እና እናንተ የፈረሰውን ግንብ ለመሥራት ምን እና በየት በኩል እንድንቆምላት ትፈልጋለች? ምን ልናደርግላት ያስፈልጋል? ኢየሩሳሌም የተባለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በብዙ ጉዳዮች ፈርሳለች። ለመሆኑ ነህምያ የተባልን እኛ ምእመናን የጸናች ግንብ የተባለች ቤተ ክርስቲያን በፈረሰበት በኩል እንድንቆምላት ምን መረዳት ያስፈልገናል?
፩. በፈረሰበት በኩል ለመቆም የሀገርን ፖለቲካዊ አዝማሚያ ተረድተናል?
ነህምያ በቤተ መንግሥት በመጋቢነት የሚያገለግል፣ አምላኩን የሚፈራ፣ ለቤቱ የሚቀና ምእመን ነበር። በሱሳ ግንብ ተቀምጦ ከዚህ በፊት የፈረሰች ኢየሩሳሌምን መፍረስ በሰማ ጊዜ «በሮችዋ ተቃጥለዋል አሉኝ ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስኩ፤ አያሌ ቀንም አዝን ነበር» እንዳለ የቤተ ክርቲያንን ቀዳዳ ለመሸፈን በፈረሰበት በኩል ለመቆም ካህን አልያም ባለሥልጣን እንዳልነበረ ሁሉ ለሀገርህ እና ለቤተ ክርስቲያን ዘር፣ ቀለም፣ ጎጥ፣ ሀገር፣ ልጅ፣ ወንዝ፣ ሳንል «እኛ ሀገራችን በሰማይ ነውና ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን» እንደተባለ ወገናችን እግዚአብሔር፣ ወገንተኛነታችን ለቤተ ክርስቲያን መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል። (ነህ.፩፥፬፤ ፊል.ጵ ፫፥፳)
ዛሬ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዱ ምእመን ነህምያ ነው። ለቤተ ክርስቲያን ራእይ ያለው፣ በአንድነት የሚያምን የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን የወደቁ የተቃጠሉ የመቅደስ በሮች ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በኅብረት የፖለቲካ እና የዘር ሽኩቻውን ትቶ ከነገዱ እና ከዘሩ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን መቅደሱ የምትበልጥበት፣ በፈረሰበት በኩል የሚቆም ነህምያ ቤተ ክርስቲያን ትሻለች። እኛስ ነህምያ ነን? እርሱ የፈረሰው ግንቡ ብቻ አይደለም፣ የፈረሰው ሥነ ልቦናችንም ነው ብሎ በማመኑ ፶፪ ቀናት ሙሉ ጠላት ግንቡን ሊያፈርስ ቢመጣ እንዴት መጠበቅ፣ እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው በቃለ እግዚአብሔር ሠርቷቸዋል። «የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ» እንዳለ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ደጀን ለመኾን እንጨክን። (ነህ. ፬፥፮) ከዚህ ባለፈ አንድ ምእመን ካልጾመ፣ ካልጸለየ፣ ቅዳሴ ካላስቀደሰ፣ ቃለ እግዚአብሔር ካልሰማ፣ ገድላቱን፣ ተአምራቱን ካላዳመጠ፣ እንዴት የጸና ግንብ ነው ማለትስ ይቻላል? «መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» ተብሎ ግንቡ ከፈረሰ ምኑን ጠባቂ ሆንን? (፩ጴጥ. ፪፥፭)
፪. በፈረሰው በኩል ለመቆም በቤተ ክርስቲያን አንድነት እናምናለን?
የወንድሞቹን ሥቃይ የየትኛውም ሀገር ሰው ይሁን እንደ ሰው ማሰብ ጤነኛ እሳቤ ነው። ከቢሮ ሥራችን፣ ከፖለቲካ ድርጅታችን በላይ በነፃ አእምሮ ከማንም ተጽዕኖ ውጭ የተጎዳው ወንድምህን ለመታደግ እተጋለን? ይህን የምናደርገው ለእግዚአብሔር ደስታ እንጂ ጀግና እንድንባል፣ የሆነ አካልን ለማስደሰት አይሁን። ብዙ ጊዜ ሰዎች ስለመደሰታቸው እንጂ እግዚአብሔር በእኛ ስለመደሰቱ ማሰብ ይሳነናል። የእግዚአብሔር ደስታ የበደለ ሲክስ፣ ያጠፋ ሲመለስ፣ በንስሓ ሲታደስ ነው። «ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል» እንደተባለ በፈጠራ ታሪኮች ተወስደን ከአጥፊዎች ጋር እንዳንተባበር። (ሉቃ. ፲፰፥፲፭)
ቤተ ክርስቲያን አንዱ ባሕርይዋ «አንዲት» የሚል ነው። በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በሐዋርያነ አበው የተሰበከች ያለ ምንም ደም መፍሰስ ባኮስ ኢትዮጵያዊ የሰበካት ቅዱስ ፍሬምናጦስ ያስተዋወቃት፣ ተስዐቱ ቅዱሳን ያስፋፉዋት ነች። ሀገርን ከእነሙሉ ክብሩ በአንድነት የጠበቀች ናትና ይቺን አንድነት መጠበቅ አለመጠበቃችንን መፈተሽ አለብን።
፫. በፈረሰው በኩል ለመቆም ፈተና የማይለውጠን ነን?
ሰንባላጥ እና ሞዓባዊው ጦቢያ ነህምያን እንደፈተኑት በብዙ ሰዎች እንፈተናለን። ሴራ ይሸርቡብናል፤ የሥነ ልቦና ጦርነት ውስጥ እንወድቃለህ። እንደ ነህምያ ስማችንን ያጠፉትም ይሆናል። ያለንን ነገር ልናጣ እንችላለን። በዚህ ጊዜ ከነቢዩ ዕንባቆም ጋር እንዲህ እንበል «ምንም እንኳ በለስ ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጎድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረት ቢጠፉ፥ ላሞች በጋጥ ባይገኙ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለሁ» (ዕን.፫፥፲፯) ስንቶቻችን ነን ፈተና የቀየረን? በሚታየው እና በሚሰማው ነገር የተቀየርን? ሞራ ያስገለጥን፣ ስኒ ያስገለበጥን? በፈረሰበት በኩል መቆም አቅቶን ራሳችን የፈረስን ብዙ ነን። ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ዘራችን፣ ከመቅደሱ ይልቅ ስማችን ከበለጠብን እውነትም ፈተና ከለወጣቸው ሰዎች ተራ ቆመናል። ነህምያ የፋርስ ነገሥታትን ልብ ያንበረከከው በእምነቱ ጥንካሬ ነው። እኛስ?
፬. በፈረሰበት ለመቆም ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን እንጸልያለን?
የነህምያ ተግባር የተጀመረው በጾም እና በጸሎት ነው። እንዲህ ነበር ያለው «የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈርሶአል በሮችዋም ተቃጥለዋል አሉኝ። ይህን በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ አያሌ ቀንም አዝን ነበረ በሰማይም አምላክ ፊት እጾም እና እጸልይ ነበር» (ነህ.፩፥፫-፬) ስለዚህ ስለ ሀገር አለመጸለይ፣ ስለራስ አለመጸለይ ነው። ወልዶ መሳም፣ ዘርቶ መቃም የሚቻለው ቤተ ክርስቲያን ፣ ሀገር ስትኖር ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ «አቤቱ ማረን አንተን ተማምነናል ጠዋት፥ ጠዋት ክንድ በመከራ ጊዜም ማዳን ሁነን» ብሎ እንደጸለየ እያሉ ዳዋ ጥሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምፀ አራዊቱን፣ ግርማ ሌሊቱን ታግሰው፣ በበዓት ተወስነው የላመ፥ የጣመ ሳይበሉ ስለ ሀገር የሚጸልዩ አበው ያሉባት ሀገር ናትና በማኅበራዊ ሚዲያው በአጸያፊ ቃላት ከመታኮስ ሰብሰብ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።
ምን እናድርግ?
፩. ግንቧ የፈረሰባት የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናትና ሳንታክት የፈረሰውን እንጠግን
የምእመናን ኅብረት እንዳይፈርስ፣ ጉባኤያት እንዳይበተኑ፣ አብነት ተማሪው ነገን እንዲረከብ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈረሰው በኩል ቁሙልኝ ትላለች። ሕፃናት ሃይማኖታቸውን እንዲያውቁ አዕማድ የተባሉ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቍርባን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን እንዲማሩ የወላጅነት ድርሻህን ተወጣ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «ስለዚህ አንታክትም ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ይታደሳል» እንዳለ (፪ቆሮ. ፬፥፲፮)
ብዙዎቻችን ለአውሮፓዊ አእምሮ ስለተማረክን፣ ለሚታየው እና ለጠፊው ዓለም ስለተገዛን፣ ከቤታችን ይልቅ በጠርሙስ ብርጭቆ ውስጥ፣ በአልባሌ ተራ ቦታ መደበቅ ስለምንሻ ፈርሰናል። የፈረሰው ውስጣችን የሚታደሰው በቅዳሴው፣ በኪዳኑ፣ በማኅሌቱ ነው። ክርስትና መሓሪውን አምላክ የምናመልክበት ሃይማኖት ነው። ፈርሰናል ስንል በንስሓ የምንመለስበት፣ ከተኛንበት አዚም የምንቀሰቀስበት መንገድ ሰፊ ነው። «አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሀል» እንዲል መጽሐፍ። (ኤፌ. ፭፥፲፬)
፪. ግንብ የተባለች ቤተ ክርስቲያን በእጁ ተቀርጻለችና እንሳለማት
ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህቺውም በመልዕልተ መስቀል ላይ በደም ዓላባ በተመቱ፣ በችንካር በተቸነከሩ በእጆቹ ትርትራት መሃል የተቀረጸች፣ የተሳለች ናት። ምድራውያኑን ከሰማያዊው ዓለም የምታገናኝ ድልድይ ነች። በዐጸደ ነፍስ ያሉት ቅዱሳኑ በዐጸደ ሥጋ ካለን ከእኛ ጋር ኅብረት የሚፈጥሩባት የእግዚአብሔር ንድፍ ዲዛይን ናት። አሁን፣ አሁን የሥርዓት ድንበር እያፈረስን ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን ደጋግመን ስናደርግ አይስተዋልም። ቅዱሳት ሥዕላትን፣ በሩን፣ ጉበኑን፣ መሬቱን ስንሳለም በእምነት ስለሚደረግልን ነገር ማሰብ ስለሚያቅተን በጥርጥራችን ደጁን ተዳፍረነዋል። «ወደ ማደርያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን» መባሉን እንረሳዋለን። አንዳንድ ጊዜ መጥፎ አርአያ የሚሆኑ ሰዎችን አርአያ ከማድረግም ይመነጫል። ወደ ቤተክርስቲያን ስንገባ በልባችንም፣ በአካላችንም ጉልበትን በማስነካት መስገድ ያስፈልጋል። ሌላኛው የፈረሰንበት ሐሳብ በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በእርሷ አምሳል ውስጥ በጎጥኛ በሀገር ልጅ ተካፍለን መባላታችን ነው የሚያስገርመው። ቢሆንልንማ መንግሥተ ሰማያት የእኛ ዘር ወገን ብቻ እንዲገባልን የምንፈልግ ሳይሆን አይቀርም። ሠዓሊ ቀለማትን ተጠቅሞ በቡርሽ ሥዕልን እንደሚሥል የቅድስት ሥላሴ አርአያ እና አምሳል በነፍሳችን ተሥሎብን እያለ ስለምን ነፍሳችንን በዘረኝነት አሳመምናት? «እኔ ቅጥር ነኝ» እንዳለ የነፍሳችን ቅጥር ጠባቂ ቅድስት ሥላሴ ከሣሉብን ተሥዕሎተ መልክእ አንውጣ። መኃ. ፰፥፲
፫. ግንብ የተባለች ቤተ ክርስቲያን ጠላትን ማምለጫ ምሽግ ናትና እንጠለልባት
ግንብ፣ ምሽግ ፣ መደበቂያ ጠላትን ማጥቂያና መዳኛ ነው። «የጸናች ከተማ አለችን ለቅጥር እና ለምሽግ መድኃኒትን ያኖርባታል» እንደተባለ (ኢሳ. ፳፮፥፩) ። ዲያብሎስን ከእነሠራዊቱ የምትጥል ናት። ሌሊቱን ሙሉ እንደ መላእክት ማኅሌት የሚቆሙ ካህናት ማደሪያ ናት ተጠለልባት። ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ እያለች የምትጸልይ፣ ብራና ፍቃ፣ ቀለም በጥብጣ የድንቁርናን ጨለማ የገለጠች ከማንም በፊት ፋና ወጊ እናት ናት ተጠለልባት። ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የሰጠችህ፣ የዳረችህ፣ የሸለመችህ፣ ወንጌል ግታ ያሳደገችህ፣ በሞት ስትያዝ ሰው ሁሉ ሲጸየፍህ ፍትሐት ፈትታ፣ በጸሎት በዕጣን አክብራ፣ አጸያፊ ሽታህን በጉያዋ ታቅፋ የምትቀበልህ ናትና ተጠለልባት። ጠባቂዋ የማይተኛ «እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ በውስጧም ክብርን እሆናለሁ» ያላት ለምን ትፍረስ? ለምን ትጎዳ? (ት.ዘካ ፪፥፭)
፬. ግንብ የተባለች ቤተ ክርስቲያን መስፈርቷ ሰማያዊ ነውና አንጠራጠራት
ሰማያዊ ኩነቶች መለኪያቸው ሰማያዊ መስፈርቱም ሰማያዊ ነው። ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ «ከእኔም ጋር የሚነጋገረው ከተማይቱንና በሮቿን ቅጽሮቿንም የሚለካበትን የወርቅ ዘንግ ይዟል። ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበረች፤ ርዝመቷም እንደ ስፋቷ ልክ ነበረ፤ ከተማይቱንም በዘንግ ለካት ዐሥራ ሁለት ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመቷና ስፋቷ፣ ከፍታዋም ትክክል ነው። ከዚህም በኋላ ቅጽርዋን ለካ፤ በሰው ክንድ መቶ አርባ አራት ነው፤ ይህውም በመልአኩ ክንድ አንድ ክንድ ነው» ብሏል። ራእ. ፳፩፥፲፭-፲፰
ይህች ርዝመቷ፣ ስፋቷ፣ ከፍታዋ ትክክል ነበር ያላት ቤተ ክርስቲያን ነች። ያስቀመጠችውን ቀኖና ትክክል መሆኑን ለሚጠይቁህ ንገራቸው። ዶግማዋ፣ ሥርዓቷ፣ ቀኖናዋ ለረጅም ዘመናት የተሻገረ ስለመሆኑ አስተምር ፤ ዝም አትበል። አንተም ጠበሉን፣ ውኃ፥ እምነቱን አፈር ማለት ከጀመርህ የፈረሰ ነገር አለ ማለት ነው። ጠበል መስፈርቱ፥ መለኪያው ሰማያዊ ስለኾነ ሲፈውስ፥ ሲቀድስ ትመለከታለህ፤ ውኃ ይህን ማድረግ አይችልም በራሱ የተለየ የማዳን ኃይል አልተላበሰም። ለምሳሌ አንድ ቁስ በቤተ ሙከራ ሲለካ የራሱ ውጤት አለው እንበልና ፍቅርን በቤተ ሙከራ መለካት ብንፈለግ መለኪያ መስፈርቱ ከዚህ ስለሚለይ እና በዚህ ስለማይለካ ውጤት አናገኝም። ስለዚህም ከጠበል ይልቅ ሆስፒታል መመላለስ ይቀለናል። ብዙ ጊዜ ለእኛ ቤተ እግዚአብሔር የመጨረሻ አማራጭ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔርን የመጀመሪያ አማራጭ ለማድረግ አትጠራጠር።
ማጠቃለያ
ነህምያ የተባለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነህምያ የጸሎት ሰው ነበር። (ነህ. ፩፥፬) አማናዊ ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎትን ያስተማረ ጸሎታችንን የሚሰማ አምላክ ነው። (ማር. ፩፥፴፭) ነህምያ ከሰንባላጥ እና አሞናዊው ጦብያ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። (ነህ. ፭፥፬) አማናዊው ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአይሁድ፣ ከጸሐፍት ፈሪሳውያን ተቃውሞ ደርሶበታል። ማቴ. ፲፪፥፲፬) ነህምያ መቅደሱን አጽድቶ ለአገልግሎት ምቹ እንዳደረገ (ነህ. ፲፫፥፯-፱) አማናዊው ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስም በመቅደስ ውስጥ የነበሩ ነጋዴዎችን በጅራፍ ገርፎ አስወጥቷል። (ማር. ፲፩፥፲፭-፲፱) ነህምያ ግብዞችን ገሥጿል። (ነህ. ፲፫፥፲፭) አማናዊው ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዝ የነበሩ አይሁድን በቃሉ ገሥጿል። ማቴ.፳፫ ፥፲፫) ነህምያ የፈረሰች ኢየሩሳሌምን ገንብቷል፤ አማናዊው ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስ ቋያ በቅሎብን የመዳን በራችን ተዘግቶብን፣ ግንባችን ተደርምሶ የነበርን የሰው ልጆች ከሲኦል ሞት ከባርነት ቀንበር ነፃ አውጥቶናል። እኛም እንደ ነህምያ በፈረሰው በኩል ቆመን የሚጠበቅብንን መልካም ሥራ ሠርተን በሃይማኖት ጸንተን የመንግሥቱ ወራሾች የስሙ ቀዳሾች እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2257
የሰው ልጅ ጥንት አታድርግ የተባለውን ሲያደርግ፣ አትብላ የተባለውን ሲበላ የተሰጠውን ተነጠቀ፤ ልጅነቱን፣ ገዥነቱን፣ ክብሩን ወዘተ አጣ። ይሁን እንጂ በተሰጠው አእምሮ ተጠቅሞ በሠራው ስሕተት ተጸጸተ፤ የበደለውን አምላኩን ይቅር በለኝ በማለት አነባ። የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሣ አምላክ ጽኑዕ የሆነ ቃል ኪዳን ሰጠውና የተወሰደችበትን ልጅነት በዚህም ምክንያት ያጣትን ርስት፣ እንደሚያገኝ ጸኑዕ ተስፋን ሰንቆ በተፈቀደለት ምድር መኖር ጀመረ። ዛሬም ቢሆን ሰው አእምሮውን ጨርሶ ካላጣ በቀር ባለተስፋ ነው። ምን አልባት ተስፋ የሚያደርገው ነገር ይለያይ እንደሆነ እንጂ በውስጡ ተስፋውን ሰንቆ የማይጓዝ የለም።
አንዳንዱ ሥራውን ተስፋ ያደርጋል፤ አንዳንዱ ትምህርቱን ተስፋ ያደርጋል፤ አንዳንዱ ሀብቱን ተስፋ ያደርጋል። ይህ ሁሉ ግን የሚያዋጣ አይደለም። ምክንያቱም አንድ ቀን ያልፋልና፤ ጭንቅ ሲመጣ ከመጣው መከራ አያድንም ራሱም አይድንም። ክርስትናውን በአግባቡ የተረዳው ደግሞ ፈጣሪውን ተስፋ ያደርጋል። ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ “ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።” (ሰቆ. ኤር. ፫፥፳፮) እንዲል። ስለዚህ ሰዎች እግዚአብሔር አምላካቸውን በማመን ማዳኑን ፣ ጥበቃውን፣ መግቦቱን፣ ይልቁንም ለሰው ልጅ ያለውን ጽኑዕ ፍቅር በማሰብ ተስፋ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በዚህ ርእሰ ጉዳይ የተስፋን ምንነት፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ፣ በተስፋ ብንኖር የምናገኛቸውን ነገሮችና መሰል ጉዳዮችን እንመለከታለን።
ተስፋ ምንድን ነው?
