ሐመረ ጽድቅ
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ሐመር
    • የማኅበሩ መልእክት
    • ትምህርተ ሃይማኖት
    • እናስተዋውቃችሁ
    • የጥያቄዎቻችሁ መልስ
    • ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት
    • ኪነ ጥበብ
    • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን
    • ከዓለም ማእዘናት
    • ዐውደ ስብከት
    • ዐቢይ ጉዳይ
  • ስምዓ ጽድቅ
    • ርእሰ አንቀጽ
    • አጫጭር ዜናዎች
    • ሪፖርታዥ
    • ቤተ አብርሃም
    • ፍሬ ከናፍር
    • የሕፃናት ዓምድ
    • ትዝብት
    • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ
  • ሙሉ ሕትመቶች
    • ሐመር በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • ሐመር በ ዓ.ም.
      • 1985
      • 1986
      • 1987
      • 1988
      • 1989
      • 1990
      • 1991
      • 1992
      • 1993
      • 1994
      • 1995
      • 1996
      • 1997
      • 1998
      • 1999
      • 2000
      • 2001
      • 2002
      • 2003
      • 2004
    • ሐመር በዓመት
      • 1ኛ ዓመት
      • 2ኛ ዓመት
      • 3ኛ ዓመት
      • 4ኛ ዓመት
      • 5ኛ ዓመት
      • 6ኛ ዓመት
      • 7ኛ ዓመት
      • 8ኛ ዓመት
      • 9ኛ ዓመት
      • 10ኛ ዓመት
      • 11ኛ ዓመት
      • 12ኛ ዓመት
      • 13ኛ ዓመት
      • 14ኛ ዓመት
      • 15ኛ ዓመት
      • 16ኛ ዓመት
      • 17ኛ ዓመት
      • 18ኛ ዓመት
      • 19ኛ ዓመት
      • 20ኛ ዓመት
    • ስምዓ ጽድቅ በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • አዳዲስ ሙሉ ሕትመቶች
      • አዲስ ሐመር
      • አዲስ ስምዐ ጽድቅ
  • ያግኙን

ሐመር መጽሔት *

የነፋስ ሽውታ

Details
Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 02 January 2021
Hits: 1592
  • ኪነ ጥበብ

ምኖረው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። አሁን ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ ከምትገኝ አነስተኛ ከተማ ደርሼ እየተመለስኩ መኪና ውስጥ ነኝ። የተሳፈርኩበትን መኪና አንደኛውን የመስኮት ጥግ ይዤ መስታውቱ ላይ ደገፍ ብዬ ተቀምጫለሁ። ስገባም እንደዚሁ ነው የተቀመጥኩት። የተሳፈርኩበት መኪና ጉዞ ከጀመረ ሁለት ሰዓታት ተቆጥረዋል። መንገዳችን በጠቅላላ ፭ ሰዓት ያህል ይፈጃል። ፊቴን እንደ ሐምሌ ሰማይ እንዳከበድኩት ይታወቀኛል። ምንም ነገር ማሰብ አልፈልግም። በጣም ከፍቶኛል። ከማንም ጋር በምንም ጉዳይ ማውራት ፍላጎቱም የለኝም። 

፳፮ ዓመቴ ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ያወቅሁትን ነገር ለሌሎች የማካፈል ጉጉቴ እጅግ ከፍተኛ ነው። አዲስ ነገር አውቄ ላላወቁት ስነግር ሳስረዳ እና ሲሰሙኝ ውስጤ የሚሰማኝ ደስታ እንዲህ በቃላት የምገልጸው አይነት አይደለም። ምንም ነገር አላግኝ ግን በቃ ያወቅሁትን ልናገር በተለይ ልብ ብሎ የሚያዳምጠኝ አካል ካለ እጅግ ደስተኛ ነኝ። በማላውቀው ነገር ግን ለመናገር አልቸኩልም። የተማርኩት የምሠራውም መካኒካል ምህንድስና ነው። ሥራየን እወደዋለሁ። 

በእያንዳንዱ ቀን አዲስ ነገር ስለማውቅበት እና የልጅነት ስሜቴ ስለነበር በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሥራውን መሥራት እችላለሁ። ይህንን ስለሚረዱ ነው መሰለኝ አለቃዬ ብዙ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ ላሉ ሥራዎች እኔን የሚመርጡት። እኔም ደስተኛ ሁኜ ነው የምሠራው።

የዛሬው ግን የተለየ ነው። ከዚህ በፊት እንደሚገጥመኝ ዓይነት ሁኔታ አልነበረም። በጣም የተከፋሁበት የመስክ ሥራ  የዛሬው ነው። ከሰዓታት በኋላ ራሱ ንዴቴ ስላለቀቀኝ በየመሃሉ በረጅሙ እተነፍሳለሁ። ብቻዬን እያወራሁ እንደሆነ የተረዳሁት “ልጄ?” የሚል ድምፅ ስሰማ ነው። በልዩ ሐሳብ ከመመሰጤ የተነሣ በቦታው ስላልነበርሁ በጥቂቱ ደነገጥኩ። ከጎኔ አብረውኝ የተሳፈሩ ካህን ነበሩ የተናገሩት። እንዴት ይህን ያህል ሰዓት አብረን ስንጓዝ ከጎኔ እንደተቀመጡ እንኳን ማስተዋል አልቻልኩም? ይህን ያህል የለሁም ነበር ማለት ነው? 

“አቤት አባ?” አልኳቸው አቀማመጤን እያስተካከልኩ። 

“ምን ሆነሃል ልጄ? እንደው ከቅድም ጀምሮ እኮ….. ስትብሰለሰል መንገዱን ጨረስከው።” አሉኝ ረጋ ባለ አባታዊ አንደበት። 

“አ…አይ ምንም አባ…እንዲሁ ስለሥራ ጉዳይ እያሰብኩ ትካዜ ገብቶኝ ነው።”

አልኳቸው ብዙም ስለጉዳዩ ለማውራት ባልፈለገ እና ለመናገር ግራ በተጋባ ስሜት። 

ምን ብዬ አስረዳቸዋለሁ…. ምኑ እንዳናደደኝ እና እንዳስኮረፈኝስ እንዴት እገልጽላቸዋለሁ? ከየት ብጀምርስ ይገባቸው ይሆን? ተውኩት። አለባብሼ ለማለፍ ወሰንኩ። ከሁለት ቀናት በፊት ዋይ.ሲ.ጅ ከሚባለው ድርጅቴ ለሥራ ወደዚች ቦታ ስለ ማሽን ተከላ(ፕላንቲንግ) ማስገንዘቢያ ሥልጠና ለመስጠት እና የማሽን ተከላውንም ለማገዝ ፱ ቀን ተልእኮ ተሰጥቶኝ ነው የተላክሁት…… ብዬ መጀመር ይኖርብኛል ነገሩን ለማስረዳት። ይህ ደግሞ ለኔ አሰልቺ  ሆነብኝ ። ማሽኖች ይተከሉበታል ተብሎ የታሰበው የሥራ ቦታ ስደርስ የገጠመኝ ነገር ግን እንደጠበቅሁት አልነበረም። ለሚመለከተው ሰው ማንነቴን አስረድቼ ወደ ሥራው ለመግባት ያለብኝን ኀላፊነት እና ሥልጣን በዝርዝር ሳስረዳ በቦታው ያሉ አለቆች ነገሩ አልተዋጠላቸውም። ፊታቸው ላይ የንቀት እና የቅያሜ ገጽታ ተነበበ። ወደ ሥራው ስንገባማ ጭራሽ ልንግባባ እና ሊያዳምጡኝ አልቻሉም። የማውቀውን ነገር ሁሉ ረጋ ብዬ ለማስረዳት ሞከርሁ። ሰዎቹ አንድ ዓይነት ሆኑብኝ። ሊያዳምጡኝ ፈቃደኛ አልሆኑም። ሥልጣናቸውን የተቀሙ ያህል ነው እየነደዳቸው ያለው። እንደተረዳሁት ከሆነ በማንም ትእዛዝ ሥር መሆን አይፈልጉም። ግን እኮ እኔ የመጣሁት በማሽን ተከላው ሥራ ላማክራቸውና ልረዳቸው እንጂ አለቃ ልሆንባቸው አልነበረም። ያውም ለ፱ ቀን ብቻ። እንዴት ቢያስቡት ነው? እየተተከለ ያለው ማሽን እኮ….. በትክክል ካልተገጠመ የሠራተኛውን ሕይወት በሙሉ ሊቀጥፍ የሚችል ነገር ነው። 

ንዴቴን አምቄ ሊፈጠር ስለሚችለው አደጋ ለማስረዳት ሞከርኩ። ትዕግሥቴ እስኪሟጠጥ ድረስ በቻልኩት መንገድ ሁሉ ለፈለፍሁ። ጭራሽ ይግረምህ ብለው የማሽን ተከላ ሥራውን ጀመሩት። ስለሥራው ስለ ማሽኑ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች ቢሆኑ እኔ ምንም አይገርመኝም ነበር። ነገር ግን ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ከአነጋገራቸው ራሱ መረዳት ችያለሁ። እነዚህ ሰዎች ገጠምን ብለው በሚሠሩት ስሕተት ነገ ሠርቼ እበላለሁ ያሉ የደኃ ለፍቶ አደር እጆች እየተቆራረጡ ሲወድቁ ማሽኑም ጥቅም ሳይሰጥ በማን አለብኝነት በተሠራ ስሕተት የሰው ሕይወት ሲቀጥፍ ማሰብ ዕረፍት ሊሰጠኝ አልቻለም። 

ጉዳዩን ለበላይ አለቆቼ ደውዬ አሳወቅሁ። ከሰዎቹ ጋር ተገናኙ አወሩ ተጨቃጨቁ….ብዙ ብዙ ነገር። ለኔም የመጨራሻ ትእዛዝ ተሰጠኝ። በቻልኩት መጠን ነገሩን አረጋግቼ ችግሩን ለመፍታት እንድሞክር እና ካልሆነ ድርጅታችን ኀላፊነቱን እንደማይወስድና ቦታውን ለቅቄ ወደ ቢሮዬ እንድመለስ ተነገረኝ። 

ዕረፍት አደረግሁና በነጋታው ከትናንትና የተራረፈች ጭላጭ ትዕግሥቴን አጠረቃቀምኩና በቦታው የሥራ መሪ ሆኖ የተመደበውን ሰው መናገር ያለብኝን ነገር ለመናገር ስጀምር ባልጠበኩት ሁኔታ በጥ…….ፊ ከደነኝ። በጣም ደነገጥሁ እንዲህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅሁም ነበር። የምናገረው ጠፋብኝ። የምለው አጣሁ። በንዴት መንቀጥቀጥ ጀመርኩ። 

የውስጤን ስሜት እንኳን ያኔ አሁንም ማሰብ አልችልም። ለራሳቸው ብዬ በረዳኋቸው? ትሞታላችሁ ይህንን አስተካክሉ ባልኳቸው?

ምንም አልተናገርኩም። ወዲያውኑ ሻንጣዬን አንሥቼ ከቦታው ጠፋሁ። አሁን ወደ መጣሁበት ለመመለስ መንገድ ከጀመርኩ ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ሆኖኛል። … ይህን ሁሉ ነገር ከጎኔ ለተቀመጡት ካህን ልነግራቸው አሰብኩና ….ለኔ ራሱ እንደገና ሕመሜን መቀስቀስ ንዴቴን ማባባስ ይሆንብኛል ብዬ አጠር አድርጌ በግርድፉ 

“ አባ…… ሥራ ቦታ…. እንዳትጎዱ እንርዳችሁ ያልናቸው ሰዎች …. መልሳቸው ክፋት ሆኖብኝ….. በሱ ቅሬታ ተሰምቶኝ ነው።” አልኳቸው እና ትንሽ ስለተሸማቀቅሁ ሸረፍ አድርጌ አየኋቸው። እስክመልስላቸው ዐይን ዐይኔን እያዩኝ ነበር። ሳልመልስላቸው ቆዬሁ እንዴ? አልኩ ለራሴ። በየመካከሉ መኪናው እንደመንገጫገጭ ይላል።

ጥቂት ቆይተው እንዲህ አሉኝ 

“ልጄ …. አሁን ወቅቱ የጾመ ነቢያት ወቅት ነው። ነቢያት የጌታን መወለድ እየተጠባበቁ እንደጾሙት እኛም በዓለ ልደቱን ለማክበር የምንዘጋጅበት፣ ለእኛ ሲል የተቀበለውን ሥቃይና መከራ የምናስብበት ወቅት ነው። ይህንን ወቅት ስታስብ ጌታ ለድኅነተ ዓለም ለሰው ልጅ ጥቅም ሲመጣ ሲወጣ ሲወርድ ሰው በተቃራኒው የደረሰበትን መከራ ታስባለህ። እና አንተም መልካም ስላደረግህ በመልካም ፋንታ ክፉ ቢመለስልህ አይግረምህ። የሰው ልጅ መድኃኒቱን መቃወም ልማዱ ነው። ‘አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር’ ይላል መጽሐፍ።” አሉኝና ወደ ፊት እያዩ ዝም አሉ።

እኔንም ወደ ሌላ አንክሮ ወሰዱኝ። ከልጅነት እስከ ዕውቀት በየቦታው የተማርኩት የነገረ ሥጋዌ ትምህርት በሐሳቤ ተመላለሰ። እንዴት ግን ክርስቶስን የሚያህል መድኃኒት በሰው ልጅ ዘንድ ተናቀ? ለዓለማት ሁሉ ፈጣሪ የሰው ልጅ ቦታ ነፍጎት በበረት ሲያስተኛው መታገሥ እንዴት አይነት ትዕግሥት ነው? ሰው ግን እንዴት ደፋር ቢሆን ነው ክፉና ደጉን ላሳይህ ያለውን ጌታውን በጥፊ የመታው? 

