- Details
- Written by: ከዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 3552
የተወደደዳችሁ የስምዐ ጽድቅ አዘጋጆች እንደምን አላችሁ? ከሰላምታዬ በመቀጠል የማካፍላችሁ ችግሬ እንዲህ ነው፦ ስሜ ክንፈ ሚካኤል ይባላል፤ ዕድሜዬ ሠላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ‹‹ከልክ ያለፈ ፍርሃት ሕይወቴን አስቸጋሪ እያደረገብኝ ነው››፡፡ ምንም እንኳን ንስሓ አስፈላጊ እንደሆነ ባውቅም ወደ አባቶች ቀርቤ ኃጢአቴን መናዘዝ እየፈለኩ ግን በፍራቻዬ የተነሣ አልቻልኩም፡፡ ከሰዎች ጋር አብሬ ጊዜ ለማሳለፍም እፈራለሁ፤ ከዚህ በተጨማሪም ጋብቻን ለመመሥረት ሀሳቡና ፍላጎቱ ቢኖረኝም ግን ሴቶችን መቅረብ እፈራለሁ፡፡ በመሆኑም ፍርሃት በሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወቴ ላይ ተጽእኖ አሳድሮብኛል፡፡ ከዚህ ችግር ነጻ ለመውጣት ብጸልይም መፍትሔ አላገኘሁም፤ አሁን አሁን ጭንቀት እየተሰማኝ ነው፤ ታዲያ ከዚህ ችግር እንዴት መውጣት እችላለሁ፡፡
ውድ ወንድማችን ክንፈ ሚካኤል በቅድሚያ ታሪክህን ስላካፈልከን እናመሰግናለን፤ ይህ ዓይነቱ ታሪክ የሌሎች እኅቶች እንዲሁም ወንድሞች ሊሆን ስለሚችል እና አስተማሪ በመሆኑ ለዚህ ዝግጅት እንዲስማማ አድርገን አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ፡፡
ፍርሃት ስሜት እንደመሆኑ መጠን ሰው ሆኖ የፍርሃት ስሜት የማይሰማው የለም፡፡ ነገር ግን ከልክ ያለፈ ፍርሃት የሰውን ሕይወት አስቸጋሪና ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ከልክ ያለፈ የፍርሃት ስሜት የሚሰማን ከሆነ በሕይወታችን ላይ ከሚያስከተለው ተጽዕኖ ነጻ ለውጣት መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡
- Details
- Written by: ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1341
የተወዳዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከርማችኋል? በእግዚአብሔር ቸርነት በሰላምና በጤና እንደቆያችሁን ተስፋ እናደርጋለን፤ ትምህርታችሁን በንቃት በመከታትል በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋልና በርቱ!
ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ታሪክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አንድ ደግ ሳምራዊ ለአንድ ሕግ አዋቂ በምሳሌ ያስተማረውን ትምህርት ነው፤ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!
አንድ ቀን አንድ የሕግ ባለሙያ ጌታችን ኢየሱስን ሊፈትነው ቀርቦ «መምህር ሆይ የዘላለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ልሥራ (ላድርግ)? ሲል ጠየቀው፡፡»
ጌታችንም ለሕግ ዐዋቂው «በሕግ በመጽሐፍ የተጻፈውን አንተ እንዴት ታነባለህ?» ብሎ ጠየቀው፤ ሕግ ዐዋቂውም ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም ኃይልህም፣ በፍጹም ሐሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ ውደድ» በማለት መለሰለት፡፡
ጌታችንም ለሕግ ዐዋቂው «እውነት መለስህ፡፡ የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት በሕይወትም ለመኖር ከፈለክ ጌታ አምላክህን በፍጹም ነፍስህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ» አለው፡፡
- Details
- Written by: ማኅበረ ቅዱሳን
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1160
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እና ሰማያዊ ተልእኮዋን ለመፈጸም በምታደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ከታች ከአጥቢያው ጀምሮ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ በሥርዓት የተዋቀረ አደረጃጀት እና መዋቅር ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለዚህም ሥርዓተ ቅዳሴውን፣ ሥርዓተ ማኅሌቱን፣ የዐውደ ምሕረት ጉባኤውን፣ የሰንበት ት/ቤቱን አገልግሎት፣ የገዳማዊውን ሥርዓት እንዲሁም የጥምቀት እና የመስቀል በዓላት የመሳሰሉት በተደራጀ እና መዋቅሩን በጠበቀ መልኩ የሚከወኑ አገልግሎቶች መሆናቸውን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ይህን በሥርዓት እና በወግ የተሠራ የቤተ ክርስቲያን አደረጃጀት ከዚህ ቀደም ይከወን ከነበረበት በተለየ የጠበቀ መዋቅራዊ አደረጃጀት መቆም ዘመኑ የሚጠይቀው ዐቢይ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ያለና የነበረው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ከትላንት በተለየ መልኩ እየተጠናከረ ይጓዝ ዘንድ ከትላንት የላቀ ኅብረት፤ ከትላንት የላቀ ሥራ ፣ ከትላንት የላቀ አገልግሎት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ይጠበቃል፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 491