ተስፋ ወደፊት እንዲሆንልን፣ እንዲደረግልን፣ እንዲሰጠን የምንፈልገውን ነገር ይሆንልኛል፤ ይሰጠኛል፤ ይደረግልኛል ብሎ ማመን ነው። ይህንንም አስመልተው ደስታ ተክለ ወልድ ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በተሰኘ መጽሐፋቸው “ተስፋ፡- አለኝታ፣ ወደፊት አገኛለሁ የማለት ጽኑዕ እምነት” (ገጽ ፲፪፻፸፬) በማለት ይገልጹታል። ስለሆነም እንደ እርሳቸው አገላለጽ ተስፋ ማለት የወደፊት ምኞት፣ አገኛለሁ፣ ይሆንልኛል፣ ይደረግልኛል የሚል ጽኑዕ እምነት እንደሆነ ነው።
ተስፋ በክርስትና ሕይወት መሠረታዊው ጉዳይ ነው፡፡ ሰው በሚያየውና በሚጨብጠው ነገር ቢተማመን ምንም የሚያስደንቅ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን በሥጋዊ ዐይን የማያዩትን፣ በሥጋዊ እጅ የማይዳስሱትንና የማይጨብጡትን አምላክ “የፈለግሁትን ይሰጠኛል፤ የሚጠቅመኝን ያደርግልኛል ለምኘው አያሳፍረኝም” ብሎ ማመን እጅግ የሚደንቅ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም በሃይማኖት ስንኖር ዋናው እና ትልቁ መሣሪያችን ተስፋ ነው፡፡ ሃይማኖት ፈጣሬ ሰማያት ወምድር የሆነውን እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ነው የተባለውም ለዚህም ነው፡፡
ተስፋ የሚታየውን በማይታየው ይቀይራል፡፡ አብርሃም በሽምግልና ዘመኑ ያገኘውን አንድ ልጁን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በዐይነ ሥጋ ሳይሆን በዐይነ ኅሊና የሚታይ የተሻለ ጥቅም ስለነበረው ነው፡፡ በመጽሐፍ ‹‹አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ በእምነት ወሰደው፡፡ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ብሎ ተስፋ ያደረገለትን አንድ ልጁን አቀረበው፡፡ እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኗልና፤ ስለዚህም ያው የተሰጠው መታሰቢያ ሆነለት›› (ዕብ.፲፩፥፲፯-፲፱፤ ዘፍ.፲፪፥፩) ተብሎ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡ አብርሃም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በተስፋም ከሚያውቀው ሀገር፣ ከሚያውቀው ሕዝብ ወጥቶ ወደማያውቀው ሀገር፣ ወደማያውቀው ሕዝብ ሄደ።
በሰው ሰውኛው ሲታይ አብርሃም የፈጸመው ትክክል አይደለም ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም ‹‹በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል›› እየተባለ ያንኑ የዘሩ መጠሪያ የሆነውን ሠዋ ሲባል ‹እሺ› ብሎ መሄድ ምን ያህል እምነትና ጽኑዕ ተስፋ እንዳለው የሚያስረዳ ነው፡፡ አብርሃም አንድ ልጁን ለእግዚአብሔር አልከለከለውም፤ እንዲሁ እግዚአብሔርም አንድያ ልጁን ለአብርሃም አልከለከለውም፡፡ እንኳን ለአብርሃም በእምነት ለታዘዘው፣ የሚታየውን በማይታየው ለውጦ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ ከሀገሩ ለወጣው ይቅርና ለጠላቶቹ እንኳን አልከለከላቸውም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት በእንደዚህ ያለ ጽኑዕ ተስፋ ያኖራል፤ በተስፋ መኖር ብቻም ሳይሆን ከክፉ ሁሉ ያለ ድንጋጤ ያሳርፋል። ስለሆነም “ተስፋ አያሳፍርም” በማለት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ የገለጸውን ልብ ማለትና በልቡና ሠሌዳ ማተም ያስፈልጋል።
ተስፋ በምቾት ጊዜ፣ ምንም መከራና ፈተና በሌለበት ወቅት ሳይሆን በሰው ሰውኛው አይቻልም በሚባልበት የጭንቅና የመከራ ዘመን ሊታጠቁት የሚገባ ረቂቅ መንሣሪያ ነው።
ተስፋ መቁረጥ ከምን ሊመጣ ይችላል?
ሰዎች ሥጋዊ ፍላጎት በሚያይልበት ዓለም፣ የክፋት፣ የተንኮል፣ የኃጢአት ወሬ በሚሰማበት ዓለም እየኖሩ የዚህ ችግር ሰለባ ሳይሆኑ በሃይማኖት ጸንተው በጎ ምግባር ሠርተው መኖር ባለመቻላቸው ተስፋ ይቆርጣሉ። ተስፋ የሚቆርጡባቸው ምክንያቶች ደግሞ በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ክፍል ግን የተወሱትን ብቻ እንመለከታለን።
፩. የእግዚአብሔርን ቃል አለመስማት
እግዚአብሔር አስቀድሞ መስማት እንድንችል ጆሮ፣ እንድናስተውል አእምሮ፣ የሰማነውን ደግሞ በተግባር ማዋል የሚያስችል አቅም ፈጥሮልናል። መቼም ቢሆን እኛ የማንችለውን አላዘዘንም፤ አያዘንምም። ነገር ግን የምንችለውን ባለማድረጋችን ሁሌም ስንጎዳ እንኖራለን። አዳም የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማት ተጎዳ፤ በርካታ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማት ተጎዱ፣ ሰብአ ትካትን፣ ሰብአ ሰዶምን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በአንጻሩ የእግዚአብሔርን ቃል የሰሙት የነነዌ ሰዎች ደግሞ ከመጣባቸው መዓት ድነዋል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ማለት አድርጉ የተባልነውን ማድረግ፣ አታድርጉ የተባልነውን ደግሞ አለማድረግ ነው፤ ቃሉ ሕይወት ነውና። ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹ንዜንወክሙ በእንተ ውእቱ ዘሀሎ እምቅድም ውእቱ ዘሰማዕናሁ በዕዘኒነ ወዘርኢናሁ በአዕይንቲነ ወዘጠየቅናሁ ወዘገሠሣሁ እደዊነ በእንተ ነገረ ሕይወት፤ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና በጆሯችን የሰማነውን በዓይናችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን›› በማለት ስሙት የተባልነው ቃል የሕይወት ቃል እንደሆነ ጽፎልናል፡፡ (፩ዮሐ.፩፥፩)
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በጾመ ድጓ ድርሰቱ ‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘያሐዩ በቃሉ፤ ከላይ ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤ በቃሉ የሚያድነውን የሁሉ ጌታ ምንም አላወቁትም›› (ጾመ ድጓ፣ ዘዘወረደ) በማለት ስሙት የተባልነው ቃል መድኃኒት መሆኑን፤ መድኃኒት የሆነው ቃል ደግሞ በቦታ የማይወሰን አምላክ ሲሆን ልዕልናውን ለመግለጽ ከላይ የወረደውን ተብሎ የተነገረለት የሕይወት ቃል መሆኑን ያስረዳናል። ይህን ከላይ የወረደውን አምላክ አይሁድ የሰቀሉት፣ የሁሉ ጌታ፣ በቃሉ የሚያድን እነርሱ ግን ያላወቁት አምላክ እንደሆነ ሊቁ ያስረዳናል። ስለዚህ ይህን ቃል ካለመስማት የተነሣ ተስፋ መቁረጥ ላይ ያደርሳል።
መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን ‹‹ ቃሌን የሚሰማ ግን በተስፋ ይኖራል፤ ከክፉም ሁሉ ያለድንጋጤ ያርፋል›› (ምሳ. ፩፥፴፫) በማለት የገለጸውን ማስታወስ ያስፈልጋል። የእስራኤል ንጉሥ ጠቢቡ ሰሎሞን በንግሥናው ዘመን ለሕዝቡ በምሳሌ ቃሌን ስሙ እያለ በተደጋጋሚ ይናገር ነበር። ነገር ግን ቃሌን ስሙ የሚለው የእርሱን ቃል ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ደግሞ ጥበበኛ ያደርጋል፤ ተስፋን ያለመልማል፤ ከክፉም ይታደጋል። ስለዚህ ‹‹ቃሌን የሚሰማ ግን በተስፋ ይኖራል፤ ከክፉም ሁሉ ያለድንጋጤ ያርፋል›› በማለት ያስረዳናል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ በተስፋ ይኖራል በአንጻሩ የእግዚአብሔርን ቃል የማይሰማ ግን ተስፋ ይቆርጣል።
፪. በሐሰተኛ ትምህርት መሞላት
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ “ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩት እነዚያ አልተጠቀሙምና” (ዕብ. ፲፫፥፱) በማለት እንደገለጸው ለምእመናን የማይገባ ትምህርት ተስፋ ያስቆርጣል።
በዘመናችን እየተስተዋለ ያለው የወጣቱ የሥነ ምግባር ዝቅጠት መማር ያለበትን ሳይሆን መማር የሌለበትን የሐሰት ትምህርት እየተማረ ስላደገ ነው። በእናት በአባቶቹ ተስፋ የቆረጠ፣ በሀገሩ ተስፋ የቆረጠ፣ ለማንነቱ ዋጋ የማይሰጥ፣ ከሰውነት የወጣ ሥራ እየሠራ ያለው፣ የተማረው ትምህርት የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርስ፣ ተስፋ የሚያስሰንቅ ሳይሆን ተስፋ የሚያስቆርጥ ስለሆነ ነው።
፫. ለምድራዊ ሕይወት መጨነቅ
የሰው ልጅ ፍላጎቱ የበዛ በውስጡ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ያለው አቅም ግን እጅግ ውሱን የሆነ ፍጥረት ነው። ፍላጎቱ ከመብዛቱም የተነሣ በሚጠቅመውም በማይጠቅመውም፣ በሚያስፈልገውም በማያስፈልገውም፣ በሚያስደስተውም በማያስድስተውም ብቻ በብዙ ነገር ይጨነቃል።
ይልቁን በዘመናችን እንደተከሠተው ዓይነት ለዓለም ስጋት የሆነ፣ በሰው ሰውኛ ሠልጥነናል ያሉ ሀገራት ሊቋቋሙት ያልቻሉት በሽታ፣ በሃይማኖታቸውና በዘራቸው እየተለዩ እንደ በግ የሚታረዱበት ሁኔታ ሲከሠት ሰዎች እጅግ ይጨነቃሉ። ይሁን እንጂ አለማሰብ ባይቻልም አለመጨነቅ ግን ይቻላል። ይቻላል ብቻ ሳይሆን እንዳንጨነቅም ታዝዛናል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ እንዳንጨነቅ ብቻ ሳይሆን በመጨነቃችን አንዳች የምንጨምረው ነገር እንደሌለን “ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማነው” (ማቴ. ፮፥፳፯) በማለት አስተምሮናል።
ስለሆነም ምእመናን ከአላስፈላጊ ጭንቀት ወጥተው እንዲያደርጉ የታዘዙትንና ማድረግም የሚችሉትን ብቻ እያደረጉ በሌላው ነገር ሁሉ ግን እግዚአብሔርን በመለመን እርሱን ብቻ ተስፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ሰዓት የመምህራን ድርሻም የሚሆነው የተባለውንም ሆነ ያልተባለውን ምእመናን የሚያንጸውንም ሆነ የሚያፈርሰውን እየተናገሩ በጭንቀት ላይ ጭንቀት ከመደራረብ ተቆጥበው የሚያጸናውንና የሚያጽናናውን የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ምእመናን መማር የሚገባቸውን መሠረታዊ ትምህርት ባይማሩ ከላይም እንደተገለጸው በሐሰተኛ ትምህርት ተሞልተው፣ ለምድራዊው ሕይወት ብቻ እየተጨነቁ ተስፋ መቁረጥ ላይ ሊደርሱ ይችላሉና መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
፬. የመከራ ጽናት
ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በየጊዜው ልዩ ልዩ መከራ ሲፈራረቅባቸው ኖረዋል። በዘመናችንም እጅግ የሚከብድና የሚዘገንን መከራ እየደረሰባቸው ነው። በዚህ ዓለም እስከ ኖሩና የክርስቶስንና የክርስቶስ ወዳጆች የሆኑትን ቅዱሳን አብነት እስካደረጉ ድረስ ወደፊትም ሊቀጥል ይችላል። ፳፻፲፪ ዓ.ም ካሳለፍናቸው ዐሥር ዐሥራ አምስት ዓመታት በተለየ መልኩ መከራው የተፈራረቀበት ዓመት ነበር። መከራው ሰው ሠራሽም ተፈጥሯዊም፣ መንግሥታዊም፣ ግለሰባዊም፣ የውስጥም የውጭም ሊባል ይችላል። ተፈጥሯዊ ሲባል የጎርፍና የእሳት አደጋዎች፣ በድርቅ ምክንያት የሚከሠት ጽኑዕ ረኀብና ዓለማቀፋዊውን መቅሰፍት የኮቪድ ፲፱ ወረርሽኝን ጨምሮ መጥቀስ ይቻላል። ሰው ሠራሽ ደግሞ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የዘር ጭፍጨፋ፣ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የሰዎች ከቀያቸው መፈናቀል፣ ወዘተ ሁሉ ተጠቃሽ ነው።
ይህ መከራ የሰው ልጅ መከላከል የሚችለውም የማይችለውም ነበር። ተፈጥሯዊ የሆነውን መከላከል ባይችልም ሰው ሠራሹን ግን መከላከል ይቻል ነበር። ይህ ማለት በቀጥታ አደጋው የደረሰበት አካል መከላከል ባይችልም አደጋውን ያመጣው አካል እንዲሁም የሚመለከተው የመንግሥት አካል መከላከል ይችል ነበር። ያም ሆነ ይህ በሚከብድና በሚዘገንን መከራም ቢሆን ከ፳፻፲፪ ዓ.ም ወደ ፳፻፲፫ ዓ.ም ተሸጋግረናል። በመሆኑም ሰዎች የዚህ ከባድ መከራ ተሸካሚ ሲሆኑ የጸኑት መከራውን ተቋቁመው ሊያልፉ ይችላሉ። ያልጸኑት ደግሞ ተስፋ ቆርጠው ሃይማኖታቸውን እስከ መለወጥም ሊደርሱ ይችላሉና የመከራው ጽናት የተስፋ መቁረጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በተስፋ መኖር የሚያስገኛቸው ነገሮች
፩. ከክፉ ያሳርፋል
የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና በተስፋ መኖር ከክፉ እንድንድን። በሐዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው ጽኑዕ የሆነውን ተስፋ የሰነቁት ሐዋርያት እሳቱን እና ስለቱን ታግሠው ለበለጠ ክብር በቅተዋል። ከመካከላቸው የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማው ይሁዳ ግን ተለይቷል፤ አልሰማም ማለት በዕዝነ ሥጋው አልሰማም ማለት አይደለም፤ በዕዝነ ልቡናው ግን በእርግጥም አልሰማም። ስለዚህ ምንም እንኳን ከሐዋርያት ጋር ቢቆጠርም፣ ትምህርቱ፣ ተአምራቱ ባይነፈገውም ክብርን ግን አላገኘም። የእግዚአብሔርን ቃል በአግባቡ አልሰማምና። (ኢሳ.፮፥፩-፲)
ምን አልባትም በተስፋ ከመኖር ይልቅ ተስፋ በመቁረጡ ግኡዝ የሆነችው እንጨት ብትሰብከው እንኳን መመለስ አልቻለም። በተስፋ መኖር እንደፈያታዊ ዘየማን የመጨረሻ ሕይወትን ያሳምራል። ተስፋ መቁረጥ ግን እንደይሆዳ በመጨረሻ ከቤት መውጣትን እስከ መጨረሻው አለመመለስን ያስከትላል። ተስፋ መቁረጥ እጅግ የከፋ አደጋ ላይ ይጥላልና።
በዘመናችንም ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ስለማያደርግ ሥጋዊ መፍትሔው ብቻ ይታየዋል። በእርግጥ ሥጋዊ መፍትሔውም የሚገኘው በእግዚአብሔር ነው። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የሥጋም የነፍስም ድኅነት እንደሆነ አለመቀበል በብዙኃኑ ዘንድ ይስተዋላል። ይህ የሆነው ደግሞ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ካለማድረግ የመጣ ነው። ሥጋዊ ዕውቀትን ብቻ ተምሮ ያደገ ሰው ሁሌም የሚታየው ሥጋዊ ድሎት ነው፤ ‹‹በቃልህ እዘዝ፤ ልጄ ይድናል›› ያለው የመቶ አለቃው ቃል ትዝም አይለው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማቱም በመጨነቅ፣ በመሸበር፣ ለውጥ የማያመጣ መፍትሔ ሲያፈላልግ ዘመኑን በከንቱ ይጨርሳል። (ማቴ. ፰፥፰)
የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ማድረግና በጽኑዕ ተስፋ መኖር የተስፋ ቃሉንም በትክክል ሰምቶ በተግባር ላይ ማዋል ከክፉ የሚታደገን መሆኑን ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን ሰምቶ የማያደርገው ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስታዎት እንደሚያይ ሰው ይመስላል። ራሱንም ተረድቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም እንዴት እንደሆነ ይረሳል›› በማለት ያስረዳናል። ይህ ማለት የተስፋ ቃሉን ሰምቶ በሕይወት መተርጎም ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ሕይወት ነው፤ ከክፉም ያለምንም ድንጋጤ ያድናል።
ያሳለፍነው ዘመን እጅግ የከፋ መከራው ተፈራረቀበት ዘመን እንደነበር ከላይ ለመግለጽ ተሞክሯል። ያሳለፍነው ዘመን ብቻ ሳይሆን ዐዲሱን ዓመትም በተቀበልን ማግስት በጎርፍ አደጋ ምክንያት በርካታ ሰዎች ሀብት ንብረታቸውን እንዳጡ፣ ከመኖሪያ ቀያቸው እንደተፈናቀሉ፤ በሃይማኖታቸውና በዘራቸው እየተመረጡ እንደተገደሉ የበርካታ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኗል። ነገር ግን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ተስፋ አያሳፍርም” በማለት እንደነገረን የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ አድርገን መልካሙን ዘመን እንዲያመጣልን፣ የክፉዎችንም ልቡና እንዲያራራልን፣ የተፈጥሮውንም ሆነ ሰው ሠራሹን አደጋ በቸርነቱ እንዲያስታግሥልን አጥብቀን መለመን ይኖርብናል። እግዚአብሔር አምላካችን በጽኑዕ ተስፋ እንደሚደረግልን አምነን የጠየቅነውን ሁሉ ያደርግልናልና።
፪. የመንግሥተ ሰማያት ወራሽ ያደርጋል።
ሰው ከሞተ በኋላ በእግዚአብሔር በሕይወት እንደሚኖር ባለመጠራጠር ማመን ተስፋ መንግሥተ ሰማይ ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል፤ ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል›› በማለት እንዳስረዳን በሥጋዊ ዐይናችን ሳናይ ሰምተን ብቻ የተቀበልነው ሃይማኖት ነው፡፡ (፩ኛ ተሰ. ፬፥፲፬) በዐይን የማይታየውን በእጅ የማይዳሰሰውን መውረስ ደግሞ በጽኑዕ ተስፋ የመኖር ውጤት ነው።
መንግሥተ ሰማያት እንዳለች፣ እንደምንወርሳት፣ በደስታ እንደምንኖርባት፣ ከአወቅን በኋላ እንደማናጣትም አምነን የተቀበልነው ለመንግሥተ ሰማያት የምታበቃውን ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት አጽንተን በእግዚአብሔርም ቸርነት እንወርሳታለን የሚለው ሙሉ ተስፋ ስላለን ነው፡፡
ደግሞም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ፣ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት›› ብሎ እንደነገረን ተስፋ የምናደርገው ነገር አለ፤ እርሱም መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ይህን ተስፋ የምናደርገውን ነገር ደግሞ በእምነት እንወርሳለን፡፡ በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር ሠርተን ስንኖር ያን ተስፋ ያደረግነውን ርስት ሊያወርሰን እርሱ የታመነ አምላክ ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው›› በማለት ያስረዳናል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፩፤ ፩ቆሮ.፩፥፱)
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በድርሰቱ “ተስፋ ሕይወት ተሠራ በሰማያት ተስፋ ሕይወት ተሠራ በሰማያት ተስፋ ሕይወት ተሠራ፤ የሕይወት ተስፋ በሰማያት ተሠራ” በማለት ሦስት ጊዜ እየደጋገመ ይነግረናል። ይህ ሊቁ በሰማያት ተሠራ ያለው የሕይወት ተስፋ በሃይማኖት ጸንተው በጎ ምግባር ሠርተው የሚወርሱት መንግሥተ ሰማያት ነው። የእግዚአብሔርን የባሕርይ አምላክነት፣ አምኖ፣ በዐይነ ሥጋ የማይታይ ዘለዓለማዊ መንግሥቱን ያወርሰኛ ብሎ በተስፋ ጸንቶ ለኖረ የሚወረስ ነውና እንዲህ በማለት ገለጸው።