ጌታስ እንዴት ትዕግሥተኛ ቢሆን ነው ለእርሱ አንዳች በማይጨምርለት ጉዳይ ላይ የሰውን ልጅ ያን ያህል የታገሠው። መከራ ሲያደርሱበት እንዴት ዝም አለ? የሰው ልጅ በሞት እንዳይወሰድ እስከመቃብር ድረስ መከራን የታገሠለት እንዴት ዓይነት ፍቅር ቢኖረው ነው? 

እያልኩ መልስ በማላገኝላቸው የመገረም ጥያቄዎች ስወጣ  ስወርድ ቆየሁና ድንገት የኔ ጉዳይ ትዝ አለኝና ውስጤ ድንግጥ አለ። ምን ያህል ከንቱ ሰው እንደሆንኩ እየተገለጠልኝ መጣ። ሰውነቴ መሸማቀቅ የጀመረ መሰለኝ። ጌታ እስከመስቀል ሥቃይን ሲቀበል፣  ለገዳዮቹ በፍቅር ሲጸልይ፣ ለወጉት መልካምን ሲያደርግ ከነበረ እኔ ስናገር አልሰሙኝም ብሎም በጥፊ መቱኝ ብዬ እንዴት ይህን ያህል እቀየማለሁ? እንዴት ወደ ስሕተት ጎዳና ሲሄዱ ወደ ጉዳት ሲገሠግሡ እያየሁ ጥያቸው መጣሁ? ምንስ ቢያደርጉኝ እና ቢበድሉኝ የኔ ጉዳት ከእነርሱ ጉዳት በልጦ ነው? እንዴት ዓይነት ከንቱ ሰው ነኝ?  

በሚደርስብኝ ነገር ሁሉ ክርስቶስን መምሰል ካልቻልኩ የኔ ክርስትና ምኑ ላይ ነው? የልቤ ላይ እምነት አንሳ አንሳ እጅ….ግ ኢምንት ሆነችብኝ። ወደ ሥራ ቦታው ልመለስ ፈለግሁ። ብዙ ርቀት መጥቻለሁ። እንደሚታየኝ ሁሉ አንገቴን አዙሬ በመኪናው የጀርባ መስታወት ወደኋላ ተመለከትሁ። አካባቢው ከዐይኔ ተሠውሯል። በረጅሙ ተነፈስኩ። 

ድጋሚ ስሜቴ ተቀይሮ ከፋኝ። አዲስ አበባ እንደደረስኩ ተመልሰህ ሂድ ብባል እና ብመለስ ደስተኛ ነኝ። የዛሬውን ፈተና ወድቄያለሁ። ለወደፊት ፈጣሪዬ እንደገና ዕድል ከሰጠኝ ለማስተዋል እሞክራለሁ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ባሳለፍኩት የክርስትና ጉዞዬ መንፈሳዊነት አልገባኝም። ቢገባኝ ባስተውል ኖሮ እነዚያ ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ለኔ ጥሩ የትሕትና ትምህርት እየሰጡኝ መከራንም እያለማመዱኝ ነበር። ምን ያደርጋል….. አልቻልኩበትም። 

አወይ የኔ ክርስትና ….. እኔም ክርስቲያን ቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ዮሴፍን የመሰሉ ብርቱና አስተዋይ ወጣቶችም ክርስቲያን…… አልኩና በራሴ እጅግ ተናደድኩ ራሴን ታዘብኩት። ድንገት ከጎኔ የተቀመጡት አባት ትዝ አሉኝና ቀስ ብዬ በኃፍረት አንገቴን በግማሽ አዙሬ አየኋቸው። ፊት ለፊት እያዩ በራሳቸው ሐሳብ የተወሰዱ ይመስላሉ። ዳዊታቸውን በእጃቸው ይዘው እያንሰላሰሉ ከጎናቸው መቀመጤን የረሱ ይመስላል። 

እውነታቸውን ነው… ምኔ ይታወሳል ደግሞ እኔ። እንደገና በራሴ ሁኔታ በመከፋት አዲስ አበባ ለመድረስ የሁለት ሰዓት ያህል ጉዞ የሚቀረውን መኪና መስኮት ተደግፌ በራሴ እምነተ ቢስነት ላይ ትካዜዬን ቀጠልሁ። 

ለካ ክርስቶስ በየዕለቱ እየተወለደ በየዕለቱ በልባችን ግርግም ይተኛል። ለካ በየዕለቱ በሕይወታችን አደባባይ ይገረፋል፤ ይገፈፋልም። ለካ “ኑ ሕይወትን ታገኙ ከሞት ትድኑ ዘንድ ሥጋዬን ብሉ ደሜንም ጠጡ” እያለ ለሚጣራው ጌታ መልሳችን መከራ እና ክፋት ሆኗል ። የእኝህ ካህን እጅግ ያነሠች እና ያልተዝረከረከች ንግግር እንደነፋስ ሽውታ ውልብ ሽው… ብላ ነገሬን ሁሉ መረመረችው ራሴንም ለራሴ ገለጠችልኝ። ምን ጊዜም ቢሆን ጾመ ነቢያትና  የጌታ ልደት  ለእኛ ሕይወት እንደ መስታወት ነው። ራስን መመልከቻ የነፍስ መስታወት ስለሚያገለግል ልንጠቀምበት ይገባል። 

የዐደባባይ በዓላት መንፈሳዊነትና ተግዳሮቶቻቸው

Details
Written by: በዲ/ን ዶ/ር አክሊሉ ደበላ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 02 January 2021
Hits: 3072
  • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን

መግቢያ

እግዚአብሔር አምላካችን  ለሰው  የሚያስፈልጉ ምድራዊ ጉዳዮችን  ከሰው ልጅ መፈጠር በፊት ያዘጋጀለት ሲሆን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን አንድ ስጦታ ግን ከሰው መፈጠር በኋላ ፈጥሮለታል። ከሰው ልጅ መፈጠር በኋላ ለሰው ልጅ የተሰጠው ይህ ውዱ ስጦታ ዕለተ ሰንበት ነው። ሰውን በራሱ አምሳል ፈጥሮ የጌትነቱ ምሳሌ አድርጎ በምድር ላይ ያሰለጠነው አምላካችን ይህችን የተቀደሰችውንም ሰንበት ለዕረፍት በማድረግ አብነቱን ይከተል ዘንድ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በዚህች ቀን ከሥራው ዐረፈ።  ዓርብ የተፈጠረውን አዳም ዘላለማዊ ሕይወትና መንግሥት  የተገባው አድርጎ ሲፈጥረው የዚህን የዕለተ ዓርብ ፍጥረት የዕረፍቱን ቀን  በራሱ በጌታ ዕረፍት በሰንበት ቀን አደረገው። በዚህም ከባሕርይ አምላክ የተሰጠው የጸጋ ጌትነት ታላቅ መሆኑን ገለጠው። ጌታችን በዳግም ምጽአት ለፍርድ ሲመጣ ሰማይና ምድር ሲያልፉ የሰው ልጅ ግን የማያልፍ ነው፤  ዕረፍት ያደርግባት ዘንድ የተሰጠችውም ሰንበት  ደግሞ የማታልፍ ናት። 

ሰንበትን የለያት፣ የቀደሳት፣ ያከበራት፣ በዓል ትሆነን ዘንድ የሰጠን እራሱ የፈጠራት እግዚአብሔር ነው። ይህንን አስቀድሞ አርዓያ ሊሆነን በሷ  በማረፍ፣ ኋላም ትእዛዝ አድርጎ በሕገ ኦሪት አደለን። በዚህም የተቀደሰችውን በዓል ማክበር ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ያለው ዋጋ ምን ያህል ጽኑዕ እንደ ሆነ አስረዳን። አሠርቱ ትእዛዛትን በመስጠት ብቻ ሳይሆን  የኦሪቱ ሰንበት አከበባር ዝርዝር አፈጻጸም ምን መምሰል እንዳለበት ሥርዓት በመስጠትም ጭምር የተብራራ ነበር። ከዕለተ ሰንበት ባሻገር እስራኤላውያን በዓል አድርገው ማክበር ያለባቸው ጊዜያት የትኞቹ እንደ ሆኑ በሕገ ኦሪት ተደንግጎላቸዋል።

ይህ ሂደት ሳይቋረጥ ወደ አዲስ ኪዳንም ተሸጋግሯል። ጌታችንም በሚያስተምርበት ወቅት በኦሪቱ ከተሰጣቸው ሕግ መንፈስ በወጣ መልኩ ሲያደርጉ የነበረውን አከባበር ነቅፎባቸዋል። ይህም የአዲስ ኪዳን በዓል አከባበር ምን መምሰል እንዳለበት ለማወቅ አንዱ ትልቅ ጉዳይ ነበር። ሌላው ደግሞ ሕግ ካልተሰጣቸው ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና የተመለሱ ምእመናን በበዓላት አከባበር ላይ የራሱ የሆነ ፈተና  የማምጣቱ ጉዳይ ነው።  በኋላ ላይ እንደምናየው እነዚህ ሁለቱ ፈተናዎች (ማለትም በቤተ አይሁድ የነበረ በዓል አከባበርና በቤተ አሕዛብ የነበረ በዓል አከባበር) ዛሬም ጭምር የኦርቶዶክሳዊ በዓላት አከባበር ፈተናዎች ሆነው አሉ።

እነዚህ ዳራዎች ዛሬ ላይ ምን ዓይነት ችግሮች ይዘው እንደ መጡና ለነገዋ ቤተክርስቲያን የሚያስፈልጉ የመፍትሔ አሳቦችን ለመጠቆም ይረዱ ዘንድ ትናንትን ማየት አስፈላጊ በመሆኑ እስቲ እንመልከት። በተለይ በዓላት በቤተ አይሁድ ከዘመነ ኦሪት፤ የቤተ አሕዛብ ልማድ፣ በዓላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት እንዴት እንደሚከበሩ፣ ዛሬ ላይ የአደባባይ በዓሎቻችን ምን እንደሚመስሉ እና መጨረሻም ላይ የነገው ምን መምሰል እንዳለበት ሐሳብ በማከል ለማቅረብ እንሞክራለን።

በዓላት በቤተ አይሁድ

ከሁሉ በፊት የቀዳሚት ሰንበት መከበር የብሉይ ኪዳን በዓላት ወኪልና ጥንታቸው ብትሆንም ብቸኛ በዓል ግን አልነበረችም። ከቀዳሚት ሰንበት ባሻገር ያሉት (ሰንበታት) ተብለው የተገለጡም ነበሩ። ዘሌ. ፳፫፥፴፪። ከዚህም በተጨማሪ የራሳቸው መነሻ ያላቸውና የሚታወቁ በዓላትም ነበሩ። ለምሳሌ

እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበትን ቀን የሚያከብሩበት፣ የቂጣ በዓልም በመሆኑ በዓለ ናዕት እያሉ የሚጠሩት ፓሳሕ ብለው የሚጠሩት በዓለ ፋሲካ (ዘጸ.፲፪፥፩-፳፣ ዘሌ.፳፫፥፭-፰)

እስራኤላውያን የአዝመራቸውን በኵራት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ቍርባን የሚያቀርቡበት በዓለ ሠዊት ወይም የመከር በዓል (ዘጸ.፴፬፥፳፪፣ ዘኁል.፳፰፥፳፮)

‹‹የዳስ በዓል›› የተባለውና አዝመራቸውን ሰብስበው ካስገቡ በኋላ ዳስ ውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን በማመስገን የሚያከብሩት በዓለ መጸለት (ዘሌ.፳፫፥፴፱-፵፬)

