ሐመርን ያውርዱ
ስምዓ ጽድቅ ያውርዱ
የወሩ የማኅበረ መልእክት
Friday, 22 October 2021 00:00

በአዲስ ዓመት አዲስ ሰውነት

Written by  በዝግጅት ክፍሉ
 በአዲስ ዓመት አዲስ ሰውነት አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ሰው ለመሆን ተዘጋጅቶ መጠበቅ ከመንፈሳውያን ሁሉ የሚጠበቅ በጎ ተግባር ነው። ሰዎች ካልተቀየርን የዘመኑ መቀየር ብቻውን ጠቀሜታ የሌለው መሆኑን ተረድተን በዘመኑ ለመጠቀም መወሰን ይኖርብናል። ከዘመን ዘመን ስለተሸጋገርን ብቻ የምንደሰት ከሆነ የተፈጠርንበት ዓላማ፣ የመኖራችንም ትርጕም አልገባንም ማለት ነው። አዲስ ዘመን ሲመጣ ሕይወትን ለመቀደስ ካልተጠቀምንበት ተፈጠሩ ሞቱ መባል ብቻ ይሆናል። ነቢዩ ዳዋት “በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ፣ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ፤ የምድረ በዳ ተራሮችም ይረካሉ፤ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ”(መዝ.፷፬፥፲፩-፲፪) በማለት የተናገረው በኃጢአት ባሕር ሲዋኝ የኖረውን፣ ከእግዚአብሔር ተለይቶ፣ ከመጥፎ ነገር ጋር ተባብሮ ይኖር የነበረውን መልካም እንዲያስብ፣ ሟች መሆኑንም እንዲገነዘብ በማድረግ የጽድቅን ጎዳና እንዲከተል ልቡናውን የቀሰቀሰው እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ለመመስከር ነው። 

 

በአንጻሩ አንዳንድ ሰዎች አምላካቸው ረጅም ዕድሜ ሲሰጣቸው የዕድሜያቸውን መርዘም ምክንያት በደንብ ባለመረዳት በኃጢአት ላይ ኃጢአት ሲሠሩ ይታያሉ። ሲሠሩት የሚጣፍጣቸው ኃጢአት ቆይቶ መከራ እንደሚያመጣ ማሰብ አይፈልጉም። ዘመናቸውን ሳያልፍ እንጠቀምበት ቢሉም ኃጢአት ሠርተው ሳይጠግቡ በመከራ መቀሰፋቸው አይገለጥላቸውም። አዲስ ሰው ለመሆን መሠራት የሚገባውም “ኃጥእን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት፤ ብመለስ ግን የነበረበትን ቦታ አላገኘሁትም” በማለት ነቢዩ ዳዊት የተናገረው እንዳይፈጸምብን ነው (መዝ.፴፯፥ ፴፭)። ዘመናችን ከመከራ ለመጠበቅ ወደ አምላካችን የምንቀርብበት እንጂ ለበለጠ መከራ የሚዳርገንን መጥፎ ድርጊት የምንፈጽምበት መሆን የለበትም።  የነበረው በቅጽበት እንዳልነበር ሲሆን እያየን፣ ከእኛ ወዲያ ሥልጣኔ ይሉ የነበሩ መታሰቢያቸው ሊጠፋ ተቃርቦ እየተመለከትን አዲሱን ዓመት በኃጢአት እንደተጨማለቅን መጠበቅ እና በኃጢአት ላይ ኃጢአት ለመሥራት ዕቅድ ማውጣት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ እንዲፈረድብን ወደን ፈቅደን በመግባታችን ነው፡፡ 