ከጥንት ጀምሮ ቅዱሳን አበው እና ቅዱሳን ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት መከራ የተቀበሉት የማይቀር፣ የማያሳፍር ተስፋ ስለነበራቸው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ ‹‹እነርሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ ተስፋቸውን አገኙ፤ የአናብስትን አፍ ዘጉ›› (ዕብ.፲፩፥፴፫) ሲል ያስረዳል፡፡ እነርሱም የተጋደሉት በእምነት ነው፤ ተጋድለውም ነገሥታትን ድል አደረጉ፤ ይጠባበቁት የነበረውን ተስፋም አገኙ፡፡ ተስፋቸው ደግሞ ድኅነት ነው፤ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ነውና፤ ይህም ሆነላቸው፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን መቼም ቢሆን ተስፋችንን አያሳጣንም፡፡ ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር ለእኛ የሚያስፈልገን መሆን አለበት፤ የሚጎዳንን አይሰጠንምና፡፡ ‹‹በእርሱም አማካኝነት ወደቆምንበት ወደ ጸጋው በእምነት ተመራን፤ በእግዚአብሔርም ክብር ተስፋ እንመካለን፡፡ የምንመካ በእርሷ ብቻ አይደለም፤ በመከራችን ደግሞ እንመካለን እንጂ፤ መከራ በእኛ ላይ ትዕግሥትን እንደሚያመጣ እናውቃለንና፡፡ ትዕግሥትም መከራ ነው፤ በመከራ ተስፋ ይገኛል፡፡ ተስፋም አያሳፍርም፤ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን መልቷልና›› (ሮሜ ፭፥፪-፭) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ ይነግረናል፡፡
በአጠቃላይ አባታችን አዳምን ከገነት ሲያስወጣው ጽኑዕ ተስፋ ሰጥቶ ወደዚች ምድር እንዲኖር ያደረገ አምላክ የሰጠውንም ተስፋ ያላስቀረ ታማኝ አምላክ ዛሬም ከኖሩበት ቦታ ተፈናቅለው፣ በማንነታቸው ተሸማቅቀው፣ በአንድ በኩል በሰው ሠራሽ አደጋ በሌላ በኩል በተፈጥሮ አደጋ እየተጨነቁ ያሉት ሁሉ ተስፋ አያሳፍርምና በተስፋ እግዚአብሔርን መለመን ያስፈልጋል። ነቢየ እግዚአብሔር ዕንባቆም “በለስ አታፈራምና በወይኑም ፍሬ ሐረግ አይሆንም፤ ወይራ ሥራዋን አበለች እርሻዎችም እህልን አላፈሩም፤ በጎች ከግጦሽ ታጡ፤ ላሞችም በበረት ውስጥ አልተገኙም፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሤትን አደርጋለሁ።” (ዕንባ. ፫፥፲፯-፲፰) በማለት እንደተናገረው በሃይማኖታችን ጸንተን በጎ ምግባር እየሠራን በእግዚአብሔር ቤት በተስፋ ልንኖር ይገባል።
በሚመጣብን መከራ ሁሉ በሃይማኖት ጸንተን፣ በጎ ምግባር ሠርተን፣ የተስፋውን ቃል በልቡናችን ማኅተም አትመን የምንችለውንና የሚጠበቅብንን ሁሉ ሠርተን በመጨረሻይቱ ዕለት “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን የአባቴን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ወደ እኔ ኑ” የሚለውን የሕይወት ቃል ያሰማን ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችን ይፍቀድልን አሜን።
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2349
ውድ አንባብያን ባለፉት ተከታታይ እትሞቻችን የክህነትን ምንነት፣ ክህነት በዘመናት ምን ይመስል እንደነበር፣ ክህነት እንዴት ይሾማል የሚሉትንና መሰል ጉዳዮችን ማቅረባችን ይታወሳል በዚህ ዕትም ደግሞ ክህነት ክብሩ ምን ይመስላል የሚለውን እንመለከታለን መልካም ንባብ።
በመጽሐፍ ቅዱስ የክህነት አገልግሎትን የሚያከናውን አካል እጅግ ተመስግኗል። ክህነት አንዱ አገልግሎት ምእመናንን መመገብ ነውና መጋቢውን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን? ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው።” (ሉቃ.፲፪፥፵፪) በማለት ይገልጸዋል። ብፁዕ ከመባል በላይ ደግሞ ክብር የለም። ይህ ሰው የተመሰገነው በእግዚአብሔር ቃል ነው።
ሰው መልካም ሥራ ሠርቶም ይሁን ሳይሠራ በሰው ዘንድ ሊመሰገን ይችላል። አመስጋኙ ከራሱ የግል ጥቅም አንጻር ተነሥቶ ሊያመሰግነው ይችላል። ወይም ደግሞ የሚመሰገነው አካል ካለበት መዓርግ የተነሣም እንዲሁ በአድር ባይነት ሰዎቹ ሊያመሰግኑት ይችላሉ። ያለምንም ማዳላት በትክክል አይቶ የሚፈርድ፣ አይቶ የሚያመሰግን በትክክል በሠራነው ሥራ የሚያመሰግነን ማለትም በአድር ባይነት ወይም እጠቀም ሳይል የሚያመሰግን እግዚአብሔር ነው። የክህነት አገልግሎትን የሚያከናውነውን ማለትም መንጋዎችን የሚመግባቸውን አገልጋይ ያመሰገነው እጠቀም ሳይል ሁሉ ያለው እግዚአብሔር አምላካችን ነውና በእግዚአብሔር ዘንድ ከመመስገን በላይ ክብር የለም የተባለው ለዚህ ነው።
የካህናትን ክብር በተመለከተ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሰዓታት በተሰኘ ድርሰቱ “ህየንተ ሱራፌል ብነ ላእካነ ምሥጢር ካህናት እለ ያቄርቡ መሥዋዕተ ንጹሐ ወቍርባነ ነባቤ ወዕጣነ ውኩፈ ዘመዓዛሁ ሠናይ። ህየንተ ሊቃናት ብነ ዲያቆናት ንጹሓን እለ አቅለሉ ክነፊሆሙ ለተልእኮ ምሥጢር በዲበ ዛቲ ጠረጴዛ፤ በሱራፌል ፈንታ መዓዛው ያማረና ተቀባይ የሆነ ዕጣንን፣ ተናጋሪ ቍርባንንና ፣ ንጹሕ መሥዋዕትን የሚያቀርቡ የምሥጢር መልእክተኞች ካህናት አሉን። በሊቃናት ፈንታ ቅድስት በምትሆን በቤተ ክርስቲያን ለመላላክ እግራቸውን ያቀለሉ ንጹሓን ዲያቆናት አሉን።” (ሰዓታት፣ኵሎሙ) በማለት ክህነት ግሩምና ድንቅ ክብር እንደሆነ ያስረዳናል።
መላእክት በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ እጅግ የተከበሩ እግዚአብሔርን ማገልገል ተግባራቸው የሆነላቸው የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረታት ናቸው። እግዚአብሔር አምላካችን መላእክትን ስሙን ቀድሰው ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ድንቅ በሆነ ጥበብ እንደፈጠራቸው የሰውን ልጅም እንዲሁ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ በጸጋ ላይ ጸጋን አጎናጽፎታል። ለመላእክት ያላደላቸውን የክህነት አገልግሎትም አድሎታል። ስለዚህ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በመላእክት ፈንታ ካህናት፣ በሊቃናት ፈንታ ዲያቆናት አሉን እያለ በክህነት አገልግሎት የሚያገለግሉ አካላት ምን ያህል ክብር እንዳላቸው ያስረዳናል።
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለ ክህነት ባስተማረው ትምህርትና ገብረ እግዚአብሔር ኪደ በተረጎመው መጽሐፍ “የብሉይ ኪዳን ካህናት ሰውነትን ከለምጽ የማንጻት ሥልጣን ነበራቸው፤ እንዲያውም የማንጻት ሥልጣን ሳይሆን የነጹ መሆን አለመሆናቸውን መመርመርና የነጻውን ነጽቷል ብሎ ማወጅ ነበር። እንዲህም ሆኖ ግን ካህናት ምን ያህል ይከበሩ እንደነበር ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ይቻላል። የዘመነ ሐዲስ ካህናት ግን ሥልጣን የተቀበሉት በሥጋ ለምጽ ላይ ሳይሆን በነፍስ ለምጽ ላይ ነው፤ ከተመለከቱ በኋላ ንጹሕ መሆን አለመሆኑን ሳይሆን በእርግጥና በፍጹም ለማንጻት ነው” (በእንተ ክህነት፣ ገጽ፶፭) በማለት ይገልጻል።
ሊቁ ከዚህ አያይዞም “የብሉይ ኪዳኑ ክህነት እንዲህ ይከበር ነበር። ነገር ግን ለሥልጣኑ ከመቅናት የተነሣ ዳታንና አቤሮን በማይገባ መንገድ በመሻታቸው መቅሠፍት ደርሶባቸዋል። የብሉይ ኪዳኑ ክህነት መቅሠፍት ካመጣ የሐዲስ ኪዳኑን ክህነት መናቅማ ምን ያህል የባሰ መቅሠፍት ሊያመጣ ይችላል “ በማለት በአጽንዖት ያስረዳል። (ዝኒ ከማሁ)
የሐዲስ ኪዳን ክህነት ከሥጋም ከነፍስም ደዌ ይፈውሳል። የብሉይ ኪዳን ክህነት ከሥጋ ደዌ መፈወስን ለማወጅ ብቻ ክብር ከነበረው የሐዲስ ኪዳን ክህነት ደግሞ ከሥጋም ከነፍስም ደዌ የሚፈውስ ነውና እጅግ ሊከበር ይገባዋል። የተከበረም ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከላቸው መልእክቱ “ክብር የሚገባውንም አክብሩ” (ሮሜ ፲፫፥፯) በማለት እንደገለጸው ክህነት ክብር የሚገባው ስለሆነ እግዚአብሔርም አክብሮታል፤ ሐዋርያትም አክብረውታል፤ ሊቃውንትም አምልተውና አስፍተው ክብር እንደሚገባው ጽፈዋል፤ አስተምረዋልም።
ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የካህናትን ክብርና መዓርግ በተመለከተ “ዝኬ ውእቱ ኪዳነ ቃልከ ዘታወሥኦሙ ለካህናት እንዘ ትብል ጼዉ ለምድር። ዘትቤሎሙ ለካህናት ብርሃኑ ለዓለም። ዘትቤሎሙ ለካህናት አዕይንተ ቤተ ከርስቲያን። ዘትቤሎሙ ለካህናት ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን። ዘትቤሎሙ ለካህናት አምሳለ መላእክት። ነዓኬ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትባርክ ሕዝበከ ወርስተከ ለዓለመ ዓለም፤ ለካህናት የነገርሃቸው ቃል ኪዳንህ ይህ ነው። የምድር ጨው ናችሁ ብለህ። ካህናትን የዓለሙ ብርሃን ናችሁ ያልሃቸው። ካህናትን የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች ናችሁ ያልሃቸው። ካህናትን የቤተ ክርስቲያን መብራት ናችሁ ያልሃቸው። ካህናትን የመላእክት ምሳሌ ናችሁ ያልሃቸው። ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሕዝብህንና ርስትህን ለዘለዓለሙ ትባርክ ዘንድ ና” (ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ) በማለት ያስረዳል። ሊቁ የካህናትን ክብር በተመለከተ የተናገረውንና የክብራቸው መገለጫ የሆኑ ነጥቦችን ዘርዘር አድርገን እንመልከታቸው።
ቃል ኪዳን፡- ቃል ኪዳን በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ የስምምነት ውል ነው። ይህን በተመለከተ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘ መጽሐፋቸው “ኪዳን በቁሙ ውል ቁም ነገር፣ የፍቅርና የአንድነት መሐላ፣ ሰላማዊ ሕግ፣ ሁለቱን ወገን አንድ የሚያደርግ፣ ስለረብና ስለ ጥቅም በተስፋ የቆመ የተጣፈ ሥርዓት፣ ቢያፈርሱት ጉዳትና ጠብ የሚያመጣ ጥቅም የሚያሳጣ” (፭፻፳፱) በማለት ያስረዳሉ። ይህ በሁለቱ መካከል የሚደረገው ቃል ኪዳን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በካህናት መካከል በተለየ መልኩ ተደርጓል። ይህ ልዩ ቃል ኪዳን ደግሞ ዘለዓለማዊ የሆነና ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት የክህነት አገልግሎት ነው። ይህን ቃል ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ለሐዋርያት “እንግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ። ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሩአቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” (ማቴ. ፳፰፥፲፱-፳) በማለት አስረድቶናል። ይህ ቃል ኪዳን ጽኑዕ ነው። እግዚአብሔር ለካህናት የሰጣቸው ጽኑዕ ቃል ኪዳን የካህናትን ክብር የሚያመለክት ነው።
ሰው ከባለሥልጣን ጋር፣ ከባለሀብት ጋር፣ ታላላቅ እና ዝነኛ ከሚባሉ ሰዎች ጋር ሲሆን ለራሱም ክብር ይሰማዋል፤ በሰው ዘንድም ይከበራል። ካህናትን እግዚአብሔር የገባላቸው ቃል ኪዳን “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” የሚል ነው። ሰው ከሰዎች ጋር ሆኖ ከተከበረ እግዚአብሔር በዘመኑ ሁሉ አብሮት ያለማ እንዴት አብዝቶ ይከበር? ስለዚህ የክህነት አገልግሎት እጅግ ክቡር ነው። በክህነት አገልግሎት የሚኖሩት አካላትም እንዲሁ እጅግ የከበሩ ናቸው።
ቃል ኪዳን የሚጠብቁትን ይጠብቃል የማይጠብቁትን ደግሞ ያጠፋል፡፡ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ፈለግሁ፡፡ ባንድ ወቅት ዳክየ እና እባብ ባልነጀርነት አበጅተው ሲኖሩ ወደአንድ ቦታ መሄድ ፈለጉና ጉዞአቸውን ሲጀምሩ ከመንገድ ላይ ታላቅ ወንዝ አገኙ፡፡ ይህን ወንዝ ዳክየ መሻገር ትችላለች እባብ ግን መሻገር አይችልም፡፡ ስለዚህ ጓደኝነታቸውን ተጠቅመው በመካከላቸው አንድ ቃል ኪዳን አስቀመጡ፡፡ ይህም ዳክየ አዝላ ልታሻግር እባብም ላይተናኮላት (ላይነክሳት) ነበር ፡፡ በዚህ ቃል ኪዳን ተስማምተው ጉዟቸውን እንደጀመሩ ከመሀል ወንዝ ላይ እባብ ዳክየን ነከሳት፡፡ በዚህ ጊዜ ምን ብለህ ነበር ስትለው የቀረብኩትን ሁሉ መንከስ ልማድ ሆኖብኝ አላስችልህ ብሎኝ ነው አለ፡፡ ግን በሚገርም ሁኔታ የተነከሰችው ዳክየ መዋኘት አልችል ብላ ስትጠልቅ እባብም አብሮ ጠልቆ ሞተ፡፡ ስለዚህ ቃል ኪዳኑን ባለመጠበቁ የራሱ መሞትና መጥፋት ሳያንሰው ያዘለችውንም አጥፍቷል፡፡ ስለዚህ ቃል ኪዳን ቢጠብቁት ይጠብቃልና ይህ የቃል ኪዳን ምልክት የሆነውና የምግብ ሁሉ ማጣፈጫ የሆነው ጨው በውስጣችሁ ይኑር ተብለናል፡፡ ይህም ቃል ኪዳናችሁን እስከመጨረሻው ጠብቁ ሲለን ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ከካህናት ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ቢጠብቁት የሚጠብቅ፣ ክብር የሚያድል፣ ባይጠብቁት ደግሞ ፍርድ የሚያመጣ ነው።
የምድር ጨው፡- የጨውን ምንነት በተመለከተ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለ መጽሐፋቸው ‹‹አሽቦ፣ አሞሌ፣ በቈላ፣ በበረሓ ከውኃማ መሬት የሚገኝ፤ በውኃ የሚቀልጥ፣ የሚሟሟ፤ መጣጣ ሖምጣጣ መባልዕትን የሚያጣፍጥ፣ ከሁሉ ገብ፣ በብዙ ወገን የሚፈለግ›› (ገጽ ፯፻፶፪) በማለት ያብራሩታል፡፡ እንደ ኪዳነ ወልድ አገላለጽ የሚጣፍጥ ብቻ ሳይሆን የሚያጣፍጥ፣ በብዙ ወገን የሚፈለግ ማለት በብዙ ወገን የሚሠራ የምግብ ዓይነትን የሚያሳምር፣ ምግብ ለሚያሻቸው ፍጥረታት ሁሉ ወሳኝ እንደ ሆነ እንገነዘባለን፡፡
ጨው በሰዎች ሕይወት ላይ ታላቅ ቦታ ያለው ነው፡፡ ማንኛውም ነገር ለሥጋዊ ሕይወት እጅግ አስፈላጊ በሆነ ቊጥር ለመንፈሳዊ ሕወት አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮችም፣ ማነጻጸሪያ እየሆነ ይጠቀሳል፡፡ ጨውም በሰዎች ሥጋዊ ሕይወት ላይ ካለው ታላቅ ቦታ አንጻር ለመንፈሳዊው ሕወትም ምሳሌ እየሆነ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ጨው ለምግበ ሥጋ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችን ያደለን ታላቅ ሥጦታም ነው፡፡ መራራውን ከምሬቱ፣ የጎመዘዘውን ከጎምዛዛነቱ፣ አልጫውንም ከአልጫነቱ አውጥቶ ጣዕምና ለዛ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፡፡
ጨው ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውል ነበር፡፡ የተወሰኑትን እናንሣና ከያዝነው ርእሰ ጉዳይ ጋርም ምን ያህል ግንኙነት እንዳለው እንመለከታለን።
ሀ.ለመድኃኒትነት፡- ጨው በቁስል ውስጥ ተፈጥረው ቁስልን የሚያባብሱና ቁስሉ እያምረቀዘ እንዳይደርቅ የሚያደርጉ ነፍሳትን ያጠፋል፤ የቆሰለውንም ያደርቃል፡፡ የጨውን መድኃኒትነት የተረዱ ሰዎች በሥራ ላይ እያሉ ስለት ሲቆርጣቸው በፍጥነት በቁስሉ ላይ ጨው ያስሩበታል፡፡ ቁስሉም በፍጥነት ይደርቃል፡፡ ‹‹በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልታተበም፤ ንጹሕ ትሆኝ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፤ በጨውም አልተወለወልሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም፤ በጭንም አልታቀፍሽም፡፡›› (ሕዝ.፲፮፥፬) በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል ስለ ኢየሩሳሌም በተናገረበት አንቀጹ ምሳሌአዊና ሰውኛ በሆነ ዘይቤአዊ አነጋገር የጨውን መድኃኒትነት ያስረዳል፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል የጨውን መድኃኒትነት አስረድቷል። ይህ የጨው መድኃኒትነት በብሉይ ኪዳን ብቻ ሳይሆን በሐዲስ ኪዳንም ያለ እውነታ ነው። እናንተ የዓለም ጨው ናችሁ የተባሉት ካህናት መድኃኒቱን በእጃቸው የያዙ ሲሆኑ የክህነት አገልግሎቱም እንዲሁ ዘለዓለማዊ የሆነ መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ነው። ማንኛውም ሰው ይከበራል ከተባለ አንድ እጅግ አስፈላጊ ነገር በእጁ አለ ማለት ነው። ካህናቱም መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ የሚገኝበት፣ ከእግዚአብሔር የምንገናኝበት ክህነት በእጃቸው ያለ ናቸውና እጅግ ክቡራን ናቸው።
ለ. ለመብአነት:- በብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የቊርባን መስዋዕት እርሾ የሌለበት እንዲሆን ሲነገራቸው ነገር ግን በጨው የጣፈጠ እንዲሆን ታዝዘዋል፡፡ ይህንም አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የእህል ቊርባን ሁሉ እርሾ አይሁንበት፤ እርሾ ያለበት ነገር፣ማርም ለእግዚአብሔር ቊርባን ይሆን ዘንድ አታቀርቡም፡፡ የምታቀርቡት ቊርባን ሁሉ በጨው ይጣፍጣል፤ የአምላክህም ቃል ኪዳን ጨው ከቊርባንህ አይጒደል፤ በቊርባናችሁ ሁሉ ላይ ጨው ትጨምራላችሁ፡፡›› (ዘሌ.፪፥፲፩-፲፫) በማለት የጨውን ተፈላጊነትና በብዙ ወገን የሚኖረውን አገልግሎት አስረድቶናል፡፡ ይህንም በማድረጋቸው ቃል ኪዳናቸውን የመጠበቃቸው ምልክት እንደሆነም አስረድቷቸዋል፡፡
የክህነት አገልግሎቱም ሆነ ካህናቱ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የጸና ቃል ኪዳን ነው። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ኢኃደጋ ለምድር እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ ምድርን ያለ ካህናትና ያለዲያቆናት አልተዋትም” በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላካችን ክህነትን ለካህናቱ ሲሰጥ ካህናቱን ለምእመናን በስጦታነት አድሎናል። በአንጻሩ ደግሞ ካህናቱም ለእግዚአብሔር የተሰጡ ልዩ መባእ ናቸው። ይህ የእግዚአብሔርና የሰው በክህነት አገልግሎትና በካህናት በኩል የሚኖረው ግንኙነት የክህነቱን ክብር እጅግ ከፍ ያደርገዋል። ምክንያቱም ሁሉ የሚቻለው አምላክ ከሰው ጋር ለመገናኘት የመረጠው መልካም መንገድ የክህነት አገልግሎት መሆኑ ነው። ካህናቱም ከሰው ተለይተው ለዚህ አገልግሎት የተመረጡ ሥራቸው እግዚአብሔርን ማገልገል ሆኖላቸው እንዲኖሩ ለጊዜው በወላጆቻቸው አቅራቢነት በዋናነት ግን በእግዚአብሔር ልዩ ምርጫ ለዚህ አገልግሎት የተለዩ አካላት ናቸው። ለእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ ከመሰጠት በላይ ክብር ስለሌለ እነሱም የተከበሩ ናቸው እነርሱ የተመረጡለት አግልግሎትም እንዲሁ ክቡር ነው።