መለከቶችን በመንፋት በዓል አድርገው የሚያከብሩበት ቀን (ዘኁ.፳፱፥፩፣ ዘሌ.፳፫፥፳፫-፳፭)

ሊቀ ካህናቱ   በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በመግባት  የመሥዋቱን ደም በታቦቱ መክደኛ ላይ ከረጨ በኋላ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ  በሚለቀቀውና የሕዝቡን ኃጢአት በሚሸከመው ሁለተኛ ፍየል  ላይ በመጫን የደኅንነት መሥዋዕት የሚሰዋበት የማሥተሥሪያ ቀን ወይም ዕለተ አሥተሥርዮ፤

በንጉሥ አርጤክስስ ዘመን በክፉው ሐማ ተንኮል ሞት ተደግሶላቸው የነበሩ እስራኤላውያን፡ መርዶክዮስ ጾምና ጸሎትን በማወጅ በየጊዜው ፉሪ የተባለውንም ዕጣ እንዲጥሉ በማወጅ፣ በጾምና ጸሎት  እስራኤላውያን እንዲተርፉ የሆነበትን ቀን በማስመልከት የሚከበር በዓል፤

በመቃብያን የተጀመረው የመቅደስ መታደስ መታሰቢያ ቀን (ዮሐ.፲፥፳፪)

ሰውም መሬትም በማረፍ ለድሆች መልካም በማድረግ የሚከበርበት በዓለ ኅድገት (ዘጸ.፳፭፥፩-፯)

የወር መግቢያ መባቻን የሚያከብሩበት ቀን (መዝ.፳፭፥፰-፲፪)

የኀምሳ ዓመት በዓልን የሚያከብሩበት ኢዩቤልዩ (ዘሌ.፳፭፥፰-፲፪)

እነዚህንና የመሳሰሉትን በዓላት እንዲያከብሩ ያዘዛቸው ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም በአጠቃላይ እስራኤላውያን በታዘዙት መሠረት በዓላትን አክብረዋል ማለት ግን አይቻልም። ይልቁንም በዘሌ.፳፫፥፩-፬ ላይ ‹‹..ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፡- ቅዱሳት ጉባኤያት ብላችሁ የምትጠሩአቸው በዓላቴ የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። ስድስት ቀን ሥራህን ትሠራለህ፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤  ለእግዚአብሔር ቅዱስ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም። በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፣ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው የተቀደሱ ጉባኤያት ናቸው።›› ብሎ በዝርዝር ከሰጣቸው የበዓላት አከባበር በተጨማሪ ራሳቸውም ያልተፈለገ ነገር በመጨመር፣ ወግ በማብዛት፣ የበዓልን ጥቅም በዘነጋና ፈቃዳቸውን ለመፈጸም በተመቸ መልኩ ያከብሩ ነበር። 

እግዚአብሔር የሰጣቸው በዓል ተግባረ ሥጋን በመተው መንፈሳዊ ጉባኤን በማድረግ፣ የነፍስ ተግባራትን በመሥራት፣ ልዩ መሥዋዕትን በማቅረብ፣ በታዘዙ ጊዜያት ወደ ቤተ መቅደሱ በመውጣት፣ ምስጋናን በማቅረብና በመሳሰሉ መልኩ የሚያከብሩበት ነበር።  ሆኖም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው  ሲያስተምር ግልጽ እንደ ሆነው መምህራነ አይሁድ የተለያዩ ወጎችን በሕዝቡ ላይ በመጫን አስጨናቂ የሆኑና ከመንፈሳዊ ዓላማ አንጻር ጥቅም የሌላቸውን የበዓል አከባበር ልማዶችን ባሕል አድርገው ነበር። ለምሳሌ መጽሐፋዊውን  ትእዛዝ በመለጠጥና ሌላ ትርጉም በመስጠት ዜና አይሁድን የጻፈው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን እንደ ገለጸው በዕለተ ሰንበት ወደ ሽንት ቤት እንኳን አይሄዱም ነበር። ከዚህም ባሻገር መጽሐፋዊ ያልሆኑ ከሕጉና ሥርዓቱ የወጡ የበዓል አከባበር ልምድም ይከተሉ ነበር። ለምሳሌ  ሰንበትን ማክበርና መንፈሳዊነት የሚገኘው ፈቃደ እግዚአብሔርን በመፈጸም ሳይሆን በሆነ ርቀት ክልል ውስጥ በመገኘት አድርገው  ያከብሩ የነበረበትና የሰንበት መንገድ ብለው ይጠሩት የነበረ (ሐዋ.፩፥፲፫)፣ ሰንበት አያከብርም በሚል ጌታችንን ሲከሱበት የነበረው ፈውሰ ሥጋን መቃወም፣ የሰውን ሥጋዊ ድካም ያላገናዘበ እጅግ ጥብቅ ሸክምን በሕዝቡ ላይ መጫንና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።  

በዓላት በቤተ አሕዛብ

ሕገ ኦሪት ያልተሰጣቸው፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ያልተባሉቱ አሕዛብ  ደግሞ በሌላ የበዓል ትርጉምና መልክ ሲያከብሩ ነበር። የዚህኛው የበዓል አክብሮት ምንጩ አምላክ ሳይሆን  ፍጡር፣ ግቡም መንፈሳዊ ሳይሆን ሥጋዊ፣ አከባበሩም ሥርዓታዊ ሳይሆን ዘፈቃዳዊ የሆነ ነበር። የአሕዛብ በዓል መነሻው የጥንት ግሪክ አማልክት ሲሆኑ ሕዝቡም ለነዚህ አማልክት ማስታወሻ በሆኑ ቀናት ያስደስታቸዋል ብሎ በሚያስብበት መልኩ በዓል ያደርጋል። አማልክቶቹም በጊዜና ዓይነት ብዙ ቢሆኑም በጣም የታወቁጽና በኦሎምፐስ ተራራ ላይ ይኖራሉ ተብለው የሚታሰቡና ኦሎምፒያንስ ተብለው የሚጠሩት፣ በቀኖናቸው  በቍጥር አሥራ ሁለት ሲሆኑ ለእነርሱ መታሰቢያነት የሚውሉ በዓላት ነበሩ። አምልኮታቸውና በዓል አከባበራቸውም መጽሐፋዊ ወይም ምሥጢራዊ ሳይሆን ከፍርሐት የመነጨ ነበር።  አማልክቶቻቸውም በፍርሐት በተሞላ ምናባቸው የተፈጠሩ ናቸው። በዓሎቻቸውም አስጨናቂ ሁኔታ ሲገጥም፣ የተፈጥሮ ክስተት ሲዛባ፣ በአካባቢያቸው አንድን ለውጥ ሲያዩ መሥዋዕት በማቅረብ የሚያከብሩት ነበር።

   ለምሳሌ፡-  

√ የፀሐይ ሙቀት ሲያይል የፀሐይና ትንቢት፣ እንዲሁም የሳይንስና ሕክምና አምላክ አድርገው የሚያስቡት አጵሎስ ‹‹ተቈጥቶ ነው›› ብለው ያስባሉ፤

√ ባሕር ስትታወክ ‹‹በባሕርና አየር ላይ ይተነፍሳል›› ብለው የሚያመልኩት  የባሕር አምላክ ፖሲደን  ‹‹ተቈጥቶ ነው››።

√ የሽብር አምላክ (Deimos), የፍቅር አምላክ Cupid (Eros)፣ የጦርነት አምላክ  የተባለው ማርስ (Ares)፣ የጥበብና ጦር አምላክ የሆነቸው Athena፣ የጉልበት አምላክ የሆነው  Kratos እና ወዘተ...

እነዚህ አማልክት የሚታሰቡበት ቀን ቢኖራቸውም በዓላቸው መሥዋትን በማቅረብ የተወሰነ፣ ሥጋዊ ተድላ ደስታን መሠረት ያደረገ ነበር። ይልቁንም ሥራን የሚከለክል አልነበረም። በአብዛኛው  ልማደ አሕዛብን በማድረግ፣ ለወንጌልም ሆነ ለኦሪት ትእዛዝ የማይመች ድርጊትን በመፈጸም የሚከበር በዓል ነበር።  ምንም ልማድ ቢፈጽሙ፣ ምንም ሥራ ቢሠሩ የሚከለክልና ስሕተት እንደ ሠሩ የሚቈጥርባቸው ሥርዓት ስላልነበራቸው ክርስትና ተሰብኮ ወደ ክርስትና በተመለሱበት ጊዜ የራሱ ችግር ይዞ መምጣቱ አልቀረም። 

በርግጥ እነዚህ ሁለቱም ወገኖች፡- አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ወደ ክርስትና በሚመለሱበት ጊዜ ወግና ልማዶቻቸውን ትተው ለወንጌል በሚመች መንገድ ለመሄድ ችግር ገጥሞአቸዋል።  በተለይ ክርስቲያናዊ ሥርዓትን ወጥ በሆነ መልኩ በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ እንዲከናወን ለማድረግ የቀድሞ ልማዶቻቸው ፈተና መሆናቸው አልቀረም። ለምሳሌ፡- ቅዳሜን እንደ ሰንበት ያከብሩት ለነበረ ቤተ አይሁድ የጌታ ዕለት የተባለችውን እሑድን ለመቀበል፣ ግዝረትን በጥምቀት ለመተካት ተቸግረው ነበር። በቤተ አሕዛብም በወንጌል የታዘዙትን ይፈጽሙ ዘንድ፣  በኃጢአትና ጽድቅ፣ በሥርዓታዊና ኢ-ሥርዓታዊነት መካከል ያለውን ድንበር ያልተለማመደው  ሕይወታቸውና  ኢክርስትያናዊ  ልማዳቸው ብዙ አስቸግሯቸዋል። የኦሪትን ትእዛዝና ሥርዓት ለመፈጸምም ተቸግረዋል። እነዚህ የኋላ ምንጫቸው የግሪክ አማልክትን ማምለክና በዚህ ሂደት ውስጥ የተለመዱ አሕዛባዊ ልማዶች የሆኑ በሥልጣኔ ሽግግር የምዕራቡን ዓለም አስታክከው እየተላለፉ መሄዳቸው አልቀረም።

በዓላት በክርስትና 

ለዓለም የተሰበከችው  ወንጌል  ሕዝብና አሕዛብን አስታርቃ ለአንዲት መንግሥተ እግዚአብሔር የምታበቃ ናት። ይህን መንፈሳዊ ዕርቅ ለመፈጸም የሕዝብና አሕዛብን ልማድ ማስታረቅ፣ የሁለቱን መንፈሳዊ ዝንባሌ ፍጹም መንፈሳዊ ወደ ሆነው ክርስቲያናዊ መንፈሳዊነት ማስገዛት የወንጌል ትምህርት ኃላፊነት ነበር። በመሆኑም የቀድሞ በዓሎቻቸው መንፈሳዊ በሆኑ ክርስቲያናዊ  በዓላት ተተክተዋል። ለምሳሌ ከቤተ አይሁድ ብንወስድ በበዓለ መጥቅዕ - ቅዱስ ዮሐንስ፣  በሠርቀ ወርኅ - ልደተ ክርስቶስ፣ በበዓለ መጸለት - በዓለ ጥምቀት፣  በበዓለ ፍስሐ - ስቅለተ ክርስቶስ፣ በበዓለ ፋሲካ - በዓለ ትንሳኤ፣ በበዓለ ሠዊት -  በዓለ ጰራቅሊጦስ፣  በጾመ አስቴር - ጾመ ረቡዕ፣ በጾመ ዮዲት - ጾመ ዓርብ፣ በጾመ ሙሴ -ጾመ እግዚእ ተተክተዋል።  

ከክርስትና በፊት በነበራቸው ልማድ አሕዛብ ብዙ አማልክቶቻቸውን ያስቡ በነበረው ልማድ እንዳይቀጥሉ፣ የበዓል ምኞቶቻቸው አሕዛባዊ ሆነው እንዳይቀሩ፣ የሕዝቡን የረዥም ዘመን ፍቅረ ጣዖት ለማስተው በነዚያ ዕለታት በጣዖታት ስም ተሰይመው ይከበሩ የነበሩ ዕለታትን  ቀደምት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን ስም እየለወጡ እንዲያከብሩ አድርገዋል። ለምሳሌ፡-  የባሕር አምላክ ፖሲዶንን ያከብሩ የነበረበትን ዕለት ወደ ክርስትና ከተመለሱ በኋላ ኒኮላዎስ  የተባለውን ቅዱስ በየዓመቱ ሲያከብሩበት፣ የጦር አምላክ የሚሉትን ኦሪስን በሚያከብሩበት ዕለት ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተክተው ያከብሩበታል።    

