- Details
- Written by: አቶ ፋንታሁን ዋቄ በማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኝነት ኃላፊ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 655
‹‹ወራሪ እየተባልን ከመገደልና ከመሰደድ ወጥተን የሀገር ባለቤትነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል››
ክፍል ሁለት
ስምዐ ጽድቅ፡- የዘር ማጥፋት መከላከያ ተቋምና ሌሎች ማኅበራት በሀገር ውዳድና በቤተክርስቲን አባቶች መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ስለሆነም ማኅበረ ቅዱሳን ከእነዚህ ማኅበራት ሕብረት ጋር ያደረገው ቅንጅታዊ አሰራር አለው ማለት ይቻላል?
አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- አንዳንዱ ማኅበራት በቅርቡ ቢመሰረቱም ወቅታዊና አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ የማኅበራቱ ምስረታ ዘገየ ቢባል ነው እንጂ አስፈላጊነታቸው ግን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በጠቅላላ ጉባኤ እየወሰነ የሚሠራቸው ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆኖ የማኅበሩ አባላት በቀናኤነት ባሉበት አካባቢና በተሰማሩበት ሙያ ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ፡፡ በቅርቡ ከተመሰረቱት ማኅበራት ጋር በተለይም “ከዘር ማጥፋ ተቋም” ጋር ይፋዊ የሆነ የሥራ ግንኙነት እስካሁን ድረስ የለንም፡፡ ነገር ግን በሽማግሌዎች ማኅበራትም ሆነ በዘር ማጥፋት መከላከያ ተቋሙ ውስጥ የእኛው ደጋፊና አባላት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ አካላት ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ይጠቅማል ያሉትን ሥራ ከሠሩ በአንድም በሌላ ማኅበሩ ሠርቷል ማለት ነው፡፡ ለወደፊቱ ግን ማኅበረ ቅዱሳን በይፋ ከእነዚህ ማኅበራት ጋር በጋራ የሚሠራ ይሆናል፤ እንመካከራለን፤ እንደጋገፋለንም፡፡ እነዚህ ማኅበራት በቅርቡ የተቋቋሙ በመሆናቸው ጠንካራ የሆነ መዋቅራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ጊዜ ወስደን ጠንክረን እንሠራለን፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ቤተ ክርስቲያን በሚደርሱ ጥፋቶች ምክንያት በተደጋጋሚ መግለጫ ከማውጣቷ ባለፈ በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ምን ብትሠራ መልካም ነው ይላሉ?
አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- ቤተ ክርስቲያን እካሁን ድረስ ከላይ እስከ ቤተሰብ ድረስ ያለውን መዋቅሯን የምትገለገልበት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት የምትሰጣቸውን ምእመናን መጠበቅ ሳትችል መንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ መስጠት ምእመናንንና ቤተክርስቲያንን ለተደራራቢ ጥፋት ማጋለጥ ነው፡፡ በምእመናንና በካህናት ላይ ንቅናቄ መፍጠር እና በፍጥነት ማደራጀት ያስፈልጋታል፡፡ ካህናትና ምእመናን ዘመኑ መቀየሩን እንዲያስተውሉ ማድረግ፤ ኦርቶዶክሳውያንን ሀገር አልባ የማድረግ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም መኖሩን ለምእመናንና ለአገልጋዮች ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሀገራችንን ከመነጠቃችን በፊት ቤተክርስቲያን ለልጆቿ ያለውን እውነታ መልሳ መላልሳ ማስገንዘብ አለባት፡፡ ፖለቲካውንም በባዕዳን እጅ ከመነጠቃችን በፊት መልሶ የራስ ማድረግ መታሰብ ያለበት ትልቅ ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ለምእመናንዋ፣ ለአገልጋቿ በተግባር የተደገፈ ሁለንተናዊ ሥልጠናዎችን ማመቻቸት አለባት፡፡ ወራሪ እየተባልን ከመገደልና ከመሰደድ ወጥተን የሀገር ባለቤት መሆናችንን በፍጥነት ልናረጋግጥ ይገባናል፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ቤተ ክርስቲያን አጋርነቱ ምን እየሠራ ይገኛል? በቀጣይስ ምን ለመሥራት አቅዷል?
አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ለአገልግሎት የጠራው መኅበር በመሆኑ ያቅሙን ያህል እየለፋ እየሠራ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ በዋናነት እየሠራ ያለው ሰውን ነው፡፡ የሰው ልጅ በሃይማኖት፣ በምግባር እንዲጸናና ዙሪያውን በአግባቡ እንዲረዳ የማድረግ ሥራዎችን ለረጅም ጊዜ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ምእመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ መልካም እንዲሆኑ፣ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸውና፣ ሀገራቸውን እዲወዱ እንዲጠብቁ የማድረግ አገልግሎቶችን እፈጸመ ይገኛል፡፡ በአገልግሎት መሀል ፈተናዎች ሁሌም ይኖራሉና ፈተናዎችን ከመቀነስና ከመከላከል ረገድ ከሞላ ጎደል ማኅበሩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ስለሆነም ምእመናንና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተረድተው በሃይማኖታቸውና በምግባራቸው ጸንተው ለዘላለም እንዲቆዩ ያስፈልጋል፡፡
ምእመናን በዚህ ወቅት በተለያዩ ችግሮች በተሰደዱና በተፈናቀሉ ጊዜ በሥነ ልቦናና በረሀብ ተጎጂዎች እንዳይሆኑ ባለጸጎችን በማስተባበር አስፈላጊው ሁሉ ሰብአዊ ድጋፍ በማኅበሩ በኩል እየተደረገ ይገኛል፡፡ ምእመናን ተሥፋ ቆርጠው እንዳይሰደዱና ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ በማኅበሩ በኩል ያላሰለሰ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ምእመናንን እያሳደዱ ወደ አንድ ቦታ በመሰብሰብ በቀጣይ “ጂሃዳዊ ጦርነት” ማወጅ አላማቸው እንደሆነ በመረዳት፤ ማኅበረ ቅዱሳንም ምእመናን ባደጉበትና በኖሩበት አካባቢ ተረጋግተው እንዲቆዩ የማድረግ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ለወደፊቱም ከዚህ የተሻሉ ሥራዎችን ይሠራል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለወደፊቱ ከቤተ ክርስቲያን ልዩ የሆነ ሥራ ባይሠራም ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠውን የልጅነት ሥራ ተቀብሎ ለመሥራት ግን ቁርጠኛ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከጥቃት የምትጠብቅበትን መዋቅር ሠርታ መንቀሳቀስ ከቻለች ማኅበሩ ቀዳሚ ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ማኅበረ ቅዱሳንን የሁሉ ነገር መፍትሔ አድርጎ መውሰድ ምእመናንን ማሳሳት በመሆኑ ተገቢ አይደለም፡፡ ማኅበሩ ማድረግ የሚችለው የድርሻውንና የአቅሙን ብቻ ነው፡፡ ምእመናን፣ ቤተ ክርስቲያንና ካህናት አገልጋዮች ደግሞ የራሳቸው የሆነ ድርሻ አላቸው፡፡ ሀገር ላይ ችግር የለም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ዋጋ ያስከፍላልና በማንኛውም ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በምትዘረጋው መዋቅር ውስጥ ማኅበሩ ተሳትፎውን በማሳደግ የራሱን ድርሻ የሚወጣ ይሆናል፡፡
በክልል በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ጨርሶ ማጥፋት ባይቻልም መከላከል ግን ይቻላል፡፡ በኦሮምያ ክልል የክርስቲያን ዘር የተባለን ሁሉ ጨርሶ ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንዳሉ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙት ተግባራት አመላካቾች ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህንን ተግባር ከማውገዝ በዘለለ ስልታዊና ሕጋዊ አካሄዶችን ተከትለን በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም በየጊዜው መግለጫ እያወጣ የተፈጠረውን ችግር ማቃለል ሳይሆን ሰዎች ያለ አግባብ እንዳይገደሉ፤ እንደይፈናቀሉ እና ሀብት ንብረታቸው እንዳይቃጠል እንዳይዘረፉ መሥራት አለበት፡፡ ችግሮች ከደረሱ በኋላም የተጎዱ ወገኖችን ማፅናናት፣ ማቋቋም፣ ካሳ መክፈል፣ የሕይዎት ዋስትና መስጠት እንዲሁም ችግር በፈጠሩ የመንግሥት አካላትም ሆነ ግለሰቦች ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት እስኪደርስላችው ድረስ ምእመናን ቀድመው ያላቸውን አቅም አሟጠው የራሳቸውን ደኅንነት ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ከዚህ በኋላ ምእመናን “መንግሥት ይደርስልናል” ብለው መዘናጋት የለባቸውም፡፡ ‹‹መንግሥት” የተባለው ቆሞ የሚያሳርድ ከሆነ ለወደፊቱ ሰላምን ያመጣል ብሎ መተማመን ከንቱ ድካም ነው፡፡
በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት መዋቅራዊና ሥርዓታዊ በመሆኑ መደረግ ያለበት ነገር ሁሉ መደረግ አለበት፡፡ ኦርቶዶክሳውያንን ለማጥፋት የደህንነትና የጸጥታ መዋቅር እያለ ደህንነት ሊሰማን ስለማይችል በደህንነቱም በፀጥታ መዋቅሩም ዘልቀን እስካልገባን ድረሰ ሞታችን ሞት ሆኖ ስለሚቀጥል በተጠቀሱት ሁለት ዘርፎች ላይ የተሻለ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ከዚህ ሥራ ያነሰ በሙሉ ኦርቶዶክስንና ኦርቶዶክሳውያንን ያጠፋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
|
ኦርቶዶክሳውያንን ሀገር አልባ የማድረግ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም መኖሩን አገልጋዮችና ምእመናን መገንዘብ አለባቸው፡፡
|
![]() |
- Details
- Written by: ዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1321
በአንድ ሐሳብ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መቆም ይገባናል
ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ፈተና ተለይቷት አታውቅም፡፡ በየዘመናቱ የሚነሡባት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ተጋፍጣ በጸሎት እየተጋች እዚህ ደርሳለች፡፡ ጠላት ዲያቢሎስ ለዘመናት የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን እያስነሣ፣ መሠረቶቿን ለማናጋት ሲታገል ቆይቷል፡፡ ለዚህም ምስክሩ ደግሞ የታሪክ መዛግብቶቻችን ናቸው፡፡
ፈተናው እንደ የዘመኑ መልኩን ቀያይሮ ቢመጣም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ግን ዓላማው አንድ ነው፡፡ ጠላቶቿ መኖርዋን ነው የማይፈልጉት፣ ማደግዋን ነው የሚጠሉት ፣ ስምዋ ከመቃብር በታች እንዲሆን ነው የሚሹት፣ ጨለማቸውን ስለምታጋልጥ ብርሃንዋን ሊያጠፉ ነው የሚጥሩት፡፡ እነርሱ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት በአንድነት ሲቆሙ እኛ ግን ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ በአንድነት መቆም አልቻልንም፡፡ እነሱ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት አንድ ቋንቋ ሲናገሩ፣ እኛ ግን እንደ ባቢሎን ዘመን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላልቋል፡፡ ከቤተ መቅደስ እስከ ዐውደ ምሕረት ፣ ሁሉም ባይሆን አንዳንዱ ከምእመን እስከ ጳጳስ አምላካዊውን ሥራ ሳይሆን የራሱን መሻት ለመፈጸም ይፈጥናል፤ አንዱ ሌላውን አይሰማም ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ስቃይ ዕለት ዕለት እንዲጨምር አድርጎታል፡፡
ራሱን በደገመው ታሪክ ውስጥ ሆነን የቤተ ክርስቲያን መከራ ከአፋችን አልወርድ ከዓይናችን አልጠፋ ብሎአል፡፡ በታሪክ እንደምናውቀው ትላንት ክርስቲያኖች ለአውሬ ሲጣሉ ነበር፡፡ ዛሬ ዓለም ሠለጠነ በተባለበት በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች በሰው መሰል አውሬዎች ታርደዋል፣ በሰው መሰል አውሬዎቸ በገዛ ሀገራቸው ላይ ስደተኛ ሆነዋል፡፡ እኛም ቆመን ይህን ክፉ ድርጊት እናያለን። በእርግጥ በቦታው ስላልነበርን እንጂ የዚህ ክፉ ድርጊት ሰለባ አካል እንሆን ነበር፡፡
በክርስቲያኑ ላይ እየዘነበ ያለው የመከራ ዶፍ ዛሬም አላበቃም፡፡ በየዕለቱ በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን አዳዲስ ጥፋት እንሰማለን አሁን አሁን ሰቆቃውን የተለማመድን ይመስላል፡፡ አጀንዳውን ከማራገብ ውጪ ምንም መፍትሔ አላመጣንም፡፡ ከተሰጠን አጀንዳ ባሻገር ማየት ያቃተን ይመስላል ትላንትናም ዛሬም ነገም የምንሰማው ነገር አንድ ነው “ክርስቲያኖች ታረዱ” ከሚል ወሬ ውጪ መሬት የወረደ ፣ በተግባር የተገለጠ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡
ሥጋዊ ፍላጎቱን አሸንፎ ቤተ ክርስቲያንን እና ማዕተቤን እያለ አንገቱን እየሰጠ በአንድነት ለቆመ ክርስቲያን በአንድነት ቆሞ አርአያ መሆን ከአባቶች ይጠበቃል፡፡ መከራውን በድል እንሻገርም ዘንድ አባቶችን የሚያከብር፣ የሚፈራ እና የሚሰማ ትውልድ መፍጠር ራስን መለወጥ ይገባል፡፡ ዘመኑ አንዱ ሌላውን በመንቀፍና በማንቋሸሽ የሚተጋበት ፤ በዘርና በጎጥ ጎራ የሚለዩበት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ሰላም በአንድነት የምንቆምበት ነውና፡፡
በየጊዜው ለሚወጡት መመሪያዎችና መግለጫዎች ተፈጻሚነት ከምእመኑ እስከ ቀዱስ ፓትርያርኩ ድረስ ‹‹እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ›› መሆንና እንደ ክርስቲያን መኖርን ይጠይቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያኝ ለሀገር የምትተርፍ ቤተ ክርስቲያን ናትና አጥብቀን ልንይዛት፣ በእውነት ልንመላለስባት፣ በአንድንት ልንቆምላት ያስፈልጋል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ መጀመሪያ ራሳችንን ልንታደግ ይገባል፡፡ ከውጭ ያለው በሰላም እንዲኖር በውስጥ ያለው ሰላም ይሆን ዘንድ ግድ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ሰላም ለምእመናንዋ ብሎም ለሀገር የግድ ያስፈልጋል፡፡ በሰላም እጦት እየታወከ ላለው ምእመን መነሻው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ሰላም ነውና ከዚያ ሊጀምር ይገባል፡፡
የሀገር ሰላም መናጋት የቤተ ክርስቲያን ሰላም መናጋት ነውና ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ሰላሙን ከቤትዋ መጀመር ይጠበቅባታል፤ ለዚህም ደግሞ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብሎ በአጸደ ቤተ ክርስቲያን የሚሰበሰብ ሁሉ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡
እያንዳንዱ ክርስቲያን ወደ ገዛ መንገዱ ከመሄድ ተቆጥቦ መዋቅርዋ ባማረው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አሰላለፉን አሳምሮ ሊጓዝ ይባል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረት መናጋት የሀገር መሠረት መናጋት ነውና ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምንም ያልጎደላት ስንዱ እመቤት በመሆንዋ በተሰናዳው መዋቅር ውስጥ በፈሪሃ እግዚአብሔር በጸሎት መትጋት የዘመኑ ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡
የሀገር አንድነትን ሆነ ሰላምን ለማምጣት የሰላማዊው ክርስቶስ ልጆች ለሰላም እና ለአንድነት በመቆም እየመጣ ያለውን የጥፋት እሳት ለማጥፋት በብርቱ ማገልገል ይጠበቃል ፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴዋ፣ ዝማሬዋ፣ ኪዳንዋና ሰዓታትዋ የሚነግሩን ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ በተግባር የሚታይና የሚጨበጥ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ይሠራ ዘንድ በሚደረገው መንፈሳዊ ጉዞ ሁሉ አባቶቻችን ከፊት ሆነው ሕዝቡን ሊመሩት ይገባል፡፡
መዋቅሩን በጠበቀ አደረጃጀት እንደ አባትና ልጅ በአንድ ላይ በመቆም አንደ ነነዌ ሰዎች ከልብ ሆነን እጃችንን ወደ እግዚአብሔር ልንዘረጋ ይገባል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› መዝ.፷፯፥፴፩ የተባለላት ቅድስት ሀገር ናትና አምላከ ቅዱሳን ለጸሎትዋ መልስ አይነፍጋትም፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዕለቱ ስለ ሀገር ፣ ስለ ዓለም ሰላም የምትጸልይ እንደሆነች ቢታወቅም ዛሬ ሀገራችን እንዲህ ሰላም ባጣችበት ወቅት ደግሞ አብዝታ ወደ አምላክ ልታሳስብ ይገባል፡፡ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ስንል ምእመንዋን፣ ካህናትዋን፣ መነኮሳትዋን፣ ጳጳሳትዋንና ሊቃነ ጳጳሳትዋን እና በአፀደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ ማለት እንደሆነ ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል፡፡
ተደጋጋሚ ፈተና ሲፈራረቅባት እና የመከራ ዶፍ ሲወርድባት የከረመችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሰባት ቀን ባወጀችው ብሔራዊ ጾም ሁላችንም እንደ ነቢዩ ዕንባቆም ‹‹አቤቱ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?›› ዕን. ፩፥፪ በማለት ልንጸልይ ይገባል፤ ያኔ አምላክ መልስ ይኖረዋል የቤተ ክርስቲያን መልስዋ ከላይ ነውና፡፡
- Details
- Written by: በመጽሐፈ ሲራክ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1504
“የአብነት መምህራን ከሌሉ ከቤተ ክርስቲያን አልፎ የኢትዮጵያ ማንነት ያሰጋኛል”
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈወርቅ ተክሌ
ክፍል ሁለት
እንደአጋጣሚ ሐምሌ ፭ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከበር ነበርና እዚያ ላይ ቅኔ እንድቀኝላቸው ስለተነገረኝ በዚያ ተገኝቼ ነበር፡፡ ለብፁዕነታቸው ቅኔ ተቀኝቼ ስወጣ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን የማውቀው ጓደኛዬ ከዚያው ደብር የቅኔ መምህር የነበሩት አባት ጡረታ ስለወጡ ለመቀጠር እንድጠይቅ ጠቆመኝ እኔ ግን እጅግ ፈራሁ፡፡ ቅዱስ ኡራኤልን የሚያህል ትልቅ ደብር ይቅርና ወደ ገጠር ለመሄድ ነበር ሐሳቤ፡፡ በጊዜው ስምንት ተማሪዎች ይዤ በኪራይ ቤት ውስጥ ነበርኩ የነገረኝን አድምጬ ”እስኪ እግዚአብሔር ያውቃል‘ ብዬው ተለያየን፡፡
በኋላ እሱው ነግሮ ይመስለኛል የደብሩ ጸሓፊ ሊቀ ሥዩማን ኪዳነ ማርያም ለደብረ ሲናው ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ጸሓፊ በመደወል ”መምህር አፈወርቅ ወደ ደብረ ጽጌ መምጣት ይፈልግ እንደሆን ጠይቅልኝ በእርሱ ስም ወደ ሀገረ ስብከት ደብዳቤ ጽፈናል‘ በማለት ነገረው፡፡ ጸሓፊው ሲነግረኝ ምንም ሳላንገራግር ሀገረ ስብከት መከታተል ጀመርኩ፡፡ በአጋጣሚ ግን ጸሓፊው ለሀገረ ስብከቱ እኔን እንደሚፈልጉ ደብዳቤ ሲጽፍ አለቃው ደግሞ በጎን ቀጨኔ ያሉት መምህር እንዲመጡ ጽፈው ኖሮ ሁለት ተቀጣሪዎች ሆነን ተገኘንና በፈተና ይለዩ ተባለ፡፡ በኋላ ላይ እሱም ቀረና በዕጣ ይለዩ ተብሎ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ባሉበት ዕጣ ሲወጣ ለኔ ወጣና በ፯፻ ብር ደሞዝ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል አገልጋይ ሆኜ ተመደብኩ፡፡ በጊዜው የደብረ ሲና ሕዝብ እንድቀርላቸው ጠይቀው ነበር እኔ ግን ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ያለዎት ያገልግሎት ጊዜ እንዴት ነው?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ ደብረ ጽጌ ጥሩ የአገልግሎት ጊዜ ነው ያለኝ፡፡ አሁን ድረስ እዚያው ነኝ፡፡ በርግጥ ብዙ ተማሪ ባይገኝም የአብነት ትምህርቱ አለ፡፡ እንደ ክረምት ወንዝ ክረምት ክረምት ይበዛል በጋ በጋ ደግሞ ይቀንሳል አንዳንዴም ይቋረጣል ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዱ የዘመናዊው ትምህርት ይወስደዋል አብዛኛው እየሠራ ነው የሚማረው ደሞዝ የለውም፡፡ ከሰኔ ጀምሮ ግን ዘመናዊው ሲዘጋ ብዙ ሰው ይማራል ዘንድሮ ግን በኮሮናው ምክንያት ትምህርቱ ጭራሽ ተቋርጧል፡፡
ደብረ ጽጌ ጥሩ ጥሩ ካህናት ነበሩ ፤ የማታ ስብከተ ወንጌልም ይሰጣል፡፡ እያንዳንዱ ካህን በየተራ እየገባ ወንጌልን እንዲያስተምር ተወያይተን ፈቃደኛ ሆነው በመገኘታቸው ማታ ላይ የሚሰብከውን ቀን ቀን ሲያጠና ውሎ ርእስ ጠብቆ ያስተምራል፡፡ በዓለ እግዚእ፣ በዓለ ማርያም ሲሆን ዋዜማ የሚመጡ ጉባኤተኛም ያስተምራሉ፡፡ እያንዳንዱ ካህን የራሱን ስብከት አጥንቶ መጥቶ ይሰብካል ፣ አስተያየት ይሰጠዋል በዚህም በደብሩ ላይ ያለው ካህን ሁሉ ሰባኪ ሆነ፡፡ በዚያ መነሻ ብዙዎቹ ካህናት የንስሓ ልጆቻቸውን እየሰበሰቡ በየወሩ ማስተማር ጀመሩ፡፡ ብዙዎች ወንጌልን የተማሩበት ትልቅ ቦታ ነው፡፡ አስተምረን ግን ለማስመረቅ ማኅተም አልነበረንምና ብዙ ተማሪዎች ማኅተም ካለበት ወደ ታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም እየሄዱ እየተማሩ የምስክር ወረቀት መያዝ ጀመሩ፡፡ ስብከተ ወንጌሉ እዚያ ተመድቤ ከሄድኩበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ አለ እኔም አስተምራለሁ፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከጀመሩ ስንት ዓመት ሆንዎት?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ብቻ ፲፩ ዓመት አገልግዬአለሁ ከ፲፱፻፹፮ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፺፯ ድረስ ማለት ነው፡፡ ከ፲፱፻፺፯ ጀምሮ እስከ ዛሬ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን እያገለገልኩ ነው ያለሁት፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ በአብነት ትምህርት ቤት ምን ያህል ጊዜ ቆዩ ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ በትምህርት ቤት ያሳለፍኩት ረጅም ዘመን ነው አንድ ፴ ዓመት ይሆነኛል፡፡ ቅኔ ቤት ከአምስት መምህራን ተምሬአለሁ፣ትርጓሜ መጻሕፍት ደግሞ ከሁለት የመጽሐፍ መምህራን ፣ እንዲሁም አቋቋም ከሁለት መምህራን ዘንድ ተምሬአለሁ፡፡ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ጠንቅቆ ማወቅ አይችልምና እኔም የተወሰነውን እና የምፈልገውን ያህል ተምሬአለሁ፡፡ ከኢሉባቦር እስከምመለስ ድረስ ለትምህርት ከሀገሬ ከወጣሁ ጀምሮ በ፴ ዓመቴ ነው ወደ ሀገር ቤት የተመለስኩት፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ በአብነት ትምህርት ቤት መምህርነትዎ ከተማሪ ጋር የነበረዎት ግንኙነት እንዴት ነበር?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ ከተማሪ ጋር ባለኝ ግንኙነት በተለይ ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ብዙም ደስተኛ አይደለሁም የዚህ ምክንያት ደግሞ ከማስተማሩ ጋር ብዙ ነገር ስላልተመቻቸልኝ ነው፡፡ ለማስተማር እፈልግ ነበር ግን ቦታው ተመቻችቶ ተማሪ በብዛት የሚገኝበት ሲሆን ነው መንፈስም የሚነቃቃው፣ ደስም የሚለው፡፡ ዛሬ አንድ ተማሪ ነገ ደግሞ አንድ ተማሪ እየተንጠባጠበ መጥቶ ሊማር ቢል ለአንድ እና ለሁለት ተማሪ ቁጭ ብሎ መዋል ብዙም አያረካም በዚህ ምክንያት ነው በደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል የማታውን ትምህርት የጀመርኩት፡፡ አብነት ትምህርቱ ላይ ሰው ሲጠፋ ነው ካህናትን ሰብስቦ ኮርስ የመስጠት ጅማሮ የነበረው፡፡ ከምእመናን እና ከሕፃናት እንዳልለይ ሐሙስ ሐሙስ አስተምር ነበር ተማሪ አልባ ዝም ብዬ እንዳልኖር በሚል ነው፡፡
ተማሪዎችን በሰፊው ለማስተማር ሐሳብ ነበረኝ ግን ተማሪ ስለሌለ አልተቻለም፡፡ ደብሩ አስፈላጊውን ነገር ለተማሪዎችም ሆነ ለመምህራን አሟልቶ ቢሆን ሁሉም ሥራ እስከሆነ ድረስ ማገልገል ይቻል ነበር፡፡ እኔ ግን አሁን በብዛት አገልግሎቴ ማሕሌት መቆምና ፍትሐት መፍታት ነው፡፡ በደብረ ጽጌ እሑድን ሳይጨምር ዘጠኝ ወርኀ በዓል አለ፡፡ እሑድ አራት ጊዜ ይቆማል ከዚያ ውጪ ዘጠኙን ወርኃ በዓል በየቀኑ እየገባሁ ስቡሕ ወዉዱስ እያልኩ አገለግላለሁ፡፡ አሁን በኮሮና ምክንያት ቀረ እንጂ ፍትሐትም መንደር ለመንደር እየሄድኩ ስፈታ እውላለሁ፡፡ በአጠቃላይ ተማሪ ስለሌለ ዛሬ ላይ የኔ አገልግሎት ፍትሐትና ማሕሌት መቆም ነው፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ ምናልባት ከተማ መሆኑ ተጽእኖ አድርጎ ይሆን?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ ከተማ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው ትልቁ ምክንያት ግን የተማሪዎች የኑሮ ሁኔታ ነው፡፡ ተማሪዎች የሚበሉት ስለሌላቸው የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ወደ ሥራ እንጂ ወደ ትምህርት አይመጡም፡፡ ጥቂት እንኳ ቢኖሩም ሙዳየ ምጽዋት እስኪያገኙ ድረስ ነው እሷም ስለማትበቃቸው ወጥተው ተጨማሪ የቀን ሥራ ይሰራሉ፡፡ ስለዚህ ከሥራ ውለው ማታ ላይ ለመማር ይደክማቸዋል ይተኛሉ፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ በአብነት ትምህርት ቤት መምህርነት ምን ያህል ተማሪዎች አፍርተዋል የእርስዎንስ ፈለግ የተከተሉ እንዲሁም በተለያዩ የቤተ ክርስቲያንቱ መዋቅር ውስጥ የሚያገለግሉ አሉ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ የተቀኙ ብዙዎች ናቸው በቁጥር እንዲህ ነው ልል አልችልም፡፡ ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ሳለሁ ቀደም እንዳልኩት የጎጃምና የጎንደር በር ስለሆነ ብዙ ተማሪዎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው እየተቀኙ ሄደዋል፡፡ ከዚህ ደብረ ጽጌ ከመጣሁ ግን የማስታውሳቸው ዘጠኝ የተቀኙ አሉ፡፡ ከዚያው ሙዳየ ምጽዋት እያገኙ የተቀኙ ወደ ዐሥር አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በጋውን አቋርጠው ክረምቱን የሚጀምሩ አሉ እንደዚያ እየሆነ ቁጥራቸው ከዚያ በላይ አልሄደም ፤ መዘምርነት እንጂ ለመምህርነት ብዙ ደርሷል እንኳ ለማለት አልደፍርም፡፡
የኔን ፈለግ የተከተለ እና እንደ እኔ መምህር የሆነ እገሌ የምለው የለም፡፡ የሚማር ተማሪ እስከሌለ ድረስ የኔን ፈለግ የተከተለ ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት አንድ ደኅና ዘራፊ አለ ተምሮ የሄደ ተስፋ የማደርገው ነገር ግን ገጠር ነው ያለው ምናልባት እርሱ እኔን ይተካ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ ቤተ ክርስቲያን እንደ እርስዎ ያሉ መምህራን እንዲበዙ ምን ማድረግ አለባት ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ መምህራን እንዲበዙ ከተፈለገ ቤተ ክርስቲያን ማድረግ ያለባት በጣም አጭር ዘዴ ነው፡፡ ቤተ ክህነቱ የመምህራንን እና የተማሪን ፍልሰት ማቆም አለበት ቀድሞ በጥንቱ እንዲህ የከፋ ፍልሰት አልነበረም ጎንጅ በጎንጅ፤ ዋሸራው በዋሸራ ፤ የዋድላውም በዋድላ አስመስክረው ከዚያው ቦታ ጎንጅ እና ዋሸራ ይቀመጡ ነበር፡፡ አሁን የሚፈልሱበት ምክንያት ይታወቃል፡፡ ዛሬም ለመምህራን በቂ ደሞዝ ሰጥቶ ባሉበት እንዲቀመጡ ቢደረግ መምህራን እንደሚበዙ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የሚፈልሱትን መምህራን እና ደቀ መዛሙርት የሚፈልጉትን አሟልቶ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ላይ ብዙ እየሠራ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ በበአታ፣ በጎንደር፣ በቤተ ልሔም፣ በዙር አምባ፣ በደቡብ ሌሎችም በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበሩ ብዙ ደቀመዛሙርት እያፈራ እንደሆነ እናያለን እንሰማለን ይህ እጅግ ደስ የሚል ሌሎችም ሊከተሉት የሚገባ መልካም ተግባር ነው፡፡
ይህ በጎ ተግባር መቀጠል መስፋት አለበት አዲስ አበባ ላይ ያሉ መምህራን ደቀ መዛሙርትን እንዲያስተምሩ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ጉባኤ ከሌለ ምን ይጠቅማል? ጉባኤያት በምንጭ ይመሰላሉ ፤ ምንጭ ከከርሠ ምድር ካልወጣ ይቆማል ምንጩ እየበዛ ሲሄድ ደግሞ ፈሳሽ ይሆናል፤ ፈሳሹ እየበዛ ሲሄድ ወራጅ ይሆናል ፡፡ ምንጩ ደጋውን፣ ወራጁ ወይና ደጋውን፣ ፈሳሹ ቆላ ደጋውን አጠጣ ማለት ነው ነገሩ የተያያዘ ነው፡፡ እንደዚህ ጉባኤያት ምንጭ ከሆኑ ከምንጭ የሚወጣው ፈሳሽ ምንድነው መምህራን ናቸው ማለት ነው፡፡ ከጉባኤ የሚወጡ መምህራን ናቸው፡፡ ወራጁ ቆላውን የሚያጠጡ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ከመምህራን የሚወጡ መጻሕፍት ማለት ነው ተያያዥ ነው፡፡ ያ ምንጭ እስካለ ድረስ መምህራንም አሉ መጻሕፍትም አሉ፡፡ ምንጩ ከደረቀ ግን ስቡሕ ወዉዱስ ብሎ የሚቆም ወይም አሐዱ ብሎ የሚቀድስ ይቅርና ተንሥኡ ጸልዩ የሚል ደቀ መዝሙር አናገኝም ይህ የታወቀ ነው፡፡
ዛሬ የምናገኛቸው አባቶቻችን ጳጳሳት በቅዳሴው በቅኔው፣በአቋቋም፣ በመጻሕፍት ትርጓሜና በሌሎቹ የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ አልፈው እዚህ የደረሱ ፤ ስለ እመ ብርሃን ብለው ከጉባኤ የወጡ ሊቃውንት እንጂ ቤተ ክርስቲያን ዝም ብላ ያመጣቻቸው አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምንጮች፣ ፈሳሾች ፣ ወራጆች እንዳይደርቁ ጉባኤያትን ማጠናከር ነው፡፡ አባቶች ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርና ምንጭ ናቸውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የዕውቀት ምንጮች በደንብ ይዛ የሚገባቸውን እየሰጠች እንዲያስተምሩ የምታደርግ ከሆነ ከሥር እየተተካ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ አሁን እንደምናየው ብዙ ዕድሜውን በአብነት ትምህርት ቤት ቆይቶ ሲወጣ ቤተ ክርስቲያን ደሞዝ ከፍላ በሚገባው ቦታ ተቀምጦ እንዲያገለግል ማድረግ አለባት፡፡ ይህ ካልሆነ ከ፳ እና ፴ ዓመት በኋላ ሊሆን የሚችለው ነገር ካሁኑ ያሰጋኛል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርት ቤቶች ምንጫቸው ከደረቀ ፣ መምህራን ከሌሉ ከቤተ ክርስቲያን አልፎ የኢትዮጵያ ማንነት ያሰጋኛል፡፡ ሀገራቸው እንደፈረሰ እንደ የመን እንደሌሎች ሀገሮች እንዳትሆን እሰጋለሁ፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አደጋ ተጋርጦ ነው ያለው፡፡