ቤተ ክርስቲያን በፀረ ክርስቲያን ኀይሎች ትላንት ተፈትናለች፤ዛሬም እየተፈተነች ትገኛለች፡፡ ታግለው ከማይጥሏት ገጥመው ከማያሸንፏት ጋር ግብግብ የገጠሙት እነዚህ ኀይሎች የመውጊያውን ብረት ቢቃወሙ ለነሱ ይብስባቸው ሆናል እንጅ ቤተ ክርስቲያን የኋላ ኋላ ማሸነፏ እንደማይቀር ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ክርስቲያኖችን በመግደልና በማሳደድ አካላዊ ዕረፍት ይነሷቸው እንደሆን እንጅ ዘለዓለማዊ የሆነውን መንፈሳዊ ዕረፍትን ግን አይነሷቸውም፡፡ ክርስቲያኖችን እንደ ክፉ አውሬ እያደኑ መግደል ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ውሎ ያደረ አረመኔያዊ ተግባር ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየነው ያለው ደግሞ ተደጋጋሚና ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡
በቤተክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲቆም ቤተክርስቲያኗ ለመንግሥት በተደጋገሚ ጥያቄ ብታቀርብም በጉልህ የታየ መፍትሔ ባለመገኘቱ ፀረ ክርስቲያን ኀይሎች የልበ ልብ እየተሰማቸው በተደጋጋሚ እጅግ አስከፊ ጥቃት እየፈጸሙ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ መረጃዎች ማወቅ እንደተቻለው በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ጥቃት በአብዛኛው በሶማሌ፣በኦሮምያ፣ በደቡብ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልሎች ነው፡፡
- Details
- Written by: መጽሐፈ ሲራክ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1186
የተወደዳችሁ አንባብያን በዛሬው የቤተ አብርሃም ዓምድ ዝግጅታችን ይዘንላችሁ የቀረብነው በሰሜን አሜሪካ የሴንት ሊውስ ደብረ ናዝሬት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የኦሃዮ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ የሆኑትን መልአከ ገነት በለጠ ይረፉን ነው፡፡
በመንፈሳዊ አገልግሎት ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከኢትዮጵያ እስከ አፍሪካ ፤ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ በብዙ አድባራት በተለያየ ኃላፊነት ተመድበው ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል፡፡
እኛም በ፳፻፲፫ ዓ.ም ፴፱ኛው ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ሀገረ ስብከታቸውን ወክለው ኢትዮጵያ በመጡበት ጊዜ አግኝተናቸው ከልጅነት እስከ እውቀት ያላቸውን የሕይወት ተሞክሮ ( የሥራ ልምድ እንዲያካፍሉን የአብርሃም ቤት እንግዳ አድርገናቸዋል እነሆ፡-
ስምዐ ጽድቅ ፦ በቅድሚያ ጥሪያችንን አክብረውና ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ ሆነው ስለተገኙልን በልዑል እግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን ፡፡
መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ፦ እኔም አክብራችሁ ሐሳቤን እንድሰጥ የሕይወት ተሞክሮዬንም ለሌሎች እንዳካፍል ለቃለ ምልልስ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ የምሰጠውም ሐሳብ የሚጠቅም እንዲሆንልኝ እመኛለሁ፡፡
Read more: "በውጪው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች ሳይሆን ተስፋፋች እላለሁ" --- መልአከ ገነት በለጠ ይረፉ ክፍል አንድ
- Details
- Written by: እህተ ሚካኤል
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1048