እዚህ ላይ መታወቅ የሚገባ ነጥብ በዓል የማክበር አስፈላጊነት በብሉይ ኪዳን የነበረና በሐዲስ ኪዳንም የቀጠለ፣ ራሱ ጌታችን የሰንበትን አከባበር በተመለከተ አይሁዳውያን ሲፈጽሙ የነበረውን ስሕተት አርሞ ክርስቲያናዊውን አከባበር ምንነት ከመንፈሳዊ ዓላማው ጋር እንዴት መዛመድ እንደሚገባው አስረድቶ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ቀናውን መንገድ ማሳየቱን ነው። ሆኖም የሰንበት አስፈላጊነት ላይ ለእስራኤል ዘሥጋ የሰጠውን ትእዛዝ ለእስራኤል ዘነፍስም አጽንቷል። ከሱ የተማሩ ሐዋርያትም፣ ኋላ የተነሡ አባቶችም ይህን አምላካዊ ትእዛዝ ፈጽመዋል። አስፈላጊ በሆነበት ጊዜም ወደ ፊት ለሚመጣ የክርስትናው ዓለም የሚበጀውን ቀኖና ቀንነው፣ ሥርዓት ሠርተው፣ በቍጥር ሰፍረው፣ በጊዜ መጥነው ሰጥተውናል። ለምሳሌ፡- የዕለተ ሰንበት አስፈላጊነት፣ የክርስቲያኖች የሰንበት አከባበር መልክ፣ የትንሣኤና የመሳሰሉትን መቼና እንዴት ሊከበሩ እንደሚገባ ከጥንት  ከአንደኛ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሊቃውንት ብዙ አስተምረውበታል። ይልቁንም ሠለስቱ ምዕትና በሌሎችም ዓለም ዓቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ላይ የተገኙ ሊቃውንት በዓላትን  አስመልክቶ  የክርስትና ዓለም መከተል የሚገባውን መንፈሳዊ መርሕ አብራርተው አስቀምጠዋል። ለምሳሌ ቅዱስ አትናቴዎስ ስለ ሰንበተ ክርስቲያን ያስተማረውን ማስታወስ ያስፈልጋል። ክርስትና ወደ ዓለም ሲስፋፋም ይህን ትምህርተ አበው መሠረት አድርጎ የሄደ በመሆኑ በተለይም ደግሞ በኦርቶዶክሱ ዓለም የበዓላት አከባበር ወጥነቱን ሳይለቅ፣ በሚከበሩበትም ወቅት የሥርዓት ልዩነት ሳይጎላባቸው ብዙ ቆይቷል። ለምሳሌ በሁሉም አኀት አብያተ ክርስቲያናት  የልደተ እግዚእ እና በዓለ ጥምቀት  እስከ አራተኛ መ/ክ/ዘመን ድረስ በአንድነት ይከበሩ ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአደባባይ በዓላት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ቀኖና የራሱ የሆነ መልክ አለው።  ለምሳሌ ቅዳሜና እሑድን እንደ አንድ ቀን አድርጋ ስታከብር  አከባበሩም እንደ አይሁድ ሰውን እንዳይጫን ሥራም እንዳይፈቱ፣ ይልቁንም እንደ ክርስቲያን  መንፈሳዊ ሥራን እንዲሠሩ ታስተምራለች። እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሰንበት፡- ዕረፍት የሚደረግባት፣ የሚገባ መንፈሳዊ ሥራ የሚሠራባት፣ በቤተ ክርስቲያን በመሰባሰብ  የታመመውን በመጠየቅ፣ የተቸገረውን በመርዳት በመማማርና የመሳሰሉትን በማድረግ ከአይሁድ ልዩ በሆነ መልኩ የሚከበርባት ናት። 

 የበዓላቱም አከፋፈል

√ ሳምንታዊ - በየሳምንቱ ይታሰቡ ዘንድ በሕግና ቀኖና የተደነገጉ ቀዳሚት ሰንበትና እሑድ፣

√ ወርኀዊ በዓላት - የጌታችንን በዓል ሥጋዌውን መሠረት በማድረግ፣ ጽንሰቱንና ልደቱ በማሰብ ወር በገባ በሃያ ዘጠነኛው ቀን፣ ከፍጡራን ሁሉ በላይ የሆነችውን  የእመቤታችን ዕረፍቷንና የመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤቷን መክበር በማሰብ በየወሩ በሃያ አንደኛ ቀን፣ በማዕረግ ከመላእክት ሁሉ የሚልቅ የቅዱስ ሚካኤልን  ገቢረ ተዓምር በማሰብ ወር በገባ በአሥራ ሁለተኛው ቀን  ይታሰባሉ።

√ ዓመታዊ በዓላት - ደግሞ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚታሰቡ፣ ልዩ መታሰቢያ የሚደረግባቸው በዓላት ናቸው። እነዚህም በኢይዓርግና ኢይወርድ ተወስነው በየዓመቱ በተለያየ ቀንና ወር የሚውሉት እንደ ስቅለት፣ ሕማማት፣ ትንሳኤ፣ ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ዕርገትና ጰራቅሊጦስን የመሳሰሉ ዓዋድያት በዓላት እና ሁል ጊዜ በአንድ ወር ውስጥ ባለው የታወቀ ቀን ላይ የሚውሉ ትስብእትን፣ ልደትን፣ ጥምቀትን፣ መስቀልን፣ በዓላተ ቅዱሳን፣ ደብረ ታቦርን የመሰሉ ዓዋድያት ያልሆኑ በዓላት ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ። 

በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ለጌታችን በዓላት ልዩ ትኩረት ሰጥታ ታከብራለች። እነዚህም ዓበይትና ንዑሳን በዓላት ተብለው ይከፈላሉ። ዓበይት  በዓላት የሚባሉት፡- መጋቢት ፳፱ የሚከበረው በዓለ ትስብእት (ጽንሰት)፣ ታኅሣሥ ፳፱ የሚከበረው በዓለ ልደት፣ ጥር ፲፩ የሚከበረው በዓለ ጥምቀት፣ ነሐሴ ፲፫ የሚከበረው በዓለ ደብረ ታቦር፣ በዓለ ሆሣዕና፣ በዓለ ስቅለት፣ በዓለ ትንሣኤ፣  በዓለ ዕርገትና በዓለ ጰራቅሊጦስ ናቸው። ንዑሳት በዓላት የሚባሉት ደግሞ፡- ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ በዓለ ጌና (ታኅሣሥ ፳፰)፣ ግዝረት፣ ልደተ ስምዖን፣ ቃና ዘገሊላ፣ ደብረ ዘይትና መስቀል ናቸው።

ከዓበይት በዓላት  ውስጥ ደብረ ታቦርና ጥምቀት፣ እንዲሁም በንዑሳት በዓላት ውስጥ ደግሞ በዓለ ጌና፣ ቃና ዘገሊላ እና መስቀል በአደባባይ ከቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሚከበሩ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑት ብሔራዊ በዓላት ሆነው ሀገራዊ ዕረፍት ታውጆ የሚከበሩ ናቸው። በሌላ መልኩ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ በዓላት ያልሆኑ የቅዱሳን መታሰቢያ በዓላትና የአደባባይ በዓላት ያልሆኑ የጌታ በዓላት ከድምቀታቸው የተነሣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በመንገዱ ሞልቶ፣ በከተማው ጎልቶ የሚታይባቸው በዓላት ብዙ ናቸው። ከዚህም ባሻገር እንደ ሀገርም እንደ ቤተ ክርስቲያንም የአከባበር ድምቀታቸው የታወቀው፣ ባላቸው የከበረ ቃል ኪዳንና መንፈሳዊ ዋጋ ብዙ  ሕዝበ ክርስቲያን  ከመላ ሀገሪቱና ባሕር ማዶ በየዓመቱ ሄዶ የሚያከብራቸው ቅዱሳት መካናት፡- ገዳማትና አድባራት እንደ አክሱም ጽዮን፣ ቁልቢ ገብርኤል፣ ግሸን ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ደብረ ሊባኖስ ወዘተ የመሳሰሉ አሉ።

የአደባባይ በዓላት ተግዳሮቶች

በመሠረታዊነት የአደባባይ በዓላት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነገረ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊቷ ተግባራዊ ማስተማሪያ መንገዶች ናቸው።  የያዙት መንፈሳዊ ዓላማ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ሠርጾ ፍሬውም በእጅ የሚዳሰስ፣ በዓይን የሚታይ፣ በጆሮ የሚሰማ፣ የሚቀመስ፣ የሚሸት፣ ከምንም በላይ በሕይወት የሚታይ መሆኑ የሚገለጽበት መንገድ ነው። ከሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን እናስተምራለን ከሚሉ ቤተ እምነቶች በተለየ መልኩ ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተማር አምስቱንም የስሜት ሕዋሳትን የምትጠቀም ቤተ ክርስቲያን ይህችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለመሆኑ ማሳያው በክርስትና ትምህርት ያበቡ በዓላቶቿ ናቸው። 

እነዚህ በዓላት በዘመናት ውስጥ የታዩና ተለዋዋጭነትን ያሸነፉ፣ መንፈሳዊ ማኅቀፋቸው በትክክል የሚታወቅ፣ በሁሉም ሕዝብ ውስጥ በጊዜና በአከባበር ሁኔታ ግልጽና የጋራ አረዳድ የፈጠሩ፣ ትውልድን የቀረጹ፣ ላለፈው ትውልድ ታሪክ፣ ለሚመጣ ትውልድ ተስፋ ሆነው ያገለገሉ፣ ወንጌል ሆነው የሰበኩ፣ መጽሐፍ ሆነው የተነበቡ፣ ቅርስ ሆነው የታዩ ናቸው። እነዚህ የአደባባይ በዓላት ከኢትዮጵያ ምድር የቅዱስ ያሬድ ጥዑም ዜማዎች ወደ ሰማይ ያረገባቸው የማዕጠንቱ አደባባዮች፣ ዓለም ኢትዮጵያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኘበት ገጾች፣ ኢትዮጵያም ለዓለም ወንጌልን የምታስተምርባቸው አትሮኖሶች ናቸው።  በነዚህ በዓላት የተነሣ ብዙ ሺህ ወንድሞቻችን ወደ ክርስትና ተመልሰው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል፣ ብዙዎች ወደ እምነቱ ባይመጡም በኦርቶዶክሳዊ ማንነት ቀንተው በአክብሮት  ቆመዋል፣ መልካም ልብስነታቸው ከቤተ ክርስቲያን ተርፎ  ለሀገርም መድመቂያና የክብርና የሞራል ብርድ የማያስመታ ሆኖ ዘልቋል።

ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ጭምር የቤተ ክርስቲያናችን የአደባባይ በዓላት ምትክ የሌላቸው የሀገሪቱ ደማቅ በዓላት፣ ኩራትና እሴቶች ናቸው። በሕዝበ ክርስቲያኑም ዘንድ ያላቸው ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ነው። መንፈሳዊ አገልግሎታቸውም የላቀ ነው።

ሆኖም ዘመኑ የራሱ የሆነ ፈተናንም ደቅኖባቸዋል። በተለይ ዓለማችን፣ ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ካሉበት ወቅታዊ ቁመና አንጻር ስንመለከት የችግሮቹን ክብደት አጉልቶ ስሚያሳየን የመፍትሔዎቹን አስፈላጊነት እንረዳለን። የአደባባይ በዓላት  መንፈሳዊ ይዘት ፈተናዎች እንደ አጠቃላይ እየወደቀ ከመጣው የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት ጋር ባብዛኛው የተያያዘ ቢሆንም ሌሎች ተጨማሪ ግፊቶችም አሉበት።

እንደ አጠቃላይ ግን ከላይ የገለጽናቸው ሐዋርያት ወንጌልን በሰበኩበት ጊዜ የነበሩ ሁለቱ ፈተናዎች ዛሬም ጭምር መልካቸውን ለውጠው ያሉ ይመስላሉ።  ለምሳሌ፡- በቤተ አይሁዳዊ  ጠባያቸው ለበዓላት አከባበር ችግር እየፈጠሩ ያሉት ልማዶች በበዓል ቀናት ምንም ዓይነት ሥራ ያለ መሥራት ዝንባሌዎች፣ በሰንበት የተቀዳ ውሃ የተወቀጠ ቡና የማይጠጡ፣ ወንዝ የማይሻገሩ፣ መጽሐፍ የማይጽፉ የማይደጉሱ፣ ልብስ የማያጥቡ ...ወዘተ አሉ። ሰንበት ነው ብሎ እነዚህን አለማድረግ ግን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና አይደለም፣ ልምዱም የቤተ አይሁድ ልማድ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በወር ውስጥ ካሉት ቀናት ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ ሁሉም ክርስቲያን ሥጋዊ ሥራውን አቁሞ እንዲያከብራቸው የምታዝዘው ሁለቱን ሳምንታዊና ሦስቱን ወርኃዊ በዓላትን ብቻ ነው። ሌሎቹ ቀናት በየአጥቢያ ምእመናን የሚከበሩ ናቸው። በሁሉም ቀናት ሥራ ፈትቶ መዋልን ቤተ ክርስቲያን አላስተማረችም።