ይህን መቋቋም ካልቻልን ትምህርት ቤቱን አባዝተን ተማሪዎች እንዲበዙ ካልተደረገ እና ካልተጠናከሩ ”ሁሩ ወመሀሩ‘ የሚለው አምላካዊ ትእዛዝ ካልተላለፈ በስተቀር ሁላችንም ደሞዝ ብቻ እያገኘን ያለማስተማር የምንቀመጥ ከሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያስፈራል፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ መጻሕፍት እንዳሳተሙ ይታወቃል ምን ያህል ናቸው ? ይዘታቸውስ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ መጻሕፍቱ እንዲህ ዝም ብሎ ከመቀመጥ የተጻፉ ናቸው፡፡ ልብም ኅሊናም ስለማያርፍ ነው እንጂ ተሰጥኦ ኖሮኝ ወይም አዋቂ ሆኜ አይደለም የጻፍኩት፡፡ ግስ ወርዶ ሲያልቅ ቅኔ ተዘርፎ ሲያልቅ የሚመጡትን ሐሳቦች ችሎታ ያላቸውን ልጆች ኑ ጻፉ እላለሁ ይጽፋሉ ያቺ ትቀመጣለች ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሌላ ሐሳብ ሲመጣ እንዲሁ ይደረጋል ያቺን አጠራቅሜ ነው መጽሐፍ ያደረግሁት፡፡
ለኅትመት የበቁት አምስት ያህል መጻሕፍት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፍ መጽሐፈ ታሪክ ወግስ የሚል ነው፡፡ በቆሎ ትምህርት ቤት የተማሪውን ችግር ለማቅለል የጻፍኩት ነው፡፡ የቆሎ ትምህርት ቤት ግስ በእጅ ተጽፎ ነው የሚጠናው ፤ መጻፍ የማይችል ሰው ከፍሎ ለማጻፍ ገንዘብ ይቸገራል በዚያ ላይ ግሱ ላይ ታሪክም ስላለ የተማሪን ችግር ለመፍታት ነው የዕለቱን ታሪክ እና ግሱን ለማጥናት እንዲመቻቸው አድርጌ የጻፍኩት፡፡ በዚህ መነሻ ነው በመጀመሪያ ግሱን ወደ አማርኛ በመተርጎም ፣ ሊቃውንት ጥንት በእጅ ጽፈውት የነበረውን ግእዙን እንዲሁ ክብረ በዓል ደግሞ ከልደታ እስከ ፴ ቀን ያሉተን በአጠቃላይ አርስተ ግስ የቅኔ ዜማ ልክ፡ የአእመረን እርባታ እነዚህ ተሰብስበው ነው መጽሐፈ ታሪክ ወግስ መጽሐፍ የተጻፈችው፡፡
ሁለተኛዋ ትምህርተ አበው ወውሉድ የምትል አነስተኛ መጽሐፍ ስትሆን የአባቶች ትምህርት ለልጆች የምትል ሰባቱን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ፣ አምስቱን አእማደ ምሥጢር ፣ ለሕፃናት የሚሆኑ ልዩ ልዩ ታሪኮችን እንዲሁም የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የያዘች መጽሐፍ ናት፡፡
ሦስተኛዋ መዝሙረ ማሕሌት ወቅዳሴ የምትል መጽሐፍ ስትሆን የሰባቱን ዕለታት እና የዐሥራ ሁለቱን ወራት አጠቃላይ ታሪክ የያዘች መጽሐፍ ናት፡፡ ምስባኩ፣ የወንጌሉ እና መልእክታቱ ፣ የዘመኑ ታሪክም ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ መስቀል፣ ዘመነ ፍሬ እና ዘመነ ዮሐንስ በሚል ተከፋፍለው የተጻፉባት መጽሐፍ ናት፡፡
አራተኛዋ መጽሐፍ ቤተሰብና እንስሳት የምትል መጽሐፍ ናት፡፡ቤተሰብ እና እንስሳት ለየት ያለ ታሪክ ያላት ሲሆን የሰውን ከልደት እስከ እርግና ያለውን ታሪክ በዕድሜ ደረጃ በመከፋፈል ፤እንዲሁም ስለ እንስሳት የሚበሉና የማይበሉትን እንስሳት በመዘርዘር ዘሌዋውያን ፲፩ ላይ ካለው ጋር በማጣቀስ የጻፍኩት መጽሐፍ ነው፡፡
አምስተኛው መጽሐፍ ሐረገ ትውልድ ዘክርስቶስ የሚል ነው፡፡ ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ያለውን ትውልድ ነው የሚተርከው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዘመነ ሐዋርያት ፣ ዘመነ ሐዋርያን አበው ፣ ዘመነ ሰማዕታት፣ ዘመነ ሊቃውንት . . . ወዘተ አካቶ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ከላይ ከጠቀስኳቸው መጻሕፍት በተጨማሪም እግዚአብሔር ቢፈቅድ ለኅትመት የተዘጋጁ ሁለት መጻሕፍትም አሉኝ፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ በሕይወትዎ ፣ በአገልግሎት ዘመንዎ የገጠምዎን ጥሩም ሆነ መጥፎ የሚሉትን እና የሚያስታውሱት ቢነገሩን?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ ጥሩና መጥፎ የምንለው ያው የተፈራረቀብን ደስታና ኃዘን ማለት ይመስለኛል፡፡ በጣም የተደሰትኩበትን ጊዜ አላስታውስም ሐዘን ግን ከልቤ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ በተለይ የዚህን ዓለም ከንቱነት ሳስብ ፣ ”ሰውና እንጨት ተሰባሪ ነው‘ የሚለው ከኅሊናዬ ሲመላለስ ሐዘን ካልሆነ በስተቀር ደስታ ወደ ሐሳቤ መጥቶ አያውቅም፡፡ ሆኖም መጀመሪያ ያዘንኩበት ቀን ልጅ ሆኜ ፍየል ስጠብቅ ቦምብ የመታኝ ቀን ነው፡፡ የምንጠብቃቸው ፍየሎች ጠፍተውብን ከጓደኞቼ ጋር ባድማ ውስጥ ስንፈልግ በጨርቅ የተጠቀለለ ነገር አግኝተን ከኛ ከፍ የሚል ልጅ ነበር ምንነቱን ለማወቅ በድንጋይ ሲቀጠቅጥ ፈነዳ እኔ ከእርሱ ጀርባ ነበርኩና ፊቴ ላይና እጄ ላይ ጉዳት ደረሰብኝ ያ ጠባሳ ትቶ አልፎአል ሐዘኑ ግን ከልቤ አይጠፋም፡፡
እንዲሁም ዳሃና ዓምደ ወርቅ ልዩ ቦታው ጉራምባ ጊዮርጊስ የኔታ ታምራት ከሚባሉ ሊቅ ዘንድ እየተማርኩ ሳለ ደግሞ ወረርሺኝ ገብቶ ነበር ፡፡ በዚያ አካባቢ የወረርሺኙን ስም ”ሽዋ‘ ይሉታል በመጀመሪያ በዚያ ወረርሽኝ ምክንያት ጓደኛዬ ሞተ። እኔም የወረርሽኙ ዕጣ ፋንታ ደርሶኝ ከሞት ተርፌአለሁ፡፡ ተማሪዎች ተራራ ላይ እንደ ጎጆ ተክለው ”ቀሳ‘ይባላል በዚያ የተወሰነ ጊዜ ቆይቼ ጓደኞቼ አስታማሚ ሆነው እየረዱኝ ድኜ ወጥቻለሁ፡፡ እንደሚታወቀው የአብነት ትምህርት ቤት እያለን አባት እናት ስለሌለ ተማሪው ነው እርስ በርሱ የሚረዳዳው። ያንን ችግር በአብነት ትምህርት ቤት ጓደኞቼ እርዳታ አልፌዋሁ፡፡
ሌላው የኢህአዴግ ሠራዊት ሰቆጣን ሲቆጣጠር እኔ ከአባ ዓለሙ ጋር ነበርሁ እየተማርኩ ምሽቱን ከደርግ ጋር ሲዋጋ አደረና ንጋት ላይ ከተማዋን ተቆጣጠረ፡፡ ጥዋቱን በየመንደሩ ሲዞር እኔ ያለሁበትን ቤት መጥቶ በሩን በመደብደብ አስከፈተኝ የኔታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ነበርና እኔን ይዘው ሊሄዱ ይጎትቱኝ ጀመር ሰዎች ልጅ ነው ተማሪ ነው ብለው ሊያስጥሉኝ ቢሞክሩም የደርግ ወታደር ነው ይኸው ጠባሳ አለው እጁ ሁሉ ተመትቷል ብለው እምቢ ብለው ሰውን ሁሉ ያስጨነቁበት ጊዜ መቼም አልረሳውም፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ ቀረ የሚሉትና የሚጨምሩት ወይም የሚያስተላልፉት ነገር ካለ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ የምጨምረው የለም ጠርታችሁ ስለጠየቃችሁኝ ከሕይወት ልምዴ እንዳካፍል ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡ዛሬ ዛሬ ዙሪያው በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ተግታ ልትሠራ ይገባታል፡፡ ሁላችንም ከቤተ ክርስቲያን የተወለድን፣ መግቢያችን ፣ መጠጊያችን እርስዋ ናት ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፋ እና እንድትበዛ ተግተን ልንሠራ ይገባል፡፡ የቤተ ክህነቱም ሆነ የማኅበሩ የቴሌቭዥን ጣቢያ በዚህ ረገድ ጥሩ እየሠራ ይገኛል፡፡ አሁንም አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ሕይወታቸው አስተማሪ የሆኑትን ሊቃውንትን ብታቀርቡ ጥሩ ነው፡፡ ብዙ የተበላሹ ነገሮች ሊስተካከሉ ይችላሉና፡፡
በቅኔው ፣በግእዙ በኩል የሐዲሳቱ ሊቃውንት ቢቀርቡ ብዙ ያስተምራሉ የጠመመውን ያቃናሉ፡፡ በተለይ ግእዝ ሞቷል፣ተቀብሯል የሚሉቱ ብዙ ናቸው እኔ ግን ይበልጥ እየጠፋ ያለው ቅኔ ነው እላለሁ፡፡ የሚያስተካክል የሚያርም አባት ቁጥር እየመነመነ ነውና፡ ለምሳሌ አቋቋም ቢበላሽ ተው እንዲህ አይደለም የሚል ብዙ ነው ሊቃውንቱ ማሕሌቱ ላይ ፤ ዜማም ሲሰበር እንደዚሁ የሚያቀናው ብዙ ነው፡፡ ቅኔ ግን ሞያው ይቅርና ዜማው ሲሰበር ተው የሚል የለም፡፡ የዚህ አገልግሎት አነስተኛ እንደሆነ እናውቃለን ፡፡
በተለይ የግእዝ መምህራንን አቅርባችሁ የግእዝ የት መጣ ገለጻ እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል፡፡ ጥንታዊ የመጀመሪያው በመሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሐዲሳትም ፣ የብሉያትም ፣ የሊቃውንቱም ፣ የመጽሐፈ መነኮሳቱም ምንጩ ስለሆነ የቅኔው እና የግእዙ ሊቃውንት እንዲበዙ ብታደርጉ በእውነቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደፊት ትንሣኤዋን ታገኛለች ብዬ አስባለሁ፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እናንተንም ይጠብቃችሁ ማኅበሩን ያስፋ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ ኢትዮጵያን ያስፋ እግዚአብሔር ይስጥልን አመሰግናለሁ፡፡
- Details
- Written by: ቀሲስ ዘክርስቶስ ፀጋዬ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1303
ጸሎት በቤተ ክርስቲያን
የተወዳዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁ? መልካም፤ እግዚአብሔር አምላካችን የተመሰገነ ይሁን፡፡ በቤታችሁ ሆናችሁ ትምህርታችሁን በጥሞና ተከታተሉ!
ልጆች ባለፈው ትምህርታችን ላይ ጸሎት በቤታችን መጸለይ እንዳለብን አስተምረናችኋል፤ አሁን ደግሞ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ስንጸልይ ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን፡፡
የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት መንገድ መካከል አንዱ ጸሎት ስለሆነ በየትኛውም ቦታ ሆነን የምንጸልየውን ጸሎት እግዚአብሔር አምላክ ይሰማል፤ ይሁን እንጂ የተመረጡ የተቀደሱ ቦታዎች አሉ፡፡ ይኸውም በቤታችን ውስጥ የተለየ የጸሎት ቦታ በማዘጋጀት መጸለይ እና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ከካህናት አባቶች እና ከምእመናን ጋራ በኅብረት የሚጸለይባቸው ናቸው፡፡
ልጆች ጸሎት በቤተክርስቲያን በዘፈቀደ(ያለ ሥርዓት) የሚከናወን ሳይሆን ራሱን የቻለ ሥርዓት ያለው ነው፡፡ ይህም ከመጸለያችን በፊት በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ማድረግ የሚገባንን ዝግጅት ለመረዳት ያስችለን ዘንድ በሁለት ወገን ከፍለን እንመለከተዋለን፡፡ ከእነዚህም አንዱ ውጫዊ (አፍአዊ ዝግጅት) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውስጣዊ ዝግጅት ነው፡፡
በዛሬው ትምህርታችን ውጫዊ (አፍአዊ ዝግጅቶች) ውስጥ የሚጠቃለሉትና ማድረግ የሚገባንን እንመለከታለን፡፡
ሀ. መታጠብና አለባበስን ማስተካከል
ከመኝታ ተነስተን ወደ ጸሎት ከመሄዳችን በፊት እጅንና ፊትን መታጠብ ያስፈልጋል
ነጠላችንን መስቀለኛ ማጣፋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲኬድ ሴቶች ረዥም ልብስ መልበስ (ሴቶች ) በጸሎት ጊዜ ጸጉርን መከናነብ ቀሚስ መልበስ ይገባል፡፡
ለ. መብራት ማብራት
‹‹መልካሙን ሥራችሁን አይተው፥ በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ›› እንደተባለው ጧፍ ወይም ሻማ አብርተን ስንጸልይ የሚበራውም መብራት የእግዚአብሔርና የቅዱሳኑን ብርሃንነት ያስታውሰናል፡፡ ቅዱሳን መላእክት(ጻድቃን ፣ሰማዕታት፣…) በዙሪያችን እንዳሉም ያሳስበናል፡፡ (ማቴ. ፭፥፲፮)
ሐ. አቋቋም (ቀዊም)
ለጸሎትና ለምስጋና በምንቆምበት ጊዜ በቅዱሳን ሥዕላት ፊት በመቆም እንደ ሥዕሉ ባለቤት የሥላሴ (የእግዚአብሔር ወልድ) ከሆነ የአምልኮት፣ የእመቤታችንና የቅዱሳን ከሆነ የጸጋ የአክብሮት ስግደት በመስገድና በመሳለም ለሥዕሉ ባለቤት ያለንን ፍቅር አንገልጥባቸዋለን፡፡
ዓምድ (ቋሚ) ሳይደገፉ፣ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ መቆም ይገባል፡፡ ‹‹በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ›› በማለት ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደገለጸው እግርን አጣምሮ መቆም አይገባም፡፡ ካልታመሙ ለመቆም የማያስችል ችግር ከሌለ ተቀምጦ( ተኝቶ) መጸለይ አይገባም፡፡ (መዝ. ፭፥፫)
ቅዱሳን ሥዕላት ከሌሉ ፊትን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ወደ ግራና ቀኝ ሳያዩ መቆም እጆቻችንን ከሰውነታችን መስቀለኛ አድርጎ በመዘርጋት /መጸለይ ይገባል/፡፡ በቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹በሌሊት በቤተ መቅደስ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም አመስግኑት›› (መዝ.፻፴፫፥፪) በማለት ተናግሯል፡፡
መ. ዓይንን ወደ ሰማይ ማንሳት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ዓይንን ገልጦ ወደ ሰማይ አቅንቶ መጸለይን ነው፡፡ ለዚህም አልዓዛርን ባስነሳው ጊዜ ዓይኑን ወደ ላይ በማቅናት ጸልዮአል፤ እንደዚሁም አምስት እንጀራና ሁለቱን ዓሳ (ኅብስቱን) አበርክቶ ሲያበላ ያደረገውን ምሳሌ በማድረግ እኛም ዓይናችንን ወደ ሰማይ ወደ ቅዱሳት ስዕላት በማቅናት በመመልከት መጸለይ ይገባናል፡፡ (ዮሐ.፲፩፥፵፩፣ ፲፯፥፩)
መ. ማማተብ
ጸሎት ሲጀመርና ሲፈጸም አመልካችን ጣትን ከሌሎች ጣቶች ጋር አመሳቅሎ በትእምርተ መስቀል አምሳል ከላይ ወደ ታች ከግራ ወደ ቀኝ በማድረግ ሳይፈጥኑና እጅን ሳያወራጩ ረጋ ብሎ ማማተብ ይገባል፡፡
በጸሎት ላይ መስቀልን የሚያነሳ ቃል ስንጠራም ማማተብ ያስፈልጋል፡፡
ስናማትብ ‹‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፤ አአትብ ገጽየ ወኩለንታየ በትእምርተ መስቀል በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፊቴንና መላ ሰውነቴን አማትባለሁ በማለት በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን›› እያልን ነው፡፡ ስናማትብም የዲያብሎስ ሠራዊትን እናርቅበታለን የጠላትን ኃይል ድል እንነሳበታለን፡፡
ሠ. አስተብርኮ (ስግደት)
ለጸሎትና ለምስጋና በምንቆምበት ጊዜ በቅዱሳን ሥዕላት ፊት በመቆም እንደ ሥዕሉ ባለቤት የሥላሴ ከሆነ የአምልኮት፣ የእመቤታችንና የቅዱሳን ከሆነ የጸጋ የአክብሮት ስግደት በመስገድና በመሳለም ለሥዕሉ ባለቤት ያለንን ፍቅር አንገጥላቸዋለን፡፡
በጸሎት መጀመሪያና መጨረሻ ጉልበትን በማስተብረክ በመስገድ መጸለይ ይገባል፡፡ ስግደትን የሚያነሣ አንቀጽ ሲደርሱም ለእግዚአብሔር መስገድ ያስፈልጋል፡፡ በዕለተ ሰንበት (ቅዳሜ እና እሑድ)፣ በበዓለ ሃምሳ በበዓለ ወልድ በሀያ ዘጠኝ፣ በእመቤታችን በሀያ አንድ፣ በቅዱስ ሚካኤል በዐሥራ ሁለት፣ ሥጋና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ በእነዚህ ቀናት ጉልበት ምድር አስነክቶ መስገድ አይገባል፡፡ የዚህም ምክንያት ዕለታቱ በዓል በመሆናቸው በአንደበታችን ማመስገንና መዘመር እንጂ በጉልበታችን ስግደት አይፈቀድም፤ ቁርባን ከጠቀበልን በኋላም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም በውስጣችን ስለሚኖር በሰውነታችን ክቡር ስለሚሆን መሬት መንካት የለብንም፡፡
ሰ. ጸሎት አለማቋረጥ
ጸሎትን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ በቃልም ሆነ በምልክት መነጋገር አይገባም፡፡
ጸሎቱን የሚያቋርጥ ችግር ከገጠመን አባታችን ሆይ ብለን በማሳረግ ጸልየን ንግግራችንን ስንፈጽም ወደ ጸሎት ስንመለስ በድጋሚ አባታችን ሆይ ብለን ያቋረጥነውን መቀጠል ይኖርብናል፡፡
ጸሎት መጸለይ ከጀመርን ጀምሮ አንድ ቀን መተው በሌላ ቀን መጸለይ ሳይሆን ከጀመሩ አለማቋረጥ ተገቢ ነው፡፡
እንግዲህ ልጆች ጸሎት ንጹሕ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔርን የምንነጋገርበት እንዲሁም አምላካችን እግዚአብሔር ያከበራቸውን ቅዱሳንን የምናናግርበት እንዲያማልዱን የምንማጸንበት መሆኑን አውቃችሁ በንጽሕናና በሥርዓት መጸለይ፣ ከመጸለያችሁ በፊትና በጸሎት ጊዜ መደረግ ያለበትን ዝግጅት በተማራችሁት መሠረት በሚገባ መፈጸም ይጠበቅባችኋል፡፡
ልጆች እስከ ዛሬ ጸሎት ያልጀመራችሁ ካላችሁ ጀምሩ፤ የጀመራችሁ ደግሞ ሳታቋርጡ አጠናክራችሁ ቀጥሉበት፡፡ ይህንን ስታደርጉ አምላካችን እግዚአብሔር ይወዳችኋል፡፡
በመጨረሻም በሚቀጥለው ትምህርት እስክንገናኝ መልካሙንና የተወደደውን ነገር ሁሉ እንመኝላችኋለን፤ ደኅና ሰንብቱ!