ሐ.ለምግብ ማጣፈጫነት፡- ጨው የሌለው ምግብ ሊጣፍጥ አይችልም፡፡ ስለዚህም ምግብ ሲሠራ ያለ ጨው አይሠራም፡፡ በመጽሐፈ ኢዮብም ‹‹በቊጥቋጦ አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚለውን አትክልት ይለቅማሉ የክትክታ ሥር ደግሞ ምግባቸው ነው፡፡›› (ኢዮ.፴፥፬) በማለት ሁሉም እጅግ የሚፈልገውና ለሕይወቱም አስፈላጊ እንደሆነ ተጽፎልናል፡፡ በተፈጥሮ ጨውነት ያላቸውን ዕፅዋት እንስሳትም ሰዎችም ሳይቀሩ አብዝተው ይፈልጓቸዋል፡፡ ከብት የሚጠብቁ እረኞች በሜዳ ሲውሉ ከቋጠሩት ምግብ ይልቅ ጨው ጨው የሚሉትን ዕፅዋትና አትክልት ይፈልጓቸዋል፡፡ ስለዚህም ምግቡ ያለጨው አይሠራም ቢሠራም አይጣፍጥም ‹‹ምግብ ያለጨው ይበላልን የጎመን ዘር ጭማቂስ ይጣፍጣልን›› (ኢዮ.፮፥፮) በማለት ጻድቁ ኢዮብ የጨውን አስፈላጊነት ያስረዳናል፡፡
ጻድቁ ኢዮብ ያለ ጨው የተዘጋጀ ምግብ ጭራሽ እንዳማይበላ ነው የነገረን፡፡ ምክንያቱም ስለማይጣፍጥ ነው፡፡ መራራውን የሚያጣፍጥ፣ የጎመዘዘውን የሚያለስልስ መሆኑንም ሰዎች ስለተረዱ ምግባቸውን ያለ ጨው አይሠሩትም፡፡ ሥጋዊው ምግብ ያለ ጨው እንደማይጣፍጥ ሁሉ መንፈሳዊው ሕይወታችን ያለክህነት አገልግሎትና ያለ ካህናት አይጣፍጥም። ይህንም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስረዳ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን እንግዲህ በምን ይጣፍጣል? እንግዲህ የሚጠቅመው የለም፤ ሰዎች ወደውጭ አውጥተው የጥሉታል፤ በእግራቸውም ይረግጡታል እንጂ።” (ማቴ. ፭፥፲፫) በማለት አስተማረ። በአበው ብሂልም ‹‹ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ ጨው ቢያልጥ በምን ያጣፍጡ›› ተብሎ ይነገርለታል፡፡
ካህናት የሰው ሕይወት የሚጣፍጥበት ጨው ናቸው። የሰውን ልጅ መክረው አስተምረው ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዲመለስ የሚያደርጉ፤ አልጫ የሆነውን ዓለም አጣፍጠው ለመንግሥተ ሰማያት እንዲገባ የሚያደርጉ ናቸው። ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት የወረደው ከድንግል ማርያም የተወለደው ያን ሁሉ መከራ የተቀበለው የሰውን ልጅ ለማዳን ነው። ካህናትም የተመረጡት የሰው ልጅ ድኅነትን ያገኝ ዘንድ ነው። ለዚህ አገልግሎት ከመመረጥ በላይ ክብር የለምና አገልጋዮችም እጅግ የተከበሩ ናቸው። አገልግሎቱም እንዲሁ የከበረ ነው።
መ. በጠላት ጦር የተያዘ መሬት ላይ ይጣላል፡- ጨው በብዙ ወገን ተፈላጊ ነው ብለናል እና ሰዎች በማጣፈጫነት እንደሚጠቀሙበት ሁሉ ለማድረቂያነትና ምድርን ወና ለማድረግም ይጠቀሙበታል፡፡ ጨው የተጨመረበት መሬት ወና ይሆናል እንጂ እህል አያበቅልም። ጠላትን ድል ለማድረግ ኃይሉን አሳጥቶ፣ ሀብት ንብረቱን ወርሶ፣ አስጨንቆ ነውና መሬቱ ላይ ጨው በማድረግ መሬቱ እንዳያበቅል በማድረግ ይጠቀሙበታል። ሰለዚህ ሰዎች ጠላትን ድል ለማድረግ ከሚጠቀሙበት የጦር መሳሪያም አንዱ በመሆን ያገለግላል፡፡
ጨው የጠላት ድል መንሻ ሆኖ እንደሚያገለግል ሁሉ ካህናቱና የክህነት አገልግሎቱም ጠላት ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት ታላቅ መሣሪያ ነው። ኃጢአት ቢሠሩ ንስሓ ገብተው ዲያብሎስን ያሳፍሩበታል። በተረፈ ቄርሎስ እና በውዳሴ ማርያም ትርጓሜ እንደተገለጸው እኩይ ፍልስጣ ዕለት ዕለት እየተከታተለ የሚጽፈውን ኃጢአታችንን ካህናቱ ፊት ቀርበን ስንናዘዝ እንደ ቅርፊት እየተላጠ ይወድቅልናልና ምእመናን ድል ይነሱበታል። ክብሩም ለምእመናንም ሆነ ለካህናት የጠላት ድል መንሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ መሆኑ ነው። (ተረፈ ቄርሎስ ፲፱፥፩-፬)
የዓለሙ ብርሃን፡- የብርሃንን ምንነት በተመለከተ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለ መጽሐፋቸው “መምህር፣ አብነት፣ መፈክር፣ መተርጕም፣ ገልጦ የሚያስረዳ” በማለት ይገልጹትና አያይዘውም አብርሀ የሚለውን “አበራ፣ አስበራ፣ አሳየ፣ ገለጠ፣ አስረዳ” (ገጽ ፪፻፹፯) በማለት ያብራሩታል። ስለዚህ ካህን የዓለም ብርሃን ነው ሲባል በጨለማ፣ በድንቁርና፣ ባለማወቅ ወዘተ የሚኖርን ሕዝብ ወደ ብርሃን የሚወስድ፣ ካለማወቅ ወደማወቅ የሚያሸጋግር ማለት ነው።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን ሲያስረዳን ለሐዋርያት የነገራቸው “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም። ከእንቅብ በታች ሊያኖሯት መብራትን አያኖሩም፤ በመቅረዝዋ ላይ አኑረዋት በቤት ላሉት ሁሉ ታበራለች እንጂ። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ.፭፥፲፬-፲፮) በማለት ነው። በድንቁርና ዓለም ለሚኖረው ዕውቀትን፣ ባለማወቅ ጨለማ ለተዋጠው ብርሃን ትሆኑታላችሁ ሲል ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መሻገሪያ የሚሆኑበትን ሥልጣነ ክህነት ሰጣቸው።
ትልቁ ክብር የሚባለውም ይህ ነው። መብራት እንደሚታወቀው ራሱ እየቀለጠ፣ በእሳት እየነደደ ለሰው ግን ብርሃኑን ይለግሳል። ካህናት ሥራቸው ለራሳቸው ምድራዊና ጊዜያዊ ጥቅም ሳይኖራቸው ራሳቸውን በተጋድሎና በመከራ እያኖሩ ሰውን ግን ወደ መንግሥተ ሰማያት ማስገባት ነው። ሰውን ከማዳን ፣ ሰውን ከጨለማ ወደ ብርሃን ከማሸጋገር፣ ለሰው ምክንያተ ድኅነት ከመሆን በላይ ክብር ስለሌለ አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያከበራቸው በእንደዚህ ያለው ሀብትና ጸጋ ነው።
የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች፡- ካህናት የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች፣ እንዲሁም አዕይንተ እግዚአብሔር ተብለዋል። “የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው ዐይንህ ብሩ ከሆነ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ነው፤ ዐይንህ ታማሚ ቢሆን ግን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ነው።“ (ሉቃ.፲፩፥፴፬) በማለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረው ካህናት የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች ናቸው ሲባል ምን ያህል ታላቅ ክብር እንዳላቸው እንድንረዳ ነው።
የሰውነት ክፍሎቻችን እርስ በእርሳቸው ተረዳድተው ይኖራሉ አንዱ ያለ አንዱ መኖር አይችልም። አንዱ ሌላውን አልፈልግም ሊል አይችልም። የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን ብዙ የአካል ብልቶች አሏት። ለሰውነት ክፍሎቻችን ብርሃኑ ዐይን እንደሆነ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍሎችም ካህናት ዐይኖች ናቸው። ለዚህ ነው የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች በማለት ሊቁ የገለጻቸው።
የቤተ ክርስቲያን መብራት፡- በጸሎተ ቅዳሴያችን “ተውህቦ መራኁት ለአቡነ ጴጥሮስ ወድንግልና ለዮሐንስ ወመልእክት ለአቡነ ጳውሎስ እስመ ውእቱ ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን፤ ለጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ተሰጠው፤ ለዮሐንስ ደግሞ ድንግልና ተሰጠው፤ ለጳውሎስም መልእክት ተሰጠው የቤተ ክርስቲያን መብራት ነውና” ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። በጸናውና በጎላው ሲነገር ይኖራል። ቅዱስ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ፣ ለቅዱስ የሐንስ ድንግልናን፣ ለቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ መልእክት ተሰጣቸው እያለች ቤተ ክርስቲያን በእያንዳንዳቸው ጎልቶ የሚታየውን አገልግሎት በማንሣት ስታመሰግናቸው ትኖራለች። የሐዋርያት ተከታይ የሆኑት ካህናትም በዚህ ድንቅና ግሩም አገልግሎታቸው የቤተ ክርስቲያን መብራት ተብለዋል።
የመላእክት አምሳል፡- ካህናት ለመላእክትም ያልተሰጣቸውን ልዩ የአገልግሎት ጸጋ እንደተሰጣቸው ከላይ ተመልክተናል። እንዲሁ በዚህም ክፍል ላይ ሊቁ የመላእክት አምሳል በሏቸዋልና የሰውን ልጅ ወደ እግዚአብሔር በማድረስና ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ አገልግሎት የሚኖሩ ስለሆኑ እንደ መላእክት ናቸው ተብለዋል። ክብር ማለት ደግሞ ይህ ነው ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ግን የመላእክት አምሳል መባል ታላቅ ክብር ነውና።
ከላይ የተዘረዘሩት የካህናትንና የክህነት አገልግሎትን እጅግ ክቡርነት የሚያስረዱን ናቸው። ጉዳዩን በጥልቀት እንድንረዳው ይረዳን ዘንድ ተጨማሪ ማስረጃ ከሊቃውንትም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት። ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በሃይማኖተ አበው “የካህኑን ምክሩን፣ ትእዛዙን፣ ተግሣጹን አንሰቀቅ፤ ነፍስን የሚያድን ባለመድኃኒት ነውና፤ የነፍስን ደዌ የሚያርቅ ይቅርና የሥጋ በሽታ የሚያድን ባለመድኃኒትስ ወደ ሥጋዊ በሽተኛ በመጣ ጊዜ ለመድኃኒቱ ከማይስማሙ ምግቦችን ከመመገብ ይከለከል ዘንድ ያዝዘዋል፤ መራራ መራራ ቅጠልን ፣ምረቱ ጭንቅ ሽታው ክፉ የሚሆን ከብዙ ወገን የተቀመመ መድኃኒትን ያጠጣዋል፡፡ በድውዩ አካል የተለያየ ሕዋሳትን አንድ ያደርግለት ዘንድ፡፡ (ሃ.አበ.፴፯፥፫)
ምእመናኑ ለካህናት የሚኖራቸው ክብር እጅግ ከፍተኛ መሆን እንዳለባቸው የሚያስረዳን ነው። ይህ ባይሆን ግን ቅጣት እንደሚያስከትል በመጽሐፍ ቅዱስ በተመዘገቡ ታሪኮች መረዳት እንችላለን። ለማሳያ ያህል የተወሰኑትን እንመልከት።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “ስለዚህ እላችኋለሁ ለሰው ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ ግን አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገር ግን በዚህ ዓለምም ቢሆን በሚመጣውም ዓለም ቢሆን አይሰረይለትም” (ማቴ.፲፪፥፴፩-፴፪) በማለት አስተምሯል። ይህ ቃል በድጋሚ “በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለምም ቢሆን በሚመጣው ዓለምም አይሰረይለትም” (ሉቃ.፲፪፥፲) ተብሎ ተጠቅሶ እናገኘዋለን።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ክፍለ ምንባቦች በብዙ መንገድ የሚተረጎሙ ናቸው።
የመጀመሪያው ትርጓሜ የሰውን ልጅ የሰደበ ማለት ወልድን ዕሩቅ ብእሲ ያለ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን ዕሩቅ ብእሲ ያለ ግን አይሰረይለትም ማለት ነው። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የኃጢአቱን ክብደት ለማነጻጸር እንጂ ይቅር የማይባል ኃጢያት አለ ማለት አይደለም። ኃጢአቱንም ያበላለጠበት ምክንያት ወልድን ምንም እንኳ እንዲህ ማለት ይገባል ማለት ባይሆንም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ስለታየ ምክንያት አላቸው መንፈስ ቅዱስን ግን ዕሩቅ ብእሲ ለማለት ምንም ምክንያት የለምና። ሰውን እንኳ በምክንያት መስደብ አግባብ ባይሆንም ያለምክንያት መስደብ እጅግ ኃጢያት ነው። ስለዚህ ኃጢያቱን ከኃጢያት እያከበደ የሚያስተምረን እኛ እንድንረዳው ነው።
እንደዚሁ ሁሉ በቀጥታ ከያዝነው ርእሰ ጉዳይ ጋር የሚገናኘውን ትርጓሜ ለማንሣት ያህል ምእመንን የሰደበ ይሰረይለታል፤ ካህንን የሰደበ ግን አይሰረይለትም ማለት ነው። እንዲህ ያለበት ምክንያት በፍጹም ስርየተ ኃጢያት የለም ማለት አይደለም የኃጢያቱን ክብደት ለመግለጽ እንጂ። ይህም የክህነትን እጅግ የከበረ ሥልጣንነት ያስረዳል። በሚታየው ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ሥልጣን ሰጥቷቸዋልና ካህናት ሊከበሩ ይገባል ሲለን ነው።
በትንቢተ ኢሳይያስ በትርጓሜው ተጽፎ እንደምናገኘው በንጉሡ በዖዝያን ዘመን ካህኑ አዛርያስ ከንጉሡ ቀኝ እየተቀመጠ ፍርዱን ይገሥበታል (ይሽርበታል)። በዚህ ጊዜ ለምን ትገሥብኛለህ? ብሎ ሲጠይቀው “እምቤተ መንግሥት የዐቢ ክህነት፤ ከቤተ መንግሥት ክህነት ይበልጣል” ይልብሀልና ይገባኛል በማለት ይመልስለታል። በዚህ ጊዜ ንጉሡ በአባቴ ከቤተ መንግሥት ብወለድ በእናቴ ከቤተ ክህነት እወለድ የለምን? በማለት ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ሊያጥን ገባ። ልምፅ ወጣበት፤ ከቤተ መቅስ አስወጥተው በአይሁድ ባህል ለምፃም ለንግሥና አይሆንም ነበርና ከከተማ አውጥተው በግዞት ድውያን ከሚኖሩበት ቦታ አስቀመጡት። በዚህ ጊዜ በዘመኑ የነበረው ነቢይ ኢሳይያስ ሳይገሥጽ በመቅረቱ በእርሱም ላይ ለምፅ ወጣበት፤ ሀብተ ትንቢቱም ተነሣው። (ኢሳ. ፮፥፩ አንድምታ ትርጓሜ)
በአጠቃላይ የምድር ጨው፣ የዓለሙ ብርሃን፣ የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች፣ የመላእክት አምሳል ወዘተ መባል ምንም እንኳ ክብሩ ሲበዛ ኃላፊነቱም እንዲሁ የሚበዛ ቢሆንም እጅግ የተለየ ክብር ማግኘት ነው። በዚህ ዓለም ስንኖር ጨው፣ ብርሃን፣ ዓይን ምን ዓይነት አገልግሎትና ጠቀሜታ እንዳላቸው መረዳት ቀላል አይደለም። ለሰውነታችንም እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው። ካህናትም እንዲሁ ከእግዚአብሔር አምላካችን ከምናገኘው ልጅነት ጀምሮ ተስፋ የምናደርጋትን መንግሥተ ሰማያትን እስከ መውረስ ድረስ በሚኖረን ህልውና እጅግ ወሳኝና አስፈላጊዎቻችን ናቸው። ይህ ማለት መንግሥተ ሰማያትን ከወረስን በኋላ አገልግሎታቸውና ክብራቸው ያበቃለታል ማለት አይደለም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንደገለጸውና ከላይም እንደጠቀስነው አገልግሎታቸው ሰማያዊ ነውና የሚያልፍ አገልግሎት የላቸውም። ስለዚህ ምንም እንኳን የካህናትንም ሆነ የክህነቱን ክብር በዚህ አጭር ጽሑፍ አጠናቅቆ መግለጽ ይቻላል ባይባልም በጥቂቱም ቢሆን እንድንረዳው በዚህ መንገድ ተመልክተነዋል። በሚቀጥለው ኃላፊነቱን በተመለከተ እንመለከታለን እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ሰጥቶ ቀጣዩን ለማየት ያብቃን አሜን።
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1178
በአውግስጦስ ዘመነ መንግሥትና በወንድሙ በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን በሉቅያኖስ ሥልጣን በዚያ ወራት ኤጌዎን በተባለች ሀገር የክርስቲያኖች ስደት ሆነ። አንድ ቆስጠንጢኖስ የተባለ ጸሐፊ ንጉሡን አቤቱ ሆይ ባይስ በተባለ ሀገር አንድ ሰው አለ አባቱም ታላቅ ሰው ነው እናቱም እንዲሁ ሥርዓታቸውም የተለየ ነው። ከየት እንደሆኑ አናውቅም ነገር ግን ክርስቲያኖች እንደሆኑ እንገምታለን አለው።
ዳግመኛም አረማውያንን ወደ ክርስትና ይመልሷቸዋል፤ ወፍ ሳይጮኽ በሌሊትም ያስወጧቸዋል በዕለቱም ብዙዎች ወደ እነርሱ ይሄዳሉ ክርስቲያንም ይሆናሉ። አሁንም ከግዛታቸው አስረው ያመጧቸው ዘንድ ጠንካራ ሰዎችን ላክ አሉት። ገዢውም አጳርጎሪስን ጥሩት አለ። ወታደሮቹም ከዚህ ቁሟል አሉት ገዢውም ብርቱ ሰዎችን ላክ የሚያሳያቸውን ይያዙና አስረው ወደእኔ ያምጧቸው እንቢ የሚል ካለ እናቱም ካለቀሰች እርሷንም አስራችሁ አምጧት አለ።
ወታደሮችም እንደታዘዙት ዚኖቢስንና ዚኖቢያን አመጡለት። ገዢውም ዚኖቢስን ሥርዓትህ ምንድን ነው? ወገንህስ ከማን ነው? ይህን የምታደርግ አንተ ሀገርህስ የት ነው? ዓለምን ታስታለህ በዚህ ሀገር የሚኖሩትን ሰዎችም ክርስቲያንም ታደርጋቸዋለህና አለው።
ዚኖቢስም ሃይማኖቴን ማወቅ ከፈለግህ ክርስቲያን ነኝ። በሁሉም የምታወቅበት ስሜም ዚኖቢስ ነው። ገዢ ነበርሁ። ከዚህም በኋላ ስደት ሆነና ተሰደድን ወዳጆችም አሉኝ፤ በሮም ሀገርም የሚያውቁኝ አሉ፤ ከዚህ እንድሄድም አሰብሁ ከዚህ በኋላም መንፈስ ቅዱስ አደረብኝ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አመንሁ ለዘለዓለሙ ይድኑ ዘንድም ብዙዎች ተሰበሰቡ ሁሉም ክርስቲያን ይሆኑ ነበር። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ማዕተብ /ምልክትም/ ይወስዱ ነበር። መንፈቀ ሌሊት በሚሆንበት ጊዜም ሂዱ እላቸዋለሁ ይሄዳሉ። ዳግመኛም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ ምእመናን ሆይ የተቀደሰ ሰማያዊ አክሊልንና መንግሥቱን ለማግኘት ስለ እርሱ እንጋደልና እንሞት ዘንድ ሁላችሁም ኑ በማለት እጠራቸዋለሁ። ለዚህ ከባድ ተጋድሎም ይሰበሰባሉ አለው።
ወገኔንና አባቴን ማን እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግህ የአባቴ ስም ሜኖፊሎስ የእናቴ ስምም ዚኖቢያ ይባላል የወንድሜ ስምም ኔዎን ይባላል እርሱም አናጉንስጢስነት ተሹሟል፤ ክርስቶስንም አመስግኗል፤ እርሱም ከእኛ ጋር አለ የወደድከውንም አድርግ አንተ በአጋንንት ዘንድም ትመራመራለህ አለው። ገዢውም ሽማግሌ ነህና አፍርሃለሁ፤ እናትህ ታላቅና ባልቴት ናትና አፍራለሁ አለው። መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ዚኖቢስና ዚኖቢያም እኛስ ስላንተ እናዝናለን ለዘለዓለሙ ትጠፋለህና አሉት። ገዢውም ፈጽሞ ተቆጣ፤ ልብሷን አውልቁና በራስ ፀጉሯ ስቀሏት፤ ይህንም ልብሱን አውልቁና ራቁቱን ስቀሉት፤ ዛሬም አያፍሩም እሺም አይሉምና አለ። በብትር ይመቷቸው ዘንድም አዘዘ።
ሲመቷቸውም ምንም አልተናገሩም ዚኖቢስና ዚኖቢያም እንዲህ እያሉ ጸለዩ ለሁሉም ክብርን የምታጎናጽፋቸው አቤቱ የሰማይና የምድር አምላክ ሆይ እኔንም አልብሰኝ አለች ያን ጊዜም ዚኖቢያ ሰፊ የሆነ ወርቀ ዘቦ ልብስን ተጎናጽፋለች ራሷም እንደንግሥት ተሸለመች የዚኖቢስ ልብስም ነጭ ነበር ገዢውም እንደ አገልጋይ ወንበር ተሸክሞ በዚኖቢስ ኋላ ይከተል ነበር ሕዝቡን በተመለከተ ጊዜም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አበራልን፤ የእርሱን ስምም ወደማወቅ አመጣን እያለ ጮኸ።