በቤተ አሕዛባዊ ገጽታው ደግሞ ያለንበት ወቅት የበዓል አከባበር ችግሮች እጅግ የበዙ ናቸው። ዛሬ ላይ የአሕዛባዊ ልማዶች መግቢያ መንገዶች ብዙ ናቸው። ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓትና ቀኖና እንዲሁም ትውፊት ውጭ ዘመኑን ተገን በማድረግ እየወረስናቸው ያሉ  ልማዶች በርካታ ናቸው። የመገናኛ ብዙኃን፣ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፣ ፊልሞችና የስፖርት መዝናኛ አማራጮች፣ ሥርዓተ ትምህርትና የንባብ ምንጮቻችን ባሳደሩብን ተጽዕኖ የተነሣ ከኦርቶዶክሳዊነት በወጣ መልኩ የምናሳልፍበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። በመንፈሳዊነት ታሽተው የመጡልን ክብረ በዓሎቻችን  የመንግሥት ፖለቲካዊ ፍላጎት እሾህ ሆኖ ሲወጋቸው ይታያሉ። የነፍስን ፍሥሐ ሲያመጡልን የኖሩትን በዓላት በመጠጥና ስካር፣  ለፍትወት ቀጠሮነት ያዋልናቸው  ብዙዎች ነን። 

ከጊዜ ጊዜ ግልጽ እየሆነ ያለው ሥልጣንን ተገን በማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቷን እየበደሉ ያሉ አሉ። ይኸውም ይዞታዋቿ የሆኑ ባሕረ ጥምቀትና ሌሎችን የአደባባይ ማክበሪያ ቦታዎቿን በመንጠቅና ለሌሎች አብያተ እምነቶች መስጠት በብዙ የሀገሪቷ ክልሎች እንደ ወረርሽኝ የተዛመተ በሽታ ሆኗል። ይዞታዎቿን ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሚነጥቁበት ሁኔታ ደግሞ እጅግ አስቂኝና  በሞራል ሚዛን ሲለካ አሳዛኝ ነው። አብዛኞቹ የተነጠቁት ይዞታዎች የማይመለሱ ቢሆንም በስንት የሕዝብ ጩኸት የሚመለሱትም ታሪካዊ ውለታ እንደ ተፈጸመላት አድርገው ብዙ ማስታወቂያ ይሠሩበታል። ቢሆን ቢሆን እስከዚያ ድረስ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ላባከኑበት ጊዜና ጉልበት ላደረሱበት የሥነ ልቦና ስብራት ይቅርታ ጠይቀው መሆን ነበረበት። ይዞታዎቿን ሲቀሙ ቦታውን ቢመልሱም ባይመልሱም የሕዝቡን አእምሮና ትኩረት ይዞታው ላይ በመትከል በዓላቱን ሊያከብራቸው የሚገባበትን መንፈሳዊ ይዘቶች ላይ ትኩረት እንዳያደርግ፣ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን በደሎች ላይ ጊዜ ወስዶ እንዳያስብባቸው፣ ከቦታ ውጭ ያሉ ትላልቅ ጉዳዮችን እንዳያነሣ፣ የሥነ ልቦና ውጊያ አካልም ናቸው።

ሌላው ችግር ቤተ ክርስቲያናችን በዋናነት ለመንፈሳዊ ዓላማ የምታከብራቸውን ቅዱሳት በዓላትን ዋና ትኩረቱን ቱሪዝም የማስመሰል ድባብ አለ። በእርግጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቋ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ ናት። ይሁንና ቤተ ክርስቲያን እነዚህን በዓላት የምታከብረው የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት ለማሳደግ እንጂ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ብላ አይደለም። ሕዝቡም የሚወጣው የቱሪዝምን በዓል ለማክበር ሳይሆን መንፈሳዊ በዓልን ለማክበር ነው። ስለዚህ  ከመንፈሳዊነት በጎላ መልኩ ቀዳሚ ጉዳይ መስሎ በብዙ ሚዲያዎች የሚሰማው ቅኝት  አንዱ አስተዛዛቢ ጉዳይ ነው። ቱሪዝሙ ከበዓሉ መንፈሳዊ ትርጓሜ በኋላ የሚመጣ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ አለበት።

ሚዲያዎች በአንድ ጎኑ የቱሪዝም እሴትነቱን ብዙ እያስተጋቡ የቀረውን ጉዳይ ደግሞ  አርቲስቶችን፣ ዘፋኞችን፣ ታዋቂ ናቸው ብለው የሚያስቡትን ሰዎች የሚጋብዙበት፣ ቀኑን በሙሉ ስለ እነርሱ ሕይወት ታሪክና ሙዚቃቸውን የምንሰማበት ያደርጉታል።  በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ ምድራዊ ዘፋኞችን ብሔራዊ ጣቢያዎች ላይ እየሰማን ውለን በዓል እንዳከበርን ይታለፋል። የመርሐ ግብር ይዘቶቹም ከበዓላቱ መንፈሳዊ ተልእኮ የወጡ ሥጋዊ መዝናኛና ፌዝ የተሞሉ፣ መብላትና መጠጣትን፣ ጭፈራን እንደ ድምቀቱ መመዘኛ የሚመለከቱ፣ በልደትና ትንሣኤ ፍጹም ሰማያዊ በዓላት ላይ የክርስትና ተቃራኒ በሆኑት የዘፈን ኮንሠርቶች ማስታወቂያ የሚያጨናንቁ፣ በዓላቱን አስታክከው ንግድን ለሚያጧጡፉ ተቋማት የሚያስተዋውቁትን ያህል የቤተ ክርሰቲያኒቷን እሴቶችና ትምህርቶች ለማስተዋወቅ ያልተሠለፉ የሬዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች በዝተዋል።

ሌላው የሚዲያዎቹ ችግር የበዓላቱን ማኅበራዊና ባሕላዊ ጎኑን እያጎሉ ነገረ ሃይማኖታዊ ጭብጦቹ ተዳፍነው የሚታለፉበት አጋጣሚ ብዙ ናቸው። ወጣቶቹ እንዴት  እንደሚጨፍሩ፣ እናቶች በዓላቱን የሚያስታውሱ ምግቦችን እንዴት እንደሚያዘጋጁ፣ ጎልማሶቹ ምን  ምን ባሕላዊ ትውፊትን እንደሚከውኑ ወዘተ.. የበዓላቱ ዋና ጭብጥ ሆነው ያልፋሉ። ከምንም በላይ በዓላቱ ሃይማኖታዊ መሆናቸው ተረስቶ ታስቦባቸውም ይሁን በመዘንጋት ተግባራዊ ትኩረት አጥተው ይታለፋሉ። ይህም በመሆኑ ሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወቱን ስለ ማሻሻል፣ ከበዓላቱ በረከትን ስለ ማግኘት ሳይሆን እንዴት ተደስቶ ማሳለፍ እንዳለበት ጥረት እንዲያደርግ ያለማምዳሉ።

በርግጥ ውስጣዊ ድክመቱ በዋናነት የራሱ የሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ ዝንባሌ ድክመት ነው። ለጥምቀት ሄዶ  ባሕረ ጥምቀቱ ጋር ተገኝቶ፡  ነገር ግን ጥምቀትን ሳያከብር የሚመለሰው ብዙ ሰው ነው። ጀበና ሲሰብር፣ ሎሚ ሲወረውር፣ ሥጋውን የሚያስደስት ጨዋታዎች ሲጫወት ውሎ ከጥምቀት የሚገኘውን መንፈሳዊ እርካታ ያገኘ መስሎት ይመለሳል። ሳያውቀው ከቤተ ክርስቲያንና ከኦርቶዶክሳዊ ማንነት ተቃራኒ ቆሞ ይገኛል። ይህም እንደ ምእመንም እንደ ቤተ ክርስቲያንም ብዙ የቤት ሥራ እንዳለ ይጠቁማል። 

በአጠቃላይ የአደባባይ  በዓሎቻችን በአሁኑ ጊዜ ውጫዊ ተጽዕኖና ውስጣዊ  ድክመት ተዳምረው መንፈሳዊ ድምቀታቸው ላይ ትልቅ ፈተና ደቅነውባቸዋል። ቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን ችግሮች አስቀድማ ተረድታ ልጆቿን ለመፍትሔ ማሰለፍ ላይ ጊዜውን የሚመጥን ዝግጅት ያደረገች አይመስልም። ችግሮቹም ከጊዜ ጊዜ እየበዙ እንጂ እየቀነሱ፣ እየሰፉ እንጂ እየጠበቡ አይደለም። ይህም በመሆኑ የነገው ትውልድ ላይ የሚኖረው አደጋ  ከፍተኛ ነውና ዛሬውኑ መፍትሔ ያሻዋል።

የማጠቃለያ አሳቦች

ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ነው። የምታደርጋቸው አገልግሎቶችም ይህን ሰማያዊ ተልእኮዋን መሠረት ያደረጉ ናቸው። የሰማያዊ ቤት አንባሳደር ሆና ፍጥረቱን በምታገለግልበት በዚህ ምድር፡ ሕይወቷ የሚመስለው  የወከለችውን  ሰማያዊ  ዓለም እንጂ የቆመችበትን ምድራዊ ዓለም አይደለም።  የሷ ገንዘብ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ይህንን ማንነቷን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።  ከዚህ የተነሣ በዓላቷም የዚህ ተልእኮዋ አካል ናቸው።  ታቦታቱን ይዛ ወደ አደባባይ ስትወጣ፣ መስቀሉን ይዛ ሕዝብ ጋር ስትሄድ፣ ከበሮና ጸናጽሉን፣ ልብሰ ተክህኖና ነጠላውን ይዛ  በየጥምቀተ ባሕሩ ስትገኝ የቆመችለትን ወንጌል ለመስበክ ነው። ከሰው ፊት ይዛ የምትቆምባቸው እሴቶቿ ሁሉ እሷን የሚሰብኩ፣ እሷን የሚገልጡ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የአደባባይ በዓላቱም መድመቅና መደብዘዝ፣ ሥጋትና ተስፋ መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር ነው። ቤተ ክርስቲያናችን ከምንም በላይ መሥራት ያለባት መንፈሳዊ ይዘቱ ላይ እየላላ ያለውን የሕዝቡ ሕይወት ላይ ነው።  በርግጥ የምታከናውነውም ሥርዓት  ሁሌም መንፈሳዊ ይዘቱ የተጠበቀ ነው። ይሁንና በዓሏን ለማክበር የሚመጣ ማንኛውም ሰው የእርሷን መመዘኛ እንዲጠብቅ የማድረግ ኃላፊነቱ የእርሷው ነው። ወደ ሰርግ ቤት የሚሄድ ሰው ለሙሽራና ለሰርጉ የሚያስፈልገውን አለባበስ የመልበስ ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓላት የሚታደሙ ሰዎች ሁሉ ለእርሷ የሚገባውን ሥርዓት ጠብቀው የመሄድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። በአለባበስ፣ በአዘማመር፣ በአካሄድ፣ በሌላ ማንኛውም ተሳትፎ ቤተ ክርስቲያን የምታዘውን ብቻ አድርገው እንዲጓዙ ለማድረጉ መብቱ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት።  በተለይ ደግሞ ምእመኗ ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

ሌላው ጉዳይ ይዞታዎቿን በተመለከተ የሕዝበ ክርስቲያኑን ንቃተ ሕሊና ማሳደግ፣ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም እንዲቆም ማድረግ፣ ማነቃቃት ያስፈልጋል። ይህንም በማንኛውም ቦታ ላለው ችግር ሁሉ  ኦርቶዶክሳዊ ተቆርቋሪነት እንዲኖረው ብዙ መሥራት ያስፈልጋል። በዚህም ታላቅነቷን፣ ተደማጭነቷን፣ የራሷን መፍትሔ  በራሷ መከተል የምትችል መሆኗን ማሳየት ይኖርባታል። ሕዝቡ ላይ ከተሠራ በኋላ ከመንግሥትና ሌሎችም አካላት ጋር ሕጋዊ መንገድን ተከትላ የተወሰዱባት ሀብቶቿን ማስመለስ፣ ማስከበር ያስፈልጋል። ለዚህም ደግሞ የተደራጁ የሕግ ባለ ሙያዎች፣ የሚዲያ ባለ ሙያዎችና መሰል የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ማሰባሰብና ማመካከር ያስፈልጋል።

የበዓላቱን አካባበር አስመልክቶ ሚዲያዎች የሚሰጡትን ሽፋን ይዘት ቤተ ክርስቲያናችን ትኩረት ሰጥታ ማየት ይኖርባታል። መገናኛ ብዙኃን ስለ በዓላቱ ሲዘግቡና በቀጥታ ሲያስተላልፉ፡ ቤተ ክርስቲያን እንዲተላለፍላት በምትፈልገው መልኩና ሃይማኖታዊ ተልእኮዋን ባገናዘበ መልኩ መሆን ይጠበቅበታል። ይህ ካልሆነና  ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ተቃራኒ የሚቆም ሚዲያም ካለ በሚዲያዎች ላይ አቋም መያዝ ትችላለች። በዓላቱን መቅረጽ፣ ቃለ መጠይቅ ማድረግ፣ በቦታው ተገኝቶ መዘገብ እነዚህ ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን ይሁንታ ያሻል። ይህን ለማስተካከልም በዓላትን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የምትከተለውን መርሕ በመመሪያም ጭምር አዘጋጅታ ይፋ ማድረግ፣ ከሚመለከታቸው አካላትም ጋር ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ከበዓላት በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ፕሬስ ኮንፍረንሶችን እያዘጋጀት ስለ በዓሉ አከባበር፣ ምን እንዲዘገብላት እንደምትፈልግና ጋዜጠኞች መከተል ስላለባቸው ሥርዓት መግለጫ ብትሰጥ መልካም ነው። ከዚህ ባለፈም በየሚዲያው ላሉ ጋዜጠኞች በየተወሰነ ጊዜ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ብትሰጥ ከሚድያዎች ጋር ያላትን ግንኙነት ከማጥበቁም በላይ፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን ለማያውቁትም ማሳወቅ ይሆናል።

ከበዓላቱ ረድዔትና በረከት ያሳትፈን!