- Details
- Written by: እህተ ሚካኤል ከጎፋ ገብርኤል
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1276
ገንዘብ እንጂ ምግብ የማይፈልጉ ነዳያን
ምጽዋት ለሌሎች ቸርነትን ማድረግ በኢትዮጵያ በተለይም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስያን ምእመን እጅግ የለመደ ነው፡፡ “ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ በደቀ መዝሙሬ ስም ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ የሚያጠጣ እውነት እላችኃለሁ ዋጋውን አያጣም” ማቴ ፲፥፵፪ የሚለውን አምላካዊ ቃል ተግባራዊ በማድረግ በእመቤታችን፣ በቅዱሳን፣ በሰማዕታት፣በመላእክት ስም ጠበል ጸዲቅ አዘጋጅተው ለነዳያን በማብላት እና በማጠጣት ከእመቤታችን፣ ከቅዱሳኑ፣ ከጻድቃኑ በረከት ይሳተፋሉ፡፡ የተቸገሩትን መርዳት በእግዚአብሔርም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ምእመኑ ያለውን በማካፈል ከሌለው ላይ እንኳ ቀንሶ በመስጠት የታወቀ ነው፡፡ ምግብ፣ ልብስ ገንዘብ የመሳሰሉትን ለሌላቸው ይሰጣል፡፡ “ለድሃ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ እንደ ስጦታውም መልሶ ይከፍለዋል ” ምሳ ፲፱፥፲፯ እንዳለ ጠቢቡ ሀብታም ደሀ ሳይል ለድሆች ይመፀውታል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ እና ዘርፈ ብዙ ችግር ያለባቸውን ነዳያን ከነሱ የተሻለው የመርዳት ባህል በእጅጉ የተለመደ ነው፡፡
ለዛሬው የትዝብት ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወደ አራት ኪሎ በሚወስደው መንገድ ላይ ያየሁት እና የሰማሁት አጋጣሚ ነው፡፡ መንገዱ የዘወትር መንገዴ ስለሆነ በዚያ ሳልፍ መንገዱ ጠርዝ ላይ ተቀምጠው የሚለምኑ አንድ አዛውንት አያለሁ፡፡ ሁሌም ሳያቸው ያሳዝኑኛል ለራሴም “እኚህ አዛውንት በዚህ እድሜአቸው እዚህ ጎዳና ላይ መቀመጥ አልነበረባቸውም፤ ሲሆን ቤታቸው ተቀምጠው በስርዓት ቤተ ክርስቲያን እየተሳለሙ ሥጋ ወደሙን እየተቀበሉ መኖር ነበረባቸው” እላለሁ፡፡ ሁሌም ባይሆን አልፎ አልፎ ገንዘብ እሰጣቸዋለሁ፡፡ ያን የማደርገው ቢያንስ ምግብ ገዝተው ይበሉበታል ብዬ ስለማስብ ነው፡፡
አንድ ቀን ግን ከዚህ የተለየ ነገር ሲያደርጉ አየኋቸው፡፡ አንድ ሰው በፌስታል በፌስታል የተቋጠረ ምግም ይዞ ከዘንቢል እያወጣ በአካባቢው ለነበሩ ነዳያን ያድላል፡፡ የራሱን ድርሻ የተቀበለ አንድ ወጣት ድጋሚ ተቀበለና ወደ አዛውንቷ እየሮጠ መጣና “ይኸው አመጣሁልዎት” በማለት እጁን ወደ ርሳቸው ዘረጋ ከአዛውንቷ የተሰጠው መልስ ግን እጅግ አስደንጋጭ ነበረ፡፡ “ውሰድልኝ ወደዚያ አሁን በምኔ ልይዘው ነው” ብለው ተቆጡት፡፡ ጥሩ ነገር ያደረገ የመሰለው ወጣት በሀፍረት ሽምቅቅ ብሎ ሲመለስ አየሁት፡፡
ከአዛውንቷ በተሰነዘረው ቁጣ ያዘለ መልስ ወጣቱ ብቻ ሳይሆን እኔም አስደነገጠኝ፡፡ እኒህ ሴት ገፋፍቶ ጎዳና ላይ ያወጣቸው አንዳች ነገር አለ እሱም ችግራቸው ነው፡፡ ሰዎች ከሚቸገሩባቸው ነገሮች ውስጥ በተለይ ጊዜ ከማይሠጡ የሰው ፍላጎቶች ውስጥ አንዱና ዋንኛው ደግሞ ምግብ ነው፡፡ በእርግጥ ሰው የተለያየ ችግር ሊኖርበት ይችላል ነገር ግን ሚዛን የሚደፋው የምግብ ችግር ነው፡፡ ምግብ የሚገፋ ነዳይ ግን ምን ዓይነት ነዳይ ነው፡፡ ሊረዳው የሚፈልገውስ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ሰው እንዴት ነው ሊረዳው የሚችለው?
የኒህ አዛውንት ገጠመኝ መነሻ ሆነ እንጂ እንዲህ ዓይነት ትዕይንቶችን በየመንገዱ በተለይም በቤተ ክርስቲያን ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በዓላት በሚከበሩበት ቀን ምእመኑ በእመቤታችን፣ በቅዱሳን ፣ በመላእክት ስም ጠበል ጸዲቅ አድርጎ የሚመጣበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ምግብ ከሆነ ላለመቀበል የሚሸሹ አሊያም ተቀብለው እዚያው ጥለውት የሚሄዱ ነዳያን ጥቂት አይደሉም፡፡
በቀድሞው ዘመን ነዳያን ከረጢት ይዘው መንደር ለመንደር እየዞሩ በመልአኩ ወይም በቅዱሳኑ ስም የሚበላ እና የሚጠጣ ነገር ነበር የሚለምኑት፡፡ በምእመን ደጅ ቆመው ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው የተሰጣቸውን በከረጢታቸው ከተው ምእመኑን አመስግነውና መርቀው ነው የሚሄዱት፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ እንደነዚህ ዓይነት ነዳያንን መንደር ውስጥ ሲለምኑ ማየት አሁን አሁን ብርቅ እየሆነ ሄዷል ጭራሽ የሉም ማለት ይቀላል፡፡
እውነት ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ነች እናም ዛሬ ዛሬ በርከት ያሉ ነዳያንን በቤተ ክርስቲያን ደጅ ተኮልኩሎ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የሚመጡትም ከመጽዋቹ ደግ ሕዝብ ምጽዋትን ሊቀበሉ ነው፡፡ ሆኖም የተቸገረ ነው ብሎ ምግብ መስጠት ለአንዳንዱ ነዳይ እንደነውር የሚቆጠር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነዳያንን ማየት ደግሞ ለቸገረው ነዳይ ለመመጽወት እስኪያስቸግር ድረስ ሰውን ጥርጣሬ ውስጥ ይከታል፡፡ ደህነኛውን ከችግረኛው ለመለየት ያስቸግራል፡፡ በእነደዚህ ዓይነቶቹና ከምግብ ይልቅ ትኩረታቸውን በሙሉ ገንዘብ ላይ ባደረጉ ነዳያን ምክንያት ሊመጸወቱ የሚገባቸው ሰዎች ሳይመጸወቱ ይቀራሉ፡፡
እንዲህ ዓይነት ነገር ሲነሳ የሞላ ኑሮ ያላቸው ትርፍ ነገር ፍለጋ አደባባይ የሚወጡ ሀብታም ለማኞችም አሉ ፣ ዛሬ ዛሬ መለመን ሱስ ሆኖባቸው እግረ መንገዳቸውን የሚለምኑ ሰዎችንም እያየን ነው፡፡ የውሸት ምክንያት እየደረደሩ የሚለምኑ፣ የውሸት የህክምና ወረቀት ይዘው ለመድኃኒት መግዣ የሚሉ አልፎም በልመና ገንዘብ ጠርቀም አድርገው ወደ ሀገራቸው ለመመለስም ከጎዳና የወጡ አዛውንቶችን ማየት ዘወትራዊ ሆኗል፡፡ ከነዚህ መሀከል የትኛው ነው ትክክለኛ ነዳይ ብሎ ለመመጽወት ሰዎችን እየፈተነ ያለበት ዘመን ነው፡፡
ከነዳያን ጋር ተያይዞ ከዘጠኝ ዓመት በፊት አንድ ወዳጄ ያጫወተችኝን ገጠመኝ እዚህ ላይ ላንሳ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የሰሚስተር ወረቀቷን በልመና ግጥም ላይ ለመሥራት ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ አንድ ነዳይ ትቀርብና የልመና ግጥሞች እንዲነግራት እና በመቅረጸ ድምጽ ልትቀዳው ትጠይቀዋለች፡፡ “በአንድ ግጥም ስንት ትከፍዪኛለሽ ?”የሚል ፈጣን ጥቀያቄ ነበር የሰነዘረላት፡፡ ነገሩ የውጤት ጉዳይ በመሆኑ በግጥም ፳ ብር ልትከፍለው ተስማምተው ቤቱ ይቀጥራታል፡፡ በዕለቱ ምግብ አዘጋጅቶ ቡና አስፈልቶ ነበር የጠበቃት፡፡ ይህ አይደለም የገረማት ቤቱ ውስጥ ቴሌቭዥን ሳይቀር ሁሉ ነገር የተሟላ ነው፡፡ በጊዜው መንገድ ላይ የተደረተ ቡትቶ ለብሶ የሚለምነውን ይኽ ነዳይ ከኑሮው ጋር አልገናኝ ብሎአት ተገርማ ነበር ያጫወተችኝ፡፡
የኒህ አአዛውንት ገጠመኝ መነሻ ሆኖ አንዳንድ ገጠመኞችን አልፎ አልፎ አነሳን እንጂ ነዳያን አካባቢ ብዙ ነገሮች ይነሳሉ የዋሁ ምእመን የመጽሐፍ ቅዱሱን “ሁለት ልብስ ያለው ለሌላው ይስጥ፤ ምግብም ያለውም እንዲሁ ያድርግ፡፡” ሉቃ ፫፥፲፩ የሚለውን ቃል በማሰብ እና ጽድቅን ፍለጋ በግልም በሕብረትም ብዙ ነገር ያደርጋል ሆኖም ለምን ዓይነት ሰው ነው መመጽወት ያለብን የሚል ነው ጥያቄው፡፡
በዚያው መጠን የሚላስ የሚቀመስ ያጡ እየቸገራቸው ኢትዮጵያዊው ባህል ይዞአቸው እጃቸውን ለልመና ለመዘርጋት አፍረው በችግር የሚማቅቁ ብዙ ሰዎች በየቤቱ መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም ፤ በንጹህ ልብስ ውሰጥ ችግር ያቆራመዳቸው ፤ በእውነት ሊረዱ የሚገባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ የቸገረውን ከደኽነኛው ለመለየት እጅግ አስቸጋሪ ወቅት መሆኑን የምናየው እንዲህ ገሀድ የወጡ ገጠመኞችን ስናይ ነው፡፡ ሆኖም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ስላሉ በጅምላ በመፈረጅ እጃችንን ከምጽዋት ፣ ልባችንን ከመራራት ልንመልስ አይገባም፡፡
- Details
- Written by: ካሣሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1203
በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ግፍና መከራ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው ግፍና መከራ እንዲቆምና በየምክንያቱ የታሠሩ ካህናትና ምእመናን ጉዳያቸው በጥንቃቄ ታይቶ ከእስር እንዲፈቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳሰበ፡፡
የታችኛው የመንግሥት መዋቅር ባለሥልጣናት ለጥፋተኞች ከሚያደርጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው አሳስቦ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ለደረሰው ጥፋትና ለወደፊትም ለሚደርሰው የሕግ ክትትል በማድረግ ችግሩን የሚከላከሉ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉር ስብከት ድረስ እንዲቋቋም መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በሀገሪቱ ያለው ወቅታዊ የሰላም እጦትና አለመግባባት ለዜጎች ተረጋግቶ አለመኖር እንዲሁም ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ በመሆኑ በቀጣይ አላስፈላጊ ሁከት ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ እርቅና ሰላም ማምጣት አስፈላጊ እንደሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አስገንዝቧል፡፡ የእርቅና የሰላም ሂደቱን የሚያስፈጽሙ ብፁዓን አባቶችም በአስታራቂነት መሰየማቸውን አስታውቋል፡፡
አገራዊ ሰላምና አንድነት እንዲኖር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት የእርቅ ሂደቱ እንዲቀጥል የፌዴራልና የክልል መንግሥታት መሪዎች ጥረት እንዲያደርጉ እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሀገሩ አንድነትና ሰላም ዘብ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አፈጻጸምን በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየተወሰኑ የተፈጸሙና ያልተፈጸሙትን በመለየት ያልተፈጸሙትን ምክንያታቸውን በመለየት ለፊታችን ግንቦት ርክበ ካህናት ውጤቱ እንዲቀርብ መወሰኑንም መግለጫው አመልክቷል፡፡
- Details
- Written by: መጽሐፈ ሲራክ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1646
የተወደዳችሁ አንባብያን በዛሬው የቤተ አብርሃም ዓምድ ዝግጅታችን በደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን የአብነት መምህር የሆኑትን ታላቅ አባት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ አብዛኛውን የዕድሜያቸውን ክፍል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ያሳለፉት በተማሪነት ከዚያም በአብነት መምህርነት መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ተክሌ የተወለዱት ዋግ የሚባል አካባቢ ሰቆጣ ውስጥ ነው፡፡ ነጋ ለኪዳን መሸ ለቁርባን ሁል ጊዜ ታታሪ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከነበሩት አባታቸው ቀሲስ ወልደ ተክለሃይማኖት እና ከእናታቸው አበባ ማርዋ መጋቢት ፳፭ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከዚያው የተወለዱበት አካባቢ ደብረ ሰላም በለዛ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከቀኝ ጌታ ተኮላ ዘንድ ከፊደል እስከ መዝሙረ ዳዊት ፤ ከግብረ ዲቁና አልፎ አርያም ሠልስቱን ተምረዋል፡፡ አሁን በደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘመናቸው ውስጥ ከልጅነት እስከ እውቀት ያለፉበትን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸው እንደሚከተለው ነግረውናል፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ በአብነት ትምህርት ቤት እስከምን ድረስ የት የት አካባቢ ተዘዋውረው ተማሩ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ፦ መጀመሪያ የተማርኩበትን አካባባቢውን ለቅቄ ለመማር ከወጣሁ በኋላ ዝቋላ ወረዳ ውስጥ ከምትገኘው ዲስቁ ማርያም የኔታ መኮንን ከሚባሉ የቅኔ መምህር ዘንድ ነው የሄድኩት፡፡ የኔታ መኮንን ፪፻ የሚደርሱ ተማሪዎች ነበሯቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅኔ የተቀኘሁት ከእርሳቸው ዘንድ ነበረ፡፡ ሰምና ወርቅ ጥሩ ችሎታ ነበራቸው፡፡ የኔታ መኮንን ከጊዜ በኋላ ላሊበላ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ሆነው ተቀጥረው ብዙ ዘመን አገልግለዋል፡ ገድለ ላሊበላን ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙትም እሳቸው ናቸው። ከእርሳቸው ዘንድ ከተማርኩ በኋላ ወደ ሰቆጣ ከተማ ሄጄ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ደብር ከሚገኙት የመጻሕት እና የቅኔ መምህር ከሆኑት ባሕታዊ አባ ዓለሙ ዘንድ ቅኔን ከነአገባቡ በሚገባ ቀጸልኩ፡፡