ከዚህም በኋላ ገዢው ወደ ዙፋኑ በተመለሰ ጊዜ ፈጽሞ ተቈጣ። እነዚህን ምን ታደርጋቸዋለህ የክርስቲያኖች አምላካቸው ብርቱ ነውና። ዚኖቢስና ዚኖብያም በአማልክትህ ምክንያት እንዴት ትስታለህ ዓለምንና የሚክዱትን ሁሉ ማጥፋት የሚቻለው እግዚአብሔርን ክደኸዋል አሉት። ከዚህ በኋላም ገዢው ፈጽሞ ተቈጣ ለየራሳቸው ትሰቅሏቸው ዘንድ ሁለት መስቀሎችን አዘጋጁ። አንዱ አንዱን እንዲያየውም እስከ ሁለት ሰዓት ተያዩ፤ እንደሚተያዩ አድርገውም ሰቀሏቸው፤ ከሰማይም ደመና መጣና ጋረዳቸው ምግብም ሰጣቸው።
በነጋተውም ገዢው መጣ ተቀምጠው የእግዚብሔርን ቃል እያስተማሩም አገኛቸው። የሚሰሟቸውና አምነው የሚድኑትም ብዙዎች ነበሩ። ያላመኑትም ለዘለዓለሙ ጠፉ፤ እነዚህን ምን ላድርግላቸው እነሆ ታላላቅ ተአምራትን ያደርጋሉና አለ። ዚኖቢስም አጋንንት እንዴት እንደሚያስቱህ አስተውል አለው። ገዢውም እንዴት እንደሚያሳስቱኝ ንገሩኝ አላቸው።
ዚኖቢስና ዚኖቢያም ኃያልና ጽኑ የምትሆን እግዚአብሔር አምላክ ሆይ የአምላክነትህን ጸጋ በሰዎች የምታሳድር፤ ውኃውን ለውጠህ ወይን የምታደርገው አንተ ነህ። ሰውንም ወደ ሃይማኖት ትመልሳለህ። አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ ርኩስና ክፉ መንፈስን አስወግደው። ለሰው ልጆችም አንተ ብቻ እንደሆህ ከአንተ ብቻ በስተቀርም ሌላ አምላክ እንደሌለ ግለጥ አሉ።
ዚኖቢስና ዚኖቢያ ከጸለዩ በኋላም ይህ መንፈስ ርኩስ እንደ ሰው ሆነ፤ ፊቱም ሁለት ነበር። በአፉ ውስጥ እሳት ይወጣ ነበር፤ ከዚህ በኋላ ይህ ርኩስ መንፈስ ተወገደ፤ ገዢውንም ለቀቀው፤ ገዢውም ጮኸ። አጋንንት እንደሚያስቱኝ አውቃለሁ አለ። አሕዛብም በአንድነት የክርስቲያኖች አምላክ ታላቅ እንደሆነ እናምናለን፤ የሚያምኑበትም ሁሉ እንደሚድኑበት እናምናለን እያሉ በአንድ ድምፅ ጮኹ።
ገዢው ተቆጣ። ከዚህ በኋላም ሁለት የብረት ወንበሮችንና ሁለት የብረት ጦሮችን አምጡ፤ አስራችሁም ከእሳት ጨምሯቸው ስትመቷቸውም ለአማልክት ሠዉ በሏቸው የአደሮ ማርና ዘይቱ ሲፈላም በእነርሱ ላይ ጨምሩት አላቸው።
ዚኖቢስና ዚኖቢያም እግዚአብሔር ኃያል ብርቱም ነው። አሁንም ቅዱስ ሆይ ጠብቀን ይቅርም በለን፤ በቅዱስ መንፈስህም ሥቃይን ሁሉ ከእኛ አስወግድ አሉ። ዚኖቢስና ዚኖቢያ ከጸለዩ በኋላም ይህ የብረት ጦር እንደ ደረቅ የእንጨት በትር ሆነ።
የእግዚአብሔር ቅዱሳንም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ፊታቸውን አማተቡ፤ ተነሡና ተቀመጡ፤ ጳውሎስ እንዳስተማረውም የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምሩ ጀመር። አሕዛብም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ነው ዛሬም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ዚኖቢስንና ዚኖቢያን ከዚህ ሁሉ ሥቃይ ያነሣ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታን እናመስግነው አሉ።
ዚኖቢስም ቆሞ ያመናችሁ ሁላችሁ ኑ፤ ከእኔ ጋርም ለእግዚአብሔር እንጋደል በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በማመንም ሰማያዊውን አክሊል እናገኝ ዘንድ እንጋደል እያለ ይጣራ ነበር። የሰሙና በቅዱሳኑ ላይ እግዚአብሔር ያደረገውን ተአምር የተመለከቱ ሁሉም እየሮጡ ይመጡ ነበር። በአብ በልድና በመንፈስ ቅዱስም ያመኑ ነበሩ ዳኑም። ገዢውም ከመመለስ ይልቅ በክፋቱ እየጸና ሄደ። ዐሥር ክንድ ያህል ከፍታ ያለው እሳት አስነድዶም በዚያ እንዲጣሉ አደረገ።
ዚኖቢስና ዚኖቢያም ዘመናትን ዓመታትን የምታፈራርቅ አንተ ነህ። ለሰው ልጆች ተአምርህን ግለጥ፤ ይህን እሳት ነበልባሉንም አቀዝቅዘው ገዢውንም መልሰው በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ። ዚኖቢስና ዚኖቢያም ከጸለዩ በኋላ እንደ ትንሽ መታጠቢያ ቤት ሆነ፤ ገዢውም የመታጠቢያ ቤት ጠባቂ ሆነ። ውኃን የመላ ማሰሮ ይዞ ነበር።
ዚኖቢስና ዚኖቢያም እግአብሔርን ፈጽመው ያመሰግኑት ጀመር። በቅዱሳን አድሮ ተአምራትን የሚያደርግ እግዚአብሔር ቡሩክ ነው አሉ። ገዢውም ወደቤቱ ሄደ፤ በዚያም ፊቱ ሁለት የሆነ ሰው አገኘ። ይህም ክፉ ርኩስ መንፈስ ነው። ገዢውም በአንተ ምክንያት እንሳሳታለን እንጠፋለንም አለው። ጠራውና ተፋበት።
ከዚህም በኋላ ገዢው ዳግመኛ ከዙፋኑ ተቀመጠ። እነዚህን ጎስቋሎች ጥሯቸውና አስቀምጧቸው አለ። ወታደሮቹም አቤቱ እነሆ በፍርድ አደባባይህ ፊት አሉ አሉት። ከዚህ በኋላ ሁሉም ሰዎች የእግዚአብሔር ኃይሉ ታላቅ ነው እያሉ ጮሁ። ገዢውም ለታላቁ አምላክ ለባኪና ለዲዮንስዮስ ቅረቡና ሠዉ አለ። ዚኖቢስም እነዚህ አማልክት ምንም እንዳልሆኑ እንደሚሰጠሙም አታውቅምን አለው።
ዚኖቢስና ዚኖቢያም ጸለዩ ሁለት የምስል አማልክትም ተሰጠሙ የነበሩበት ቦታም ምድረ በዳ እንደሆነ የአትክልት ቦታ ሆነ። ዚኖቢስና ዚኖቢያም አሰምተው ተናገሩ ገዢውንም አማልክቶችህ የት አሉ አሉት እነሆም እርሱ ብቻ አምላክ የሆነ እግዚአብሔርን ክደኸው እነርሱም እነሆ ጠፉ ምን ትላለህ ከእንግዲህ ወዲህ በምን አምላክ ታመልካለህ አሉት።
ሕዝቡም አሰምተው ተናገሩ፤ እነሆ ዛሬ የክርስቲያኖች አምላክ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ተረድተናል አሉ። ገዢውም ተናደደ፤ ውሰዷቸውና ግደሏቸው አርቃችሁም ጣሏቸው። ነገ በእሳት አቃጥላቸው ዘንድም በድናቸውን ጠብቁ አላቸው። ይዘውም ገደሏቸው፤ በሚገድሏቸው ጊዜም ነጎድጓድና መብረቅ ብልጭታም ሆነ። በመደንገጥም አምስት መቶ ሰዎች ሴቶችም ወንዶችም ሞቱ።
ሲመሽም ከምእመናን ወገን በሌሊት መጡ በድናቸውንም ወሰዱ ሁለት መቃብርም ቆፍረው በሰቀሉባቸው ቦታ ሁለቱንም ጎን ለጎን ቀበሯቸው። በማግስቱም ገዢው በአደባባዩ ተቀመጠ። በእሳት እናቃጥል ዘንድ የእነዚያን ሰዎች በድን አምጡ አላቸው ወታደሮችም አቤቱ ምሽት በሆነ ጊዜ ነጎድጓድ ብልጭልጭታ፣ መብረቅና ብዙ ጎርፍም ሆነ። ዳግመኛም በመንፈቀ ሌሊትም እንደ መብረቅ ያለ ተመለከትን በቤታችንም ድምፁን ሰማን አሉት።
ገዢውም ይህን ተአምር በሰማ ጊዜ እኔም ክርስቲያን መሆን እሻለሁ አለ ይህ ገዢና ወታደሮቹም ሁሉ አመኑ።
ተጋድሏቸውም በኤጌዎን ሀገር ሉቅያኖስም የአሕዛብ አለቃ ሳለ፤ አውግስጦስ በተባለው በቀላውዴዎስ ዘመን ነው።
የቅዱሳኑ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።
(ምንጭ ገድለ ሰማዕታት ቅጽ ፩)
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1620
የቃሉ ተናጋሪ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፡፡ ቃሉን የተናገረበት ምክንያትም እንዲህ ነው፡፡ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ልምሾ ሆኖ የተወለደ በቤተ መቅደስ በር ላይ ተቀምጦ ምጽዋት የሚለምን አንድ ሰው ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ በበሩ ላይ ተቀምጦ ሳለ አያቸውና ምጽዋት ለመናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ “ወደእኛ ተመልከት አለው፡፡ ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጽዋት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡” ጴጥሮስም “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው ያን ጊዜም እግሩና ቊርጭምጭሚቱ ጸንቶለት ቆሞ እየሮጠ ተራመደ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደቤተ መቅደስ ገባ፡፡
በዚህ ታሪክ ሰውየው ከተቀመጠበት ቦታ፣ ሰውየው ከሚፈልገው ነገር፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ከተናገራቸው ንግግሮች፣ እንዲሁ ለሰውየው ካደረገለት መልካም ነገር በመነሣት ልንማረው የሚገባንን መሠረታዊ ትምህርት አንድ በአንድ ለመመልከት እንሞክር፡፡
ምን እንማራለን
ከሰውየው ፡- ሰውየው ከታሪኩ መረዳት እንደቻልነው ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ልምሾ የሆነ ነው፤ በቤተ መቅደስ በር ላይ ሰዎች እየወሰዱት ልመና የሚያከናውን ነው፤ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት ከደዌው የተፈወሰ ነው፡፡ ስለዚህ ልንማረው የምንችለው ነገር በመጀመሪያ፡-
በቤተ መቅደስ በር መቀመጥ
ይህ ሰው ችግሮቹ የተደራረቡ ናቸው፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር ለመለመን ተጨማሪ ልመና ማድረግ አለበት፡፡ ምን ማለት ነው ለልብሱ ለጉርሱ የሚሆን ለማግኘት ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ሽባ በመሆኑ ሠርቶ መብላት አይችልም፡፡ ስለዚህ ያለው ብቸኛ አማራጭ ደግሞ መለመን ነው፡፡ ለመለመን ደግሞ ሰው የሚገኝበትና ምቹ የሆነ ቦታ መሄድ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም መሄድ የማይችል ልምሾ ስለሆነ የሚወስደው ሰው መኖር አለበት፡፡ ይህ ነው የተደራረቡ ችግሮችና ለልመናም ሌላኛ ልመና ማድረግ የግድ የሚያደርገው፡፡
ይሁን እንጂ በሰዎቹ እርዳታ ሰው ከሚበዛበት ምቹ ቦታ ላይ እየሄደ ይለምን ነበር፡፡ ይህ ምቹ ቦታ ደግሞ በወቅቱ የቤተ መቅደሱ በር ነበር፡፡ ይህ በወቅቱ ለሰውየው ምቹ ቦታ የነበረው ቤተ መቅደስ ዛሬም የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ ከእግዚአብሔር ለመጠየቅና ችግራችንን ለመንገር በቤተ መቅደሱ በር መቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በአለንበት ዘመንም ለሰዎች ርኅራኄ የሚሰበክበት፣ ሰው ለመስጠት ልቡናው የሚራራበት፣ ውስጡ የሚነካበትና ለመስጠት ፈቃደኛ የሚሆንባት ቦታ ቤተ ክርስቲያን ናትና በርካታ ችግረኞች ተቀምጠው የዕለት ጉርሳቸውን ይለምኑባታል፡፡
የተቸገሩት ሰዎች ለሥጋቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንደሚጠለሉ ሁሉ መንፈሳዊ ችግራቸውን ለመፍታትም ቤተ መቅደሷ፣ ቤተ ክርስቲያኗ መተኪያ የሌላት ተመራጭ ቦታ ናት፡፡ ለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” (መዝ.፻፳፩፥፩) በማለት ያስረዳን፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ ያለው ችግሮቹ ሁሉ ስለሚፈቱለት ነው፡፡ እኛም የነቢዩን የዳዊትን የትንቢት ቃልና የዚህን የችግረኛ መንገድ የምንከተል ከሆነ ችግራችን በሙሉ ሊፈታ የሚችለው ከቤተ ክርስቲያን በር ስንቀመጥና ችግራችንን ለሚመለከተው አካል ስንናገር ነው፡፡
ችግረኛው ከቤተ መቅደሱ በር ላይ በመቀመጡ ብርና ወርቅ ከሚሰጡት ሰዎች ባሻገር ከደዌው ፈውሰው ዘላቂ መፍትሔ የሚያስገኙለትን ሐዋርያትን አገኛቸው፡፡ እኛም ወደቤተ ክርስቲያን ብንመላለስ ከነፍስም ከሥጋም ቁስል የሚፈውሱንን ካህናትን እናገኛለን፡፡ ከሥጋችን ቁስል ብቻ ሳይሆን ከነፍሳችን ቁስል ተፈውሰን እንደበሽተኛው እግዚአብሔርን እያመሰገንን በሰላም ወደቤታችን እንመለሳለን፡፡
ለምኖ ማግኘት (ጥቂት ለምኖ ብዙ ማግኘት)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከት ላይ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ “ለምኑ ይሰጣችኋልም፤ ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋልም፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልግም ያገኛልና ደጅ ለሚመታም ይከፈትለታልና፡፡” (ማቴ.፯፥፯-፰) የሚል ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ ሰው የፈለገውን እንደሚያገኝ በማመን ከቤተ መቅደሱ በር ላይ ተቀምጦ ይለምን ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምኑ ብቻ ሳይሆን ከምንለምነው በላይ አብዝቶ አትረፍርፎ እንደሚሰጠንም ነግሮናል፡፡ በዚህ መሠረት ይህ ችግረኛ እርሱ ከለመነው በላይ አግኝቷል፡፡ ምክንያቱም እርሱ የለመነው ጊዜያዊ ወርቅና ብር ነው ሐዋርያት ግን ጤንነትን፣ ፈውስን በነጻነት እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲመላለስ አደረጉት፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ሰጭ እርሱ እንደሆነ አምነን እርሱን እንድንለምን መልካም ፈቃዱ ነው፡፡ እርሱም ለምነነው እንደማያሳፍረን ይልቁንም አብዝቶና አትረፍርፎ እንደሚሰጠን በማይታበል ቃሉ ነግሮናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም ይህን ሲያስረዳ “ጥበብን ያጣት ሰው ቢኖር ሳይነቅፍና ሳይነፍግ ለሁሉ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል፡፡” በማለት ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር ሰጭ እንደሆነ አምኖ ለሚለምነው ሁሉ ሳይነቅፍና ሳይነፍግ የሚሰጥ መሆኑን የተረዳው ሐዋርያ አምኖ እግዚአብሔርን ይለምን አለን፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ የእርሱ ገንዘቡ ነውና ሀብታም ድሃ፣ ነጭ ጥቁር፣ ዘር ቀለም አይለይም፡፡ ለሚያምኑት ሁሉ የለመኑትን ያድላቸዋል፡፡ የለመኑትን ብቻ ሳይሆን አብዝቶና አትረፍርፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ለምኖ ማግኘትን ብቻም ሳይሆን ጥቂት ለምኖ ብዙ ማግኘትንም ከአባቶቻችን ሕይወት እንማራለን፡፡ ለማስረጃ ያህል የተወሰኑትን እንጥቀስ፡፡
ዳዊት ፡- ዳዊት እንደልቤ የተባለ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኘ ታላቅ አባት ነው፡፡ በሰውነቱ ቢበድልም ፈጥኖ ወደ ንስሓ የተመለሰና በንስሓ ሕይወቱም አብነት የሚደረግ ሰው ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቅርብ ከመሆኑ የተነሣ ጥቂት ነገር ለምኖ ብዙ ያገኘ አባት ነው፡፡ ዳዊት የለመነውንና የልመናው ምላሽ ሁኖ የተሰጠውን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፡፡
“አቤቱ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤ ለእግዚአብሔር እንደማለ፣ ለያዕቆብ አምላክም እንደተሳለ፤ ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም ወደ መኝታዬም አልጋ አልወጣም፤ ለዐይኖቼም መኝታን ለቅንድቦቼም እንቅልፍን ለጉንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም የእግዚአብሔርን ቦታ የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ እንደተሳለ ዐስብ፡፡ እነሆ በኤፍራታ ሰማነው ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንሰግዳለን” (መዝ.፻፴፩፥፩-፯) እንዲል፡፡
ዳዊት የለመነው ወደ ቤቴም አልገባም ብሎ የተሳለው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስቦ ነበር፡፡ ይህ ካልተፈቀደልኝ ወይም የእግዚአብሔርን ቦታ የያዕቆብን አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ አልተኛም ብሎ ነበር፡፡ ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ቤቱ እንዲሠራለት የፈቀደው በሌላ ሰው ቢሆንም ለእርሱ የተሰጠውና የተፈቀደለት ግን ከዚህ እጅግ የሚበልጠውን ነገር ነው፡፡ ይህ የሚበልጠው ነገርም ነገረ ሥጋዌ ነገረ ድኅነት ነው፡፡ ይህን ደግሞ የእግዚአብሔርን ቦታ የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ሲል የነበረው “እነሆ በኤፍራታ ሰማነው ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን” በማለት የተገለጸለትን ልዩ ምሥጢር እርሱም የምሥጢረ ሥጋዌ የነገረ ድኅነት ጉዳይ እንደሆነ የተናገረው ኃይለ ቃል ያስረዳናል፡፡
በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ፡- በእርግጥ ይህ በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ የለመነው ልመና ጥቂት የሚባል አልነበረም፡፡ እንዲያውም እኛ የዕለት ተዕለት ልመናችን ሊሆን የሚገባው የሰማያዊው ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ እንደ ፈያታዊ ዘየማን በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ ልንል ይገባናል፡፡ ፈያታዊ ዘየማን አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ ብሎ በቅን ልቡና በትሑት ሰብእና በተሰበረ ኅሊና ፈጣሪውን ሲጠይቅ የሚያስፈልገንን ሁሉ ሳንለምነው የሚያውቅና የሚያዘጋጅ እንዲሁ የሚያድለን አምላክ የመለሰለት መልስ ግን ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ የሚል ነበር፡፡ በመጀመሪያ ለማኙ የለመነው ነገር ከዚያም ደግሞ የተለመነው አምላክ የመለሰው ምላሽ እጅግ የሚገርም ነበር፡፡ ለማኙ የኋለኛውን ይጠይቃል ሰጪው ደግሞ ከአሁን ጀምሮ ነው እንጂ እስከኋለኛው ለምን ትጠብቃለህ በማለት መልሱን በቅጽበት መልሶለታል፡፡
ስለዚህ እኛም በእምነት ሁነን ስንለምነው እኛ ከለመነው በላይ የተሻለ፣ ጊዜያዊውን ሳይሆን ዘለዓለማዊውን፣ ሥጋዊውን ሳይሆን መንፈሳዊውን ሀብት ያድለናል፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ያዕቆብ “አምኖ ይለምን፤ አይጠራጠር፤ የሚጠራጠር በነፋስ የሚገፋና የሚነዋወጥ የባሕር ማዕበልን ይመስላልና” (ያዕ.፩፥፮) በማለት እንደተናገረው የሰው ልጅ ያለምንም ጥርጥር የፈለገውን መለመን ይኖርበታል፡፡
ከቅዱስ ጴጥሮስ ምን እንማራለን፡- ቅዱስ ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ ከመንገድ ላይ ተቀምጦ ወርቅ ብር የሚለምነውን ሰው አገኙት፡፡ በዚህ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ መሄዳቸው፤ እኛም ዛሬ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ጸሎት ማድረግ እንደሚገባን የሚያስረዳን ነው፡፡ ምክንያቱም ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት ወደቤተ መቅደስ ወጡ ብሎ ነው መጽሐፍ ቅዱሱ የሚያስረዳን፡፡ ስለዚህ የጊዜያት ጸሎትንም ሐዋርያት ያደርጉ እንደነበር እንረዳለን፡፡
የሚቀድመውን ማስቀደም