የጌታችን የልደት በዓል በዓለም ዙሪያ

Details
Written by: ዲ/ን ኅሊና በለጠ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 02 January 2021
Hits: 1464
  • ከዓለም ማእዘናት
የጌታችን የልደት በዓል በዓለም ዙሪያ

ልደተ እግዚእን እኛ በታኅሣሥ ፳፱ (January 7) ስናከብር፡ ምዕራባውያን በታኅሣሥ ፲፮ (December 25) ያከብራሉ። ከእኛ ጋር በአንድ ዓይነት ቀን የሚያከብሩ ብዙ የኦሪየንታልና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ጥቂቶቹን ከአከባበር ሥርዓታቸው ጋር እስኪ በጥቂቱ እንዳሳቸው። 

ከግብፅ አጠቃላይ ሕዝብ ክርስቲያኑ ፲፭ በ፻ ይሆናል። ከነዚህ መካከል ብዙዎችን የያዘችው የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የልደት በዓል የምታከብረው በደመቀ ሁኔታ ነው። በዓሉ የሚውልበት የቅብጥ ወር ‹‹ኪያክ (Kiahk)›› ሲባል፡ ቅብጣውያኑ ከበዓሉ በፊት ለ፵፫ ቀናት ጾመ ነቢያትን ይጾማሉ። በጾሙ ወቅት ከሰንበታተ ክርስቲያን አገልግሎት በፊት ዘወትር ቅዳሜ ማታ ምእመናን ልዩ መዝሙራትን ይዘምራሉ።

በበዓሉ ዋዜማ በታኅሣሥ ፳፰ ማታ ከሦስት ሰዓት ጀምሮ ምእመናን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይገኛሉ። የመቅደሱ ሥርዓት አራት ሰዓት ተኩል ሲል ይጀምርና እኩለ ሌሊትን ተሸግሮ ብዙ ጊዜ እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት ይዘልቃል። የመቅደሱ አገልግሎት ተፈጽሞ ካህናቱ ሕዝቡን ካሰናበቱ በኋላ፡ ምእመናን ወደየቤታቸው በመሔድ ‹በትልቁ የልደት ገበታ› ከቤተሰባቸው ጋር ተሰይመው ጾማቸውን ይፈታሉ።

‹‹የኦርቶዶክስ የገና ዕለት›› ተብሎ በሚታወቀው በቀጣዩ ቀን፣ ማለትም በታኅሣሥ ፳፱ ምእመናን በየቤቱ እየሔዱ በመጠያየቅ በዓሉን በደስታ ያከብራሉ። ብዙ ጊዜ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ሲሔዱም ‹‹ካህክ (Kahk)›› የተባለውን ልዩጣፋጭ ብስኩት በስጦታነት ይወስዳሉ።

የግብፅ ሕዝብ አብዛኛው ክርስቲያን ባይሆንም፡ የገና በዓልን ግን በአብዛኛው እንደ ብሔራዊ በዓል ማክበር ይፈልጋሉ፤ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ብዙ የገበያ እንቅስቃሴ ይኖራል፤ መንገዶች በዓሉን በሚገልጹ ጌጣጌጦች ያጌጣሉ።

የግብፅ ሕፃናት እነርሱ ‹‹ባባ ኖኤል (Baba Noel)›› የሚሉት የገና አባት በበዓሉ ዕለት ስጦታ እንዲሰጣቸው ይናፍቃሉ። ከጣፋጭ ብስኩቶችም ‹‹ለባባ ኖኤል›› ብለው ያስቀምጣሉ።(https://www.whychristmas.com/cultures/egypt.shtml)

የሕንድ የማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም በዓሉን በተመሳሳይ የአምልኮ ሥርዓት ብታከብርም፣ በቤተ መቅደስ ውስጥ ከሚፈጸመው አገልግሎት ውጪ ደመራን መደመርም በቤተ ክርስቲያኗ የተለመደ ነው። ቀሲስ ዶክተር ኬኤም ጊዮርጊስ የተባሉት የቤተ ክርስቲያኗ ካህን ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ከልደተ እግዚእ በዓል አገልግሎት አንዱ የሆነው ደመራን የመደመር ሥርዓት ከሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተወረሰ ትውፊት ነው። ደመራው በሚለኮስበት ቦታ ምእመኑ ከበውት ይቆማሉ። በዚያም የሉቃስ ወንጌል ይነበባል።››

ደመራውን ከበው በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን በእጃቸው ዕጣንን ይይዛሉ። ከዚያም በታዘዙ ጊዜ ዕጣኑን ወደ ደመራው እሳት ይጨምሩታል። የዕጣኑ መልካም መዓዛ የምሕረት፣ የቅድስና፣ የንጽሕና ምሳሌ ነው። እሳቱ ነዶ ካለቀ በኋላም ምእመናን አመዱን አፍሰው በመውሰድ በጸበል በመበጥበጥ ቤት ውስጥ ታሞ ላለ ሰው ይሰጡታል፤ ይህም ለሥጋዊም ለመንፈሳዊም ፈውስ የሚጠቅም ነው።

የደመራው እሳት በአንድ በኩል በብርሃኑ የክርስቶስን ብርሃንነት የሚመስል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማቃጠል ባሕርይው የጌታችንን ፈራጅነት ይመስላል። (https://www.google.com/amp/s/indianexpress.com/article/religion/christmas-celebration-indian-church-jesus-birth-ritual-5508260/lite/)

የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አከባበሯ በብዛት ከሕንድ ጋር የሚመሳሰል ስትሆን የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን በዓሉን በተለየ መልኩ አንድ ቀን ቀደም ብላ በታኅሣሥ ፳፰ ቀን ታከብራለች። በዕለቱ የጌታችንን ልደት ብቻ ሳይሆን ጥምቀቱንም አክብረው ያልፋሉ። አንዳንድ አርመናውያን ከበዓሉ በፊት ያለውን ሳምንት ሙሉ ይጾማሉ። የገና ዋዜማ ላይ የሚመገቡት ምግብ ‹‹ኬቱም (Khetum)›› ተብሎ ይጠራል። (https://www.whychristmas.com/cultures/armenia.shtml)::

ከኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ውጪ ያሉት የራሺያና የግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን የመሰሉት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትም በዓሉን በታኅሣሥ ፳፱ በቅዳሴና በተለያዩ መሰል የአምልኮ ሥርዓቶች በድምቀት ያከብራሉ።

ቅጽል

Details
Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 02 January 2021
Hits: 1756
  • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን

ውድ አንባብያን ባለፈው ዕትማችን ግልጠ ዘ ቅጽሎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ማቅረባችን ይታወሳል። የቀረበውን ትምህርት መሠረት አድርጋችሁም ግልጠ ዘ ብለን በዘረዘርናቸው ቅጽሎች በእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዐረፍተ ነገሮችን እንድትሠሩባቸው የቤት ሥራ መስጠታችን ይታወሳል። መልሳችሁን ለማረጋገጥ ያህል እንደሚከተለው እንመልሳቸው።

“ዘ” ብፁዕ ብእሲ ዘኢሖረ በምክረ ረሲኣን፤ በዝንጉዎች መንገድ ያልሄደ ምስጉን ነው። (መዝ.፩፥፩)

ዘወረደ እምሰማያት ዐርገ ውስተ ሰማያት፤ ከሰማያት የወረደው ወደ ሰማያት ዐረገ።

“እንተ” ፡- ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህቺ ናት። (መዝ.፻፲፯፥፳፬)

ብፅዕት ብእሲት እንተ ታፈቅር ብእሲሃ፤ ባሏን የምትወድ ሚስት ብፅዕት ናት።

“እለ” ወተገሠፁ ኵልክሙ እለ ትኴንንዋ ለምድር፤ እናንተ የምድር ፈራጆች ተገሠፁ። (መዝ.፪፥፲)

ብፁዐዓን ኵሎሙ እለ ተወከሉ ቦቱ፤ በእርሱ የታመኑ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። (መዝ.፪፥፲፪)

ውድ አንባብያን መልሱ ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም በዚህ መልኩ በልዩ ልዩ መንገድ ሊሠራ ይችላልና ይህንም ልብ ማለት ያስፈልጋል።

የቅጽል ሙያ

ቃላት በማንኛውም ሰዋስዋዊ መዋቅር ውስጥ ያለአንዳች ሙያ አይቀመጡም። ቅጽልም ከቃል ክፍሎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን በማንኛውም ሰዋስዋዊ መዋቅር ሲገባ ሙያ አለው። ባለፉት ተከታታይ ዕትሞቻችን ምንነቱንና ክፍሎቹን ተመልክተናል። በዚህ ዕትማችን ደግሞ ቅጽልን በተመለከተ የመጨረሻ የሆነውን የቅጽልን ሙያ እንመለከታለን።

ቅጽል በስም ላይ ተጨምሮ ስምን ከመጠን፣ ከግብር፣ ከፀባይ፣ ከዓይነት ወዘተ አንጻር የሚገልጽ የቃል ክፍል ነው። ይህን በተመለከተ መምህር ደሴ ቀለብ ትንሣኤ ግእዝ በተሰኘ መጽሐፋቸው “ቅጽል በስም ላይ እየተጨመረ የስምን ኩነት፣ አካል፣ መልክእ፣ ቅርጽ፣ ቅርበት፣ ርቀት፣ ዓይነት፣ መጠን፣ ወይም ማንነት የሚገልጥ የስም አጎላማሽ (ገላጭ) ነው።” በማለት ይገልጹታል። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘ መጽሐፋቸው “ቅጽል በስምና በግብር የሚጨመር ቃል የአካልንና የግብርን አኳሆን ጠባዩን፣ መልኩን፣ የሚገልጥና የሚያስረዳ ነው” (ገጽ ፰፻፬) በማለት ይገልጹታል።

ከሁለቱም ምሁራን እንደምንረዳው ቅጽል በስም ላይ ተጨምሮ ስሙን ከመጠን፣ ከዓይነት፣ ከግብር፣ ከፀባይ ወዘተ አንጻር የሚገልጽ፣ ስለ ስም ተጨማሪ መረጃ የሚሰጥ የቃል ክፍል መሆኑን ነው። ከዚህ በመነሣት የቅጽል ሙያ ምንድን ነው? ብለን ስንመለከት የገላጭነት ሙያ አንዱ መሆኑን እንረዳለን። በተሻለ መልኩ ግልጽ ለማድረግ በምሳሌ እንመልከተው።

መጠንን የሚገልጹ ቅጽሎች ፡- ነዊኅ፣ ሐጺር፣ ንኡስ፣ ብዙኅ፣ ዐቢይ… 

ብዙኅ ሰብእ መጽአ ኀበ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ጸሎት፣ በጸሎት ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን  ብዙ ሰው መጣ።