ከዚያ መልስ ወደ ዳሃና ዓምደ ወርቅ ልዩ ቦታው ጉራምባ ጊዮርጊስ በመሄድ የኔታ ታምራት ከሚባሉ ሊቅ ዘንድ ዝማሬ መዋሥዕት፣ ጾመ ድጓ፣ ድጓና ምዕራፍን ተምሬአለሁ፡፡ በኋላም ወደ ናአኩቶ ለአብ በመሄድ የድጓና የቅኔ መምህር ከሆኑት የኔታ ኃይለ ማርያም ቅኔውን አጠናቀቅሁ፡፡
ከየኔታ ኃይለ ማርያም ዘንድ ቅኔውንና ዜማውን ካጠናቀቅሁ በኋላ ዓይኔን ታምሜ ስለነበር ቦሩ ሜዳ የዓይን ሐኪም አለ ስለተባለ አባቴ ከላስታ ወደ ዋድላ ደላንታ ይዞኝ መጣ፡፡ ቦሩ ሜዳ/ከደሴ ከተማ ወጣ ያለ ነው/ ስንደርስ ግን ሐኪሙ ለዓመት ስለቀጠረን አባቴ ወደ ሀገሩ ሲመለስ እኔ ህክምናውን መጠበቅ ስለነበረብኝ ደሴ ውስጥ ደብረ ቤቴል ሥላሴ ከየኔታ ዕንቁ ባሕርይ /መምህር ኃይለ ማርያም/ ዘንድ ትምህርት ቤት ቀረሁ፡፡ መምህር ኃይለ ማርያም አራቱ አይናማዎች ከሚባሉት አንዱ ናቸው፡፡ አራቱ አይናማዎች ዓይነ ስውሮች ናቸው፡፡ አራቱም በአንድ ወቅት የወጡ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ሊቃውንት ነበሩ። እኔም የሕክምናዬን ቀጠሮ እየጠበቅሁ እሳቸው ዘንድ ክብረ በዓልን፣ወርኀ በዓልን ተማርኩ፡፡ ከዚያም ደሴ ከተማ ውስጥ ከነበረው አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቼ ትርጓሜ ሐዲሳትን ተማርኩ፡፡
በዚያው በትምህርት ላይ እንዳለን ወቅቱ ፲፱፻፸፯ ዓመተ ምሕረት ደሴ ላይ ረኀብ ጸንቶ ነበርና መምህራችን የኔታ ዕንቁ ባሕርይ ከዚህ ከከተማው ገጠሩ ይሻላል ወደ ኤልሻማ መድኃኔ ዓለም ሄዳችሁ ብትማሩ ጥሩ ነው ብለው ደብዳቤ ጻፉልን፡፡ እኔ ከሌሎቹ ትንሽ ከፍ እል ነበርና የሰጡኝን ደብዳቤ ይዤ ስድስት ተማሪዎችን አስከትዬ ቅኔውንም አቋቋሙንም እያስቀጸልኩ ወደ ኤልሻማ መድኃኔ ዓለም ስንጓዝ ያገኙኝ ገበሬዎች መንገድ ለመንገድ /አስፋልቱን/ ስትሄድ ጓደኞችህን ደርግ ይነጥቅህና ብቻህን ትቀራለህ አንተ ደካማ ነህ ወደዚህ ወደ ገጠሩ ነው እንጂ ወደ ኤልሻማ መድኃኔዓለም አስፋልቱን አትሂዱ ብለው ወደ አማራ ሳይንት እንድመለስ ነገሩን፡፡ በጊዜው መምህር ዕንቁ ባሕርይ ያዘዙንን ትተን ወደ አማራ ሳይንት ወደ ላይ ሄድን፡፡ አማራ ሳይንት የኔታ መንግሥቱ የሚባሉ የአቋቋም መምህር ነበሩና ከእርሳቸው ዘንድ ገባን ሆኖም ወቅቱ የረኀብ ነበርና ከዚያም የጠበቀን የከፋ ችግር ነበር።
ከዚያ ብዙም ስላልተመቸን በሽሎውን ተሻግረን ስማዳ ከተማ ጃምባ ተክለ ሃይማኖት የተክሌ አቋቋም መምህር ከነበሩት ከየኔታ ኪዳነ ማርያም ዘንድ ለመማር ገባን፡፡ እኔ የተማርኩት ጎንደሬ ነው እሳቸው ደግሞ ተክሌ ስለሆኑ በጊዜው መግባባት አልቻልንም፡፡ ብዙም ሳንቆይ መምህራችን የኔታ ኪዳነ ማርያም “ስለተጠራሁ ወደ ወለጋ ልሄድ ነውና ደብረ ኤልያስ ጠብቁኝ‘ ብለው ደብዳቤ ጽፈው ሰጡን፡፡ እንደገና ስድስቱን ጓደኞቼን እንደያዝኩ የአባይን በረሃ በእግራችን ተያያዝነው፡፡ ከወንዙ ስንደርስ ውሃው ከብብታችን እየደረሰ መሻገር አቅቶን ነበር ሆኖም እንደምንም በአካባቢው የነበሩ ዋናተኞች አሻግረውን ደብረ ወርቅ ጉንደ ወይንን አልፈን ደብረ ማርቆስ ደረስን፡፡ መምህራችን ያዘዙን ደብረ ኤልያስ እንድንጠብቃቸው ቢሆንም በየመንገዱ የሚያገኘን ሰው ሁሉ ሲጠይቀን ”ክህነት ልንቀበል ነው‘ እያልን አልፈናቸው እንሄድ ነበር፡፡
ደብረ ማርቆስ ደርሰን ደኅና የቅኔ መምህር መፈለግ ጀመርን፡፡ የሚያስተምረን ደኅና የቅኔ መምህር እንፈልጋለን የት እናገኛለን ብለን ሰዎችን ስንጠይቅ መምህር ጥበቡ ደስታ የሚባሉ ሊቅ በደንበጫ /ከደብረ ማርቆስ ወጣ ያለች ትንሽ ከተማ/ አሉ ብለው ስለጠቆሙን ፈልገን ከየኔታ ጥበቡ ዘንድ ገባን፡፡ በዚያም የጎንጅ ቅኔ፣አገባብ እርባ ቅምር ተምሬ የምስክር ወረቀት ተቀብያለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዋሸራውን ወደ ጎንጅ እየገለበጥኩ ብዙ ጊዜ በተማሪነት የኖርኩ ከእርሳቸው ዘንድ ነው፡፡ ዋናው መምህሬ እርሳቸው ናቸው ማለት ነው።
ስምዐ ጽድቅ ፦ በቀሰሙት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የት የት አካባቢ ተዘዋውረው አገለገሉ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ፦ እንደሚታወቀው ተማሪ ትምህርት ቤት ገብቶ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕውቀት ለመቅሰም ፴ እና ፵ ዓመት ይማራል የሚያገለግለው ግን ውስን ነው በትምህርት ቤት የሚያሳለፈው ጊዜ ይበልጣል፡፡ በአገልግሎቱም ጠንካራም ደካማም ጎን ሊኖረው ይችላል፡፡ እኔ ከየኔታ ጥበቡ አስተምር ተብዬ የምስክር ወረቀት ከተቀበልኩ በኋላ አቋቋም ለማስመስከር እፈልግ ስለነበር ወደ ጎንደር ነው የኔድኩት፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ገጠር አስተምሬ አዘዞ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ማርያም ደብር የምትባል አለች እዚያ የኔታ ኤርምያስ ጋር የተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፡፡ ብዙ ተማሪዎች ስለነበራቸው ብዙም አልተመቻቸልኝም እንደገና ወደ ጎንደር ተመልሼ አዘዞ አቢየ እግዚእ ኪዳነ ምህረት ደብር ነው የገባሁት፡፡ በዚያ የነበሩት መምህር የኔታ አክሊሉ ይባላሉ የአቋቋም መምህር ናቸው እሳቸው ጋር ተጠግቼ እየተማርኩ ሳለ የደብሩ አለቃ አለቃ ገዳሙ ይባላሉ ፶ ብር እንክፈልህና ቅኔ አስተምር ስላሉኝ አቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት ቀን ቀን እያስነገርኩ ማታ ማታ ቅኔ እየዘረፍኩ ብዙ ተማሪዎች አስተምሬአለሁ፡፡ በዚያ ቅኔ ብቻ ሳይሆን አቋቋምም አስተምር ነበር። በደብሩ መምህር አክሊሉ እና መምህር ዳዊት የሚባሉ በአካባቢው የሚያስተምሩ በአንድ ደብር ሁለት የአቋቋም መምህራን ነበሩ፡፡ እኔም በዚያ ተቀምጬ እያስተማርኩ ያልተማርኩትንም እማር ነበርና ብዙ ጥቅም አግኝቼበታለሁ፡፡
ከዚያ በኋላ አቋቋም አስመሰክራለሁ ብዬ ከየኔታ ሄኖክ /መጋቤ አዕላፍ/ አሰፈቅጄ ነበረ ነገር ግን ወንበር ተይዞአል ስለተባለ ወንበር አላገኘሁም እንዲሁ በተመላላሽ ከእርሳቸው እማር ነበረ፡፡ እንግዲህ በዚያ ዘመን የተወሰነ ጊዜ አስተምሬ ነበር ፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ እንዴት ሊመጡ ቻሉ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ አጋጣሚ ሆኖ መምህር ሰሎሞን የሚባል ቅኔ ቤት አብረን የነበርን ጓደኛዬ ቀደም ብሎ አዲስ አበባ መጥቶ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም በቅኔ መምህርነት ተቀጥሮ ነበረ፡፡ ወደ እኛ መጥቶ በተገናኘን ጊዜ አዲስ አበባ ለመምጣት ፈልጋለሁና እባክህ ቦታ ፈልግልኝ ብዬው ስለነበረ ሌላ ጊዜ ስልክ አስደውሎ “አዲስ አበባ ቦታ ተገኝቶልሃልና አሁን ና ” ብሎ መልእክት ላከብኝ ፡፡ መልእክቱ በደረሰኝ ጊዜ ለመሄድ ብነሳም ምንም መጓጓዣ አልነበረኝም ያው እንደሚታወቀው ለምነን የተገኘውን ከተማሪ ጋር ነው ተካፍለን የምንበላው እንጂ ምንም ጥሪት የለንም፡፡ የተማርኩባቸውን መጻሕፍት ሽጬ ሁለት ተማሪዎች አስከትዬ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ ስደርስ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ መምህር ሰሎሞን ተቀብሎ ከብፁዕ አቡነ ገሪማ ጋር አገናኘኝ፡፡ ብፁዕነታቸው ያኔ የጅማና የኢሊባቡር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ ብዙ ጥያቄዎችን ከጠየቁኝ በኋላ ”መቱ ከተማ የካህናት ማሰልጠኛ አለ በዚያ ለካህናቱ ቅኔ እንድታስተምር ነው የጠራሁህ፡፡ ቅኔ ፣ አቋቋም ፣ዝማሬ መዋሥዕት፣ ዜማ ትችላለህ?‘ ብለው ጠየቁኝ፡፡ ”አዎን እችላለሁ‘ አልኩአቸው፡፡
እንግዲህ በብፁዕነታቸው መልካም ፈቃድ ወደ ኢሊባቡር እንድሄድ ሆነ ወዲያውኑ ከቤተ ክህነት ደብዳቤ ተጻፈልኝ ሁለት ተማሪዎችን ይዤ ወደ ጅማ ከዚያ ወደ ኢሉባቡር ሄድኩ፡፡ ከ፲፱፻፹፫ እስከ ፲፱፻፹፮ ዓመተ ምሕረት ድረስ የተቀጠርኩበት መደቤ በቅኔ መምህርነት ስለነበር ቅኔ እያስማርኩ ቆይቻለሁ፡፡ ማሠልጠኛው በዓመት ፻ ካህናት ያሠለጥናል፡፡ ስልጠናው በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ነው በመጀመሪያው ዙር ከመስከረም እስከ የካቲት ፶ ካህን እናሠለጥናለን፤ በሁለተኛው ዙር ከየካቲት እስከ ሰኔ ፶ ካህናት እናሰለጥናለን፡፡ በዚህ ረገድ ከሥልጠናው ጋር ተያይዞ የእኛን ማሠልጠኛ ጨምሮ ሌሎች መሰል የካህናት ማሠልጠኛዎች በአኃት አብያተ ክርስቲያናት ይረዱ ነበር፡፡ ከዚያ የሚመጣው ገንዘብ ነው የማሠልጠኛው በጀት፡፡ ለምሳሌ የጎንደርና የጎጃም ካህናት የሚሠለጥኑት ባሕር ዳር ፤ የወሎ እና የትግራይ ካህናት መቀሌ፤ ምስራቅ ሸዋና ሐረር ዝዋይ፤ እንዲሁም የወለጋ፣ የጅማ የኢሊባቡር ካህናት ደግሞ እኔ ከነበርኩበት መቱ ማሰልጠኛ ነበር የሚሠለጥኑት። ጥሩ ትምህርት ተሰጠ የምለው ያን ዘመን ነው።
በዚያ ብዙ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ እኔ ቅኔ ሳስተምር ሁሉም መምህራን አሉ የሐዲስ ኪዳን መምህር ፣ የብሉይ ኪዳን መምህር፣ የአቋቋም መምህር ፣ የቅዳሴ መምህር ፣ የዜማ መምህር ይገኛሉ፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን ክፍል ቢያስተምሩም ሌላው ሲያስተምር ደግሞ ቁጭ ብለው ይማራሉ፡፡ ሁሉም ሰው መምህርም ተማሪም ነው፡፡ ሁሉንም በማዋሐድ የወንጌል ትምህርት በደንብ የተሰጠበት ትምህርት ጊዜ ነበር፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው ለሚሠለጥኑት ካህናት ብቻ አይደለም በአካባቢ ለነበሩት ምእመናን እና የምእመናን ልጆች ሁሉ ነበር ፡፡ ዘመኑ መናፍቅ የጠፋበት ዘመን ነበረ፡፡ ተሳትፎው በጣም ጥሩ የነበረበት ጊዜ ነበር ፡፡ እነዚህ አሁን የቆጠርኳቸው ማሠልጠኛዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አንደበቶች ነበሩ፡፡ ዛሬ እነርሱ ቢኖሩ ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ባልተቃጠለችም ነበር መናፍቃንም ባልበዙ ነበር፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ ማሠልጠኛዎቹ መቀጠል አልቻሉም ነበር ? ምን ነበር ምክንያቱ ?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ ከተወሰነ ዓመታት በኋላ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ለማሠልጠኛዎቹ የሚመጣው በጀት ቆመ ተባለ፡፡ ምክንያቱን ስንጠይቅ ርእሰ መምህሩ ሰብስበውን በጀቱን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ወደ ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ማዞራቸውን ነገሩን፡፡ ለምሳሌ እኔ ከማሠልጠኛው የማገኘው ገንዘብ ፻፶ ብር ነበረ ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ስለምቆም ፶ ብር አገኝ ነበረ አንድ ላይ ፪፻ ብርማለት ነው፡፡ ደሞዙ ትንሽ ቢሆንም ምግብ እዚያው ስለሚሠራ የምንመገበው ከማሠልጠኛው ነበረ ደቀ መዛሙርቱም ከዚያ ይመገቡ ነበረ፡፡ በጊዜው በጀቱ ወደ ቅድስት ሥላሴ እስኪዞር ድረስ ሁሉ ነገር የተመቻቸ ነበረ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ድርጅቱ ሲዞር መምህራን እና ተማሪዎች እንዲበተኑ ምክንያት ሆነ፡፡
በጊዜው እንደ ዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የነበሩ የካህናት ማሠልጠኛዎች ራሳቸውን የቻሉ ቀደም ሥራ ሰርተው የነበሩ በራሳቸው ገንዘብ ለመቀጠል በቅተዋል፡፡ እንደነ መቱ የካህናት ማሠልጠኛ እኔ የነበርኩበት ማለት ነው እና ሌሎች ማሠልጠኛዎች ደግሞ አቅም ስላልነበራቸው መምህራንን ደቀ መዛሙርትንም ለማሰናበት ተገደዋል፡፡ “የምንከፍላችሁ ደሞዝ የለም ወደ የመጣችሁበት ወደ ሀገራችሁ ሂዱ‘ ብለው አሰናበቱን፡፡ ሁሉም መምህር ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ እኔም ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ መጥተን የምናስተምርበት ማሰልጠኛ ጠይቀን ነበር አዲስ አበባ ላይ ማሠልጠኛ ሳይሆን ደብር ነው የምንሰጣችሁ የሚል መልስ ተሰጠን ሆኖም ቦታውን ሳናገኝ እስከ ስድስት ወር ቆየን፡፡
በዚህ መሃል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም አስቀድሰው ሲወጡ ሦስት ቀን በተከታታይ አገኙኝ በሦስተኛው ቀን ግን ቆም ብለው “ይህ ሰውዬ ችግሩ ምንድነው'' ብለው ጠየቁ ሊቄ ብርሃኑ መኮንን ችግሬን እና ያለሥራ መቆየቴን ያውቁ ስለነበር ”የቅኔ መምህር ነው ቦታ ይሰጠው ሌላ ቸግር የለበትም ‘ ብለው አስረዱልኝ በዚህ ጊዜ ብፁዕነታቸው ”እኛ እንፈልገዋለን እዚህ ቅደስት ማርያም ቶሎ ይጻፍለት‘ ብለው ፈቀዱልኝ፡፡ይህን ሲሉኝ ደስታዬ ወደር አልነበረውም፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ ስለዚህ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ሥራውን ጀመሩ ማለት ነው?