አምላካችን እግዚአብሔር ወደ አዲስ ዓመት የሚያሸጋግረን አዲስ ሰው እንድንሆን  ነው፡፡ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ለመሥራት ባለመጥገባችን ዓለማችንን በየቦታው ጦርነት፣ በሽታ፣ ጎርፍ፣ ወረርሽኝ እያስጨነቃት ነው። እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር ጣትን ወደ ሌላ ከመጠቆም ይልቅ ራስን በመመርመር የችግሩ አካል መሆን አለመሆንን ማየት ይገባል። ሁላችንም ችግሩ የሌሎች መሆኑን እንናገራለን እንጂ የችግሩ ምክንያት “እኔ እሆን ?” ብለን ራሳችንን ጠይቀን አናውቅም። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን “እውነት እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ባላቸው ጊዜ እኔ እሆን? አሉ እንጂ ሌባ መሆኑን የሚያውቁት ይሁዳ ይሆናል አላሉም። ለአምላካቸው መሰቀል ምክንያት አለመሆናቸውን እያወቁ እኔ እሆን? ብለው ራሳቸውን በመጠየቃቸው አምላካቸው ለሞቱ ምክንያት የሆነውን ይሁዳን አሳያቸው። 

በቀጣዩ አዲስ ዓመት አዲስ ሰው ለመሆን የሚያግዙንን መልካም ተግባራት ማከናወን እንደሚኖርብን ማቀድ እንጂ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ለመደረብ መዘጋጀት የለብንም። ዘመናችንን የተባረከ የሚያደርገው አእምሯችንን ንጹሕ የሚያደርግ ተግባር መፈጸም ነው። ለዚህም ቀዳሚው ተግባር ከአጥፊዎችና ከጥፋታቸው ጋር አለመተባበር ነው። ከጥፋት አለመተባበር ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት እና የአገር መገለጫ የሆኑ ቅርሶቻችን እንዳይወድሙ መጠበቅም ይኖርብናል። የኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች ወገኖቻችን የእምነት ተቋማትም አደጋ እንዳይደርስባቸው የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርብናል። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር “ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ተብሎ የተነገረንን በተግባር ለመግለጥ ያግዘናል። በጦርነቱ ምክንያት በየቦታው ቅርሶቻችን እየወደሙ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በመተባበር ጥበቃ 

ልናደርግላቸው ይገባል። ግንባር ላይ የተሰለፉ ወገኖችም ቅርሶች የራሳቸው ንብረት መሆናቸውን ተረድተው በጦርነቱ ምክንያት እንዳይወድሙ አስፈላጊውን ጥበቃ ሊያደርጉላቸው ይገባል። 

 

የአገራችን የሆነው ሁሉ የእኛ በመሆኑ ክርስቲያኖች የእኛ የእምነት ተቋም ብቻ ይጠበቅ አንልም። የአገራችን የሆነው ሁሉ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር ማደረግ የሁላችን ኃላፊነት ነው።  ሁላችንም ሰላማውያን ለመሆን ካልተዘጋጀን በተወሰኑ ሰዎች ሰላማውያን መሆን አገር ሰላማዊ አይሆንም። አገር ሰላማዊ የምትሆነው፣ አምላካችን ጸሎታችንን የሚቀበለው በአዲሱ ዓመት ከሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ቃል ከመግባት ዐልፈን ተግባራዊ ሥራ ስንፈጽም፣ አዲስ ሰው ለመሆንም ስንዘጋጅ ነው። ሌላውን አጥፍተው ለመኖር መሞከር የሚፈልጉ ወገኖች የደረሰባቸውን መከራ እያየን ነው። ከተከሠተው  የበለጠ መከራ እንዳይመጣብንና የመጣውም መከራ በቶሎ እንዲቆም በፍጹም ልባችን ወደ አምላካችን በመመለስ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ተግባር ለመፈጸም መዘጋጀት ይኖርብናል። አምላካችን ቤተ አይሁድን “ኑ እና እንዋቀስ  ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ቢሆን እንደ በረዶ አነጻዋለሁ፤ እንደደምም ቢቀላ እንደ ባዘቶ አጠራዋለሁ። እሽ ብትሉና ብትሰሙኝ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤እንቢ ብትሉና      ባትሰሙኝ    