ሕመምተኛው የለመናቸው ወርቅና ብር ነበር፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ከወርቁና ከብሩም ሊሰጠው ከሚችለው ፈውስም በፊት መቅደም ያለበትን ነገር ነገረው፡፡ እርሱም ወደ እነርሱ እንዲመለከት ነበር፡፡ ወደነርሱ እንዲመለከት ማለት በእነርሱ ሃይማኖት እንዲያምን፡፡ እነርሱ የሚያምኑትን ሃይማኖት ካላመነ ሊሰጠው የሚችለው ነገር እውን አይሆንለትም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለችግረኛው የሚሰጠው ነገር ከነበረበት ሕመም መፈወስ ነው፡፡ ከዚህ ከነበረበት ሕመም ለመፈወስ ደግሞ የሚፈወሰው ሰው አስቀድሞ ማመን አለበት፡፡ ስለዚህ ወደእኛ ሃይማኖት ተመለስ አለና የሚቀድመውን ሃይማኖት አስተማረው፡፡
በዚህ የቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር ልንማረው የሚገባው ነገር ቢኖር ማንም ከምግባረ ነፍስም ከምግባረ ሥጋም በፊት ሊያውቀው፣ ሊረዳው፣ ገንዘብ ሊያደርገው የሚገባው ነገር ሃይማኖት እንደሆነ ነው፡፡ ተቀባዩ ብቻ ሳይሆን ሰጪውም ቢሆን አስቀድሞ ለተቸገሩት ሃይማኖትን ማስተማር እንደሚገባ ያስረዳል፡፡ ይህም በተራራው ስብከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብፁዓን መሓርያን፤ የሚራሩ ብፁዓን ናቸው” (ማቴ.፭፥፯) ብሎ ያስተማረውን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሦስት መንገድ ተርጉመውታል፡፡
የወንጌሉ ትርጓሜ እንዲህ ነው፡፡ የመጀመሪያው ምሕረት ሥጋዊ፡- ቀዶ ማልበስ፣ ቈርሶ ማጉረስ፣ ቢበድሉ ማሩኝታ ቢበደሉ ይቅርታ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ምሕረት መንፈሳዊ፡- ክፉውን ምግባር፣ በጎ ምግባር መስሎት ይዞት ሲኖር መክሮ አስተምህሮ ወደ በጎ ምግባር መመለስ ነው፡፡ ሦስተኛው ምሕረት ነፍሳዊ፡- ክፉውን ሃይማኖት በጎ ሃይማኖት መስሎት ይዞት ሲኖር መክሮ አስተምህሮ በጎውን ሃይማኖት ማስያዝ ነው፡፡ ብለው በትርጓሜ ወንጌል አብራርተውታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ያደረገው ከእነዚህ ከሦስቱ አንዱን ምሕረት ነፍሳዊን ነበር፡፡ ይህንም አስቀድሞ ወደ እኛ ተመልከት በማለት የእርሱን ሃይማኖት አስተማረው ከዚያ በኋላ ለበሽተኛው የሚገባውን ሐዋርያውም የሚችለውን አደረገለት፡፡
ማድረግ የሚችሉትንና የማይችሉትን መለየት
ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ አስቀድሞ በእጁ ያለውንና የሌለውን፣ ማድረግ የሚችለውንና የማይችለውን ጠንቅቆ አውቋል፡፡ ይህም “ወርቅና ብር የለኝም ካለኝ ግን እሰጥሃለሁ” በማለቱ ይታወቃል፡፡ ሐዋርያት ወርቅና ብር እንዳይኖራቸው ያደረገው ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ “በመቀነታችሁም ወርቅ ወይም ብር ወይም መሐልቅ አትያዙ፡፡ ለመንገድም ስልቻ፤ ወይም ሁለት ልብስ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋልና” (ማቴ.፲፥፱-፲) በማለት በተልእኳቸው ሁሉ ስንቅ ልብስ፣ ጫማ፣ ወርቅ፣ ብር ወዘተ የመሳሰለውን ሁሉ ካልያዝን ምን እንሆናለን እንዳይሉ አስተምሯቸዋል፡፡
ይህ እንዳትይዙ ያላቸው ነገር ለአገልግሎታቸው መሰናክል እንዳይሆንባቸው፡፡ ደግሞም በአጋንንት ላይ ሥልጣን እንደሰጣቸው፣ እባቡን ጊንጡን መጨበጥ እንደሚችሉ ጽኑዕ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋልና ለሚደረግላቸው ሁሉ ጥበቃ እነርሱ በያዙት ነገር የዳንን እንዳይመስላቸው የእርሱን አምላካዊ ጥበቃ በፍጹም እንዲረዱት መልካም ፈቃዱ ስለነበር ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ትምህርት መሠረት በማድረግ አገልግሎቱን የጀመረው ሐዋርያ ምን ማድረግ እንደሚችል ምን ማድረግ እንደማይችል ከተረዳ በኋላ በቀጥታ በሌለው ነገር አልተጨነቀም ማደረግ የሚችለውን ብቻ አደረገ፡፡
በሌለው ነገር አለመጨነቅ፡- ቅዱስ ጴጥሮስ አስቀድሞ በእጁ ያለውንና የሌለውን፣ ማድረግ የሚችለውንና የማይችለውን ጠንቅቆ ካወቀና ከተረዳ በኋላ እርሱ እጅ ላይ በሌለው ነገርና ሊወቀስበት በማይችለው ጉዳይ መጨነቅ አልፈለገም፡፡ ስለሆነም ሰውየው የሚፈልገው ወርቅና ብር ቢሆንም እርሱ ግን ወርቅና ብር የለኝም ካለኝ ግን እሰጥሃለሁ በማለት የእርሱ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት ተናገረ፡፡ ዛሬም “ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም” ይባላልና በሌለ ነገር ሳይጨነቁ ባለ ነገር ላይ ተመሥርቶ የሚገባውን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ባለን ነገር ላይ ተመሥርተን መልካም ሥራ እንድንሠራ ይጠብቅብናል እንጂ በሌለን ነገር አይጠይቀንም፡፡ የምንችለውን ባለማድረጋችን ግን ተጠያቂዎች ነን፡፡
ያለውን አለመንፈግ፡- አንዳንድ ሰው ያለውን መስጠት አይችልም በሌለውና ሊያደርገው በማይችለው ነገር ግን ይጨነቃል፡፡ ነገር ግን ለመስጠት መሠረቱ ፍላጎት ነው፡፡ የመስጠት ፍላጎት ያለው ሰው ከጥቂቱም ቢሆን ይሰጣል፡፡ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው አንዲት መበለት ካላት ነገር ሰጠች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ አመሰገናት፡፡
ደግሞ ሰው ያለ አንድ ስጦታ አልተፈጠረምና ያለውን ከሰጠ እግዚአብሔር እጅግ ይወድለታል፡፡ ሐዋርያት ወርቅ ብር የላቸውም ይሁን እንጂ ያላቸውን ነገር ከመስጠት ግን ወደኋላ አላሉም፡፡ ምን ነበራቸውና ከምናቸው ይሰጡ ነበር ቢባል መጽሐፍ ቅዱስ “ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ያወጧቸው ዘንድ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ ይፈውሱ ዘንድ በርኩሳን መናፍስት ላይ ሥልጣንን ሰጣቸው” ማቴ.፲፥፩) “ድውያንን ፈውሱ፤ ሙታንንም አንሡ፤ ለምጻሞችንም አንጹ፤ አጋንንትንም አውጡ፤ ያለ ዋጋ የተቀበላችሁትን ያለ ዋጋ ስጡ” (ማቴ.፲፥፰) በማለት የተሰጣቸውን ነገር ያስረዳናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ያለዋጋ የተቀበለው እንዲሁ ያለዋጋ እንዲሰጠው የታዘዘው ብዙ ጸጋ ነበረው፡፡ የተወሰኑትን እንኳን እንደማስረጃ ለመጥቀስ ሃይማኖትን ተቀብሏል፤ ክህነትን ተቀብሏል፤ ሀብተ ፈውስን ተቀብሏል፡፡ ከመንገድ ላይ ተቀምጦ ይለምን ለነበረው ችግረኛም ከእነዚህ ስጦታዎች ሁለቱን ሰጥቶታል፡፡ እነዚህም ስጦታዎች ሃይማኖትና ፈውስ ናቸው፡፡ አስቀድሞ ሃይማኖትን አስተማረው ከዚያም ባመነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲነሣና እንዲሄድ አደረገው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ከተከናወኑለት በኋላ ሰውየውም ያመነውንና የፈወሰውን አምላክ ከሐዋርያት ጋር እያመሰገነ ወደቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ብዙዎች ችግራቸው ከተፈጸመላቸው በኋላ ዙረው አይመለከቱም ይህ ሰውየ ግን የፈወሰውን አምላክ እያመሰገነ ወደቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ከበር ላይ ተቀምጦ ወርቅና ብር ይለምን የነበረው ችግረኛ ወደቤተ መቅደስ ገብቶ እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመረ፡፡
በዚህ ዘመን ዓለምን እያስጨነቀ ያለ ወረርሽኝ እንዲወገድልን ከአባቶች እንደቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጡትን ጸጋ ሳይነፍጉ መለገስ ይጠበቃል፡፡ ከምእመናንም አስቀድሞ ማመንና ከልብ መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን ልመናችንን፣ ጸሎታችንን፣ ጩኸታችንን ሁሉ ላይቀበልልንም ይችላል፡፡ ይህንም በእስራኤል ሕይወት መማር ይቻላል፡፡ ብዙ ጾመው፣ ብዙ ጸልየው፣ ብዙ ጩኸው ነገር ግን እነርሱ የጾሙት እግዚአብሔር በሚፈቅደው መንገድ ስላልነበረ እንደተነቀፈባቸው ነቢዩ ኢሳይያስ ጽፎት እናገኛለን፡፡ (ኢሳ. ፶፰፥፩-ፍጻሜ) የእኛም ጾምና ጸሎት፣ ጩኸታችን ሁሉ እንዳይነቀፍብን አስቀድመን ማድረግ የሚኖርብንን ልናደርግ ግድ ይላል፡፡
በአጠቃላይ ችግራችንን ለመፍታት አስቀድመን ወደቤተ መቅደስ መቅረብ ከዚያም የሐዋርያትን ቃል፣ የካህናትንና የመምህራንን ትምህርት መስማት፣ ርትዕት የሆነችውን የቅዱሳንን ሃይማኖት መከተል፣ ያስጨንቀን የነበረው ችግር ሲፈታልን ደግሞ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል፡፡ ለመምህራን ደግሞ አስቀድሞ እንደቅዱስ ጴጥሮስ መቅደም ያለበትን ነገር ማስቀደም፣ ሃይማኖትን መስበክ፣ እግዚአብሔርን እንዲያውቅ ማድረግ፣ ከዚያም የሚያስፈልገውን ነገር በተቻለ መልኩ ማሟላት ይገባል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ ሰውየው የሚበላው አጥቶ በራብ ሊሞት የተቃረበ ከሆነ ለማናገርና ሃይማኖትን ለማስተማርም እያሰቃየው ካለው የረኀብ ስሜት መውጣት ስላለበት አንገብጋቢ የሆነውን ችግር መመልከት ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለመምህራንም ጥበቡን ገልጾላቸው፤ ለችግረኞችም ችግራቸውን የሚፈታ አባት አድሏቸው ዕድሜ ልኩን ተደራራቢ ችግሮች ሲያስጨንቁት የነበረው በሽተኛ ባንዲት ቃል ከችግሩ እንደተገላገለና እግዚአብሔርን ለማመስገን እንደበቃ የእኛንም የዕለት ተዕለት ችግር እንዲያስወግድልን የእግዚአብሔር አምላካዊ ፈቃድ ይሁንልን አሜን፡፡
- Details
- Written by: እንዳለ ደምስስ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 2099
ቀኑ ለምሽት ተራውን እየለቀቀ ነው፡፡ ፀሐይ ከወደ መጥለቂያዋ የእሳት አሎሎ መስላ በሰከንዶች ልዩነት ከአድማስ ማዶ ቁልቁል ለመሸሸግ ትጣደፋለች፡፡ አክሊሉ አራት ኪሎ ከሚገኘው መሥሪያ ቤቱ ወጥቶ በቀጥታ ያመራው ሲኤምሲ ቅዱስ ሚካኤል ጀርባ ካለው መኖሪያ ቤቱ ነው፡፡
ጠዋት ከቤት ከመውጣቱ በፊት ልጁ ናሆም የጠየቀው ጥያቄ ጤናማ ጥያቄ ነው ብሎ ማመን ቸግሮት ዕረፍት ሲነሣው ውሏል፡፡ በቂ መልስ ሊሰጠው አለመቻሉም አስጨንቆታል፡፡ የጠዋቱ ሁኔታቸው እየተመላለሰ ይረብሸዋል፡፡
ጠዋት የ፲፪ እና የ፰ ዓመት ልጆቹ ቀድመውት ከእንቅልፋቸው ተነሥተው ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድ እየተዘጋጁ ነው፡፡ አክሊሉ ሌሊቱን ጥሩ እንቅልፍ ባለመተኛቱ ድካም ቢሰማውም እየተነጫነጨም ቢሆን ተነሣ፡፡ ቁርስ የመብላት ልምድ ስለሌለው ባለቤቱ እስክታቀርብለት አልጠበቀም፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድ የሚጣደፉት ልጆቹን ስሞ ወደ በሩ እያመራ ሳለ የመጀመሪያ ልጁ ናሆም ያልጠበቀውን ጥያቄ ጠየቀው፡፡
“አባዬ እኛ ለምንድነው ቤተ ክርስቲያን ሔደን የምንሰግደው?” ሲል ጠየቀው፡፡
ያልጠበቀው ጥያቄ ነበር፡፡ ናሆም ገና የ፲፪ ዓመት ልጅ ነው፡፡ ሁል ጊዜ መጠየቅ ይወዳል፣ ትምህርት ቤት ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ከአእምሮው በላይ ስለሚሆኑበት ወደ ቤት መጥቶ አባቱን ይጠይቃል፡፡ አክሊሉ ከቢሮ ይዞት የመጣውን ሥራ ለማጠናቀቅ በሚል ትኩረቱ ሁሉ ኮምፒዩተሩ ላይ ቢሆንም ለልጁ ጥያቄ በጥቂቱም በተከፈለ ልቡ ለመመለስ ይሞክራል፡፡ በልጁ ጥያቄዎች ብዙ ጊዜ ይገረማል፣ የጓደኞቹም ፈጣን አእምሮ ያስደንቀዋል፣ አንዳንዴም ያበሳጨዋል፡፡ የዛሬው የጥያቄው ጤናማነት ግን አጠራጠረው፡፡
“ማነው ይህን የጠየቀህ?” አለው ምላሹን ከመስጠት ተቆጥቦ፡፡
ሙሴ ነዋ፡፡ አጠገቤ የሚቀመጠው ጓደኛዬ:: ብታይ ምሳ ስንበላ ዓይኑን ጨፍኖ ነው የሚጸልየው፣ እመቤታችንን ደግሞ አይወዳትም፣ ብዙ ጊዜ ይሳደባል፡፡ እኔም ዝም አልለውም ለምን ይሰድባታል ብዬ እንደባደባለን፡፡ ባለፈው እንኳን የአማርኛ አስተማሪያችን ቲቸር በላቸው ገረፈኝ ብዬ አልነገርኩህም?”
“አዎ፡፡ ለምን እንደገረፈህ እኮ አልነገርከኝም?” አለ ምክንያቱን ሳይጠይቀው ማለፉን አስታውሶ፡፡ በሥራ እየተጠመደ ልጆቹ የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታትም ሆነ ምን ዓይነት ተማሪዎች እንደሆኑ ለመጠየቅ ከመምህራኖቻቸው ጋር ለመመካከር ጊዜ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ከትምህርት ቤት መልእክት ሲመጣ፣ ስብሰባ ወይም ውጤት ለመቀበል እንኳን ሔዶ አያውቅም፡፡ የልጆቹን ጉዳይ አሳልፎ ለባለቤቱ ሐና ሰጥቷታል፡፡ ልጆቹን መከታተል አለመቻሉ አሳፈረው “ወይኔ ልጆቼ! ወልጄ ብቻ ተውኳችሁ ማለት ነው?” በማለት ሁለቱን ልጆቹን እያፈራረቀ በጥፋተኝነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ተመለከታቸው፡፡
“ሌባና ፖሊስ ስንጫወት ሳሸንፈው ጊዜ እመቤታችንን ተሳድቦ ሲሮጥ ድንጋይ ወርውሬ ጭንቅላቱን መታሁትና አለቀሰ፡፡ የአማርኛ አስተማሪያችን ደግሞ ገረፈኝ፡፡ ከዚያ ደግሞ አስታረቀን” አለ ጣፋጭ በሆነ አንደበቱ፡፡
“ታዲያ ይህን ጥያቄ ሙሴ ለምን ጠየቀህ?” አለው በስጋት፡፡
“ሊያናድደኝ ነዋ፡፡ ስላልመለስኩለት ደግሞ ለጓደኞቻችን አስቆብኛል” አለ እየተሸማቀቀ፡፡
“አየህ ልጄ እሱ የሚልህን አትስማው፡፡ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ አለ፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ስሙ የሚጠራበት፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምንቀበልበት፣ ጸሎት የምንጸልይበትና ጸሎታችንም የሚሰማበት ቅዱስ ቦታ ስለሆነ በእግዚአብሔር በቅድስናው ሥፍራ በቤተ ክርስቲያን እንሰግዳለን፡፡ ሁል ጊዜም ቤተ ክርስቲያን ሔደን እንሰግዳለን፣ እንሳለማለን” አለ፡፡ መልሱ ልጁን አርክቶት ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ በትኩረት አስተዋለው፡፡ ግራ እንደተጋባ ሲረዳ ከአቅሙ በላይ በሆነ አገላለጽ ምላሹን እንደሰጠው ተረዳ፡፡ አቅልሎ ለመንገር ቃላት መምረጥ ፈለገ፡፡
ከመጽሕፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሶ ሊያስረዳው አሰበ፡፡ ነገር ግን ከአቅሙ በላይ በሆነ መንገድ የባሰ እንዳያደናግረው ስለሰጋ እንዴት ላስረዳው በሚል ተጨነቀ፡፡
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትዝ አለው፡፡ “ይኸውልህ ልጄ ነቢዩ ሕዝቅኤል የተባለው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሰው ነበር፡፡ እርሱ ምን አለ መሰለህ “በሰሜኑም በር መንገድ በቤቱ ፊት አገባኝ፡፡ እኔም አየሁ፣ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበር፡፡ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ” እያለ ይናገራል፡፡ (ሕዝ.፵፬.፬)፡፡ ሌላው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ስንሔድ ራሳችን አዘጋጅተን መሆን አለበት፡፡ ነቢዩ ሙሴ ቁጥቋጦው በእሳት ሲቃጠል ታየው፣ ነገር ግን ወደ ቁጥቋጦው ቀርቦ ሲመለከት ቁጥቋጦው አልተቃጠለም፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ “ሙሴ ሙሴ ወደዚህ አትቅረብ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ” አለው፡፡ ይህ ለምን ይመስልሃል? የእግዚአብሔርን ቤት ቤተ ክርስቲያን የተቀደሰች ሥፍራ እንደሆነች ሲያስተምረን ነው፡፡ (ዘፀ.፫.፪-፭)፡፡ ስለዚህ ጫማችንን እናወልቃለን፣ እንሰግዳለንም፡፡ አሁንስ ገባህ?” አለ ልጁ በመልሱ ይርካ አይርካ መገመት አቃተው፡፡ ከአእምሮ በላይ ሌሎችን ጥቅሶች እየደረደረ ሊያስጨንቀው አልፈለገም፡፡ ሰዓቱን ሲመለከት ለልጆቹም ሆነ ለእርሱ እንደረፈደ ተረዳ፡፡
“በቃ ማታ በደንብ እንነጋገራለን፡፡ ሁለተኛ ከማንም ጋር እንዳትጣላ” ብሎ ሁለቱንም ልጆቹን ስሞ ቅር እያለው ወጣ፡፡
አክሊሉ ለስሙ መሥሪያ ቤቱ ይሂድ እንጂ ቀኑን ሙሉ ለልጁ እንዴት ማስረዳት እንዳለበት ቃላት እየመረጠ አንዱን እየጣለ ሌላውን እያነሣ በሐሳብ ሲባዝን ውሎ ነው የተመለሰው፡፡
ጎጃም ከቤተሰቦቹ ጋር ሳለ በልጅነቱ ከፊደል አንስቶ እስከ መዝሙረ ዳዊት በአጥቢያቸው ካሉት የኔታ ዘንድ ይማር እንጂ ጠለቅ ብሎ እንደ ሌሎቹ የሠፈሩ ልጆች የአብነት ትምህርት የመማር ዕድል አልገጠመውም፡፡ አዲስ አበባ የሚኖሩት አጎቱ በልጅነቱ ወደ አዲስ አበባ ወስደው ዘመናዊውን ትምህርት አስተማሩት፡፡ ዛሬ በአንድ መንግሥት መሥሪያ ቤት በኃላፊነት በመሥራት ላይ ነው፡፡ ልጆቹን ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ አለማስገባቱ ጸጸተው፣ ቤትም ውስጥ እርሱ ያወቀውንና የተማረውን ትምህርት ለልጆቹ የሚገባቸውን ዕውቀት ባለማስጨበጡ ራሱን እንደ ባለ ዕዳ ቆጠረ፡፡
ገና ወደ ቤት ከመግባቱ በጉጉት ሲጠብቀው የዋለው ልጁ ዘሎ አንገቱ ላይ ተጠመጠመ፡፡ “አባዬ እ- እ- ጠ- ጠ- ዋት የ- የነገረከኝን ሁሉ ለሁሉም ጓደኞቼ ነገርኳቸው፡፡ ሙሴ መልስ መመለስ አቃተው፣ እንዳበሸቀኝ አናደድኩትና ጓደኞቼ ሳቁበት” አለ ናሆም በድል አድራጊነት ፈንድቆ፡፡
“ጎበዝ የኔ ልጅ፡፡ መጣሁ ልብሴን ልቀይር” ብሎ ወደ መኝታ ቤት ገባ፡፡
ናሆም ለረጅም ጊዜ ለአእምሮው ጥያቄ የፈጠረበትና መልስ ያጣለት ተጨማሪ ጥያቄ ለአባቱ ለመጠየቅ ተዘጋጀ፡፡ ማታ ለጠየቀው ጥያቄ በሰጠው መልስ ጓደኛውን ድል ስላደረገ ተጨማሪ ማብራሪያ አልፈለገም፡፡ ለዛሬው ጥያቄ ደግሞ ተዘጋጀ፡፡
አክሊሉ ከመሥሪያ ቤት ሆኖ ሲሠራ ውሎ አላልቅ ያለውን የጽሑፍ ሥራ እቤቱ ሆኖ ለመጨረስ ፍላጎት ቢኖረውም ከዚያ በፊት ልጁን ማረጋጋት እንዳለበት ስለተረዳ ልብሱን ቀይሮ ለጥቂት ደቂቃዎች ከልጆቹ ጋር ማሳለፍ ውስጡን አሳምኗል፡፡ የልጆቹን ኃላፊነት በሚስቱ ሐና ላይ ጥሎ ስለነበር ኃላፊነቷን በአግባቡ ባለመወጣቷ አጉረመረመ፡፡
ናሆም ዛሬ ደግሞ ሲከነክነው የዋለውን ጥያቄ ለአባቱ ይዞ መጥቷል፡፡ ሳሎን እንደተቀመጡ ጥያቄውን ለማንሣት ፈለገ፡፡
“አሁን ጠዋት ለጠየቅኸኝ ጥያቄ መልሱን ላብራራልህ” አለ አክሊሉ ሁለቱን ልጆቹን ግራና ቀኝ አስቀምጦ፡፡
“ገብቶኛል አልፈልግም፡፡ ሌላ ጥያቄ ደግሞ አለኝ” አለ ናሆም አባቱ ይመልስለት ዘንድ ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ፡፡
“ደግሞ ምንድነው ጥያቄህ?” ስጋት ገባው፡፡
“እ- እነ ሙሴ ለምንድነው ዓይኖቻቸውን ጨፍነው የሚጸልዩት? ብታይ እ- እሱ ዓይኖቹን ጨፍኖ ሲጸልይ ጓደኞቼ ምሳውን ይሰርቁበታል፣ ከዚያ ይደባደባሉ፡፡ ጋሼ በኃይሉ ደግሞ እየሮጡ መጥተው ሁላችንንም ይገርፉናል” አለ በችኮላ፡፡
“አንተ ግን በእንደዚህ ዓይነት መጥፎ ድርጊት ውስጥ መሣተፍ የለብህም፡፡ ጥል፣ ተንኮል መሥራት፣ መሳደብ ኃጢአት ነው፣ እግዚአብሔርን ማሳዘን ነው ብዬ ከዚህ በፊት ነግሬህ የለም?”