በሀገሪቱ ከመጣው ለውጥ ጋር ተከትሎ በተለያዩ ክልሎች ላይ ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ በሰው እና በንብረት ላይ ብዙ ጉዳት ደርሷል፤ብዙዎች የተወለዱበትን፣ ያደጉበትን እና የኖሩበትን አካባቢ ለቀው ተሰደዋል፡፡ ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ብዙ የነበራቸው ባንድ ጀንበር ንብረት አልባ ሁዋል፡፡ ለዚህ መሰሉ ጥቃት ከተጋለጡት ውስጥ ደግሞ አንደኛዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መንግሥት በተለዋወጠ እና ሀገሪቱ ላይ አንድ ነገር በተከሠተ ቊጥር ግንባር ቀደም የጥቃት ዒላማ የምትሆነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ ኋላ ሄዶ የመንግሥት ለውጥ ታሪካችንን ማየቱ በቂ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የመንግሥት ለውጥ ጋር ተያይዞ ቤተ ክርስቲያን ብዙ መከራን አሳልፋለች፡፡ በእሳቱ ውስጥ ካለፉ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ደግሞ አንዱ የምሥራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ በወቅቱ የደረሰውን የቤተ ክርስቲያን ጥቃትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሚከተለው አነጋግረናል ይከታተሉን፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፦ አባታችን ይህን ቃለ መጠይቅ እንድናደርግ ስለፈቀዱልን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡ በቅድሚያ ሙሉ ስምዎትን ከየት እንደመጡና የአገልግሎት ድርሻዎትን ይግለፁልን
መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ደሳለኝ፦ እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝና እንድናገር ስለፈቀዳችሁልኝ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፡፡ መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ደሳለኝ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሲሆን የአገልግሎት ድርሻዬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ነኝ፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1113
ጥንታዊውንና ታሪካዊውን የሀግያ ሶፊያ ኦርቶዶክሳዊ ቤተ መቅደስን የቱርክ መንግሥት ወደ መስጅድነት የቀየረበትን ሂደት ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ ዩኒስኮ ማስታወቁን የኦርቶዶክስ ታይመስ ድኅረ ገጽ አስነብቧል፡፡
የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ ወደ መስጅድነት መቀየሩን በተመለከተ ከተለያዩ አካላት ይሰጥ የነበረውን አስተያየት ዩኒስኮ ከተመለከተ በኋላ ኃላፊነቱን ወስዶ በጉዳዩ ላይ ከሐምሌ ፳፻፲፪ ዓ.ም ጀምሮ ምርመራ ሲያካሄድ እንደቆየ ዘገባው አስታውሷል፡፡
ዩኒስኮ በቤተ መቅደሱ ላይ ያለው አቋም የማይለዋወጥ መሆኑን ዘገባው ያነሳ ሲሆን ቅርሱ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለመገምገም ቀደም ሲል የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎቹን ወደ ስፍራው እንደላከ ተገልጧል፡፡ ባለሙያዎቹም በቅርሱ ላይ የተደረገውን አካላዊ ለውጥና ወደ መስጅድነት መለወጡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖረው ስለሚችል ተፅዕኖ ገምግመዋል ተብሏል፡፡
የምርመራ ውጤትና ሂደቱን ከሰኔ ወይም ከሐምሌ ወር ፳፻፲፫ ዓ.ም ጀምሮ ለዓለም አቀፍ የቅርሶች ጥበቃ ኮሚቴ እንደሚቀርብ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በቅርሱ ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ ባለመጠናቀቁ ውጤቱን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንዳልተቻለ ዘገባው አመልክቶ ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ክብካቤ ሕግጋትን ጠብቆ ዩኒስኮ እየሠራም እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ሃያ አንድ አባላት ያሉት ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴም እንዲሁ ቅርሱ ወደቀደመ ክብሩ የሚመለስበትን ሁኔታ እያመቻቸ እንደሆነ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡
- Details
- Written by: በጋዜጣው ሪፖርተር
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1115
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ፲፬ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ኅዳር ፭ እና ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በማኅበሩ ጽ/ቤት ሕንፃ አካሔደ፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ጸሎተ ወንጌል እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን የዕለቱ መርሐ ግብር በማኅበሩ ሰብሳቢ በአቶ ታምሩ ለጋ የ“እንኳን ደህና መጣችሁ” መልእክት ተጀምሯል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ የ፳፻፲ ዓ.ም እና የ፳፻፲፩ ዓ.ም የውጪ ኦዲት ዘገባን ጨምሮ የማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣የኤዲቶሪያል አገልግሎት ሪፖርት የማኅበሩ ኦዲት አገልግሎት ሪፖርት፣ የማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ የአጋማሽ ዘመን ግምገማ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚሉ አንኳር ርእሰ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡
በቀጣይ ቀንም ፮ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫና የኦርቶዶክሳውያን ተሳትፎ ፣ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳዮች እይታ፤ በኦርቶዶክሳውያን አንድነትና ኅብረት የማኅበረ ቀዱሳን ድርሻ ፣ የማእከላት እና የዋናው ማእከል ግኑኝነት ከፋይናንስ አኳያ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት መመሪያ ማሻሻያ ምክረ ሓሳብ የሚሉ አጀንዳዎች ቀርበው በሁሉም ርእሰ ጉዳዮች ላይ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ጉባኤውን ሲከታተሉ በነበሩ አባላት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ-ጂንካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ኃላፊ፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፤ ከየማእከላቱ የተወከሉ የማኅበሩ አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው እሑድ ኅዳር ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በነበረው የመጨረሻ መርሐ ግብሩ ማኅበሩን ለቀጣይ ዓመታት የሚመሩትን የሥራ አመራር አባላት በማስመረጥ እንዲሁም አገልግሎት ያጠናቀቁ የሥራ አመራር አባላትን በክብር በመሸኘት ጉባኤውን አጠናቋል፡፡
- Details
- Written by: ካሳሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1056
ጆርጂያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለጥንታዊው የጆርጂያ ጀቫሪ ገዳም ጥገና የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡
በምሥራቃዊ ጆርጂያ የሚገኘው ይህ ጀቫሪ የተሰኘው ኦርቶዶክሳዊ ገዳም በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተገደመ ሲሆን የአሜሪካ ኤምባሲ ለጥገናው ወጭ ያደረገው ገንዘብ ቅርሱ ይዘቱን እንደጠበቀ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ይህ ታሪካዊና ጥንታዊ የጆርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገዳም በዩኒስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ ስለሆነም የአሜሪካ ኤምባሲ ለገዳሙ ጥገና የሚውል ከአምስት መቶ ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በጆርጂያ የአሜሪካ ኤምባሲ አምባሳደር የሆኑት ኬሊ ዲኛን መንግሥታቸው በጆርጂያ ኦርቶዶክስ ገዳም ላይ ለሚደረገው መሠረታዊ ጥገና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ በእጅጉ ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
የጆርጂያ ገዳማት ለጆርጂያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት የላቀ ሚና እንዳላቸው የተጠቆመ ሲሆን የረጅም ጊዜና ዘመን ተሻጋሪ ሆነው መገኘታቸው ለመካከለኛው ዘመን የጆርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ህያው ምስክሮች ሆነዋል ተብሏል፡፡
- Details
- Written by: በካሣሁን ለምለሙ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1187
የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ታወቀ
የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኢሪንጀ ሰሞኑን በተደረገላቸው ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል፡፡
ቅዱስነታቸው በዚህ ሰዓት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ዘገባው አስታውሶ ቤልግሬድ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ሕክምና ማእከል ውስጥ ተገቢው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቅዱስነታቸው ከዚህ ቀደም በሀገራችን ኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ያወገዙ ሲሆን በሀገራቸው አምባሳደር በኩልም ለቤተ ክርስቲያን ያላቸውን አጋርነት ማሳየታቸው ይታወሳል፡፡