ነዊኅ ብእሲ ይትአመር በኀበ ኵሉ ሕዝብ፤ ረጅም ሰው በሁሉ ሕዝብ ዘንድ  ይታወቃል።

ሐጺር ዘኬዎስ ኢክህለ ይርአይ ክርስቶስሀ ዘእንበለ ይቁም ላዕለ ኦም፤ አጭር ዘኬዎስ ዛፍ ላይ ሳይቆም ክርስቶስን ማየት አልቻለም።

ንኡስ ወልድ ኢክህለ ይጹር ዕርፈ፤ ትንሽ ልጅ ዕርፉን መሸከም አልቻለም።

ግብርን የሚገልጹ ቅጽሎች፡- ሐናጺ፣ ሐራሲ፣ ቀዳሲ፣ ጸሓፊ፣…

ሐናጺ ሰብእ ገብረ ማኅደረ፤ አናጺ ሰው ቤትን ሠራ።

ሐራሲ ወልድ የሐርስ ገራህተ ለአቡሁ፤ አራሽ ልጅ ለአባቱ እርሻን ያርሳል።

ቀዳሲ ካህን ይትረከብ ቅድመ ውስተ ቤተ መቅደስ፤ ቀዳሽ ካህን አስቀድሞ ከቤተ መቅደስ ውስጥ ይገኛል።

ጸሓፊ መምህር ጸሐፈ መጽሐፈ፤ ጸሓፊው መምህር መጽሐፍን ጻፈ። 

ዓይነትን የሚገልጹ ቅጽሎች፡- ጸዐዳ፣ ጸሊም፣ ቀይሕ፣…

ቀይሕ ብእሲ ቀነየ ጸዐዳ ላሕመ፤ ቀዩ ሰው ነጭ ላምን ገዛ።

ጸሊም ብእሲ ያፈርህ ሕፃናተ፤ጥቊር ሰው ሕፃናትን ያስፈራል።

ፀባይን የሚገልጹ ቅጽሎች፡- ሠናይ፣ እኩይ፣ የዋህ፣ ኄር፣ …

የዋህ ብእሲ ይገብር ምሕረተ ለነዳያን፤ የዋህ ሰው ለችግረኞች ምሕረትን ያደርጋል።

እኩይ ብእሲ ይወስድ ሀብተ ዘኢኮነ ዘዚኣሁ፤ ክፉ ሰው የእርሱ ያልሆነውንም ሀብት ይወስዳል።

የባለቤትነት ሙያ፡-

ቅጽል በዐረፍተ ነገር ውስጥ በገላጭነት እንደሚገባ ሁሉ በባለቤትነትም ይገባል። በዚህ ጊዜ በቃል ክፍሉ ቅጽል ሆኖ በሙያው ግን በስም ቦታ ገብቶ ስምን ተክቶ ባለቤት መሆን ይችላል።

ለምሳሌ፡- 

ሐራሲ ሐረሰ ገራህተ፤ አራሽ እርሻን አረሰ።

ጸሓፊ ጸሐፈ መጽሐፈ፤ ጸሓፊ መጽሐፍን ጻፈ።

ቀዳሲ ቀደሰ ቅዳሴ፤ ቀዳሽ ቅዳሴን ቀደሰ።

ከላይ በምሳሌነት በቀረቡት ዐረፍተ ነገሮች ባለቤቶች በቃል ክፍላቸው ቅጽሎች ሲሆኑ በሙያ ደረጃቸው ግን ባለቤት ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለዚህ ቅጽል በስም ላይ ተቀጽሎ ስምን የሚገልጽ ብቻ ሳይሆን በስም ቦታም ገብቶ እንደስም ሁሉ ባለቤት ወይም ድርጊት ፈጻሚ ይሆናል ማለት ነው። 

 

የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም ክፍል ሁለት

Details
Written by: ወግደረስ አዳል
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1715
  • እናስተዋውቃችሁ
የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም      ክፍል ሁለት

ውድ አንባብያን ባለፈው ዕትማችን በእናስተዋውቃችሁ ዓምዳችን “የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳምን ከአመሠራረቱ ጀምሮ በርከት ያሉ ጉዳዮችን ማቅረባችን ይታወሳል። ቀሪውንና ክፍል ሁለትን በዚህ ዕትማችን እናቀርባለን። መልካም ንባብ።

፫. ገዳሙ ካለፉት ፳ ዓመታት ጀምሮ ያሉ እንቅስቃሴዎች

ገዳሙ ከተዳከመበት ተነሥቶ ዳግም በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ከቀናበት ዓመት ጀምሮ እስካሁን እጅግ አርአያ 

የሚሆን ፈጣን ዕድገት ላይ ያለ ገዳም ነው። በገዳሙ ውስጥ የአባቶችን የገዳማዊ ሕይወት አጥብቆ በመያዝ አሁን ላይ ያሉ የዘመኑ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል አሠራርን የሚከተልና ገዳማዊ ሕይወት እውነትም በጸሎትና በሥራ የሚገለጽ መሆኑን ተመጽዋችነት የገዳማውያን ባህል አለመሆኑን የሚያሳይ አርአያ ገዳም ነው። በዚህም ጠንካራ የሥራና የጽኑ አንድነት ሥርዓት በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ከሦስት ወደ ፲፬ ከፍ ያደረጋቸውን የመነኰሳት ቁጥር በ፳፻፲፩ ዓ.ም. ፮፻፲፮ መናንያንና ከ፴ በላይ የአብነት ተማሪዎች እንዲኖሩት አስችሎታል።

Read more: የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም ክፍል ሁለት

የጥያቄዎቻችሁ መልስ 

Details
Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1719
  • የጥያቄያዎቻችሁ መልስ
የጥያቄዎቻችሁ መልስ 

ውድ አንባብያን በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዓምዳችን ወቅታዊውን የሀገራችረን ጉዳይ በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን መምህር ግርማ ባቱን ጋብዘን። ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ንባብ።

ሐመር፡- መምህር ወቅቱን መሠረት ያደረጉና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ለምናነሣቸው ሐሳቦች ምላሽ ለመስጠት ፈቀደኛ ስለሆኑልን አስቀድመን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን። 

መምህር ግርማ ባቱ፡- እኔም  ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።

ሐመር፡-  በሀገራችን እየተስተዋለ ያለው ጦርነት በቤተ ክርስቲያን እይታ ሲታይ ከምን የመጣ ነው ብለው ያምናሉ?

መምህር ግርማ ባቱ ፡- ታሪኩ ረጅም ነው በተቻለ መጠን በአጭሩ ለመመለስ አሁን እየታየ ያለው ውጤት የረጅም ጊዜ ሂደት ነው። ሂደቱ ያስከተለውን የብዙ ችግሮች ውጤት ነው አሁን እየተመለከትን ያለነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ላለፉት ከ፴-፵ ዓመታት ያህል ሀገሪቱ ስትከተለው የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት፡-

Read more: የጥያቄዎቻችሁ መልስ

ግብረ ሰዶማዊነት ክፍል ሁለት

Details
Written by: ዲ/ን ተስፋዬ አሰፋ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1710
  • ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት

ውድ አንባብያን ባለፈው ዕትማችን ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት በሚለው ዓምዳችን ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ ክፈርል አንድን ማቅረነባችን ይታወሳል። ክፍል ሁለትን ደግሞ በአሁኑ ዕትማችን እናቀርባለን። መልካም ንባብ።

ዓለም አቀፍ የማስፋፍያ መንገዶች ምንድን ናቸው?

ማርሴል ከርክ እና ሀንተር ማድሰን የተሰኙ አሜሪካውያን የዚህ ድርጊት አስተባባሪዎች after the ball በተሰኘው መጽሐፋቸው ለማስፋፋት መጠቀም ያለባቸውን ዘዴ በትክክል አስፍረው ዛሬም ድረስ ተግባራዊ እየሆነ ነው። (፲፱፻፹፱)

፩. ስለ አኗኗራቸው ምንም ነገር እንዳይነሣና እንዳይወራ ማድረግ።

፪. ቃሉን ደጋግሞ ለጆሮ ማለማመድ፡- ዛሬ ቃሉ ሲነገር እንደ ነውር የምንደነግጠው ነገር ቀርቷል ይህ የእነሱ የሥራ ውጤት ነው። ሚዲያን፤ መንግሥታትን፤ ታዋቂ ሰዎችን በመግዛት ወደ ፊት እየመጡ ነው።

፫. ግብረ ሰዶማውያን በዓለም የተጎዱ የተገፉ አድርጎ ማቅረብ። የታቀደ ድብደባ እንዲደረግባቸው በማድረግ ዓለም እንዲያዝንላቸው ቁስላቸውን በማሳየት አማኝ ኅሊና መግዛት።

፬. ማኅበራዊ ፍትሕ እንደ ተነፈጋቸው አድርጎ ማቅረብ ፡- ጉዳዩን ከመብት፤ ከሰብኣዊ መብት (human right) አንጻር እንዲታይ መንግሥታትን መቃወም፤ ማሳመን፤ በአሜሪካና መሰል ሀገሮች ወንጀል መሆኑ እንዲቀር ከማድረግም ባለፈ ሰብኣዊ መብት እንደ ሆነ አድርጎ ማቅረብ። united nations ካስቀመጣቸው የሰብኣዊ መብት ውሳኔዎች (human right declaration) አንዱ ቤተ ሰብ ለኅብረተ ሰብ ዋና ምሰሶ በመሆኑ ከፍተኛ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል የሚል አንቀጽ አለው። ሆኖም ግን ግብረ ሰዶማዊነት ይህን የሚጻረር ሆኖ እናገኘዋለን።

፭.  ዓለም አቀፍ የቱሪዝም፤ የስፓርት፤ የቱሪስት እንዲሁም ትልልቅ ኮንፈረንሶችን መጠቀም፡- ኅዳር ፳፮/ ፳፻፬ ዓ.ም. የተካሄደው ICASA በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ከተላላፊ በሽታዎች ጋር በተያያዘ የተደረገ ስብሰባን ምክንያት በማድረግ ስብሰባ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። በሀገራችን ኢትዮጵያም በ፳፻፲፩ ዓ.ም.  የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ለመጎብኘት በሚል ሰበብ ለመምጣት አቅደው አልተሳካላቸውም፤ ሌሎቹንም የስፖርት ውድድሮች፤ የቱሪስት መዳረሻዎች በመጠቀም ለመስፋፋት ይጠቀሙባቸዋል።

Read more: ግብረ ሰዶማዊነት ክፍል ሁለት

“እመኚ እንጂ አትፍሪ”

Details
Written by: ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1760
  • ኪነ ጥበብ

የጽጌ ወቅት አልፎ የበጋው ወራት ከተተካ ሰነባብቷል፣ በዘመነ ጽጌ ፈክተው የነበሩ  አበቦችና ልምላሜ የተላበሱት ዕፅዋት ጊዜ ገድቧቸው ደርቀዋል፣ በአበቦችና ነፋሻማ አየር ታጅቦ ውስጣዊ ስሜትን በሐሤት ይሞላ የነበረው ጊዜ አልፎ ደረቅ ነፋስና የፀሐዩ ግለት ነፍስን ያስጨንቃል። ዕለቱ ሐሙስ እኩለ ቀን ነው፤ ፀሐይዋ አናት ላይ ስታርፍ ከጥንካሬዋ የተነሣ እንደ መርፌ አናት ትበሳለች። 

ጽዮን ከማንም ጋር ላለመገናኘት ራሷን አግልላ ከተሸሸገች ሰንብታለች። ዛሬም ውኃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ ከሚወርዱ አንዳንድ ልጃገረዶች በስተቀር ማንም በማይንቀሳቀስበት ሰዓት በእኩለ ቀን የፀሐይዋን ሙቀት ተቋቁማ እንሥራዋን በጀርባዋ አዝላ ውኃ ልትቀዳ ብቻዋን ወደ ወንዝ ወረደች። ነገር ግን መንገዱን ከጀመረች በኋላ ተጨናነቀች። 