“አዎ፡፡ ግን እኔ የምጣላው በቤተ ክርስቲያን ነገር ሲሳደቡ ብቻ ነው፡፡ አሁን የጠየቅሁህን ጥያቄ አትመልስልኝም?” አለ አንገቱን ሰበር አድርጎ መሬት መሬት እያየ፡፡
“እመልስልሃለሁ፡፡ ዓይንን ጨፍኖ መጸለይ ትክክል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የጨለማ አምላክ አይደለም፣ የብርሃን እንጂ፡፡ ጨለማ የሰይጣን ምሳሌ ነው” አለ እንዴት ማስረዳት እንዳለበት እየተቸገረ ሳለ ባለቤቱ ወ/ሮ ሐና ከቢሮ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
“እንዴት ዋላችሁ?” ብላ ሦስቱንም ስማ ወደ ውስጥ ገባች፡፡
“እንዴ አባዬ ጨለማንና ብርሃንን፣ ሁሉንም ነገር የፈጠረው እግዚአብሔር ነው ብለህ አልነገርከኝም? እንዴት እግዚአብሔር የብርሃን አምላክ ብቻ ይሆናል?”
ናሆም ሌላ ጥያቄ አባቱ ላይ ጫነ፡፡ አክሊሉ በልጁ ፈጣን ጥያቄዎች ተደናገጠ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደማደጉ ዘመናዊውን ትምህርት ብቻ ሲያሳድድ ለመንፈሳዊው ዕውቀት ባዕድ እየሆነ መምጣቱን እነዚህን ቀላል የሚመስሉ ጥያቄዎችን መመለስ ባለመቻሉ በራሱ አዘነ፡፡ መልሶ ደግሞ የሚያውቀውንም ለማስረዳት ለልጁ ከአቅሙ በላይ እንደሚሆንበት ተረዳ፡፡
“አየሽው ልጅሽ የሚጠይቀው ጥያቄ? በደንብ ብትከታተይው ኖሮ እንዲህ ጠያቂ ብቻ አይሆንም ነበር” አለ አክሊሉ ሐና ከመኝታ ቤት ወደ ሳሎን ስትወጣ ደካማ ጎኑን በሚስቱ ለማሳበብ እየሞከረ፡፡
“ምነው ገና ከመግባቴ ነገር ይዘህ ቆየኸኝ፡፡ ልጆቹ እንደሆነ የእኔም የአንተም ናቸው፡፡ ያለን ኃላፊነት እኩል ነው፡፡ ከቢሮ እያመሸህ ትመጣለህ፣ ቤት መጥተህ ለቤተሰብህ ጊዜ መስጠት ሲገባህ ሥራ ይዘህ ከኮምፒዩተርህ ጋር ትፋጠጣለህ፡፡ እኔ ብቻዬን ምን አድርጊ ነው የምትለኝ?” ሐና ፊት ለፊቱ መጥታ እጆቿን ወገቧ ላይ አድርጋ በንዴት ቁልቁል እየተመለከተችው፡፡
“የልጆቹን ኃላፊነት የወሰድሽው አንቺ ነሽ፡፡ ምን በሉ፣ ምን ለበሱ ብቻ ሳይሆን ውሎአቸውንም መከታተል አለብሽ፡፡ እኔ ጊዜ እንደሌለኝ ታውቂያለሽ” አለ ሚስቱን እንዳስቆጣት ሲረዳ ንግገሩን በማለዘብ፡፡
“እኔም እኮ መሥሪያ ቤት ስለፋ ውዬ ነው የምመጣው፡፡ ቤት መጥቼ ደግሞ የቤት ውስጥ ሥራው ይጠብቀኛል፡፡ አንተ እንደሆንክ የወደቀ ዕቃ እንኳን ቀና አታደርግም፡፡ ውለህ፣ አምሽተህ፣ እንደገና ኮምፒዪተር ላይ ታፈጣለህ፡፡ ጊዜ ወስደህ የቤት ሥራቸውን እንኳን ለመከታተል አትሞክርም፣ እኔ ስንት ቦታ ልድረስ?” ሶፋው ላይ ተቀምጣ ቁጭ ብላ አለቀሰች፡፡
አባትና ልጆች ተደናገጡ፡፡ ልጆቹ ሮጠው እናታቸው ላይ ተጠመጠሙ፡፡ የእናቷን ማልቀስ የተረዳችው ኤፍራታ እናቷን እንዳቀፈች አለቀሰች፡፡ አክሊሉ የሚይዘውን፣ የሚጨብጠውን አጣ፡፡ የፈጠረውን ችግር መልሶ ለመጠገን ተቸገረ፡፡ ለቅሷቸውን እስኪያቆሙ ጠብቆ “ይቅርታ እናቴ ሳላስበው አስቀየምኩሽ” ብሎ ሐናን አቅፎ ለማባበል ሞከረ፡፡
“ለምን ታሰቃየኛለህ? ሁሉን ችዬ ዝም ስላልኩህ ነው? ለምን አታግዘኝም? የቢሮ ሥራህን ቢሮ ውስጥ ጨርሰህ ሠርተህ ወደ ቤትህ መምጣት፣ ባትጨርስ እንኳን በማግስቱ ትደርስበታለህ፣ ቤት ውስጥ ደግሞ ለቤተሰብህ ጊዜ ስጥ፡፡ ሁሉን ነገር እኔ ላይ ጥለህ እንዴት እችላለሁ? አላሳዝንህም? ለልጆችህስ አታዝንምን?”
አክሊሉ የልጁ ብቻ ሳይሆን የባለቤቱ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን መመለስ ተሳነው፡፡ ምን ያህል ቤቱን እንደበደለ ሲያስበው ለፀፀት እጁን ሰጠ፡፡ ይህን ያህል ችግር ያመጣል ብሎ ያላሰበው ጉዳይ ቤተሰቡን መጉዳት መቻሉ አሳፈረው፤ ቀና ብሎ ባለቤቱንና ልጆቹን ለማየት አቅም አጣ፡፡ ሳሎኑ በዝምታ ድባብ ተዋጠ፡፡ ሁሉም ዝም . . . ፡፡
የቤቱ ራስ የሆነው አክሊሉ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ግዴታ መሥዋዕትነት መክፈል እንዳለበት ተረዳ፡፡ ጭቅጭቁ በዚሁ ከቀጠለ አቅጣጫው እንደሚቀየር ገብቶታል፡፡ “ይቅርታ የኔ ውድ! እውነትም በድያለሁ፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል እስክትጎጂ ለምን ጠበቅሽ? እስከ ዛሬ ለምን አልነገርሽኝም?” አለ ባለቤቱን ቀና ብሎ ለማየት እየተሸማቀቀ፡፡
ልጆቹ በየተራ አንድ ጊዜ አባታቸውን፣ መልሰው ደግሞ እናታቸውን እያዩ ዓይኖቻቸውን ያቁለጨልጫሉ፡፡ ላስተዋላቸው ፊታቸው ላይ ፍርሃት ይነበባል፡፡
“እንዴት አይገባህም? እኔ ስንት ቦታ ልበጣጠስ?” አለች በቁጣ እያፈጠጠችበት፡፡
“ይቅርታ አልኩሽ እኮ፡፡ አሁንም ቢሆን አልረፈደምና የተፈጠረውን ችግር በጋራ እንፍታው፡፡ ተጨቃጭቀን አንዘልቀውም፡፡ ቤታችንን ለማፍረስ የሚታገለንን ዲያብሎስ ማሳፈር አለብን፡፡ እኔ እኮ በኢኮኖሚ እንዳንጎዳ፣ ነገ የተሻለ ኑሮ እንኖራለን በሚል ነው ያለ ዕረፍት የምሠራው፡፡ በቅንነት እንጂ አንቺን ወይም ቤተሰቤን ለመጉዳት አስቤ ያደረግሁት አይደለም፡፡”
“ስለ ነገ እያሰብኩ ዛሬን አላበላሽም፡፡ እየኖርን ያለነው ዛሬን ነው፣ ነገ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም፡፡ ለምን ራስህንም ቤተሰቦችህንም ትጎዳለህ? ትዳራችን በሚመጣ ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚቆመው፡፡ ስንተሳሰብ፣ ስንረዳዳ፣ አንዳችን ለአንዳችን ስንጨነቅ ነው፡፡ በውድቅት ሌሊት ትተኛለህ፣ የጎሕ መቅደድ ተከትለህ ትወጣለህ፣ ለምን? እሑድ እንኳን ቅዳሴ አለቀ አላለቀ እያልክ ስትቁነጠነጥ ትጨርሳለህ፣ በቃ ቤትህ ውስጥ አትታይም፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታችን ምን ያህል ባዶ እንደሆነ አስተውለሃል? ከተጋባንበት ጊዜ አንስቶ ምን ያህል ጊዜ እንደቆረብን ታውቃለህ? ስጠይቅህ ነገ ነገ እያልክ ጊዜውን ገደልክ፡፡ የንስሓ አባታችንን መቼ ነው ያገኘናቸው? መቼ ነው ንስሓ የገባነው? መንፈሳዊ ሕይወታችን አያሳስብህም? ያ ሁሉ ጥንካሬህ የት ሔደ?”
አክሊሉ ጥፋቶቹን ሲያስባቸው ሊሸከመው የማይችለው ፀፀት ውስጡን በላው፡፡ የልጁን ጥያቄ መመለስ ተስኖት ጭራሽ የባለቤቱን፣ የግማሽ አካሉን ብሶት ቀሰቀሰ፡፡ ምንም መከራከሪያ ነጥብ በአእምሮው ሊመጣ አልቻለም፡፡ ሐና ትክክል እንደሆነች ውስጡን አሳመነ፡፡ ንግግራቸው ወደ ጭቅጭቅ ሳይሆን ወደ ውይይት መውሰድ እንዳለበት ተገነዘበ፡፡
ሳሎኑ አሁንም ዝምታውን ተረከበ፡፡ አክሊሉ በኃፍረት አቀርቅሯል፣ ሐና ገንፍሎ የመጣውን ብሶት ያዘለ ንዴቷን ለማብረድ፣ ለቅሶዋን ለማቆም ትታገላለች፣ ናሆምና ኤፍራታ በዝምታ ወላጆቻቸውን ይመለከታሉ፡፡
ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ “ወደ ኋላ መመለስ አንችልም፡፡ የሆነው ሆኖ አልፏል፡፡ ጥፋቴን አምኛለሁ! ሁሉንም በይቅርታ እንለፈው፡፡ ይቅር ማለት የሚችሉ ልቦች የታደሉ ናቸው፡፡ ይቅር በይኝ ውዴ! ያለፈውን እንርሳ፣ ቤታችንን በይቅር ባይነት ደግመን እንሥራው” ብሎ በባለቤቱና በልጆቹ መካከል በግንባሩ ተደፍቶ “ይቅር በሉኝ!” አለ፡፡
ሐና ደነገጠች፡፡ በአንድ ጊዜ እንዲህ ውስጡ ይሰበራል ብላ አላሰበችም፡፡ ባለቤቷን ትወደዋለች፣ ታከብረዋለች፣ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ማንነቱን ታውቃለች፣ ስላመነበት ነገር ይሞታል፡፡ ለእሷ ያለውን ፍቅር ወሰን እንደሌለው ትረዳለች፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ጭልጥ ብሎ ሥራው ላይ ብቻ መጠመዱ እያሳሰባት፣ ፍርሃት እየገባት ሁሉን ተሸክማ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡
ፊት ለፊቷ ተደፍቶ ይቅርታ ሲጠይቃት ንዴቷ ከላይዋ ላይ እንደ ጢስ ተነነ፡፡ አዘነችለት፡፡ የፍቅር ትኩስ ዕንባ እያነባች ከተደፋበት ብድግ አድርጋ አቀፈችው፡፡ ሁለቱም ተያይዘው ተላቀሱ፣ ልጆቹ ወላጆቻቸውን አቅፈው በዕንባ ተከተሏቸው፡፡ የፍቅር፣ የፀፀት፣ የጭንቀት፣ የደስታ ዕንባ፣ ድምፅ አልባ የዕንባ ዘለላዎች ጎረፉ፡፡
“ይቅርታ አድርገሽልኛል?” አለ አክሊሉ ከእቅፏ ወጥቶ ግንባሯን በፍቅር እየሳመ፡፡
“አዎ፡፡ እኔንም ይቅር በለኝ” አለች ዕንባዋን እየጠረገችና ሶፋው ላይ ቁጭ እያለች፡፡
“አዎ ውዴ! አንቺ ምንም አላጠፋሽም፣ እኔ ነኝ ኃላፊነቴን የዘነጋሁት፡፡ ወደፊት በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለብንም፡፡ መተጋገዝ አለብን፡፡ እኔ የልጆቻችንን ኃላፊነት በአግባቡ እወጣለሁ፡፡ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ካሉ ልትሰጪኝ ትችያለሽ፡፡ ይህንን ስል አንዳችን የአንዳችንን ጉድለት ከመሙላት ጀምሮ እየተነጋገርን እንረዳዳለን፡፡ አይመስልሽም?” አለ አክሊሉ ባለቤቱን በፍቅር ዓይኖቹ እያስተዋላት፡፡
“ደስ ይለኛል፡፡ የተጠራቀመ ብሶቴን በአንድ ጊዜ አራገፍኩብህ አይደል? ለዚህም ይቅርታ! በዋናነት በቅድሚያ ትኩረት የምናደርገው መንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ እሑድ ከቅደሴ መልስ የንስሓ አባታችንን እናነጋግራለን፡፡ እርሳቸው በሚሰጡን አቅጣጫ በጸሎት እየበረታን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እናጠናክራለን፡፡ ጎን ለጎን የልጆቻችንም፣ የቤታችንም ኃላፊነት በጋራ እንወጣለን፡፡ አይመስልህም?” በፈገግታ ባለቤቷንና ልጆቿን ተመለከተች፡፡
“እስማማለሁ፡፡ እናደርገዋለንም፡፡ እስከ አሁን ብዙ ተጎድተሻልና አንዲት ረዳት ብትኖረን ደስ ይለኛል፡፡ በሥራ ደክመሽ ውለሽ እንደገና ወደ ጓዳ ማለቱ እጅግ አድካሚ ነው፡፡”
“እያሰብኩበት ነው፡፡ ጥሩ ሰው ከተገኘ አጠያይቃለሁ፡፡”
“መልካም፡፡ ኑ ልጆች እናታችሁን እናመሰግናለን! ብላችሁ ሳሟት” አለ አክሊሉ እየሳቀ፡፡
ሁለቱም እናታቸው አንገት ላይ ተጠመጠሙ፡፡ እቅፍ አድርጋ ስትስማቸው ቆይታ “አሁን ተራው ለአባታችሁ ነው ሒዱና ሳሙት” አለች ፈገግታ እየመገበቻቸው፡፡
ልጆቹ በእናታቸው ትእዛዝ መሠረት አባታቸውን አቅፈው ከሳሙት በኋላ ኤፍራታ ከአባቷ ጋር መጫወት ፈለገች፣ ናሆም ደግሞ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ፈለገ፡፡
ሐና ባለቤቷንና ልጆቿን በፍቅር ዓይኖች እያስተዋለች “በሉ እናንተ ተጫወቱ፡፡ እኔ እራታችንን ላዘጋጅ” ብላ ወደ ጓዳ ገባች፡፡ ከላይዋ ላይ ትልቅ ሸክም ተነሣላት፡፡ ለብዙ ጊዜ ሲያስጨንቃት የቆየው ጉዳይ ባልጠበቀችው ጊዜ መፈታት መቻሉ አስገረማት፡፡ እፎይታ በውስጧ ነገሠ፡፡
ቤቱ በአንድ ጊዜ ከዝምታ ድባብ ወደ ፍቅር ጨዋታ ተለወጠ፡፡ ቤቱ ውስጥ ሲያንዣብብ የነበረው ዳመና ተገፈፈ፡፡ ጥቂት ሲጫወቱ ቆይተው ናሆም ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ “የቅድሙ ጥያቄ እኮ አልመለስክልኝም” አለ፡፡
“እኔ መጫወት ነው የምፈልገው” አለች ኤፍራታ እያኮረፈች፡፡
አክሊሉ “ቆይ ለወንድምሽ አሁን ጠይቆኝ ለነበረው ጥያቄ መልስ ልስጠውና ከአንቺ ጋር ደግሞ እንጫወታለን፡፡ እሺ?” አላት ዐይን ዓይኗን እየተመለከተ፡፡
ኤፍራታ እንዳኮረፈች ተቀመጠች፡፡
አክሊሉ የልጁን ምላሽ አልጠበቀም ከናሆም ጋር ጀምረውት ወደ ነበረው ጥያቄና መልስ አመሩ፡፡ አክሊሉ ለልጁ እንዴት በቀላሉ ሊያስረዳው እንደሚችል ማሰብ ጀመረ፡፡
“ቅዱስ ዳዊት ምን ይላል መሰለህ ልጄ? “እግዚአብሔር ያበራልኛል፣ ያድነኛልም” ይላል (መዝ.፳፯.፩)፡፡ በብርሃንና በጨለማ እኩል አንጓዝም፣ በጨለማ ውስጥ ሆነን የምናየውን ነገር መለየት ያቅተናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የተሰወረውን እንደሚገልጥልን እያመንን ዓይኖቻችንን ገልጠን እንጸልያለን፡፡ በቅድስናው ስፍራ በቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም በቤታችን ሆነን እንጸልያለን፡፡ ሌላው ደግሞ “የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፣ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ የሚሠሩትን ክፋትና ተንኮልን በጨለማ መስሎ ነግሯቸዋል፡፡(ዮሐ.፰.፲፪)፡፡
“በተጨማሪም “ሕይወት በእርሱ ነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፣ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም” በማለት ወንጌላዊው ዮሐንስ ይነግረናል፡፡ እኛም በብርሃን ልንመላለስ ይገባል፡፡ (ዮሐ.፩፥፭)፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎ የተናገረውንና እርሱ ብርሃን ሆኖ ብርሃንነቱን የገለጠልን የአምላካችን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ማመንና መቀበል፣ እንዲሁም እንደ ቃሉም መኖር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እኛ ዓይኖቻችንን ጨፍነን አንጸልይም፡፡ ሌሎችም ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ለጊዜው ይበቃናል፡፡ አንተ በሆነው ባልሆነው አትደናገጥ፣ አትከራከር፡፡ በዚህ ዕድሜህ ማወቅ ያለብህን እንጂ ከአቅምህ በላይ መጓዝ የለብህም፣ መጀመሪያ መማር ይቀድማልና፡፡ ከቅዳሜ ጀምሮ ሰንበት ትምህርት ቤት ሁለታችሁንም አስመዘግባችሁና በየሳምንቱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ትከታተላላችሁ” አለ አክሊሉ በትክክል መግለጹንና ልጁ የተናገረውን ይረዳ አይረዳ ለማወቅ በትኩረት እየተመለከተው፡፡
“ገብቶኛል፡፡ እኔ እኮ ሲከራከሩ አላስችልህ እያለኝ ነው” አለ፡፡
“እኔ ነገ ትምህርት ቤት ሄጄ ከኃላፊዎቹ ጋር እነጋገራለሁ፡፡ በተረፈ የእናንተ ግዴታ መማር ብቻ ነው፡፡ ገና ሕፃናት ስለሆናችሁ ስለ ሃይማኖት መከራከር አይገባችሁም” ብሎ አስጠነቀቀው፡፡
“እሺ! አመሰግናለሁ” አለ ናሆም በመልሱ ተደስቶ፡፡
“ራት ደርሷል፣ እጃችሁን ታጠቡ” አለች ሐና ከጓዳ ውስጥ ሆና ድምጿን ከፍ አድርጋ፡፡
ናሆም የእጅ ውኃ ከሰጠ በኋላ በአንድ ላይ የተዘጋጀውን ማዕድ መቋደስ ቀጠሉ፡፡
አክሊሉ ተፀፅቶ፣ ለቤተሰቡ የነፈጋቸውን ጊዜ በመስጠቱ፣ የልጁንና የሚስቱን ጥያቄ መመለስ በመቻሉ፣ ከሚስቱንም ጋር በመወያየቱና መግባባት በመቻላቸው ተደሰተ።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1286
ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢራቅ በአሸባሪው አይኤስ ቁጥጥር ሥር በወደቀችበት ወቅት ተዘርፈው የነበሩ በርካታ የኢራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሞሱል ሀገረ ስብከት ጥንታዊ መጻሕፍት ለቤተ ክርስቲያኗ እንደተመለሱ የኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘገባ ያሳያል፡፡