- Details
- Written by: ቅዱስ ሲኖዶስ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 786
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማህበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
፩. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የቀረበው የጉባኤ መክፈቻ ንግግር የበጀት ዓመቱ የሥራ መመሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡
፪. ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት የ፴፱ኛው አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ የጋራ መግለጫ ጉባኤው ተቀብሎ ያፀደቀው በመሆኑ ለሚመለከታቸው ሁሉ ተላልፎ በሥራ እንዲተረጐም ተወስኗል፡፡
፫. የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ችግር አስመልክቶ በጉባኤው ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ባለፈው አንድ ዓመት በአገራችን በኢትዮጵያ በቤተ ክርስቲያናችንና በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ግፍና መከራ እንዲቆም በየምክንያቱ በክርስቲያንነታቸው ምክንያት የታሰሩ ካህናትና ምእመናን ጉዳያቸው እየታየ ከታሰሩበት እንዲፈቱ፣ የመንግሥት የበታች ባለሥልጣናትም ለጥፋተኞች ከሚያደርጉት ድጋፍ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ጉባኤው አጥብቆ አሳስቧል፡፡ ከዚሁ ጋር በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ ላለፈው ለደረሰው ጥፋትና ለወደፊትም የሕግ ክትትል በማድረግ ችግሩን የሚከላከሉ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት ድረስ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
፬. ወቅታዊ አገራዊ ሰላምን በተመለከተ ጉባኤው በሰፊው ተነጋግራል፡፡ በአገራችን ያለው ወቅታዊ የሰላም እጦት እየታየ ያለው አለመግባባት ለዜጐች ተረጋግቶ አለመኖርና ለሁከት አልፎ ተርፎ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ በመሆኑ በቀጣይም አላስፈላጊ ሁከት ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ እርቅና ሰላም ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ጉባኤው አምኖበታል፡፡ በመሆኑም የእርቅና የሰላም ሂደቱን የሚያስፈጽሙ ብፁዓን አባቶችን በአስታራቂነት ሰይሟል፡፡
፭. በአገራችን ኢትዮጵያ የሕዝባችን የዘመናት ድህነትና የኑሮ ጉስቁልና አስወግዶ ለአገራችንም ብልጽግና ሆነ ለሕዝባችን ዕድገት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አካባቢያዊ ጦርነት እንዲነሣ ያስተላለፉት መልእክት አገራችን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ወይም በሞግዚትነት ለማስተዳደር የተደረገ ሙከራ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ተቃውሞታል፡፡ የዓለምም መንግሥታትና ሕዝቦች እንዲህ ዓይነቱን ትንኮሳ እና የቅኝ ግዛት ፍላጐት እንዲቃወሙ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፮. በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ ፶ የሚገኘው በአሁኑ ጊዜ ባለው የሀገረ ስብከቱ አሠራር ላይ አመቺ ሆኖ ስለአልተገኘ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲወጣ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደማንኛውም ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ ሊቀጳጳስ ተመድቦለት እንዲመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ ከዚህም ጋር አሁን እየተሠራበት ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከወቅቱ ጋር ተገናዝቦ መሻሻል እንዳለበት ስለታመነ ይኸው እየተሠራበት ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መርምረውና አጥንተው መሻሻል የሚገባቸውን ነጥቦች አሻሽለው ወደፊት በቋሚ ሲኖዶስ ከሚመረጡ ሕግ ባለሙያዎች ጋር ሕጉን አሻሽለው ለግንቦቱ ርክበ ካህናት እንዲያቀርቡ ሦስት ብፁዓን አባቶችን ጉባኤው መድቧል፡፡
፯. የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አፈጻጸም አስመልክቶ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየተወሰኑ የተፈጸሙና ያልተፈጸሙትን በመለየት ሊፈጸሙ ያልቻሉበት ምክንያት ተገልጾ ለፊታችን ግንቦት ርክበ ካህናት ውጤቱ እንዲቀርብ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