መጋቤ ምሥጢር መምህር አፈ ወርቅ ፦ አልጀመርኩም ቅዱስነታቸው እንዳዘዙ ለጊዜው ይጻፍልሃል ተብዬ ነበር በማግሥቱ ወደ ሊቄ ብርሃኑ ስሄድ ግን የብፁዕነታቸው ቃል ተፈጻሚ አልሆነም ”እኔ ለቅድስት ማርያም አልጽፍልህም ሂድ ወደ ሀገረ ስብከቱ ብፁዕ አቡነ ማትያስ እዚያ ይጠብቁሀል‘ አሉኝ፡፡ አሁን ካናዳ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ማትያስ በወቅቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ በነገሩኝ መሠረት ወደ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሄድኩኝ ፡፡ እሳቸውም ገና እንዳዩኝ ”ለምንድነው ፓትርያርክ ሲመጣ አላስገባ አላስወጣ እያልክ የምትጮኽ?‘ አሉኝ ፡፡ እኔም ”አባታችን ምን ላድርግ ራበኝ መልአክ አይደለሁ ሰው ነኝ ምን ልብላ? የት ልደር? ይዤ የመጣሁትን ገንዘብም ጨርሻለሁ እና ቸግሮኝ ነው‘ አልኳቸው፡፡ ”ምነው ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም አስኮ ገብርኤል፣ ምልክት አድርጌልህ ነበር ለምን አልገባህም?‘ አሉኝ ፡፡ እኔም ”ይኸው ርእሰ መምህሩን ይጠይቋቸው ሁለቱም ቦታ አልጽፍም ብለው አስቀርተዋል‘ አልኳቸው፡፡ ብፁዕነታቸው ካሳሁን የሚባሉትን /ያን ጊዜ የሀገረ ስብከቱ ርዕሰ መምህር / ጠርተው ሲጠይቁ ገነተ ጽጌ በራሳቸው ሰው ስላመጡ ሌላ ተጨማሪ አንፈልግም ብለው ነው፣ አስኮ ገብርኤልም በጀቱ ተመልሷል ስላሉ ልጽፍላቸው አልቻልኩም አሉ፡፡ አቡነ ማትያስም ”ቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲቀጠሩ ስላዘዙ ነገ ባስቸኳይ እንዲጽፉላቸው ብለው ተቆጡ፡፡ ርእሰ መምህሩም ጽፍልሃለሁ ከነገ ወዲያ ና ብለው አዘዙኝ፡፡ በተባልኩት ቀን ሄድኩ፡፡ በሥራ አስኪያጁ በሊቀ ካህናት አለማየሁ ኀይለ ሥላሴ የተፈረመ ፻፴ ብር እያገኙ ደብረ ሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግሉ የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ አዲሱ ገበያ ያለው ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው፡፡
ደብዳቤው እንደደረሰኝ ወዲያው ወደ ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሄድኩ፡፡ ደሞዙ ብዙም ባይሆን ቦታው ጥሩ ቦታ ነበረ ፤ እኔም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ እዚያ አለቃ ኤልያስ የሚባሉ ታላቅ ሰው ነበሩ በወቅቱ ከአለቃ አያሌው ታምሩ ጋር በጠቅላይ ቤተ ክህነት የጉባኤ ሊቃውንት ዋናዎች ነበሩ፡፡ አለቃ ኤልያስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን እሑድ እሑድ ወንጌል የሚያስተምሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡ በጊዜው የማታ ስብከተ ወንጌል አይሰጥም ነበርና የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ተነጋግሮ ደብዳቤ በመጻፍ እንድጀምር ኃላፊነቱን ለኔ ሰጡኝ፡፡ እኔም ከካህናት ማሰልጠኛ ከኮርስ ስለሄድኩ የደብሩ የአቋቋም መምህር ከሆነው መምህር ዳንኤል ጋር እየተፈራረቅን ለመጀመሪያ ጊዜ የማታ ስብከተ ወንጌል ጀመርን፡፡
በጊዜው ብዙ ሕዝብ እየመጣ መማር ጀመረ፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ወንጌል የተጠማ ሕዝብ ነበርና እየበዛ ሄደ፡፡ በኋላ ላይ አለቃ ኤልያስ ”እንደግዲህ እኔ ደክሞኛል በኔ ቦታ እየገባህ አስተምር ብለው‘ ሁሉንም ወደ እኔ አስተላለፉ፡፡ ሕዝቡም ተቀበለው በየተራ እየገቡ የመድኃኔ ዓለም ዝክር፣ የእግዚአብሔር አብ ዝክር ይዘክሩ ነበር እኔም በየወሩ እየገባሁ አስተምራለሁ፡፡ የእግዚአብሔር አብ ሕዝብ እንደ ከተማ ሕዝብ ሰምቶ ሂያጅ አይደለም ትምህርት ተቀባይ ጠንካራ መንፈሳዊ ፣ ቅዱስ ሕዝብ ነው፡፡ ከስብከተ ወንጌሉ በኋላም ማታ ማታ የቅኔ ትምህርት ነበር በተለይ ከጎጃም እና ከጎንደር የሚመጣው ወደ ከተማ መግቢያው በሩ በዚያ ስለሆነ ብዙ ተማሪዎች ወደ እኛ እየመጡ ያርፉ፣ይማሩም ነበረ፡፡ ብዙዎች ቅኔ ተቀኝተዋል፣ ትልቅ ደረጃም ደርሰዋል፡፡ እንግዲህ እዚያ ብዙ ጊዜዬን ያሳለፍኩት በስብከተ ወንጌል እና ቅኔን በማስተማር ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ግን አገልግሎት እጅግ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር፡፡ አንዴ ሌቦች የጽሕፈት ቤቱን ጣሪያ ቀደው ገብተው ገንዘብ ሰረቁ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የጥበቃ ሠራተኞች ሰበካ ጉባኤ ላይ ተጠርተው ሲጠየቁ መምህር አፈወርቅ ጋር የሚመጡ፣ መቃብር ቤት የሚያድሩ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ብዙ ተማሪዎች ስላሉ ግቢውን መቆጣጠር አልቻልንም አሉ፡፡ መቃብር ቤት ያሉት ይልቀቁልን የሚል አቤቱታም በጽሑፍ ለጽሕፈት ቤቱ አስገቡ፡፡ ሰበካ ጉባኤውም ሰኔ ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም መቃብር ቤቱን ለቅቄ እንድወጣና አንድም የአብነት ተማሪ እንዳይገኝ የሚል ደብዳቤ ጻፈልኝ፡፡ እውነት ለመናገር እጅግ ያዘንኩበት ጊዜ ቢኖር ያኔ ነው ምክንያቱም እኔም ኾንኩ የማስተምራቸው በርካታ የአብነት ተማሪዎች ሊበተኑ መሆኑ ነው ያሳዘነኝ፡፡ በመሠረቱ ቦታው ከ፲፱፻፹፮ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ያገለገልኩበት ቦታ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ከዚያ ቦታ ስለመሄድ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ አንዴ አስታውሳለሁ ጓደዬ ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ሊያስቀጥረኝ ወስኖ ነበር በጊዜው ግን ”አባቴ አለቃ ኤልያስ ከቦታው እንዳልሄድ ቃል አስገብተውኛልና አልሄድም‘ ጥሪውን አልቀበልም ብየው ነበር፡፡ አሁን ግን በደብዳቤ ጭምር መቃብር ቤቱን ለቅቄ እንደወጣ ስለታዘዝኩኝ ወደ ሌላ ቦታ እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክን ”ደሞዝ አልልም ሰው ካለበት ብቻ አድርሰኝ‘ እያልኩ በጸሎት እማጸነው ነበር፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1091
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው ዐበይት በዓላት መካከል የጥምቀትና የመስቀል ደመራ በዓላት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ እነዚህን የአደባባይ ሕዝባዊ በዓላት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እንደተጠበቀ ከዘመን ዘመን ስታከብር ቆይታለች፡፡ በእነዚህ የአደባባይ በዓላት አማካይነት ቤተ ክርስቲያኗ ሃይማኖታዊ ሥርዓቷን ለመላው ዓለም ከማስተዋወቅ አልፋ የሀገርን ባህልና ዕሴት ማሳየት ችላለች፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሀገራችን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገቢ ምንጭ ሆናለች፡፡ በዓላቱን ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚመጡ ዜጎች በሀገራችን በሚኖራቸው ቆይታ የሚገኘው ገቢ ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱን ማስተዋል ይቻላል፡፡
ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ዜጎችም በሚያዩት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተደስተው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓትና ሀገሪቱን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ያስተዋውቃሉ፡፡ በዚህም በየዓመቱ በዓላቱን ለመታደም የሚመጡት የውጭ ሀገር ዜጎች ከጊዜ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህንን የተመለከተውና የበዓላቱን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በደንብ የገመገመው ዩኒስኮ የጥምቀትና የመስቀል ደመራ በዓላት የዓለም ቅርስ ሆነው እንዲመዘገቡ አድርጓል፡፡ በዓላቱ በዩስኮ ከተመዘገቡ በኋላም የጎብኝው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር ሁለተናዊ ጥቅም ፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡
በዓላቱ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለየ ድምቀት ከመከበራቸው ባለፈ ኦርቶዶክሳውያን ባሉበት የዓለም ክፍል ሁሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ተጠብቆ ይከበራሉ፡፡ አሁን ላይ በዓላቱ በሌላው ዓለም የሚከበሩትን ያህል በኢትዮጵያ በአንደንድ ቦታዎች በነጻነት እየተከበሩ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በዓላቱ በአንዳንድ የኢትዮጰያ ክፍሎች በሚከበሩበት ወቅት የበዓሉን ድባብ ለማበላሸት ፀረ ክርስቲያን ኃይሎች ሁልጊዜ ሁከትና ብጥብጥ ይፈጥራሉ፤ በታቦተ ሕጉ ላይ ድንጋይ ይወረውራሉ፤ የምእመናን ነጠላ ይነጥቃሉ፤ ያሳድዳሉ እንዲሁም “ታቦተ ሕጉ በእኛ አካባቢ አይሄድም” በማለትም መንገድ ይዘጋሉ፡፡ እነዚህ ሕገ ወጥ ድርጊቶች በአመዛኙ በድሬደዋ፣ በሐረር፣ በምዕራብ አሩሲና በባሌ አካባቢዎች ይስተዋላሉ፡፡
በበዓላቱ ላይ እየተፈጸሙ የመጡ ትንኮሳዎች ተጠናክረው በመቀጠላቸው የመንግሥት ሹማምንቶች የመስቀልና የጥምቀት በዓላትን ማክበሪያ ቦታዎችን እስከመንጠቅ ደርሰዋል፡፡
በተለይ በአሁኑ ወቅት በዩኒስኮ የተመዘገቡ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ያለአግባብ መንጠቅ የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡ በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የአደባባይ በዓላት ማክበርያ ቦታዎች እየነጠቁ ያሉት የበዓሉን ጥቅምና ጣዕም ያልተረዱ አንዳንድ የመንግሥት ሹማምንቶች እንደሆኑ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች ምእመናን በኩል ከሚመጡ መረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን በተመለከተ በአብዛኛው ቅሬታ ከሚስተናገድባቸው ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በግንባር ቀደምነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከአንድም ሁለት የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን የየአካባቢው የመንግሥት ኃላፊዎች እንደነጠቁ ከሀድያና ጋሞ ጎፋ አህጉረ ስብከት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሀድያ ዞን የመንግሥት አመራሮች ደግሞ የዚህ ተግባር ማሳያዎች ናቸው፡፡ የሀድያ ዞን የመንግሥት አመራሮች ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን ትተው ‹‹የእኔ›› ለሚሉት የሃይማኖት ተቋም በመሥራታቸው የተነሳ ኦርቶዶክሳውያን ለረጅም ዘመናት የአደባባይ በዓላትን የሚያከብሩባቸውን ይዞታዎች እንደተነጠቁ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በቅርቡ በመግለጫቸው ማስረዳታቸው ይታወቃል፡፡
በሆሣዕና ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ‹‹ጎፈር ሜዳ›› የተባለውን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታ የመንግሥት አካላት መንጠቃቸውን ተከትሎ የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን በዓላቱን ማክበሪያ ቦታ ከማጣታቸው ባለፈ ለከፍተኛ ሥነ ልቡናዊ ጫና እየተዳረጉ እንደሆነ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ አንዳንድ የዞኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ለቤተ ክርስቲያኗ ካላቸው ጥልቅ ጥላቻ የተነሳ ቤተ ክርስቲያኗ ያነሳችውን የይዞታ ይገባኛል ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ‹‹ወራሪ›› እያሉ መሳደብ የሚቀናቸው እንደሆኑ ብፁዕነታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡ የተጠየቀውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ተገቢ ሆኖ ሳለ የሕዝበ ክርስቲያኑንና የቤተ ክርስቲያንን መብት በኃይል በመጨቆን በሕዝቦችና በመንግሥት መካከል መጠራጠር፣ ግጭትና ሁከትን ለመፍጠር የሚተጉ የዞኑ አመራሮች እየተከራከቱ መምጣታቸውንም ከብፁዕነታቸው ንግግር መረዳት ይቻላል፡፡ እስከአሁን ድረስ በሀድያ ዞን ሆሣዕና ከተማ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታ ችግር እንዳልተፈታ ይታወቃልና የቤተ ክርስቲያኗንና የአካባቢውን ምእመናን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ካልተቻለ ለሀገር አንድነትም ሆነ ሰላም እንቅፋት መሆኑን መርዳት ያስፈልጋል፡፡
በሀድያ ዞን በሆሣዕና ከተማ አስተዳድር ያለው ችግር መፍትሔ ሳያገኝ በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ የላሃ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለ፶፫ ዓመታት ያህል ለአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ሲጠቀሙበት የነበረውን ቦታ የወረዳው የመንግሥት ኃላፊዎች መንጠቃቸውን የመሎ ኮዛ ወረዳ ቤተ ክህነት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚሁ ሀገረ ስብከት የሚገኘውን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታን የወረዳው የመንግሥት ኃላፊዎች ያለአግባብ መንጠቃቸውን አስመልክቶ የአካባቢው ምእመናን ድርጊቱን በማውገዝ ከወረዳ እስከ ፌዴራል መንግሥት አቤቱታ ያቀረቡ ፳፪ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ያለ አግባብ በእስርና በገንዘብ ተቀጥተዋል፡፡ በሐሰት ክስ ከ፯-፱ ዓመታት ከመታሰራቸው ባለፈ በእያንዳንዳቸው ላይ የተወሰነ መቀጮ በአጠቃላይ ሲደመር ፻፹፱ ሺህ ፭፻ ብር ሲሆን የእስር ትእዛዙም ሆነ የብር መቀጮው ተፈጻሚ ሆኖ የሐሰት ክስ የቀረበባቸው ምእመናን በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ እንደሚገኙ የመሎ ኮዛ የወረዳ ቤተ ክህነት ለዝግጅት ክፍላችን የላከው መረጃ ያሳያል፡፡
በጋሞ ጎፋ ዞን በመሎ ኮዛ ወረዳ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታ ላይ በመንግሥት ኃላፊዎች አማካይነት እየተፈጸመ ያለውን ግፍና በደል የወረዳው ቤተ ክህነት በቀን ፲፪/፲፩፳፻፲፩ ዓመተ ምሕረት በጻፈው ደብዳቤ በዝርዝር ለሀገረ ስብከቱ ማሳወቁን ተከትሎ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም በቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መመሪያ እንዲሰጡ ቢጠየቁም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ውሳኔ ሳይሰጡ በመቅረታቸው ድርጊቱን የተቃወሙ ከ፳፪ በላይ ንጹሓን ምእመናን ለከፍተኛ እስር፣የገንዘብ መቀጮና እንግልት ተዳርገዋል፡፡
ጉዳዩ ሳይጠነክርና ሳይከፋ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በቀን ፪/፱/፳፻፲ ዓመተ ምሕረት በጻፈው ደብዳቤ የምእመናኑ ጥያቄ እንዲመለስና የሃይማኖት ነጻነት እንዲረጋገጥ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ይህ ሁሉ ሕጋዊ መንገድ ታልፎም ታድያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ የመንግሥት ሠራተኞች “ሃይማኖታችሁን ደግፋችኋል” በሚል ሰበብ ደምወዛቸውን መቁረጥ፣ የትምህርት እድል ውድድር መከልከል እንዲሁም ሃይማኖታቸውን ለማስለወጥ እንቅስቃሴ እያደረጉባቸው ነው ሲሉ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በቀን ፲፯/፭/፳፻፲፩ ዓመተ ምሕረት ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርእሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን በአግባቡ ተረድቶ የምእመናንን ጥያቄ በመመለስ ምእመናኑ በቀድሞ ቦታቸው የመስቀልና የጥምቀት በዓላትን በነጻነት እንዲያከብሩ እንዲደረግ በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
ምእመናኑ ተከሰው በፍርድ ቤት ቅጣት የተበየነባቸው ‹‹የበዓላት ማክበሪያ ቦታችን ለምን ይነጠቃል?›› ብለው በመጠየቃቸው ብቻ እንደሆነ የወረዳ ቤተ ክህነቱ አስታውቋል፡፡ በአንጻሩ በወረዳው የመንግሥት ኃላፊዎች በኩል በቀን ፲፰/፭/፳፻፲ ዓመተ ምሕረት በተጻፈ ደብዳቤ “ምእመናኑ የተከሰሱበት ለመናኸሪያ ተብሎ በተወሰነው ቦታ ላይ ሕገ ወጥ ግንባታ በመገንባታቸው ነው” ብለዋል፡፡ ምእመናኑ በተጠቀሰው ቦታ ሕገ ወጥ ግንባታ እንዳያከናውኑ ቢነገራቸውም እምቢተኛ በመሆን በኃይል ግንባታውን በማካሄዳቸው በክሱ መሠረት የእስራትና የገንዘብ መቀጮ እንደተጣለባቸው የክሱ ዝርዝርም ያስረዳል፡፡
ይሁን እንጂ በ፲፪/፲፩/፳፻፲፩ ዓመተ ምሕረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከጋሞ ሀገረ ስብከት የደረሳቸውን ቅሬታ ተቀብለው ለሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የአቤቱታ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ በደብዳቤውም በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ አስተዳደር የሚገኘው የላሃ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ከ፶ ዓመታት በላይ ሲገለገሉበት የነበረውን የጥምቀትና የመስቀል ማክበሪያ ቦታ የመሎ ኮዛ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ለሌላ አገልግሎት በማዋሉ ማኅበረ ምእመናኑና ካህናቱ የይገባናል ጥያቄ በማንሳታቸው ለከፍተኛ እስራትና እንግልት እየተዳረጉ እንደሆነ በደብዳቤው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ታይቶ አመራር እንዲሰጥበት ቅዱስነታቸው ጠይቀው ነበር፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን የመሎ ኮዛ ወረዳን ፓሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ይስሐቅ ጩርጋ እና የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ኤርምያስ ወሰንን የጠየቅን ቢሆንም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ ነገር ግን የወረዳውን የብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰሎሞን ስባቱን አናግረን “ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ወረዳው ከሕግ ውጭ የሆነ ሥራ እየሠራ ከሆነ አጣርተን መፍትሔ እንሰጣለን” የሚል ምላሽ ሰተውናል፡፡
ሁለቱ የአደባባይ በዓላት መከበራቸው ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመገንዘብ መንግሥት የበዓላቱን ማክበሪያ ቦታዎች የይዞታ መብት ቢያረጋግጥ መልካም ነው፡፡ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ላሉ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ለቤተ ክርስቲያኗ ሕጋዊ ሰነድ አዘጋጅቶ ሲሰጥ ሀገሪቱ ከብጥብጥና ሁከት ትድናለች፡፡ በዓሉን በዩኒስኮ ያስመዘገበው ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በመከበሩ ነውና የበዓላቱ ማክበሪያ ቦታዎች ሕጋዊ ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗንና የምእመናንን ድምፅ መስማትም ተገቢ ነው፡፡ በየአካባቢው ያሉ የአደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ጥያቄ ያለመመለስ በሀገሪቱ ሰላምና ፍቅር እንዲሁም መረጋጋትን ስለማያመጣ መንግሥት ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል እንላለን፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1264
በኢትዮጵያ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ኦርቶዶክሳዊያን ክርሰቲያኖች ለአሰቃቂ ግድያና ስደት ተዳርገዋል፡፡ በተለይም የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎና የፓለቲካ ትርክት ታክሎበት ክርስቲያኖች በየጊዜው የችግሮች ሁሉ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ግፍ ግን እስካሁን ከደረሰው ግፍ ሁሉ በዓይነቱም ሆነ በመጠኑ የተለየና እጅግ አሰቃቂ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ/ም በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከተፈጸመው ጥቃት አንስቶ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችና በደቡብ ክልል በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች እጅግ ጭካኔ የተሞላባቸው ናቸው፡፡
ክርስቲያኖች በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ በተለያየ ጊዜያት በአሰቃቂ ሁኔታ በገጀራ ተቀልተው፣ በቆንጨራ ተቆራረጠው፣ በጦር ተወግተው፣ በጩቤ ተዘክዝከው፣ በሜንጫ ተተልትለው፣በዱላ ተቀጥቅጠው እንዲሁም በድንጊያ ተወግረው ሞተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ሕገ አራዊት ባለበት ሀገር ሳሆን ሰዋዊ ሕግ ባለበት ሀገር ነው፡፡ ክርስቲያኖች በየአካባቢው በሕይዎት የመኖር ተፈጠሮዊ መብታቸው ተነፍጎ በሚከተሉት እምነት ብቻ ተለይተው መገደላቸው ለምን ይሆን? ስንል እንጠቃለን፡፡ የተከበራችሁ አንባቢያን “ለምን ይሆን” ስንል ለጠየቅነው ጥያቄ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል የትብብርና የሕዝብ ግንኝነት አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ የሆኑትን አቶ ፋንታሁን ዋቄን ለቃለመጠቅ ጋብዘናል፡፡ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ሁለንተናዊ ጥቃቶች የጀመረው መቼ ነው?
አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንዋን ማጥቃት የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዘመናት ይፋዊ ጥቃት የተከፈተባት ቢሆንም ያንን ሁሉ በደል በጥበብ ተሻግራ እየኖረች ያለች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የመጀመሪያውን የቤተ ክርስቲያን ጥቃት የፈጸመችው ዮዲት ጉዲት ስትሆን ሁለተኛው ደግሞ በኦቶማን ቱርክ ቀለብ ይሰፈርለት የነበረው የአዳሉ ግራኝ አሕመድ ያደረሰው መጠነ ሰፊ ጥቃት ነው፡፡
ይህ ግለሰብ (ግራኝ አሕመድ) በወቅቱ ኢትዮጵያን አፍርሶ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት ወደ ቱርክ ያግዝ የነበረ ፀረ ኢትዮጵያ ነበረ፡፡ ፀረ ቤተ ክርስቲያን በመሆኑም በቤተ ክርስቲያን ላይ በፈጸመው ጥቃት ዘመን የማይሽረው ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ከግራኝ አሕመድ ጥፋት በኋላ ደግሞ ጣሊያኖችና ፓርቹጋሎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ከፋፍለው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ታሪክ የማይዘነጋው ግፍ ተፈጽሟል፡፡ ፋሽስት ጣሊያኖች ሁለት ጊዜ ሀገራችንን ሲወሩ የኢትዮጵያ የአንድነትና የማንነት ምስጢራዊ ቋጠሮ የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ዘመናዊ መሣሪያን ከመጠቀም በተጨማሪ በምእመናን ላይ የመርዝ ጋዝን ተጠቅመዋል፡፡ በነዚህ የግፍ ዘመናት ሁሉ ባንዳ ሙስሊሞችና ሌሎች ከጠላት ጋር አጋርነት ፈጥረው ቤተ ክርስቲያን ሲያጠቁና ሲያስጠቁ ነበር፡፡
ከአርባ ዓመታት ወዲህ ‹‹የብሔር ነፃ አውጭ ነን›› የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ቤተ ክርስቲያንን በጠላትነት በመፈረጅና በርዕዮተ አለማቸው ጭምር በማካተት ማታገያ ሲያደርጓት ቆይተዋል፡፡ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር የተባለው የፓለቲካ ድርጅት “የኦርቶዶክስን አከርካሪ መስበር” የሚል ርዕዮተ አለም ይከተል እንደነበረ ያዘጋጀው ሰነድ ምስክር ይሆናል፡፡ በዚሁ ፓለቲካ ድርጅት በከፍተኛ አመራርነት ይሠሩ የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የተባሉ ግለሰብ ሳይቀር በመጻሕፋቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን “አከርካሪ መስበር” የፓለቲካ ድል እንደሚያስገኝ ገልጠዋል፡፡ “የኦሮሞ ሕዝብ ነፃ አውጪ ነኝ” ብሎ የተነሳው የፓለቲካ ቡድን ደግሞ ‹‹ቤተ ክርስቲያን የወራሪዎች ፊት አውራሪ ነች›› ብሎ ተነሳ፡፡ በዚህ ምክንያት ኦሮምያ ክልል ተብሎ በተከለለው የሀገሪቱ ክፍል በሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ ይፋዊ በደል መፈጸም ጀመረ፡፡ “የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያለችው በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል ነው እንጂ እኛጋ ያለችው ባህላችንና መሬታችንን የወረረችው ነች” የሚል የሀሰት ክስም ያቀርባሉ፡፡ በክልሉ ያደጉ ሕፃናትም ይህንን መሰል የጥፋት መርዝ ሲጋቱ በመኖራቸው ካደጉ በኋላ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እያየን ያለነውን ጥፋት ያለምንም ርህራሄ እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡
አንደንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሯት ሌላ አካላት ናቸው ብለው ስለሚያስቡ “ከጭቆና ለመውጣት ቤተ ክርስቲያንን ማጥፋት ነው” የሚል ትርክት በትውልዱ አእምሮ ውስጥ ስለገባ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ የጥቃት ኢላማ ትሆናለች፡፡
“የኦሮሞን ሕዝብ ከጭቆና ነፃ አወጣለሁ” የሚል “የኦሮሞ ምሁር ነኝ” ባይ ሕዝብን ከጭቆና ለማውጣት ቤተ ክርስቲያን እንደጨቋኝ በመቁጠር ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያልተገባ ግብግብ ውስጥ ይገባል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ኃይላት በሙሉ ሆን ብለው ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ይረባረባሉ፡፡ የቀኝ ገዥዎቻቸውን ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ እውን ለማድረግ በዳይ ያልሆነችን ቤተ ክርስቲያን ያልሆነ ሥም በመስጠት ዛሬም ትናንትም ሁለንተናዊ ጥቃት እያደረሱባት ይገኛሉ፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ጥቃት ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን ከበደኖ እስከ በሻሻ፣ ከሊሙ ገነት እስከ ዶዶላ፣ ከኮፈሌ እስከ ሻሸመኔ እንዲሁም ከካራሚሌ እስከ ጅግጅጋ ድረስ በጥናት የተደገፉ ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ግፍ ሲፈጸም ነበር፡፡ በነዚህ ቦታዎች ሁሉ የተፈጸሙ ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ተግባራት ሁሉ ከላይ በተገለጠው አስተሳሰብ ምክንያት የተፈጸሙ የግፍ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አንዳንድ አካባቢዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ተግባር ርዕዮተ አለማዊ አመራር ያለው ነው፡፡ በክልሉ የደረሰውን ጥፋት ወደ ግጭት ዝቅ አድርጎ የሚመለከት አካልም ጥፋቱን ደብቆ ሆን ብሎ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ያለመ ፀረ ኦርቶዶክስ ነው፡፡ በዚህ ዓመት በተከታታይ የተከሰተው ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ተግባር የታቀደ፣ ፍልስፍና ያለው እንዲሁም ኦርቶዶክስን ሀገር አልባ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በምእመናንና በንብረታቸው ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ቤተ ክርስቲያን መግለጫ እንዳወጣች ይታወሳል፡፡ ይህንን መግለጫ እርስዎ እንዴት ገመገሙት?
አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ያወጣችው መግለጫ በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት መንግሥታዊ መዋቅርን የተላበሰ፣ በርዕዮተ ዓለም የታገዘ እንዲሁም በፍልስፍና የታጀበ ጥቃት መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ያወጀችበት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያወጣችው መግለጫ ማስመሰል የለሌበትና በአደባባይ ወጥታ ለተከታዮቿ መሬት ላይ ያለውን እውነት ያስረዳችበት ነው፡፡ እንደምናስታውሰው ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ መግለጫዎች አብዛኛውን ጊዜ እውነቱን ከመግለጽ ይልቅ መንግሥትን ወደ መማጸን ያደሉ ነበረ፡፡ በዚህ ጊዜ የወጣው መግለጫ ግን ጠንካራና እውነቱን ያወጣ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
ቤተ ክርስቲያንን እያጠቃ ያለው ጥቂት የስርዓቱ ደጋፊዎች ሳይሆኑ ራሱ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንደሆነ በግልጽ ያስቀመጠችበት መግለጫም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የመንግሥት ኃይል እያጠቃት እንደሆነ የሚያመለክተው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተፈጸሙ አንዳንድ ጥቃቶች የመንግስት ኃላፊዎችና የፖሊስ አዛዦች ሳይቀር የጥፋቱ ተባባሪዎች መሆናቸው ነው፡፡ በአንጻሩ እራሳቸውን በሚከላከሉ ክርስቲያኖች አጥቂዎች ጉዳት ሲደርስባቸው አምቡላንስ ሲላክላቸው ተጠቂዎች ደግሞ በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ይደርጋል፡፡ ከሞት የተረፉ ምእመናን ደግሞ የደረሰባቸውን በደልና መከራ እንዳይናገሩ እና ሰብአዊ ድጋፍም እንዳይደረግላቸው የየአካባቢው ባለሥልጣን መከልከላቸውንም መግለጫው በሚገባ አሳይቷል፡፡
አባቶቻችንም ይህንን በይፋ መናገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምእመናን የመግለጫው ሐሳቡ በደንብ እንዲገባቸው የመተንተንና የማብራራት ሥራ ኦርቶዶክሳዊ ሚዲያዎችና የሃይማኖት አባቶች ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምእመናንን በማስተባበር ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ነቅተው እንዲጠበቁ የሚያደረግ ምክረ ሀሳብ አባቶቻችን ማቅረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት የኦርቶዶክስ ጠላት እንዲሆን ማድርግ ሳይሆን ኦርቶዶክስ የመንግሥት እንድትሆን የማድረግ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ምእመናን በትኩረት እንዲሰሩ የማስተባበርና የማንቃት ኃላፊነት ያለው ከአባቶች ትከሻ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም አባቶች ሳይፈሩና ሳያስመስሉ እውነታውን መጋፈጥ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ዘረኝነት ቦታ ሥለሌለው በአባቶች መካከል በዘረኝነት የተለከፉ ካሉ በጥንቃቄ ወደ እውነተኛው መሥመር በመመለስ በጋራ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ አባቶቻችን ዘረኝነትን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠርና የልጆቻቸውን አንድነት መጠበቅ አለባቸው፡፡
- Details
- Written by: ረቂቅ መቻል
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 3129
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከስድሳ ሚሊዮን በላይ አማኝ ያላት፣ በውስጧ ብዙ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ቅርሶችን ይዛ በሀገር በቀል ዕውቀቶቿም ለኢትዮጵያ የሥልጣኔ አሻራዋ መሆኗ እሙን ነው፡፡ ታዲያ ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ቅርስና ልዕልና መነሻ በመሆን ትልቁን አስተዋጽኦ ያበረከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ቤተ ክርስቲያንና ቅርሶቿ ለሀገር ያበረከቱትን አበርክቶት በዘመን ከፍታ ላይ ቆመው እንዳይመለከቱ ልባቸው የጠፋ፣ ዐይናቸው የተንሸዋረረ ግለሰቦችም ሆኑ ጽንፈኛ ቡድኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ መምጣታቸው አሳዛኝ ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም እየመጣ ካለው ትውልድ ውስጥ አንዳንድ ግለሰቦች የሀገራችንንም ሆነ የሃይማኖታችንን ታሪክና ቅርስ እንዲሁም የማንነት ገጽታውን ጥላሸት እየቀቡ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህነ ገን እንዴትና ማን ቅርሶቻችንን ለትውልድ ያሻግር? ሀገሬና ሃይማኖቴ ያፈሩትን የጋራ ታሪክና ቅርስ ማን ይሆን የሚጠብቀው ብዬ እንድታዘብ የተገደድኩባቸው ዐበይት ምክንያቶችም አሉኝ፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እና ኦርቶዶክስ ሃይማኖት በዓለም መድረክ እንደ አንድ ልብ መክረው በሰላም፣ በበጎነት፣ በመከባበር ለሌሎች አርአያ በመሆን የሚታወቁ፣ምእመናን በመፈቃቀር አብረው የሚኖሩ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ባህላቸውን፣ ዕሤታቸውን፣ ቅርሶቻቸውን ለመጠበቅ ችለዋል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም ቤተ ክርስቲያን የሀገር ባለውለታ የሆኑ የታላላቅ ነገሥታት ታሪክን ሰንዳ የያዘች ፣ ቅርሶችን በመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘገብ ያደረገችበት የታሪክ ዐውድም ብዙ በመሆኑ የቀደሙት መንግሥታት በሚሄዱበት ሁሉ ከፍ አድርገዋት ቅርሶቿንና ልዕልናዋን አስጠብቀዋል፡፡
አዲሱ የዘመን ብራናችን እንዲበላሽና ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ቅርሶቻችን ለትውልድ እንዳይቀመጡ በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦችና አክራሪ ቡድኖች በሃይማኖታችን ላይ እያደረጉት ያለውን ዘመቻ እንዴት ተባብረን እናስቁም? የሚለውን እናስብ፡፡
እነዚህን ቅርሶች እንዳይጠፉ በትጋት የሚጠብቁት ታላላቅ አባቶች ከየቦታው በግፍ ተገድለዋል፣ ደማቸውም እንደ አቤል ደም በሁላችን ሕሊና ውስጥ እየጮኸች ዓመቱ እንደዋዛ አልፏል፡፡ በተለይ ስለ አብያተ ክርስቲያናት ሲሉ የንዋያተ ቅድሳት መቃጠል አስጨንቋቸው ሥጋቸውን የሚገድሏቸውን ሳይፈሩና ለሥጋቸው ሳይሳሱ የተቃጠሉ፣ ቤተ ክርስቲያናቸውን ከቃጠሎ ለመከላከል ሲሉ በሚሰጡት ተግሣጽ ዘወትር ግፍና መከራን በሰማዕትነት የተቀበሉትን ልንረሳቸው አንችልም፡፡
በእርግጥ ቤተ ክርስቲያንን የናቋትና ሁሉ ነገ እውነቱ ሲገባቸው ከእግሯ ዝቅ ብለው ማሪን እንደሚሉ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም በቅዱስ መጽሐፍ ትንቢት እንዲህ የሚል ተጽፏል “ለአንቺም የማይገዙ ነገሥታት ይሞታሉ፤ እነዛም አሕዛብ ፈጽመው ይጠፋሉ፤ የመቅደሴንም ስፍራ ያከብሩ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው ባርስነቱም ወደ አንቺ ይመጣሉ የአስጨናቂዎችሽ ልጆች እየተንቀጠቀጡ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእስራኤል ከተማ ቅዱስ ተብለሽ ትጠሪያለሽ፡፡” (ኢሳ. ፷፥፲፪‐፲፬)
የትም ሊገኙ የማይችሉ ቅርሶችን የያዘች ቤተ ክርስቲያን በብርቅዬ ቅርሶቿ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እንድትታወቅ ከማድረግ አኳያ የበኩሏን አስተዋጽኦ ማበርከቷ መዘንጋት አልነበረበትም፡፡
አባቶቻችን ያቆዩልን ቅርስ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ሳስብ ይኸኛው ትውልድ ጥበብ መውረስ ይቅርና እንዳለ ጠብቆ ማቆየት አለመቻሉ ምን ያህል ተጠያቂ እንደሚያደርገው መገንዘብ ከባድ አይሆንም፡፡
የዚህችን የታላቋን ቤተ ክርስቲያን ቅርሶችና ሀብቶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ማንም እንደፈለገው ሲያደርጋቸው ”መጣፉም ዝም ቄሱም ዝም ” እንደሚባለው ዝምታው እስከመቼ ነው? መጽሐፉ እንኳን የሚያነበው አለመኖሩ እንጂ አንዴ የተጻፈው ለዘላለም ይናገራል፡፡ በእውነቱ የቤተ ክርስቲያናችን ዜማ እንዲሁም መሣሪያዎቹ በሌሎች እየተወሰዱ ባንጻሩ ደግሞ የኛዎቹ መዝሙራት ከያሬዳዊ ዜማና መሣሪያዎቹ እየተፋቱ ዘፈን ዘፈን እየሸተቱ መሄዳቸው ዕለት ዕለት የምናይና የምንሰማው ቢሆንም ችግሩን ተረድቶ ሕጋዊ ማስተካከያ (ርምጃ) የሚወስድ አካል ከሌለ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የባለቤትነት መብታችንንም እንዳናጣ ያሰጋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያሏት የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ማንነታቸው እንዳያጡ ፣ ከሥሪታቸው እንዳይለዩ እና ጠፍተው እንዳይቀሩ ብሎም ተጠብቀው እንዲቆዩ የቤተ ክርስቲያን፣ አባቶች እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን በጋራ በመሆን ሊሠሩ ይገባል
በአጠቃላይ ቅርስን መጠበቅ ማንነትን መጠበቅ ነውና እነዚህ የማይነጣጠሉ ሀገርና ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ እንዴት ለመጪው ትውልድ እናቆይ? ቅርስ ማጣት ታሪክ ማጥፋት ነውና የነገሥታቶቻችን ታሪክ፣የቤተ ክርስቲያን ቅርስ ሁሉም የኢትዮጵያ መሠረቶች በመሆናቸዉ ሐሳብና መፍትሔ ቢሆኑ ያልኳቸውን ጥቂት ሐሳቦች አክዬ የዛሬ ትዝብቴን እቋጫለሁ
ቅርሶች የአንድን ማኅበረሰብ ታሪክና ማንነት በማሳየት ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ለቅርሶቹ ግንባታ የዋሉት ቁሳቁሶችና አሠራራቸው ለዘመናዊ ሥነ ሕንፃ መማሪያም ነው፡፡ ቅርሶች ለሚገኙበት አካባቢ ነዋሪዎች ሥራ ከመፍጠር ጀምሮ ለሀገር ውስጥና የውጪ ኢንቨስትመንት መስፋፋትና ለቱሪዝም ዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦም ታላቅ ነው፡፡ ስለዚህ ቅርሶች ለሀገርና ለቤተክርስቲያን ያላቸውን ጠቀሜታ ለምእመናን በየዐውደ ስብከቱ እንዲሁም በሥርዐተ ትምህርት ተካቶ በሕዝቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲጨምር ቢደረግ መልካም ነው፡፡