ጽዮን በዲፕሎማ ተመርቃ ካደገችበት ከቢቸና ከተማ  በዐሥር  ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የገጠር ቀበሌ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባስተማሪነት ትሠራለች። በትዳር ለመወሰን ካላት ጉጉት የተነሣ ጥያቄያቸውን ያለምንም ማንገራገር ብትቀበልም በየተራ የቀረቧት ሦስት ወንዶች ከቀረቧት በኋላ ከድተዋታል። ሦስቱም እሺ እስክትላቸው ድረስ ለእውነተኛና ዘላቂ ትዳር እንጂ ለጊዜያዊ ፍላጎት እንደማይፈልጓት ይነግሯታል። ይሁን እንጂ እሽ እንዳለቻቸውና  የትዳር ጥያቄያቸውን እንደተቀበለቻቸው ሲረዱ ለጾታዊ ግንኙነት ይጠይቋታል። እርሷ ደግሞ በሰንበት ትምህርት ቤት በተማረችው መሠረት ከትዳር በፊት ግንኙነት ኃጢአት እንደሆነ ተረድታለችና እንቢ ትላቸዋለች። በዚህ ምክንያት ከሦስቱም ሳትስማማ ቀርታ ተለያይተዋል። ይሁን እንጂ ከሦስቱም ጋር አብራ ትታይ ስለነበር በማኅበረ ሰቡ ዘንድ እንደዝሙተኛ እየተቆጠረች መገለል ደርሶባታል። ራሷን መደበቅ የፈለገችውም በዚህ ምክንያት ነበር። ውኃ መቅዳት ስታስብም ቀትር ላይ መሄድን የወሰነችውም ከሰው ዐይን ለመራቅ በወሰነችው ውሳኔ ነበር።

Read more: “እመኚ እንጂ አትፍሪ”

ጾመ ነቢያት

Details
Written by: ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 2501
  • ዐውደ ስብከት

በኢትዮያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ። እነዚህን የአዋጅ አጽዋማት በተመለከተ ፍትሐ ነገሥት (ፍትሕ መንፈሳዊ) አንቀጽ ፲፭፥፭፻፷፬ ጀምሮ ተጽፏል። በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭፥፭፻፷፰ “ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡ መጀመርያው የኅዳር እኩሌታ፡ ፋሲካው፡ የልደት በዓል ነው።” ተብሎ የጾመ ነቢያት መነሻውና መድረሻው ተገልጿል። ይህ ማለት በሦስቱ ወንጌላውያን ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስና በዘመነ ሉቃስ ከኅዳር ፲፭ ጀምሮ  ኅዳር ፳፱ የሚፈሰክ ሲሆን በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ መነሻው ያው ከኅዳር ፲፭  ጀምሮ ይሆንና ኃዳር ፳፰ ቀን የሚፈሰክ ይሆናል ማለት ነው።    

ጾመ ነቢያት በሌሎቹ ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በተለምዶ ካቶሊክ እያልን በምንጠራቸው ዘንድ የታወቀ ነው። እኛ ጾመ ነቢያት የምንለውን ሌሎቹ የልደት ጾም (The Nativity Fast) በማለት ይጠሩታል። ይህ ጾም የሚጾምበት ዋና ምክንያት የክርስቶስን ልደት ለመቀበልና ነቢያት አስቀድመው ልደቱን በመመኘት የጾሙትን ጾም ለማስታወስም ነው። ይህን ጾም የግብፅ ቤተ ክርስቲያን የምጽዓት ጾም (The Advent Fast) በማለት ትጠራዋለች። ምክንያቱም አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ለመወለድ መምጣቱን በማሰብ የሚጾም ነውና። 

Read more: ጾመ ነቢያት

ኦሪት ወነቢያት ወወንጌል ሰበኩ በክርስቶስ (ሃ.አ. ምዕ ፯ ክፍል ፩ ቁጥር ፪)

Details
Written by: መ/ር ተስፋማርያም ቢሰጥ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1936
  • ትምህርተ ሃይማኖት

የተወደዳችሁ ኦርቶዶክሳውያን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ምሥጢር ሲገባ ኅሊናን ሰብሰብ አድርጎ መቃኘት ተገቢ ነው። ለምን ቢባል የሰው ልጅ ልቡና በአራት ነገር ተመስሏል። ይህውም  በመንገድ፣ በዓለት፣ በእሾህና በመልካም መሬት ነው። (ማቴ. ፲፫፥፬-፱)  ከነዚህ መካከል ለዘር ተስማሚው ማሳ መልካም መሬት የተባለው ነው። ይህም የዘሩበትን የሚያበቅል አንድ ቅንጣት ተዘርቶበት ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ የሚያፈራ የታደለ መሬት ነው። የሰው ልቡናም መልካም መሬት ሲሆን መምህራን ሊቃውንት የዘሩበትን ቃለ እግዚአብሔር ያበቅላል ከውኃ ዳር የተተከለች ዛፍ ሁልጊዜ ልምላሜ እንደማይጠፋባት ፍሬን ከመስጠት ከዓመት እስከ ዓመት እንደማትጎድል ሁሉ እኛም የሰው ልጆች በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘን በቤተ መቅደስ ተተክለን በእግዚአብሔር ቃል ታርመንና ተኮትኩተን የምናድግ ከሆነ ልምላሜ ሃይማኖትን፣ ጽጌ ትሩፋትን፣ ፍሬ በረከትን (ምግባርን) ከመስጠት ወደ ኋላ አንልም። 

ይህንም ለማድረግ ከሥጋዊ ሐሳብ ተላቆ ለሰይጣን የሚሆነውንና ሰይጣን የሚወደውን ለሰይጣን አሽቀንጥሮ በመጣል የእግዚአብሔር የሆነውን በመያዝ ልቡናን አስተካክሎና አጽንቶ መቅረቡ ተገቢ ነው። የሰይጣን ገንዘቦች የሚባሉት ጣዖት ማምለክ፤ ዝሙት፤ ርኵሰት፤ ሟርት፤ ጥል፤ ክርክር፤ ቅንዓት፤ ቁጣ፤ ራስ ወዳድነት፤ መለያየት፤ አድመኝነት፤ ምቀኝነት፤ ስካር፤ መናፍቅነት ይህን የሚመስል ነው። እነዚህን ለሰይጣን መልሶ የእግዚአብሔር የሆኑትን ዘጠኙን የመንፈስ ፍሬዎች ታጥቆ መኖር ልቡናን የተስተካከለ ያደርጋል። ወደ ርእሰ ጉዳያችን ስንመለስ ልቡናው የቀናለት ቅዱስ ሄሬኔዎስ የሐዋርያት ደቀ መዝሙራቸው ሲሆን ኤዶም በምትባል ሀገር በኤጲስ ቆጶስነት ተሹሞም አገልግሏል። ይህ ሊቅ የክርስቶስን ነገር ሲነግረን ‹‹ኦሪት፣ ነቢያትና ወንጌል ክርስቶስን ሰበኩ›› በማለት ገልጾታል።

Read more: ኦሪት ወነቢያት ወወንጌል ሰበኩ በክርስቶስ (ሃ.አ. ምዕ ፯ ክፍል ፩ ቁጥር ፪)

''በስሜም ሰላም በሉት’’፩ኛ ሳሙ.፳፭፡፭

Details
Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 1149
  • ርዕሰ አንቀጽ

ለሰው ልጆች ህልውና እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች መካከል ሰላም ዋናው ነው። ሕይወትና ኑሮ ሊታሰብ የሚችለው ራሱ ሰላም ሲኖር ነው። ሰላም ከሌለ መምህሩ ማስተማር፣ ተማሪው መማር፣ ነጋዴው መነገድ፣ ሸማቹም መሸመት አይችልም። ሐኪሙ ማከም፣ መሐንዲሱ መገንባት የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ሐኪሞ አክሞ የሚያድነው ሟችን፣ መሐንዲሱ የሚገነባውም ፈራሽን ይሆናል። ሰላም ከሌለ ገበሬው ዘርቶ ሀገር መመገብ አይችልም፤ የሃይማኖት አባቶችም ያልተማረውን ለማስተማር የተማረውንም ለማጽናት ፈተናው ይበረታባቸዋል። የሰላም ዋጋው እጅግ ውድ ነው። የትኛውም ሰው የዕለት ግብሩን ለመፈጸም በቅድሚያ ሰላም ሊኖረው ይገባዋል። ለዚህ ነው መዝሙረኛው ‹‹ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን ሻት ተከተላትም፤›› ሲል የዘመረው። (መዝ.፴፫፥፲፬)።

አብዛኛው የሀገራችን ታሪክ በጦርነት የታጀበ ነው። ብዙ ጠላቶች በየዘመናቱ እየተነሡብን የመከትነውን ያህል፡ እርስ በእርስ የተገዳደልንባቸው ታሪኮቻችንም ትንሽ የሚባሉ አይደሉም። በሁሉም ጦርነቶች ግን ወንድሞች ተገዳድለዋል፣ ሕፃናት በወላጅ እጦት ተርበው አልቀዋል፣ ወገን ተጨፍጭፏል፣ ሀገር ወድማለች። ይህ ሁሉ ክስረት በየዘመናቱ የተከሰተው እርስ በእርስ ወንድማማቾች ተጣልተው መሆኑ ደግሞ ሕመሙን የከፋ ያደርገዋል።

Read more: ''በስሜም ሰላም በሉት’’፩ኛ ሳሙ.፳፭፡፭

ዕቅበተ እምነት (Apology)

Details
Written by: ሕግና ዕቅበተ እምነት አገልግሎት ማስተባበሪያ
Category: ሐመር በመስመር ላይ
Published: 04 December 2020
Hits: 5144
  • ዐቢይ ጉዳይ

ዕቅበት፤ ዐቀበ ከሚለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ። ትርጉሙም መከላከል፣ መጠበቅ (Apology) ማለት ነው። ዕቅበተ እምነት እምነትን መጠበቅ ማለት ሲሆን እምነትም የሚጠበቀው ከኢአማንያንና ከከሓድያን የሐሰት ትምህርት፤ ከመናፍቃን ቅሰጣ፤ ከዓለማዊ ፍልስፍና፤ ከዓለማዊነት (Secularism) ከግለሰባዊ ፍላጎትና ጥርጣሬ ሁሉ ነው። ዕቅበተ እምነት፤ በእምነት ሕይወት ላይ የጸና የግለሰቡን ሰብእና፣ ዕውቀትና ጥበብ መሠረት አድርጎ የሚቀርብ አገልግሎት ነው። እምነት በአማኙ ሁሉን አቀፍ የሕይወት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተግባር የሚገለጽና በግንኙነቶች የሚታወቅ እንደ መሆኑ መጠን ዕቅበተ እምነትም እንደዚሁ በትምህርትና በምግባር አርአያነትን የሚፈልግ ለቤተ ክርስቲያን የመቆም የባለ አደራነት ሥራ ነው። 

ዕቅበተ እምነት በሰፊው የሚታወቀው ከሐዋርያት ተከትለው፣ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ወይንም በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩ “ዐቃብያነ ሃይማኖት፣ የእምነት ጠበቆችና ቀዋምያን ለቤተ ክርስቲያን (Apologists)” በሚሉ መጠሪያዎች ከሚታወቁ አባቶች ጋር በተገናኘ ነው። (ቀ/ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ)፣ አንደኛ መጽሐፍ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፣ ገ. ፪፻፷፯) በዋናነት ሁለተኛውን ክፍለ ዘመንና እነዚህን ቀዋምያን እናንሣ እንጂ ጥብቅናው የጀመረው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን፣ ክብር ይግባውና በራሱ በጌታችን ስለ ራሱ በቀረቡ ክርክሮች ነው። የዮሐንስ ወንጌል ም.፩ እስከ ም. ፯ የተዘገቡት ጉዳዮች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው። ሐዋርያቱም በዚሁ መንገድ ቀጥለው ለዐቃብያነ እምነት አስረክበዋል። ሃይማኖታችንና ክብራችን ተነካ ከሚሉት ከማኅበረ አይሁድ፣ ራሳቸውን ሲያስመልኩ ከነበሩት የሮም ነገሥታትና የግሪክ ፈላስፎች የተጋረጠውን የወቅቱን ታላቅ ፈተና ተረድተው ለቤተ ክርስቲያን የቆሙት እነዚህ አባቶች ከቀደምቶቻቸው ከሐዋርያት የወረሱት ብዙ ነገር አለ። 

Read more: ዕቅበተ እምነት (Apology)

Page 5 of 9

  • 1
  • 2
  • 3
  • 4
  • 5
  • 6
  • 7
  • 8
  • 9

የቅጅ መብት © ማኅበረ ቅዱሳን 2012 ዓ.ም.

ዋናው ማዕከል | Afaan Oromoo | English |አሜሪካ ማዕከል | አውሮፓ ማዕከል | ካናዳ ማዕከል | ትሩፋት
MK Facebook MK Telegram MK Youtube
አጫጭር ዜናዎች የሕፃናት ዓምድ ትዝብት ሪፖርታዥ ቤተ አብርሃም ፍሬ ከናፍር ምሥጢሬን ላካፍላችሁ ርዕሰ አንቀጽ Oct ኪነ ጥበብ June ዐውደ ስብከት sept እናስተዋውቃችሁ ትምህርተ ሃይማኖት Nov Mar Apr ዐቢይ ጉዳይ ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት የነገዋ ቤተ ክርስቲያን የጥያቄያዎቻችሁ መልስ July የማኅበሩ መልእክት Jan Aug May 1997 13 ከዓለም ማእዘናት