፷. የብፁዓን አባቶች የሥራ ምደባና ዝውውር በማስፈለጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን ሁኔታ ከመረመረ በኋላ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ዝውውርና አዲስ የሥራ ምደባም ተካሂዷል፡፡
፱. በምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት በቆጋ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ተከስቶ የነበረውን የዶግማና የቀኖና ጥሰት አስመልክቶ ችግሩ በአጣሪ ልዑካን እንዲጣራ ተደርጐ በቀረበ ሪፖርት ላይ ጉባኤው ተነጋግሮ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በመንፈስ ቅዱስ ጵጵስና ተሹመናል ያሉት መነኮሳት የፈጸሙት ድርጊት አግባብነት የሌለው ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ሆኖ ስለተገኘ መነኮሳቱ በራሳቸው የለበሱት ልብሰ ጵጳስናና የጵጵስና ቆብ አውልቀው ንስሐ ተሰጥቷቸው በምንኩስናቸው ብቻ ተወስነው በገዳሙ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲኖሩ ተወስኗል፡፡ ከዚሁ ጋር ተፈጸመ የተባለው ዳግም ጥምቀትና ክህነት ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጭ የሆነና ቤተ ክርስቲያናችን የማትቀበለው በመሆኑ ይህን ድርጊት የፈጸሙ ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
፲. የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ነን ከሚሉ አባላት ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ደረጃ ላይ በመደረሱ ክህነታቸው የተያዘ ካህናት ክህነታቸው ተለቆ በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ውስጥ የሥራ መደብ ተሰጥቷቸው እንዲያገለግሉ ተወስኗል፡፡
፲፩. የቤተ ክርስቲያኒቱ የ፳፻፲፫ ዓ.ም. አጠቃላይ በጀት ላይ የተነጋገረው ምልዓተ ጉባኤ ከበጀትና ሂሣብ መምሪያ በቀረበው የበጀት ድልድል ላይ ተነጋግሮ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሥራ ላይ እንዲውል አጽድቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከላይ በተጠቀሱ ነጥቦች እና እንዲሁም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በስፋት ተነጋግሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው ጐርፍ መጥለቅለቅና የአንበጣ መንጋ በበርካታ ወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ችግር ከፍተኛ መሆኑን ጉባኤው ተገንዝቧል፡፡ በመሆኑም ሕብረተሰቡ ለተቸገሩ ወገኖቻችን የተለመደ ድጋፉን ከማድረግ ወደኋላ እንዳይል ምልዓተ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በአገራችን በኢትዮጵያ በዓለማችንም ጭምር እየታየ ያለው አለመግባባት፣ የጐርፍ መጥለቅለጥ፣ የበሽታ ወረርሽኝ የመሳሰሉት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክ በምሕረቱ ተመልክቶ ሰላሙንና አንድነቱን ለዓለማችንና ለሕዝባችን ይሰጥልን ዘንድ ከህዳር ፩-፯ ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ በመላ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
በመጨረሻም፡-
አገራዊ ሰላምና አንድነት አስመልክቶ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት የእርቅ ሂደቱን የሚቀጥልበት ሆኖ ከዚሁ ጋር የፌዴራል መንግሥቱ የየክልል መሪዎች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለአገራችን አንድነትና ሰላም ለልማቱና ለሕዝባዊ አንድነቱ በጋራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን እያቀረበ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከጥቅምት ፲፩ እስከ ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ድረስ ለ ፲፫ ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ በጸሎት አጠናቋል፡፡
ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን
- Details
- Written by: ዝግጅት ክፍሉ
- Category: ስምዓ ጽድቅ
- Hits: 1179
«በሃይማኖት መለያየት ምክንያት የምወዳትን ባለቤቴንና ልጆቼን እንዳላጣቸው እፈራለሁ››
ክፍል ሁለት
፪. በራስህ እምነት ጠንካራ ሆነህ መገኘት