፩. የቤተ ክርስቲያንም ሆነ የሀገርን ቅርሶች የሚመለከታቸው አካላት በእኩል አይተው ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ ቢያደርጉ፤
፪. የቤተክርስቲያን ቅርሶች የሀገር ቅርሶች እንደመሆናቸው መንግሥት ሁሉንም የኢትዮጵያ ቅርሶች እኩል ቢመለከት፣ ከርዳታ ሰጪዎች ከሚመጣው ገንዘብ ላይ በቤተ ክርስቲያን ለሚገኙ ቅርሶች በጀት ቢበጅትና ቅርሶቹ የሚገኙባቸው ነባራዊ ሁኔታ ተመዝነው በየጊዜው እድሳት ቢደረግላቸው፤
፫.የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች የሀገሪቱ ዜጎች( ምእመን) ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም መገለጫ በመሆናቸው ለጥበቃቸው በጋራ መረባበረብ ቢቻል፤
፬.የቅርሶች ጥበቃ ጉዳይ በመንግሥት ወይም በበጎ አድራጊዎች ችሮታ ብቻ ግቡን ስለማይመታ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ማኅበረሰቡ ቅርሶችን እንዲጠብቅ ማበረታታት፤ ብሎም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ፡፡
፭. ቤተ ክርስቲያን በሁሉም ቅርሶቿ አሠራር እና አጠባበቅ ላይ ብቻ የሚሠራ በሊቃውንት አባቶቻችን የሚመራ በባለሙያዎች የተደራጀ አካል ቢኖራት፤ እያንዳንዱ ባለሙያ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ማእከላዊ በሆነ መንገድ ሥልጠና የሚያገኝበት ሁኔታ ቢቀረጽ እንዲሁም እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ቅርስ ሕጋዊ ጥበቃ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ቢመቻች ቤተ ክርስቲያን ነገ ለልጆቿ የምታስረክበው ያልተበረዘ ቅርስ ይኖራታል፡፡
፮. የቅርሶቹ ባለቤቶች ውስጥ ከሆኑት አንዷ የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶቿ ይሰረቃሉ በሚል ስጋት ላለፉት ዓመታት ዲጂታላይዜሽንን እንደማታበረታታ ይነገራል። "በተለይም የውጪ ሀገር ምሁራን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ሲመጡ፤ ቅርሶቹ ተዘረፉ ስለሚባል በቤተ ክርስቲያን ዘንድ የዲጂታይዜሽን ጥቅም ብዙም አይታይም። ደግሞም ቤተ ክርስቲያኗ በውጪ ተመራማሪዎች በቅርስ ጥናት ስም ከሚደርስባት የቅርስ ዘረፋ ቤተ ክህነት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችም ለዲጂታላይዝ ተግባሩ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ብዙም አያስደንቅም
ምክንያቱም ቅርሶች ይሰረቃሉ የሚለው የቤተ ክርስቲያን ስጋት መሠረት ስላለው ነው። ይሁንና ከዘመኑ ሥልጣኔ አንጻር ዛሬ ላይ ቅርሶችን ዲጂታላይዜሽን ማድረግ ደግሞ አማራጭ የሌለው ዘዴ ነው። ስለሆነም ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ቅርሶችን ሰንዶ መያዝ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡
- Details
- Written by: ረቂቅ መቻል
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1342
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ሰነበታችሁ ስሜ ጸጋ ሥላሴ ይባላል የምኖረው ወሊሶ ከተማ ሲሆን በየጊዜው የሚወጡ ጽሑፎቻችሁን አነባለሁ ፡፡ እናም እኔም በትዳር ሕይወቴ ችግር የሆነብኝን ጉዳይ እንደሚከተለው ጻፍኩላችሁ ፡፡ እኔና ባለቤቴ ትውውቃችን ዩኒቨርስቲ እያለን ነበር አሁን የአንድ ወንድ ልጅና የአንዲት ሴት ልጅ ወላጆች ሆነናል፡፡ ከተጋባን ድፍን ፲፪ ዓመት ሞላን፡፡ ነገር ግን በወቅቱ እኔም የነበረኝ የእምነት ጥንካሬ የላላ በመሆኑ የትዳሬ ዋና ጉዳይ እምነት መሆኑን ብዙም አስተውዬ አላውቅም ነበር፡፡ እናም ትዳራችንን በመግባባትና በመፈቃቀድ ላይ አድርገን መሠረትን፡፡ እየቆየን በዕድሜም ሆነ በአእምሮ እየጎለመስን ስንመጣ ባለቤቴ የቤተሰቤ እምነት የምትለውን እስልምና አጥብቃ በመከታተል በኔና በልጆቼ ላይም ተጽዕኖ ማድረግ ጀመረች፡፡ ልጆቼን ባላት ትርፍ ጊዜ የእስልምና ትምህርት ማስተማር ፣ ወደ ቁርአን ቤት መላክ ወዘተ የመሳሰሉትን ነገሮች ማከናወን ጀመረች ፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ተነጋግረን መግባባትና መፍትሔ ማምጣት አልቻልንም፡፡ ስለዚህ እኔ ብዙ ዓለማዊ የመፍትሔ አማራጮችን ተጠቅሜ ትዳሬንና ልጆቼን ለማቆየት ሞክሬ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር ቁልቁል ሆነብኝ እናም በእናንተ በኩል መንፈሳዊ ምክርና አስተማሪ መፍትሔ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ ከልጆቼም ከባለቤቴም ተለይቼ ባልኖር ግን እመርጣለሁ ፡፡ ምክንያቱም ብቸኝነት ያስፈራኛል ፡፡
የተከበርክ ውድ ወንድማችን በቅድሚያ በገጠመህ ችግር ብቻህን ከመጨነቅ ይልቅ መፍትሔ አገኛለሁ ብለህ ያስጨነቀህን ጉዳይ ስላካፈልከን እናመሰግንሃለን። እኛም በዝርዝር ያነሳኸውን ታሪክ መነሻ በማድረግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ ለገጠመህ ችግር መፍትሔ ይሆናሉ ብለን ያሰብናቸውን ምላሾች ከዚህ በታች ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
ውድ ጠያቂያችን አብዛኛውን ጊዜ ትዳር አደጋ ውስጥ የሚገባው ወይም ባልና ሚስት የሚፋቱትና ልጆች የሚበተኑት ቅድመ ጋብቻ ላይ በሚፈጸም የጥንቃቄ ጉድለትና ትክክል ያልሆነ የትዳር አመሠራረት ሂደት ነው፡፡ የቅድመ ጋብቻ የትውውቅ ወቅት ወይም የትውውቅ ጊዜ የጥንዶቹ የትዳር ሕይወት መሠረት የሚጣልበት ወርቃማ ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት በስሜታዊነት፣ በችኮላ ወይም በግዴለሽነት በሚደረግ ውሳኔ የሚፈጠሩ ስሕተቶች በስተኋላ ያልተጠበቀ ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀርም።
ትዳር ተቃራኒ ጾታ ባላቸው ጥንዶች የሚመሠረት፣ ለትልቋ ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ስኬታማነት መሠረት የሆነ ቤተሰብን ያቀፈ የተቀደሰ አንድነት ነው። በምድራዊ መንግሥት አንጻር ካየንም ትዳር ትንሹ መንግሥት በመሆን ለትልቁ መንግሥት ግንባታ በመሠረትነት ያገለግላል። ትንሿ ቤተ ክርስቲያንና ትንሹ መንግሥት የሚጀምረው በተቀደሰ ጋብቻ ከሚመሠረት ትዳርና ቤተሰብ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ትዳር ለአመሠራረቱ፣ ለውጤታማነቱና ለዘላቂነቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚገባ ልዩ ተቋም ነው።
ውድ ጠያቂያችን ስለትዳርህ እንደገለጽከው ከሆነ ቀድሞ መሠራት የሚገባውን ቅድመ ዝግጅት ባግባቡ መሥራት ባለመቻልህ የትዳራችሁ መሠረት በመናጋት ላይ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ብዙ ጊዜ የውበትን ትክክለኛ ትርጉም ስለምናዛባው በራሳችን የእይታ ስሕተት በወጥመድ ተይዘን እንሠቃያለን። የአንድ ሰው ትክክለኛ ውበት አፍኣዊና ውሳጣዊ በሚሉ ሁለት ክፍሎች ተከፍሎ ይገለጻል። በሌላም መልኩ የሰው ማንነት ሲጠና በተመሳሳይ ሁኔታ ውጪያዊና ውስጣዊ ማንነት ተብሎ በሁለት ይከፈላል። አፍኣዊ (ውጪያዊ) ውበት (ማንነት) መገለጫው ውጪያዊ ገጽታ ነው። ይህም ተክለ ሰውነትን፣ አኗኗርን፣ አለባበስን፣ አነጋገርን፣ ጠባይን፣ ሥራውንና የመሳሰሉትን ያካትታል። ውሳጣዊ ውበት (ማንነት) ደግሞ ባሕርይውን፣ ፍልስፍናውን ማለትም የሕይወት እይታውን፣ ዕውቀቱን፣ አስተሳሰቡን፣ እምነቱን፣ ምኞቱን፣ ስሜቱንና ማኅበራዊ ዕሴቱን ያጠቃልላል።
በአግባቡ ካልተያዘ መረጋጋትንና ማስተዋልን በሚጋርደው የወጣትነት ዕድሜ ጎልቶ የሚታየው ውጪያዊ ውበትና ማንነት ይሆንና ተፈጥሮአዊ በሆነው አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ለውጥ እየታገዘ በስሜት ማዕበል ይናወጻል። አፍኣዊው ገጽታ ውሳጣዊውን ውበት እንዳናይ አሳውሮ በጭፍን የመንዳት አቅም እንዲያገኝ ዕድል ከሰጠነው ወደማንወጣበት ዐዘቅት ይከተናል። ብዙዎች እኅቶቻችንና ወንድሞቻችንን አታሎ ገደል የሚከታቸው ደግሞ ውስጣዊው ማንነት በውጪያዊው ማንነት በሚደበቅበት ጊዜ ነው። ውስጣዊው ማንነት በውጪያዊው ማንነት ካባ በሚሸፈንበት ጊዜ እጅግ አደገኛ ይኾናል። ምክንያቱም በዚህ ጊዜ የአንድን ሰው ትክክለኛ ማንነት መረዳት አስቸጋሪ ስለሚኾን ነው። አንድ ሰው ውሳጣዊ ማንነቱ በተለይም መንፈሳዊ ሕይወቱ የላላ ከኾነ በሌሎች ውጪያዊ ውበት በቀላሉ የሚማረክ መኾኑ አይቀሬ ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ችግር ብዙ ወጣቶችን አታሎ ወደማይጠቅም ሕይወት ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡ ወንድማችን አንተም የችግርህ ምንጭ ከእነዚህ ነጥቦች ውጪ ሊሆን እንደማይችል ከጻፍከልን ጥያቄ መረዳት እንችላለን።
ውድ ጠያቂያችን ምንም እንኳን መፍትሔ የሚሰጠው እግዚአብሔር ቢሆንም በማኅበረሰቡ ውስጥ ስንኖር ለችግሮቻችን መፍትሔ ሰጪ የሚሆኑ ሰዎችና ተቋማት በመኖራቸው እንደ እግዚአብሔር በሰው ላይ አድሮ ችግርን ይፈታልና እኛም ካህናትንና ሊቃውንት አባቶችን በማማከር ያገኘነውን ምክረ ሀሳብና ሃይማኖታዊ መፍትሔዎች ብሎም በኦርቶዶክሳዊ ሕይወትህ ልትጠቀምባቸው ይገባሉ ያልናቸውን መፍትሔዎች እንደሚከተለው አስቀምጠናል፡፡
፩. አሁን ያላችሁበትን የትዳር ሁኔታ በጥልቀት መመርመር
ውድ ጠያቂያችን እንደገለጽከው ደግሞ በ፲፪ ዓመት የትዳር ቆይታችሁ ፪ ልጆችን እስከ ማፍራት ደርሳችኋል። ባለቤትህ በስተኋላ ባንተና በልጆቻችሁ ላይ እያደረሰች ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ገልጸህ "እንዴት ነው መቋቋምና ማስተካከል የምችለው?" ብለህ ጠይቀኸናል። ይህ የአንተ ዓይነት ችግር በመጽሐፍ ቅዱስም ተመዝገቦ የሚገኝ የነበረ፣ ያለና የሚኖር የብዙዎች ምእመናን ፈተና ነው። ለምሳሌ በመጽሐፈ ዕዝራ እንዲህ የሚል ሃሳብ እናገኛለን"ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ፥ ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። አሁንም የአባቶቻችንን አምላክ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ፤ አላቸው።" (ዕዝ. ፲፥፲-፲፪) የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጥሰው ከእንግዶች ሴቶች ጋር የተጋቡ በርካታ ወንዶች መገኘታቸውን ካህኑ ዕዝራ በስም በስማቸው ዘርዝሮ፦ "እነዚህ ሁሉ እንግዶቹን ሚስቶች አግብተው ነበር፤ ከእነዚህም ሚስቶች ዐያሌዎቹ ልጆችን ወልደው ነበር።" (ዕዝ. ፲፥፵፬) ይላል።
ቅዱስ መጽሐፋችን ባልና ሚስት አንድ አካል መሆናቸውን ያስተምረናል። አንድ አካል መሆን እውን የሚሆነው ደግሞ ጥንዶቹ በሁሉም ነገር ፍጹም የሆነ ተዋሕዶ ሲኖራቸው ነው። "ከወንድሞቻችን መካከል የማታምን፥ ባልዋንም የምታፈቅር ከእርሱም ጋር ለመኖር የምትወድ ሚስት ያለችው ሰው ቢኖር ሚስቱን አይፍታ። ሴቲቱም የማያምንና ሚስቱን የሚያፈቅር ከእርስዋም ጋር ሊኖር የሚወድ ባል ቢኖራት ባልዋን አትፍታ። የማያምን ባል በሚስቱ ይቀደሳልና፤ የማታምን ሚስትም በባልዋ ትቀደሳለችና፤ ያለዚያማ ልጆቻችው ርኵሳን ይሆናሉ፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው።. . . ሚስትም ባልዋን ታድነው እንደ ሆነ አታውቅምና፤ ባልም ሚስቱን ያድናት እንደ ሆነ አያውቅምና።" (፩ ቆሮ. ፯፥፲፪-፲፯) በቅድሚያ የምናነሣው ነጥብ የማታምን ሚስትን ፥ ወይም የማያምን ባልን መፍታት አይገባም የሚለው ነው። መረሳት የሌለበት ጉዳይ ሐዋርያው ኢአማኒ የትዳር አጋርን አትፍቱ ሲል ያስቀመጣቸውን መሠረታዊ መሥፈርቶች የሚያሟላ/የምታሟላ ከሆነ/ች ነው፡፡ እነዚህም የማታምን ሚስት ባልዋን የምታፈቅርና ከእርሱ ጋር ለመኖር የምትወድ ከኾነች የሚለው ነው። የማያምን ባልም በተመሳሳይ ሚስቱን የሚያፈቅርና ከእርስዋ ጋር ሊኖር የሚወድ ከሆነ ከሆነች አይፍታት፤ አትፍታው ብሏል። እዚህ ላይ በጥንቃቄ መታየት ያለበት አንዱ ጉዳይ ሐዋርያው በመልእክቱ የሚያምን ክርስቲያን እምነቱ የማትመስለውን እንዲያገባ ፈቃድ እየሰጠ ነው ማለት አይደለም። የማያምን ባል ስላላት ሚስት ወይም የማታምን ሚስት ስላለችው ባል ነው እየተናገረ ያለው እንጂ ወደፊት በዚህ መስመር ስለሚጋቡት አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተመሥርቶ ችግር ውስጥ ስላሉት ነው እያስተማረ ያለው።
ውድ ወንድማችን አንዱ መመርመር ያለብህ ነጥብ ይህ ነው። ሚስትህ እነዚህን ነጥቦች የምታሟላ ካልሆነ አብራ ልትኖር የምትችልባቸውን ዕድሎች ልታጣ ትችላለች። የዚህም ምክንያቱ ራሷ ነች። ዳሩ ግን መሥፈርቶቹን የምታሟላ ከሆነች አንተም በተመሳሳይ የምታፈቅራትና አብረሃት ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ልትፈታ አይገባትም። እንዳየነውም ሐዋርያው አብሮ የመኖርንና ያለመኖርን መብትና ነፃነት በባልና በሚስት ፍላጎትና ውሳኔ ላይ ነው ያኖረው። ሐዋርያው ለምንድነው አማኙ ባል ከማታምነው ሚስቱ ጋር እንዲኖር የፈቀደው? ለሚለው ጥያቄም፦ "የማታምን ሚስት በባሏ ትቀደሳለች፤. . .ባልም ሚስቱን ያድናት እንደኾነ አያውቅምና።" በማለት ተገቢውን ምላሽ ሰጥቷል።
ክርስቲያን በእምነት የማትመስለውን ሚስቱን ይቀድሳል የሚለው ኀይለ ቃል የሚያሳየው አማኙ ባል የማታምን ሚስቱን የሚቀድስበት ኀይል እንዳለው ነው። ምንድን ነው ያ ኀይል? የክርስትና ሃይማኖት ፍጹም እምነት በመሆኑ የዚህ እምነት ባለቤት (ክርስቲያን) እንደተገለጸው በኢአማኒው እምነት እስካልተጠለፈ ድረስ በማንኛውም ዓይነት እምነት መሰል አስተሳሰብ አይረክስም። በተቃራኒው ይህ እውነተኛውን የባሕርይ አምላክ (እግዚአብሔርን) የሚያመልክና ሀብተ ወልድና ተቀብሎ በስሙ የተጠራ ክርስቲያን ማንኛውንም ዓይነት ከክርስትና የተለየ አማኝን ይቀድሳል።
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1168
ከኃያላን መሪዎችም ሆነ ከሌሎች ሀገራት የሚጎሰመውን የጥፋት ጥሪ በአንድነት በመከባበርና በመመካከር መመከት እንደሚያስፈልግ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳሰበ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫውን የሰጠው ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ጄ ትራንፕ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ሀገራትን ወደ ግጭትና አለመግባባት ውስጥ የሚያስገባ የጥፋት መልእክት ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የዶናልድ ትራፕን ግጭት ቀስቃሽ መልእክት በሐዘን እንደተመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቆ ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ታፍራና ተከብራ የኖረችና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ምሳሌ የሆነች ሀገሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቡ ደግሞ ሕዝበ እግዚአብሔር በመሆኑ ነው ሲል በመግለጫው አስታውሷል፡፡
ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም ሆነ ከሌሎች ተመሳሳይ አካላት በሀራችን ላይ እየተላለፈ ያለው የጥፋት ጥሪ መተዛዘቢያ ከመሆኑ በቀር ሀገራችን ጠባቂዋ በሆነው እግዚአብሔርና በሕዝቦቿ አንድነት ተከብራና ተጠብቃ ትኖራለች ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ አስገንዝቧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በሀገራችን ላይ ያስተላለፉትን የጦርነት ጥሪ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጦ መላው የዓለም መንግሥታትና ሕብረተሰብ ችግሩን በጥልቀት እንዲገንዘቡ አሳስቧል፡፡
ሀገርን የመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው የፌዴራልና የክልል መሪዎች እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግልና የቡድን አመለካከቶችን ወደጎን ትተው አንድነታቸውን አጠናክረው ለሀገራቸው ህልውና ዘብ እንዲቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