የተዘረፉት የኢራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ መጻሕፍት ለሞሱል ሀገረ ስብከት እንደተመለሱ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡ እነዚህ ጥንታዊ መጻሕፍትም የአልታአሂራአ ቤተ ክርስቲያን ንብረት የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡ በኢራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሞሱል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ የኒንቪህ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጎበኙበት ወቅትም ስለተዘረፉት የቤተ ክርስቲያኗ ጥንታዊ መጻሕፍትና በሞሱል ሀገረ ስብከት በአሸባሪዎች ላይ ስለሚደረገው የወንጀል ምርመራ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጉዳዩን ጉዳያችን ነው ብለው የቤተ ክርስቲያኗ ጥንታዊ መጻሕፍት ከተሰረቁበት እንዲመለሱ ላደረጉ የጸጥታ ኃይሎች ብፁዕነታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የአካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ፍትሕን ሳያጓድል የተሰረቁ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያኗ መጻሕፍት ለባለቤቱ እንዲመለሱ ላደረጉት ያለሰለሰ ጥረት አክብሮታቸውን ገልጠዋል፡፡
የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፊርማ እያሰባሰበች እንደሆነ ተጠቆመ
ሀግያ ሶፊያ የተባለውን ጥንታዊ የኦርቶዶክሳውያን ቤተ መቅደስ በቱርክ መንግሥት አማካይነት ወደ መስጅድነት መለወጡን አስመልክቶ በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአሜሪካ ሀገረ ስብከት ፊርማ አሰባስቦ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሊያስገባ እንደሆነ ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነብቧል፡፡
ሀገረ ስብከቱ ለጥንታዊ ቅርሶች ትኩረት እንዲሰጥ፣ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ባሕልና መብት እዲጠበቅ፣ የአናሳ መብት እዲረጋገጥ፣ የሃይማኖት ነፃነት እንዲከበርና የቱርክ መንግሥት ሆን ብሎ ታሪካዊ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ቅርሶች ከታሪክ ውጭ ከማድረግ ሥራው እንዲቆጠብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ፊርማ በማሰባሰቡ ሂደት ላይ ጠይቋል፡፡
ጉዳዩ በፍጥነት መስተካከል የማይችል ከሆነም ዓለም አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ሊጠራ እንደሚችል ሀገረ ስብከቱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡ ጥንታዊው የሀግያ ሶፊያ ካቴዴራል ቤተ ክርስቲያን ወደ መስጅድነት መቀየሩን የቱርኩ ፕሬዘደንት ርሲፕ ጣኢፕ ኢርዶጋን በ፳፻፲፪ ዓ.ም በይፋ ማወጃቸው ይታወሳል፡፡
የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለአረፅአካህ የአምስት መቶ ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገች
በአዘርባጃንና በአርመን መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ለከፋ ችግር ለተጋለጡት የአረፅአካህ ክርስቲያኖች የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአምስት መቶ ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስታውቋል፡፡
የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ካሪኪን ዳግማዊ አማካይነት አምስት መቶ ሺህ ዶላር ወጪ ተደርጎ ለአርፅአካህ ድጋፍ እንደተደረገ ተገልጿል፡፡ ቅዱስነታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ወቅት ድጋፉን እንዳስጸደቁ ከዘገባው ለመርዳት ተችሏል፡፡
ቅዱስነታቸው የገንዘብ ድጋፉን ከማጽደቃቸው በፊት ለሀገራቸው ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡ አርመንያውያን ክርስቲያኖች በመላው ዓለም በጸሎት እንዲታሰቡ አሳስበዋል፡፡ በተካሄደው ስብሰባ የተወሰነው የገንዘብ ድጋፍ ለአረፅካህ ሕዝብና የጦር ሠራዊት አባላት ድጋፍ የሚውል ይሆናል ተብሏል፡፡ የገንዘብ ድጎማው የአረፅካህ ሪፐብሊክን ወቅታዊ የጦርነት ሁኔታ ያገናዘበ እንደሆን ቅዱስነታቸው በስብሰባው ገልጠዋል፡፡ የአዘርባጃን መንግሥት በአረፅካህ ሪፐብሊክ እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ ርምጃ በተመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለዓለም መንግሥታት፣ ለአኅት አብያተ ክርስቲያናት፣ ለሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ለሃይማኖት ተቋማት ኅብረት ድርጅቶች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የዓለም አብያተ ክርስቲያናትና የሃይማኖት ጉባኤ ተቋማት የአረፅካህ ክርስቲያኖች መብት በሚጠበቅበት ሁኔታ ላይ ጠንክረው ሊሠሩ እንደሚገባም ቅዱስነታቸው አሳስበዋል፡፡ በስብሰባው ለሀገራቸው ሲሉ ሕይወታቸው ላለፈ የጦር ሠራዊት አባላት ጸሎተ ፍትሐት እንዲካሄደ የተወሰነ ሲሆን ለአርመንያ ጦር ሠራዊት አደረጃጀትና ጥንካሬ የአህጉረ ስብከት ጥምረት በጣም ወሳኝ እንደሆነ ተነሥቷል፡፡
አርመንያ ከጥንታዊ ኦርቶዶክሳውያን ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን፤ ለመጀመያ ጊዜ ኦርቶዶክሳዊ መንግሥትን ያቋቋመች ብቸኛ የዓለማችን ሀገር ናት፡፡ በአዘርባጃን ግዛት ውስጥ የምትገኘው ኖጎሮ ካራባክህ ራስ ገዝ ሀገር ስትሆን በርካታ የአርመን ክርስቲያኖችም ይኖሩባታል፡፡ በቅርቡ በአዘርባጃንና በአርመን መካከል በተቀሰቀሰ ጦርነት ንጹሓንን ጨምሮ በርካታ ወታደሮች ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ጉዳት የደረሰባቸውን የአካባቢው ኗሪዎችንና የጦር ሠራዊቱን ያማከለ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
- Details
- Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1201
ውድ አንባብያን ባለፈው ዕትማችን የቅጽል ዓይነቶችን ጀምረን የተወሰኑትን የውስጠዘ የቅጽል ዓይነቶች መመልከታችን ይታወሳል። የተወሰኑትን ደግሞ በዚህ ዕትም እንመለከታለን። መልካም ንባብ።
መስም ቅጽል
መስም ቅጽል ባዕድ ቅጽል ተብሎም ይጠራል። ይህ የቅጽል ዓይነት ከግስ የሚመሠረት ሲሆን ባዕድ ፊደል “መ” ን ሁሌም በመነሻነት ይጠቀማል። ይህ ቅጽል በሳድስ በሣልስም ይጨርሻል።
ይህ ቅጽል እንደ ሳድስ ውስጠዘ በአምስት መንገድ ይተረጎማል። ይህም በአድራጊ፣ በተደራጊ፣ በአስደራጊ፣ በተደራራጊና በአደራራጊ ይፈታል ማለት ነው። ይህን አስመልክቶ መምህር ዕንባቆም የግእዝ ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ ለተማሪዎች በልዩ አቀራረብ የተዘጋጀ በተሰኘ መጽሐፋቸው “መስም /ባዕድ/ ቅጽል በባዕድ ቀለም “መ” የሚጀምር ውስጠዘ ሲሆን አማርኛው እንደ ሳድስ ውስጠዘ በአንድ ተነቦ በአምስት ይተረጎማል።” በማለት ይገልጹትና በምሳሌም ሲያስረዱ “ መቅትል፡- የገደለ፣ የተገደለ፣ ያስገደለ፣ የተገዳደለ፣ ያገዳደለ” ተብሎ እንደሚፈታ ይገልጻሉ። (ገጽ.፷፯)
መምህር ኀይለ ኢየሱስ መንግሥትም የልሳነ ግእዝ መማሪያ በተሰኘ መጽሐፋቸው “መስም ቅጽል፡- ዝንቱኒ ዘመደ ቅጽል ይወጽእ እምነ ግስ ወይትነሣእ ኵለሄ በ “መ” ፊደል ወባሕቱ ይፌጽም በሳድስ ፊደል አምሳሊሁ ለሳድስ ቅጽል፤ ይህ የቅጽል ዓይነት ከግስ የሚመሠረት ሁሌም እንደ ሳድስ ቅጽል በሳድስ ፊደል ብቻ የሚጨርስ ነው።” በማለት ያስረዳሉ። (፳፻፲፪፣ገጽ.፹፰) መምህር ኀይለ ኢየሱስ ምንነቱን በዚህ መንገድ ከገለጹት በኋላ በምሳሌ ሲያስረዱ
ግስ መስም ቅጽል (ነጠላ) መስም ቅጽል በብዙ
ደንገጸ (ደነገጠ) መደንግጽ መደንግጻን/ት
ተንበለ (ለመነ) መተንብል መተንብላን/ት
ፈከረ (ተረጎመ) መፈክር መፈክራን/ት
ዘመረ (አመሰገነ) መዘምር መዘምራን/ት
በማለት ሁሌም በ “መ” እንደሚጀምር መጨረሻውም ሳድስ ፊደል እንደሆነ ይገልጻሉ። መምህር ኃይለ ኢየሱስ በሳድስ ብቻ ይጨርሳል ይበሉ እንጂ በሣልም እንደሚጨርስ መመልከት ይቻላል።
መምህር ዕንባቆም መስም ሣልስ ቅጽል የሚባል እንዳለና በሣልስ እንደሚጨርስ ቀተለ ከሚለውም ግስ መቅተሊ የሚል መስም ሣልስ ቅጽል እንደሚወጣ ሲተረጎምም እንደ መስም ሳድስ ቅጽል በአምስቱም አዕማድ እንደሚተረጎም ያስረዳሉ። ለምሳሌ መቅተሊ የሚለው መስም ሣልስ ቅጽል የገደለ፣ የተገደለ፣ ያስገደለ፣ ያገዳደለ፣ የተገዳደለ ተብሎ እንደሚተረጎም ገልጸዋል።
መምህር አስበ ድንግል ግእዝ ልሳነ ኢትዮጵያ በተሰኘ መጽሐፋቸው “መስም ሣልስ ቅጽል” ብለው “መንጽሒ፣ መፍቀሪ፣ መስተፍሥሒ ፣መቅለሊ…” የሚሉትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። (፳፻፱፣ ገጽ.፳፱)
ከላይ በመምህር ዕንባቆም፣ በመምህር ኀይለ ኢየሱስና በመምህር አስበ ድንግል የተገለጸውን መነሻ አድርገን መስም ቅጽል ምን ማለት ነው የሚለውን ስናጠቃልል ከግስ የሚመሠረት፣ በዋና ግሱ ላይ በማይገኝ ባዕድ ፊደል። “መ” የሚጀምር በዚህም ባዕድ ቅጽል ተብሎ የሚጠራ፣ በሳድስና በሣልስ ፊደል የሚጨርስ የቅጽል ዓይነት ነው። መስም ቅጽል እንደ ሳድስ ቅጽል ሁሉ በአድራጊ፣ በተደራጊ፣ በአስደራጊ፣ በተደራራጊና በአደራራጊ የሚፈታ የቅጽል ክፍል ነው።
መድበል ቅጽል፡-
መድበል ማለት አመድበለ አከማቸ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ስብስብ፣ ክምችት፣ አንድነት የሚል ትርጉም ይሰጠናል። ይህን አስመልክቶ መምህር ዕንባቆም የግእዝ ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ ለተማሪዎች በልዩ አቀራረብ የተዘጋጀ በተሰኘ መጽሐፋቸው “መድበል ማለት አንድነት፣ ክምችት፣ ጥቅል፣ ድምር፣ የተዳበለና የተጋራ፣ የሚታይና የማይታይ፣ የፍጥረት ስብስብ፣ ሁሉም ጾታ የሚጠሩበት ስያሜ ሲሆን በአንድ ተነቦ በአምስት አዕማድ ይተረጎል። ለምሳሌ፡- ቀተልት፡- የገደሉ፣ የተገደሉ፣ ያስገደሉ፣ የተገዳደሉ፣ ያገዳደሉ” በማለት ምንነቱን ከነምሳሌው ያስረዳሉ። (ገጽ ፷፰)
መድበል ቅጽል በብዙ ቁጥር በወንድ በሴት እንደሚነገር መምህር ኀይለ ኢየሱስ የልሳነ ግእዝ መማሪያ በተሰኘ መጽሐፋቸው “ዝንቱ ዘመደ ቅጽል ይትነገር ኵለሄ በብዙኅ ለብእሲ ወለብእሲት ወዝኒ ይትመሠረት እምነ ግስ፤ ይህ የቅጽል ዓይነት ሁል ጊዜ በብዙ ቊጥር በወንድ በሴት ይነገራል፤ የሚመሠረተውም ከግስ ነው ” በማለት ያስረዳሉ።
መድበል ቅጽል መነሻው የግሱን መነሻ ያደርግና መድረሻው ግን “ት” ይሆናል።
ምሳሌ፡- ቀደመ (ቀደመ) በሚለው ግስ መድበሉ ቀደምት ይሆናል።
ጸሐፈ (ጻፈ) በሚለው ግስ መድበሉ ጸሐፍት ይሆናል።
ነግሠ (ነገሠ) በሚለው ግስ መድበሉ ነገሥት ይሆናል።
ግሱ በ “ተ” ፣ “ጠ “፣ “ደ” መድረሻነት የሚነገር ከሆነ ደግሞ የመጨረሻውን ፊደል ማለትም ት፣ ጥ፣ ድ ን በማጥበቅ ትን ሳይጠቀም ይጨርሳል።
ምሳሌ፡- ከበተ (ሸሸገ) በሚለው ግስ መድበሉ ከበት (ት ይጠብቃል) ይሆናል።
ፈለጠ (ለየ) በሚለው ግስ መድበሉ ፈለጥ (ጥ ይጠብቃል) ይሆናል።
ሰገደ (ሰገደ) በሚለው ግስ መድበሉ ሰገድ (ድ ይጠብቃል) ይሆናል።
ውድ አንባብያን ከላይ የቀረበው ትምህርት ግልጽ እንደሆነላችሁ ተስፋ እናደርጋለን።
እናንተ ደግሞ የሚከተሉትን ግሶች በመጠቀም መስም ቅጽል በሣልስና በሳድስ እና መድበል ቅጽል መሥርታችሁ አሳዩ።
| ተ.ቁ | ግስ | መስምሳድስ ቅጽል | መስም ሣልስ ቅጽል | መድበል ቅጽል |
| ፩ | ከሠተ | |||
| ፪ | ተለወ | |||
| ፫ | ተንበለ | |||
| ፬ | ነበረ | |||
| ፭ | ሜጠ | |||
| ፮ | ሰፈነ | |||
| ፯ | ነገደ |
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ሐመር በመስመር ላይ
- Hits: 1386
በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮአችን እያደግንና እየጠነከርን መሄድ የምንችለው፡- በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ጥፋቶችና የወደቅንባቸውን ችግሮች በትክክለኛው መንገድ በመለየት ተጸጽተን ለዘለዓለማዊ ሕይወታችን ንስሓ ስንገባ፣ ለማኅበራዊ ችግሮቻችንም ተጠብበንና ተጨንቀን መፍትሔ የምንፈልግ ስንሆን ነው፡፡=
ማኅበረሰባዊ ለሆኑ ችገሮች መፍትሔ በምንሻበት ጊዜም በተቻለን መንገድ የምንመርጣቸው ስልቶችና መንገዶች፣ ሁል ጊዜም መልካምና ለችግሩ አግባብነት ያላቸው እንዲሆኑ የሚጠበቁ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ እንደየግል ግንዛቤአችን የምንሄድ ከሆነ ወደምንፈልገው ግብ የማያደርሱን ወይም በተቃራኒው ችግሩን የሚያባብሱ ወይም ችግሩን ለጊዜው የጠፋ በሚመስል መንገድ በማዳፈን፣ በኋላ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህም ጊዜያዊ የሆነ ፋታን በመፈለግ መሠረታዊ የሆነውን ችግር ከነምክንያቱ ለመስማት፣ ለማወቅና ለመናገር፣ ብሎም ለመፍትሔው አቅማችን በፈቀደ መጠን ኃላፊና ባለድርሻ የመሆን ግዴታ ያለብን መሆኑን ከፍ ያለ ዋጋ ካለመስጠት ሊመጣ የሚችል ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም በአሁኑ ዘመን በሀገራችን ውስጥ ሕገ ወጥና ኢ-ሰብአዊ በሆኑ ድርጊቶች ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ላይ በተለየ ሁኔታ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ ሰቆቃና በአምልኮ ነፃነት ላይ የሚደረግ ክልከላ፣ የንብረት ውድመትና ቃጠሎን አላየንም፤ አልሰማንም፤ በድንገት የተፈጠረ ነው፤ ወይም ጉዳቱና ጥፋቱ የተለየና ምንም አይደለም! ብለን ማለፍ የማንችለው ነው፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኦርቶዶክስ ምእመናን ላይ ታቅደው እየተፈጸሙ ያሉ ድርጊቶችን ስንመለከታቸው፡- ሰበባቸው ምንም፣ ይሁን ምን፣ ለጥቃቶቹ ዒላማ የሚደረጉት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ምእመኖቿ መሆናቸውን ለማስረዳት በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ የቆዩ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በአስረጂነት በማቅረብ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
Read more: ችግሮች የሚወገዱት፣ አውጥተን ስንነጋገርባቸው እንጂ፣ ስንሸፋፍናቸው አይደለም!