ክርስቲያን የማያምነውን የትዳር አጋሩን የሚቀድሰው እንዴት ነው? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ክርስቲያን አማኙ በሃይማኖቱና በምግባሩ ከሌሎች እምነት አማኞች ተሸሎ ሲገኝ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ አንድ ክርስቲያን ሦስት መሰረታዊ ቁም ነገሮች ሊኖሩት ይገባል እነዚህም፡-
ሀ. ክርስቲያን የእምነት ጥንካሬ ሊኖረው ይገባል። እግዚአብሔር የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን ሁሉ እንደሚችልና እንደሚቀይር አምኖ የሚያሰጨንቀውን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ መሆን አለበት። "በሰው ዘንድ ይህ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል።" (ማቴ. ፲፱፥፳፮) "ቢቻልህ ብለሃል፤ ብታምንስ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል።" (ማር. ፱፥፳፫) "ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ድል ይነሣዋልና፤ ድል መንሣቱም ይህች ናት፤ ዓለምን ድል የሚነሣውም እምነታችሁ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን ድል የሚነሣው ማን ነው?" (፩ ዮሐ. ፭፥፬-፮) ተብሎ እንደተገለጸው።
ለ. ክርስቲያን ስለ እምነቱ ማስተማርና መመስከር ይኖርበታል። አማኙ የማታምን የትዳር አጋሩን ሊቀድሳትና ከዘለዓለም ሞት ሊያድናት ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ ስለ ሃይማኖቱ የሚሰጠው ምስክርነት ነው። "በሰው ፊት የሚያምንብኝን (የሚመሰክርልኝን) ሁሉ እኔም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት አምነዋለሁ። በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት እክደዋለሁ።" (ሉቃ. ፲፪፥፰-፲) እንዲል። ክርስቲያን በሃይማኖቱ ሳያፍርና ሳይፈራ በየትኛውም ጊዜና ቦታ የሚያምነውን የሚመሰክር መሆን ይገባዋል። በተለይም እንዲህ ዓይነቱ በጋብቻ የመተሳሰር ክሥተት ሲፈጠር አጋጣሚውን ተጠቅሞ በፍቅርና በጥበብ የማያምነውን አጋር ለማዳን እምነትን መመስከር ከአማኙ ይጠበቃል።
ሐ. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መላበስ ይገባል፡፡ ማንኛውም ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከሚገልጽባቸው መንገዶች አንዱ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መላበስ ነው። አንዳንድ ሰነፎች ክርስትናን በሕይወት ማሳየት ባለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ከክርስትናው በተቃራኒ ስለሚጓዙ እንኳንስ ኢአማንያንን ሊማርኩ ይቅርና አምላካቸውን የሚያሰድቡ ይሆናሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዚህ ነው "እነሆ፥ በእናንተ ምክንያት አሕዛብ የእግዚብሔርን ስም ይሰድባሉ።" (ሮሜ ፪፥፳፬) በማለት ነው ያስተማረው።
የክርስቲያን ሕይወት የሚነበብ ወንጌል በመሆን ብዙዎችን ስቦና ማርኮ የሚቀድስ መሆን አለበት። ክርስቲያን ባል ለማታምን ሚስቱ ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ ታዛዥነትን፣ ርኅራኄን፣ ትዕግሥትን፣ ርጋታን፣ . . . ያለማስመሰል በቋሚነት ካሳያት በሃይማኖቱ መሳቧ አይቀርም። ክርስቲያን አልጫውን ዓለም እንዲያጣፍጥ የተጠራ የእግዚአብሔር መልእክተኛ መኾኑን ማመንና በተግባርም ተልእኮውን መወጣት ይጠበቅበታል። ክርስቲያን ባል የማታምን ሚስቱን አልጫ ሕይወት በቅዱስ ቃሉና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባሩ ለማጣፈጥ እግዚአብሔር የሰጠውን ዕድል መጠቀም ይገባዋል። "ሥነ ምግባራቸው እንዲህ ያማረ ሃይማኖታቸው ምንኛ ቢያምር ይኾን?" እያሉ በክርስቲያኖች ሕይወት ተማርከው ለቅድስና የበቁ ሰዎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። የእውነተኛ ክርስቲያኖች የጾም፣ የጸሎት፣ የስግደት፣ የምጽዋት፣. . . ክርስቲያናዊ ሕይወት ብዙዎችን ካለማመን ወደ ማመን አምጥቶ በምግባር በሃይማኖት አጽንቶ የመንግሥተ ሰማያት ምርኮኞች አድርጓቸዋል፡፡
ውድ ወንድማችን ባለቤትህን እንደምትወዳት እንገነዘባለን። ክርስቲያን የሆነ ሰው ደግሞ እስከ ሞት ድረስ ደርሶ የሰጠለትን ክርስቶስን እንዲመስል ተጠርቷል። ራስን ከመስጠት የሚበልጥ ስጦታ የለምና እሱ እኛን በመውደዱ ራሱን ነው የሰጠን። እኛም ለምንወደው ሰው የምንሰጠው ስጦታ ለእኛ የምንመኘውንና ውዱን ሀብት ሊኾን ይገባል። ለክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ ከመኾንና ያዘጋጀለትን ሰማያዊ መንግሥቱን ወርሶ ከመኖር የሚበልጥ ምን ሀብትና ስጦታ ይኖረዋል? እወዳታለሁ፤ እወደዋለሁ፤ ለሚለው ሰው ይህን እንዲያገኝ ካልተመኘና እንዲያገኘውም ማንኛውንም መሥዕዋትነት ካልከፈለላት፥ ካልከፈለችለት እንዴት እወደዋለሁ ሊል/ልትል ይችላል/ትችላለች? የትዳር አጋሩ፣ ልጆቹ፣ ቤተሰቡ፣. . . በጨለማ ውስጥ እየኖሩና ወደ ዘለዓለማዊ ቅጣት እየተጓዙ በግዴለሽነት ማየት ፈጽሞ የሚገባ አይደለም ለዚህም የማይከፍለው ምንም ዓይነት ሰማዕትነት አይኖርም።