ባትሰውኝ ግን ሰይፍ ትበላችኋለች፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህን ተናግሯል”(ኢሳ.፩፥፲፰) በማለት የተናገራቸው ይህን ዘመን የሚመለከት ነው። በቅዱሳን የተነገረውን ቃል ሰምተን ባንታዘዝ የሚገጥመን መከራ ነግሮናል። ጥፋታችንን አምነን ወደ እርሱ ብንመለስ ደግሞ የምናገኘውን በረከት አሳውቆናል። አዲስ ሰው ለመሆን የሚገባንም የእግዚአብሔር ሰይፍ እንዳይበላን ነው። የእግዚአብሔር ሰይፍ የሚባለው ጦርነት፣ በሽታ፣ ወረርሽኝ፣ ጎርፍ፣ ማዕበል እና የመሬት መንቀጥቀጥ ነው።    

አምላካችን እግዚአብሔር ኑና እንዋቀስ በማለት የተናገረው እርሱ ጥፋት ኖሮበት ሳይሆን እኛን በፍቅር ሊስበን ፈልጎ ነው። አምላካችን እንዳንጠፋበት ፈልጎ በፍቅር ሲጠራን እኛ ደግሞ  በቁጣ ከሚመጣ መቅሰፍት ለመዳን የፍቅር ጥሪውን ተቀብለን በንስሓ ወደ እርሱ መቅረብ አለብን። ጥሪውን አልሰማ ብለን በኃጢአት የምንቀጠል ከሆነ መከራውን ወደ ራሳችን እየጋበዝን፣ የሚመጣብንን መቅሰፍት እያፋጠንን፣ የሞት መንገዳችንንም እየሠራን እንጂ ለጽድቅ የሚያበቃንን እየፈጸምን አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ዝሙትንና ምኞትን፣ ፥ስካርን እና ወድቆ ማደርን ያለልክ መጠጣትንና ጣዖት ማምለክን ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋልና። እንግዲህ ወደዚህ ሥራ እንዳትሮጡ ዕወቁ፤ ከዚች ጎዳናና መጠን ከሌለው ከዚያ ሥራም ተለዩ” (፩ኛ ጴጥ.፬፥ ፫-፬) በማለት የተናገረው በእንደዚህ ዓይነት የመከራ ዘመን ወደ አምላካችን ብንመለስ ከደረሰብን መከራ በኃጢአት ከመሞትም እንድናለን። 

ራሳችንን መጠበቅ የሚኖርብንም አካላችን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ብቻ ሳይሆን ኃጢአት ሠርተን ከአምላካችን ተጣልተን እንዳንቀር ጭምር ነው። ዝሙት፣ ስካር፣ ወድቆ ማደር የአሕዛብ ፈቃድ በመሆኑ ሐዋርያው “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ዘመን ይበቃችኋል” በማለት ነገረን። አልመለስ ካልንም የሚደርስብንን መከራ አስታወቀን። ከክፉ ርቀን መልካም ነገር የምናደርገው አምልኮ የምንፈጽምባቸውን አብያተ ክርስቲያን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ችግር የገጠማቸው እንዲጽናኑ የምንችለውን ሁሉ በመሥራት ጭምር ነው። ታሪክ ሠርተን ማለፍ፣ እግዚአብሔርንም የሚያስደስት ተግባር መፈጸም ሲገባን አባቶቻችን ለዘመናት ከውጭ ወራሪ ጠብቀው ያቆዩዋቸው ቅርሶች ሲወድሙ ቆመን ማየት ወይም እንዲጠፉ መተባበር ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ቀጣዩንምት ትውልድ መግደል ነው። የራሳችንን ሕይወት ከመቀደስ በተጨማሪ አገልጋይ ሊቃውንትን እና አብያተ ክርስቲያናትን ጠብቀን ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ማድረግ በዚህ ዘመን ከምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚጠበቅ  ኃላፊነት መሆኑን መግለጥ እንወዳለን።

Read 2959 times

ማስታወቂያ