ከጻፍክልን ጥያቄ እንደተረዳነው ባለቤትህ ይጠቅመኛል ብላ በያዘችው "እምነቷ" በሥራ ቀድማሃለች። ከልጆችህም አልፎ ተርፎ አንተንም ክርስትናህ ልታወጣህ መንገድ ጀምራለች። በዚህም ምክንያት አብረህ ለመኖር በምታደርገው ግብ ግብ ከውዝፍ ሥራህ ጋራ ተደምሮ የቤት ሥራህን አክብዳብሃለች። ይሁን እንጂ የዘረዘርናቸውን መሠረታዊ ነጥቦች ያለ መነጣጠል ይዘህ ከተነሣህ ጊዜ ሊፈጅብህ ቢችልም ባለቤትህንና ልጆችህን ወደ ሕይወት መመለስህ አይቀርም። መጠንቀቅ የሚገባህ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለባለቤትህ ክፉ ወይም ያልተለመደ ደረቅ ቃል እንዳትናገራትና ፊትህንም እንዳታጠቁርባት ነው።
፫. በእምነትህ ተስፋ ሳትቆርጥ ለቀጣይ ሕይወታችሁ መፍትሔ ማበጀት
የእግዚአብሔር ቃል "ዘመኑን እየዋጃችሁ ከሃይማኖት ወደ ተለዩ ሰዎች በማስተዋል ሂዱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንደምትመልሱ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን።" ይላል (ቈላስ. ፬፥፭-፯) እንደሚታወቀው ምንም እንኳን ጨለማ በአዳራሹ ውስጥ በአስፈሪነት ሞገሱ ነግሦ ቢኖርም ብርሃን ሲመጣበት ሥፍራውን ለቆ መሸሹ አይቀርም። ጨለማው ቀድሞ ቦታ ይዞ በመቀመጡ ፈርቶና ተስፋ ቆርጦ ሻማውን መለኮስ የሚያቆም የለም። አንተም ምንም እንኳን በቸልተኝነትህ ብትቀደምና ቢረፍድብህም አልመሸም። በቁጭት ከንፈር በመምጠጥ ያለፈውን በማማረር የሚባክን ጊዜ ሳይኾን ጠንክረህ በቁርጠኝነት ከሠራህ ዛሬም ገና ዕድሉና ተስፋው አለህ። ማንንም ሊቀድስ የሚችል፣ በምንም ነገር የማይረክስ፣ እውነት የኾነ፣ በማንኛውም ነገር የማይሸነፍ፣ ጨለማውን ሁሉ የሚገፍ፣ የሰይጣንን ወጥመድ የሚሰባብርና ከኀያሉ እግዚአብሔር ፊት የሚያቆም ሃይማኖት ባለቤት መሆንህን ማመን አለብህ። ከነቢዩ ከቅዱስ ዳዊትም ጋር አብረህ፦ "እግዚአብሔር ያበራልኛል፤ ያድነኛልም፤ ምን ያስፈራኛል? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ ምን ያስደነግጠኛል?" (መዝ. ፳፮፥፩) በማለት እየዘመርህ በኀይል ሳይኾን በጥበብ ሚስትህንና ልጆችህን ለመታደግና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመምራት የምትጀምርበት ጊዜ ሩቅ አይኾንም።
እንደዚህ ያለ የትድግና መንፈሳዊ ተግባር ሲፈጸም መረሳት የሌለበት አንዱ ቁም ነገር አልጋ በአልጋ የሆነ መንገድ እንደሌለና ያለ ፈተናም አለመፈጸሙ ነው። ሰይጣን ዝም ብሎ ስለማያይህ የጠበቅሃቸውንና ያልጠበቅሃቸውን ልዩ ልዩ ፈተናዎች እያመጣ ተስፋ ቆርጠህ እንድትተወው ያለመሰልቸት ይዋጋሃል። በጸሎት፣ በጾም፣ በስግደትና በምጽዋት እግዚአብሔርን እየለመንክ፣ ወደ ገዳማት መባዕ በመላክ ገዳማውያን አባቶች በጸሎታቸው እንዲያስቡህ ማድረግና አንተም በጽናት መጋደል ይጠበቅብሃል።
፬. ንስሓ አባት በመያዝ በንስሓ መመላለስ
የንስሓ አባት ከሌለህ ከአካባቢህ አጥቢያ የተሻለውን ካህን በማድረግ በካህኑ ምክርና በጸሎቱ ከመጠቀም ጋር የአሸናፊነትን መንፈስና ኀይለ እግዚአብሔርን ለመታጠቅ ትችል ዘንድ ንስሓ ገብተህ ራስህን አንጻ። በቅርብ የምታገኛቸውን የቤተ ክርስቲያን መምህራን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የጠነከሩና ሊያግዙህ የሚችሉ የቤተ ዘመድ አባላትንና ጓደኞችህን በአጋርነት መጠቀም ብልህነት ነው። አቅም በፈቀደ መጠን በፍቅር ሆነህ በጉብኝት ስምም ቢሆን እያግባባህ ወደ ልዩ ልዩ ገዳማትና አድባራት ይዘህ በመሄድ በረከት እንዲቀበሉና የሚያዩትና የሚሰሙትም በልባቸው ጽላት እንዲታተም ዕድል መፍጠር ይገባል።
ከምንም ነገር በፊት ግን አንተ በሃይማኖትህ ጸንተህ መቆም ይጠበቅብሃል። አሁንም ያ ቆሜአለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።" (፩ ቆሮ. ፲፥፲፪) እንደተባለ የሚቀድመው የአንተ በሃይማኖት ጸንቶ መገኘት ነው። ለዚህም በቃለ እግዚአብሔር ራስህን መገንባትና በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋት እንዲሁም ከላይ በተገለጹት መልካም ምግባራት ሁሉ መጠንከር ይኖርብሃል። ከእነዚህ ምግባራት ጋራ እግዚአብሔር በጥረትህ ውስጥ እንዲረዳህ በተቻለ መጠን በዕንባ (በለቅሶ) ድንግል ማርያምን በመማጸን ወደ እግዚአብሔር መጮህን አዘውትር። ለጊዜው ፈተናዎች ተነባብረው ቢያውኩህም በምንም ነገር ተስፋ ሳትቆርጥ ጸንተህ ከታገልክ የኋላ ኋላ ራስህን፣ ባለቤትህን. ልጆችህንና ቤተሰብህን የቅድስና ሕይወት ባለቤት ማድረግህ አይቀርም። እኛም ሐሳብህንና ፍላጎትህን ለማሳካት የምታደርገው ጥረትህ ለፍሬ ክብር እንዲበቃ ቅዱሳን በጸሎታቸው፥ እመቤታችን በአማላጅነቷ፥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በቸርነቱ ከአንተ ጋር ሆነው ይረዱህ ዘንድ ፈቃዳቸው እንዲሆን እንመኛለን።